የሃጫሉ ሁንዴሳ አሳዛኝ ግድያና ያስከተለው መዘዝ

Achaluየሃጫሉ ሞት ብዙ መልስ የሚሹ ጥያቄዎችን አንስቷል፡፡ ማን ገደለው? ለምን? ገዳዮቹ እሱን በመግደል ሊያሳኩት ያሰቡዋቸው ዕኩይ ዓላማዎች ምን ነበሩ? ከእሱስ ግድያ በኋላ ምን እየተደረገ ነው?

ፅንፈኛ ኦሮሞዎችና የኦነግ-ኦፌኮና የህወሓት አፈቀላጤዎች ከባሕር ማዶና ከመቀሌ ሆነው ግድያውን ያስፈፀመው የዶክተር ዐቢይ መንግሥት ነው የሚል፤ ከየትም አቅጣጫ ቢታይ ውሃ የማያነሳ መሰረተ ቢስ ወሬ እያናፈሱ ነው፡፡ ማንም ማሰብ የሚችል ሰው ዶክተር ዐቢይ ከሃጫሉ ግድያ የሚያገኘው ውጥንቅጡ የበዛና የመንግሥቱን ኅልውና ከአደጋ ላይ የሚጥል ችግር እንጂ አንዳችም ጥቅም እንደሌለ መረዳት አይሳነውም፡፡

በሌላ በኩል ለህወሓት ያለውን ጥላቻና ንቀት ደጋግሞ በአደባባይ ያረጋገጠው ሃጫሉ እነ ጃዋር፣ በቀለ ገርባና ሕዝቅኤል ጋቢሳ ከህወሓት ጋር ዛሬ ባጦፉት ወዳጅነት እንደተቀየመና እንዳዘነ ይታወቅ ነበር፡፡ በኦሮሞ ልጆች ደም ዕጁ የተጨማለቀው ህወሓት መቼም ቢሆን ያለፈውን በደል በሚያስታውስ ማንም ኦሮሞ እንደ ወዳጅ ሊታይ እንደማይችል ሃጫሉ በተለያዩ አጋጣሚዎች አሳውቋል፡፡ ስለዚህ በምክንያታዊ መነፅር የተደረገውን ነገር ስንመረምረው ለጃዋርና ለግብረ አበሮቹ ሃጫሉን ማስገደል በአንድ ድንጋይ ብዙ ወፎች መግደል የሚያስችል ብልጥነት መስሎ ታይቷቸው ነበር ቢባል ከእውነት አይርቅም፡፡ በአንድ በኩል ሃጫሉ ለህወሓት የነበረው ጥላቻና ከእነርሱ ጋር ህብረት በፈጠሩ ከሃዲዎች የተሰማውን ቅሬታ መግለፁ እንዲቀጥል አልተፈለገም።  የህወሓትን የግፍ አገዛዝ ተቃውመው ለስቃይና ሞት የተዳረጉ ኦሮሞዎችን መስዋዕትነት አርክሰውና እረግጠው፤ በስልጣን ጥማቸውና በአማራና በኢትዮጵያዊነት ጥላቻቸው ከህወሓት ጋር ተዛምደው ፀረ-መንግሥትና ፀረ-አገር ሴራ እየጠነሰሱ ለነበሩት እነ ጃዋርና በቀለ ገርባ የሃጫሉ አቋም በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ የነበራቸውን ተቀባይነት ጥርጣሬ ላይ የሚጥል ስለመሰላቸው ተወዳጁን አርቲስት ማስወገዱ ከስጋት ያላቅቀናል ብለው ሃጫሉን ለማስገደል ቆርጠው ተነሱ ቢባልም ለማመን አይቸግርም፡፡

