ሻሸመኔ ስትወድም መንግስት የት ነበር ? #ግርማካሳ

ሻሸመኔ
ሻሸመኔ ከተማ እንደ አሌፖ ሲሪያ መውደሟን እይተናል፡፡ ሻሸመኔ የሻሼ ቤት ማለት ነው፡፡ በንግድ በተለያዩ ምክንያት ወ/ሮ ሻሼ የሚባሉ ጠላ ቤት የነበራቸው እናት ነበሩ፡፡ እርሳቸው ጋር፣ ከመንገዳቸው ሰዎች አረፍ ይሉ ስለነበረ፣ ጠላ ለመጠጣት፣ ቦታው የሻሼ ቤት ወይንም ሻሸመኔ ተባለ፡፡ አንድ የሻሸመኔ ሰው እንዳጫወተኝ፡፡
ሻሸመኔ የምእራብ አርሲ ዞን ዋና ከተማ ብቻ ሳይሆን ትልቅ የንግድ ማዕከል ነበረች፡፡ በሕዝብ ቆጠራ ውጤት መሰረት፣ በሕዝብ ብዛት ፣ በኦሮሞ ክልል ካሉ ከተሞች ከናዝሬትና ከጂማ ቀጥሎ በሶስተኛነት የምትቀመጥ ናት፡፡ ከነ ነቀምቴ፣ አሰላና መቱ ሁሉ የትናየት የምትበልጥ፡፡
በሻሸመኔ ዉድመት ሲፈጸም በከተማዋ ከ500 በላይ የኦሮሞ ክልል ፖሊሶች፣ የአንድ የመከላከያ ደቡብ ዕዝ ብርጌድ ወታደራዊ ካምፕ ነበር፡፡ በአንድ ብርጌድ ከ1500 እስከ 3000 ወታደሮች ይኖራሉ፡፡ በአጠቃላይ  ከ2000 እስከ 3500 የታጠቁ የፖሊስና የመከላከያ አባላት ነበሩ፡፡ ከከተማዋ 27 ኪሎሚትር ርቆ በሚገኘው ወንዶ ጢቆ በሚባል ቦታ የአየር ወለድ ትልቅ ካምፕ አለ፡፡ በካምፑ አዛዥ የነበሩት ኮሎኔል ተክለብርሃን ገብረመድህን ሲሆኑ የርሳቸው አለቃ ደግሞ ሜጀር ጀነራል ሹማ አብደታ ናቸው፡፡ ከሻሸመኔ 7 ኪሎሚትር ብቻ ርቃ በምትገኘው በደቡብ ክልል ባለችው ቶጋ ደግሞ በጀነራል ሰለሞን የሚመራ ሌላ የመከላከያ ጦር አለ፡፡ በአጠቃላይ በሻሸመኔ፣ በቶጋና በወንዶ ጢቆ ከ5000 እስከ 9500 ታጣቂዎች ነበሩ፡፡
ሻሸመኔ ከዚህ በፊት ሁለት አሳዛኝና አንገት አስደፊ ክስተቶችን አስተናግዳለች፡፡ የመጀመሪያው ጃዋር መሐመድ በሻሸመኔ ህዝባዊ ስብሰባ ሊያደርግ አስቦ በነበረበት ወቅት፣ ከሻሸመኔ ዙሪያ ደጋፊዎቹ መጥተው፣ በከተማዋ ፍራፍሬ ሻጭ የነበረን ዜጋ፣ “ቦምብ ይዘህ ነው” በሚል፣ ቀጥቅጠውና ገድለው፣ ሰቅለዉት፣ የሰው ልጆችን ደም በማፍሰሳቸው በስፖርት ዋንጫ ያገኙ ይመስል ሲጨፍሩ የነበረበት፣ እጅግ በጣም አሳዛኝ ክስተት ነበር፡፡ ከዚያ በኋላ ብዙም አልቆየም፣ የሙስሊም ሽማግሌ አባትን፣ ጽንፈኞች፣ መሬት ላይ ጥለው ሲደበድቡ የሚያሳይ ሰቆቃ በሻሸመኔ መፈጸሙን አይተናል፡፡ ከነዚህ ሁለት አሳዛኝ ክስተቶች በተጨማሪ በተለያዩ ጊዜያት ከከተማዋ ዙሪያ በፈለጉ ጊዜ በጭፍራ በሚመጡ ጽንፈኞች ፣ በከተማዋ ያሉ ሕብረ ብሄራዊና ሰላማዊ የሆኑ ዜጎችን ማሸበር የተለመደ ነበር፡፡ በአጭሩ፣ የዶር አብይ አህመድ አስተዳደር ስልጣን ከያዘ በኋላ ፣ ሻሸመኔ ፣ የነዋሪዎቿ መብት ተረግጦ ፣ የወሮበሎች መፈንጫ ሆና ነው የቆየችው፡፡
