ሶሪያ ወይም ሊቢያ እንዳይመስላችሁ የኛዋ ሻሸመኔ ናት – ወንድሰን ሽመልስ

ሶሪያ ወይም ሊቢያ እንዳይመስላችሁ የኛዋ ሻሸመኔ ናት – ወንድሰን ሽመልስ
ሻሸመኔ ፦ ሻሸመኔ ከሀገራዊ ለውጡ ቀደም ብሎ ባሉት ወራት በ2010 ዓ.ም እና በ2012 ዓ.ም ጥቅምትና ሰኔ ላይ ተደጋጋሚ ውድመቶችን አስተናግዳለች። ምንም እንኳ ችግር የለመደች ብትመስልም የአሁኑ ሁኔታዋ ግን የሰላም መደፍረስን አስከፊነት ለመግለጽ ወደ የመንና ሊቢያ ከተሞች ማማተር በቃ፤ እዚሁ ከጓዳችሁ አለ የሚያሰኝ ይመስላል።
ዛሬ ላይ ሻሸመኔ የሆቴል የገበያ ማእከላት የመኖሪያ የባንክና የትምህርት ቤቶችን ጨምሮ ለቁጥር ቀርቶ ለአይን የሚታክቱ በርካታ ህንጻዎቿ በእሳት ጋይተው ከሰል መስለው ቆመዋል። አንዳንዶቹም በከፊል በእሳት ጋይተው በከፊልም ተሰባብረውና ፈራርሰው የህንጻው ውስጥና ውጪ በአመድና ፍርስራሽ ተሞልተው ይታያሉ። ገሚሶቹ በርና መስታወታቸው ተሰባብሮ በቆሻሻ ተከበው ሲታዩ መሰረታቸው እየወጣ ያለ ጅምር ህንጻዎች ይመስላሉ።
እነዚህ ከግዙፍ እስከ አነስተኛ የንግድና የመኖሪያ ቤቶች በውስጣቸው የያዙት ቁስና ንብረት አንድም በእሳት ወድመዋል፤ አሊያም ተሰባብረዋል ወይም በዝርፊያ ተነጥቀዋል። ለህንጻና ለሌሎች ሀብቶቿ አለኝታ መሆን ያልቻለችው ሻሸመኔ ለነዋሪዎቿም ቢሆን የስጋት፣ የስደት፣ የሞትም ምንጭ ሆናለች። በዚህም በሞት ከሸኘቻቸው ነዋሪዎቿ በስተቀር አብዛኞቹ በሰቀቀን የሚኖሩባት በርከት ያሉትም ሀብት ንብረታቸውን ተነጥቀው ለእለት መጠለያ ቀርቶ ጎርሶ ማደር የሚናፍቁባት፣ በርካቶችም እያነቡ በየጎዳናውና በየፍርስራሾቿ ስር የሚታዩባት ሆናለች።
አቶ ዮናስ ጸሀይ በሻሸመኔ ከተማ በሀይሌ ሪዞርት በጥበቃ ሰራተኝነት እያገለገሉ የነበሩ የአካባቢው ናቸው። ሪዞርቱ በሰኔ 23 ጥቃት ሙሉ ለሙሉ መውደሙን ተከትሎ ስለነጋአቸው እያሰቡ ከሚያነቡት የሻሸመኔ ከተማ ነዋሪ መካከል እንዱ ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ሪዞርቱ ሙሉ ለሙሉ ወድሟል፤ ነገ አዲስ ተአምር ተፈጥሮ ስራ መጀመር ካልተቻለ በስተቀር ባለው ሁኔታ የእሳቸውና መሰል የሪዞርቱ ሰራተኞች ጉዳይ ያበቃለት ይመስላል።
መተዳደሪያቸው በጥበቃ ስራቸውና ከመከላከያ ሲሰናበቱ በተቆረጠላቸው ጡረታ ክፍያ በሚገኝ ገቢ የነበረው አቶ ዮናስ “እኔ እድሜዪ የገፋ ህክምና የምከታተል በመሆኑና ሌላ የምሰማራበት ሙያ የሌለኝ በመሆኑ ከአሁኑ መንገዴ ጨልሞብኛል” ይላሉ፣ አሁን ሌላ የጥበቃ ስራ ልወዳደር ብል እንኳን ካለኝ ሁኔታ አንጻር የሚሳካ አይመስለኝም ። ዘጠኝ መቶ ብር የቤት ኪራይ ፣200 ብር ለትምህርት ቤት እና በየወሩ የህክምናና ሌሎች ወጪዎች በምን ሊሸፍኑት እንደሚችሉ ገና ካሁኑ ሀሳብ ሆኖባቸዋል።
“ሪዞርቱ መውደሙን ተከትሎ ምን አልባት የነገ እጣ ፈንታቸው መለመን ሊሆን ይችላል። ምን አልባት ሪዞርቱን ያቃጠሉትና ያወደሙት አካላት ሻለቃ ሀይሌን የጎዱ ሊመስላቸው ቢችልም በእጅጉ የጎዱት እሳቸውን እና ሌሎች የሪዞርቱን ሰራተኞች መሆኑን ይናገራሉ። እሳቸው ከሪዞርቱ ብዙ ሲጠቀሙ እንደነበርና ልጆቻቸውን ከማስተማር ጀምሮ ሌሎች ወጪዎችን የሚሸፍኑት ከጥበቃ በሚያገኙት ገቢ እንደነበርም ያስረዳሉ።
