ከሊብራል ዴሞክራሲ ወደ ሶሻል ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ለውጥ አድርገናል (ምክክር ፓርቲ)

midker partyተሻሻለው የምክክር ፓርቲ ፕሮግራም ነው። ፕሮግራሙ በሕገ መንግስት ላይ ፓርቲው ያለው አቋም፣ከሊብራል ዴሞክራሲ ወደ ሶሻል ዴሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ለውጥ አድርገናል… ቀሪውን እንዲያነቡና ለሕዝብ ይፋ እንዲያደርጉልን በኢትዮጵያ አንድነት ስም እንጠይቃለን።

1. መግቢያ

   ምክክር ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (ምክክር ፓርቲ) አገር አቀፍ የፖለቲከ ፓርቲ ሲሆን በመላው ኢትዮጵያ የሚንቀሳቀስ ሕብረብሔራዊ ፓርቲ ነው፡፡ ፓርቲው የዜጎችን ነፃነት ለማስከበር የሶሻል ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም የሚከተል ሲሆን ፅንሰ ሀሳቡንና ፍልስፍናውን ከሀገራችን ነባራዊ ሁኔታ የሕዝብን ፍላጐት መሠረት ያደረገ ጠቃሚ እሴቶችን በመውሰድና በማጣመር ከሚቀርፃቸው ፖሊሲዎች አንፃር የሕዝቡን ተጠቃሚነት ላይ መሠረት በማድረግ ፖለቲካዊ እንቅስቃሴውን ያደርጋል፡፡

    ምክክር ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ (ምክር ፓርቲ) የሶሻል ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም መመሪያ አድርጎ የትግሉ ራዕይ ምን መምሰል ይኖርበታል?፣ የፖለቲካ ፕሮግራሙ፣ የሥነ-ምግባር መመሪያው፣ የአመራሩና የመዋቅሮቹ አደረጃጀት ብሎም በአባላት መካከል ያለው ግንኙነት እንዲሁም በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ልዩ ልዩ አደረጃጀቶች ግንኙነትና ልዩነቶች የአፈታት ዘዴዎች ምን መምሰል ይኖርባቸዋል? የሚለውን በዚህ የፓርቲ ፕሮግራም ውስጥና አስተዳደር ነክ ጉዳዮች በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ ውስጥ ተካቷል፡፡

ምክክር ፓርቲ በየጊዜው የሚታገልበት የፖለቲካ ፕሮግራም ሀገራዊና ዓለምአቀፍ ሁኔታዎችን በማገናዘብ ከኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታዎች ጋር በማገናዘብ ችግሮችን፣ ግንዛቤዎችን፣ ቁሳዊ ዝግጅቶችን እያጠና በተግባር ሊያውላቸው የሚችለውን ፖሊሲዎች ያወጣል፤ እርምጃዎችንም ይወስዳል፡፡

    በአገራችን ኢትዮጵያ ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር እንዲኖር የዲሞክራሲ እሴቶች ተግባራዊ እንዲደረግ ከሀገራችንም አልፎ በአፍሪካ አህጉር ተምሳሌት የሆነ ነፃ፣ ገለልተኛና ተአማኒ ምርጫ እንዲኖር የተቋማት መገንባትና ከመንግስት ጥገኝነነት የወጣ ምርጫ ቦርድ እንዲቋቋም ግዴታ የሚያስቀምጥ የፖለቲካ ፓርቲ ነው፡፡ ይህን ለማሳካት ዜጎች ነፃና ገለልተኛ የሆኑና በሕዝብ ቀጥተኛ ምርጫ የሚመረጡ 7 አባላት ያሉት የቦርድ አባላትን ያስመርጣል፡፡ የምርጫ ቦርድ ጽ/ቤቶች በሁሉም ምርጫ ጽ/ቤቶች በቋሚነት የሚያገለግሉ ይሆናሉ፡፡

በዚህ የፓርቲ ፕሮግራም ውስጥ የተካተቱት በዋና ዋና የፕሮግራም አቋሞች ላይ የተመሰረቱትን በጥቂቱ ተቀምጠዋል፡፡ የፓርቲው ፖሊሲዎች፣ የሚመራበት ማኒፌስቶና ሌሎች ዝርዝር ሁኔታዎች በፓርቲው የፖሊሲ አጥኚ ቡድን የተዘጋጁ ሲሆን እንደወቅቱ ሁኔታና እንደሀገራችን ተጨባጭ ሁኔታ የሚዳብሩ ይሆናል፡፡

    ሀገራችን ኢትዮጵያ መንግሥት የሚባለውን ማህበራዊ ተቋም በቀደምትነት ከመሠረቱትና በሥልጣኔም ከታወቁት ሀገሮች መሃል የምትመደብ ብትሆንም በረጅም ዘመናት ታሪኳ አምባገነን ሥርዓቶችና ገዥዎች የተፈራረቁባት፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችም ያልተከበሩባትና የመልካም አስተዳደርን በረከት ተነፍጋ የኖረች ሀገር ነች፡፡ የተፈጥሮና ሰብዓዊ ሀብቱ እያለ በሁሉም ዓይነት ድህነት ውስጥ ተዘፍቃ የምትገኘው ኢትዮጵያ ሕዝቧ ለረሃብና ለልዩ ልዩ ጉስቁልና በመጋለጡ በእርዳታና ብድር ላይ ወድቃለች፡፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብት የታደለችና ከምድሯ ስፋትም አብዛኛው ለግብርና ልማት ሊውል የሚችል ሀገር እንደሆነች ይታቃወቃል፡፡  በከርሰ ምድሯ የያዘችው እምቅ ሀብት ገና በውል የታወቀ አለመሆኑም ግልጽ ነው፡፡  ከሕዝቧም ገሚሱ ያህሉ በአምራችነት ሊሰማራ የሚችል ሲሆን ከዚህም ውስጥ እጅግ የሚልቀው ቁጥር ኋላቀር በሆነ ሥልተ ምርት ውስጥ የተጠመደ እና ለራሱ የሚበቃ ቀለብ ማምረት የጀመረበት ደረጃ ላይ ነው፡፡ አሁን ባለንበት ደረጃ አርሶ አደሩ የተሻለ ዘር እና ማዳበሪ እየተጠቀመ የተሻለ ምርት እያመረተ ይገኛል፡፡

