ከሽብሩ ጀርባ ጀርባ – አሁንገና ዓለማየሁ

ሰሞኑን በአዲስ አበባና በኦሮሚያ ስለተከስተው የሽብርና የሰቅጣጭ ጭካኔ ድርጊት በተለያዩ የመገናኛ ብዙኅን ግልብ ትንታኔዎች ሲሰጡ ይስተዋላል። የነዚህ ትንታኔዎች ግልብነት የመነጨው ሽብሩን በነጠላው ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ብቻ ለመረዳት ከመሞከር ይመስለኛል።

እርግጥ ለሽብሩ ሰፈርኛ ምክንያት ስነፈልግለት ሕወሓት በለሆሳስ ወደ ነጻ ሀገረ መንግሥት ለሚያደርገው የጨለማ ግስጋሴ ትኩረት ማስቀየሻ ተኩስ ነው ልንል እንችላለን። ያስኬዳልም።

ሽብር ግን በዓለማችን ላይ ታላላቅ የኢኮኖሚ እና ጂኦ ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ለማራመጃ በረቀቀ ስልት የሚተወን ብዙ ተዋናዮች፣ የመድረክ ቅንብር መሪዎችና ጸሐፌ ተውኔቶች ያሉበት ክሥተት ነው። ሽብርን ቅኝ ገዢዎች፣ የእጅ አዙር ቅኝ ገዢዎችና የነርሱም አሻንጉሊቶች ጭምር ትላልቅ ጥቅሞቻቸውን ለማስከበሪያ የተጠቀሙበት፣ በዘመናትም እጅግ ያራቀቁት መሣሪያ ነው። የሽብር አጠቃቀም ዋና መለያው የሽብሩ ዋና ተጠቃሚ እና ጸሐፌ ተውኔት በተዋናይነት ቦታ አሸባሪውን ወክሎ የማይጫወት መሆኑ ነው። የሽብሩ ደራሲና ዋና ተጠቃሚ እንዲያውም ችሎታው ከሠመረለት ሽብሩን ሊያጠፋ እንደሚሯሯጥ ሥርዓት አስከባሪ፣ የሰላም ተቆርቋሪ ሆኖ ነው የሚተውነው።

በቀጠናችን ይህን ስትራቴጂ ቀደም ባለ ጊዜ በተሳካ ሁኔታ ተጫወተች ተብላ የምትገመተው እንግሊዝ ናት። ከመቶ ዓመታት በፊት በሱማሊያ ከየት እንደመጣ የማይታወቅ እብዱ ሙላህ (Mad Mullah) የሚል አሸባሪ ከሥታ፣ እርሱን ካካባቢው ሕዝብ አቅም በላይ በስውር ካስታጠቀች በኋላ፣ ሱማሌዎችን ከዚህ ሰው ሽብር ልታደጋችሁ በማለት “ስትደርስበት፣ ሲያመልጣት” ድፍን ሶማልያን (የእንግሊዝ ሶማልያ ይባል የነበረውን) ለመቆጣጠሪያ ተጠቅማበታለች። የሽብሩ ትያትር መጋረጃ ሲዘጋ ”እብዱ ሙላህ“ ድንገት እንደ ተከሠተ ድንገት ተሠውሯል። (እዚህ ላይ ታላቋና ገናናዋ አሜሪካም እንዴት ውትፍትፉ የቢን ላድን ድርጅት በአፍሪካና በእስያ ምድር “ስትደርስበት ሲያመልጣት” እንደነበር እናስታውስ)

