ፓትሪያሪክና ጳጳሳት ሆይ! በጎቻችሁን ለቀበሮ ቤተክርስትያናችሁን ለእሳት ገብራችሁ ወደ እማይቀረው ዓለም ስትሄዱ የሰማዩን ዳኛ ምን ሰርተን መጣን ልትሉት ነው?

በላይነህ አባተ (abatebelai@yahoo.com)

Popesፓትሪያሪክና ጳጳሳት ሆይ! ከሁለት ዓመታት በፊት ሶስት ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን ተሰደው መኝታቸው ጪንጫ መሬት ትራሳቸው ድንጋይ ሲሆን እናንተ ትንቡክ ተሚል ፍራሻችሁ እንቅልፋቸውን ስትለጥጡ እንደከረማችሁ ይታወቃል፡፡ ከዚያም ባለፈው ጥቅምት ወር ደመወዛችሁን የሚከፍሉት ክርስቲያኖች አንገታቸው ሲቀሉና  ቤተክስቲያኖች ባለቤት እንደሌለው ጫካ ሲቃጠሉ አንድ ሁለታችሁ የይስሙላ ድስኩር ደሰኮራችሁና በሱሰኞች ተጠምዛችሁ ተመልሳችሁ ተፎቃችሁ ተንፈላሳችሁ መኖርን እንደቀጠላችሁ መለኮትም ሕዝብም ያውቀዋል፡፡

ከዚህኛው ግፍ ቀጥሎም ሮጠው ያልጠገቡ ልጃገረዶች በጭራቆች ታስረው በሚሰቃይበት ሰዓት እናንተ በታገቱት ልጃገረዶች ስለት ፍትፍታቸውን እየበላችሁና በሽንጣም መኪና እየተሽከረከራችሁ አለማችሁን መቅጨት ጀመራችሁ፡፡ ዛሬ ደግሞ ከበፊቱም የከፋ አገር በእሳት እየነደደ ክርስቲያኖች  በገጀራ ሲቀሉ፣ በጦር ሲወጉ፣ በባሩድ ሲረግፉና መጤ እየተባሉ በላያቸው ቤታቸው ሲቃጠል አፋችሁን ምዕመናን በሚጋግሩት ዳቦና በሚሰሩት ዶሮ ወጥ ጠቅጥቃችሁ ዝም አላችሁ፡፡

መጽሐፉ እስተንፋስ ያለው ሁሉ እንዲተነፍስ ያዝዛል፡፡ ዳሩ ግን እናንተ ይህንን የመጽሐፍ ቃል በመሻር በጎንደር አንድ ሚሎዮን የሚጠጋ ሕዝብ ሜዳ ሲያደር፣ በመተከል ሲታረድ፣ በሸዋ፣ በአሩሲ፣ በባሌና ሀረር ሕዝብ በገጀራ ሲቀላና ቤት በገላው ሲፈርስ፣ በጌዲዮ ሕዝቡ ስደተኛ ሆኖ በርሃብና በበሽታ ሊያልቅ፣ ሻሸመኔ በእሳት ስትወድም፣ በዝዋይ፣ በአዳሚ ቱሉ፣ በድሬዳዋ፣ በአሩሲና በሌሎችም ቦታዎች ዜጎች እንደ በግ ሲታረዱ እናንተ እንኳን እንደነ አቡነ ጴጥሮስ ራሳችሁን ለመስዋእትነት ልታቀርቡ ያላዬ ያልሰማ መስላችሁ ባቄላ እንደ ዋጠ አውራ ዶሮ ጪጪ አላችሁ፡፡

