መንግስት እና ህገ- መንግስታዊ ስርዓት – ሀይማኖት መሐሪ

Oromo 8

በማደግ ላይ ያሉ እና ባደጉት አገራት ሁሉም የፖለቶካ ድርጅቶች ፕሮግራማቸውን ለህብረተሰቡ በጽሁፍ፣ በቴሌቭዥን በሬድዮ እና መሰል በሆኑ የብዙኃን መገናኛዎች በመጠቀም የፖለቲካ ፕሮግራማቸውን ለህዝብ ያስተዋውቃሉ። ይህንን በሰላማዊ ውይይት በማድረግ፣ በሃሳብ በመሞገት እና ሃሳብን በሃሳብ በማሸነፍ መልዕክታቸውን ለህዝብ ያደርሳሉ። ህዝቡም ውይይቶቹን በጽሞና በመከታተል፣በማድመጥና ንቁ ተሳትፎ በማድረግ ይጠቅመኛል ብሎ ያመነበትን የፖለቲካ ፓርቲ ይመርጣል ወይም ድምጹን ይሰጣል። እነዚህ በሕዝብ የተመረጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች(የህዝብ እንደራሲዎች) አገርን ለመምራት እና ህዝብን ለማገልገል እንዲያስችል ህገ- መንግስት ያረቃሉ አልያም ያሻሽላሉ። በዚህ መሰረት ህዝብን እያገለገሉ የአገልግሎት ዘመናቸው ሲያልቅ እና ተመሳሳይ ምርጫዎች እየተደረጉ ስልጣናቸውን በሰላማዊ መንገድ ያስረክባሉ። ማናቸውም የህዝብ እንደራሴዎች፣ ሚኒስትሮች፣ ጠቅላይ ሚንስትሩን እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት  ባለስልጣናት ለህገ መንግስቱ እና ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱ ብቻ ተገዢ ይሆናሉ። ህግን የሚተላለፍ ግለሰብም ይሁን ቡድን በህግ አግባብነት ተጠያቂ ይሆናሉ። በዚህ መሰረት መንግስት እና ህዝብ የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታ በመሆን ልጆቻቸውን በሀገር ፍቅር እና ኩራት እየቀረጹ ሀገርን እና ለትውልድ ያስተላልፋሉ።

 

ይህ በእንዲህ እንዳለ አንባቢውን ወደ አገራችን ኢትዮጵያ መውሰድ እፈልጋለው:

በውኑ ህገ መንግስት አለን? ካለንስ በአግባቡ ተግባራዊ ሆኖስ ያውቃል? መልሱን ለእናንተ…… ይህንን ለመመለስ ከላይ በጽሑፌ ለማስጨበት የሞከርኩት ማየት ብቻ በቂ ነው ብዬ አስባለው። ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ሀሳባቸውን በነጻነት የሚገልጹበት መድረክ ተዘጋጅቶ በሰላማዊ መንገድ ፕሮግራማቸውን ለህዝብ እንዲያስተዋውቁ ተደርጎ፥በሀሳብ አሸንፈው ዲሞክራስያዊ፣ ፍትሐዊ እና  ተአማኒያዊ ምርጫ እንዲካሔድ ተደርጓል? ለአገዛዝ እንዲያመች ተደርጎ ተጽፎ ጸድቃል የሚባለው ህገ መንግስት አፓርታይዳዊ ነው። ይህንን የምንልበት ምክንያት ሁሉን ያላሳተፈና ህዝብ ያልተወያየበት እና በወቅቶ ስልጣን ላይ የመጣው ፓርቲ በህዝብ ምርጫ ሳይሆን በአፈሙዝ በመሆኑ ነው። መንግስት በአፈ ሙዝ በትረ ሥልጣኑን ከጨበጠበት ጊዜ ጀምሮ አፋኝ እና አግላይ ህገ መንግስቱን በመጠቀም ህግ አውጪውም ህግ ተርጓሚና አስፈጻሚ በመሆን በሃሳብ የሚሞግቱትን ሁሉ ሰብስቦ በማሰር አፋኝ የሆነውን ህገ መንግስት እያጣቀሰ ብቸኛው የምርጫ ተዋናይ በመሆን ምርጫውን 99.9% አሸንፌያለው በማለት እና ፍትሃዊ እና ተአማኒያዊ ምርጫ አካሂጃለው በማለት አለም ዓቀፉን ህብረተሰብ ሲያታልል እንደነበር የቅርብ ጊዜ ትውስታችን ነው። የሀገር መከላከያ ሰራዊትን፣ የፌደራል እና የክልል ፖሊስን፣ ፍርድቤትን፣  ምርጫ ቦርድን እና ሚድያውን ሙሉ በሙሉ በመንግስት ቁጥጥር ስር አውሉ እንዴት ፍትሃዊ እና ተአማኒነት ያለው ምርጫ ሊካሔድስ ይችላል? ስንቱን የፖለቲካ ተፎካካሪዎች፣ ጋዜጠኞች፣ የዩንፈርሲቲ ተማሪዎች እና የፍትህ ያለህ ብለው ድምጻቸውን የሚያሰሙትን ሁሉ ወደ እስር ቤት ጠቅልሎ በመውሰድ ህገ መንግስቱን ለመናድ በኃይል ተንቀሳቅሰዋል ሀገርን ለማፍረስ ከአሸባሪዎች ጋር ተሰልፈዋል በማለት ያለምንም ማስረጃ እና መረጃ እስር ቤት አጉረው ስንቱን አሰቃይተዋል፣ ደብድበዋል፣ የሀይላንድ ውሃ በብልት ላይ አንጠልጥለዋል፣ ወንድ/ሴት ደፍረዋል፣ ጥፍር ነቅለዋል?

