ሐጫሉን ማን ገደለው?ለምን? መንግስት ሆይ ቁማሩ ይብቃ! – ሰርፀ ደስታ

hachalu 1አሁንም ያችው የተለመደች ነገርን አደበስብሶ ማለፍ ላትደገም አንዳቸውም ዋስትና የለንም፡፡ መንግስ የሚባለው አካል እኛ እሱም ባይነግረን የምንናገረውን ነው እስካሁም መልሶ እየነገረን ያለው፡፡ የጠቅለይ አቃቤ ሕጓ አበበች አቤቤ ለጋዜጠኞች የሰጠችው መግለጫ እንደምታወራው ነገሮች የሚፈጸሙ ከሆነ ጥሩ ነው፡፡ በቃ እንዳለቸው የዘመናት በሕዝብ ደም፣ ሞትና ሥቃይ ላይ መቆመር ሊበቃ ይገባዋልና፡፡ ሌሎች የሚያወሩትን ብዙም ትኩረቴን ሊስበው አልቻለም፡፡ አሁንም ማስመሰል እንደሌለበት ምንም ማረጋገጫ የለንም፡፡ በአብዛኛው የምንሰማቸው የባለስልጣኑ ንግግሮች የእኛን ስነልቦና ለመማረክ እንጂ ከውስጥ የሆነ ቁርጠኝነት ለመሆኑ ምንም ዋስትና የለም፡፡ የምንሰማቸው ድምጾች ከምናውቀው የማስመሰል ንግግራቸው ምንም የተለየ አደለም፡፡ ወሳኝ የሆነ በተግባር የተገለጠ እርምጃ ለማየታችን እጅግ እጠራጠራለሁ፡፡ አሁን ሁኔታው በጣም ስለተጋጋለ እንጂ ከአንድ ሶስት ቀን የመረጋጋት በኋላ እንደተለመደው ላም ባልዋለበት አይነት ሌላ ፖለቲካ በመፍጠር እውነትን መበረዝ ሊኖር እንደሚችል እሰጋለሁ፡፡ አሁንም አንዳንድ የማያቸው እንቅስቃሴዎች ጥሩ አደሉም፡፡

እንግዲህ የሐጫሉን ግድያ እየመረመርኩ ነው የሚለን ፖሊስ እስካሁን ቢያንስ ማን እንደገደለው በግልጽ አላወኩም የሚል ከሆነ መቼም ቢሆን አውቄዋለሁ እንደማይለን ጠብቁ፡፡ ሐጫሉን የገደሉትን እስካሁን አሳምሮ ያውቃል ግን በተለመደው ነገሮች በረድ ሲሉ አድበስብሶ ሊያልፈው እንጂ፡፡ እስካሁን ከአላወቀው ደግሞ መቼም ሊያውቀው አይችልም፡፡ በተደጋጋሚ ጉዳዩ የረቀቀ ነው እያሉን እንሰማለን፡፡ ለምንና በየትኛው ፖለቲካዊ ወይም ሌላ ሴራ ከገዳዮች ኋላ ያሉ ግለሰቦችን ሰንሰለት ማወቁ ጊዜ ሊወስድ ይችላል፡፡ ሆኖም ግን ገዳዮች እነማን እንደሆኑ በከፊልም ለምንና በምን ሴራ ሐጫሉን እነድገደሉት በዚህ ሶስት ቀን በእርግጥም ማወቅ ይገባዋል ባይ ነኝ፡፡

