‹‹የህወሓት አሁነኛ እንቅስቃሴ የመውረዱና የመዝቀጡ ነፀብራቆች ናቸው›› – ዶክተር አረጋዊ በርሄ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሰብሳቢ

aregawi ‹‹የህወሓት አሁነኛ እንቅስቃሴ የመውረዱና የመዝቀጡ ነፀብራቆች ናቸው››   ዶክተር አረጋዊ በርሄ የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሰብሳቢአዲስ አበባ፡- ህወሓት አሁን እያደረጋቸው ያሉት እንቅስቃሴዎች የመውረዱና የመዝቀጡ ነፀብራቆች መሆናቸውን ዶክተር አረጋዊ በርሄ አመለከቱ፡፡
ከፌዴራል መንግሥት ‹‹ጦርነት እገባለሁ፣ ሊወረኝ ነው›› በማለት የሌለ ትርክት ፈጥሮ ለጦርነት ህዝቡን እያዘጋጀ መሆኑንም አመለከቱ፡፡
የትግራይ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሰብሳቢ ዶክተር አረጋዊ በተለይ ከአዲስ ዘመን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ህወሓት በአሁን ወቅት ለውጡን ከሚቃወሙ ሃይሎች ጋር እያደረገ ያለው ሕብረት፣ ከዛም ባለፈ ለውጡን ለማደናቀፍ እየሄደባቸው ያሉ የጥፋት መንገዶች የመውረዱና የመዝቀጡ ነፀብራቆች ናቸው ሲሉ አመልክተዋል።
በሥልጣን ዘመን ሲያካሄድ የነበረው የተደራጀ ሙስና፣ ህዝብ ላይ ሲፈፅመው የነበረው የአስተዳደር ግፍና በደል፣ ከዛም በላይ በህዝቦች መካከል ጥላቻን በመዝራት የፈጠረው ችግርና ችግሩ ያስከተለው
አዲስ ዘመን ሐምሌ 5 2012 ዓ.ም ጥፋት ለመውረዱና ለመዝቀጡ መሠረታዊ ምክንያቶች እንደሆኑም ገልፀዋል።
የህወሓት አመራር ከመሐል አገር ተፈንግሎ ከሄደ ወዲህ ሥልጣኑ ያመጣለትን ጥቅም አጥቷል ብለዋል። ያንን መልሶ ለማምጣት የሆነ ያልሆነ ሰበብ እየፈጠረ እንደሚገኝ አመልክተው፤ የፌዴራሊስት ሃይሎችን አሰባስባለሁ በሚል ዘዴ ብዙ ያኮረፉ አጋር ድርጅቶችን ሰብስቦ መሃል አገር ሁከትና ግርግር በመፍጠር ወደሥልጣን ለመመለስ አቅዶ ሲሠራ እንደነበር አመልክተዋል።
አጋር ከሚላቸው ሸኔም ሆነ ሌሎች ለውጡን ከማይደግፉ ቡድኖች ጋር ግንኙነትና ያልተቀደሰ ጋብቻን መፈፀሙን ጠቁመው፤ በይፋ መቀሌ ላይ እየሰበሰበ ሲደግስላቸውና ምክክር ሲያደርጉ መክረማቸውን አስታውሰዋል፡፡ ሂደቱ በይፋ እንጂ በድብቅ ያልተካሄደ እንደነበረም ጠቁመዋል፡፡
ድርጅቱ የኢትዮጵያ ህዝብን ምን ያህል እንደበደለ የሚታወቅ መሆኑን የተናገሩት ዶክተር አረጋዊ፤ ‹‹አብዮታዊ ዴሞክራሲ›› የሚለውን ማፈኛ ዘዴ እየተጠቀመ ሥልጣን ላይ ለዘላለም ለመንደላቀቅ በአንፃሩ ህዝቡ ደግሞ እየተሰቃየ እንዲኖር ፈርዶበት እንደነበርም አስታውቀዋል፡፡
ህወሓት ኢህአዴግ 27 ዓመታት በፖለቲካው ዘርፍ ሁሉንም ሥልጣን በእጁ አስገብቶ ሕገ መንግሥት በጣሰ መልኩ ግፍ ሲፈፅም እንደነበረ አመልክተው፤ ራሱ ባረቀቀው ሕገ መንግሥት የማይገዛ መሆኑን ያፈሰሰው የህዝብ ደም እና ያፈነው የሕዝብ ልሳን እማኝ ነው ብለዋል፡፡
