“ማለን ጅራ” ምኑን አለሁ! ሃጫሉ ለምንና እንዴት ተገደለ? – ከስዩም ደገፋ

9a76b6236465f0575693ae5dfe519f85 3የሳምንቱ መባቻ እንደወትሮው አይደለም። የወርሃ ሃምሌ ሰማይ ያረገዘውን ዝናብ ቁልቁል ይለቃል።
እለተ ሰኞ የጣለው ዝናብ ያረጠበው መሬቱን እንጂ ከቶም በክፋት ተጠምዶ የዋለውን ልብ አልነበረም።ክፋት የጸነሰው ክፉ መንፈስ ያን ሎጋ ሊቀጥፍ ሲጣደፍ ዋለ እንጂ ሄድ መለስ ሲል እንደዋለ ዝናብ
ትዕግስትን ተላብሶ ሊያሳልፍ አልቻለም።ማንም ውሎውን እንጂ ማምሻውንና አዳሩን አያውቅም።እንደወትሮው ሁሉ የዕለት ምግባሩን ከውኗል።በማለዳ የወጣችው ጀንበር ስትጠልቅ ብቻዋን አልሄደችም። ያንን ብዙዎች የሚወዱትን ፤ከፍም ሲል እንደ ነጻነት ታጋይ የሚቆጥሩትን የኪነጥበብ ሰው አስከትላ ጠለቀች።ጥበብ አንድ ልጇን አጣች።በኪነጥበብ ዘርፍ የራሱን አሻራ ጥሎልን ላይመለስ ሄዷል
ሃጫሉ ሁንዴሳ።
ሰኞ ምሽት የጨለማው ጽልመት በቤተሰቡ ላይ ብቻ አልነበረም የሃዘን ድባቡን ያሳረፈው። አዲስ አበባ ውስጥ በጥይት የተገደለው የኪነጥበብ ሰው ሃጫሉ ሁንዴሳ መገደል በራሱ መዘዙ የበዛ ሆኗል።
የዜና እረፍቱን መሰማት ተከትሎ በተለያዩ የሃገሪቱ ክፍሎች አለመረጋጋት ተከስቷል።በየእለቱ በሁሉም አዕምሮ መልስ የሚሹ በርካታ ጥያቄዎች እያጫረ ነው።ሃጫሉ ለምን ተገደለ? በማን ተገደለ?የሚሉት ከሚነሱትና መልስ ከሚያሻቸው አንኳር ጥያቄዎች የሚካተቱ ናቸው።
ከአንድ መሰረታዊ እውነት መነሳት ይቻላል። በሃጫሉ ሞት ወይም ግድያ ላይ ተቃውሞን ለማቅረብ ምንም አይነት የብሄር ወይም የኃይማኖት ትሥሥር አያሻም። ሰው ሆኖ መፈጠር በራሱ በቂ
ነው።አንዳንዶች ወደራሳቸው ዝቅ ወዳለ ሰብዕና በመክተት በአያገባችሁም ፈሊጥ ሲጋበዙ ብናይም የምናደምጥበት ጆሮ የለንም።ማንም ቢሆን በየትኛውም ሚዛን በግፍ ሊገደል አይገባውም።
ሃጫሉ እንደማንኛውም ወላጅ የሚያሳድጋቸው ልጆቹ ይፈልጉታል፤ አሳድጎ የወላጅ ወግ ማዕረግ የማየት መብቱን በግፈኞች ከቶም ሊነጠቅ አይገባውም።ክቡር ሞቱ ለሰማዕት እንዲሉ ዛሬ ወደ የትኛውም ጽንፍ እየጎተቱ ሰማእትነቱን ለማሳነስ መሞከር አይገባም። ይህ ሰውኛ እሳቤ ነው። ከዚህ ከፍ ሲል ደግሞ ባለው የትኛውም አመለካከት ይባል የብሄር መገኛው ለጥቃት ሊጋለጥ አይገባውም። ይህ ለእርሱም ፤ ለእኛም ለሁላችንም የሚሰራ ነው።
