ከብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ የተሰጠ መግለጫ

ብልጽግና በመግለጫው ካነሳቸው ነጥቦች መካከል
  • ጥቂቶችን የያዘው የዝርፊያ ቡድን የህዝብን አደራ ፈፅሞ በረሳና ለነፃነትና ለእኩልነት የተከፈለውን እልፍ መስዋዕትነት በዘነጋ ሁኔታ ለሁለት አስርት ዓመታት ሀገሪቱን ሲመዘብር ኖሯል።
  • ይህ ቡድን አሁን ላይ በሠራው ወንጀል ሲጠየቅ ግን በህዝብ ጉያ ውስጥ ገብቶ ተሸሽጓል።
  • የዚህን ቡድን የጥፋት ሴራ በመገንዘብ ከእኩይ ተግባሩ እንዲመለስ ጫና ሊያደርጉበትና መደበቂያ እንደማይሆኑት በተግባር ሊያሳውቁት ይገባል።
  • ወጣቶችም በልማትና በመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ለመሆን የሚያሰሙትን ድምፅ ሳይቀር ለማፈን ጉልበቱን ሳይሰስት በሚጠቀመው አፋኝ ቡድን ላይ የሚያሰሙትን ተቃውሞ ፓርቲያችን እውቅና የሚሰጠውና የሚደግፈው ነው
  • ወጣቶች የብልጽግና መሠረቶች እንደሆኑ ፓርቲያችን በጥብቅ ያምናል። ሀገራዊ ለውጡ እንዲመጣ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉ ብቻ ሳይሆኑ ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው፤ አሁንም ለውጡን ከጥፋት ሃይሎች ለመታደግ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆኑን ፓርቲያችን ይረዳል።
  • መላው አባላችንና አመራሩም ከመቼውም ጊዜ በላይ ያለንበትን ወቅታዊ ሁኔታ መገንዘብና አንድነቱን ማጠናከር ይጠበቅበታል። ሀገራዊ ለውጡ እውን እንዲሆንና በፈተናዎች ውስጥ ሆኖም አንፀባራቂ ድሎችን እያስመዘገበ እንዲቀጥል የተጫወታችሁትን ታሪካዊ ሚና በዚህ ወቅትም በላቀ ሁኔታ እንደምትፈፅሙት የብልጽግና ፓርቲ ሙሉ እምነት አለው።
  • የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥት እነዚህ የሀገር ውስጥና የውጭ ሃይሎች በጥምረት የደቀኑትን ፈተና ለመመከት በሚችልበት ሙሉ አቅምና ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ገምግሟል።
**********************
የመግለጫውን ሙሉ ቃል እነሆ!
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ዛሬ ሐምሌ 4/2012 ዓ.ም ባካሄደው ስብሰባ በሀገራችን ወቅታዊ ፖለቲካዊ ሁኔታዎችና የወደፊት አቅጣጫዎች ላይ ውይይት አካሂዷል።
ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴው በቅርቡ የጥፋት ሃይሎች ሰለባ በሆነው አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ሞት እና ይህንኑ ተከተሎ በተለያዩ አካባቢዎች በነበረው ግጭት ህይወታቸው ላለፈ ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን በመግለፅ ለሟች ዘመዶችና ወዳጆች እንዲሁም በአጠቃላይ ለኢትዮጵያ ህዝቦች መፅናናትን ተመኝቷል።
