ኢትዮጵያዊነት – ጌታቸው ለገሰ

Ethiopiawinetእንደወጣትነቱ ያሸተ … በአስተዋይነቱ የጎለመሰ
እንደ አዛውንትነቱ የሰከነ … ማክበር መከበርን የተላበሰ
ከንቱነትን … ክፋት … ምቀኝነትን … አርቆ የቀበረ
በማትበትነው ድርና ማግ የተሳሰረ፤

ከመኖሬ ግንድ … ከገናናው ማንነቴ
እንደ ጠዋት ጤዛ ለማያረፋፍድ ድንፋታ ያለመፈታቴ
ሚስጥሩን ልንገርህ ? የጸና ነው መሰረቴ
በማይሞት መንፈስ የተገነባ … አለምአቀፉ ማንነቴ
አዎ አንድ እና አንድ ነው ኢ!ት!ዮ!ጵ!ያ!ዊ!ነ!ቴ! … ኢትዮጵያዊነቴ።

ከአየር ከእስትንፋሱ … መቼም የማትሸሸው
የቀሰርከውን ጣት … ጠብበህ የማትሸሽገው
ምላስና ልብህ ባልተገናኙበት … ክደህ የማትክደው
ለቅርቡም ለሩቁም … አፍሪካ … እስያ ሌላም ለምትለው
በህብረ ቀለም አምሮ … ለነጻነት ኩራት ፋና ወጊ የሆነው
እኔም አላስምለህ … አንተም አትክደው
አለምም መስክሯል … ኢትዮጵያዊነት ነው።

የስልጣኔውን ስረመሰረቱን
የስነ ህንጻውን … የፊደሉን ግብአቱን
ሃሪቲ … ጤናአዳም … የነጭ ሽንኩርቱን
ለዘመኑ ክኒን … የፍውሰት ብልሃቱን፤

በድንቅነሽ እየታጀብን … ለፍጥረታት መገኘቱ
በአትንኩኝ ባይነት … የአያት የቅድመ አያት ጀግንነቱ
ለሁሉ የምትበቃ እናት ሃገር ወርሶ መኩራራቱ
ኢትዮጵያዊነት ነው …. አዎ ኢትዮጵያዊነት ነው ለዚህ ሁሉ መሰረቱ።

በከርሰ ምድሯ ያልተነካ ሃብቷ ታምቆ
ለሌላው ተርፎ ገነት የሚያደርግ ወንዟ የኛ ሆኖ… ከእኛ ርቆ
በ ፟ይውደም! ፟ጩሀት ውሀ እየጠማን ላንቃችን ደርቆ
ዘመናትን ገፍተን …. ዛሬም እንደ ትናንቱ ጦር ተሰብቆ፤

ለእኔም ለአንተም …. ስለምትበቃ ለሁላችንም በምትተርፈው
እጅህን ከብረት አንሳና ሞፈር ቀንበር ላይ አውለው
ጣትህን መቀሰር አቁመህ ወንድምህን ያዘው እቀፈው
የአያቶችህን አላውቅም ብለህ ላይካድ ብትክደው፤

አባቶቻችን … እናቶቻችን …. ዛሬም እሚኖሩት
አንዱ አንዱን አቅፎ ተደጋግፈው ነው በቀዬው ያሉት
ወጥረን ይዘን ብንጓተተው በማይበጠስ ጥብቅ ማንነት

ጠብበው አይደለም… በትልቁ ነው
አምሮና ደምቆ በተገመደው ኢትዮጵያዊነት።
የአረንጓዴው ……
የቢጫው ……
የቀዩ ….. የቀስተደመናው ጥምረተ ግምጃው
የአርነት ሰንደቅ … የግፉአን ከፍታ ዝማሬው
ጥበብ ነው ….የእምነት የአስተሳሰብ የአንድነታችን መገመጃው።