ዛሬ በሃጫሉ ላይ የደረሰው የሞት አደጋ ሲሰማ አንድ ታሪክ ታወሰኝ። የዚያ የቆራጡ የአንጋፋው የኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር ዋና ጸሃፊና የኢሰመጉ ባልደረባ አሰፋ ማሩ አሟሟት ።በማለዳ ወደ እለት
ስራው ባለቤቱንና ልጆቹን ተሰናብቶ ሲኳትን እግር በእግር በመኪና ተከታትለው ሲጠባበቁት የነበሩት የክንፈ ገ/መድኅን የጸጥታ ሰራተኞች በጥይት መትተው ገድለውት ሄዱ።
ማለዳ ወደስራ ገበታቸው በጎዳና የነበሩ ሁሉ ተደናገጡ ፤ ተሸበሩ። የመንግስትን ስልጣን በእጁ የያዘ መንግስት ሰላማዊ ዜጋን ጎዳና ላይ
ገድሎ ሲሄድ ያልተፈራ ምን ይፈራል?የአሰፋ ማሩ ደም ዛሬም ይጣራል። ፍትህ ይጠይቃል። ገዳዩ እንግሊዝ ሃገር ይኖራል ከሚባል ሃሜት በቀር የሚታወቅ የለም።በወቅቱ ኢሰመጉ እና የሰብዓዊ መብት
ተከራካሪዎች ፤ አንጋፋው ኢመማ ፤ የነጻ ፕሬስ ውጤቶች አቤት አሉ ፤ ሰሚ ግን አልነበረም።ይህ አንድ ምሳሌ ነው። በወቅቱ ይህ ድግግሞሽ የበዛ ነበር።
ህወሃት ሽግግር ብሎ ከጀመረበት እለት አንስቶ አስብላችኋለሁ ያለውን እንባ በደም ቀየረ እንጂ ከቶም አላቆመም። የአሰፋ ማሩ ቀብር ላይ ከሙያ ባልንጀራዬ በፈቃዱ ሞረዳ ጋር አብረን ነበር የሄድነው። ከሞቱ
ስርዓተ ቀብሩ ልባችንን ሰብሮት መመለሳችንን አስታውሳለሁ። ብዙዎች ፈርተው ይሁን በሌላ ምክንያት በስፍራው አልነበሩም።እርሱ ግን ዛሬም ድረስ በብዙዎች ልብ ሲያበራ ይኖራል። የተሰዋለት የነጻነትና የዴሞክራሲ ጥያቄ ዛሬም ከፍ ብሎ ይውለበለባል።
ህወሃት የሚመራው መንግስት የሚቃወመውን በመግደልና በማስወገድ ያምናል።በደም የሚጸና የስልጣን መንበር ነውና ህልማ ቸው ዘወትር ከዚህ አዙሪት መውጣት ተስኗቸው በዚያው አዙሪት ይሽከረከራሉ፤ ህዝቡም የመከራ ሰብሉን ያጭዳል።
ከመነሻዬ ወደተነሳሁበት አበይት ጉዳይ እንመለስ ። ሃጫሉ ለምን ተገደለ? ለሚለው አሁን ምርመራ የጀመረው የፖሊስ አካል በበቂ ሁኔታ መልስ እንደሚሰጥበት ሊጠበቅ ይችላል።ይሁንና ግድያው ፖለቲካዊ አንድምታ የለውም ብለን የቂል ግምት ላንገምት እንችላለን።ወይም ግድያው ፖለቲካዊ ይዘት እንዳለው ለመናገር የግድ ነቢይ መሆን አይጠበቅብንም።ለምን ቢባል ለዚህ የተለያዩ አስረጂዎችን መጥቀስ
አይገድምና ነው።
የሃጫሉ ዜና እረፍቱ ከተሰማ በኋላ አስከሬኑ ወደ አምቦ ሲሸኝ በነበረበት ወቅት ከመንገድ በማገት የተሰራው ድራማ እጅግ ያሳዝናል።ይህ በህግ የተያዘ በመሆኑ እዚህ ላይ መነጋገሩ ፋይዳ ባይኖረውም ከዚህ የሚገኝ ፖለቲካዊ ትርፍ ቢኖር እንኳን ለማትረፍ ሲባል ያን የመሰለ መጉላላት በአስከሬኑና በቤተሰቡ ላይ መድረሱ ድርብ ሃዘን መሆኑን መግለጽ ግን ይገባል።