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በሀገራችን ኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ህዝቦች የሚያነሷቸውን ጥያቄዎችና በድርጅቱ በውስጡ የነበሩ ትግሎችን መሠረት በማድረግ ኢህአዴግ የነበሩበትን የፍትሃዊነት፣ የዴሞክራሲያዊነት፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና እውነተኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ያለመገንባት ችግሮች በማረም ወደ እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ እና ፌዴራላዊ ሥርዓት ለመሸጋገር ያስችለው ዘንድ ራሱን ፈትሾ መለወጥ የሚያስፈልገው መሆኑን በማመን ወደ ለውጥ መገባቱን አስታውሷል።
በሀገራችን የተመዘገው ለውጥ ይቅር ባይነትንና ወደፊት መመልከትን፣ ህብረ ብሔራዊ አንድነታችንን ማጠናከርን፣ የዜጎችን መብቶች ሳይሸራረፉ ማክበርን እና በሕግና በመርህ የሚመራ የፖለቲካ ሥርዓት መመስረትን አላማዎቹ አድርጎ ጉዞውን ጀምሯል። የህዝቦችን እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትህ የማግኘት መብት ማረጋገጥን አበይት መርሆዎቹ አድርጎ ሲፈፅም ቆይቷል። ባለፈ ታሪክ ላይ ተቸክሎ የሚካሄድ የመጠፋፋት ፖለቲካን ለማስቀረት ታግሏል። በመደመር እሳቤ ሁሉንም በጎ እሴቶቻችንን መጠቀምና የማይጠቅሙትን ደግሞ ማረም ለውጡ ይዟቸው የተነሳ መሠረታዊ ባህሪዎቹ መሆናቸውን ሥራ አስፈፃሚው አንስቷል።
ይህን ተከትሎ ሀገራዊ ለውጡ ባለፉት ሁለት ዓመታት የህዝባችንን የረጅም ጊዜ ፍላጎትና ጥያቄዎች የመመለስ እርምጃዎችን ሲወስድ ቆይቷል። ህብረ ብሔራዊ አንድነታችን እንዲጎለብት፤ እኩልነት፣ ነፃነትና ፍትሃዊነት እንዲነግሥ፤ የዴሞክራሲ ሥርዓታችን ማነቆዎች እንዲወገዱ ለማድረግ እርምጃዎች ተወስደዋል። እነዚህ እርምጃዎች በየደረጃው ህዝባችን ተስፋ እንዲሰንቅ ያደረጉ ሲሆን ሀገራችን በሁሉም መስኮች የያዘቻቸውን ዕቅዶች እንደምታሳካ የሚያሳዩ አበረታች ሁኔታዎች ተፈጥረዋል። ይህ ወቅት ቀድሞ በሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና በሙስና ስሟ መግነን ጀምሮ የነበረውን የሀገራችን ሁኔታ በመቀየር ኢትዮጵያ በዓለም አደባባይ ከፍ ብሎ ስሟ እንዲጠራ ያደረገ የኖቤል ሽልማት ባለቤት የሆነችበት ነው።
እነዚህን ሀገራዊ ለውጦች የሚመራው ብልጽግና ፓርቲ በውስጡ የከረሙ የፖለቲካዊ ይዘትና የአደረጃጀት ችግሮችን በመቅረፍ ላይ ነው። ቀድሞ “አጋር” በመባል ከቁልፍ የሀገሪቱ ውሳኔዎች የተገለሉ ብሔር ብሔረሰቦችን ባካተተ ሁኔታ በህብረ ብሔራዊ መልክ ራሱን ዳግም አደራጅቷል። በዚህም ከዋና ዋና ሀገራዊ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ውሳኔዎች ተገልለው የነበሩ ህዝቦችን በማቀፍ የመላው ኢትዮጵያውያን ፓርቲ ለመሆን ችሏል።