    ኢትዮጵያ በርካታ እንስሳት፣ አዕዋፋት፣ አዝርዕትና የልዩ ልዩ ተክሎች ምንጭ ብትሆንም ያላትን የተፈጥሮና ሰብዓዊ ሀብቶች ለመጠበቅ፣ ለማልማትና ለመጠቀም የነበራትና ያላት አቅም ውሱን እንደነበረና እንደሆነም እሙን ይመስለናል፡፡

   የድህነታችን ዓይነተኛ ምንጭ በዘመናዊ ተክኖሎጂ የተማረ የሰው ኃይል

አለመኖር፣ የፖለቲካ ሥርዓቱ አወቃቀር ችግርና የመልካም አስተዳደር ዕጦት መሆኑን መገንዘብ ለምናደርገው ትግል አንዱና ዋነኛ ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያዊያን የቅኝ ገዥዎችን ሕልም ያመከኑ፣ በአፍሪካ አህጉር ለነፃነቱና ለሀገሩ ሉዓላዊነት ቀናኢ የሆነ ሕዝብ መኖሩን በተጋድሎአቸው ያስመሰከሩ አፍሪካዊ ጀግኖች ልጆች ነን፡፡  የቀደሙ አባቶቻችን የተውልንን ለነፃነት የመታገልን ውርስና ቅርስ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቻችን መከበር፣ ለእኩልነትና ፍትሕ መረጋገጥ፣ ለመልካም አስተዳደር መስፈን ወዘተ ልናውለው ጊዜው የግድ ይለናል፡፡  በዚሁ መንፈስና እምነት ነፃነት የትግል ውጤት እንጂ በስጦታ የማይገኝ መሆኑን ፣

ከሁሉም ይበልጥ አሁን የምንገኝበት ታሪካዊ ሁኔታ ሕዝባችን ለዘመናት ተነፍጎት የኖረውን መብቱን ለማስከበር፣ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ለመገንባት፣ አስተማማኝ ሠላም ለማስፈንና ከድህነት አረንቋ ለመውጣት ያለውን ፍላጎትና ምኞት በቁርጠኛነት ያረጋገጠበት ወቅት በመሆኑ የሕዝብንና የሀገርን ጥቅም ከሁሉ በማስቀደም አራምዳለሁ፣ እውን እንዲሆንም አታገላለሁ፣ የሚል ዴሞክራሲያዊ ኃይል ሁሉ ያለ ኃይሉን በአንድ በማሰባሰብ የተቀናጀና የተባበረ ትግል በማድረግ በምርጫ ካርድ ስርዓቱን መቀየር እንችላለን ብለን እናምናለን፡፡  ሕዝብ በሚሰጠን ድምጽ ለኢትዮጵያ ሕዝብም እውነተኛ ፍላጎት ታማኝና ታዛዥ መሆናችንን እናረጋግጥበታለን፡፡

 

 1. የፓርቲው ራዕይ፣ ተልዕኮና ዓላማዎች

2.1 ራዕይ

የምክክር ፓርቲ ራዕይ  የሕግ የበላይነት የተረጋገጠባት፣ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያላንዳች ገደብ የተከበሩባት፣ ድህነት ተወግዶ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ብልፅግናና ሰብዓዊ ልማት የሠፈነባትና የዜጎችዋ ሁሉ መኩሪያና መከበሪያ የሆነች ኢትዮጵያን መገንባትና የኢትዮጵያ አንድነት የተጠበቀባት፣ የብሔርና የጎሳ አደረጃጀቶች ለሀገር አንድነት ስጋት መሆኑን በመገንዘብ የአንድነት ሀይሉ እንዲጠናከር በማድረግ ነው፡፡

 

  1. ተልዕኮ

የፓርቲያችን ዐብይ ተልዕኮ ራዕያችንን ማሳካት ቢሆንም በተለይ ግን በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲሠፍንና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ ዋስትና ሊሰጥ የሚችል በሕዝብ ለሕዝብ የቆመ መንግሥት ይመሠረት ዘንድ የሕብረተሰቡን ፖለቲካዊና ማሕበራዊ እንቅስቃሴ በመምራት ለድል ማብቃትና የሕብረተሰቡን ሠላምና የኑሮ ዋስትና ማረጋገጥ ይሆናል፡፡

 

  1. ዓላማዎች

የፓርቲያችን ዐብይ ዓላማ ራዕዩን እውን ለማድረግ የሚረዳው ተልዕኮ ወደ ተግባር መለወጥ ሲሆን ጠቅለል ያሉ ፖለቲካዊ፣ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዓላማዎች በሚከተለው ሁኔታ ቀርበዋል፡-

   1. በኢትዮጵያ የዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች የተከበረበት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እንዲመሠረት ማድረግ፡፡

   2. የኢትዮጵያን ዜጎች እኩልነት፣ ሀገራዊ አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፡፡

   3. ሀገሪቱን ካለችበት የድህነት አዘቅት ለማውጣት በሚደረገው ጥረት የሚደነቅ ቢሆንም ልማትንና ማህበራዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ የሚረዳ ኢኮኖሚያዊ ሥርዓት መገንባት፡፡

   4. ማሕበራዊ ደህንነትን፣ ሠላምን፣ መከባበርንና አብሮነትን፣ ሠርቶ የመኖር ዋስትናን የሚያረጋግጥ ማሕበራዊ ሥርዓት መገንባት፡፡

   5. ግልጽነትና ተጠያቂነት የሠፈነበት አስተዳደራዊ ሥርዓትን መፍጠር፤  በመንግሥት ተቋማትም ሆነ በሕብረተሰቡ ውስጥ መልካም አስተዳደርን ማጎልበት፡፡

