የከተማዋ ነዋሪዎች ለሰላም ከመንግሥት ጎን እንደሚሆኑ ገለጹ

addis ababa የከተማዋ ነዋሪዎች ለሰላም ከመንግሥት ጎን እንደሚሆኑ ገለጹመምሩ ዋሲሁን የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው። ወልደው ከብደው የልጅልጅ አይተው 60 ዓመት በዚህች ምድር ሲኖሩ በዕድር፣ በዕቁብ፣ ዘመድ ለማፍራት ልጃቸውን ክርስትና ሲሰጡ፣ እርሳቸውም ለዝምድና ተፈልገው ክርስትና ሲሰጣቸው፣ አማች እና ምራት ሲሆኑ በሌላም ማህበራዊ ግንኙነት በጉርብትና አብረዋቸው ከኖሩት ጋር በዘርና ሐረግ ሳይሆን ሰው በመሆናቸው ብቻ ተሳስበው፣ ተከባብረውና ተዋድደው እንደኖሩ ይናገራሉ።
እርሳቸው በዕድሜያቸው የሚያውቁት ኦሮሞ በጉዲፈቻ ልጅ ሲያሳድግ። ያሳደገውንም ከወለደው ልጅ እኩል ሲያደርገው ነው። በዚህ የሚያውቁት ኦሮሞ ዛሬ የሰው ህይወት ሊያጠፋ ተነሳ ሲባል መስማታቸው እንግዳ ነው የሆነባቸው። ወንድም በንወድሙ ላይ መነሳቱ፣ አብሮ የኖረን ሰው ለማለያየትና ለውጭ ጠላት አሳልፎ ለመስጠት የሚደረግ ጥረት የኢትዮጵያውያን ድርጊት ነው ብለው ለመቀበልም ይቸገራሉ። በየጊዜው የሚነሱ ሁከትና ግርግሮችንም አጥብቀው ይቃወማሉ።
‹‹መሪ ለመሆን የሰው ህይወት መጥፋት የለበትም። ንብረትም መውደም የለበትም። ያልተመቸ ነገር ካለ በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት ነው የሚሻለው። በኃይል ወንበር ላይ ቢቀመጡም የወደመ እና ዜጎቿ የተጎዱባትን ሀገር መረከብ ነው የሚሆነው›› ያሉት መምሩ፣ እንዲህ ያለው አካሄድ ሀገርን ቁልቁል እንጂ እንደማያሳድግ ይገልጻሉ። መንግሥት ሳይቸኩል ነገሮችን በብስለትና በትዕግሥት ማለፉ ጥሩ ቢሆንም ዜጎች ወጥተው ለመግባት ሥጋት ላይ እስኪወድቁ ድረስ መሆን የለበትም ይላሉ። ህብረተሰቡንም ከጎኑ በማድረግ የሀገር ሰላምን ማረጋገጥ አለበትም ብለዋል።
ሌላዋ የከተማ ነዋሪ ወይዘሮ አስረበብ ደመቀ ይባላሉ፣ በሌሎች ሀገሮች ሲፈጸም በመገናኛ ብዙሃን ይሰሙና ያዩ የነበረው ሁከትና ግርግር ኢትዮጵያ ውስጥ ማየታቸው ያሳዝናቸዋል። ኢትዮጵያዊ ሥነምግባሩ የት ደረሰ ብለውም ይጠይቃሉ። ትንሽ ትልቁ መንግሥትን ሲተችና ከሥነምግባር ውጪ የሆነ ነገር ሲናገሩ ይሰማሉ። ልማትና ዕድገቱ ቀርቶ ትችትና ጥፋቱ መበርከቱን ይታዘባሉ። ችግሩ የመንግሥት ብቻ ነው ብለውም አይወስዱም። ወላጆች ልጆቻቸውን በሥነምግባር አንጾ በማሳደግ ላይ ክፍተት አሳይተዋል ብለው ያምናሉ።
‹‹ዛሬ ሁከትና ግርግር ላይ የሚሳተፈው ከየቤቱ የወጣ ወጣት ነው›› የሚሉት ወይዘሮ አስረበብ፣ ወላጅ ልጁን ቢቆጣጠር፣ መንግሥትም የሚጠበቅበትን የሀገር ሰላም ማስከበር ተልዕኮ ቢወጣ አሁን የተፈጠረውን ችግር መቀነስ ይቻል እንደነበር ይገልጻሉ። ድርጊቱ ወደፊትም እንዳይደገም መንግሥትና ህዝብ ተባብሮ መሥራት እንዳለበት ተናግረዋል።
ወይዘሮ ትርሐስ ሞላ የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው፣ ችግሩ በህዝብ አንድነት ላይ ባለመሠራቱ የመጣ ክፍተት እንደሆነ ያምናሉ። እርሳቸው እንዳሉት ዛሬ መገናኛ ብዙሃን ሰፍተዋል። ሁሉም የመሰላቸውን መረጃ ይሰጣሉ።ሰውም በመሰለው መንገድ ሃሳቡን ይቀበላል። መልካም ነገርን ከመቀበል መጥፎውን መከተል የሚመረጥበት ጊዜ ላይ መደረሱንና ችግሩ ሥር ሳይሰድ ከወዲሁ መስተካከል አለበት ይላሉ።