የአንድ መንግስት ትልቁ ሃላፊነቱ ዜጎችን መጠበቅ ነው፡፡ ጉዳት ከደረሰ በኋላ መግለጫ ማውጣትና ሌሎች ላይ ጣቶች መቀሰር ሳይሆን ፣ ጉዳት እንዳይደርስ አስቀድሞ መስራትና አስፈላጊዉን ጥንቃቄዎች ማድረግ ትልቁና ዋናው ስራ ነው፡፡
 
በዚህ ረገድ በሻሸመኔና አካባቢዉ እየጠነከረ የመጣው አክራሪነት በአጭሩ እንዲቀጭ አለመደረጉና የተደራጁ ጽንፈኞች፣ በነጻነት፣ አልፎ አልፎም በመንግስት ሃላፊዎች የሕገ ከለላ ድጋፍ እየተደረገላቸው፣ መንግስት የሌለ ይመስል፣ ወይንም ራሳቸውን እንደ መንግስት በመቁጠር፣ ከአመት በላይ ሲንቀሳቀሱ ዝም መባሉ፣ ሰሞኑን ለተፈጠሩ እልቂቶችና ሰቆቃዎች በዋናነት መንግስትን ተጠያቂ የሚያደርግ ነው፡፡
ከላይ እንደዘረዘርኩት በሻሸመኔና አካባቢዋ ብቻ ከ5000 እስከ 9500 የፖሊስና መከላከያ አባላት እያሉ ሻሸመኔ ስትወድም ለምን ዝም አሉ ? ለምን ዉድመቱን ማስቆም አልቻሉም ? መንግስት የት ነው የነበረው ?????
አገር ቤት የሚታተመው የፍትህ ጋዜጣ እንደዘገበው፣ በሻሸመኔ ከተማ ውስጥ ያለው የአንድ ብርጌድ የመከላከያ ጦር ፣ ከተማዋ ስትቃጠል ካምፑን ዘግቶ ነበር የተቀመጠው፡፡ ቶጋ የሚገኘውም በኦሮምኛ ተናጋሪው ጀነራል ሰለሞን የሚመራው የመከላከያ ጦርም ምንም አላደረገም፡፡ በወንዶ ጢቆ አዛዥ የነበሩት ኮሎኔል ተክለ ብርሃኑ ገብረ መድህን፣ ሃጫሉ የሞተ ዕለት ማታ ችግር በሻሸመኔ መፈጠሩን ሰምተው፣ በነጋታው ጠዋት በሻለቃ ግዛቸው የሚመራ የአየር ወለድ ሻለቃ ጦር በሻሸመኔ አሰማርተው ነበር፡፡ ሆኖም ግን ሻለቃዉና ኮሎኔሉ ከአዛዣቸው ከሜጀር ጀነራል ሹማ አብደታ መመሪያ አልተሰጠንም በሚል ምንም አይነት እርምጃ አልወሰዱም፡፡ እንደ ፍትህ ጋዜጣ ዘገባ፡፡
የአየር ወለድ ነገር ከተነሳ፣ ፣ ከሻሸመኔ 17 ኪሎሜትር ርቀት ተንቀሳቅሰው አየር ወለዶች ዜጎችን ከአሸባሪዎች እንዲጠብቁ መመሪያ መስጠት ያልቻሉት፣ ሜጀር ጀነራል ሹማ አብደታ፣ ከአንድ አመት በፊት ባህርዳር ተነስቶ በነበረዉ ግርግር ፣ በአንቶኖቭ የዚያኑ ማታ፣ ወዲያው ጦር ልከው እንደነበረ ፍትህ ጋዜጣ ሳይጠቁም አላለፈም፡፡ ችግሮች ሊፈጠሩ የሚችሉ ምልክቶች ታይተውም አስቀድሞ ጥንቃቄ አለመደረጉ፣ ችግሮች በተፈጠሩበት ወቅትም ያ ሁሉ የከተማ፣ የወረዳ፣ የዞን የክልል የፌዴራል ፖሊሶችና መከላከያ ሰራዊት አባላት እያሉ፣ ሻሸመኔን ማዳን ዜጎችን መጠበቅ አለመቻሉ፣ እጅግ በጣም ትልቅ የፖለቲካ አመራር ውድቀት ካልተባለ ምንድን ነው ሊባል የሚችለው ? ትልቅና ዋና መንገድ ላይ ያለን ከተማን፣ ሻሸመኔን፣ መጠበቅ ያልቻለ መንግስት ፣ ራቅ ያሉ አካባቢዎችን እንዴት መጠበቅ ይችላል ተብሎ እምነት ሊጣልበት ይችላል?