በሁለተኛ ደረጃም አሁንም እንግሊዝ በኤርትራ ጣልያንን ተክታ በገባች ጊዜ እንግሊዝ በኤርትራ ቆላ ያሉትን እስላም ጎሳዎች እያስታጠቀች፣ የሚፈጥሩትንም “ሽብር” ለመቆጣጠር “ተቸግራ” ነበር። የኋላ ኋላ የዚህ የቆላ እስላም ታጣቂ ሽፍቶች ከጀብሃ ለቀደመው የኤርትራ ነጻ አውጪ ድርጅትና ለጀብሃ ሠራዊት የታጣቂ አስኳል ሆነው አገልግለዋል። እንደሚታወቀው የእንግሊዝ ፍላጎት ቆላ ኤርትራን ገንጥላ በዘመኑ “ንብረቷ” ከነበረው ሱዳን ጋር መቀላቀል ነበር። ይህ ተንኮል የከሸፈው በዋናነት አሜሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ የነዳጅ ኮንሰሺን በማግኘቷ እና ይህ ነዳጅ ከተገኘ ኢትዮጵያ በራሷ ወደቦች ብታወጣው ተመራጭ ሆኖ በኩባንያዎቹ በመታመኑ ነበር። ይህንንም ፍላጎት ለመንግሥታቸው በግልጽ በማስታወቃቸው ነው። በዚህም ምክንያት አሜሪካ ለገዛ ጥቅሟ ስትል ኤርትራ እንድትገነጣጠል ወይም ተገንጥላ በሌላ ቅኝ እንድትገዛ ወይም ነጻ ሀገር ሆና እንድትወጣ አልፈለገችም። በUN ያላትን ተጽእኖ ተጠቅማ ከኢትዮጵያ ጋር እንድትቀላቀል አድርጋለች። ( ለ”በዓሉ ድምቀት“ ሲደረጉ የነበሩ ተጓዳኝ ተውኔቶችን አናነሳም)። በቀዝቃዛው ጦርነት ጊዜ ደግሞ ጥቅሟ የሚከበረው በኤርትራ መገንጠል ስለነበር ይህንኑ በትጋት አስፈጽማ ለግብ አብቅታዋለች። (የደቀቅነውን ሣሮች ጉዳይ ባናስበው ይሻላል።)

121 ከሽብሩ ጀርባ ጀርባ   አሁንገና ዓለማየሁ

የምእራባውያን ኩባንያዎች የመንግሥቶቻቸውን ጡንቻ ተጠቅመው በሽብርም ይሁን በዲፕሎማሲ የዘረፋ “የንግድ ኢንቨስትመንት እና ሪሶርስ ኤክትራክሽን” እንቅፋት የሆኑትን አጥሮችና መሰናክሎች መበረጋገዳቸው የተለመደ ነው። ለምሳሌ የማእድን ኩባንያዎች ለመሬቱ ከባድ ክፍያ ከፍለው ማእድኑን በአግባቡ ድርሻ ጠብቀው ከሀገሬው ተካፍለው ከመጠቀም ይልቅ በሙስና የማእድንኑን መሬት ወስደው፣ ማእድኑን በዝቅተኛ ክፍያ ማውጣትና ተገቢውን ድርሻ ለባለቤቱ ሕዝብ ሳይከፍሉ የመጠቀም ታሪክ አላቸው። በተለይም ማእድኑ የተገኘበት መሬት ለእርሻ እጅግ ተስማሚ ሆኖ ገበሬ የሰፈረበት ከሆነ ወደድ የሚለውን በቂ ካሳና ክፍያ ለገበሬው ከፍሎ ከማስነሳት ይልቅ ገበሬውን በሽብር ከሥፍራው ማስወገድን ተመራጭ አድርገው ይወስዳሉ።  ለዚህ ማሳያ ቺያፓስ የሚባለው የሜክሲኮ ክፍል አንዱ ነው። በቡና፣  በካካዎ (ቸኮላት)፣ በሸንኮራ አገዳና ሌሎችም ምርቶች የበለጸገ ነው። የሃብታም ሀገራት ኩባንያዎች የከርሠ ምድር ማእድኑን ፈለጉት። ከላዩ የሰፈሩትን ሃብታም ገበሬዎች እጅግ አሰቃቂ የሽብር ተግባር የሚያከናውን የፉገራ እንቅስቃሴ ባካባቢው በመፍጠር ገበሬዎቹ ነፍሳቸውን አትርፈው ከተሰደዱ ከሃያ አመታት በኋላ እንኳን ሀገራቸውን ሲያስቡት እንዲያንገሸግሻቸው ተደርጓል። ሽብሩ ዓላማ ቢስ የመሰለ እና የተፈጸመውም ጭካኔ ሆን ተብሎ እጅግ ሰቅጣጭ ነበር።  ተመሳሳይ ምሳሌ በምሥራቅ ኮንጎም እናገኛለን። በከርሠ ምድር ማእድን እጅግ ከበለጸጉ የምድር አካባቢዎች ዋናው ነው። ባልተለመደ መልኩ ደግሞ መሬቱም ለእርሻ፣ ለከብት እርባታና ለግብርና ኑሮም እጅግ ተስማሚ ነው። እጅግ ብዙ ሕዝብም በላዩ ሰፍሯል። ለከርሠ ምድሩ ማእድን አስገላጊውን ካሳ ከፍለው ድርሻ ተስማምተው መጠቀም ያልፈለጉት ምዕራባውያን የሩዋንዳን የሽብር ተውኔት ጽፈው በታላቅ ችሎታ በመመድረክ ያንን ሽብር ወደ ምሥራቅ ኮንጎ አዛምተው የአካባቢውን ነዋሪ ከሥፍራው ነቅለውታል። እዚህ ላይ እጅግ ከፍተኛ ስትራቴጂክ ማእድናት አሉት ለተባለው ለዚህ ቀጠና ከአራት በላይ ሀገሮችን ማተራመስ አስፈልጓቸዋል። የ3  ሀገራት ርእሰ ብሔሮች ጭዳ ተደርገዋል። ከሚሊዮን በላይ ሕዝብ ታርዷል። ከሶስት ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ተፈናቅሏል። ዛሬም ሽብሩ በአነስተኛና ጥቃቅን ተደራጅቶ ቀጥሏል። የማእድን እና የተፈጥሮ ሃብት ዝርፊያው ግን እንገጭ እንጓ ሳይል በሰመረ ፍሰት ቀጥሏል። በተጓዳኝም ሰፊ መዋእለ ንዋይ አፍስሰው ብዙ ጭስ፣ አቧራና የፕሮፓጋንዳ ደመና በመፍጠር ተመራመርን የሚሉትን እንኳን ይህንን በሰው ልጅ ላይ የተፈጸመ አስነዋሪ ወንጀል መንስኤ እና ግብ ጠልቀው እንዳያዩ የሚሸፍን የተሳካ ግርዶሽ ፈጥረዋል።