በእርሳቸው ዕድሜ የሀገር መሪን ደፍሮ መተቸት ቀርቶ ታላቅን ቀና ብሎ ማየት አይቻልም። ፍራቻና አክብሮቱ መልካም የሆነ ግንኙነትን ሲፈጥር እንጂ ለጠብ ሲጋብዝ እንዳላዩ ያስታውሳሉ። አንዱ ሌላውን ማክበር እንደሽንፈት የሚታይበት ጊዜ ላይ መደረሱ ያሳዝናቸዋል። ነገሮችን በሽማግሌ የመፍታቱ ባህል እየተሸረሸረ ሄዶ ፀብንና ብጥብጥን መምረጥ፣ አልፎ ተርፎም ሀገር እስከማፍረስ ደረጃ መደረሱ አግባብ አይደለም ይላሉ። አሁንም ሁሉም በየአካባቢው ለሰላም እንዲሠራ መደረግ አለበት ይላሉ።
‹‹የድምፃዊ ሀጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ የተነሳው ሁከትና ግርግር፣ የጠፋው የሰው ህይወትና የወደመው
ንብረት በእምነትም በሰብዓዊነትም የማይደገፍ ነው›› የሚሉት አቶ ይትባረክ ጌታቸው የአዲስ አበባ ነዋሪ ናቸው፡፡ የሆነውን ነገር ዳግም እንዳይከሰት ሁሉም በየዕምነቱ በፀሎት እንዲሁም ድርጊቱን በመኮነን ዳግምም እንዳይከሰት ሊሠራ እንደሚገባ ያስረዳሉ። መንግሥት አብረውት የሚሠሩትንም የሥራ ኃላፊዎች መፈተሽ አለበት ይላሉ። አንድ አካባቢ ችግር ሲከሰት የአካባቢው አስተዳደር አፋጣኝ ዕርምጃ እንዲወሰድ ካላደረገ የማስተዳደር ኃላፊነቱን ተወጥቷል ለማለት እንደሚያስቸግር ገልጸዋል።
አቶ ይትባረክ፣ ሰላም ትልቅ ዋጋ እንዳለው መንግሥት ዕርምጃ መውሰድ ከጀመረ ወዲህ መገንዘባቸውን ይናገራሉ። መንግሥት አጥፊዎችን በህግ ለመጠየቅ እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ ጥሩ ቢሆንም መዘናጋት እንደማያስፈልግ ይናገራሉ። እርሳቸው እንዳሉት ችግሮች ከመድረሳቸው በፊት ለመከላከል የሚያስችል ሥርዓት መዘርጋት አለበት። ሦስት ሰኔዎች በሰው ህይወት መጥፋትና ንብረት መውደም አልፈዋል። ከዚህ በኋላ ሌላ ሰኔ መደገም የለበትም። አሁንም ህዝብ ተረጋግቶ የዕለት ተዕለት ተግባሩን እንዳይወጣ የሚያደርጉ መልዕክቶች እየተላለፉ ስለሆነ ህዝብ በተሳሳተ መረጃ የማይሆን ነገር ውስጥ እንዳይገባ ከህዝብ ጋር መሥራት እንደሚያስፈልግም አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2012
ለምለም መንግሥቱ

2 Comments

  1. Tear off Woyane and OLF’s constitution !!
    Ban ethnic and faith based parties !! Whatever it takes !
    በየከተማው የሰላም እና መረጋጋት ኮሚቴ በማቁዋቁዋም ህዝቡ ራሱን ይጠብቅ !!
    Make a national call and form a broad based national Front to salvage our beloved Country !!
    Let us all boost the moral of Abiy’s leadership.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.