ይሁን እንጂ ለውጡ ስኬትና ተስፋ ብቻ ሳይሆን ፈተናና እንቅፋቶችም ተጋርጠውበታል። የቆየና የተበላሸን ሥርዓት በአዲስና የተሻለ ሥርዓት ለመቀየር የሚደረግ ጥረት ሁሌም በነባሩ ሥርዓት ባልተገባ መንገድ ተጠቃሚ የነበሩ ቡድኖችን ማስከፋቱ አይቀሬ ነው። ለውጡ ለአጠቃላይ ህዝቡ ይዞት የመጣው ትሩፋት ሳይሆን ለጥቂቶች የዘጋው የዝርፊያና የወንጀል በር ብቻ የሚታያቸው ሃይሎች ለውጡን ለመቀልበስ የቀራቸውን አቅም ሁሉ አስተባብረው በመረባረብ ላይ ናቸው። ብልጽግና ፓርቲ ግጭትን ለማስቀረት ሲል ለውጡን በይቅር ባይነት መርህ እየመራው ቢቆይም የእነዚህ ሃይሎች የጥፋት ሴራና ድርጊት የፓርቲውን እና የመንግሥትን ጥረቶች ሁሉ በአያሌው እየፈታተኑት ይገኛል።
ከእነዚህ ሃይሎች መካከል ግንባር ቀደም የጥፋት ሚናን የያዘው ደግሞ ያለፈውን ሥርዓት ሲመራ የነበረው ዘራፊ ቡድን ነው። ይህ የጥፋት ቡድን ሀገራዊ ለውጡን ባለመቀበል ከፓርቲ ውህደቱ አፈንግጦ ከወጣ ጀምሮ “እኔ ካልበላሁት ጭሬ ልበትነው” በሚል ዓይን ያወጣ የስግብግቦች ፈሊጥ እንዳሻው የሚጋልባቸውን ሆድ አደር ግለሰቦችና ቡድኖች በማደራጀት በሀገሪቱ ሁሉም አካባቢዎች ለሽብር ተግባር አሰማርቷል።
ብልጽግና አሁን ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መልካም ዕድሎችን ይዞ የመጣ፣ ቤተኛና ተመልካች የሌለበት፤ እውነተኛ ህብረ ብሔራዊነቱን በተግባር ያሳየ፣ ለዜጎች ክብርና ነፃነት ትኩረት ሰጥቶ የሚንቀሳቀስ፣ የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት የተለያዩ እርምጃዎችን የወሰደ ፓርቲ መሆኑን በሀገርም በውጭም ያሉ ኢትዮጵያውያን የሚገነዘቡት ሃቅ ነው።
የብልጽግና ፓርቲ የተጀመረውን ሀገራዊ ለውጥ ወደፊት ለማስቀጠል እና የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ግንባታ ለማፋጠንና የውሃ ሙሊት ለማስጀመር ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ ነው። ከዚህም ባሻገር የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ያስከተለብንን አደጋ ለመከላከል ህዝቡን በምልዓት ያሳተፈ ርብርብ በማድረግ ላይ ይገኛል። ወረርሽኙን ተከትሎ ኢኮኖሚያችን የከፋ ጉዳት እንዳይደርስበት ሁሉን አቀፍ ጥረት በመደረግ ላይ ሲሆን በተለይ የግብርና ምርታማነትን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ ቅድሚያ ትኩረት ተሠጥቶ እየተሠራበት ነው።
በዚህ ወሳኝ ወቅት የዜጎች ጤናና ልማት፤ የሀገር ክብርና ሉዓላዊነት ደንታ የማይሰጣቸው ሃይሎች የኢትዮጵያን በጎ ከማይመኙ የውጭ ሃይሎች ጋር ተጣምረው በማያባራ የሚዲያ ዘመቻና የጦርነት ቅስቀሳ ላይ ተሰማርተዋል። የጥፋት ቡድኖቹ የፈጠሩት ግንባር አላማ ለውጡን በመቀልበስ ሀገርን የማፍረስና ብጥብጥ የማንገሥ ነው። ለዚህ ደግሞ አገራዊ ቀውስ ሊያስከትሉ የሚችሉ አመራሮችንና ታዋቂ ሰዎችን በመግደል ህዝብን በህዝብ ላይ በማነሳሳት ትርምስ መፍጠር አንዱ ስልታቸው ነው። ጥቅማቸውን ለማስከበር ሲሉ ሀገሪቱን ሰውተው ማንኛውንም የሽብር ድርጊት ከመፈፀም ወደኋላ እንደማይሉ እንረዳለን። በለውጡ ሂደት ድርጅታችና መንግሥት ያሳዩትን ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት እንደ ደካማነት በመቁጠር የሀገራችን ሉዓላዊነትና የህዝባችንን ደህንነት አደጋ ላይ ለመጣልና ዓይናችን እያየ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቀን ከሌሊት ሲታትሩ ይታያሉ።