አሁን ግን ስራ ሲያጡ ከእርሳቸው ባለፈ በእሳቸው ስር ያሉ ልጆቻቸውንና የሌሎች ሰራተኞች ቤተሰቦችም የሚጎዱበት መሆኑን በመግለጽ ይህ ድርጊት ሀይሌን ሳይሆን እሳቸውን መሰል ድሆችን የጎዳ አርቀው በማያስቡ ሰዎች የተፈጸመ ብቻ ሳይሆን ይህን መሰል ድርጊት በከተማዋ ሲፈጸም ለሶስተኛ ግዜ መሆኑን አሳዛኝ ነው። ኢትዮጵያ አቅዳ መስራት ሰትጀምርና ውጤት ሲጠበቅ ይህን መሰል ችግር ለሚያመጡ አካላት ፈጣሪ ልቦና እንዲሰጣቸው መንግስትም በዚህ እኩይ ተግባር የተሳተፉትን ተጠያቂ እንዲያደርግና የተጎዱ ወገኖችም ሊታገዙበት የሚችል እድል ሊመቻች እንደሚገባ አመልክተዋል።
በሁከቱ ቤታቸው ከተጎዳባቸው መካከል አንዱ የሆኑት መቶ አለቃ እንየው ፈንታዪ በበኩላቸው እንደሚሉት፣ በእለቱ የወጣቶች ጩሀት ነበር፤ ወዲያውም የግቢያችንን አጥር በማቃጠል የቤት በርና መስኮት በመሰባበር እቃዎችን ከቤት እያወጡ ማቃጠል ጀመሩ። ሁለተኛው ቡድን ደግሞ ቤቱን በእሳት ለኮሰው በዚህ ሂደት የአካባቢው ሰዎች እኔን ወደውጪ እንድወጣ በማድረግ እየተቃጠለ ያለውን ቤት ለማጥፋት ባደረጉት ጥረት ሙሉ ለሙሉ ከመውደም አዳኑልኝ።
ከተማው ከደረሰው የንብረት ውድመትና የሰው ሀይወት መጥፋት እጅጉን የሚያሳስብና በርካቶችንም ያለቤት ንብረት ያስቀረ ተግባር ነው። እኔም በውትድርና ህይወቴ ቆጥቤ የሰራኋትን ቤት በዚህ መልኩ ማጣቴ እጅጉን ጎድቶኛል። እኔ ደግሞ ጠንካራ ማህበራዊ ግንኙነት ያለኝና የሀረርጌ ተፈናቃዮች እንኳን ጥቁር ውሃ ቤት ሲሰራላቸው በቀዳሚነት ስራውን ሲያስተባብሩ ከነበሩት መካከል አንዱ እንደመሆኔ ይህ አይነት ተግባር ይፈጸምብኛል ብዬ አስቤ አላውቅም። ይሄን ያደረጉት ወጣቶችም ምንም እውቀት የሌላቸው ሲሆኑ ህብረተሰቡም ሲከላከላቸው የነበሩ ናቸው። በመሆኑም አሁንም ህብረተሰቡ ሊያጋልጣቸውና ሊያወጣቸው መንግሥትም ህጋዊ እርምጃ ሊወሰድ ይገባል።
ወይዘሮ ጫልቱ ሮባ የተባሉ የከተማዋ ነዋሪ በበኩላቸው እንደሚሉት በእለቱ ወጣቶቹ ከተማዋን ሲበጠብጡ ነበር። በሂደትም ሰው ወደመግደልና ንብረት ወደማጥፋት ተሸጋገሩ። በዚህ ሂደት የእርሳቸውንና የመቶ አለቃ እንየውን ቤትና ንብረት ለማቃጠል መጡ። እሳቸውም ይሄ የኔ የወንድሜ ነው ብለው ለማስቆም ቢሞክሩም አንቺ በገንዘብ ተገዝተሽ ነው ብለው የመቶ አለቃን ቤትና ንብረት ማቃጠል ጀመሩ። ሆኖም እኛ በክፉም በደግም አብረን የምንኖር ህዝቦች በመሆናችን የተቻለንን አደርገን እሳቱን ማጥፋት ችለናል። ይህን ያደረጉ ወጣቶች ግን ከአካባቢው ያልሆኑና የማያውቋቸው ናቸው። ህዝቡ ግን ተጎጂዎችን በማስጠለል ጨምሮ እያቀፈ ይገኛል። ለቀጣይ ግን ይህን አይነት ተግባር እንዳይፈጠር ህዝብም መንግስትም በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
