ከግብፅ ሴራ ጀርባ ያሉ ኃይሎች እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ ተጠየቀ

J06A8575 696x464 1አዲስ አበባ፡- በአባይ ግድብ ምክንያት ከግብፅ ሴራ ጀርባ በመሆን የሚንቀሳቀሱ የውጪ ሆነ የውስጥ ኃይሎች እጃቸውን ከኢትዮጵያ ላይ እንዲያነሱ የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት አሳሰቡ።

ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባላት በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል በአካል ቀርበው እንዳመለከቱት፤ በአባይ ጉዳይ አንዳንድ የውጪና የውስጥ ኃይሎች እየሄዱበት ያለው መንገድ ትክክል ያልሆነና በየትኛውም መመዘኛ ያልተገባ ነው።

የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማህበር አባል የሆኑት አቶ ደስታ አርቤሎ፣ የሀገር ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ገልጸው፤ አንዳንድ የውጪና የውስጥ ኃይሎች አባይን በተመለከተ የሚያራምዱት አቋም ተገቢ አለመሆኑን አስታውቀዋል።

የትናንት ጀግኖች በጦር ሜዳ በብዙ መስዋዕትነት ያቆዩልን ሀገራችን ስትነካ ያማል ያሉት አርበኛው ፣ ይህ ህመም የትኛውንም ዋጋ ለሀገር ለመክፈል አቅም የሚፈጥር እንደሆነ አስታውቀዋል።

ሁሌም ኢትዮጵያ ለመልማት ስትንቀሳቀስ የውጭ ኃይሎች የልማቱ አደናቃፊ ሆነው እንደሚቆሙ አመልክተው፣ ግብፆች እነሱ እየለሙ እኛ በድህነት እንድንኖር ሊፈርዱብን አይገባምም፤ ለዚህ የሚሆን አቅምም ሥልጣንም የላቸውም ብለዋል።

የኢትዮጵያ ነገሥታትና መንግስታት ውስጥ ከአጼ ቴዎድሮስ ጅምሮ ያሉት ብናይ ለአንድነታቸው ሲታገሉ ሲቃወሟቸው የነበሩት የራሳቸው ወገኖች ናቸው። ግብጽንም ብንመለከት የተለያዩ የውጪ ኃይሎችን ጨምሮ ከውስጥ ኃይሎች ጋር በመሆን የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ውስጥ የሚከቱ ተግባራትን ስታከናውን ቆይታለች፤ አሁንም እያከናወነች እንደምትገኝ አመልክተዋል።

ከግብጽ ሴራ በስተጀርባ ውስጣዊ ጠላት አለ የሚሉት አርበኛ መሪጌታ አምዴ ወልደ ጻድቅ በበኩላቸው፤ ጠላት ምን ጊዜም ጠላት ነው። አስቀድሞ መጠንቀቅ የውስጥ ጠላትን ነው ብለዋል።

እኛ በሰላም የምትኖር ሀገር እየተመኘን ነው ያሉት አርበኛ መሪጌታ አምዴ፣ በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ስልጣን ለኛ ካልደረሰን ሀገሪቷ መበታተን አለባት በማለት ሕዝባችንን በቋንቋ፤ ኃይማኖትና በዘር እየከፋፈሉ ሀገሪቱን ወደ አልተገባ መንገድ የሚወስዱ ኃይሎች ከዚህ ካልተገባ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ጥሪ አቅርበዋል ።

እኛ ግድቡ የምንፈልገው ያለብንን የኤሌክትሪክ ኃይል እጥረት ለመቅረፍ ነው። ይህ ደግሞ በወንዞች በመጠቀም መብታችን የምናረጋግጠው ነው ያሉት አርበኛ መሪጌታ አምዴ፣ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል በአባይ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቅ ወጥ አቋም ሊኖረው እንደሚገባ አመልክተዋል።

ግብጽች በራሳቸው ላይ ሊሆን የማይፈልጉትን በኛ ማድረግ የለባቸው የሚሉት አርበኛ ስዩሜ ተክለብርሃን በበኩላቸው፤ ድርድሩም ቢሆን ሰላማዊ በሆነ በስምምነትና በመግባባት ላይ በተመሠረተ መንገድ ማለቅ እንዳለበት አስታውቀዋል። ከዚህ ውጪ ግብጾች ጦር መዘው የሚመጡ ከሆነ ግን፤ እኛም ሀገራችንን አናስደፍርም፤ ትውልዱም አያስደፍርም ብለዋል።

የአባይ ግድብ የሚለያየን ሳይሆን የሁላችንና የጋራ ጉዳያችን ነው ያሉት አርበኛው፤ እንደ ሀገር መልካሙ ነገር እያስቀጠልን መጥፎውን እየተውን መሄድ እንደሚኖርብንም መክረዋል።

አርበኛ ሻምበል ግዮን ዴሬሳ በበኩላቸው አያቶቻችን እራሳቸውን በአድዋ ላይ መስዋዕት ያደረጉት ለተተኪ ትውልድ ነጻ የሆነች ሀገር ለማስረከብ ነው። ይህ ነጻነታችን የውሀ ሀብታችንን ያለ ማንም ከልካይ በፍትሐዊነት እንድንጠቀም ትልቁ አቅማችን መሆኑን ጠቁመዋል።

ግብፅ ከአባይ ግድብ ጋር በተያያዘ የያዘችው የተሳሳተ አቋም ሆነ የጀመረችው ማስፈራራት ተገቢ እንዳልሆነ አመልክተዋል። ጦርነት ለማንም የማይበጅ ስለሆነ ለሁሉም መልካም በሆነው ሀሳብ ላይ መስማማት ይበጃል ብለዋል። አልፎ የሚመጣ ነገር ካለ ግን ለሀገራቸው ለመሞት ኢትዮጵያውያን አዲስ እንዳልሆኑ አስታውቀዋል።

አዲስ ዘመን ሰኔ 22

ወርቅነሽ ደምሰው

የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት/

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.