ሊብያንም ማየት ይቻላል። የሊብያ ሽብር ባሰቃቂ ሁኔታ ቢባባስም የነዳጅ ፍሰቱ ሳይቋረጥና ሳይታወክ ቀጥሏል። የሊብያ ሕዝብ ግን ተጠቃሚ አይደለም። ለነዳጁ ሽያጭ ዶላር ሳይሆን ፈንጂና ባሩድ ይሰጠዋል። የዚህ ቀጠናም የሽብር ኢሰባዊ ጭካኔ ዋናውን ጭካኔ (የሰውን ልጅ በገዛ ሃብቱ የፍትሐዊ ተጠቃሚነትን በመንፈግ በድኅነት እንዲማቅቅ ማድረግን) የሚጋርድ ሆኗል።

ወደ ሀገራችን ስንመጣም ኢህአዴግ ሀገሪቷን ያላትን ብቻ ሳይሆን የተበደረችውንም ሙልጭ አድርጎ ከዘረፋት በኋላ ሥርዓቱ በቸርኬው ሲጥጥ ብሎ ሲቆም “ጥልቅ ተሃድሶ” ብሎ ከጌቶቹ ተማክሮ የሃገሪቷን አንጡራ መንግስታዊ ጥሪት ለመሸጥ ይስማማል። ( በነገራችን ላይ ደርግንም የሶቪየት ድጋፍ ሲቆምበት በቸርኬ መቅረቱ እንጂ ጀግናው የድሪቶ ሠራዊት ስለደመሰሰው አይደለም እጅ የሰጠው) በግራ ዘመም ትውልድ፣ በመሬት ላራሹና በሶሺያሊስት አስተሳሰብ የተቃኘችው ሀገር ላይ እንዲህ ዓይነቱ አንጡራ የሕዝብ ተቋማት ሽያጭ ተቃውሞ እንደሚገጥመው ኢህአዴግም ጌቶቹም በመረዳታቸው፣ ማስቀየሻ ተኩስ፣ ማሳሳቻ ውጊያ ማስፈለጉን ያምኑበታል። ስለዚህም ሕዝቡን በሽብር ወጥረው እንዲህ ያለውን የሃገር ችብቸባ አጀንዳ ተባብሮ እንዳይቃወም፣ እለት እለት በሥጋት እንዲኖር ያደርጉታል። ከጀርባ ግን ጨረታውና ችብቸባው የተያዘለትን መርሐግብር ይዞ እየተመመ ነው።