   6. የሴቶችን፣ የሕፃናትን፣ የአረጋዊያንን፣ የአካል ጉዳተኞችንና ማህበራዊ መገለል የሚደረግባቸውን የሕብረተሰቡ አካላትና አባላትን መብቶች ማስከበርና ተገቢ እንክብካቤም ማድረግ፡፡

   7. ከዓለም ሕብረተሰብ ጋር በመተባበር፣ በመከባበርና በእኩልነት ላይ የተመሠረተ የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም በሚያስከብር መርህ ላይ የተመሠረተ ጤናማና ሠላማዊ ግነኙነት መገንባት፡፡

   8. የኢትዮጵያ ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች የብሔራዊ እርቅ በማድረግ ገንቢ ሚና እንዲጫወቱ ትግል ማድረግ፣፣

3. የፓርቲው ርዕዮተ ዓለም

ምክክር ፓርቲ በሶሻል ዲሞክራሲ መሠረታዊ መርሆችና ፍልስፍና ይመራል፡፡  አመለካከቶች መካከል ጠቃሚ የሆኑ እሴቶችንም ለሕዝብና ለሀገር ይጠቅማሉ የምንላቸውን ያካትታል፡፡

 

3.1 የፖለቲካ መርሆዎች

3.1.1 የፖለቲካ ሥርዓቱ አደረጃጀት

ሀ. የፖለቲካ ሥርዓቱ ሕገ መንግሥታዊ ይሆናል፡፡

ለ. የመንግሥት የፖለቲካ ሥልጣን የሚያዘው በነፃ ውድድርና በምርጫ ካርድ ከሕዝብ ፈቃድ የሚመነጭና በሕግ የበላይነት የሚመራ ይሆናል፡፡

ሐ. ማንኛውም የፖለቲካ ጥያቄዎች በዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መርሆዎች እና በውይይት እንዲፈቱ ይደረጋል፡፡ በሕዝቦች መካከል አለመግባባት የሚፈጥሩ ጉዳዮች ካሉ የሕዝበ ውሣኔ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

መ. የዜጎች ሁሉ የመምረጥና የመመረጥ መብት የተከበረ ይሆናል፡፡

ሠ. የፖለቲካ ሥርዓቱ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ይሆናል፡፡

ረ. የኢትዮጵያ የግዛት አንድነት ሊገሰስ የማይችልና የማይጣስ መሆኑን የሚያረጋግጥ አቋም ይኖረናል፡፡ በኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ውስጥ የሚገኝ ማንኛውም የሀገሪቱ ዜጎች የተፈጥሮ ሀብቱ የጋራ ተጠቃሚ መሆን አለባቸው ብሎ ምክክር ፓርቲ ያምናል፡፡

ሰ. በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ዜጎች ምንም አይነት ገደብ ሳይጣልባቸው መንቀሳቀስ፣ መሥራት፣ ሀብት ማፍራት እንዲችሉ ተደርጎ በሕገ-መንግስቱ ውስጥ ይካተታል፡፡

3.1.2 የፌዴራል መንግስት አወቃቀር

ሀ. ምክክር ፓርቲ አሁን ያለው ሕገ-መንግስት ሙሉ ለሙሉ በመላው ሕዝብ ተሳትፎ ሊቀየር ይገባል ብሎ ያምናል፡፡ ሕገ-መንግስቱ የግለሰብ መብትን ቅድሚያ የሚያስከብር ሆኖ የሚቀረፅና የቡድን እና የወል መብቶች ከግለሰብ መብቶች የሚመነጩ በመሆናቸው ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

ለ. መንግሥታዊ ስልጣኑ በፕሬዝዳንታዊ ስልጣን ላይ የተመሠረተ ሆኖ በመላው ህዝብ ቀጥተኛ ምርጫ ከጠቅላላ መራጩ 50 ሲደመር 1 የተመረጠ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት የሀገሪቱ መሪ ይሆናል፡፡የመንግሥቱን አስፈጻሚ አካል በበላይነት ይመራል፡፡ ለአንድ ጊዜ የተመረጠው ፕሬዝዳንት ሀገሪቱን ለ5 ዓመት ይመራል፣ ይህ ፕሬዝዳንት ከ2 ጊዜ በላይ በፕሬዝዳንታዊ ምርጫ አይወዳደርም፡፡ (አይመረጥም)፡፡

ሐ. በፕሬዝዳንትነት የሚወዳደረው ሰው በመጀመሪያ ዙር ውድድር ከ 50 ሲደመር 1 በታች የመራጮች ድምፅ ካገኘ ከተወዳዳሪዎች መካከል አንደኛ እና ሁለተኛ ሆነው የመራጮችን ድምፅ ያገኙ እጩዎች ለሁለተኛ ጊዜ ተወዳድረው ያሸነፈው ሰው የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ይሆናል፡፡

መ. በፕሬዝዳንቱ ስር የሚቋቋመው የሕግ አስፈጻሚው አካልና ሕግ በሚያወጡት ሁለት ምክር ቤቶች እንዲሁም ሕግ በሚተረጉሙት 3ኛ አካል መካከል አንዱ በሌላው ሥራ ላይ ጣልቃ ሳይገባ ተግባራቸውን በነጻነት ያከናውናሉ፡፡

ሠ. የክፍለ ሀገራት አስተዳደር አደረጃጀት የህዝቦችን ታሪካዊና ባህላዊ ትስስርን፣ ቋንቋን፣ የሕዝብን አሰፋፈር፣ መልክዓ ምድርን፣ የአስተዳደርና የልማት አመቺነት እንደየአካባቢው ሁኔታ እነዚህ መስፈርቶች በአጠቃላይ ወይም በተናጠል በመጠቀም በክፍለ ሀገራት ስያሜ ይከለላሉ፡፡

