ከሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ የታሰሩ ሰዎች ቁጥር 4988 ደረሰ

military 1ከድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ 4988 ሰዎች መታሰራቸውን የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ተናግረዋል። በአዲስ አበባ ከታሰሩ ሰዎች መካከል የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ፣ የህወሓት እና የባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ ፓርቲዎች አመራሮች ይገኙበታል።

በኢትዮጵያ ድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ከተገደለ በኋላ የታሰሩ ሰዎች ቁጥር 4988 መድረሱን የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ ተናገሩ። በድምፃዊው ግድያ እጁ አለበት ተብሎ ይፈለግ የነበረው ሶስተኛ ተጠርጣሪ በቁጥጥር ሥር መዋሉን የኢትዮጵያ መንግሥት አስታወቋል።

ሶስተኛው ተጠርጣሪ ከበደ ገመቹ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ሸዋ ዞን አደኣ አካባቢ በቁጥጥር ሥር መዋሉን ትናንት ማምሻውን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማስታወቁን የገዢው ፓርቲ ንብረት የሆነው ራዲዮ ፋና ዘግቧል። ጠቅላይ አቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ ሐጫሉ ሁንዴሳን በቀጥታ ተኩሶ ገድሏል የተባለ ተጠርጣሪ እና ተባባሪው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ቀደም ብለው ትናንት በሰጡት መግለጫ ተናግረው ነበር። በጠቅላይ አቃቤ ሕግ አዳነች አቤቤ መግለጫ መሠረት ጥላሁን ያሚ የተባለው ግለሰብ ድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳን ባለፈው ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ተኩሶ በመግደል ተጠርጥሯል። አብዲ አለማየሁ የተባለ ሌላ ተጠርጣሪ በግድያው እጁ አለበት የተባለ ሲሆን በቁጥጥር ሥር መዋሉን ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጓ ገልጸዋል።

ከድምፃዊ ሐጫሉ ሁንዴሳ ግድያ በኋላ በተቀሰቀሰ አለመረጋጋት የበርካቶች ሕይወት ጠፍቷል። ስድስት ፖሊሶች እና አምስት የሚሊሺያ ባልደረቦችን ጨምሮ 167 ሰዎች መገደላቸውን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ በትናንትናው መግለጫቸው ተናግረዋል።

ባለፈው ረቡዕ የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ተጠባባቂ ኮሚሽነር ሙስጠፋ ከድር በኦሮሚያ ክልል ብቻ 215 ሰላማዊ ሰዎች እና ዘጠኝ የጸጥታ አስከባሪዎች በአጠቃላይ 224 ሰዎች መገደላቸውን ዋልታ ለተባለው የቴሌቭዥን ጣቢያ መናገራቸውን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቦ ነበር። ባለሥልጣናቱ ባለፈው ሳምንት እንዳሉት ሌሎች አስር ሰዎች ከድምፃዊው ሞት በኋላ በአዲስ አበባ ተገድለዋል።

የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል አራርሳ መርዳሳ በትናንትናው ዕለት በሰጡት መግለጫ 523 የግለሰቦች መኖሪያ ቤቶች፣ 195 ሆቴሎች፣ 232 የንግድ ቤቶች፣ 8 የተለያዩ ፋብሪካዎች 273 የግል እና የመንግሥት ተሽከርካሪዎች እና ሞተር ሳይክሎች “ጉዳት” እንደደረሰባቸው ተናግረዋል።

“እዚህ ውስጥ የተሳተፉ የመንግሥት መዋቅር ወደ 44 የሚሆኑ፤ የፖሊስ ኃይል 20 ከተለያዩ ኅብረተሰብ ወደ 4924 የሚሆኑ በአጠቃላይ 4988 ግለሰቦች በዚህ ጥፋት ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለዋል” ሲሉ ተናግረዋል።

ከድምፃዊው ግድያ በኋላ በአዲስ አበባ ከታሰሩ መካከል የኦሮሞ ፌድራሊስት ኮንግረስ አመራሮች የሆኑት አቶ ጃዋር መሐመድ እና አቶ በቀለ ገርባ ይገኙበታል። የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ሥራ አስኪያጅ አቶ ግርማ ጉተማን ጨምሮ የቴሌቭዥን ጣቢያው ሰራተኞች ፤ባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የተባለው ፓርቲ አመራሮች የሆኑት አቶ እስክንድር ነጋ እና የአቶ ስንታየሁ ቸኮልም እስር ላይ ናቸው።

የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ የአዲስ አበባ ጽህፈት ኃላፊ እና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ተወልደ ገብረ ፃዲቅ እና የኢትዮጵያ የፍትሕ እና የሕግ ምርምር እና ስልጠና ኢንስቲትዩት ምክትል ዳይሬክተር የነበሩት አቶ ተስፋለም ይሕደጎ መታሰራቸው ተሰምቷል።

እሸቴ በቀለ

DW

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.