ለባእዳን ሰፋፊ የመካናይዝድ እርሻ ይውሉ ዘንድ የተመረጡ መሬቶች ተለይተው የረጅም ጊዜ የማፈናቀል እና አራሽ ትውልድ የማሳጣት ሥራ ተሠርቶባቸዋል። በጣም የታወቁትን የጋምቤላ፣ ጌዶ፣ ኮንሶ፣ ቤንሻንጉል ሽብሮች ለጊዜው እንተዋቸውና ያለ ሽብር በሌሎች ስልቶች ሊፈናቀሉ የተዘጋጁ ገበሬዎችን እንመልከት። ለሽብሩ ስልት ማወዳደሪያ ይሆኑናል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ ጎጃም ነው። የጎጃምን ገበሬ ከግብርና ሕይወቱ ነቅሎ መሬቱን ለመረከብ የረቀቀና የመጠቀ ዘመናትን የፈጀ ሥራ ተሠርቷል። በመጀመሪያ የተደረገው ለዚህ ፍላጎት ከተለዩ አካባቢዎች ሕጻናትን አዲስ አበባ በማምጣት ሎተሪ እና ሸንኮራ አዟሪ አድርገው የእርሻውን ሥራ ተረካቢ ትውልድ መንሳት ነው። ከተማ በገቡት ልጆቻቸው ምትክ ወልደው እንዳይተኩ ሴት ወንዱን በመርፌና በቀዶ ጥገና ማምከን ቀጣዩ ተግባር ነበር። በተጓዳኝ ማዳበሪያ በካድሬ ማስፈራሪያ ጭምር በመሸጥ እና የተደራራቢ ዓመታት እዳ ውስጥ በመዝፈቅ ገበሬውን እርሻውን ጥሎ ለቀን ሥራ ወደ ከተማ እንዲሰደድ ማድረግ ነው። በእነዚህ አካባቢዎች በማዳበሪያ እዳ የተዘፈቀው ገበሬ ሦስት ወንድማማች አባወራዎች ቢኖሩ አንዱ ቀዬውን እንዲጠብቅ ትተው ሁለቱ ከተማ ገብተው የቀን ሥራም ሆነ የተገኘውን እየሠሩ እዳቸውን ለመክፈል ይባዝናሉ። (እነዚህ ለሰፋፊ መካናይዝድ እርሻዎች የተለዩ የጎጃም አካባቢዎች ጣልያንም በፋሺስት ወረራ ዘመን ለዚሁ ተግባርና ጣልያኖችን አምጥቶ ሊያሰፍርባቸው የመረጣቸው የነበሩ በመሆናቸው ሰፊና ተደጋጋሚ ወታደራዊ ጥቃት አካሂዶባቸዋል።) እዚህ ላይ በእምቦጭ ሊደርቅ የታሰበውን ጣናን እና ባለቤት የሌለውን የጣናን “መሬት” በዚህ ዓይነቱ እሳቤ እየተሠራበት ሊሆን እንደሚችል አለመጠርጠር የዋህነት ነው።  እምቦጭ ለምን ሥራዬ ተብሎ መጣ? ለምንስ መንግሥታዊ ትኩረት “ተነፈገው”? ያልተገደበውን ዐባይን ለመገደብ ይህን ያህል እየተሟሟትን የተገደበውን ጣና እንዲደርቅ ለምን ፈቀድን? ይቅርታ ከርእሱ ወጣሁ።

የኢህአዴግ ጌቶች ሰፋፊ መሬቶችን በቀላሉ ለማስለቀቅ የሚጠቅመውን የክልል ሥርዓት ኢህአዴግ እንዲለውጥ አይፈልጉም። ለምሳሌ የጋምቤላን ጎሳዎች “ደገኛውን ከመሬታችሁ አስወጡ” በሚል መሸንገያ በደገኛው ላይ ሽብር ፈጥረው እንዲነቅሉት ካበረታቷቸው በኋላ እነሱንም ጨፍጭፈው መሬቱን ለውጪ ኩባንያዎችና ለወያኔ ታጋይ “ኢንቨስተሮች“ አከፋፍለውታል። ቤንሻንጉልና ምእራብ ወለጋም ተመሳሳይ ነገር ተሠርቷል። ይህ መሬትን በጅምላ የማግኛ ዘዴ እጅና እግራችን እንደተጠፈረ ባእዳን ኩባንያዎች እስኪወርሱን ድረስ እንዲጸና ይፈለጋል።

