/

የመለስ ራዕይና የአሻንጉሊቶች ነገር የእነ እስክንድርም ጉዳይ – አሁንገና ዓለማየሁ

melesየመለስ ራዕይ አስቀጣዮች ከሸገርና ከመቀሌ ሆነው ራዕዩን በማስቀጠል እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ሲጣሉ ተመሳስሏቸው ያላጥወለወለን ካለን ባስነሱት አቧራ ምክንያት ልብ ብለን ያላስተዋልናቸውን ብቻ ነው። የቋንቋ ለውጡም ሸውዶን ይሆናል።  መለስ እንደሞተ ራዕዩን እናስቀጥላለን እያሉ በሦስት ቋንቋ (አማረኛ፣ ኦሮምኛና ትግሪኛ) ሲፎክሩ ለይስሙላ የሚጮኹ እንጂ የገዛ ግልገል ካድሬዎቹም እንኳን ያን የበከተ፣ ሀገር የሚከፋፍል፣ ዘረኛ እንስሳዊ ሥርዓት ለማስቀጠል ሊያልሙ ቀርቶ በልባቸው ‘ተገላገልን!’ ብለው እፎይ ያሉ ነበር የሚመስለኝ። ከቴም ያንን ሀገር በታኝ ሰነድ ወርሰው ይሟሟቱለታል፣ መለስ ሀገር ያስተዳደረበትን በፍትሕ የማላገጥ ዘይቤ ከነድርብ ሰረዙ ይቀዳሉ የሚል ግምት አልነበረኝም።

እንዲህ ያለ መመሳሰል ያስደነግጣል። መለስ ስልጣን እንደያዘ ከሻዕቢያ ጋር ያደርገው የነበረ ሽርሙጥና (ይቅርታ ከበድ ያለ ቃል ስላጣሁለት ነው)እነ ዐቢይ ከነጃዋር ጋር ካደረጉት ጋር ፍጹም ተመሳሳይ ነበር። መለስ ሻዕቢያዎችን ሀገራችን አይደለችም ባሏት ኢትዮጵያ ላይ አዛኝ ናዛዥ፣ የፈለጉትን አሳሪና ገዳይ የፈለጉትን ሀብት ጫኚ አድርጓቸው ነበር።  ሲጣሉ ደግሞ …. ታውቁታላችሁ። እነጃዋርም ከፍርድ ነጻ ሆነው ዘቅዝቀው ሲያሰቅሉ፣ በቁም ሲያቃጥሉ፣ ከታትፈው ሲያስበሉ ከርመዋል። መለስና የመንፈስ ልጆቹ ጠላቴ ባሉት ላይ ሲዘምቱም ተመሳሳይነት አላቸው። መለስና ተማሪዎቹ ግጥሚያው ቦክስ ቢሆን እነሱ ግን ከጨዋታው ሕግ ውጪ፣ ከጩቤ አንስቶ ቦምብና ሮኬት ከመጠቀም ወደ ኋላ አይሉም።

በመሆኑም በእነ እስክንድር ላይ በአቃቤ ሕጓ አፈ ቀላጤነት በመገናኛ ብዙሃን የተደረደረው ቅጥፈታዊ ክስ የመለስን የቅንጅቶች ክስ የሚያስታውስ ቀፋፊ፣ እና ከሳሽን የሚያስገምት፣ አድማጩን በንቀት የሚሳደብ ነው። እስክንድር ስለ ቄሮ በጓዳ እና በሹክሹክታ ሳይሆን የተናገረው በአደባባይ ነበረና ሁላችንም ሰምተነዋል። አቃቤ ሕጓ በአደባባይ እንደ እነ መለስ፣ እንደ እነ ስዩም የቅጥፈት ንግግር ተናግራለች። ኦሮሞ አይገዛንም ምናምን አሉ የሚል ነገር ቀባጥራለች። ከኦኤምኤን ዘረኛ ቅስቀሳ ምን ልዩነት አለው ይሄ? በለውጡ ሰሞን በንግግራቸው ከወደድኳቸው መሪዎች አዳነች አበቤ ዋናዋ ነበረች። ያሳዝናል። ዐቢይ ኦሮሞ መኖኑን ብቻ ሳይሆን የኦሮሞ ፓርቲ ሊቀመንበር መሆኑንም ጭምር እያወቀ የአዲስ አበባ ሕዝብ ከፍተኛ ድጋፍና አቀባበል ነው ያደረገለት። መንግሥቱ ኃይለማርያም ደርግን በመሠረቱ ወታደሮች ተመርጦ ነው የተሾመው። ኦሮሞ ነው ወይም ቀለሙ ጠቆረ አላሉም መሪያቸው ሲያደርጉት። ጨፍጫፊ ሆኖ ራሱን እስኪያስጠላ ድረስ፣ በኋላ የጨፈጨፋቸው ወጣቶች ሳይቀር እየዘለሉ ያቅፉት ነበር። ጎጠኞች ሌላውን ኢትዮጵያዊ በነሱ ዘረኛ መሥፈርት መለካት ይወዳሉ።

