ከለውጡ ማግስት ጀምሮ ህዝቡ ይብቃ እስኪል ድረስ መንግስት ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት ተስተውሎበት ቆይቷል – ንጉሱ ጥላሁን

Nigusu
ንጉሱ ጥላሁን

አሁን ግን ትዕግስትም፤ ሆደ ሰፊነትም ልክ አለው፤ ባንዳነት ሀገር እስኪያፈርስ አይጠበቅም ብሎ ቁርጥ እርምጃ ወስዷል። እየሰወደም ነው፤ ይወስዳልም።

 ከዚህ በፊት መንግስት የሚታወቀው በመግረፍ፣ በመግደል፣ በማሰቃየት፣ በማፈን ነው። በእስር ቤቶች በኢ-ሰብዓዊ ድርጊት ነው የሚታወቀው። በለውጡ ሂደትም የታገልነው እና ውስጣችንንም እንድንታገል ያደረገን ይሄ ነው።
 የመንግስት ትእግስትና ሆደ ሰፊነት ዴሞክራሲን መልሶ የሚበላና ዴሞክራሲን የሚያጠፋ፣ ጥቃቅንና አጉራ ዘለል መንግስታት መሰል ቡድኖችን የሚፈጥር ከሆነ አገር ስለሚያጠፋ መንግስት ትእግስቱና ሆደ ሰፊነቱ ይብቃ ብሏል።
 የመንግስት ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት ግን ሀገርንና ህዝብን አደጋ ላይ ጥሎና አጋልጦ አገር እየተበተነ፤ ህዝብ እየተበደለና እየተሰቃየ እየተባላ ሊቀጥል ስለማይችል፤
 የዴሞክራሲ መርሆዎችንና መሰረታውያኑን ጠብቀን ዴሞክራሲን እንገነባለን፤ መንግስትም፣ አመራሩም በዚህ በኋላ ወደፊት ልንሄድ የመጨረሻውን ትዕግስታችንን አሳይተን የመጀመሪያ እርምጃችንን ጀምረናል።
 መንግስት ትእግስቱና ሆደ ሰፊነቱ ይብቃ ሲል በማስፈራራት ብቻ አይደለም። አይነኬ የሚመስሉ ግለሰቦች ጭምር ማንም ከህግ በላይ አይሆንም በሚል በህግ ጥላ ስር እንዲውሉ በማድረግ ነው።
 እኛ የህዳሴ ግድባችንን ዛሬም ነገም ለማጠናቀቅ ርብርብ ስናደርግ፤ በሌላ ወገን ደግሞ ከዚህ የሚያስተጓጉሉ ውስጣዊና ውጫዊ ጠላቶች እንዲሁም ባንዳዎች ከውጫዊ ጠላቶች ጋር በመተባበር ይሄንን ጉዟችንን ማደናቀፍ አማራጭ የሌለው አማራጫቸው ነው።
 አንዴ ምርጫ፤ አንዴ ግድያ፤ ሌላ ጊዜ ምንም ቢባልም የኢትዮጵያ ህዝብ የነዚህን ሀይሎች ሚስጥር እየተረዳው ነው። የኢትዮጵያን ህዝብ ይዘን ለውጡን እውን እናደርጋለን። ከውጭም ከውስጥም በጠላት የሚሰነዘር ጥቃት አያንበረክከንም ብሎ መንግስት በቁርጠኝነት ጉዞውን ቀጥሎበታል።
 የህወሓት፣ የኦነግ ሸኔ፣ የባልደራስ፣ በለውጡና በነውጡ መካከል በመዋዠቅ ከለውጡ ወደ ነውጡ ማምራት ይበቃል፤ ዴሞክራሲን ለማስፋት መንቀሳቀስ ማለት ዴሞክራሲ እስኪቀለበስ መጠበቅ ባለመሆኑ መንግስት ይሄንን ጉዳይ በትዕግስት መመልከት አክትሟል ብሎ እርምጃ መውሰድ ጀምሯል። ይሄም ይቀጥላል።
 ሃጫሉ የነጻነት ታጋይ ነው። ጥበብን ተጠቅሞ የኢትዮጵያን ወጣት ለትግል አነሳስቷል። በህወሓት አገዛዝ ሲታሰር ሲፈታ ቆይቷል።
 የዚህ የጥበብ ሰው ግድያ የኦሮሞን ወጣት፣ የኢትዮጵያን ህዝብ ያስቆጣል፤ ያሳዝናል ከዚህ በመነሳትም ሊከሰት የሚችለውን የህዝብ ቁጣ ወደ ስልጣን መመለሻ እድል ይሆናል ከሚል ነውረኛ ሀሳብ ነው ይህን ወጣት የገደሉት።