ግድያውን ያዘጋጁት ሰዎች ሃጫሉን የመሰለ በኦሮሞ ሕዝብ ዘንድ በሰፊው ተወዳጅነትን ያተረፈ ሰው ገድሎ ከተጠያቂነት ማምለጥ ቀላል እንደማይሆን ያውቃሉ። ለዚህም ይመስላል ሃጫሉ ከመሞቱ ጥቂት ቀናት በፊት የጃዋር ንብረት ከሆነው የኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ ቴሌቪዥን ተጋብዞ አፄ ምኒልክን የሚያንቋሽሽ ነገር እንዲናገር የተጋበዘው። የዚህ ድርጊት ስሌት ግድያውን በንግግሩ በተቆጡ “ነፍጠኛ” አማራዎች ላይ ለማላከክ ያስችላል ተብሎ እንደሚሆን መገመት እይከብድም ፡፡ ከግድያው በኋላም ልክ ከአሁን በፊት ፅንፈኞቹ ቄሮ የሚሏቸውን ተከታዮቻቸውን እንደፈለጉ በስሜት ኮርኩረው እየነዱ በተደጋጋሚ አሰቃቂ ፀረ-አማራ ድርጊቶች እንዳስፈፀሟቸው ሁሉ አሁንም ወጣቶቹን ለንፁሃን ጭፍጨፋ ማሰማራት እንደሚችሉ ገመቱ፡፡ በነፍጠኛ ወገንተኝነት የሚያሙትን ዶክተር ዐቢይንም ከደሙ ንፁህ አይደለም ብለው ለመወንጀል ራሳቸው በድርጊቱ ተመሳጣሪነትና ተባባሪነት ከሚጠረጠሩት የህወሓት ሰዎች ጋር ተስማሙ፡፡ በኋላም የታየው የሃጫሉን አስከሬን አዲስ አበባ ለማስቀረት የተፈጠረው ለማመን የሚከብድ ድራማ የግድያው አቃጆችና ፈፃሚዎች ከተማዋን የዕልቂት አውድማ አድርገው የመንግሥት ግልበጣን ለማስከተል ቆርጠው ተነስተው እንደነበር ግልፅ አድርጓል፡፡

ከግድያው በኋላ የዶክተር ዐቢይ መንግሥት የወሰደውና እየወሰደ ያለው ቆፍጠን ያለ እርምጃ የኢትዮጵያን ህልውናና የሕዝቦቿን ደኅንነት የሚመኙትን ሁሉ እሰይ አሰኝቷል፡፡ የኦነግ-ኦፌኮ የጥፋት ሰራዊት፣ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ቆርጦ መነሳቱን ደጋግሞ በግልፅ የተናገረው ጃዋርና፣ የጎሳዎች ግጭትን ለመቀስቀስና ለማቀጣጠል ጧት ማታ የጥላቻ መርዝ የሚነዛው ኦ.ኤም.ኤን. እስከ አሁን ድረስ በቸልታ መታየት የነበረባቸው ባይሆኑም ዘግይቶም ቢሆን በሚገባቸው ሕጋዊ ተጠያቂነት ስር መውደቃቸው ለብዙዎች እፎይታ ሆኗል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ኦነግ-ኦፌኮንና መቀሌ የሰፈሩትን የህወሓት የጥፋት ኃይሎች እስከ አሁን ድረስ ለምን የሚያስፈልገው ዋጋ ተከፍሎ እንዲወገዱ ለማድረግ አልደፈረም? እነዚህ ሕዝብን ከሕዝብ አጋጭተው አገር ለማፍረስ በይፋ የሚንቀሳቀሱ ተውሳኮችን የመታገሱ ፋይዳ ምንድነው የሚለው የብዙዎቻችን ጥያቄ ነው፡፡ ምንም እንኳን የኦሮሞ ድርጅቶች ፅንፈኝነታቸው ቅጥ ያጣ ቢሆንም በኦ.ዴ.ፓ. ድጋፍ ከጠቅላይ ሚኒስትርነቱ ወንበር ላይ የተቀመጠው ዐቢይ የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎቹንና ታዋቂ አባላቱን መጋፈጡ የከፋ አደጋ ሊያስከትል የሚችል ነገር ነው ብሎ ሳያስብ አልቀረም፡፡ የሽግግር መንግሥቱ ተጠናክሮ በእግሩ ባልቆመበት በዚህ ጊዜ ቀዳዳ ፍለጋ አሰፍስፈው ከሚጠብቁት ጠላቶች ሁሉ ጋር ግብ ግብ ከመግጠም ይልቅ በዘዴና በትዕግስት በሂደት እያዳከሙ ወይም አቋማቸውን አለዝበው እንዲቀላቀሉ መሞከሩ ይሻላል ብሎ ይመስላል ብዙ ያስታመማቸው፡፡ ከዚያም ባሻገር አንድ ግልፅ ነገር ቢኖር አሁንም ድረስ ከከፍተኛ የመንግሥት ስልጣን ወንበር ላይ የተቀመጡ የፅንፈኞቹ ስውር አጋሮች እንዳሉና አጋጣሚውን ካገኙ በዐቢይና በሽግግር መንግሥቱ ላይ ፊታቸውን አዙረው ከፅንፈኞቹ ጋር ከመወገን ወደኋላ የማይሉ ሰዎች መኖራቸው ነው፡፡ ሆኖም ግን አገር አፍርሰው የጎጥ ፈላጭ ቆራጭ  መሆን ለሚያልሙ የግል ጥቅም ቋማጮችና የስልጣን ጥመኞች የእስካሁኑ የዶክተር ዐቢይ ትዕግስትና የመደመር ግብዣ ከንቱ ድካም እንደነበር አሁን እሱ ራሱም እንተረዳው ተገንዝበናል፡፡