የዶር አብይ አስተዳደርና ሆነ የኦሮሞ ክልል መንግስት የተጠመደው ኦነግ ሸኔንና ወያኔን በመክሰስ ላይ ነው፡፡ ሌሎች ላይ በማሳበብ፡፡ ችግሩን ወደ ውጭ ከማውጣትና externalize ከማድረግ ፣ ወይንም አቶ ንጉሱ ጥላሁን እንዳሉት፣ “የባሰ ይሆን ነበር” ብሎ ሰበብ ከመፈለግ፣ የፌዴራል መንግስት ሃላፊነትን መውሰድና fail አድርገናል ብሎ አምኖ ህዝብን ይቅርታ መጠየቅ ፣ አስቸኳይና ተጨባጭ እርምጃዎች መውሰድ አለበት፡፡ ነገሮችን መሸፋፈን ቆሞ፣ መሰረታዊ ፣ ችግሮችን ከስር መሰረታቸው ለመንቀልና መፍትሄዎች ለማምጣት መዘጋጀት ያስፈለጋል፡፡
መንግስትን ራሱ ተጠያቂ በማድረግ ዙሪያ ፣ የሻሸመኔ ከተማ ከንቲባና የከተማዋ የሰላምና ጸጥታ ሃላፊ ጨምሮ ከ50 በላይ በመንግስት መዋቅር ያሉ ሃላፊዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ሰምተናል፡፡ ይሄ ጥሩ እርምጃ ነው፡፡ ሆኖም ፣ አንደኛ የምእራብ አርሲ ዞንና የኦሮሞ ክልል ርእሰ መስተዳድሮችና የጸጥትና ፖሊስ ሃላፊዎች፣ ቶጋ ያለው የደቡብ ዕዝ ጦር ሃላፊ የሆኑት ጀነራል ሰለሞን፣ ወንዶ ጢቆ ካምፕ ሃላፊ የነበሩት ኮሎኔል ተክለ ብርሃን ገብረ መድህንና አለቃቸው ሜጀር ጀነራል ሹማ አብደታ ሳይቀሩ ተጠያቂ መሆን አለባቸው፡፡
በሁለተኛ ደረጃ ችግሩ ግለሰቦችን በማሰር ወይንም በማባረር ብቻ እንደማይፈታ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ከግለሰቦች ያለፈ ሲስተማቲክ የሆነ ችግር ነው ያለው፡፡ ሻሸመኔ በጽንፈኞች የወደመችው፣ በዚያ የሚኖሩ ነዋሪዎች ሕብረ ብሄራዊ በመሆናቸውና የከተማዋ ነዋሪዎችን ጽንፈኞቹ መጤና ሰፋሪ፣ ወራሪና ጠላት አድርገው ስለሚያዩዋቸው ነው፡፡ ከተማዋን የነርሱ ጎሳና የነርሱ ኃይማኖት ተከታይ ከሆኑት ለማጽዳት በሚመስል መልኩ፣ ነዋሪዎችን በማሽበርና በማስደንገጥ፣ ጥለው፣ ከተማዋን ለቀው እንዲወጡ ነው። ይህ አይነቱ ተግባር እንዲፈጸምና ሻሸመኔ ያሉ ኦሮሞ ያልሆኑ ነዋሪዎች፣ ሻሸመኔ አገራቸው እንዳልሆነ ተደርጎ እንዲታይ ያደረገው የጎሳ ፖለቲካ አስተሳሰብ ነው፡፡ “ይሄ የኦሮሞ መሬት ነው፣ የኦሮሞ አገር ነው” ከሚል ዘረኛነት የተነሳ ነው፡፡ ይሄ ሕገ መንግስትና አወቃቀር ካልተቀየረ፣ ዜጎች ለነርሱ ጎሳ ከተመደበው መሬት ውጭ በሌሎች አካባቢዎች የመኖር ዋስትናቸው የተረጋገጠ አይሆንም፡፡
ማሰሪያው፣ በአገር ደረጃ የዘር ድርጅቶች፣ የዘር ሜዲያዎች በአጠቃላይ የዘር ፖለቲካ መታገድ ነው ያለበት፡፡ ሩዋንዳዉያን በዘር ፖለቲካው ምክንያት ትልቅ ዋጋ ስለከፈሉ ነው የዘር ፖለቲካን ያገዱት፡፡ እኛም ከሩዋንዳ መማር አለብን፡፡ ትላንት በዘር ማጥፋት ወንጀል የተጨማለቀችዋ ኪጋሊ አሁን በአፍሪካ ካሉ ምርጥ ከተሞች መካከል አንዷ ሆናለች፡፡ ምርጥ ከተማ፡፡ ሻሸመኔ አሁን አንገት እንዳስደፋችን፣ ለውጥ እንዲመጣ ምክንያት ሆና፣ “ሻሸመኔ እንዲህ ሆኖ ነበር” ብለን ክፉ ማውራት ሳይሆን “በሻሸመኔ ምክንያት ይሄ ጥሩ ለውጥ መጣ” የምንልባት ከተማ እናደርጋት ዘንድ ትልቅ ምኞት አለኝ፡፡ ሻሸመኔን ያወደማት የዘር ፖለቲካ ነው፡፡ ሽሸመኔን በተሻለ መንገድ ወርቅ አድርጎ የሚገነባት ደግሞ የዘር ፖለቲካ ማርከሻ ሲገኝ ነው፡፡

2 Comments

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.