 በአገራችን ላይ የህልውና አደጋ እንዲያንዣብብ፤ በህዝቦች አንድነትና ህልውና ላይ ጥቁር ጠባሳ እንዲጣል የሰሩት እነዚህ ሃይሎች ደግሞ ለውጡ ጥቅማቸውን ያስቀረባቸው፣ ወደጎን የገፋቸው አድራጊ ፈጣሪዎች የነበሩ ናቸው።
 እነዚህ ሃይሎች ይሄንኑ ለማድረግ የትግሉን አቅጣጫ አዲስ አበባ ላይ እናደርገዋለን፤ አዲስ አበባን ደም በደም እናደርጋለን ብለው ሲያሟርቱና ሲዝቱ የነበሩ ናቸው።
 በዚህ ሃይሎች የኢትዮጵያን ህዝብ ስጋት ውስጥ በመጣል አንድ ጊዜ ምርጫ፣ ሌላ ጊዜ ህገ መንግስት፣ ሌላም ጊዜ ደግሞ ፌዴራሊዝም እና ሌሎች አጀንዳዎችን በመቅረጽ አገር በነውጥ እንድትታመስ እቅድ ይዘው ለውጡን ለማጨናገፍ የሚሰሩ አካላት ናቸው።
 ሁል ጊዜ የበላይነት እንጂ እኩልነት የማይመቸው ቡድን ስለሆነ፤ እኩልነት ሲባል የተዋረደ ስለሚመስለው የህዝብን ድምጽ የማፈንና በግርግር በስልጣን ላይ የመቆየት ይፈልጋል
 ግድያውን ከፈጸሙ በኋላ የኦሮሞን ህዝብ በአማራ ላይ ለማነሳሳት ግድያውን የፈጸሙት ነፍጠኞች ናቸው በማለት በሁለቱ ህዝቦች መካከል ግጭት በመፍጠርና ግጭቱን በማራገብ ላይ ነበሩ፤
 በዓለም አደባባይ ኢትዮጵያ አንድነት የሌላት፤ የህዳሴውን ግድብ ማጠናቀቅ የማትችል፤ እና ባስቀመጠችው ግብ መሄድ ያልቻለች ደካማ አገር አድርጎ ለማሳየት፤ ለጠላት የሚመች አውድ በመፍጠር የባንዳነት ሚናቸውን ለመወጣት ነበር።
 እነዚህ ወገኖች ሃጫሉን የመሰለ ምልክት ሲነኩ ብዙ ትርፍ ያተርፍልናል ብለው ነበር። የሃጫሉን ህይወት ቀጥፈው እርሱን ተከትሎ የበርካቶች ህይወት እንዲጠፋ፤ ዜጎች ለፍተው ጥረው ግረው ያፈሩት ሀብት እንዲወድም አድርገዋል።
 ግድያውን ያቀናበሩ ሃይሎች ካሁን በኋላ ደደቢት ተመልሰን አንገባም ትግሉን አዲስ አበባ ጀምረን አዲስ አበባ እንጨርሰዋለን እንዳሉት፤ታዋቂ ሰዎችንና አመራሮችን ኢላማ በማድረግ አቅደው ሲንቀሳቀሱ ነበር፤ ሚዲያዎቻቸውንም አቀናጅተዋል።
 በአዲስ አበባ ጀምረን አዲስ አበባ እንጨርሰዋለን ያሉት ጉምቱ የህወሓት አመራር አምባሳደር ስዩም መስፍን ሲታወሱ፤ ደደቢት ተመልሰን አንገባም ያሉት አቶ ጌታቸው ረዳ ሲነሱ በአጠቃላይ ትንታኔ፤ እንዲሁም ከሌሎች ምርመራዎችና የፖሊስ መረጃዎች እንዲሁም የጸጥታ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት ለውጡ የመጣበት ህወሓት እና የኦነግ ሸኔ ከውጭ አካላት ጋር በመመጋገብ የባንዳነት ሚናቸውን ተጠቅመው ይሄንን ሀገር የማተራመስ እቅድና ተልእኮን መርተውታል።
 ይሁን እንጂ አሁን ይሄ ህልማቸው አልተሳካላቸውም። ኢትዮጵያ አትፈርስም፤ ለውጥ የመጣበት ነውጥ ይፈጥራል፤ ለውጡ ግን ይቀጥላል።
 የአማራ ህዝብ ይህ ለምን እንደሚደረግ ይረዳል፤ ምን ያህል የጥቃት ሰለባ እንደሆነ፣ ምን ያህል ሰይፍ እንዲመዘዝበት እንደተደረገ ይገነዘባል።
