“የክልልነት ጥያቄ ያላቸው ከሲዳማ የትግል ሂደት ውጤቱን ብቻ ሳይሆን ውድቀትንም መማር አለባቸው”አቶ ደስታ ለዳሞ የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር

desta lidamo• ሲዳማ በትግል ባለፈበት መንገድ አንዴ ሲወድቅ ሌላ ጊዜ ሲነሳ ቆይቶ ነው እዚህ ሊደርስ የቻለው። ስለዚህም መማር ካለብን ከጥንካሬም ከድክመትም ነው። ምናልባት ይጠቅማል ብለን ካሰብን ደግሞ ጥንካሬውን ይዘን መቀጠል እንችላለን። ድክመቱን ግን መድገም አይኖርብንም። ሞኝ ከራሱ፤ ብልህ ደግሞ ከሰው ይማራልና።
• እኛ አሁን ክልል ስለሆንን ምንም ጥያቄ የለንም፤ ትግልም የለም ማለት አይደለም። ሲዳማ ክልል ሆነ ሲባል የሆነ ሰፈር ደግሞ እኔ ዞን ካልሆንኩ የሚል ጥያቄ ከወዲሁ ቀጥሏል። አንዳንድ ቀበሌዎች ደግሞ ተሰብስበው እኛ ወረዳ እንሆናለን ብለዋል። ስለዚህ አይነቱ ይቀያየር እንጂ ትግሉ በየወረዳው አለ። እነዛ ትግሎች ደግሞ ወደቅራኔ ተቀይረው ቅራኔው ለጠላት ምቹ ሁኔታ ቢፈጥርና ጫጫታው ቢበዛ እንዲሁም ቢሰፋና ቢቀጥል ወደሁከትና ቀውስ ነው የሚያመራው። ስለዚህ ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል።
• ጥያቄው ወደ አመጽ ተቀይሮና ቤት ንብረት ወድሞ ግለሰቦች ተጎድተውና ተንገላተው መታሰርና መጨነቅ የደረሰበት አይነት ውጤት የሚያስከትል ትግል ተመራጭ አይደለም። ተመራጩ በሰላማዊ መንገድ፣ በውይይትና በምክክር የሚደረግ ትግል ነው።
• የሲዳማ ህዝበ ውሳኔ ተካሂዶበትና የክልልነት ጥያቄው ይሁንታ ካገኘ በኋላ እንኳ ለምን ዘገየብን በሚል በጉልበት መንግስት ለመመስረት ሲኬድ ነበር። በዚህ አካሄድ ተፈቅዶ ቢሆን ኖሮ ተመሳሳይ ውድቀት ይገጥመን ነበር። በዛ መንገድ ሂዶ ቢሆን ኖሮ እንዳሁኑ ያማረ ሳይሆን የሚበላሽ አይነት ይሆን ነበር።
• የመጣው የለውጥ ሀይል የሲዳማን ጥያቄ ቀደም ብሎ ይሰማው ስለነበር ጥያቄው ትክክለኛ መሆኑን አምኖ ተቀብሏል፤ ለማፈን አልሞከረም። እንዲያውም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በፓርላማ ንግግራቸው የህዝቦችን ጥያቄ በአክብሮት ተቀብለናል ሲሉ ጠቅሰዋል፤ በህጋዊ መንገድ መልስ እንደሚሰጥና እስከዛው ግን ያልተገባ ተግባር እንዳይፈጸም ጥንቃቄ አድርጉ ሲሉ ማሳሰባቸው ይታወሳል።
• የለውጥ ሀይሉ የሲዳማን ጥያቄ በአክብሮት ስለተቀበለው ሲዳማ ጥያቄዬ ይመለስ ብሎ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ በኃይል ለመመከት እንዲሁም ለማደናቀፍ አልሞከረም፤ የፈጠረው ምቹ ሁኔታን ነው። የብልጽግና ፓርቲ ሊቀመንበር የሆኑት ዶክተር ዐብይ አህመድ ለሲዳማ ጥያቄ ትክክለኛ መልስ እንዲገኝ አይነተኛ ሚና የተጫወቱ መሪ ናቸው። ከዚህ በተጨማሪ የህዝቡ አንድ መሆንና ትግሉን አጠናክሮ መቀጠል ምላሽ ሊያሰጥ ችሏል።