ከላይ በመንግስት የተፈጸሙትን ግፎች እና ህገ ወጥ ድርጊቶች እራሱ መንግስት ጥልቅ ተሃድሶ አድርጌያለው እያለ መልሶ ተመሳሳይ ድርጊቶችን ሲፈጽም ቆይቷል። በዚህም በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።   ህዝባዊ ዓመጽ በመላው ሀገሪቱ እየተቀጣጠለ በመምጣቱ፣ በውስጥና በሀገር ውስጥ ያሉት በቅንጅት በመስራት በተለይ ለሀገዛዝ እንዲያመች ተደርጎ በአማራ እና በኦሮሞ ህዝቦች መካከል እሳት በመለኮስ፥ ታሪክን አጣሞ ትውልድን በጥላቻ እና በቂም በቀል እና በጥርጣሬ እንዲተያዩ ሲያደርጋቸው የነበሩት ሁለቱ ህዝቦች አንድ በመሆን አምረው በመታገል ከፈፈይ እና አግላይ የሆነውን ሥርዓት ላይመለስ ወደ መቀሌ ሸኝተውታል። የለውጥ ኃይሉ በወቅቱ በቲም ለማ እና በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው እና አቶ ደመቀ መኮንን የሚመራው አሁን በስልጣን ላይ ያለው አመራር ያለፈውን ስርዓት ካወገዙ በኃላ ለአገራችን እትዮጵያ የብርሃን ፍንጣቂ እና ተስፋ በመሆን ያለ አግባብ በአሸባሪነት የተፈረጁ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች ከሀገርም ይሁን ከውጪ ወደ ሀገራቸው ገብተው ትጥቃቸውን ፈተው በሰላማዊ መንገድ ሀሳብን በሃሳብ እንዲያሸንፉ እና በምርጫ እንዲወዳደሩ የፖለቲካው ምህዳር እንዲሰፋ ተደርጓል፣ የታሰሩ የፖለቲካ ፓርቲ አባሎች እና አመራሮች፣ የሰበዊ መብት ተዓጋቾች፣ ጋዜጠኞች፣ ታዋቂ ባለሃብት እና ግለሰቦ እንዲሁም የሀይማኖት አባቶች ከእስር እንዲፈቱ ተደርጓል፣ ለሁለት የተከፈለውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቅዱስ ሲኖድዮስ እንዲታረቁ ተደርጓል። በዚህም የተነሳ የብርሃን ፍንጣቂ በመሆን በሁሉም በሚባል ደረጃ የህዝብ ድጋፍ አግኝተዋል፥ ህዝቡም በአደባባይ አጋርነቱን በአደባባይ በመውጣት ገልጿል አሳይቷልም። ይሁን እንጂ ይህ አግላይ እና ከፋፋይ ህግ መንግስት ከዚህ በፊት በአደባባይ በኦሮሞ ሊህቃን ሲወገዝ የነበረው፥ የህገ መንግስት ጠበቃ በመሆን ይህ ህገ መንግስት እንዳይነካ በማለት አይናቸውን አፍጠው ጥርሳቸውን አግጠው በአደባባይ መግለጫዎችን ጭምር ሲሰጡ አይተን ታዝበናል። በዚህም የተነሳ ሀሳባቸውን በነጻነት በመግለጽና ሀሳባቸውን በሃሳብ እንዲያሸንፉ እድል ቢሰጥም አሻፈረኝ በማለት ትላንት በእስር ቤት ሲሰቃዩ የነበሩት እና በምህረት ከእስር ቤት የተለቀቁ ግለሰቦች እስር ቤት ምንም አይነት ድብደባ አልተፈጸመብኝም በማለት በአደባባይ ተናግረዋል ከአሳሪዎቻቸው ጋርም ጋብቻ በመፈጸም አይናቸውን በጨው አጥበው መቀሌ ድረስ በመሄድ በህዝብ እምቢተኝነት የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ ከሚያሴሩት ጋር አጋር ሆነዋል።