ረ. ምክክር ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ (ምክክር ፓርቲ) በኢትዮጵያ አንድነት ላይ በምንም መልኩ አይደራደርም፡፡ ፓርቲው የመንግስት ስልጣን በተናጠል ወይም በጥምረት ከያዘ የኢትዮጵያን አንድነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ አደረጃጀቶችን የሕግ ማእቀፍ በማውጣት እና ከሕዝብ ጋር በመምከር ይወስናል፡፡ ይህ ማለት ማንኛውም ሰው፣ ቡድን የፖለቲካ ጥያቄ ያላቸው ወገኖች በአንድነት ኃይሉ ውስጥ ገብተው በጋራ የመደራጀትና ሐሳባቸውን በነፃነት የማቅረብ መብታቸውን ይጠብቃል፡፡

ሰ. በአስፈጻሚ አካል ውስጥ የሚሾም የፖለቲካ ሹመኛ ሰው ሀላፊነቱ ተለይቶ በሕግ እንዲቀመጥ ይደረጋል፡፡ የሥራ ኃላፊነቱም በሀገሪቱ ፕሬዝዳንት አቅርቢነት በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሲፀድቅና በሥራ ላይ ሲውል ተግባራዊ ይሆናል፣ በሲቪል ሰርቪስ ሠራተኛ እና ሲቪል ሰርቪሱን የሚመራው አካል ከፖለቲካ ገለልተኛ የሆነ በችሎታና በብቃቱ ላይ የተመሠረተ አመራር ይመደባል፡፡

 

3.1.3 ሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች

ሀ. በተባበሩት መንግስታት የፀደቁ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌዎች ላይ የሰፈሩ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ ኢኮኖሚያዊና የሲቪል መብቶች እንዲሁም የአፍሪካ ህብረት የሰብዓዊ መብቶች ውሎችና ስምምነቶች ወዘተ ሁሉ የሀገሪቱ ህግ አካል ይሆናሉ፡፡

ለ. የዜጎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር፣ የመሥራት፣ በፈለጉበት ቦታ የመሥራትና የመኖር፣ በግልና በጋራ ንብረት የማፍራት፣ የመጠቀም፣ የመሸጥ፣ የመለወጥ፣ የማውረስ መብቶች ያለገደብ ይከበራሉ፡፡

ሐ. የዜጎች ሃሳብን በነፃ የመግለፅ፣ የመደራጀት፣ የመሰብሰብ፣ የድጋፍ ወይም  የተቃውሞ ሰልፍ የማድረግ፣ ስራ የማቆም ወዘተ መብቶች ይከበራሉ፡፡

መ. ዜጎች በአእምሮም ሆነ በአካል ላይ የሚደረጉ ጥቃቶችና መሰቃየቶች እንዳይደርስባቸው ይጠበቃሉ፡፡  ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ አይታሠሩም፣ አይመረመሩም፣ ቤታቸው፣ ሰውነታቸውና ንብረታቸውም አይፈተሽም፡፡

ሠ. በሕገ-መንግስት ላይ እውቅና የተሰጣቸውን ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ሳይሸራረፉ ያስከብራሉ፡፡

3.1.4 የዜጎች እኩልነት

ኢትዮጵያ በርካታ ቋንቋ ተናጋሪ ያሉባት ሀገር እንደመሆንዋ መጠን ምንም ዓይነት አድልዎ ሳይፈፀምባቸው እኩልነታቸው ተረጋግጦ የሚኖሩባት ሀገር ትሆናለች፡፡

ሀ. ዜጎች በቋንቋቸው የመጠቀምና ባህሎቻቸውን የማበልፀግ መብቶቻቸው ይከበራሉ፡፡

ለ.  በአንቀጽ 3.1.2 (ሠ) ስለ ክ/ሀገር አስተዳደር አደረጃጀት የተገለፀው እንደተጠበቀ ሆኖ በአንድ ክ/ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች እራሳቸውን የማስተዳደርና አካባቢያቸውን የማልማት መብታቸው ይረጋገጣል፡፡

ሐ.   በቁጥር በዛ ካሉ ዜጎች ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ አናሳ ብሔረሰቦች (demographic and political minorities) ማናቸውም መብቶቻቸው ባሉበት አካባቢ ይከበራሉ፡፡

መ.  የልዩ ልዩ ብሔረሰብ አባላት የሆኑ ዜጎች በይበልጥ እንዲቀራረቡና የጋራ በሆኑ ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ በህብረት እንዲቆሙና ኢትዮጵያዊነትን እንዲያጎለብቱ ተገቢው ድጋፍ ይሰጣል፡፡

 

3.1.5 የፆታ እኩልነት

    በሀገራችን የሴቶች ተዋፅኦን ያላማከለ ፖሊሲዎች ሲወጡ ይታያል፡፡ በተለይ ሴቶች በፖለቲካው ያላቸው ተሳትፎና የአመራርነት ቦታ ዝቅተኛ ነው፡፡ በመሆኑም ምክክር ፓርቲ፡-

ሀ.  በሀገራችን ለዘመናት ሰፍኖ የኖረውና በፆታዎች መካከል ያለ የተዛባ ግንኙነት በማስተካከል የፆታዎችን እኩልነት ያረጋግጣል፡፡

ለ.  የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ ይበልጥ እንዲጎለብት ይደረጋል፡፡

ሐ. የሴቶችን አቅም በመገንባት የውሳኔ ሰጪነት ኃላፊነቶች እንዲረጋገጡ ሁሉ አቀፍ ድጋፍ ይደረግላቸዋል፡፡ የወጣቶች፣ የአካል ጉዳተኞች፣ የሴቶች የፖለቲካ አስተዋፅኦ ዝርዝሩ በማኒፌስቶ ተካቷል፡