ምንም እንኳን በህዝብና በመንግሥት በተለይም ራሱን ለመስዋዕትነት እየዳረገም ቢሆን ለሀገር ደህንነት በቆመው መለዮ ለባሽ ቅንጅታዊ መከላከል በርካታ ሙከራዎቻቸው ቢከሽፉም ከሰሞኑ በነፃነት ታጋዩ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ላይ የፈፀሙት የተቀነባበረ ግድያ ለዚህ አንዱ ማረጋገጫ ነው። በዚህ የጥፋት ድርጊታቸው የበርካታ ዜጎች ህይወት ሲያልፍ በግለሰቦች፣ በህዝብና በመንግሥት ሀብት ላይ ከፍተኛ ውድመት ደርሷል። በዜጎች ሥነ ልቦና ላይ የደረሰው ጉዳትም ቀላል አይደለም። የፓርቲያችንና የመንግሥት መዋቅሩ ከህዝብ ጋር በመቀናጀት የተፈጠረውን ቀውስ ማስቆም ባይችሉ ኖሮ ህዝብን ከህዝብ ጋር በማጫረስ ከዚህም በላይ ጥፋት ለማድረስና ሀገርን ለመበታተን ታቅዶ እንደነበር ገሃድ ነው።
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በዛሬው ዕለት ባካሄደው ስብሰባ መላ የፓርቲው መዋቅርና በፓርቲው የሚመራው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ. መንግሥት እነዚህ የሀገር ውስጥና የውጭ ሃይሎች በጥምረት የደቀኑትን ፈተና ለመመከት በሚችልበት ሙሉ አቅምና ነባራዊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ገምግሟል። ከዚህ በመነሳትም በቀጣይ የሚፈፀሙ የፖለቲካና የዲፕሎማሲ ሥራዎች ላይ አቅጣጫ አስቀምጧል። ከሕግ አንፃርም የተጀመረው ሕግ የማስከበር ሥራ ያለምንም ማወላወል እንዲቀጥልና የፀጥታ መዋቅሩንና የፍትህ ተቋማትን ሕግ የማስከበር ሥራ ማጠናከር እንደሚገባ ወስኗል። በዚህም የሀገርንና የህዝብን ደህንነት ለመጠበቅ ሲባል ችግሮችን አስቀድሞ ለመግታት የሚያስችሉ ሁሉን አቀፍ ሥራዎች መሥራት እንደሚገባ አፅንዖት ሰጥቷል።
መላው የሀገራችን ህዝቦች ወቅታዊ የሀገራችን ሁኔታ እንደሚያሳስባችሁ ፓርቲያችን ይረዳል። መላ ህዝባችን ሕግ በማስከበር ረገድ መንግሥት ተገቢ የሆኑ እርምጃዎችን ሁሉ መውሰድ እንደሚገባው ሲጠይቅ ቆይቷል። የታገስንበትን ምክንያት የሚረዳና የሚቀበል ቢሆንም እንኳን ከልኩ ያለፈ ትዕግስት ዋጋ እያስከፈለን በመሆኑ ጥብቅ እርምጃ እንዲወሰድ ህዝቡ ጥያቄ ሲያቀርብ ነበር። ትዕግስትና ሆደ ሰፊነት ገደቡ የሀገር ሉዓላዊነትና የህዝብ ደህንነትን አደጋ ላይ እስካልጣለ ድረስ ብቻ መሆን ስላለበት የማያዳግም እርምጃ መውሰድ ተጀምሯል። ሥራ አስፈፃሚውም ይህ የተጀመረው የሕግ የበላይነትን የማስከበር ሥራ መቀጠል እንዳለበት አቅጣጫ አስቀምጧል።
ከአብዛኛዎቹ የሀገራችን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር የፖለቲካ ልዩነቶች ቢኖሩም ኢትዮጵያን በማስቀጠልና በሀገር ሉዓላዊነት ላይ አንድነት እንዳለን እናምናለን። የተለያዩ ሲቪክ ማህበራትም ከመንግሥት ጎን ቆማችሁ ሀገርን በማረጋጋትና ጥፋተኞችን በመገሰፅ ሚናችሁን እየተወጣችሁ እንደሆነ እንረዳለን። ብልጽግና ፓርቲ ከሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ጋር በመሆን እየወሰዳቸው ባሉና በቀጣይ በሚወስዳቸው ሕግን የማስከበር እርምጃዎች ከጎኑ እንድትቆሙ ጥሪውን ያቀርብላችኋል።
