ባንዲራ (ዘ-ጌርሣም)

ETHflagየሀገር ልዕልና ማስጠሪያ
የነፃነት ዘመን ማስቆጠሪያ
ለህዝብ አብሮ መኖር በጋራ
በደስታም ይሁን በመከራ
የአንድነትና የአኩልነት መንበር
የህዝብ ውህደትና ስብጥር
ከማንም ለማንም በስጡታ ያልተገኘሽ
የጋራ እንጅ የግል ያልሆንሽ
ለዜጎችሽ መለያ ምልክት ሆነሽ
አረንጓዴው ልምላሜሽ
ብጫው ተስፋሽ
ቀዩ ደምሽ
በመስዋዕትነት የተገኘሽ
እንች ባንዲራ
የታሪክ ባለአደራ
የሀገር ድንበር አስከባሪ
የህዝብ መብትና ኩራት አብሳሪ
የዋጋ ተመን ያልወጣልሽ
ማንም በፍላጎቱ የማይቀይርሽ
የህዝብና የሃገር የጋራ ሀብት የሆንሽ
ዜጎችን በደምና በሥጋ አስተሳስረሽ
በኩራት ሰገነት ላይ ያስቀመጥሽ
የሀገር አምባሳደር
የዜግነት መለያ ስንክሳር
አንድም ሦስትም ሕብርም የሆንሽ
ለነፃነት በአርያነት የታወቅሽ
የዓለም ህዝቦችና ሀገሮች የሚያከብሩሽ
ከፍ አርገው በክብር የሚያውለበልቡሽ
ባንዲራ የጦር አበጋዝ መሪ
የክተት አዋጅ አስነጋሪ
የህዝብ ስሜት ሰላቢ
የተበተነዉን ሰብሳቢ
ሰማዕታትን አስታዋሽና አዘካሪ
የስማ በለው ነጋሪት አስመችና አስነጋሪ
የጀግናን ስሜት ኮርኳሪ
የጠላትን ሰፈር አሸባሪ
ህዝብን አቆራኝ ሰንሰለት
የማትከፋፈይ በሃይማኖት
የማትይ ወንድ ወይም ሴት
ሁሉን ሰብሳቢ በአንድ ጥላ
የመኖር ተስፋ ከለላ
ለማንም ያልሆንሽ የጡት እናት
የጋራ እንጅ የሁሉም ሀብትና ኩራት
ለቅርጫ የማትቀርቢ
ህዝብ ለህዝብ አቀራራቢ
ነችና ይህች ባንዲራ የሁላችን ኩራት
ተገቢ ነው ልንሞትላትና ልናከብራት
ባንዲራችን የጋራ ሀብታችን ናት
መታወቂያችን
ለኢትዮጵያዊነታችን
ኑሪልን ለክብራችን

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.