ሌላው አደገኛ የሆነው ንግግራቸው ይሄን ጉዳይ ሁሉም ትግላችንን አዲስ አበባ ጀምረን አዲስ አበባ እንጨርሳለን ያሉ ቡድኖች ናቸው የሐጫሉን ግድያ ያቀነባበሩት ሲሉ ጊዜም አልፈጀባቸውም፡፡ ይሄን ያህል ከወቁ ደግሞ ገዳዮቹን ብቻም ሳይሆን ከገዳዮቹም ጀርባ እነማን እንደሆኑ አውቀዋል ማለት ነው፡፡ ይሄ ከሆነ ደግሞ በቀጥታ እነዚያኑ የተባሉትን ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች በሐጫሉ ግድያ ስለጠረጠርኳቸው ይዣቸዋለሁ ማለት እንጂ እንደ ልብ ወለድ ዝም ብሎ በጅምላ መናገር ጉዳዩን ግልጽ የሆነ ትኩረት እንዳያገኝ የሚደረግ ጥረት እንዳይሆን እሰጋለሁ፡፡ ከዚህ በፊት የአማራ ክልል ሰዎች የተገደሉ ጊዜ አሳምነው ነው ገዳይ ለማለት ጊዜ አልፈጀባቸውም ነበር፡፡ ጉዳዩን ገና ሲጀመር ነበር መፈንቅለ መንግስት ያሉት፡፡ ይባስ የአገሪቱ የታማጆር ሹምን የሚያህል ሰው ሲገደል በቅጽበት አሁንም በአሳምነው የተቀጠረ የገዛ ጠባቂያቸው አሉን፡፡ ያ ጠባቂ መጀመሪያ ሞተ ተባለ፣ ከዛ ተነሳ፣ ከዛ ደግሞ መናገር አይችልም እስከሚሻላው ብለውን ይሄው ሌላ ሰኔ መጥቶ አሁነም ሌላ አደጋ አየን፡፡ እንግዲህ እንዲህ ያሉ ቁማሮችን ስንሰማ ቆይተን የሐጫሉን ጉዳይ በግልፅ ፍትህ ያገኛል ለማለት እርገጠኞች መሆን አንችልም፡፡ መሠረታዊ ችግራችን እዚህ ጋር ነው፡፡ ሕዝቡ የሚለውን ማስተጋባት ሳይሆን መንግስት ተብዬው ከሕዝብ በተለየ መረጃ ሊኖረው ይገባል፡፡ አደጋው እስከሚከሰት ላይታወቅ ይችላል ሆኖም አደጋ ከተከሰተ በኋላ በፊትም ምልክቶች ነበሩኝ የሚል መንግስት አሁን እነማን እንደፈጸሙትና እንዴትና ለምን የሚለውን ለመመለስ ጊዜ ሊወስድበት አይችልም፡፡ በመሆኑም መንግስት ነኝ የሚለው አካል ራሱን በተግባር በሚገለፁ እውነታዎች ራሱን ለሕዝብ ግልጽ ሊያደርግ ይገባል እላለሁ፡፡ ከወዲሁ ነገሮችን ማሳከር የሚመስሉ ምልክቶችም አያለሁና፡፡

ሌላው ለመላው ኢትዮጵያውያን፡፡ ዛሬስ ትንሽ እንኳን ብትሆን መማር እንችል ይሆን? የዘርና ጥላቻ ትርክት አንድ ዛሬ ሙሉ ቢያንስ 30ዓመት የሞላው ትውልድ እንደፈጠረ ማስተዋል እንችል ይሆን? 30 ዓመት ያልኩት ሁለተኛ ትውልድ የተጀመረበትን እንጂ 60ና 70ዓመትም በጥላቻና ዘረኝነት እድሜያቸውን እያገባደዱ ያሉም አሉ፡፡ በዚህ ሁኔታ አብረን እንደሕዝብ ለመኖራችን አጠያያቂ ነው፡፡ እባብ ሞኝን ሁለቴ ነደፈው ይባላል፡፡ አንዴ ሳያየው ሁለተኛ ጊዜ ግን ከጓደኛው ጋር መንገድ ሲሄድ እባብ መንገድ ላይ ተጠቅልሎ ሲያገኝ ባለፈው የነደፈኝ እኮ ይሄ ነገር ነው ብሎ በእጁ ነክቶ ለጓደኛው ሲያሳይ ነው፡፡ እንጂማ እባብ ብልጡንም በድብቅ በተደጋጋሚ ሊነክሰው ይችላል፡፡ የእኛ ግን የሚመሳሰለው ከሞኙ ጋር ነው፡፡ ብዙ ጊዜ አይናችን ያየውን፣ የሆነብንን ሁሉ ሳናስተውል ዛሬም ለአራጆቻችን የእርድ በግ መሆናችን ነው የሚገርመው፡፡ የዘር ፖለቲካ ይቅር ሲባል እንደዛ እብድ የሚያደርጋቸው፣ የፍቅርና የሠላም የሚመስሉ ነገሮችን ሁሉ ነፍጠኛ፣ አሀዳዊ፣ ሚኒሊካዊ፣ የቀድሞ ሥርዓት ናፋቂ፣ የመሣሰሉት በማለት ያሳክሩናል፡፡ የሚያናድደው ግን በጣም በወረዱ ወራዳዎች እንዲህ መዘወራችን ነው፡፡ የማንም ወሮበላ ከምንም ተነስቶ በዚህ መልኩት ትልቅ እየሆነ አገርና ሕዝብ ሠላም ይሆናል ብላችሁ ካመናችሁ አዝናለሁ፡፡