ጥቂቶችን የያዘው የዝርፊያ ቡድን የህዝብን አደራ ፈፅሞ በረሳና ለነፃነትና ለእኩልነት የተከፈለውን እልፍ መስዋዕትነት በዘነጋ ሁኔታ ለሁለት አስርት ዓመታት ሀገሪቱን ሲመዘብር ኖሯል። ይህ ቡድን አሁን ላይ በሠራው ወንጀል ሲጠየቅ ግን በህዝብ ጉያ ውስጥ ገብቶ ተሸሽጓል። ብልጽግና ፓርቲ በሁሉም የሀገራችን አካባቢዎች ያሉ ህዝቦች በሀገራቸው ሉዓላዊነት፣ ደህንነትና ክብር ላይ የማይደራደሩ፤ ይልቁንም የበለፀገች ኢትዮጵያን ማየት የምንግዜም ራዕያቸው እንደሆነ በፅኑ ያምናል። በመሆኑም የዚህን ቡድን የጥፋት ሴራ በመገንዘብ ከእኩይ ተግባሩ እንዲመለስ ጫና ሊያደርጉበትና መደበቂያ እንደማይሆኑት በተግባር ሊያሳውቁት ይገባል። ወጣቶችም በልማትና በመልካም አስተዳደር ተጠቃሚ ለመሆን የሚያሰሙትን ድምፅ ሳይቀር ለማፈን ጉልበቱን ሳይሰስት በሚጠቀመው አፋኝ ቡድን ላይ የሚያሰሙትን ተቃውሞ ፓርቲያችን እውቅና የሚሰጠውና የሚደግፈው ነው።
ወጣቶች የብልጽግና መሠረቶች እንደሆኑ ፓርቲያችን በጥብቅ ያምናል። ሀገራዊ ለውጡ እንዲመጣ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉ ብቻ ሳይሆኑ ለውጡ ቀጣይነት እንዲኖረው፤ አሁንም ለውጡን ከጥፋት ሃይሎች ለመታደግ ከፍተኛ መስዋዕትነት እየከፈሉ መሆኑን ፓርቲያችን ይረዳል። በሌላ በኩል ደግሞ ጥቂት ወጣቶች ባለማወቅም ይሁን በጊዜያዊ ጥቅም በመታለል የጥፋት ሃይሉ መሣሪያ ሲሆኑ እያየን ነው። ወጣቶች በጓደኞቻቸው የህይወት መስዋዕትነት ጭምር የመጣውን ይህን ለውጥ በውስጥና በውጭ ሴረኞች እንዳይቀለበስ ተግተው እንዲንቀሳቀሱ ፓርቲያችን ጥሪውን ያቀርባል።
መላው አባላችንና አመራሩም ከመቼውም ጊዜ በላይ ያለንበትን ወቅታዊ ሁኔታ መገንዘብና አንድነቱን ማጠናከር ይጠበቅበታል። ሀገራዊ ለውጡ እውን እንዲሆንና በፈተናዎች ውስጥ ሆኖም አንፀባራቂ ድሎችን እያስመዘገበ እንዲቀጥል የተጫወታችሁትን ታሪካዊ ሚና በዚህ ወቅትም በላቀ ሁኔታ እንደምትፈፅሙት የብልጽግና ፓርቲ ሙሉ እምነት አለው።
የፓርቲያችን አመራሮች፣ የመንግሥት የሥራ ሃላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ባለሀብቶችና የዕርዳታ ድርጅቶች የአርቲስት ታጋይ ሃጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በጥፋት ሃይሎች ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖቻችንን ለመርዳት፣ ለማቋቋምና አምራች ሃይል ሆነው እንዲቀጥሉ ለማድረግ አስፈላጊውን ሁሉ እንድታደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን። በአንድ በኩል የተጎዱትን በማቋቋም፣ በሌላ በኩል ዳግም ጥፋቶች እንዳይከሰቱ ነቅተን አካባቢያችንን ከፀጥታ አካላት ጋር በመጠበቅ የጀመርነውን የብልጽግና ጉዞ ከታሰበለት ግብ እንድናደርሰው ብልጽግና ፓርቲ ጥሪውን ያቀርባል።
የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ
ሐምሌ 4/2012 ዓ.ም
አዲስ አበባ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.