3.1.6 የሃይማኖት ነፃነትና እኩልነት

ሀ.  ማንኛው ዜጋ የፈለገውን ሃይማኖት የመከተል ነፃነት ይኖረዋል፡፡

ለ.  በኢትዮጵያ ያሉ ሃይማኖቶች ሁሉ እኩል ናቸው፡፡  መንግስትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡  አንዱ በሌላው ተግባር ጣልቃ እንዲገባ አይፈቀድም፡፡

3.1.7 የብዙሃን መገናኛ

ሀ.  ዜጎች ሃሳባቸውን ያለምንም ገደብ የመግለጽ መብት እንዳላቸው ሁሉ መረጃ የማግኘት መብታቸውም የተከበረ ይሆናል፡፡

ለ.   የመገናኛ ብዙሃን ተግባራቸውን በነፃነት እንዲያከናውኑ ይደረጋል፡፡

ሐ.  በመንግስትም ሆነ በግል ይዞታ ስር ያሉ የመገናኛ ብዙሃን አስፈላጊ የሆኑ መረጃዎች ለማግኘትም ሆነ ለማሰራጨት ነፃነት ይኖራቸዋል፡፡

መ.  የመንግሥት መገናኛ ብዙሃን ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር አይወግኑም፤ በነዚህ አካላት ተጽዕኖም አይደረግባቸውም፣ ስለሆነም ይህንን ለማረጋገጥ ከፖለቲካ ፓርቲ ነፃ በሆኑ አባላት ይተዳደራሉ፡፡

ሠ.  ማህበራዊ ኑሮን፣ የሀገርን አንድነትና ሉዓላዊነት፣ የህዝቦችን መልካም ግንኙነት፣ የግለሰቦችንና ማህበራዊ አካላትን ነፃነቶች እንዲሁም የመገናኛ ብዙሃኑን ነፃነት ለመጠበቅ ካልሆነ በስተቀር ምንም ዓይነት የህግ ገደብ አይጣልባቸውም፡፡

3.2 የኢኮኖሚ መርሆዎች

3.2.1 አጠቃላይ

    ምክክር ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ በሶሻል ዴሞክራሲ ፍልስፍና መርህ መሠረት ዜጎች ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ሊኖራቸው ይገባል ብሎ ያምናል፡፡ ኢኮኖሚያዊና ፍትሐዊ ተጠቃሚነታቸውን የሚያረጋግጥ ፖሊሲዎችን በኢኮኖሚ ፕሮግራም ውስጥ ያረጋግጣል፡፡

ሀ.  ለሀገሪቱ ልማትና ብልፅግና ትኩረት የሚሰጥ፣ የመላውን ህብረተሰብ የኑሮ ደረጃና ማህበራዊ ህይወት የሚያሻሽል ዘላቂና ሁለንተናዊ የእድገትና የልማት ስትራቴጂ ተቀርፆ ተግባራዊ ይደረጋል፡፡ ለዜጎች ሥራ መፍጠር የኢኮኖሚው ፖሊሲ ዋነኛ መርህ ይሆናል፡፡

ለ.  በሶሻል ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ላይ የተመሰረተ የገበያ የኢኮኖሚ መርህ ፖሊሲ ተነድፎ ሥራ ላይ እንዲውል ይደረጋል፡፡

ሐ. የአጠቃላይ የኢኮኖሚ እድገት መሠረት የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ ስለዚህም የኢኮኖሚው ፖሊሲ ትኩረት ሀገራዊ የኢኮኖሚ ሃይሎችን መፍጠርና ማጠናከር ይሆናል፡፡ የአገርን ኢኮኖሚ ለማሳደግ አስፈላጊ ስለሆኑ የውጭ ባለሀብቶችና እርዳታ ሰጪዎች የሶሻል ዲሞክራሲ ርዕዮተ ዓለም ባልተጻረረ መልኩ ይበረታታሉ፡፡

መ. የኢትዮጵያ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት ሀገራዊ መሠረት ሊኖረው የሚችለው ከፖለቲካ ፓርቲ ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆነ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንዱስትሪዎች እድገት ሲበረታታ በመሆኑ ለዚህ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡

ሠ. የዜጎች ሀብት የማፍራት፣ የመያዝ፣ የመጠቀም፣ በህጋዊ መንገድ ለሌላ ወገን ለማስተላለፍ ወዘተ መብቶች ይከበራሉ፡፡

ረ. የአካል ጉዳተኞች በኢኮኖሚው ውስጥ ሙሉ ተሳታፊና ተጠቃሚ የሚሆኑበት ስልት ይቀየሳል፡፡

ሰ. የልማት ስትራቴጂውም ሆነ የኢኮኖሚ ፖሊሲው የተፈጥሮ ሀብትንና አካባቢን ከመንከባከብና በአግባቡ ከመጠቀም መርህ ጋር የተቆራኙ ይሆናሉ፡፡

3.2.2 የኢኮኖሚ ዘርፎች

ሀ. የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ከፍተኛ እድገት እንዲያስመዘግብ መዋቅራዊ ለውጥ ያስፈልገዋል፡፡  ለዚህም የግብርናውን ዘርፍ ከማዳበር ጋር አብሮ ከግብርና ውጪ ያሉ እንደማዕድን፣ ኢንዱስትሪ፣ አገልግሎት የመሳሰሉ የኢኮኖሚ ዘርፎች ልማት ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ አገራዊ ኢኮኖሚውን ከግብርና ጥገኝነት ለማላቀቅ ከፍተኛ ጥረት ይደረጋል፡፡

ለ.  የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የእድገት አቅጣጫ በግብርና ላይ ብቻ ሳይሆን እንዳካባቢው አንፃራዊ ጠቀሜታና አቅም እየተመዘነ በሌሎች ዘርፎች ላይም የሚመሠረት ይሆናል፡፡

ሐ.  በሁሉም ዘርፎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂና በሰለጠነ የሰው ኃይል የመጠቀም አቅም እንዲጎለብት ይደረጋል፡፡

