አስቸኳይ አገራዊ ጥሪ ለመላዉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዉንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በሙሉ!!

Global አስቸኳይ አገራዊ ጥሪ ለመላዉ አገር ወዳድ ኢትዮጵያዉንና የኢትዮጵያ ወዳጆች በሙሉ!!ቀን 24/10/2012 ዓም

በቅድሚያ በሰኔ  22 ቀን 2012ዓ. ም. ምሽት ላይ በመኖሪያ ቤቱ አካባቢ እንዳለ በአሰቃቂ ሁኔታ በቅጥረኞች እጅ ህይዎቱ ያለፈዉ ወንድማችን አርቲስት ሀጫሉ ሁንዴሳ ሞት ድርጅታችንን እጅጉን ያሳዘነ እና ድርጊቱን በፅኑ የምናወገዘዉ ሲሆን ወንድማችን ላለፉት በርካታ  አመታት የሀገራችን የሙዚቃ ፈርጦች ዉስጥ አንዱ ነበር::  በዚህም ስራዉ መላዉ የሀገራችን ህዝብ ሲያስበዉ ይኖራል::  መንግስትም እነዚህን ወንጀለኞች እስካሁን እንደተደረገዉ በሆደ ሰፊነት በሚል ወንጀለኞች የፈለጉትን እየሰሩ የሚኖሩበት ዘመን ማብቃትና ሁሉም ሰዉ በህግ ስር መሆኑን ሊያሳይ የሚችል ተመጣጣኝ እርምጃ እንዲወስድ አበክረን እንደ እሰከ ዛሬዉ እንጠይቃለን::

ሀገራችን ኢትዮጵያ ላለፉት ብዙ ሽህ ዘመናት ዓለምን ያስደመሙ ስልጣኔዎችን፣ የታሪክ አሻራዎችን፣ የነፃነት ትግሎችን ለዘመናት ፈፅማለች ወደፊትም ትፈፅማለች::  በአንፃሩም እጅግ አስከፊ የእርስ በእርስ ጦርነቶችን፣ የተፈጥሮ ድርቅና እርዛትን፣ የሰብአዊ መብት ጥሰትን በሰፊዉ ሲፈፀምባት ነበር:: ያሉንን መልካም ነገሮች አዳብረን የጎደሉንን እያሟላን ከአባቶቻችን የተረከብናትን ሀገር ለልጆቻችንን እና ለልጅ ልጆቻችን ለማስረከብ ብርቱ ጥረት የምናደርግበት ወቅት አሁን በፊታችን ተደቅኗል::

በአጠቃላይ ላለፉት ሰላሳ አመታት ሀገራችንን እንደ ሀገር እንዳትቆም የሚፈልጉ የዉጭ  መደበኛ ጠላቶቿና  የዉስጥ ተከፋይ ቅጥረኛ ኃይሎች ሀገራችንን ከአለም ካርታ ላይ ለመሰረዝና ህዝቡን በሞት፣ በስደት፣ በድህነት፣ እና በመሳሰሉት አስከፊ ችግሮች እንዲገባ ሌት ተቀን እየሰሩ እንደሆነ ሁላችንም እያየነዉ ያለ የአደባባይ ሚስጥር ነዉ:: በተቃራኒዉ ሀገራችንን እንጠብቃለን የምንል ከማንኛዉም ነገራችን በላይ የሀገራችን ህልዉና የሚያሳስበን ኢት ዮጵያዉያን ከሞላ ጎደል የቋንቋ፣ የሀይማኖት፣ እንዲሁም ሌሎች ልዩነቶች ሳይገድቡን የምንችለዉን ስናደርግ ነበር:: ምንም እንኳን በትናንሽ ነገሮች በመራኮት ትልቅ ስራ የምንሰራበትን ገንዘባችንን፣ ጊዜአችንን፣ እዉቀታችንና ኃይላችንን ለብዙ ጊዜ ጠላትንና ወዳጅን ባለየ ሁኔታ ስንጋፋ ብንኖርም፣ አሁን ግን ከጫፍ ጫፍ ለሀገራችን ዘላቂ ጥቅምና ልአላዊነት  የምንቆምበት ጊዜ አሁን ባለነዉ ኢትዮጵያዉያን እጅ ላይ ወድቋል::