በአብሮነት እና በአንድነት ተዋልዶ/ተሳስሮ በኖሩት ህዝቦች መካከል የጥላቻ ንግግርን በአደባባይ በመስበክ ወንድም ወንድሙን በጥርጣሬ እና በጥላቻ እንዲተያይ በማድረግ ብዙዎቹ ተወልደው ካደጉበት፣ ከተማሩበት፣ሀብት ንብረት ካፈሩበት እና አግብተው ከወለዱበት ስፍራቸው እና ቀዬአቸው ተፈናቅለዋል እንዲሁም ተገድለዋል። የእምነት ተቋማት እንዲቃጠሉ፣ አማኞች እና ካህናት በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲገደሉም ተደርጓል። የሌላ ብሔር ተወላጆችን በተለይ አማራውን በገዛ አገሩ እንዳይኖር መጤ እና ሰፋሪ በማለት በስነ ልቦና፣ በማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ እንዲወድቁ በማድረግ በግፍ ተፈናቅለዋል ተገለዋልም። በህዝቦች መሐከል በአደባባይ ጥላቻን በራሱ ሚዲያ የሚሰብከው የኦሮሞ ሚድያ ኔት ዎርክ እና አሜሪካዊ ዜግነት ያለው አቶ ጃዋር መሐመድ ጠቅላይ ሚንስትሩ አፍንጫ ስር ሆኖ ሁለት መንግስት እንዳለ በድፍረት ሲናገር እና ጠቅላይ ሚኒስትሩንም በድፍረት በተደጋጋሚ ሲያወግዝ አይተናል። መንግስትም ይህንን ግለሰብ በተደጋጋሚ አይቶ እንዳላየ በመሆኑ ብዙዎቹን አስቆጥቷል። ይህ ግለሰብ ተከብቢያለው ብሎ የድረሱልኝ አይነት ጥሪ ለተከታዮቹ መልዕክት ባስተላለፈበት ወቅት መንገዶች ተዘግተዋል፣ ንጹኃን ዜጎች በተለይ የአማራ ተወላጆች ላይ ዘር ተኮር ጥቃቶች እንዲፈጸሙ እና ንብረታቸው እንዲቃጠሉ እንዲሁም በአሰቃቂ ሁኔታ 86 ሰዎች እንዲገደሉ ተደርጓል። ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአገር ውስጥ ባለመኖራቸው ከመንግስት አካል ድርጊቱን ደፍሮ የሚያወግዝ አልተገኘም። እንዲያውም የኦሮሚያ ርዕሰ መስተዳድር ይቅርታ በሚመስል መንገድ ድርጊቱን ከማውገዝ ይልቅ ስህተት እንደሆነ በአደባባይ ተናግሯል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ ሲጠበቁ እንኳን እርምጃ ሊወስዱ እዚህ ግባ የማይባል መግለጫ ለማውጣትም ከሳምንት በፊት ፈጅቶባቸዋል። ግለሰቡ ከህግ በላይ በመሆን የሚጠይቀው የመንግስት አካል ባለመኖሩ በሰሜን ሸዋ ኦሮሚያ ከተሞች በመዘዋወር ከባባታችሁ ምድር ነፍጠኛውን ጠራርጋችሁ አስወጡት፣ ቤ/ክ ሰብረህ ግባ እና ተቆጣጠር እያለ ሲሰብክም መንግስት እንዳልሰማ እና እንዳላየ ሆኖ አልፏል። በቅርቡ ከሃጫሉ ሁንዴሳ እልፈት ጋር በተያያዘ መንግስት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን በመግለጽና ከወንጀሉ ጋር ተባባሪ የሆኑትንም ጭምር በህግ ተጠያቂ ለማድረግ እየሰራ መሆኑን ገልጾ ግድያውን በጽኑ አውግዟል። የሐጫሉን አስከሬን በክብር ወደ ቤተሰቦቹ እንይመለስ አስከሬኑን በጉልበት በመንጠቅ እና በማንገላታት ይህንም አጋጣሚ በመጠቀም ከውስጥ እና ከውጪ በመደራጀት መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ታስቦ እንደነበር እና መክሸፉንም የፌደራል የፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር፣ የአቃቢ ህግ እና ሌሎች ባለ ስልጣናትም ተናግረዋል።