• ሲዳማ ሲታገልለት ለነበረው ጥያቄ በአግባቡ ምላሽ አግኝቷል። ምላሽ በማግኘቱም የራሱ የሆነ መንግስት አቋቁሟል።
• ባለፉት ሁለት ዓመታት ስህተት የተፈጸመው በሆነ ጊዜ ነው። ያንንም ስህተት የሲዳማ ሽማግሌዎች በአጠቃላይ ማህበረሰቡ ወዲያውኑ ነው ያረሙት። ህብረተሰቡ ደግሞ የዚያን አይነት ስህተትና ውድቀት ስለማይፈልግ ሁለተኛ አልደገመም።
• አሁን ግን ሰሞኑን ሲዳማ ራሱን በራሱ የሚያስተዳድርበት ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት መስርቶ ከዚህ በኋላ ህግም ፖሊሲም አውጪ ሆኖ በውስጥ ጉዳዮቹም እንደነባራዊ ሁኔታ ችግሮችን የሚፈታበት ውሳኔም የሚያስተላልፍ መንግስት መሆን ችሏል።
• ሲዳማ በአገር ደረጃም ቢሆን ከሌሎች መንግስት ከሆኑ አካባቢዎች ጋር እኩል ተሳታፊ ይሆናል። እነዚህ ልዩነት ያላቸው ፖለቲካዊና ስነልቦናዊ ጉዳዮች በመሆናቸው ትልቅ ትርጉም የሚሰጣቸው ነው። ይህን ለማግኘት ደግሞ መቶ ዓመት እና ከዛ በላይ ዋጋ ተከፍሏል።
• የሲዳማ ህዝብ ድሮም ቢሆን ከኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ጋር ሚዛኑን ጠብቆ፣ ተባብሮና ተጋግዞ መኖር የሚፈልግና ፤ የሚችል ህዝብ ነው።
• አሁንም ከኢትዮጵያ ብሄር፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጋር የመሆን፣ እኩል የመሳተፍና የመረዳዳት መብት ነው ያገኘው።
• የሲዳማ ህዝብ ከዚህ በኋላ ለመብት ብሎ የሚታገለው በመንግስቱ ውስጥ ምናልባት የመልካም አስተዳደር ጉድለት ካለ፣ ከራሱ አብራክ የወጡ መሪዎቹ የሚበድሉት ከሆነ፣ ሌላ መሪ ለመቀየር እንጂ፤ ሌላ መንግስት ለማቋቋም፤ አሊያም ሌላ አገር ለማቋቋም የሚያደርገው የነጻነት ትግል የለውም።
• ስለዚህም ትናንት ሲደረግ የነበረው አይነት ትግል በእኛ እድሜ አብቅቷል። በልጅ ልጆቻችንም እንኳ ይደገማል ብለን አንጠብቅም።
• እኛ የሲዳማ ክልል ብቻ ሳንሆን የኢትዮጵያም አካል ነን። ኢትዮጵያ ስትኖር ነው ሲዳማ የሚጠቀመው። ወተት ለማግኘት ሲባል ላሟን መግደል ስህተት ነው። ስለዚህ እንደዛም እንዳይሆን ጥንቃቄ ያስፈልጋል። የሚቆረስ ዳቦ ትልቅ ከሆነ ድርሻው እየተለቀ ይሄዳል። ዳቦው ትልቅ እንዲሆን ደግሞ ተባብሮ መስራትና ሀብት መፍጠር ያስፈልጋል። ሀብት ለመፍጠር የምናደርገውን ጥረት ደግሞ የሚቃወሙ ኃይሎችም አሉ።
• አሁን ያለንበትን አጠቃላይ አገራዊና አካባቢያዊ ሁኔታን ግምት ውስጥ በማስገባት የጠላት ኃይሎችን እጅ አስገብቶ ብጥብጡንና ወድቀታችንን እንዳያሰፉ ይህንን የሚያደርጉት የእኛ ጥያቄ እንዲመለስ ፈልገው ሳይሆን በእጅ አዙር የራሳቸውን ጥቅም ለማስጠበቅ መሆኑን መረዳት አለብን። በመሆኑም የሚደረጉ ትግሎች ስህተቶችን የማይደግሙ ቢሆኑ መልካም ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ወቅታዊ አገራዊ ሁኔታውን ከግምት ውስጥ ማስገባትም ብልህነት ነው።