እነዚህ ጎሰኛ ባለሥልጣናት ግን  ዋናው አላማቸው በሥልጣን ለመቆየት ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ የምትባለውን ሀገርና ፍትሕ የሚባለውን እሳቤ ማዋረድ ይመስላል። ይሄንን ጥምር ተመሳስሎ ስናስብ እነ ዶ/ር ዐቢይ ፍትሐዊ ምርጫ አድርገው ሥልጣን ያስረክባሉ የሚል ብናኝ የዋሕነት ቀርቶን ከነበረ አሁን ተንኖ ይጠፋል። እኔ በግሌ ምርጫ የሚባለው ነገር ብዙ ንጹሐን የሚገበሩበት አስፈሪ ጣዖት ነው የሚመስለኝ። ሆኖም ብዙ የምርጫንና የዲሞክራሲን ጨዋታ አስፈላጊነት እና ጠቃሚነት ከልብ የሚያምኑበት ስላሉ ከወዲሁ ግምታቸውን አስተካክለው ቢቀመጡ ጥሩ ነው።  እንደ እኔ በጎሳ ሕገመንግሥት ስር ምርጫ ምርጫ እያልን የንጹሐን ደም የሚገበርበት ጨዋታ ከምንጫወት ቁርጡን ነግረውን ነግሺያለሁ ብለው ቢገዙን ይሻላል። በንግሥና አገዛዝ 3000 ዘመን ኖረናልና። ለነገሩ ዶክተር ዐቢይ ቀላቀለው እንጂ (አንዴ ንጉሥ ነኝ አንዴ ሥልጣኑን በምርጫ ውሰዱት እያለ) ዳር ዳሩን ነግሮናል። ዐይኑም የሚያማትርበት የዘመን ርቀት እውነቱን ያሳብቃል።

እኔ ቄሮ፣ ፋኖ የሚባሉ ቡድኖች ለበዓሉ ድምቀት (ለለውጡ አጀብ) ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረከቱ ቢሆንም በዋናነት ለውጡ (የወያኔ ማፈግፈግ)የግብጽና የምዕራባውያን የስለላ ድርጅቶች ቅንጅት ውጤት ነው  የሚል አረዳድ ነው ያለኝ።  በመሆኑም ሕወሃት ብሩን ይዛ ስትሰወር አሜሪካ በአረቦች አቀባይነት ለነዶክተር ዐቢይ የነፍስ ማቆያዋን ጥቂት ቢልዮኖች እንደ “ሰጠች” ይገባኛል። There is no freee lunch in America የሚሉት ወዳጆቻችንም በሳምንታት ጊዜ ውስጥ አዲስ አበባ ተከሥተው ቻይናን በሚተኩባቸው ዘርፎችና በሌሎችም የኢንቨስትመንት መስኮች አዳዲስ ፊርማና መሓላዎች የተቀበሉ ይመስለኛል። 60 ገደማ ኩባንያዎችን የሚወክለውን በለውጡ ማግሥት ከች ያለ የአሜሪካ የኩባንያዎች ቡድን ያስታውሷል።  የአፍሪካ ሀገሮችና ሌሎችም ባለማደግ ላይ ያሉ ሀገራት በአሻንጉሊት መሪዎች እንደሚመሩ ይታወቃል። ይሄ አሻንጉሊት የሚለው አባባል የመጣው በገመድና በሌላ ነገር እየተሳቡ እንቅስቃሴ የሚያደርጉና ትርኢት የሚያሳዩ አሻንጉሊቶችን ወይም ፓፔቶችን መሰረት አድርጎ ነው። ታድያ አሻንጉሊቱ የእውነት እንዲመስል (የሚስቡትንም ክሮች ለመደበቅ) የማለባበስና የማዘናነጥ የማሳመር ተግባራት ይከናወናሉ። ዛሬ ደግሞ በሪሞት ማንቀሳቀስ ይቻላል። እድሜ ለቴክኖሎጂ።