በሌላ በኩል እጅግ የሚያሳዝነውና የሚያስቆጣው ነገር ኦሮሞዎች ተነካን ባሉ ቁጥር በየቀያቸው ያገኙዋቸውን አማራዎች ማረዳቸውና መጨፍጨፋቸው ነው፡፡ ዛሬም እንደገና በሃጫሉ ሞት ማግስት ብዙ ንፁሃን አማራዎች፣ ጉራጌዎችና  ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያን በኦሮሚያ ታርደዋል፤ በድንጋይ ተወግረው ተገድለዋል፡፡ ንብረታቸው ተዘርፏል፤ ቤቶቻቸው ተቃጥለዋል፡፡ እስከ መቼ ድረስ ነው አማራዎች በጥላቻ ለሰከሩ መንጋዎች የጥቃት ሰለባ የሚሆኑት?

በኦሮሚያ በሚኖሩ አማራዎች ላይ እስካሁን ለተፈፀሙት አሰቃቂ ግድያዎችና የዘር ማጥፋት ሙከራዎች ከፅንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ቅስቀሳ እንዲሁም ከመንግሥት የአቅም ወይም የቁርጠኝነት ወይም የሁለቱም አለመኖር ጋር እኩል ተወቃሹ በአማራ ብሔርተኝነት ስም ሲደረግ የነበረው አቅጣጫውን የሳተና ዓላማውን የዘነጋ ፍሬ-ቢስ እንቅስቃሴ ነው፡፡ እውነት ነው፤ የአማራ ህዝብ ለብዙ ዓመታት የብሔር ማንነቱን ምክንያት ያደረገ አረመኔአዊ ግፍና ግድያ ሲቀበል ስለኖረ ይህንን ብሄር ተኮር ጥቃት ለመከላከል የግድ የአማራውን ጥቅምና ደህንነት መሠረት ያደረገ የአማራ የብሄር ድርጅት አስፈላጊ ነው። በድርጅቱ የሚቀነቀነው የብሔርተኝነት ፖለቲካ ግን የአማራን ሕዝብ ከሌላ ብሔሮች ነጥሎ ከጎጥ ላይ የሚያስቀምጥ መሆን አልነበረበትም። ጭራሹን በአማራዎች መሐል የእርስ በእርስ አለመተማመንና ጥላቻ ፈጥሮ ደም እስከማፋሰስ የሚያደርስ ነውረኛ አካሄድ መከተል በፍፁም አልነበረበትም፡፡  ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ዙሪያውን የፍፃሜ ሴራ በሚሸርቡበት በዚህ የሞትና የሽረት ወቅት የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊነት ግዙፍ ምሰሶ ሊሆን ይገባው የነበረውን የአማራ ሕዝብ ከፋፍሎ ጉልበቱን ያዳከመው፤ መነሻና መድረሻውን ስቶ እንዲባዝንና በስሜታዊነት እንዲጋልብ ያደረገው አስተዋይነት የጎደለው የአማራ ብሔርተኝነት ፖለቲካ ነው፡፡ ከዚህ አሳፋሪ የሽንፈት መቀመቅ፤ ከዚህ የአማራን ሕዝብ መሳለቂያና የጥቃት ሰለባ ካደረገው አካሄድ በአስቸኳይ ለመውጣት ፖለቲካው በበሰሉ አርቆ አሳቢዎች መመራት ይኖርበታል፡፡ አማራነት ከኢትዮጵያዊነት በጭራሽ ተነጥሎ የሚኖር አይደለምና የኢትዮጵያን ሉዓላዊነትና የሕዝቦቿን አንድነት ከሚሹ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ጋር የአማራ ሕዝብ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት መፍጠሩ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡

በሃጫሉ ሞት ማግስት የተከሰተውን ብጥብጥ ቀስቅሰዋል ተብለው ከታሰሩት መሐል የባልደራሱ እስክንድር ነጋ ይገኛል፡፡ እስካሁን እንደሰማነው እስክንድርን ለእስርና ለክስ ያበቃው ወንጀል በእነ ጃዋርና በቀለ ገርባ ቅስቀሳ የደም ጅረት ለማፍሰስ ከአዲስ አበባና ከዙሪያዋ ከተነሱት የቄሮ መንጋዎች የአዲስ አበባ ሕዝብ ራሱን እንዲከላከል ለማንቀሳቀስና ለማስተባበር መሞከሩ ነው፡፡ የታሰረበት ምክንያት በእርግጥም ይህ ከሆነ በምን መስፈርት ነው ወንጀል የሚሆነው?  ቆሜለታለሁ ያለው ሕዝብ በማንነቱ ብቻ የዕልቂት አደጋ ሲጋረጥበት በአንድነት ተነስቶ እንዲመክትና ሕይወቱን እንዲያተርፍ እስክንድር ማነሳሳቱን የሚነቅፍ ሞራላዊም ሆነ ኅብረተሰባዊ ሕግ ይኖራል? ከሃጫሉ ሞት በኋላ የሚፈጠረውን ግር ግር እስክንድር ከእነ ጃዋር ጋር ‹‹በመናበብ›› ረብሻ ለመፍጠር ሲንቀሳቀስ ነበር ሲባል የሰማነው ውንጀላ የበሬ ወለደ ዓይነት የማይመስል ነገር ነው፡፡ እስክንድር ከጃዋር ጋር የሚካፈለው ዓላማና ግብ የለም፡፡ ሌላ የሚያስጠይቀው ወንጀል ፈፅሟል ከተባለ ከነማስረጃው ይፋ ይሁን። ካልሆነ ግን ለእስርና ለክስ ያበቃው የአዲስ አበቤዎችን መብት ለማስጠበቅ እሟገታለሁ ብሎ በመነሳቱ ጥርሳቸውን ነክሰውበት የቆዩ የ”ፊንፊኔ ለኦሮሞዎች ብቻ” ሕልመኛ ባለሥልጣኖች አጋጣሚውን ተጠቅመው ቁጭታቸውን ለመወጣት ስለፈለጉ ይመስላል።

የሆነው ሆኖ ግን በአሁኑ ሰዓት ወለል ብሎ ሊገለፅልን የሚገባው እውነታ ከጃዋር ሙሐመድ፣ ከበቀለ ገርባና ከቢጤዎቻቸው ጋር በድርድር ለአገርና ሕዝብ ከሚበጅ ስምምነት ላይ ይደረሳል ብሎ ማሰብ ሞኝነት መሆኑን ነው። እነሱ ፈረንጆቹ rotten apples የሚሏቸው ዓይነት ናቸው፤ የበሰበሰ አፕል ተመልሶ ደህና እንደማይሆን ሁሉ እነሱም ከተጠናወታቸው ሕዝብን የማናከስና የሚጠሏትን ኢትዮጵያን የማፍረስ አባዜያቸው የሚያላቅቃቸው ነገር የለም። በእርጉም ተልእኮአቸው ከቀንደኛ የህወሓት አድራጊ ፈጣሪዎቹ ከእነ ስብሃት ነጋ ፣ ስዩም መስፍን፣ ዐባይ ፀሐዬና ሌሎቹ ፈፅሞ የሚለዩ አይደሉም።

እና አሁን ወዳጅ ጠላቱ በተወሰነ ደረጃ በለየበት ጊዜ በተፈፀመው ግድያና ይከተላል ተብሎ የታሰበውን ዕልቂት በመደገስ ተወንጅለው በቁጥጥር ስር የዋሉት ግለሰቦች ተገቢውን ሕጋዊ ፍርድ እንዲያገኙና በማን አለብኝነት ሲካሄድ የኖረው ግልፅ የሆነ ብሄር ተኮር የጥላች ዘመቻና የዘር ማጥፋት ቅስቀሳ ከአሁን ወዲያ ፈፅሞ ቦታ እንዳይኖረው ቁርጥ አቋማችንን ማሳወቅ ይኖርብናል። ከድክመቱና ከሰራቸው ስህተቶች ጋር የዶክተር ዐቢይ መንግሥት ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ለሕዝቦቿ ደህንነትና ብልፅግና የቆመ መሆኑን መጠራጠር ንፉግነት ነውና ይህን ጠላቶችና ተግዳሮቶች የበዙበትን የሁለት ዓመት መንግሥት ከጎኑ ቆመን ልናግዘው ይገባል።

