ከውጭ ሃይል ጋር የሚሰሩ ፓርቲዎች በህግ ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ ተገለፀ (በማህሌት አብዱል)

አዲስ አበባ፡- ከውጭ ሃይል ጋር ተቀናጅተው የአገር ሉኣላዊነትንና አንድነትን ለመናድ የሚሰሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተለይተው በህግ ተጠያቂ ሊሆኑ እንደሚገባ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲዎች አስታወቁ።
አዲስ ዘመን ጋዜጣ ያነጋገራቸው አንዳንድ ፓርቲዎች እንደተናገሩት፤ መንግስት በቅርቡ በአገሪቱ ለተከሰተው አለመረጋጋት ምክንያት የሆኑና ከውጭ ሃይሎች ጋር የሚሰሩ ፓርቲዎች ስለመኖራቸው ከመግለፅ ባለፈ ድርጊቱ በሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ በመሆኑ በአገር ክህደት ወንጀል ተጠያቂ ሊያደርጋቸው ይገባል።
ethnic
የህብር ኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ እንደተናገሩት፤ ማንኛውም በህጋዊ መንገድ ለመስራት የተመዘገበ ፓርቲ የአገሪቱን ህገ መንግስት አክብሮ የመስራት ግዴታ አለበት።
የፖለቲካ ፓርቲ በመሆኑ ብቻ ከተጠያቂነት ሊያመልጥ የማይችል በመሆኑ ይህንን ህጋዊ መስመር ጥሶ ሲገኝ ተጠያቂ ሊሆን ይገባል።
«እነ ከሌ እንዲህ አሉና እነከሌ እንዲህ አደረጉ እየተባሉ የሚነገሩት መረጃዎች በማስረጃ ሳይደገፉ ለፕሮፖጋንዳ ጥቅም ከማዋል ይልቅ ከውጭ ሃይላት ጋር ግንኙነት ፈጥረው የኢትዮጵያን ጥቅም የሸጡ አካላት ካሉ በህጉ መሰረት አስፈላጊው እርምጃ ሊወሰድባቸው ይገባል» በማለት አቶ ግርማ ገልፀዋል። በተለይም መንግስት ከውጭ ሃይሎች ጋር ተቀናጅተው በአገር ውስጥ ነውጥ የሚያስነሱ ህዝብና ህዝብ የሚያጋጩ ፓርቲዎች ስለመኖራቸው የተጣራ ማስረጃ በመያዝ ተጠያቂ ሊያደርጋቸው እንደሚገባ አስረድተዋል።
እንድ አቶ ግርማ ገለፃ፤ ከምንም በላይ የሀገር ሉዓላዊነት ጉዳይ ማንም ለድርድር ሊያቀርበው የሚገባ ጉዳይ አይደለም። የውስጥ ችግር በውስጥ ሃይሎች መፈታት እየተቻለ ከውጭ ሃይል ጋር በመቆራኘት የሚሰራ ማንኛውም ተግባር በከፍተኛ ወንጀል የሚያስጠይቅ የአገር ክህደት ነው። በተለይም ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአንድ ድምፅ የተስማማበትና በጋራ እየገነባ ያለውን የታላቁ ህዳሴ ግድብን መሰረት ያደረጉ የተቃውሞ እንቅስቀሴዎች የሌሎችን አጀንዳ ለማስፈፀም የታለመ ከመሆኑም ባሻገር እንታገልለታለን በሚሉት ህዝብ ላይ የታቃጣ አደጋም ነው።
« በአሁኑ እኛም ሆነ ሌሎች ፓርቲዎች ያሉትን ችግሮች መንግስትን እየገሰፅንና እየተቸን እንዲስተካከሉ እየታገልን ሳለ በውጭ ያሉ አንዳንድ አካላት ከኛ በላይ ተጎጂ ሆነው የቀረቡበት አግባብ ‘የምጣዱ ሳለ የእንቅቡ ተንጣጣ’ እንደሚባለው ሁሉ ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም» ብለዋል። በህጋዊ መንገድ ለመስራት የተመዘገቡት ፓርቲዎች ድርጊቱን ወንጀል መሆኑን የሚያምኑ ከሆነ ደጋፊዎቻቸው የአገርን ህልውና አደጋ ላይ ከሚጥሉ የተቃውሞ እንቅስቀሴዎች እንዲታቀቡ ማድርግ እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።
የትግራይ ዲሞክራቲክ ፓርቲ ሰብሳቢ ዶክተር አረጋዊ በርሄ በበኩላቸው፤ ኢትዮጵያ በታሪኳ በውጭ ሃይሎች በሚደረግባት ወረራ አንዳንድ የአገርንና የህዝብን ጥቅም አሳልፈው የሚሰጡ ግለሰቦችና ቡድኖች ያጋጥሟት እንደነበር አስታውሰዋል።
በቅርቡም ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ግብፆች በዲፕሎማሲም ሆነ በጦርነት አልሆን ያላቸውን ጉዳይ ሰርጎ ገቦችን በመጠቀም የአገሪቱ አንድነትና ሰላም እንዲናጋ በማድርግ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል። «በተለይም ውስጣችንን ያለውን መከፋፈል ተጠቅመው ተቃዋሚ ሃይሎችን እንደሚደግፍ ይታዋቃል፤ አሁን አሁን እየጨመረ የመጣው ግጭት የውጭ ሃይል እጅ እንዳለበት እሙን ነው» በማለት ገልፀዋል።
