እንኳን መሞት አለ ማርጀት (ዘ-ጌርሣም)

 

fikerአያ እርጅና
ተደብቀህ ትከርምና
ሰዎችን አዘናግተህ
ትመጣለህ ዕድሜ ቆጥረህ
ቀርቷል ተብለህ ስትታማ
ከች ትላለህ ሳታቅማማ
እንኳን መሞት አለ ማርጀት
ብሎ ነበር የኔ አባት
ስለገባው መዳከሙ
እጅና እግሩ መዛሉ
አያ እርጅና እንዴት ከረምክ
ዕድሜ አስልተህ ከየት ብቅ አልክ
ማሸበቱ ሳይበቃህ
የራስ ፀጉር መጨረስህ
ፊትን አጨማዶ
መጅራትን ጨምድዶ
ዓይኖችን አሞጭሙጨህ
ወገብን አሽመድምደህ
ጉልበተን በማንበርከክ
ህዝበ አዳምን ጉድ አረክ
ትልቁን ትንሽ አርገህ
ነበርኩ እንዲል አሰኝተህ
በጫማህ ስር አዋልከው
የሰው እጅ አሳየኽው
ሴት ወንዱን ስታስፈራራ
ዕድሜን በውል እንዳይጠራ
ሽማግሌ ላለመባል
ራሱን እንዲሸነግል
ድንገት ብቅ ትልና
ትለዋለህ ወደኔ ና
ማን አለብኝ ብሎ ሲኩራራ
ትቢት ይዞት ሲንጠራራ
ሁብታም ነኝ ብሎ ሲደነፋ
በአፍ በጢሙ ሰው ሲያዳፋ
እንዳልነበር በአንድ ወቅት
ዛሬ ሊሆን ተረት ተረት
አንተ መጥተህ ስትጎበኘው
አቅሙን ነስተህ ስታስተኛው
እንኳን መሞት አለ ማርጀት
ብሎ ነበር የኔ አባት

 

አያ እርጅና እንዴት ከረምክ
ዕድሜ አስልተህ ከየት ብቅ አልክ
የዚያን ጀግና ጉልበት ሰርቀህ
ያን ዉበቷን በቁም ገፈህ
ፀጉርን በቀለም አስለቅልቀህ
መከበሪያን ፂም አስላጭተህ
አሻንጉሊት በማስመሰል
ዕድሜ ጠገብ ላለመባል
ላብ ጠብ ተደርጉ የተገኘው
የኮስሞቲክ ሲሳይ ነው
ከንቱ ድካምና ልፋትህ
እርጅና እንደሁ አይቀርልህ
ለገባውና ለተረዳው
ማርጀት እኮ መከበር ነው
ዳሩ ግን ክብር ጠፍቷል
መዋረድን ሁሉም ለምዷል
ያውም ለእርጅና ለማይቀረው
የተፈጥሮ ህግ ለሆነው
እንኳን መሞት አለ ማርጀት
ብሎ ነበር የኔ አባት

 

አያ እርጅና እንዴት ከረምክ
ዕድሜ አስልተህ ከየት ብቅ አልክ
ኑሮ ኑሮ ማርጀት
የሚለየው ከመሞት
ጥሩ ዳኛ ሀቀኛ ነው
ለሚፈርደው ይግባኝ የለው
ሀብታም አይል ትልቅ ቦርጫም
ድሃም ቢሆን አመዳም
ዳኛ ቢኖር በከሰስኩህ
ጠበቃ አቁሜ በሞገትኩህ
ሰውን ያክል በመጣልህ
እጅና እግሩን በመያዝ
አዕምሮን በማደንዘዝ
በርካታ ነው ወንጀልህ
በህግ የሚያስጠይቅህ
ስፖርተኞች ቢያድሙም
ባለጠጎች በምቾት ቢደጉሙም
የሰራዊትህ ብዛቱ
የሚያስሩና የሚፈቱ
ወገብ የሚጠመዝዙ
ማጅራት መተው የሚያፈዙ
ጉልበት ጠርናፊው
የቁም እስር አጓሪው
የራስ ፍልጠት
የሆድ ቁርጠት
ከፈጣሪህ አጣልተው
አሞኝ እንጅ ተመስገንን አስረስተው
ወዳጅ አልባ አደረጉህ
ሁሉም ከልብ ጠላህ

እንኳን መሞት አለ ማርጀት
ብሎ ነበር የኔ አባት

አያ እርጅና እንዴት ከረምክ
ዕድሜ አስልተህ ከየት ብቅ አልክ
እንኳን መሞት አለ ማርጀት
ብሎ ነበር የኔ አባት

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.