 የኦሮሞም ህዝብ አቃፊነቱን፣ አብሮነቱንና ወዳጅነቱን የሚሸረሽር ስም ለመለጠፍ የሚደረግበትን ዘመቻ ይገነዘባል። ኦሮሞነትና አማራነት ተዋህደው፤ ከመላው ብሔር ብሔረሰቦች ጋር ተጣምረው ኢትዮጵያን ኢትዮጵያ ያደርጋሉ።
 እነሱ እንደሚሉት ኦሮሞነት እና አማራነት እሳትና ጭድ ሳይሆን ማርና ወተት ሆነው ኢትዮጵያን ይገነባሉ
 የተፈጠረውን ችግር ለማስቆምና ወገኖቻቸውን ለመታደግ የኦሮሞ ወጣቶች፣ የኦሮሞ ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎች፣ የፖለቲካ አመራሮች ሰለባ ሆነዋል።
 የአማራ ወጣቶችና የአማራ ምሑራን፤ የአማራ ባለሀብቶችና መላው የአማራ ህዝብ በአማራ ክልልም ከአማራ ክልል ውጪም ያለው ይሄን ይገነዘባል።
 ጥቃት የተሰነዘረው በኦሮሞ ህዝብ፣ ጥቃት የተሰነዘረው በአማራ ህዝብ፣ ጥቃት የተሰነዘረው በመላው የኢትዮጵያ ህዝብና በኢትዮጵያዊነት ላይ በመሆኑ፤ ኦሮሞና አማራ ብቻ ሳይሆን መላው ኢትዮጵያውያን ብሔርና ሃይማኖት ሳይለያቸው አንድ ሆነው፣ ድርና ማግ ሆነው ፣ይሄንን የፈተና ጊዜ ያልፉታል።
 አገራዊ አንድነታችን ቢጠነክር ጠንካራ ኢትዮጵያ የምትፈጠር መሆኑን ስለተገነዘቡ፤ የጠንካራ ኢትዮጵያ መፈጠር ለእነርሱ ስጋት ስለሆነ የህዝቦች አንድነት ስጋት ውስጥ ለመጣል እየሰሩ ነው።
 ለውጡን በነውጥ፤ ለውጡን በብጥብጥ ማርከስ እና አገር ማፍረስ ዓላማቸው ነው። ትክክለኛ ወቅት ብለው የወሰዱት የሚመጣውን መስከረም ወይም ያለፈውን መስከረም አይደለም።
 በቀውስ ወቅት ጽንፈኛ ሚዲያዎች ግድያን የሚያቀነባብሩ፤ ለግድያ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ፤ ግድያ ከተፈጸመ በኋላም በተቀነባበረ ሁኔታ አጀንዳ ቀርጸው ህብረተሰቡን በቀረጹት አጀንዳ እንዲፈስ የሚያደርጉ፤ ከዛም በተረፈ የህዝባችንን የአንድነት መሰረት ድርና ማግ የሚበጣጥሱ ሚዲያዎች እንደ ህጉ አግባብ እርምጃ ይወሰድባቸዋል።
 የባንዳነት ሚና መጫወት፤ ከውጭ ሆነው መርዝ የሚረጩብን ሚዲያዎች አጋር ሆኖ የመረጃ ምንጭና መነሻ መሆን በፍጹም ከኢትዮጵያዊነት ያፈነገጠ በመሆኑ ይሄን የባንዳነት ሚና መመከት፤ ለህዝቦች አብሮነትና አንድነት መስራት ከሁሉ የሚቀድም መሆኑን ሚዲያዎች ማስተዋል ይገባቸዋል።
 በቀጣይ ሚዲያዎችም እንደ ህጉ አግባብ የሚስተናገዱ ይሆናል። ህዝብና ህዝብ ከማጫረስ ብሎም አገር ከማፍረስ ሊቆጠቡ ይገባል።
 አገር በማፍረስ ህዝብን በማጫረስ የሚገኝ ትርፍ የለም ፤ ሚዲያዎችም በፈረሰ አገር በሚጫረስ ህዝብ መካከል ሆነው ሚዲያ አይሆኑምና ከዚህ ሊቆጠቡ ይገባል የሚል ሀሳብ አለኝ።
 ዛሬ በተለያየ አካባቢ ወጣቱን ለነውጥና ለቀውስ ሲያነሳሱ የነበሩ፤ ጦርነት ሲሰብኩና ሲያባሉ የነበሩ ወገኖች በህግ ጥላ ስር ውለው በህግ አግባብ ጉዳያቸው እየታየ ነው። ጉዳያቸው በህግ አግባብ መታየቱም ይቀጥላል።