መ. መሬት እንዳስፈላጊነቱ በግል፣ በወል ወይም በመንግሥት ባለቤትነት ስር ሆኖ እንደማንኛውም ንብረት በልዩ ልዩ መንገድ በኢኮኖሚ ዝውውር ውስጥ እንዲገባ ይደረጋል፡፡

ሠ. ከዚህ በፊት በልማት ግንባታዎች ትኩረት ያላገኙ የህብረተሰብ ክፍሎችና  አካባቢዎች ለኢኮኖሚ ግንባታ ቅድሚያ ይሰጣል፡፡

3.2.3 የመንግስት ሚና

ሀ.  ኢኮኖሚን የማሳደግና አገርን የማልማት ኃላፊነት የግሉ ክፍል ቢሆንም መንግስት ለሀገሪቱ እድገትና ልማት አንዲሁም ደህንነት አስፈላጊ ሆነው ለሚገኙ የግሉ ዘርፍ በአቅም ማነስ ወይም በአዋጭነት የተነሳ የማይሳተፍባቸውንና ስትራተጂካዊ ጠቀሜታ ባላቸው በራሱ ወይም ከሌሎች የኢኮኖሚ አልሚ ኃይሎች ጋር በመተባበር የኢኮኖሚ ዘርፎች ሁሉ ይሳተፋል፡፡

ለ.  እንዳስፈላጊነቱ የግሉን ዘርፍ በሚያሳተፍ ሁኔታ መንግስት ትላልቅ መሠረተ ልማት ግንባታዎችን ያካሄዳል፡፡

3.2.4 የውጭ ባለሀብቶች ሚና

ሀ.  ከሀገሪቱ ጥቅሞች ጋር በማይጋጭ ሁኔታ የውጭ ባለሀብቶች በኢኮኖሚው እንቅስቃሴ እንዲሳተፉ ይበረታታሉ፡፡

ለ.  ዘመናዊ ቴክኖሎጂን፣ የሥራ ልምድንና ዕውቀትን በስፋት ወደ ሀገር ማስገባት ለሚችሉ የውጭ ባለሀብቶች ልዩ ድጋፍ ይደረጋል፡፡  ለዚህም የግብርናውን ዘርፍ ከማዳበር ጋር አብሮ ከግብርና ውጭ ያሉ እንደማዕድን፣ ኢንዱስትሪና አገልግሎት የመሳሰሉ ዘርፎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ አገራዊ ኢኮኖሚውን ከግብርና ጥገኝነት ለማላቀቅ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል፡፡

ሐ. የውጭ ባለሀብቶች የሚሠማሩበትን ሥራ ሁሉ በኢትዮጵያዊያን ዜጎች እንዲሸፈን ያደርጋሉ፡፡ ሆኖም ግን ኢትዮጵያውያን ተገቢው ልምድና ዕውቀት በሌላቸው መስኮች የውጭ ዜጎችን ማሠራት ቢችሉም በሂደት ግን ኢትዮጵያዊያንን በማሠልጠን እንዲተኩ የማድረግ ግዴታ ይኖርባቸዋል፡፡

 

3.3 የማሕበራዊ መርሆዎች

3.3.1 አጠቃላይ

ሀ.  ሀገራዊ ስሜቱ የጎለበተ፣ በብሔራዊ ማንነቱ የሚኮራ፣ በአካልም ሆነ በአእምሮ የዳበረና የሥራን ክቡርነት የተገነዘበ ብርቱና ጤናማ ዜጋ ለመፍጠር የሚያስችሉ የትምህርት፣ የጤናና የባሕል ፖሊሲዎች ይቀረፃሉ፡፡

ለ.  ዜጎች ያለምንም አድልዎ በአገራቸው ሁለንተናዊ ልማት ውስጥ እኩል የመሳተፍ መብት ይኖራቸዋል፡፡

ሐ. ማሕበራዊ ደህንነት፣ ሠላም፣ መከባበር፣ አብሮነትና ሠርቶ የመኖር ዋስትና ይረጋገጣል፡፡

መ. የዜግነት ክብርን፣ ሠላም፣ ማሕበራዊ ሕይወትንና የእምነት ነፃነትን የሚያረጋግጥ ማሕበራዊ ሥርዓት ይገነባል፡፡

ሠ. የፌዴራል የሥራ ቋንቋ ሆኖ የሚያገለግል ሁለት ቋንቋ ይኖራል፡፡

 

 3.3.2 ትምህርት

ሀ.  ተግባር ተኮርና ጥራት ያለው ትምህርት ለዜጎች ይሰጣል፡፡ ሳይንስና ቴክኖሎጂ እንዲሁም ሥነ ጥበባት ይበረታታሉ፡፡  እንዲሁም በተለይ የፈጠራ ችሎታ ላላቸው ዜጎች ልዩ እንክብካቤ ይደረጋል፡፡

ለ.  ዜጎች እስክ ሁለተኛ ደረጃ ፍጻሜ ያለውን በመንግሥት ት/ቤት ትምህርት በነፃ የመማር መበታቸው ይረጋገጣል፡፡ ከዚያ በላይ ያለውን ትምህርት እንደአስፈላጊነቱ ተማሪዎች ከወጭው እንዲጋሩ ይደረጋል፡፡

ሐ. በትምህርት ሥራ የግል ባለሀብቶችም በሁሉም ደረጃ አንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡ የትምህትን ጥራት የመጠበቅ ኃላፊነት የመንግሥት ይሆናል፡፡

መ.  መንግሥታዊ  ያልሆኑ ድርጅቶችም በትምህርትና በሥልጠና መስክ እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡

ሠ. አካል ጉዳተኞችና ሴቶች እንዲሁም ማሕብራዊ መገለል የሚደረግባቸው ማሕበረሰቦች የትምህርት ተሳትፎአቸውን እንዲያጎለብቱ ልዩ ትኩረት ይሰጣል፡፡