ሃጫሉ ገና ከልጅነቱ ነው በህወሃት የደህንነት መ/ቤት ጥርስ ውስጥ የገባው።አስረውታል ፤ገርፈውታል።በቂም በትር ነክሰውታል። ከነፍስ መንጠቅ በመለስ የቻሉትን አላደረጉም አይባልም። ይህ የነጻነት መሻት ጥያቄው ለጋ እድሜውን እንደ እድሜ እኩዮቹ እንዳያሳልፍ አድርጎታል መታሰር በአርሱ የሚያስከትለው ጫና አለ። ለዚያውም ዓመታትን ሲያስቆጥር ከዕድሜው ላይ አንዳች ማጉደሉ አይቀርም።ለበረታ የመንፈስ ብርታት ይሆናል፤ ለተሸነፈ ደግሞ ስብራት ይሆናል።
ይህ ሁሉ ጫናና እስር የሃጫሉን የትግል መንፈስ አጠነከረው እንጂ አልበረበረውም። እንደምን ቢባል ጉምቱ ሹማምንት በተሰየሙበት የሚሊኒየም አዳራሽ ያሳየው ድፍረት የተሞላበትና እውቅና ያተረፈበት
በቀረርቶ የታጀበው ዜማው አስረጂ ነው። በወቅቱ በስልጣን ላይ የነበሩትን በተለይም የህወሃትን ሰዎች ከፍ ዝቅ አድርጓል። ከዝግጅቱ በኋላም ያ መርሃግብር በቀጥታ ስርጭት የተላለፈ መሆኑ በራሱ
ያሳደረባቸውን ቁጭትና ንዴት ስናስታውስ ሰዎቹ የነከሱበትን ጥርስ ምን ያህል ብርቱ እንደነበር መገመት አያዳግትም። “ማለን ጅራ” እያለ አዚሟል። “ምኑን አለሁ” ሲል ። ይህ ዜማው የሚያጠይቀው
ማንነት ለህይወቱ የሚሰጠውን ትርጉም ነው።ሁላችንም የምንሻው ማንነት ከራሳችን አልፎ ለልጆቻችን ልናወርስ የምንወደው ማንነት ነው። ሰው ሆኖ የመቆጠር ፤ ሰው ሆኖ የመኖር ነጻነት ይመስለኛል።
ይህ ደግሞ በአምባገነኖች ሰፈር አይወደድም።
ትላንት ብዙዎች ለዚህ የነጻነት ብርሃን መምጣት ተሰውተዋል።ዛሬ ደግሞ ሃጫሉ ሁንዴሳ ወደ እነርሱ አምርቷል። ልክ የአሰፋ ማሩ የግድያ ትራጄዲ በእርሱም ተደገመ። የተነከሰበት ጥርስ እንዳልበላው አስረጂ ባይኖርም ለመጠርጠር የሚያበቁን ብዙ የይሆናል ግምቶችን ልናቀርብ እንችላለን።
ከህልፈቱ ጥቂት ቀናት አስቀድሞ በኦሮሚያ ሚዲያ ኔት ወርክ የሰጠው ቃለ ምልልስ ወይም መግለጫ ነበር። ምናልባት ቃለ ምልልስ ከወትሮው በተለየ መልኩ በበርካታ የኅበረተሰብ ክፍሎች ቅሬታና
ተቃውሞ አስከትሎ ነበር ። በተለይም ከአጼ ምኒሊክ ጋር በተያያዘ በተናገረው ።ዋናው ቁምነገር ከሞቱ በኋላ ስለምን ያንን በዚህ ጊዜ እንዲናገረው ተደረገ? ብለን ስንጠይቅ እጅግ በርካታ ተጨማሪ የመላምት ጥያቄዎች መንገዶችን ይከፍታል።