አቶ ጀዋር መሐመድ እና ጠባቂዎቹ የሐጫሉን አስከሬን በመቀማት እና ወደ ኦሮሚያ የባህል ማዕከል ጥበቃዎችን ጥሰው በመግባት የፖሊስ ሰራዊት መግደላቸውንም በህላም በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም መንግስት አስተኣውቋል። ይህንን ተከትሎ በኦሮሚያ የተቀሰቀሰው ተቃውሞ በተለይ በሻሸመኔ እና ዝዋይ ከተሞች ዘር ተኮር ጥቃት በተለይ በአማራ እና ጉራጌ ተወላጆች ላይ አሰቃቂ ግድያ በማድረስ ንብረታቸውን ዘርፈዋል፣ አቃጥለዋል አውድመዋል። በክልሉ ያለው የኦሮምያ ብሔራዊ ርዕሰ መስተዳድር በኦሮሚያ ውስጥ ላሉ ሌሎች ብሔር ተወላጆች ምንም አይነት ጥበቃ ባለማድረጉ ዜጎች በተደራጁ መንጋዎች የስነ ልቦና፣ የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ውስጥ ገብተዋል በግፍ እና በአሰቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፣ሀብት ንብረታቸው ተዘርፏል እንዲሁም ወድሟል። በጣም ገራሚ የሆነው ደግሞ የሀጫሉ ሞት እና ሌላው ንጹ ዜጋው ከጉዳዩ ጋር ምንም ንክኪ የሌለውን ህብረተሰው ዘሩን እና ኃይማኖቱን በመለየት በአሰቃቂ ሁኔታ መግደል፣ ንብረቱን መዝረፍ እና ማውደምን ምን አመጣው? ይህንን ንጹህ ህሊና ያለው ሁሉ በአደባባይ ሊያወግዘው የሚገባ ጉዳይ ነው።  ለዚህ ሁሉ ቀውስ ምክንያት የሆነው የባለፈው ሥርዓት እና ለአገዛዝ እንዲያመች ህዝቦችን በኃይማኖት፣በቋንቋ፣ በዘር እና በጎሳ የሚከፋፍል ፖሊሲ በመቅረጽና ትውልዱን በሀሰት ትርክት ኮትኩቶ በጥላቻ እንዲያድግ በመደረጉ ነው። ለዚህም ማስፈጸሚያ እንዲሆን ለሰበዊ መብት ተቆርቃሪ የሆኑትን ሁሉ እያደኑ እስር ቤት ማስገቢያ እና ማስፈጸሚያ ህገ መንግስቱ ነው። አሁንም ቢሆን ይህ ከፋፋይ እና አድሎዋዊ ህገ መንግስት በህዝብ የተመረጡ እንደራሲዎች/የፓርላማ ተወካዮች ሁሉንም ባሳተፈ መልኩ እንደ አዲስ ካልረቀቀ የሀገራችን የወደፊት እጣ እንደ ሱማሌ እና የመን ሊያመራን ይችላል።

 

Haimanot Mehari Tewelde, PHD

 

Email: haimanotmeharit@gmail.com

Oslo, Norway

1 Comment

 1. የጥፋት ሀይሎች፣ ከስልጣን የተገፉ ፣ገለመሌ እያሉ ማሽሞንሞን የንጹሃን ደም መፍሰስን ኣላቆመውም። ሀገራችንንም ከመፈራረስ ዳር ኣድርሶኣታል።
  ኣቶ ሽመልስ እንዳፈነዱት የኢትዮጵያ ያለመረጋጋት መንስዬ ወያኔ እና ኦነግ ሸኔ መሆናቸው ተገልጾኣል።
  የኢትዮጵያን ሉኣላዊነት ለሚያምኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች የ ” ሀገር ኣድን ” ጥሪ ተደርጎ ሰፊ” ብሄራዊ ህብረት ” በመፍጠር እና ለኢትዮጵያ ህዝብ የክተት ጥሪ ኣቅርቦ ከመዝመት ውጭ የሊቢያን ሁኔታ መጋበዝ ነው ። We are running short of time .
  ንጹህንን በመግደል የተረጋገጠባቸው ወንጀሉን በፈጸሙበት ስፍራ መቀጣጫ በሚሆን መልኩ በኣፋጣኝ እርምጃ ሊወሰድባቸውይገባል።Retributive justice should be practiced .ማድበስበሱ ይብቃ።
  ኣሰማሪዎቹን በጄኖሳይድ እና በሀገር ክህደት መክሰስ። ብሀገራች ከሀዲዎችን መቅጣት ኣዲስ ነገር ኣይደለም።
  መንግስት በጀመርከው መንገድ ቀጥል!!! የኢትዮጵያ ኣምላክ ይርዳህ !!!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.