ከዚህ አኳያ በተለይም የህወሓት አመራር በአሁኑ ወቅት እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ አቅጣጫውን የሳተና የሃገርን ህልውና ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ መሆኑን አስገንዝብዋል። ህወሓት እንደቀድሞው ስልጣኑን አስጠብቆ መቆየት እንደማይችል በመገንዘቡ ለውጡን ለማደናቀፍ የተለየዩ ጥረቶችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ በተለይም የተለያዩ ቡድኖችን በማደራጀትና መሳሪያ በማስታጠቅ ጭምር ለውጡን ለማደናቀፍ ከፍተኛ ስራ ሲሰራ መቆየቱን አስረድተዋል።
የህወሓት አመራሮች ወደ መንበረ ስልጣኑ ለመመለስ ሲሉ ብቻ የአገርን ጥቅም አሳልፎ ለመስጠት የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩን አመልክተዋል። « አሁን አሁን በፌዴራል መንግስቱ ላይ የጦርነት ነጋሪት መጎሰማቸውን አብዝተዋል» ያሉት ዶክተር አረጋዊ፤ ለዚህ ደግሞ የውጭ ሃይል ድጋፍ ስለመኖሩ ያላቸውን እምነት ተናግረዋል። በመሆኑም መንግስት ለግል ጥቅማቸው ሲሉ የአገርን አንድነትና ሉዓላዊነትን አደጋ ላይ የጣሉ ፓርቲዎችን በህግ ተጠያቂ ሊያደርግ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። «ህዝቡ እነዚህ ሃይሎች እየሄዱበት ያለው መንገድ ህዝብ ለህዝብ የሚያጨራርስና አገር አሳልፎ የሚሰጥ መሆኑን ሁሉም ሊገነዘብና ሊቃወማቸው ይገባል» ብለዋል።
«በአገር አቀፍ ደረጃ እንደታላቁ የህዳሴ ግድብ ያሉ ፕሮጀክቶችን ከግብ ለማድርስ እየተንቀሳቀስን ባለንበት በዚህ ወቅት የውጭ ሃይሎች ፍላጎታቸውን በአገር ውስጥ የፖለቲካ እንቅሳቀሴ ሽፋን ዓላማቸውን ለማሳካት እየተንቀሳቀሱ መሆኑን በግልፅ በራሳቸው ሚዲያም ሲዝቱ ታይተዋል» ያሉት ደግሞ የኢዜማ የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ናትናኤል ፈለቀ ናቸው።
እንደ አቶ ናትናኤል ገለፃ፤ በታሪክም የውጭ ሃይሎች የውስጥ ልዩነቶችንና ችግሮችን ተጠቅመው የራሳቸውን አላማ ለማስፈፀም እንደሚጥሩ ይታወቃል። ማንኛውም ለኢትዮጵያ ህዝብ ቆሚያለሁ የሚል አካል የግብፆች ያላማ ማስፈጸምያ ማሳሪያ መሆን የለበትም። የውስጥ ችግሮችን በመነጋገር ከመፍታት ባለፈ የውጭ ጣልቃ ገብነት እድል መስጠት አይገባውም።
«አገር ውስጥ በሚፈጠር መበጣበጥ ችግር ቢፈጠር ጉዳቱ የሁላችንም ነው » የሚሉት ሃላፊው፤ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ሁኔታዎችን ፓርቲያቸው እንደሚያወግዝ ተናግረዋል። ከዚህ አኳያ በኢትዮጵያ ውስጥ በህጋዊ መንገድ ተመዝግበው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሙሉ ህጉ በሚያዘው መሰረት እንቅስቃሴያቸው በሙሉ የአገር ሉዓላዊነትና የአገርን አንድነት በጠበቀ መልኩ መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው ተናግረዋል።
ማንኛውም የፖለቲካ እንቅሳቀሴ የሚያደርግ የፖለቲካ ሃይል ህግን ማክበርና ከምንም በላይ ለህዝቡ ደህንነት ቅድሚያ መስጠት እንዳለበትም አመልክተዋል።
(ኢ ፕ ድ)
ተጨማሪ ያንብቡ:  "ውሳኔው እየመረረን የዋጥነው እውነታ ነው" ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

1 Comment

  1. ወደዳችሁም ጠላችሁም ከውጭ ሀይሎች(ከኤሜርካ ፣ከግብፅ እና ከኢሳያስ) ሀገር የመሸጥ ስራ እየሰራ ያለው ባንዳው አብይ ነው ስለዚህ እየታዩ ያሉትን ጥፋቶች ወደ ተወሰኑ ድርጅቶች የማላከክ አባዜ ሊቆም ይገባል፡፡ የሴራ ፖለቲካ ይቁም ህወሀት የህዳሴ ግድብ አፈጻፀም 66% አደረሰ እንጂ ካይሮ ሂዶ ወላሂ ወላሂ ብሎ አልሸጠም ለምን ይዋሻል እውነት እየነጋ ይጠራል እንደሚባለው ጊዜው ሲደርስ እውነት ይውጣል፡፡ የብዙ ንፅሀን ዜጎች ገዳይም አስገዳይም ማን እንደሆነ ግልፅ ነው እናንተም ታውቅታላችሁ፡፡ የእናንተ ፍላጎት ህወሀት/ትግራይ ማንበርከክ ነው ነገር ግን መቼም አይሳካላችሁም ፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.