ረ. የትምህርትን ሥራ አተገባበርና የሥርዓተ ትምህርቱን አደረጃጀት ግልጽ የሚያደርግ የትምህርት ሕግና ፖሊሲ በሕብረተሰቡ ተሳትፎ ይቀረጻል፡፡

ሠ. በመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እርከን ላይ ሕፃናት አፍ በፈቱበት ቋንቋ ወይም ወላጆቻቸው በመረጡት እንዲማሩ እድል ይሰጣቸዋል፡፡

ሰ.  ማንኛውም ቤተሰብ ልጁን ወይንም በሥሩ የሚገኙ ማንኛውም ህፃናትን እስከ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የማስተማር ግዴታ አለበት፡፡

ሸ. ፊደል ያልቆጠረ ማንኛውም የህብረተሰብ ክፍል መሰረተ ትምህርት የመማር ግዴታ አለበት፡፡

3.3.3 ጤና

    ዜጎች የጤና እና ሁለገብ የማኅበራዊ ዋስትና ማግኘት አለባቸው፡፡ ዜጎች የማኅበራዊ ዋስትናውን ተጠቃሚ እንዲሆኑ ተመጣጣኝ መዋጮ እንዲያደርጉ እናበረታታለን፣ የማኅበራዊ ዋስትና የሚያስፈልጋቸው ዜጎች ከኢኮኖሚ ዕድገት ደረጃ ጋር እየተገናዘበ ማስተካከያ የሚደረግበት ሲሆን አሁን በሥራ ላይ ያለው የማኅበራዊ ዋስትና ከሕዝብ ጋር በመምከር ማሻሻያ ይደረግበታል፡፡

ሀ.  የጤና አጠባበቅ ሥርዓት በሽታን መከላከል መሠረት ያደረገ ይሆናል፡፡ ለዚህ ደግሞ የግልና የአካባቢን ንጽሕና መጠበቅ ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋልና ተግቢውን ስልት ይቀይሳል፡፡ በወረርሺኝ መልክ በመሰራጨት ላይ ያሉ  እንደ ሳምባ ነቀርሳ፣ ወባና ኤች.አይ.ቪ. ቀሳፊ በሽታዎችን ለመግታት ተግባራዊና ትምህርታዊ እንቅስቃሴ ይደረጋል፡፡ ለእናቶችና ሕፃናት ጤና የተለየ እንክብካቤ ይደረጋል፡፡

ለ.  ዜጎች በያሉበት ተደራሽ የሆነ የጤና አገልግሎትን እንዲያገኙ ይደረጋል፤ መድኃኒት በርካሽ እንዲያገኙ ይደረጋል፤ የመጀመሪያ ደረጃ ሕክምና የሚሰጡ ባለሙያዎች በቅርብ ርቀት እንዲያገኙ ይደረጋል፡፡

ሐ.  በጤናው ዘርፍ መንግሥት ወሳኝ ድርሻ ቢኖረውም የግል ባለሀብቶችም በሁሉም ደረጃ እንዲሳተፉ ይደረጋል፡፡

መ. ከፍተኛ ወጪ ዜጎች አውጥተው ውጭ አገር ሔደው እንዳይታከሙ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችና የውጭ ዜጎች  በጤና ዘርፍ እንዲሳተፉ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፡፡

ሠ. ከሶሻል ዲሞክራሲ አስተሳሰብ ጋር ያልተፃረረ የግል ባለሀብቶች የጤና አገልግሎት በተመጣጣኝ ዋጋ በየአካባቢው ተደራሽ እንዲሆን መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል፡፡

 

3.3.4 ማህበራዊ ደህንነትና የሥራ ዋስትና

ሀ.  የዜጎች ሠርቶ የመኖር መብት የተከበረ ነው፡፡ ሠራተኛውና ሥራ ክቡር ናቸው፡፡ የዜጎች የሥነ-ምግባርና የስብዕና ዋና መመዘኛ ሥራ ይሆናል፡፡ ስለዚህም የሠራተኛነት ባሕል እንዲዳብር አስፈላጊው ጥረት ይደረጋል፡፡

ለ.  ሠራተኞች በማህበር ተደራጅተው ጥቅሞቻቸውን እንዲያስከብሩና ሀገራቸውንም እንዲጠቅሙ ሁኔታዎች ይመቻቻሉ፡፡

ሐ.  የበጎ አድራጎትና የልማት ተራድኦ ማህበራት፣ ራስ አገዝ ህዝባዊ ማህበራት፣ የሙያ ማህበራት ተፈጥረው በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ይደረጋል፡፡

መ. መንግሥት የአካል ጉዳተኞችንና  ጡረተኞችን ይንከባከባል፡፡ወቅቱን ያገናዘበ ድጋፍ ያደርጋል፡፡

3.3.5 ባሕልና ባሕላዊ ዕሴቶች

    ሀገራችን ኢትዮጵያ እምቅ የቱሪስት ሀብት ለመጠቀም እንዲሁም የአለም ዋነኛ የቱሪስት መዳረሻ ለማድረግ ዝርዝር ፖሊሲዎችን ምክክር ፓርቲ ይቀርፃል፡፡ የህዝቦችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የፓርኮችን ልማት እና ለቅርሶች የሚደረገው ጥበቃ ዘመናዊ አደረጃጀት እንዲኖረው ሥርዓት ይዘረጋል፡፡

ሀ.  የሀገሪቱ ልዩ ልዩ ባህሎችና ባህላዊ ቅርሶች በሕግና በእንክብካቤ ይጠበቃሉ፡፡

ለ.  ባሕላዊ ቅርሶችና ዕሴቶች ኢትዮጵያውያንን ይበልጥ እንዲያቀራርቡና የጋራ ብሔራዊ ስሜታቸውን እንዲያጎለብቱ አስፈላጊው ጥረት ይደረጋል፡፡