• ይህ ሲዳማ ነው፤ ያኛው ሲዳማ አይደለም የሚል ነገር አይኖርም። የተማረ ያልተማረ ነውም አይባልም። እንደየአካባቢው ሁኔታ ሊተገበር የሚችልና በአካባቢያችን ያለውን ነገር ታሳቢ የሚያደርግ እና መፍትሄ ያዘለ መነሻ እቅድ አዘጋጅተን አሳታፊ በሆነ አግባብ መምከር ነው።
• የጸጥታ መዋቅሩ በአጠቃላይ የክልል መንግስት እንደመሆናችን ያስፈልገናል። ይህን የማደራጀት ድንጋጌም ሆነ ስልጣንም አዲሱ ክልል ያለው በመሆኑ በሲዳማ ክልል ህገ መንግስት ውስጥ ተካቷል። የፖሊስ ኃይል የሲዳማ ዞን ቀድሞም ያለው ሲሆን የልዩ ኃይል ግን አላደራጀም። ከዚህ በኋላ ግን ሌሎች ክልሎች እንዳሏቸው ሁሉ ሲዳማ ልዩ ኃይል ጨምሮ የፖሊስ ኃይልንም ቁጥር፣ የቴክኒካልና የትጥቅ ብቃትንም በሚያሳድግ መልኩ ጠንካራ የጸጥታ መዋቅር አደራጅቶ የውስጥ ችግሮቹን ጸጥታ ኃይሉ በሚፈታበት አግባብ ይፈታል።
• ነገሮችን በጥንቃቄና በልኩ ብናይ ጥሩ ነው፤ ክልል መሆን አገር አይበትንም። ግን ሁሉም ክልል እሆናለሁ ካለ ችግር አለው። እንዴት ቢባል፣ ኢትዮጵያ ወደ 80 ብሄር ብሄረሰቦች አሏት። ህገ መንግስታችን ላይ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ይላል፤ በመሆኑም ሁሉም ይችላሉ ማለት ነው። በዚህ ላይ ገደብ የለውም ማለት ነው። ይህ ከሆነ ደግሞ 80 ክልል ሊጠየቅ ይችላል። ይህ ከሆነ በአገሪቱ ውስጥ ያለውስ ኢኮኖሚ ይችላል ወይ? ኢኮኖሚውም ቢፈጠር የሚከፋፈለው በቀመር ነው። ቀመር ውስጥ ደግሞ ከፍተኛ ድርሻ ያለው የሕዝብ ብዛት ነው። በመሆኑም
• ትልቅ በጀት ትልቅ ህዝብ ወዳለበት ይሄዳል። እነዚህ በንጽጽር መታየት ያለባቸው ጉዳይ ናቸው እንጂ ክልል መሆን አገር ይበትናል ብዬ አላስብም። ነገር ግን ክልል መሆን ብቻውን በቂ አይደለም። ጎን ለጎን ግን አስፈላጊ የሆኑ ወጪዎችን ከየት አምጥተን እንደምንሸፍን አብሮ ማሰቡ ተገቢ ነው ብዬ አምናለሁ።
• እኛ ኢትዮጵያውያን ከተባበርን ማኛውንም ጠላት መመከት እንችላለን። እኛ በሀብታችን ከራሳችን ምድር ከሚመነጨው ውሃ ይህን ያህል መድከም አይጠበቅብንም። የሚመነጨውን ይህን ውሃ ብዙ አገራት ወደሀብት ቀይረው የሕዝባቸውን ህይወት እየለወጡበት ነው። እኛም በተመሳሳይ መልኩ የህዝባችንን ህይወት የሚለውጥ ሀብት አድርገን እንጠቀምበት ብለን
• የግብጾች የዲፕሎማሲ ጥረታቸው ከዚህ በፊትም የተለመደ ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ የሚደረጉ በርካታ የአመጽና የሑከት እንቅስቃዎችን በእጅ አዙር ፋይናንስ ማድረጋቸውም የሚታወቅ ነው። አንዳንድ ነጻ አውጪ ኃይላት ጭምር ከዚህ በፊትም ቢሆን በእነሱ ይደገፋሉ።
ምንጭ አዲስ ዘመን ሐምሌ 9/2012
ተጨማሪ ያንብቡ:  "የትግራዩ መንግስት አማራውን እየገደለ ያለው በጥይት ብቻ አይደለም" - የአማራ ተጋድሎ አክቲቪስት ቤተልሄም ዓለምሰገድ | ሊያዩት የሚገባ ቪዲዮ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.