የነጋ ልጆች እስር – አሁንገና ዓለማየሁ

woyane 2አንዱ ትግሬ፣ አንዱ አማራ፣ አንዱ ጉራጌ ናቸው። ስብሐት ነጋ (ወልደሥላሴ)፣ እስክንድር ነጋ፣ ብርሃኑ ነጋ። የተለያየ እድሜ እና የፖለቲካ ታሪክ ነው ያላቸው። የተለያየ የትምህርትና የትግል ዝግጅትም ነው ያላቸው። ለሁሉም ለእያንዳንዳቸው “ታግሎልኛል” እና “ባለውለታዬ ነው” የሚላቸው የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ክፍል አለ። ሁሉም ከኦርቶዶክስ ክርስትያን ቤተሰብ ነው የመጡት። ሁሉም ላመኑበት ነገር ለመታገል ታላቅ ቆራጥነት ያሳዩ፣ ለረጅም ዘመናትም የዘለቀ ታላቅ መስዋእትነትም የከፈሉ ናቸው።

ምቾቱ እና ስፋቱ ይለያይ እንጂ ሁሉም ግን በአሁኑ ሰዓት በእስር ቤት ውስጥ ይገኛሉ። አንዱ መቀሌ፣ አንዱ ማእከላዊ፣ አንዱ አዲስ አበባ። ስብሐት ነጋን ያሰረው የሰላሣ ዓመት ወንጀሉ ሲሆን፣ እስክንድር ነጋን ደግሞ ያምናውንም የዘንድሮውንም ተረኛ ተገዳድሮ ለፍትሕ መቆሙ ነው እስረኛ ያደረገው። ብርሀኑ ነጋን ደግሞ ”አድጎና ጎልምሶ ቀንድ፣ መንቆርና ጥፍር ያወጣው የጎሳ ፌዴራሊዝም“ ነው ያሰረው። በልጅነቱ እና በወጣትነቱ ኢትዮጵያ ብሎ የታገለላት ሀገር ዛሬ በጎልማሳነቱ የለችም። በዚያችኛዋ ኢትዮጵያ የነበረው የእንቅስቃሴ ነጻነቱም የለም።  ከሸገር ትግራይ ሄዶ የትጥቅ ትግል ለማድረግ ይቅርና ዛሬ ሀገሩ በአፓርታይድ ክልሎች ታጥራ፣ በነዚህም ክልል ውስጥ ተወላጅና ባይተዋር በሕገ መንግሥት ተደንግጎ፣ ተወልዶ ባደገባት ደብረ ዘይት (ቢሾፍቱ) እንኳን በሙሉ ዜግነት መኖር እንዳይችል ሆኗል። ለጊዜውም ቢሆን ነጻ እንቅስቃሴ ማድረግ የሚችለው በአዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ነው። አዲስ አበባም በተሸበረ መንፈስ ውስጥ እንድትኖር የተደረገች ራስን በቢራና በሱስ ካላደነዘዙ በስተቀር ኅሊና ያላቸው የሰላም እንቅልፍ ተኝተው የማያድሩባት የጭንቅ ሀገር ሆናለች። ዘንድሮ ደግሞ ሻሸመኔን አይታ “ነግ በኔ” “ነግ በኔ”በማለት ላይ ያለች ከተማ ናት። ባሁኑ ዙር እንደ ገሞራ ባትቃጠልም እንደ ነነዌ ዳር ዳሯን ተለብልባለች።

እንግዲህ ከዚህ አንጻር እስክንድር ከትልቁ እስር ቤት ወደ ጠባቡ እስር ቤት ነው የገባው ለማለት ያስደፍራል። በተለይ እሱ ደግሞ ሁል ጊዜም የጸጥታ ሠራተኞች እና የጃሮ (የጃዋር ቄሮ) አጀብና ክትትል ሳይለየው ሰብዓዊ፣ ዲሞክራሲያዊና ሕጋዊ መብቶቹ ተገድበው የቆየ ነው። ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ስብሰባ፣ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ፣ ድሆች ለመጎብኘትም በተከታታይ ሲከለከል ቆይቷል።

ከሁሉ የከፋው የስብሐት ነጋ እስር ሳይሆን አይቀርም። ሌሎቹ የነጋ ልጆች ቢያንስ የኅሊና ነጻነት አላቸው። እንታገልልሃለን የሚሉትን ሕዝብ ያለ አጃቢ፣ ያለጥበቃ ሄደው ለማነጋገር ከሕዝቡ የሚመጣባቸው የአደጋ ስጋት የለም (ሕዝቡ ስል የታጠቁና ሌላ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸውን ኃይሎች አይጨምርም)። ስብሐት ነጋ ግን ጦር ካልጠበቀው በየትኛውም የትግራይ ከተማ መንቀሳቀስ አይችልም። ያለ ጠባቂ ቢገኝ በስሙ ነግዶ እና ዘርፎ የዶላር ቢሊየነር የሆነበት ሕዝብ እንደ እባብ ቀጥቅጦ እንደሚገለው የሚያጠራጥር አይደለም። የፈያታይ ዘየማንን ልቡና ይስጠው።

የሲዳሞ ክፍለ ሀገር ኢህአፓ ሊቀመንበር የነበረው ስብሐት ነጋ በትግራይ ትግሪኝ አጀንዳ ተጠልፎ የሻዕቢያን ተልእኮ ለመቀበልና ሀገር ለማስገንጠል ብሎም የሕዝብን ትግል ከድቶ ግዙፍ የዘረፋ ተቋም ለማቋቋም ያስቻለው የስብእና ለውጥ እጅግ ገራሚ ነው። ከሁሉ የሚገርመው ግዙፍ የዘረፋ የቢዝነስ ኤምፓየር ለመገንባት ሲንቀሳቀስ ለመቶ ዘመናት በዚሁ ተግባር የተራቀቁት ዓለምአቀፍ “ሕጋዊ” ማፍያዎች በዝምታ ይመለከቱኛል ብሎ የማሰቡ የዋሕነት ነው። የነሞቡቱና ሌሎችም አሻንጉሊት አስዘራፊ ዘራፊዎችን መጨረሻ ለማስተዋል እንዴት ሳይችል ቀረ?