3.4 ፍትሕ

ሀ.  ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በሕግ ፊት እኩል ናቸው፡፡ ማንኛውም ግለሰብ ሆነ ድርጀት ከሕግ በላይ ሊሆን አይችልም፡፡

ለ.  ኢትዮጵያዊያን ሁሉ በዜግነት አንድነት እኩል በመሆናቸው በትውልድ፣ በሀብት፣ በሃይማኖት፣ በጎሳ፣ በቋንቋ፣ በጾታ፣ በፖለቲካ፣ በእምነት ወዘተ ምክንያት ልዩነት ሳይደረግባቸው በተሟላና ፍትሐዊ በሆነ ሥርዓት ውስጥ የመኖር መብታቸው ይከበራል፡፡

ሐ. ዜጎች በሚኖሩበት አካባቢ ሁሉ ኢኮኖሚያዊ፣ ማሕበራዋና ፖለቲካዊ ፍትሕ የተረጋገጠበት ሕይወት እንዲኖራቸው ይደረጋል፡፡

 

3.5 ስፖርትና ኪነ ጥበብ

ዜጎች በአካልና በመንፈስ ዳብረው ጠንካራ ዜጎች እንዲሆኑ ስፖርትና ኪነ ጥበብ ትኩረት ይሰጣቸዋል፡፡ እንደ ወቅቱ ሁኔቴ ዝርዝር ፖሊሲ ወጥቶ ይተገበራል፡፡

 

3.6 የውጭ ግንኙነት፣ የመከላከያ፣ የፖሊስና የድህንነት ጉዳይ መርሆዎች

3.6.1 የውጭ ግንኙነት

    ምክክር ለአንድነትና ለዲሞክራሲ ፓርቲ ኢትዮጵያን ከሚዋስኗት ሀገሮች ጋር የሚኖረን ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ እንዲሆንና የንግድ ግንኙነታችን ከመሠረተ ልማት ጋር የተሳሰረ መሆኑ አስፈላጊ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ይህ ግንኙነት ከጥርጣሬ የፀዳ የኢኮኖሚ ግንኙነት በጋራ መልማት እጅግ ጠቃሚ መሆኑን ትምምን ይፈጥራል፡፡

ሀ. የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ የብሔራዊ ጥቅሞች ማራመጃ መሣሪያ ሲሆን ከማንኛውም አገርና መንግሥት ጋር በእኩልነት፣ በጋራ ጥቅም፣ በውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ባለመግባትና በመከባበር ላይ የተመሠረተ እንዲሆን ይደረጋል፡፡ በተለይ ከጎረቤት አገሮች ጋር ቅርበት ያለው የወዳጅነት፣ የትብብር፣ የመተጋገዝና የጋራ እድገት ግንኙነቶች እንዲፈጠሩና እንዲጓዙ ጥረት ይደረጋል፡፡

ለ. የኢትዮጵያን መሠረታዊ ጥቅሞች የማይፃረሩ ኢትዮጵያ የገባቻቸው ግዴታዎችና ዓለም አቀፍ ህጎች በሙሉ ይከበራሉ፡፡

ሐ.  በውጪ ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ መብታቸው እንዲከበርና ጥረው ግረው ያፈሩት ሀብታቸው እንዲጠበቅ አስፈላጊው ጥረት ይደረጋል፡፡

መ. በፊደል ሰ የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ ከኢትዮጵያ አብይ የውጭ ጉዳዮች በቀዳሚነት የሚታየው የሕዳሴው ግድብና የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ስለሆነ በሰላማዊና ፍትሐዊ በሆነ መንገድ እንዲረጋገጥ አለም አቀፍ የወደብ አጠቃቀምን መሠረት በማድረግ ችግሮቹን በውይይት ይፈታል፡፡

ሰ. ከኤርትራ ሕዝብና መንግስት ጋር ውይይት በማድረግ ኤርትራ ወደ እናት አገሯ እንድትመለስ ውይይት ያደርጋል፡፡

ረ. ምክክር ፓርቲ ኢትዮጵያ ያላትን ሀገራዊ ሀብቶች መሠረት በማድረግ ድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን የመጠቀም ተፈጥሮአዊ መብት ያላት በመሆኑ በወንዙ ተጠቃሚነት ላይ ከጎረቤት ሀገራት ጋር የትብብር ዘላቂ መአቀፍ እንዲኖር ይሰራል፡፡

ሰ. በምክክር ፓርቲ እምነት ከኢትዮጵያ ውጭ በተለያየ ምክንያት ተበትኖ የሚኖረው ኢትዮጵያዊ እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሀገራችንን ችግር ለመፍታትና ወደ ተሻለ ሁኔታ ለማሸጋገር በሚደረገው ጥረት ትልቅ አስተዋፅኦ ያላቸው በመሆኑ በጋራና በተናጠል ውይይት በማድረግ ትኩረት ሰጥቶ ግልፅ ፖሊሲ ያወጣል፡፡

3.6.2 መከላከያ

ሀ. ለህገ-መንግሥቱ ተገዥ የሆነ ለኢትዮጵያ ዳር ድንበርና ሉዓላዊነት መጠበቅ ለሕዝቡ ሠላምና ደህንነት መከበር የቆመ ብሔራዊ የመከላከያ ኃይልና እንደአስፈላጊነቱም የሚሊሺያ ኃይል ይኖራል፡፡

ለ. ተጠባባቂ ጦር ይደራጃል፡፡ የመከላከያ ኃይሉ በጥንቅሩ ከሁሉም የሕብረተሰቡ ክፍሎች የተውጣጣ ሆኖ በሎጂስቲክና በዘመናዊ መሣሪያ የተጠናከረ፣ የሙያ ብቃት ያለው፣ ዘመናዊና ግዳጁን ለመወጣት ዝግጁ የሆነ ሠራዊት እንዲኖረው  ይደረጋል፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.