ኢትዮጵያ፤ ሱዳን እና ግብፅ ከሰሞኑ

ግብፅ የአባይ ግድብ ጉዳይን ወደ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት መውሰዷ በበርካቶች ዘንድ በአፍሪቃ ኅብረት ድርድር ሙሉ እምነት አላደረባትም አስብሏል። በኹለቱ ሃገራት ነዋሪዎች ዘንድ ስለ አባይ ጉዳይ ንግግሩ በጎላበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተጠበቀ አስደንጋጭ ኹኔታ ተከስቷል።

DW

ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተጠበቀ አስደንጋጭ ኹኔታ ተከስቷል

ግብፅ የአባይ ግድብ ጉዳይን ወደ የተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት መውሰዷ በበርካቶች ዘንድ በአፍሪቃ ኅብረት ድርድር ሙሉ እምነት አላደረባትም አስብሏል። በተለይ በኢትዮጵያውያን እና ግብጻውያን ነዋሪዎች ዘንድ ስለ አባይ ጉዳይ ንግግሩ በጎላበት ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ ያልተጠበቀ አስደንጋጭ ኹኔታ ተከስቷል። የታዋቂው ድምፃዊ ሐጫሉ ሑንዴሳ መገደል በአዲስ አበባ እና ተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች ተቃውሞ እና ኹከትን ቀስቅሶ ወደ 100  ሰዎች መገደላቸውን የተለያዩ የዜና አውታሮች ዘግበዋል። በጎረቤት ሀገር ሱዳን ደግሞ ዳርፉር ውስጥ ነዋሪዎች መንግስት ደኅንነታችንን ከታጣቂዎች አላስጠበቀም በሚል ላለፉት አራት ቀናት የተቃውሞ ሰልፍ አከናውነዋል።

106345633 1681765631974778 5283093066410245533 o e1593360637746

የ«ታላቁ ሕዳሴ ግድብ» ፍጥጫ

ግብፅ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በአባይ ጉዳይ ዛሬም እንደተፋጠጡ ናቸው። ኢትዮጵያ በ4.6 ቢሊዮን ዶላር የምትገነባው ግዙፉን የ«ታላቁ ሕዳሴ ግድብ» አጠናቃ የውኃ ሙሌት በኹለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ እንደምትጀምር ያሳወቀችው በቅርቡ ነው። ግብፅ በበኩሏ ኅልውናዋን ለማስጠበቅ ማናቸውንም አማራጮችን ልትጠቀም እንደምትችል ስተገለጥ ተደምጣለች።

ግብፅ በተደጋጋሚ ያንጸባረቀችው አቋም እና እንቅስቃሴ ኢትዮጵያውያንን በተለየ ኹኔታ ወደ አንድ የጋራ ሀገራዊ ግብ አሰባሰቦ የኢትዮጵያ ድምፅ በዓለም መድረክ ጎልቶ እንዲሰማም አስችሎ ነበር። የተለያየ የፖለቲካ አቋም ያላቸው ቡድኖች እና ግለሰቦች ሳይቀሩ ለአባይ ወንዝ ግድብ በጋራ መቆማቸውን ግን ለግብፅ መንግሥት ቅርብ የኾኑ ፖለቲከኞች እና ታዋቂ ሰዎች የወደዱት አይመስልም። በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎቻቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ቅራኔ ሊነሳ እንደሚችል፤ በሀገሪቱ ያለው ሰላምም አስተማማኝ እንዳልኾነ በተደጋጋሚ በዘመቻ መልክ በመግለጥ ሲንቀሳቀሱ ተስተውለዋል።

የ«ታላቁ ሕዳሴ ግድብ» የማደራደር ተግባርን የአፍሪቃ ኅብረት በያዘበት ወቅትም ግብጽ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መመልከቷ በእርግጥ ግብፅ የአፍሪቃን ችግር በአፍሪቃውያን መፍታት ለሚለው መርኅ ትገዛለች ወይ የሚል ጥርጣሬ አጭሯል። የግብፅ ኅልውና አደጋ እንደተደቀነበት በመጥቀስ «የመኖር ኅልውና የምርጫ ጥያቄ አይደለም» ሲሉም የውጭ ጉዳይ ሚንስትሩ ሳሚ ሹክሪ በጸጥታው ምክር ቤት የኢንተርኔት ስብሰባ ከካይሮ ኾነው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ በኩል በተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ቋሚ መልእክተኛ አምባሳደር ታዬ አጽቀ-ሥላሴ በምክር ቤቱ በዕለቱ ያሰሙት ንግግር በበርካቶች ዘንድ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቅ ቆፍጠን ያለ መልስ በሚል ተወድሷል። የ«ታላቁ ሕዳሴ ግድብ» ጉዳይ ወደ ፀጥታው ምክር ቤት መቅረቡ በራሱ «ፍትኃዊ አይደለም» ብለዋል አምባሳደሩ። በአካባቢ ሃገራት መካከል ውዝግቦች ሲነሱ ሃገራቱ ቅድሚያ በቃጣናዊ ተቋሞቻቸው በኩል መፍትኄ መፈለግ እንዳለባቸው የተባበሩት መንግስታት እንደሚያበረታታም ጠቅሰዋል።