በእርሱ ላይ የሚደርስ ማንኛውም ጥቃት የሚያስከትለውን ቀውስ ከግምት በማስገባት ከዚያ ለማትረፍ የሚሹ አልወጠኑትም ወይም አያደርጉትም ልንል አንችልም። አሁን ሃገሪቱ ያለችበትን ነባራዊ ሁኔታ
ስንመለከት የይሆናል ግምቱን ወደ እውነት ያቀርበዋል።
የፖለቲካ ሥልጣን ማጣታቸው ያስከፋቸው አኩራፊ አምባገነኖች ሥልጣን ወይም ሞት ብለዋል። እኛ ካልገዛን ኢትዮጵያ ትጥፋ ብለው ያለይሉኝታ ተነስተዋል።ዛሬ በስልጣን ላይ ለሚገኘው የለውጥ ኃይል ትልቅ ተግዳሮት ናቸው።
በአንጻሩ ከህዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ ግብጽ የኢትዮጵያ ሰላም ተኝቶ ማደር ያባጃታል። አክራሪ ብሄርተኞች በተለይም በጀዋር የሚመራው ክንፍ እንዲሁ ሌላ የስርአቱ ሳንካ ነው።
እነዚህ ኃይሎች በቅርቡ ሃጫሉ ያደረገውን ንግግር ተጠቅመው ከዚያ ጋር ተያይዞ ጥቃት ደረሰበት በማለት በሚፈጠር ቀውስ ሊያተርፉ ወይም በአቋራጭ ለሚመኙት ሥልጣንና ፖለቲካዊ ፍላጎት እንበቃለን
ብለው አይመኙም ማለት እንደምን ይቻላል?
አሁን በስልጣን ላይ የሚገኘውና በዶ/ር አብይ የሚመራው ኃይል ላለፉት 27 ዓመታት ከተገነባው የብሄር ፖለቲካ ወደ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት ማዘንበሉ ሰላም ነስቷቸዋል።ይህ በአብዛኛው ኢትዮጵያዊ
ዘንድ ተቀባይነት ማግኘቱ ያስከፋቸው ብሄርተኞች ድምጻቸውን እያሰሙ ነው።
ሕወሃት በትግራይ ክልል እንደለመደው ብቻውን የሚወዳደርበት ምርጫ ለማድረግ እየተገላገለ ይገኛል። እነዚህ ኃይላት የተዘጋው በር ሊከፈት የሚችለው በቀውስ ውስጥ ብቻ ነው ብለው ቢነሱ
የሚያዋጣቸው ሊመስላቸው ይችላል።
ከሕወሃት የኋላ ታሪክ ስንነሳ እንዲያ ጥርስ የነከሱበትን ሃጫሉን
ከመሰዊያው ላይ ማቅረብ ቀርቶ ምንም ከማድረግ አይመለሱም። ይህ የይሆናል ግምት ወደ እውነታ የተቃረበ ነው የሚሉ ብዙ ናቸው።
አሁን በሃገሪቱ የሚታየው የለውጥ አየር ዕድል የሰጣቸው ያገኙትን ዕድልና ተስፋ እንዴት እያጣጣሙት ነው? ብለን ስንጠይቅ በርካታ መስቀለኛ ጥያቄዎችን ሊያጭርብን ይችላል። በመገናኛ ብዙሃን ዘርፍ
የሚታየውም የራሱ ድርሻ አለው። ምን ያህል የኃላፊነት ስሜትንና ሙያዊ ስነምግባርን በአግባቡ የመከወን ግዴታ እየተወጣ ነው? የሚለው ሲታይ ጥያቄአችንን ያጎላዋል።ለብዙዎቻችን ስደት ምክንያት የሆኑ ወይም ከአሳዳጆቹ ተርታ የነበሩ ዛሬ ጉምቱ ተንታኝና የነጻነት አጋፋሪ ነን ሲሉን ተሸክመን የምንሄድ ነንና ሌላው ተግዳሮት ላለመሆኑ የሚያጠይቅ አይኖርም።