የወልደ ሥላሴ ( ስብሐት) ነጋና የቤተሰቡን ስሞች ለተመለከተ የቤተክርስያን ጉልላቶችን የሚያስጌጡ፣ ለሃይማኖታቸው ቀናኢ ክርስትያኖች ስሞች እንጂ የቤተክርስትንን መሠረቷን የሚንዱ፣ ኦርቶዶክሳውያንን የሚያሳድዱ፣ ካህነት ጳጳሳትን የሚያስክዱ፣ የእግዚአብሔር የለሾች ስብስብ ስሞች አይመስሉም። ወልደ ሥላሴ፣ ቅዱሳን፣ ጻድቃን፣ ገብረ እግዚአብሔር፣ ተከሥተ፣ ተወልደ፣ ብርሃነ፣ አምኃ ሥላሴ፣ ትሩፋት። እንዲህ ዓይነት ስሞች በአረቦችና በግብጽ ሴራ በምእራባውያንም ተንኮል ተባባሪ ሆነው ክርስትናንና ክርስትያንን የሚጎዳ ኢክርስትያናዊ ድርጅት ይፈጥራሉ ብሎ ለማሰብ ይከብዳል። ገዳማትን ለማጥፋት፣ ቤተክርስትያንን ለመናድ፣ ክርስትያኑን ሕዝብ በሁለገብ አዳክሞ ዘለአለማዊ ጠላቶች ፈጥሮ እረፍት ለመንሳት፣ ክርስትያኑን ከርስቱ ለመንቀል፣ ክርስትያኑን ከፋፍሎ እንደጠላት እንዲተያይ ለማድረግ፣ የክርስትያኑን ሀገር ለባእድ ቅኝ ግዛት ለማመቻቸት፣ ያለ እረፍት የሚተጉ ሰዎች ስሞች አይመስሉም። ምን ያለ እርግማን ይሆን?

ስለ ስም ካነሳን የእስክንድር፣ የብርሃኑና የስብሐት አባቶች ስሞች የሁሉም ነጋ የተባለበት ተመሳሳይ ምክንያት ይሆረው ይሆን? ምናልባትም ከጠላት ወረራ በኋላ መንግሥት ተመልሶ ሲጸና የተወለዱ በመሆናቸው ነጋ ተብለው ይሆናል። ጨለማው ዘመን አለፈ ለማለት። ለኛም ለአዲሱ ጨለማ ዘመን ነዋሪዎች ቸሩ ፈጣሪ ጨለማችንን ያንጋልን።

ብዙ ነፍሰ ገዳዮች ደም እየጠራቸው፣ ደም ወዳፈሰሱበት ቦታ ይመጣሉ። በእልፍ ጉድጓዶች ከነሕይወቱ ተቀብሮ ያለፈው የትግራይ ክርስትያን ነፍስ እየጮኸ ጠርቶ እነስብሐትን መቀሌ አምጥቶ አስሯቸዋል። ያፈሰሱት የአርበኛ ቤተሰብ ደም ሲሚንቶ፣ የከሰከሱት አጥንት ደግሞ የብረት አጥር ሆኖ በዙ (zoo) ውስጥ እንደሚጎበኝ አውሬ በዚያ ፍርግርግ ውስጥ ብቻ ለመንቀሳቀስ ተገደዋል።

እስክንድርን ከእስር ቤት ውጭ ያለው ወገኑ ከእስር መውጣቱን በጉጉት የሚጠባበቀው ነው። ስብሐትንም እንደዚሁ። ስብሐትን ግን ቀጥቅጦ ለመግደል፣ ወይም ሬሳውን ለመጎተት ነው የሚጠባበቁት — ከእስር ቤቱ ውጭ ያሉት ወገኖቹ። የብርሃኑ ነጋ መፈታት ደግሞ  የሁላችንንም መፈታት የሚያበስር ስለሆነ ኢትዮጵያዊ በሙሉ በጉጉት የሚጠብቀው ነው። ማለትም ኢትዮጵያዊ ሁሉ ያለስጋት ከአዲስ አበባ ውጪ የትም ቦታ ሄዶ ብሔርና ሃይማኖቱ ሳይታይ በሰላም መንቀሳቀስ (በፖለቲካ፣ በንግድም ሆነ ሌላ ሥራ) የሚችልበት ጊዜ ሲፈጠር ለብርሃኑ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሰው ከእስር የመፈታት ዘመን ይሆናል ማለት  ነው።

የነጋ ልጆች እስር ለሀገር ሰላም ጠንቅ ነው። የነጋ ልጆች እስር መንስኤ የሁላችንም የነጻነት እጦት ምንጭ ነውና ሊፈታ ይገባዋል።

ብሔርና እምነት ተኮር የሰላማውያን ጭፍጨፋ ይብቃ!

አሁንገና ዓለማየሁ

 

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.