ሰፍረህ … ቆንጥረህ… ቅናሽ ቅንስናሽ አርገህ የማትሰጠኝ
ኮሽ ሲል ብቻ ሰንደቅ አንስተህ የማትደልለኝ
ጠላት ሲታገድ …. ሆ ብለህ ወጥተህ የማትሸልመኝ፤
ስሩ … ከሩቅ ነው ከካምና ሴም የተመዘዘ
መድረሻውማ የትዬለሌ … ከአድማስ ማዶ ጥግ … ምድርን የያዘ።
ለምድር ካስማ … አለምን በጥበቡ ያስደመማት
ዛሬ ላይ እኛ ካልጠፋ ብለን …
ልንንድ …
ልናፈርስ …
ልንጎትት …. ከሰማየ ሰማያት
ባናውቅ … ብንከድ… ነው እንጂ ጥብቅ የሆነውን ማንነት
በአክሱም … በፋሲል … በላሊበላ ስረመሰረት
የተገነባው ጽኑውን ማንነት፤
የሐረር ግንብ … የኮንሶው መልክዓ ምድር
የጢያ መስህብ … የትክል ድንጋዮቹ ድርድር
የሶፍ ዑመር ዋሾች … የማንክደው ምስክር፤
የአብሮነት … ባህሉና እምነት ተቀምሮለት
በሸንጎ … በገዳው
በመስቀል … ኢሬቻው
የጠምበለላው … የአሸንዳው
ማህተም አለው … ስሙ ጎልቶ የተጻፈበት
“አንቺ” ም “አንተ”ም … አይደለም “አንቱ” የሚባልበት ነው ኢ!ት!ዮ!ጵ!ያ!ዊ!ነ!ት!!!
አክሱማዊነትን በከዱ
ማወቅ ባልፈለጉ … ባልተረዱ
ዛሬ ኢትዮጵያዊነትን … ሊንዱ
ሲያነድዱ … ሲያስነድዱ፤
ለዛሬው እኔነቱ … አጥንት ከስክሰው
በደም ግብር … ስጋቸውን ከምድሪቷ ለውሰው
ማይጨው … አድዋ…. ላይ በክብር በጀግንነት አልፈው፤
እነ ምኒልክ … እነመይሳው
አሉላ … ዮሃንስ … ባልቻ አባነፍሶን ትረሳው?
ዑመር ሰመተር …. በላይ ዘለቀን
ካዖ ጦናን … ደጃች ገረሱን … ምለህ ትክደው?
ለ እኔና ለአንተ … ኢትዮጵያን ሲሉ ጥንት የተሰዉት
በየድንበሩ ደረታቸውን ለጦር የሰጡት
ነክሰህ ባትክደው … አውቀህ ባታውቅም
የአባት የእናቱን … የቄስ የሼኩን
የእህት ወንድምን … የጨቅላ ህጻን … አንገት አልቀሉም ።
አይ መርገምት! … ያ ክቡር ምድር አንተን አብቅሎ
ህብር … ግምጃውን … የአባቶቹን ግንድ ገዝግዞ አስጥሎ
ለዚህ ብንደርስ …. ሰማይ ጉም አዝሎ
የንጹሃንን እንባ አንጠልጥሎ
በአያት ቅድመ አያት … በምንጅላቴ እምላለሁኝ አለን! … አንፈርስም !
ጠብባ … ኮስምና …. ሰፍታ… አንሰራርታ… ከእቅፏ አንሸሽም።
አንተም ታውቃለህ …
እናት…
አንድነት …
ኢትዮጵያዊነት
ትናንትም ነበር፣ ዛሬም ይኖራል፣

የነገን ፋናም … ሰንደቅ… አርማውን
ከፍ አድርጎልን …. ያሻግረናል፤
አሜን ! ባትልም ያባቶች ምህላ መቼ ጠብ ይላል
ሲጎተት … ይጠብቃል
ሲጦዝ ሲወጠርም … ጭራሽ ይገመዳል
ስትቆርጠው … ይቀጠላል
ስትረግም … ይመረቃል
ኢትዮጵያዊነት ከፍ ከፍ ብሎ … በክብር ይኖራል።
የ “ይሓ’’ እና የ “ደአማት’’… ስርወ መንግስት
ከአክሱም …. ዘመን በፊት
የ ‘’ጉሎ’’ ‘’መኸዳዋ’’ን … የ ’’ሳባ’’ … (የማክዳንና የአዜብን)
ከክርስቶስ ልደት የቀደመና … 800 አመት የዘለቀውን
በ “ኢትዮጵስ” … ‘’ኢትዮጵያ’’ ተብላ የኖረችውን
በ”ሄሮዶቱስ” … በ”ቶራህ” …. የተከተበውን
ከ 40 ጊዜ በላይ ስሟ የተጠራውን፤
ነጉስ ‘’ቲርሃቅ’’ ግብጽ ድረስ ዘልቆ ያስተዳደረበት(690 __ 664 ዓ.ዓ. ን እንመልከት)
‘’አርቴክስ’’ ከህንድ እስከ ኢትዮጵያ የገነነበት (መጽሃፈ አስቴር)
127 አገሮች ላይ የነገሰበት
…. ሌላም ሌላም … ማስረጃ ያለበት
ወዴት ወዴት ነው …..ኧረ ወዴት ነው የሚገፋበት?
ወደ መቶ አመት የወረደና … አራት ሺህን … የሚካድበት
ገፍተህ ላትገፋው …. አትገፋፋ፣ መቸም አይጠፋ ኢትዮጵያዊነት!
የሺህዎች አመታት … የካበተ ባህሉን…. ልምዱንና እምነቱን
የተከበረውን … የሚታፈረውን
ቀንዓዊነቱን … ፍትሃዊነቱን
ሁሉም በየእምነቱ … በአንድ ላይ ጸሎቱን
የኛን ሊቃውንቶች ካልከኝ አይሰሙ፣ … ያንዬም በዘራቸው ከተጠረጠሩ
እንግዲያማ እንካልኝ ….. ከግሪክ መቃብር
‘’ሆሜር’’፣ “ሔሮዶቱስ”፣ “ፕሊኒ” ም … ይጠሩ
ኢትዮጵያዊነቴን … ኢትዮጵያዊነትክን እንዲመሰክሩ።
ከላይ የተሰጠን ፀጋ … በምንም የማንደራደረው
እንደነሚጡ በ”ጨዋታው ፈረሰ” … የማንበተነው
በነእንቶኔ … የአንድ ትውልድ እድሜ ትርክት የማንመነዝረው
ስንፈልግ ለብሰን … ሳንፈልግ የምናወልቀው
አይደለም ! … መሰረታችን ጥልቅ … ፅኑ ነው።
የእኩልነት …. የአብሮነት … ግምድ አውደ ምህረት
ታይቶ … ተብሎ… የማይጠገብ በትእግስት የሰከነ ማንነት
ምድሪቷም ኢትዮጵያ … መንፈሷም ኢትዮጵያዊነት
አዎ ! የእኛ ክብረት ነው … አንቱ የምንለው ኢ!ት!ዮ!ጵ!ያ!ዊ!ነ!ት! ኢትዮጵያዊነት
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.