ለክርስትናና ለፍትህ ሲሉ  ተዘቅዝቀው የታረዱትንና የተሰቃዩትን ሐዋርያት ስም ጴጥሮስን፣ ጳውሎስን፣ ማርቆስን፣ ሉቃስን፣ ዮሐንስን፣ ማትያስን፣ ገብርዔልን፣ ቀውስጦስን፣ ገሪማን ወዘተርፈ ወርሳችሁ እናንተ እነሱን ታሰቃዩአቸውና ታረዷቸው ጪራቆች ጋር ቆማችሁ ስትታዘዟቸው ትታያላችሁ፡፡ አቡነ ጴጥሮስና አቡነ ሚካዔል የጨበጡትን መቋሚያ እየጎተታችሁ የሞሶሎኒን የአላማ ዲቃላዎችን ትላካላችሁ፡፡ አቡነ ቴዎፍሎስ፣ አቡነ ጎርጎሪዎስና መላከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ የጣፏችውን መጽሐፍት እያገላበጣችሁና በቆሙበት መንበር ተገትራችሁ ለከሀዲ ገዥዎች “የልማት” ካድሬ ሆናችሁ ስትታዘዙና ስታገለግሉ ትውላላችሁ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የጠፋውን የማሌዥያ አውሮፕላን የበላው ጅብ አልጮህ አለ፤ (ከዚህ በፊት 5 አውሮፕላኖች ጠፍተው እንደነበር ያውቁ ኖሯል?)

በስግብግብነት፣ በራስ ወዳድነት፣ በሆዳምነትና በፍርሃት የሚቀልቧችሁን በጎቻችሁን ለቀበሮ ገብራችሁ ወደ እማይቀረው ዓለም ስትሄዱ የሰማዩን ዳኛ ምን ሰርተን መጣን ልትሉት ነው?

“ቤተክርስትያን እየተቀጣለ ምእመናን ሲደደዱና በገጀራ ሲቀሉ እናንተ እነሱን ለማዳን እንደ ጳውሎስና ጴጥሮስ መስዋእት እንድትሆኑ ቤተክርስትያን አደራ ስትጥልባችሁ ድምጣችሁን አጥፍታችሁ ክትፏችሁንና ቁርጣችሁን ትዝቁ ነበር” ብሎ መለኮት ሲያፋጥጣችሁ ምን ልትመልሱ ነው?

“ልጃገረዶች ከትምህርት ቤት ተጠልፈው ሲሰቃዩና ወላጆቻቸውም የምድር ሲዖል ሲኖሩ እናንተ እነሱ የከፈሉትን አስራት እየዋጣችሁ በምቾት ኑሯችሁን ትቀጩ ነበር” ብሎ ተሚዛን ሲያስቀምጣችሁ ምን ሊውጣችሁ ነው?

ሥራ የሌለው እምነት የሞተ ነው የሚለውን ጠቅሶ “የጨበጣችሁትን መስቀል፣ የደፋችሁትን ቆብ፣ የደረባችሁት ካባና የተሸከማችሁትን የሐዋርያትና የቅዱሳን ስም በምን ሥራ ተረጎማችሁት?” ብሎ ቢጠይቃችሁ በምን ግብር ተረጎምነው ልትሉት ነው?

ታሪክስ “በእናንተ ዘመን ቤተክርስትያን ስትከፋፈል፣ ምእመናን እንደ በግ በካራ ሲታረዱ፣ የክርስቶስ ማደሪያ ቤተክርስትያኖች ባለቤት እንዳጣ ጫካ በአሪዎሶች ሲቃጠሉ እናንተ ፓትሪያሪኮችና  ጳጳሳት ምንም ሳታደርጉ ጪጪ ብላችሁ ሆዳቸውን እየሞላችሁ በምእመናን አስራት በተገነባ የአማረ ህንፃ ውስጥ ትንቡክ በሚል አልጋ ስትንፈላሰሱ ታድሩ ነበር” እያለ በጦር እየወጋችሁ ሲኖር ህመሙን እንዴት ልትችሉት ነው?

ፓትሪያሪክና ጳጳሳት ሆይ! በጎቻችሁን ለቀበሮ፣ ቤተክርስትያናችሁን ለእሳት ገብራችሁ ወደ እማይቀረው ዓለም

ስትሄዱ የሰማዩን ዳኛ ምን ሰርተን መጣን ልትሉት ነው?

ሐምሌ ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.

 

3 Comments

  1. Disrespectful article. I am wondering why this man is always negative. He doesn’t have solutions. Negative…negative… negative…… First ask yourself about what you contributed to the country before opening your big mouth on others.

  2. Ayi Tensaye

    Do not you think telling the truth is a big contribution to a county and society. Can you pinpoint any thing untrue about this article? Is it better to stand behind those who failed to fulfill their duty, engulfed in corruption, mischief and betrayal like you?

    We are glad these writer is exposing these EPRDF cadres who are killing our beloved church.
    Tell us any positive thing happening in the country to write about, woslataw Tesay?

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.