 የመንግስት ሆደ ሰፊነት እና ትእግስት ተገቢና አስፈላጊም ነበር። ይሄ ደግሞ ዴሞክራሲን ለማስፈን፤ አንድነትን፣ አብሮነትና ሰላምን እውን ለማድረግ ታልሞና ታስቦ የነበረ ነበር ፤
 የመንግስት ሆደ ሰፊነት እና ትእግስት እንደ ደካማነት በሚቆጥር ደካማ አስተሳሰብ ምክንያት የህዝብ ደህንነትና የአገር ህልውና አደጋ ላይ ሲወድቅ መንግስት አስፈላጊውንና ተመጣጣኝ እርምጃ በመውሰድ የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታው እንዳይቀለበስ፤ ለዴሞክራሲ ሥርዓቱም ጥብቅና መቆም ስላለበት ራሱ የዴሞክራሲ ሥርዓቱን ያስጠብቃል። ይሄም ተጀምሯል።
 ህወሓት ይሄንን ለውጥ ይቀበላል ብሎ ማለት ይከብዳል። ለምን ቢባል ህወሓት አዲስ አስተሳሰብ አይቀበልም። የመጀመሪያው ምክንያት ያረጀ ያፈጀ አስተሳሰብ በያዙ ያረጁ ያፈጁ አመራሮች ስለሚመራ ነው።
 ሁለተኛው፣ ህወሓት በፌዴራሉ መንግስት ስልጣን ላይ በነበረበት ጊዜ በትግራይ ህዝብ ስም ሲምል ሲገዘት፤ ሀብት ሲዘርፍ፤ የነበረ የአንድ ቤተሰብና የአንድ ስርወ መንግስት ቡድን በምንም መልኩ ይሄንን ለውጥ ሊቀበል አይችልም።
 የህወሓትን አገር የማተራመስ አጀንዳ ላንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በቃ ሊባል ይገባል። በመንግስት በኩልም እንደ ህጉ አግባብና እንደ ህገ መንግስቱ አስፈላጊው ነገር ሁሉ ይደረጋል።
 ህብረተሰቡ ለዘመናት አብሮ ኖሯል። አብሮ በኖረበት የታሪክ ሂደት ውስጥ ደግሞ ችግርና ፈተናም አለ፤ ውድቀትና ስኬትም አለ። እነዚህን ሁሉ በጋራ አልፏል፤ አሳልፏል።
 ኢትዮጵያን ከገነባንበት ከጥንት ጀምሮ እስከዛሬ በርካታ መልካም መልካም ነገሮችን በተናጥል ሳይሆን በጋራ ፈጽመናል።
 እንዲህ አይነት ብጥብጦችን ለመፍጠር አቅደው የተንቀሳቀሱ ወገኖች አንደኛው ምክንያት የህዝብ ደህንነት አደጋ ውስጥ መውደቅ ስለማይገድዳቸው ነው።
 አጥፊዎች ከህግ አያመልጡም። ምናልባት አጥፊዎች ጥፋት አቅደው ሲፈጽሙ መውጫ መንገዳቸውንም አቅደው፤ ከህዝብ መረጃ መውጫ መንገዳቸውንም አዘጋጅተው፤ አጀንዳ ቀርጸውና ራሳቸው ገርፈው ራሳቸው ጮኸው ህዝብን የሚያደናግሩ ናቸው። እነርሱ በምንም መልኩ ቢጓዙ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ በየእለቱ የምርመራ ሂደቱን ለህዝብ ያደርሳል። የዜጎችን ህይወት መታደጉንም ይቀጥላል።
 ህብረተሰቡም ሁሉንም ነገር በትዕግስት መርምሮ መራመድ እንዳለበት፤ በፍትህ አካላት የሚሰጠውን ውሳኔና ብይንም በትዕግስት እንዲጠብቅ በዚሁ አጋጣሚ ማሳሰብ እፈልጋለሁ።

(ኢ ፕ ድ)

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.