ከምዕራባውያን አኳያ በአሻንጉሊት መምራት የሚፈለግበት ምክንያት ዲሞክራሲ ቅብጥርሴ የሚባለው ነገር የእውነት ከሆነና ምዕራባውያን ለጥቅማቸው በሚያደርጉት ጥያቄ ላይ ፓርላማ፣ ምክር ቤት ምናምን የሚወያይበት ከሆነ ፈጣን ውሳኔ ወይም አርኪ ውሳኔ ላያገኙ እና እንዲያውም በተቃራኒው ለሀገሩ ሕዝብ የሚበጅ ተቃዋሚ ውሳኔ ሊገጥማቸው ይችላል።  ከዚህ ይልቅ ከአንድ አሻንጉሊት ጋር ተደራድረው ውል መጨረስን ይመርጣሉ።

የአሻንጉሊት ነገርን በራሳችን ሀገር ለመረዳት መለስ ዜናዊ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የደቡብ፣ የአፋር እና ሌላም ክልል አሻንጉሊቶችን ሾሞ ፍጹም አምባገነናዊ ሥርዓትን ለማስፈን እንዴት ይጠቀምባቸው እንደነበር ማስታወስ በቂ ነው። ይገርማል የአሻንጉሊትም አሻንጉሊት! ዛሬም ብልጽግና አሻንጉሊቶች ለመፈብረክ በደቡብ የክልል እንሁን ጥያቄን ራሱ ኮሚቴ ፈጥሮና በጀት መድቦ እያካሄደው ነው የሚል ሀሜት አለ። ከአህያ የዋለች ጊደር የሚባል ነገር ስላለ ብዙም አይገርምም። የትናንቱ አሻንጉሊት ዛሬ ባሻንጉሊት ይጫወታል ማለት ነው (ካሻንጉሊትነቱ ሳይወጣ)።

እስኪ የአፍሪካ አሻንጉሊት መሪዎችን አማካይ የግዛት ዘመን እናስላ። ሁሉም በቀጥታ ለኢኮኖሚ ዘረፋ ብቻ የሚያገለግሉ ሳይሆን አንዳንዶቹ ለከባቢው ጂኦ ፖለቲካዊ አፈና የሚጠቅሙ ናቸው  (ምሳሌ ኢሳይያስ — ለኢትዮጵያ በሮች በመወተፊያነት)

ስም                              የግዛት ዘመን                                                                   ሀገር

ሙባራክ                        30 ዓመት  (አገልግሎቱ ያበቃ)                                     ግብጽ

አል በሺር                        30 ዓመት          (አገልግሎቱ ያበቃ)                            ሱዳን

ካጋሜ                            30 ዓመት            (አገልግሎቱ የቀጠለ)                        ሩዋንዳ

መለስ                            22 ዓመት (አገልግሎቱ በሞቱ የተቋረጠ)                       ኢትዮጵያ

ኢህአዴግ                       30 ዓመት (አገልግሎቱ ቆዳ ቀይሮ የቀጠለ የሚመስል)   ኢትዮጵያ

ኢሳይያስ                        30 ዓመት (አገልግሎቱ የቀጠለ)                                    ኤርትራ

ሙሴቪኒ                       34 ዓመት (አገልግሎቱ የቀጠለ)                                     ዩጋንዳ

ቴዎዶሮ ምባሶጎ               41 ዓመት (አገልግሎቱ የቀጠለ)                                    ኢ. ጊኒ

ዶ ሳንቶስ                       38 ዓመት (አገልግሎቱ ያበቃ)                                       አንጎላ

ሞቡቱ                           32 ዓመት (አገልግሎቱ ያበቃ)                                      ኮንጎ (ዲሪ)

ሳኒ አባቻ                        5 ዓመት (አገልግሎቱ በሞቱ የተቋረጠ)                         ናይጄሪያ

ብሌዝ ኮምፓውሬ           27 አመት (አገልግሎቱም ያቋረጠ)                                ቡርኪናፋሶ

 

እንደምታዩት አማካዩን የአሻንጉሊት የግዛት ዘመን ለማስላት የሚመች ባይሆንም(በሞት ያመለጡ ስላሉ) 25 ዓመት ያነሰ እንደማይሆን ደምሳሳ ግምት መስጠት ይቻላል።  እግዚኦ!በመለስ ራዕይ አስቀጣዮች ሌላ 25 ዓመት! ፈጣሪ ምን አልነው? አያድርግብን። ወይ ልቡና ይስጥልን ወይ ልቡና ያለው ይስጠን።

