Sport: ቀነኒሳ በቀለ በኤደንበርግ አገር አቋራጭ ውድድር ላይ እንደሚሮጥ ታወቀ

ከቦጋለ አበበ

ወደር የማይገኝለት የረጅም ርቀት አትሌት ቀነኒሳ በቀለ በእዚህ ወር መጨረሻ በኤደንበርግ አገር አቋራጭ ውድድር እንደሚሮጥ ታውቋል፡፡ የዓለምአቀፉ አትሌቲክስ ማህበር ድረገፅ ሰሞኑን እንዳስነበበው ቀነኒሳ በኤደን በርግ ዘንድሮ ሲሳተፍ ለስድስተኛ ጊዜ ነው፡፡
የሠላሳ አንድ ዓመቱ የኦሊምፒክ የሦስት የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ቀነኒሳ እ.አ.አ ከ2006 ጀምሮ ለሦስት ተከታታይ ጊዜ በኤደንበርግ አገር አቋራጭ ውድድር ቢያሸንፍም 2010 ላይ ባልተጠበቀ ሁኔታ አራተኛ ሆኖ አጠናቅቋል፡፡ ከሁለት ዓመት በኋላም አሥራ አንደኛ ሆኖ ውድድሩን ማጠናቀቁም ይታወሳል፡፡

ቀነኒሳ በዘንድሮው ውድድር ግን ሁለት ጊዜ የተሸነፈበትን ታሪክ ለመቀየር መዘጋጀቱ እየተነገረ ይገኛል፡፡
ቀነኒሳ በዓለም አገር አቋራጭ ውድድር በረጅምም ሆነ በመካከለኛ ርቀት አሥራ አንድ ያህል የወርቅ ሜዳሊያዎችን በመሰብሰብ የሚስተካከለው አትሌት የለም፡፡
በፈጣን የአጨራረስ ብቃቱ የተለየ ዝና ያለው ቀነኒሳ በቀለ እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ በጉልበቱ ላይ በአጋጠመው ተደጋጋሚ ጉዳት ምክንያት በተለያዩ ውድድሮች ድል ሳይቀናው ቀርቷል፡፡ በተለይም በለንደን ኦሊምፒክ በአምስትና አሥር ሺ ሜትር እንዲሁም በሞስኮው የዓለም ሻምፒዮና በተመሳሳይ ርቀቶች ያመለጡት የወርቅ ሜዳሊያዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡
ቀነኒሳ በሞስኮው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ባይካፈልም ከሻምፒዮናው በኋላ በተለያዩ የጎዳና ላይ ውድድሮች ወደ ድል መመለሱን አሳይቷል፡፡ አሁንም ቀነኒሳ የቀድሞ ክብሩን ለማስመለስ ጥረት እያደረገ እንደሚገኝና ለ2016 የሪዮዲጄኔሮ ኦሊምፒክ እየተዘጋጀ እንደሚገኝ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
ቀነኒሳ በመጪው ዓመት ከመም ውድድሮች ወጥቶ ወደ ማራቶን የመግባት እቅድ እንዳለው በመግለጽ አሁን ወደ ቀድሞ አቋሙ እንደተመለሰና በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኝ ለዜናው ምንጭ ከሰጠው አስተያየት ማወቅ ተችሏል፡፡
ቀነኒሳ ባለፈው ክረምት በታላቁ የሰሜን በግሬት ኖርዝ ረን ኒውካስትል ውድድር ላይ በአሥር ኪሎ ሜትር የጎዳና ተወዳድሮ ላይ ውድድር የአገሩን ጀግና አትሌት ኃይሌ ገብረሥላሴና የወቅቱን የአምስትና አሥር ሺ ሜትር ንጉሥ ሞሐመድ ፋራን በማሸነፍ ወደ ቀደሞ ብቃቱ እየተመለሰ እንደሚገኝ አስመስክሯል፡፡
በኤደንበርግ ለማሸነፍ እንደተዘጋጀና በራስ መተማመኑም ከፍተኛ እንደሆነ የተናገረው ቀነኒሳ፤ኤደን በርግ ላይ ከተሸነፈባቸው ውድድሮች ይልቅ ባሸነፈባቸው ውድድሮች ጥሩ ትዝታ እንዳለውና ያንን ትዝታውን አሁን መድገም እንደሚፈልግ ገልጿል፡፡ ቀነኒሳ በተለይም በ2008 በዓለም ሻምፒዮና የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቱ ይታወሳል፡፡
በስኮትላንድ ኤደንበርግ ከተማ በየዓመቱ የሚካሄደው የአገር አቋራጭ ውድድር በዓለማችን ታዋቂ አትሌቶችን ከሚያሳትፉ ውድድሮች አንዱ ነው፡፡ ዘንድሮም ውድድሩ ከአውሮፓና አሜሪካ እንዲሁም ከአፍሪካ የተውጣጡ ጠንካራ አትሌቶችን እንደሚያሳትፍ ታውቋል፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በምንጃር ሸንኮራ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት ቁጥራቸው በወል ያልታወቀ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ

Share