ሰሞኑን ከሐጫሉ ግድያ ጋር በተያያዘ ይዘንዋል እያሉ የሚያቅራሩብን አሸባሪና ወሮበላ ከጅምሩ ጀምሮ የእሱን ተራ የሽብር እንቅስቀሴ እያሳደጉለት የመጡ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህ ግለሰብ ከጅምሩ ከአሰላ ወጣቶችን በማሳሰር ለወያኔ ሲሰራ የነበረ ኋላም ወደ ሲንጋፖር አንድ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተላከ፣ ከዛም በአሜሪካ ለተመሳሳይ የዘርና ጥላቻ ሥራ የተላከ ነው፡፡ ይሄው ግለሰብ በሳን ፎርድ የፖለቲካ ሳይንስ አጠናሁ ይልሀል፡፡ የሳንፎርድ የፖለቲካ ሳይንስ የቀድሞ ተማሪዎችን በድህረ ገጹ በደንብ መዝግቦ እናያለን፡፡ ይሄን እንግዲህ ሁሉም ገብቶ ሊያየው ይችላል፡፡ በነገራችን ላይ በተለይ በኦሮሞ ሕዝብ እየነገዱ ያሉ ያአገርና ሕዝብ ጠላቶች ሌሎችም አሉ ያልደረሱበትን ትምህርት በራሳቸው ተመርቀናል በሚል ራሳቸውንም ዶ/ር እስከማለት የደረሱ፡፡ ይህን ማንነታቸውን ሕዝብን ለመመረዝ ስለሚጠቀሙበት እንጂ የፈለጉትን ማለት ይችላሉ፡፡ እንደነ ጀዋር ያሉ ወሮበሎችን እዚህ ለማድረስ ታዲያ የኢትዮጵያ ነን የሚሉ ብዙ ሚዲያዎችም አስተዋጾ አላቸው፡፡ ጀዋር እንዲህ አለ እየተባለ አጫፋሪውም ብዙ ነበር፡፡ ከወራዳ ጋር ወራዳ ትሆናለህ እንደተባለው ማለት፡፡ ዛሬ መንግስት የሚባለው አካል ይዤዋለሁ ይለናል፡፡ ሆኖም ግን  አስከሬን በመመለስ በሚል ሊድበሰበስ ተሞክሯል፣ በገዳይነት ለማለት አልፈለጉም በኋላ አድበስብሰው ሊያልፉት እያዘጁ ሊሆን እንደሚችል አገምታለሁ፡፡

መረራ ጉዲና ዛሬ በኦኤም ኤን ቀርቦ መፍትሄው መነጋገር ነው ይለናል፡፡ በሽምግልና ምናምን እየተባለ ስንት ወንጀል የሰራን እንደዋዛ ሲቀልዱብን ኖረዋል፡፡ የመረራ ንግግር ስለፍትህና ሕግ አንዳች ግድ እንደሌለውና ወንጀል ሊያውም ሰው የገደለን፣ አገርን ለማፈራረስ ያሴረን አደገኛ ወንጀለኛ በመነጋገር ሊዳኝ ይገባዋል ይለናል፡፡ መረራ ጉዲና ዛሬ አትሸውደንም፡፡ ይህ ግለሰብ ሲጀምር ኢትዮጵያዊነ ነው ወይ የሚለውን አሁንም መንግስት ተብዬው እሰካሁን ግልጽ ሊሆን አልቻለም፡፡ እንግዲህ እንደፈለጉ ከሕግና ስርዓት ውጭ ወንጀለኞችን ዋስትና እየሰጡ በአገርና ሕዝብ መቆመር የለመዱት በመሆኑ ነው የዛሬው የመረራ ንግግር፡፡ አዝናለሁ በሐጫሉ ሞት ምክነያት ብቻ ሳይሆን ቀድሞም 86 ሰው(ቁጥሩ ከዚህ በላይ ነው መንግስት የተባለው ያለውን እንጂ) ደም ሁሉ ሕግ ከሠራ ፍትህ እንፈልጋለን፡፡ ይሄ እንግዲህ በማንነት እየተከለሉ የፈለጋቸውን እየሰሩ ለሚኖሩ አይመቻቸውም፡፡ ሆኖም ግን ከዚህ በኋለ  ወይ ሕግና ሥርዓት መከበር ግድ ሊሆን ይገባል እላለሁ፡፡ መንግስ የሚባለው ይሄ የሕዝብን ሥነለቦና እየተከተለ የሚቆምረውን ቁማር ሊያቆም ይገባል እላለሁ፡፡ እጅግ ወደከፋ ነገር እየሄድን ነው፡፡ በተለያዩ ቦታዎች በጥቅምት ወር አደጋ የደረሰባቸው ዛሬም በድጋሜ የሚያሳዝን አደጋ ደርሶባቸዋል፡፡ ለዚህ ዋነኛ ተጠያቂው ደግሞ መንስት የሚባለው አካል ነው፡፡

በመጨረሻም እደግመዋለሁ የሐጫሉ ገዳዮች እስካሁን መታወቅ አለባቸው፡፡ ይህ ካልሆነ ከዚህ በኋላ እያጣራን ነው የሚለው የተለመደው ቁማር ሊሆን እንደሚችል እሰጋለሁ፡፡ ዛሬውኑ የወንጀለኞችን ሥም ዝርዝር እንዲያወጣልን አደለም፡፡ ግን አንዳንድ ንግግሮች ነገሩን ለማደባበስ እየተሞከረ እንደሆነ ስለሰጋሁ እንጂ

ቅዱስ እግዚአብሔር የወንድማችንና በግፍ የሞቱትን  ነብስ ሁሉ  በገነት ያኑር! ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከክፉ ይጠብቅ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.