የዛሬውም የአርሲ የባሌና የምሥራቅ ሐረርጌ ሽብር ተመሳሳይ ግቦች ያሉት ነው። የጎረቤቴን ማሳ እወርሳለሁ፣ ሀገሩ ይሰፋኛል ብሎ የሚያስበው የዋህ፣ እርሱንም ጭምር የሚያወድም፣ ከቦታው የሚያስወግድ እቅድ ውስጥ እየተሳተፈ መሆኑን አያውቅም። ክፍል 1ን እየተወነ ነው። ክፍል 3 ላይ መጋረጃው ሲከፈት እሱም በመድረኩ ላይ አይታይም።

ወንድሜ

የደገሱልህን ጉድክን ሳትሰማ

እወርሳለሁ ብለህ የወንድም ባድማ

ጎጆውን አንድደህ ከብቱን ብትነዳ

ሌላ እልቂት አለ ላንት የተሰናዳ።

ሌላም ደብዳቤ አለ በርሊን የተጻፈ

ሎንዶን የተጻፈ/ ዲሲ የተጻፈ

ፓሪስ የተጻፈ

ያንተን ድርሻ ጭምር ለባእድ ያሳለፈ።

እናማ

ከሰማህ ልንገርህ ልምከርህ የኔ ጓድ

በሜንጫ፣ ገጀራ አትቆፍር ጉድጓድ

ሀገርህ ዙሪያዋን የቆመው ጅባጅብ ጃርትና አሳማ

ሱባኤ የያዘው ሊፈነጭበት ነው ያባትክን ባድማ።

ስለዚህ የዋሁ! ወንድምክን አትግደል

ላንተው መቅበሪያ ነው ያስቆፈሩህ ገደል።

ሀገሪቷን በጎበዝ አለቃ ከፋፍሎ በየጎጡ ካለው ወርቅም ሆነ ሌላ ማእድን ፍርፋሪ እና የመንደር ዙፋን ማስጠበቂያ ለጎበዝ አለቃው እየወረወሩ መዝረፍ በምእራብውያን ድንበር ዘለል ኩባንያዎች እጅ በሌሎች ሀገሮች ላይ እየተተገበረ ያለ ሥርዐትና ወደ እኛም እያዘገመ የመጣ አደጋ ነው።

ስለዚህ የ30 ዓመቱ ሽብር ባለቤት ኢህአዴግ ቢሆን ከዚያ ጀርባ ደግሞ  እንደ ግብጽ ያሉ ሀገሮች ቢኖሩበት፣ ከነሱ በስተጀርባ ደግሞ የነርሱም ጌቶቻቸው የሆኑ እነ እንግሊዝና አሜሪካን የመሳሰሉ ናቸው የማስተር ፕላኑ ጸሐፍያነ ተውኔትና ተጠቃሚዎች።

ዛሬ ለእርድ የቀረበውን የቴሌና ሌላም ፍሪዳ ማን እየተጫረተ ማንስ ጨረታውን ”እያሸነፈ“ እንደሆነ ልብ ብለን እናስተውል። በጦር ሜዳ ያሸነፍናቸው ቅኝ ገዢዎች በቀጭኑ ሽቦ መጥተውልናል። ኧረ የምን ሽቦ? ያለሽቦ እንጂ። ይሄ የደህንነት ፣ የግንኙነት እና የፋይናንስ ነገሮችን የሚጠቀልል ሴክተር ከእጅ ወጥቶ በዲጂታል ኮሎናይዜሽን ዘመን ነጻ ሀገር ነኝ ማለት ማላገጥ ነው የሚሆነው።

ቴሌኮም ሲባል እንደታቻምናው የስልክ ኩባንያ ብቻ አይደለም። በ21ኛው ክፍለ ዘመን ቴሌኮም በተለይ በአፍሪካ ከፍተኛ የፋይናንስ ዘርፍ ያለው የባንክን እና የደህንነትንም ሥራዎች የሚሠራ በማሕበራዊ ኢኮኖሚው ውስጥ ግዙፍ ድርሻ ያለው የእያንዳንዱን ዜጋ ሕይወት የሚቆጣጠር ተቋም ነው። በዲጂታል ኮሎኒያሊዝም ዘመን ይህንን ቁልፍ ሴክተር ለቅኝ ገዢዎች  አስረክቦ ነጻ ሀገር መባል ፌዝ ነው።