የከተማዋ ነዋሪና ሽማግሌ የሆኑት አቶ አማን ገመዶ በኩላቸው ክስተቱ ሲጀመር ሀዘን የሚገልጹ ነበር የሚመስሉት። ስንወጣ ግን ንብረት እያወደሙ የሰው ህይወትም እያጠፉ መሆኑ ታየ። እንዲህ አይነት ተግባር ደግሞ በከተማዋ ታይቶ የማያውቅ ህብረተሰቡም በክፉም በደግም አብሮ የኖረና የተዋለደ ነው። ይህን ያደረጉ ወጣቶች ከገጠር የመጡና አብዛኛውም ታዳጊ ወጣቶች ሲሆኑ አብዛኛውም ይህን ያደረጉት በብሄር ብሄረሰቦች መካከል ግጭትን ለመፍጠር ባለሙ ሀይሎች ምክንያት ነው። በመሆኑም ተግባሩ የሚወገዝና ተቀባይነት የሌለው ብቻ ሳይሆን መሰል ተግባር እንዳይደገም ህዝቡም ተባብሮ ሊሰራ መንግሥትም የህግ የበላይነትን ሊያስጠብቅ ይገባል። በቀጣይም ህዝቡ የተጎዱትን በማገዝና መልሰው እንዲቋቋሙ በማድረግ የበኩሉን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የሻሸመኔ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የኢንተርፕራይዞች ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ሽብሩ ሱልጣን በበኩላቸው ፤ የሀጫሉ ሞት ድንገተኛ እንደመሆኑ ህዝቡ ሀዘኑን ለመግለጽ ወጥቷል። ከከተማው ውጪ ያሉ ወጣቶችም ወደ ከተማው መጥተዋል። ጸረ ሰላም ሀይሎች የህዝቡን ሀዘን ተገን በማድረግ የጥፋት ሴራቸውን ማከናወን ጀምረዋል።
በዚህም በተፈጠረው አደጋ ሆቴሎች መኖሪያ ቤቶች ተሽከርካሪዎችና የድርጅት ጽህፈት ቤቶችም ተቃጥለዋል። 89 ሆቴሎች 249 የመኖሪያ ቤቶች 79 ተሽከርካሪዎች፣ 36 ባጃጆች የተቃጠሉ ሲሆን 251 አባወራዎችም ተፈናቅለው በየሰው ቤትና ቤተእምነቶች ተጠልለው ይገኛሉ።
ይህ ይፈጠራል የሚል እምነት አልነበረንም። ክስተቱም ሌሊት የተፈጸመ እንደመሆኑ አስተዳደሩ ያልተዘጋጀበትና ብዛት ያለው ህዝብም ወደ ከተማ የገባበት በመሆኑ ከጭለማው ጋር ተዳምሮ የመከላከል ሂደቱን አዳጋች አድርጎታል። ከዚህ በተጨማሪ መንገዶችን እየዘጉ በብዛት የሚንቀሳቀሱ ከመሆናቸው አንጻር በሃይማኖት አባቶች ልመናም በጸጥታ ሀይሉም ትብብር ለማስቆም ባለመቻሉ ጥፋቱ ሊደርስ ችሏል። ሲነጋ ግን የመከላከያ ሰራዊት ደርሶ የጠፋው ጠፍቶ የተቀረው እንዲተርፍ የሆነው የአካባቢው ህብረተሰብ ከመከላከያ ጋር በመተባበር በመስራቱ ነው።
ሻሸመኔ የፍቅር ከተማ እንደመሆኗ የተፈጠረው ነገር የሚያሳዝን ነው። የከተማ አስተዳደሩ ግን የሚያሳዝን ነው ብሎ ዝም የሚል ሳይሆን የህግ ማስከበር ስራውን በትኩረት እያከናወነ ነው። በዚህም ከ200 በላይ ተጠርጣሪዎቸ በቁጥጥር ስር ውለዋል። በቀጣይም የህብረተሰቡ ጥቆማ እየመጣ አንደመሆኑ ያንን መሰረት ያደረገ ተጠያቂ የማድረግ ስራዎች የሚከናወኑ ይሆናል። ከዚህ በተጓዳኝ የተጎዱ ወገኖችን መልሶ የማቋቋም ተግባራት ይከናወናሉ ብለዋል።
Ethiopia press Agency/ኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት
በወንድሰን ሽመልስ
ፎቶ ዳኜ አበራ
(አዲስ ዘመን ሐምሌ 3 ቀን 2012 ዓ.ም)
ተጨማሪ ያንብቡ:  የሰማያዊ ታርቲ የስብሰባ ጥሪ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.