በመጨረሻም በህወሓት ዘመን ከሌሎች ብሔሮች ተለይቶ ለግፍና ሰቆቃ ተዳርጎ በኖረው የአማራ ሕዝብ ላይ በፅንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ቁስቆሳ የሚካሄደው ፍፃሜ አልባ ግድያና ማፈናቀል ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቆሞ የወንጀሉ ተሳታፊዎች ከላይ እስከ ታች ተለቅመው ለፍርድ እንዲቀርቡ በአንድነት ድምፅ አጥብቀን መጠየቅ ይኖርብናል። በውጭ አገር ሆነው የአማራ ጥላቻ የሚሰብኩና የኦሮሞ ወጣቶች በክልላቸው የሚገኙ አማራና ኦሮሞ ያልሆኑ ኢትዮጵያውያንን እንዲገድሉ፣ እንዲያፈናቅሉ፣ ቤት ንብረታቸውን እንዲዘርፉና እንዲያወድሙ ቅስቀሳ ሲያካሂዱ የኖሩትን እነ ጸጋዬ አራርሳን የመሰሉ የዘር ማጥፋት ዘመቻ አቃጅና አስተባባሪዎች ሲፈፅሙ የኖሩትን ወንጀል ከነማስረጃው የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚኖሩባቸው አገሮች መንግሥታት አቅርቦ አስፈላጊው ሕጋዊ እርምጃ እንዲወስዱ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

አማራዎች በግፍ በታረዱ ቁጥር እኛም በሃዘን ከንፈራችንን መጥጠን ማለፉን መልመዳችን ነውር ነው። ግዴለሽነታችን ለሟቾቹ ሁለተኛ ሞት ነው። ስቃይና ሞታቸው የህሊና ቁስል ሆኖ እረፍት ሊነሳን የሚገባ የወገን ጥቃት ነውና አንድ ሆነን የሟች ቤተሰቦች ፍትህ፤ ሌሎች በኦሮሚያ የሚኖሩ አማራዎች ደሞ የሕይወትና የንብረት ዋስትና የሚያገኙበትን መንገድ ለማረጋገጥ እንትጋ።

ፋሲል ይትባረክ

 

 

2 Comments

  1. Blaming the atrocities committed on Amharas on the victims ie Amharas themselves puts your ramblings useless and says a lot about you unfortunately. Contrary to what you obviously beleI’ve it’s the lack of Amharas identity and unity that has resulted in The atrocities. May I remind you it is your beloved Abiy who invited and financed Jawar, omn, old and all that are still committing these crimes. Also choose one stand don’t waiver.

  2. “ዶክተር ዐቢይ ከሃጫሉ ግድያ የሚያገኘው ውጥንቅጡ የበዛና የመንግሥቱን ኅልውና ከአደጋ ላይ የሚጥል ችግር እንጂ አንዳችም ጥቅም እንደሌለ መረዳት አይሳነውም፡” ይልቅስ አንተን ብቻ ነው የተሳነህ! ሃጫሉን ገድሎ በጅዋር እና ሌሎች የኦሮሞ ፖለቲከኞች አሳቦ በማሰር፣ በመግደልና እንደወያኔ ከሃገር በማባረር፣ ተቀናቃኝ የሌለበት 7ኛው ንጉስ የመሆን የጨቅላ ልጅ ምኞት ለማሳካት የወሰደ ያለው እርምጃ ነው። ህልሙ እውን ይሆናል ወይ ሌላ ነው። ግ ን እሱ በዚህ የስልጣን ጥማት የተጠመደ ስለሆነ፣ በዚያው የምንልክን ስርዐት ለመመለስ የሚያልሙ አዕምሮ ቢሶች፣ ድርጊቱ ሃገሪቷን ገደል እንደሚከታት ማሰብ የማይችሉ የንፍጠኛው ስርዐት ውልዶች ከኋላው ሆነው ይገፋፉታል። ያ ህልማቸው ቅዠት ሆኖ በቅርቡ ያባንናቸዋል!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.