የጥፋቱ ኃይል እጅግ መሰረት በያዘና በተቀነባበረ ሁኔታ ከአለም አቀፍ እስከ አገር አቀፍ ድረስ የጥፋት ሰንሰለት ዘርግቶ በሀገራችን ሁለንተናዊ ህልዉና ላይ እጅግ የተወሳሰበ ሴራ እየሰራ ይገኛል:: ለአብነት የሩቁን ትተን በቅርብ የተከሰቱ ክስተቶችን ብናነሳ፣ ሀገራችን በግዛቷ ዉስጥ ያለዉን ሀብቷን ለመጠቀም ሁሉም የአለም ክፍል እንደሚደረገዉ በአባይ ወንዝ ላይ ለሚሰራዉ ግድብ የዉሀ ሙሊት እንዳትጀምር ከአሜሪካ መንግስት እስከ አረብ ሊግ በአንድ ላይ ከግብፅ መንግስት ጋር በመቆም አለም አቀፍ መብት ከሚፈቅደዉ ዉጭ በሀገራችን የመልማት መብት ላይ ጣልቃ በመግባት የወሰዱት ታሪካዊ አሳፋሪ ዉሳኔ ዘወትር ትዉልድ የማይረሳዉ ነዉ::  ከዚህ በተጨማሪ የአለም ባንክ ከዚህ በፊት በንጉሰ ነገስቱ ዘመን የአባይ ግድብ እንዳይገደብ ብድር በመከልከል ለአርባ አመት በላይ እንዳዘገየን ሁሉ አሁንም ለሀገራችን ለሌሎች ሀገሮች እንደሚሰጠዉ ሁሉ የሚሰጠዉን ብድርና እርዳታ ከተፈራረመ በኋላ መከልከሉን ስንሰማ እጅጉን ከተኛንበት እንቅልፍ ነቅተን በአንድነት እንድንቆም እንጅ እንድንለያይ የሚያደርገን አይደለም::   ይህንን አለም አቀፍ ጫና እና ሴራ በመጀመሪያ የራሳችን አቅም በማቀናጀት፣ በተጨማሪም በአለም ያሉትን የኢትዮጵያ ወዳጆች  በማንቀሳቀስ ትልቅ እምቅ ኃይል በመፍጠር ዳግማዊ አድዋን በዚህ ትዉልድ መድገም አለብን  ::  በሀገር ዉስጥም እንዲሁ በተቀነባበረ ሁኔታ ከዚህ በፊት ከአመት በፊት ተከብቤያለሁ በሚል ቲያትር ከጉዳዩ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸዉ ንፁሀን በአደባባይ ሲታረዱ ያየን ሲሆን በቅርቡ ወንድማችን በግፍ ከተገደለ በኋላ በተመሳይ ሁኔታ በተጠናከረ ሁኔታ ከአገር አቀፍ እስከ አለም አቀፍ የተቀነባበረ የጥፋት ስራ እየተሰራ ነዉ::  እነዚህ ኃይሎች በተቀነባበረ እና በተደራጄ ሁኔታ ስራ በመከፋፈል በአለም አቀፍ ደረጃ የሀገራችንን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በማበላሸት፣ በሀገር ዉስጥ ንብረትን በማዉደም፣ በሰዉና በንብረት ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት በማድረስ፣ ታሪካዊ ሀዉልቶችን ከሀገር ዉስጥ እስከ አለም አቀፍ ድረስ በማፍረስ፣ አገራዊ ሚስጥሮችን አሳልፎ በመስጠት፣  በህገመንግስታዊና ፖለቲካዊ መብቶችን እንደ ተገን በማድረግ የፖለቲካ ምህዳሩ በዉጥረት እንዲሞላ በማድረግ፣ በመንግስቱ መዋቅር ዉስጥ ፈጥነዉ በመግባት ከኤምባሲ እስከ ፖሊሲ አዉጭ ድርስ በመሰግሰግ በተናበበ ሁኔታ አወዛጋቢ ነገሮችን በማሰራጨት፣ በዉጭ ሀገር በተደራጄ ሁኔታ በመንቀሳቀስ ሰልፎችንና ረብሻዎችን በማድረግ፣ የተለያዩ ሚዲያዎችን በመጠቀም ሀገሪቱ ወደ ብሄርና ሀይማኖት ብጥብጥ እንድትገባ ሌት ተቀን መስራትና የመሳሰሉትን ተግባራት ያለመታከት እየሰሩ ይገኛሉ::

ከዚህ ሁሉ ከተፈረደብን ዉጥንቅጥ ዉስጥ ለመዉጣት ብቸኛዉ መፍትሄ ልዩነትን አቻችሎ ለሀገር ህልዉናና ጥቅም  በአንድነት በመቆም ሀገራዊ ጥቅምንና ህልዉናን ከግልንና ከቡድን ጥቅሞች በማስቀደም  እጅ ለእጅ ተያይዘን የሀገራችንን ህልዉና እና እድገት እዉን ለማድረግ በጋራ መረባረብ  እንጅ ሀገር ስትደማ ቁሞ መመልከት ወይም በየፊናችን ለየግላችን መሮጥ አይደለም ::   ይህንን ስንፍና እኛ ሀገር ወዳዶቹ የምንፈፅም ከኆነ ለሀገር አጥፊዎቹ ቦታ እንዲሰፋቸዉ መልቀቅ ነዉ   አሁን ያለዉ በስልጣን ላይ  ያለዉ መንግስትም የሀገራችንን አንድነትና ልአላዊነት በማስከበር የህግ የበላይነትን እንዲያሰፍንና ወንጀለኞቹን ለፍርድ እንዲያቀርብ እንጠይቃለን::  በዚህ ሽፋን ግን ለሀገራችን እዉነተኛ ዲሞክራሲያዊ ለዉጥ የሚታገሉትን ሀይሎች እንዳያጠቃ ለማሳሰብ እንወዳለን::  ::  ድርጅታችን እስካሁን እንደሚያደርገዉ  አሁንም ከሁሉም ሀገር ወዳድ ኃይሎች ጋር ተባብሮ ለመስራት ፈቃደኛ መሆኑን ይገልፃል ::

ድር ቢያብር አንበሳ ያስር!!

ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር

አለም አቀፍ የኢትዮጵያዉያን የትብብር መድረክ

Email. Inter.ethiopiansolidarityforum1@gmail.com

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.