በኢኮኖሚው ዘርፍም ማንም የማይቆጣጠራቸው የኢኮኖሚ ተቋሞች መስርቶ ሲበዘብዝ እንደነበር በመጠቆም፤ የኢትዮጵያ መሬቶችን ሲቸበችብ እና ለአመራሩ ጥቅም ሲያውል መቆየቱን አስታውቀዋል፡፡
ላለፉት 27 ዓመታት የሰፈነው አፈና እና ብዝበዛ ሕዝቡ አንገሽግሾት በተቃውሞ ከመሐል አገር መባረሩን አስታውቀው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ይህ ሃይል ሽብርተኛ እና ሕግ የማይገዛው መሆኑን ቀደም ባለው በተቃውሞ እንቅስቃሴው ማረጋገጡን አመልክተዋል፡፡
አሁን የተዘጉት ዲ ደብሊው እና ሌሎችም መገናኛ ብዙሃን ለህወሓት ገዢ መደብ አገልጋይ እንደነበሩ የጠቆሙት ዶክተር አረጋዊ፤ ህዝቡንም ሆነ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የማገልገል ተልዕኮ እንዳልነበራቸው አመልክተዋል፡፡
ሥራቸው ገዢው የህወሓት አመራርን ማገልገል ብቻ እንደነበር ጠቁመው፤ ከእዚህም አልፎ ‹‹አማራ መጣብህ፣ አሐዳዊ መንግሥት መጣብህ… ›› በሚል ህዝብን ከህዝብ የሚያጋጩ ፕሮፖጋንዳዎች ሲነዛ ነበር ብለዋል:: እስካሁንም የጦርነት ዳንኪራ እየመቱ መሆናቸውንም አስታውቀዋል፡፡
የሚዲያ ተቋማቱ ህብረተሰቡን የማያገለግሉ፣ እንዳውም ህዝብ እና ህዝብን ለማጋጨት የሚሠሩ እንደነበሩ ገልፀው፤ የሚዲያ ሥነ ምግባር እና ሕግን የጣሱ በመሆናቸው በሕግ መታገዳቸውም አግባብነት አለው ብለዋል፡፡ በሕግ መጠየቅ እንዳለባቸውም አመልክተዋል።
የህወሓት አመራር ከመሐል አገር ኮብልሎ መቀሌ ገብቶ ከመሸገ በኋላ በኢትዮጵያ ያለው ለውጥ በቀጣይ በኢትዮጵያ ሕዝብ ላይ ባደረሱት ከተጠያቂነት ለማምለጥ እየሞከረ እንደሚገኝ አስታውቀዋል፡፡ አፋና እና ጭቆና፣ በህዝቦች መካከልም የፈጠሩት ግጭት ያስከተለው ጥፋት እንደሚያስጠይቀው ስለገባቸው
ከተጠያቂነት ለመዳን ከመሐል አገር ካለው የፌዴራል መንግሥት ‹‹ጦርነት እገባለሁ፣ ሊወርረኝ ነው›› በማለት የሌለ ትርክት ፈጥሮ ለጦርነት ህዝቡን እያዘጋጀው እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የጦርነት ዝግጅቱ እስካሁን መቀጠሉን ‹‹አሐዳዊ መንግሥት በእኛ ላይ ጦርነት ማወጁ ስለማይቀር ለጦርነት ክተት›› በማለት ህዝቡን እየቀሰቀሰና ሠራዊቱን እያሰለፈ እንደሚገኝም አስታውቀዋል፡፡ ይህ የጦርነት ቅስቀሳ ለማንም የማይጠቅም፣ አውዳሚ፣ አጥፊና ከፋፋይ በመሆኑ የትግራይ ህዝብና መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሊኮንነው ይገባል ብለዋል፡፡ ፓርቲያቸውም ፀረ ጦርነት ቅስቀሳ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ሐምሌ 6 2012 ዓ.ም
ዘላለም ግዛው

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.