ምናልባት በሽብሩ ጫጫታና ጭስ ምክንያት ዜናውን ላልተከታተላችሁ፣ የቴሌን ጨረታ ከሚወዳደሩት ውስጥ በግንባር ቀደም የቅኝ ገዢዎች ኩባንያዎች ይገኙበታል። እጅግ የሚደንቀው በወራዳው የአፍሪካ ቅኝ ግዛት ታሪካቸው የሚሸማቀቁት እነዚህ ሰዎች በኬንያ እና በኢትዮጵያ የሚያደርጉትን ኢንቨስትመንት አፍሪካዊ ባለቤት ያለው ለማስመሰል የሚሄዱት ርቀት ነው። ለምሳሌ አንዱን የእንግሊዝ ተጫራች እንይ። በኬንያ ይኸው ግዙፍ የእንግሊዝ ኩባንያ ራሱን ሳፋሪ ኮም በሚል ”የትግል ስም“ ሲጠራ በኢትዮጵያ ጭራሽ ”ግሎባል ፓርትነርሺፕ ፎር ኢትዮጵያ“ የሚል ”የትግል“ ማላገጫ እየተጠቀመ ነው። ኢትዮጵያ በሚል ስም ኢትዮጵያን መግደል እንደሚቻል ኢህአዴግ በሚል ስም ኢትዮጵያን ስትገድል ከኖረችው ወያኔ ትምህርት ወስዷልና ። አስተማሪው ማን ሆኖ?አትሉኝም። የሚገርመው ልክ እንደ ኢህአዴግ ያው አንዱ የእንግሊዝ ኩባንያ የተለያዩ ድርጅቶች ፈጥሮ የሶስት ድርጅቶች ”ግንባር“ ሆኖ ነው የተከሠተው።  እኔ ራሴ መጀመሪያ ስሙን ሳነብ በዳይስፖራ ያሉ ኢትዮጵያውያን ያቋቋሙት የኢንቨስትመንት ቡድን ነበር የመሰለኝ። አፍሪካን እየጠቀለለ ያለው የእንግሊዙን ቮዳፎን ከተጫራቾች ዝርዝር ሳጣው ጊዜ ነው ቀረብ ብዬ ስሞቹን መመርመር የያዝኩት። ባንዱ ምሕጻረ ቃል ውስጥ አገኘዋለሁ ብዬ ሳስብ ጭራሽ ባላሰብኩት ጭምብል ነው የተመዘገበው።  ብራቮ!የራሳቸውን ታሪካዊ የተንኮል ሥራ እንዲሁም የኛን ሥነልቡና ከሚያውቁ ሰዎች የሚጠበቅ ተግባር ነው። ከመቶ ዓመታት በኋላ እንደ ድመት አድፍጠው ይዘውናል። ቀጣዩ ዓይናችንን አጥፍተው የሚጫወቱበት ክፍል ይሆናል ማለት ነው። ተዋናዮች ይለዋወጣሉ፣ ተውኔቱ አይለወጥም።

አቧሯና ጭሱ ሲወገድ ደመና

እርሻህም አይታይ እንኳን በሬህና።

ስለዚህ ወገን ስለሽብሩና ጭካኔው ሃይማኖታዊ፣ ሥነልቡናዊና ባህላዊ ትንታኔ መስጠት ላይ ከማተኮር ብዙ የመዋዕለ ንዋይና የእቅድ ግብአት የፈሰሰበት ሽብር ዓላማና ግብ ያለው መሆኑን አውቀን ራሳችንን እና ሀገራችንን በምንችለው ሁሉ እንታደግ።

 

አሁንገና ዓለማየሁ

*ይህ “የሩዋንዳ ሾርባ” ግጥም ዘንድሮ በግንቦት ወር የተደረሰ ሲሆን ብዙ ሰዎች የተጋነነ ወይም አጉል ሟርት ነው የሚል ዐይነት ምላሽ ሰጥተውበታል። አዲስ አበባ የዙፋኑ መቀመጫ መሆኗ በጃት እንጂ የአርሲ ሻሸመኔ እልቂት በእልፍ ተባዝቶ ሊከሠትባት ይችል ነበር። ሰውረን ማለቱ ጥሩ ጸሎት ሆኖ ባሌ አጋርፋና አርሲን ካዩ በኋላ እጅ አጣጥፎ መቀመጡ ግን በውጤቱ ተጠቂ ብቻ ሳይሆን ተጠያቂም የሚያደርግ ነው።

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.