ይቅርታ እንግዲህ ተስፋ ለማስቆረጥ ሳይሆን ቁርጣችንን አውቀን ራሳችንን ሳናታልል በትክክለኛው ቅንብብ ለሚያስፈልገው ሁሉ እንድንዘጋጅ ለማለት ነው። ይሄን ዓይነቱ አመለካከት የሚከተለውን ግጥም ዓይነት ስሜት ይፈጥርብኛል።

ስንቄን አጮልቄ

አስቀድሜ አይቼ

ጉዞው ረዘመብኝ ዛሉ ጉልበቶቼ።

አገልግሉን ባላይ ምን እንደቋጠረ

ባልከበደ ነበር ጉዞው ባልጠጠረ።

ቢሆንም ዛሬ ያለው የቀጠናው ሁኔታም ሆነ አጠቃላዩ የዓለም ሁኔታ እጅግ ተለዋዋጭ በመሆኑ መጪው ዘመን ያለፉትን 50ና እና 60 ዓመታት ይመስላል ለማለት ይከብዳል። ዲሞክራሲ ግን እንኳን ሊስፋፋ ከዚህ በፊትም ሰፈኖባቸዋል በሚባሉ ሀገራት የመቀጨጭ አደጋ ነው እያጋጠመው የመጣው። በፊት በሽብር አሁን ደግሞ በወረርሽኝ ሥጋት ተጠቅሞ የሰዎችን እንቅስቃሴ ለመገደብ፣ ለመቆጣጠር ያለመ አካሄድ እየተስተዋለ እንደሆነ የሚጠቁሙ ብዙ ነገሮች አሉ።

እናቴ ባሰበችው ሳይሆን ሚስቴ ባሰበችው አውለኝ ብሏልና ሰውዬው እዚህ እንደ “ተሟረተው” ሳይሆን ያልታሰበውን ያልተገመተውን መልካሙን ያጋጥመን። ለሱ ምን ይሳነዋል?

ነገሬን በዚች ግጥም ልቋጭ

የምርጫ ቅስቀሳ በኮሮና ቀርቷል

ለምርጫ ክስከሳው ማድቀቁ ግን ደርቷል።

በዘረኞች ጭፍጨፋ የተገደሉትን ንጹሐን ነፍስ ይማርልን። የተረፉትን ያጽናናልን። ሀብት ንብረት የወደመባቸውን፣ ባንድ አዳር ቤት የለሽ፣ ንብረት የለሽ የሆኑትን ፈጣሪ ጉዳታቸውን ይመልከት። ለጎሳ ነጋዴ ባለሥልጣናትና ተቃዋሚዎች ወይ ልቡና ወይ ፍርድ ይስጥልን። ግብጽና ወኪሎቿን ያስታግስልን።

አሁንገና ዓለማየሁ

 


ለወያኔ አዛውንት
አለቀቃችሁም የመግደል አባዜ
ንስሐ አይሻልም በቀራችሁ ጊዜ?
ትናንት በልጅነት አምሮባችሁ ትግሉ
በጎልማሳ እድሜም በቅታችሁ ለድሉ
ያንን ቀን ፈጣሪ ለእናንተ ብሎት
በላችሁ፤ ጠጣችሁ፤ ኖራችሁ በድሎት
ያማራችሁ ነገር ሁሉ እየተሟላ
ፈልጣችሁ ቆርጣችሁ
ረግጣችሁ ገዛችሁ፤ ከእንግዲህ በኋላ
የቀረውን እድሜ የእግዜር እህል ውሃ
ለእርቅ ብታውሉት ለኃጢአት ንስሐ
አይሻላችሁም ከመውረድ በረሃ?
በሰባ ሰማንያ በእርጅና ወራት
እልቂት ከመደገስ ክተትን ከመጥራት?
የንጹሐኑ ደም የድሆቹ እንባ ቢነሳችሁ ሰላም
ይቅር ባይ ነው አምላክ ፈጥሮ ሰው አይጠላም
ይልቅ
ለግፍና በደል የእስካሁኑ ይብቃ
አትጨምሩበት ባለቀች ደቂቃ
ጭራሽ ሳትወሰድ ነፍሳችሁ ተነጥቃ
ከዘራፍ ዘራፉ ከዘገር ንቅነቃ
ንስሐው ይሻላል ምሕረቱን ጥየቃ።

አሁንገና ዓለማየሁ


ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.