ግድያ የተፈጸመበት ታዋቂው ድምፃዊ ሐጫሉ ሑንዴሳግድያ የተፈጸመበት ታዋቂው ድምፃዊ ሐጫሉ ሑንዴሳ

ታዲያ ግብፅ የአፍሪቃ ኅብረት ጉዳዩን በያዘበት ወቅት ወደ ፀጥታው ምክር ቤት ማምጣቷ ተገቢ አለመኾኑን አስምረውበታል።

አስደንጋጩ ግድያ

ሰኞ ምሽት ይኽንኑ የፀጥታው ምክር ቤት ንግግር በርካታ ኢትዮጵያውያን በንቃት በሚከታተሉበት ወቅትም ኢትዮጵያውያንን እጅግ ያስደነገጠ ነገር ተከሰተ። ታዋቂው ድምፃዊ ሐጫሉ ሑንዴሳ መገደሉ ተሰማ። ቊጣ፤ ተቃውሞ እና ኹከት በአዲስ አበባ እና በኦሮሚያ ክልል በቀጣዩ ቀናት ተከስቶም ወደ 100 ሰዎች መገደላቸውን የዜና አውታሮች ዘገቡ።

መንግስት ወንጀል ፈጽመዋል ሲልም ታዋቂ ፖለቲከኞችን እና በርካታ ሰዎችን በቊጥጥር ስር አዋለ። ከታሰሩት መካከል የኦሮሞ ፖለቲካ አቀንቃኙ እና የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ መስራች አቶ ጃዋር መሐመድ፤ የኦሮሞ ፌደራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) አንጋፋ ፖለቲከኛ አቶ በቀለ ገርባ እና ሌሎችም ይገኙበታል። ባልደራስ ለእዉነተኛ ዴሞክራሲ የተባለዉ ተቃዋሚ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋም ከታሰሩት መካከል እንደሚገኝ ተጠቅሷል።

የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኘው ጣቢያ የተዘጋ ሲኾን፤ ቊጥራቸው በውል ያልታወቊ ሠራተኞቹም በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጧል። የታሳሪዎቹ ጉዳይ በፍርድ ሒደት እንደሚታይ መንግስት ዐስታውቋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቴሌቪዥን ፊት ቀርበው ንግግር ሲያሰሙጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቴሌቪዥን ፊት ቀርበው ንግግር ሲያሰሙ

በሀገር ቤት በተለይ አዲስ አበባ ወደ ቀድሞ መረጋጋቷ ስትመለስ ከሀገር ውጪ በተለያዩ ሃገራት በሚገኙ ከተሞች ግን የኦሮሞ ብሔር ተወላጆች ተቃውሞዋቸውን አሰምተዋል።  እንግሊዝ ለንደን ከተማ የሚገኘውን የአጼ ኃይለሥላሴ ሐውልት ያፈረሱ ሰዎችን የእንግሊዝ መንግሥት ለፍርድ እንደሚፈልጋቸውም ተዘግቧል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ዐርብ እለት በቴሌቪዥን ፊት ቀርበው ባሰሙት ንግግር በ«ታላቁ ሕዳሴ ግድብ» ጉዳይ ስኬታማ ያልኾኑ የውጭ እና የሀገር ውስጥ ኃይላት በዚህ ወቅት በሀገሪቱ ትርምስ ለመፍጠር ከፍተኛ ጥረት ማድረጋቸው እና መክሸፉን  ይፋ አድርገዋል።

ተቃውሞ በሱዳን

በመቶዎች የሚቆጠሩ ሱዳናውያን ዳርፉር ግዛት ውስጥ መንግስት ደኅንነታችንን ያስጠብቅ ሲሉ ትናንት የተቃውሞ ሰልፍ አከናውነዋል። የተቃውሞው ምክንያትም በቅርቡ በነዋሪዎች ላይ በተከሰቱ ግድያዎች እና ምዝበራዎች የተነሳ መኾኑን የዐይን ምስክሮች መናገራቸውን የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ሱዳን፤ ዳርፉር ግዛት ትንሽ ልጅ የእንቷን ልብስ ይዛ በዛም ዛም ስደተኞች ሠፈር ስትጓዝሱዳን፤ ዳርፉር ግዛት ትንሽ ልጅ የእንቷን ልብስ ይዛ በዛም ዛም ስደተኞች ሠፈር ስትጓዝ

ባለፈው ሳምንት ያልታወቊ ታጣቂዎች ኔርቲቲ ከተማ ውስጥ ሦስት ገበሬዎችን ገድለው መሰወራቸው በአካባቢው ውጥረት አንግሷል። ከተቃውሞ ሰልፈኞቹ አንዱ ለዜና አውታሩ እንደተናገረው ተቃዋሚዎች ኔርቲቲ ከተማ ውስጥ ከሚገኘው የመንግስት መሥሪያ ቤት ፊት ለፊት ሰልፍ ማከናወን ከጀመሩ አራት ቀናት አልፏቾዋል። ዳርፉር ውስጥ ለ17 ዓመታት ግድም በዘለቀው ግጭት ዳፋ 300,000 ሰዎች መገደላቸውን እና 2.5 ሚሊዮን ነዋሪዎች ከቀዬያቸው መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታ ዘግቧል።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.