መንግሥት ህግ እና ስርዓትን ለማስከበር ቤቱን ያጽዳ ዛሬም የዜጎች ሕይወት ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ይቁም!

የድምጻዊ ሓጫሉ ሁንዴሳን ግድያ ተከትሎ በቅጽበት ምንም ባልተጨበጠ ማስረጃ በዋናነት አማራ ላይ ያነጣጠረና ቆይቶም ሌሎችንም ያካተተ የዘር ማጥፋት ዘመቻ ታውጆዋል።በዚህ አዋጅ ሳቢያ ከሶስት ቀን በፊት ባወጣነው መረጃ ከመቶ በላይ ንጹሃን መጎዳታቸውን እና መንግስት ህግ እና ሥርዓት የማስከበር ሀላፊነቱን እንዲወጣና የንጹሃንን ሞት እንዲታደግ ጥሪ አድርገናል። በመንግሥት በኩል የተገለጸ የማረጋጋት ሥራ የመሰራቱን ያህል ችግሩን ፍርጥ አድርጎ መፍትሄ የመፈለግ ላይ ዛሬም ዳተኝነት አለ።
106711070 3393949240626680 8242413433580452585 nዜጎች በማያውቁት እና ባላጠፉት ወንጀል አማራ ጉራጌ ክርስቲያን እና ሌላም በመሆናቸው በሰፊው ተዘምቶባቸዋል። ለአብነት የደረሰውን ጭካኔ የተሞላበት ነውረኛ እና ዘረኛ ጥቃት የሚያሳዩ ጥቂት ፍቶቶዎችን እዚህ ለማጋራት ኣንችልም። ተጋድሞ የታረደ ኣንገት፣በድንጋይ የተጨፈጨፈ ክቡር ሰውነት አውሬ እንኳን በማያዳርገው ጫካኔ ዝመትበት ተብሎ የዛመተው ሃይል ይህን ያህል ጥፋት ከአሳሳ እስከ ሻሸመኔ፣ከአዳማ እስከ ባሌ፣ከዝዋይ እስከ ሐረር ከድሬዳዋ እስከ አዲስ አበባ ያን ሁሉ የንጹሃን ሕይወት የቀጠፈው እንቅስቃሴ ለምን በአጭሩ አልተገታም ? የክልል እና የፌደራል የጸጥታ አካላት የት ሔደው ነው የሚለውን ዛሬም መንግስት በኣግባቡ ሊፈትሽ ይገባል።
በመንግስት ውስጥ በአደባባይ ወጥተው አማራ ላይ ዝመት እንዳሉት በይፋ ያላየናቸው ሥልጣናቸውን ተገን አድርገው ይህንኑ የፈጸሙ፣የዜጎች ህይወት እና ለዓመታት ዜጎች በጥረታቸው የገነቧቸው ጥሪቶች እንዲወድሙ ሲደረግ በክልል እና በፌደራል ሥልጣን ስም በልዩ ልዩ ደረጃ ያሉ የጸጥታና የፖለቲካ አመራሮች ተሳትፎ የላቀ ነው።
መንግስት ውስጡ የተሰገሰጉ ዘር አጥፊዎችን አበል እየተቆረጠላቸው፣ከተዘረፈ እየተካፈሉ፣በለው በለው ሲሉ የነበሩ እና ባግልጽ የመከላከያ ሰራዊት አመራሮችን ጭምር እያሳሳቱ እና እያዘናጉ፣ሀሰተኛ መረጃ እየሰጡ በንጹሃን ላይ የተከፈተው የዘር ማጥፋት የተሳካ እንዲሆን የኦሮሚያ እና የሐረሪ አንዳንድ የፖለቲካና የጸጥታ አካላት፣በፌደራል እና በአዲስ አባባ ፖሊስ እና አስተዳደር የተሰገሰጉ የተወሰኑ ዘረኞች ለጥፋቱ መባባስ የየራሳቸው ድርሻ ተወጥተዋል።
ይህ. በቀላሉ ተድበስብሶ ከታላፈ ለጥቂት ቀናት በአንዳንድ ቦታዎች ረገብ ያለው ችግር ተመልሶ ሊያገረሽ ይችላል የሚል ሥጋት አለ። መንግስት ድርጊቱን የፈጸሙ እና ያስፈጸሙን የራሱን ደባል የፖለቲካ ፍላጎት ወደ ጎን አድርጎ ውስጡን ፈትሾ ካላጠራ ትላንት በጃዋር ተከብቤያለሁ ጊዜ ከ86 በላይ ንጹሃን ሞት ምክንያት የሆኑ አመራሮች ፣ የጸጥታ ሰዎች እና አመራሮቻቸው መካከል የነበራቸው ተሳትፎን አድበስብሶ ለማላፍ መሞከሩ መንግስት ውስጥ ያሉ ታማኝ ደጋፊዎቹን የተማመነው ሀይል በይፋ የዘር ማጥፋት ሲያውጅ ተቀባይ እና አስፈጻሚ ሀይል ጭምር በውስጥ እንዳለው ስላወቀ ነው።
ለዓመታት በዜጎች ልፋት የተገነቡ ከተሞች ወድመዋል። ዝዋይ እና ሻሸነኔ ለዚህ ማሳያ ናቸው። በጠራራ ጸሐይ ማየት እንደተቻለው የክልሉ የጸጥታ ሀይል ተገቢውን ሀላፊነቱን አልተወጣም። በዘር ቅስቀሳ ተገፍተው የወጡት ማንም እንደማይነካቸው ያገኙትን መተማምን መሰረት አድርገው ነው። ስለዚህም መንግስት ዳባል የፖለቲካ ፍላጎቱን ወደ ጎን አድርጎ ዘር አጥፊዎችን እና በግልጽ ሀላፊነታቸውን ያልተወጡትን ጭምር ከውስጡ ያጥራ።
የሕግ የበላይነትን በወሬ ሳይሆን መንግስት ውስጡን በመፈተሽ እና ተገቢውን ህጋዊ ምላሽ በመስጠት በተግባር ካላረጋገጠ በኔትወርክ እና በዘር አጥር ውስጥ ውስጡን አንዱ አንዱን አሳልፎ ላለመስጠት የሚደረገው መሯሯጥ ለጊዜው ጋብ ያለውን ችግር መልሶ የሚያቀጣጥል ጥፋት ያረገዘ የተዳፈነ እሳት ነው።
ዜጎች ላይ ያንዣበበው ስጋት ሙለ ለሙለ አልተወገደም። ይህ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል።
ሕብር ራዲኦ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.