ምንም ተባለ ምን ሃጫሉ የትኛውንም አይነት አመለካከት ቢኖረው ለጥቂቶች የፖለቲካ ቁማር ሲባል እንደሰው የማሰብ መብቱን ነውና የተጠቀመው ሞት አይገባውም። ሰው ነንና ይህን ድርጊት እንቃወማለን ። ተቃውሞአችን ሌላ ጥፋትን የሚያስከትል ሳይሆን የግፍና የጭካኔ እጃቸውን ያነሱበት የእጃቸውን በፍትህ አደባባይ እንዲያገኙ በመጠየቅ ነው። ዛሬ የሁሉም ልብ ተሰብሯል። የተሰበረ ልብ የሚጠገነው ሌላ የወገን ልብ በጭካኔ በመስበር ከቶም ሊሆን አይገባም።የትላንቱ የጨለማ ዘመን ዳግም እንዲመጣ አንመኝም። ዛሬ ሃጫሉን ሁላችንም አጥተነዋል።ዜማው ሃሴትን በነፍሳችን ያጭራል። ሃብትነቱ የሁላችንም ነው። ሃጫሉ የእኛ ብቻ ነው ብላችሁ የምትጋበዙ ግድ የላችሁም አትሞኙ የሁላችንም ሃብት ነው፤ ታሪኩ እኛም የምንጋራው ታሪክ ነው። ስለመኖሩ ትርጉም የሰጠው “ማለን ጅራ” ማለቱ ለዚሁ ነው። መኖሩ ለራሱ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ነውና ። ሁሉም ለሌላው ነውም።
ቸር እንሰንብት

2 Comments

  1. ስህተትህ አሰፋ ማሩን በስልጣን ላይ ያሉ ገደሉት፣ የዛሬዎቹ ግን እጃቸው የለበትም ለማለት መዳዳትህ ነው! ዋነኛ ተጠርጥሪ የአቢይ ክሊክ ነው! ሃቅን ለመደበቅ ከመጣር ነው እንጂ፣ የሃጫሉ ሬሳ ፍንፍኔ እንዲመለስ ያዘዘው የኦሮሚያ ፕሬዚደንት ትብዬው ነው! በህዝብ መሃል ነው እኮ ነው ትዕዛዙ የመጣው። የፈደራል ፖሊሶች ከሃጫሉ ቤተሰብ ተጨማሪ 2 ሰው፣ ሌሎት 27 ሰዎች ገድለው ራሳቸው በፈለጉበት መንገድ መቅበራቸው ራሱ ማስረጃ ነው!! አይናችሁን ጨፍኑ እናሞኛችሁ ከሆነ አይሰራም! በሩጫ ኦ እም እንን መዝጋትና የኦ ኤል እፍ እና የኦፌኮ ከፍተኛ አመራሮችን ያሰሩበትስ ሰበብ ምንድር ነው?? የገደሉትን ሳይይዙ፣ አሟሟቱን ሳይመረምሩ *አዉቶፕሲ እንኳ አልተደረገም* የሚጠሉትን ተቃዋሚዎች ለማሰር መሮጣቸው፣ ግድያውን ራሳቸው እንዳቀናበሩት ያጋልጣል! ማየት አልፈልግም ካልክ ሌላ! የምትጠሉት ላይ ብቻ ማነጣጠር ስሜታዊ መሆንን እንጂ እውነታን አያንጻባርቅም።

  2. ሀቅ በራስዋ ጊዜ ትወጣለች አስገዳዩ በአንተም ህሊናህ አለ እሱም አብይ ነው ነገር ግን ነፍጠኞች ሁሌ ጥፋቱ ወደ ሶስተኛ ወገን(ወያኔ ሸኔ) ማላከክ ትወዳላችሁ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.