እውነትም ክፉ አዙሪት ! – ጠገናው ጎሹ

June 28, 2020
ጠገናው ጎሹ

Ethiopia 1ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ ከዓመታት በፊት ከሌሎች ግጥሞቹ ጋር በDVD በማሳተም በእራሱ አንደበት ያነበበውን “እውነትም እኛ…” የተሰኘውን ግጥሙን በወቅቱ ደጋግሜ አዳምጨዋለሁ ። ከሰሞኑም አዳመጥኩት። ።ይህ እጅግ ህሊናን ወጥረው በሚይዙ ሃይለ ቃላት ተደርሶ በእራሱ በደራሲው ቀልብን በሚገዛ አንደበት የተነበበው የግጥም ሥራ ከዓመታት በኋላም (ዛሬም) ስለምንገኝበት የማንነትና የምንነት ቀውስ (እንቆቅልሽ) ነው የሚነግረን። ግዙፍና መሪር መስዋእትነት የተከፈለባቸው የለውጥ እንቅስቃሴዎች (መልካም ሁኔታዎች) የታሰበላቸው የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ እውን ይሆን ዘንድ የግድ ከሚለን  አቅጣጫና መንገድ እየተንሸራተትን ተመልሰን በነበርንበት የፖለቲካ ፣ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና ሞራላዊ ቀውስ አዙሪት ውስጥ የመገኘታችን እንቆቅልሽ  አስከፊነት ነው “እውነትም እኛ…” የሚነግረን ።

ነፃነትንና ፍትህን በእውን በሚሹ (በሚፈልጉ) ንፁሃን ዜጎች ለዘመናት በተከፈለ መስዋዕትነት የተከፈተውን ፍኖተ ዴሞክራሲ  ለሩብ  መቶ ክፍለ ዘመን የተለከፉበትን እኩይ ሥርዓት ከነ ህገ -አገዛዙ (ህገ-መንግሥት ተብየው) እና ከነ መዋቅራዊ ይዘቱና ቁመናው እንደ ሥርዓት አስቀጥለው “እየመጣችሁ ተደመሩ!” ሲሉን  ወደ አምልኮ በሚጠጋ አኳኋን “አሜን(ይሁን)!” ብለን መቀበል የጀመርን እለት ነበር ተመልሰን በነበርንበት ክፉ አዙሪት  እንደምንከረቸም ግልፅ የሆነው።

አዎ! ይህ ትውልድ የውድቀቱን መሪር እውነትነት ለመጋፈጥ ስለሚፈራ የሚቀለው ሃቁን መካድ (denial) በመሆኑ ነው እንጅ የህወሃት የበላይነት መወገዱን ብቻ እንድ የትግሉ መጠናቃቂያ ምእራፍ በመቁጠር “ተደመር!” በሚል እጅግ ደምሳሳና ግልብ የፖለቲካ ዝማሬና ጭፈራ  ዳንኪራ የመታለት ነበር የፖለቲካ አስተሳሰቡን እንጭጭነት (political infantility/stupidity) ለሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች ገልጦ ያስነበባቸው ። አዎ!ይህ ትውልድ ዛሬም  ለሩብ ምእተ ዓመት በፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበከተውንና የከረፋውን ሥርዓት  አስወግዶ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውን ለማድረግ  ይታገልበት ከነበረው አምባ ላይ እየተንሸራተተ  በመውረድ በኦዴፓ/ኦነግ የበላይነት ለሚመራው የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ ሰለባ መሆኑን ነው  “እውነትም እኛ …” ዛሬም የሚነግረን ።

ምንም  እንኳ ግጥሙ የተፃፈውና ለህዝብ የቀረበው ከዓመታት በፊት ቢሆንም የተሸከመው መሪር እውነት የሚነግረን ዛሬም  መልስ ስላልተገኘለት እንቆቅልሻችን ነው።   በእውነት ስለ እውነት ከተነጋገርን  ይህ ትውልድ   ኢትዮጵያ የሚለውን ስም እንኳን  ለመጠቀም ለመጥራትም በመፀየፋቸው  ኢህአዴግን በቀድሞዎቹ አጋር ድርጅት  ተብየዎች አሳጅበው የኦሮሞ ብልፅግና ፣የአማራ ብልፅግና፣ የትግራይ ብልፅግና እና የደቡብ ብልፅግና ፣ወዘተ ብለው በመሰየም “ብልፅግና በብልፅግና ልናንበሸብሽህ ነው” ሲሉት “በከፈልኩት መስዋእትነት አትሳለቁ!በቃችሁ!” ለማለት ተስኖት ወደ መጣበት ክፉ አዙሪት ሲንሸራተት ማየት እንቆቅልሽነቱ በጅእጉ ከባድ ነው ።

አዎ! ቀደምት ትውልዶች በከፈሉት  እጅግ ክቡር ዋጋ ያስረከቡንን ታላቅ አገር ለምንኖርበት ዘመን  በሚመጥን  ሁኔታ የዴሞክራሲና  የሰብአዊ መብቶች የተከበሩባት እና የጋራ ብልፅግና የተረጋገጠባት  አገር ለማድረግ አለመቻላችን አልበቃን ብሎ እንዲያውም ይባስ ብለን  በየጎሳውና በየጎጡ በጣጥሰው ለሚገዙን ሸፍጠኛ ፣  ባለጌና ጨካኝ   ገዥ ቡድኖች እየተመቻቸን የመቀጠላችን ክፉ አባዜ (አዙሪት) የሚፈጥረው  ድብልቅልቅ ስሜትና የህሊና ህመም በእጅጉ  ከባድ ነው። የጤናማ ስሜት ባለቤት ለሆነና ክፉ ነገርን የሚፀየፍ ህሊና ላለው የአገሬ ሰው።

እንደ እኔ አረዳድ ይህ  ግጥም በሞራለ ቢስና ባለጌ ገዥ ቡድኖችና ፖለቲከኞች ምክንያት ወገኑ ከመከራና ከውርደት አዙሪት ለመላቀቅ አለመቻሉ በእጅጉ የሚያሳስበውና የሚያስጨንቀው ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ዜጋ በህሊናው አምጦ የወለደውና በብእሩ የከተበው   ግዙፍና ጥልቅ ሥራ ነው። አዎ! ይህ ግጥም  “ይህ ትውልድ መላልሶ ከሚዘፈቅበት ክፉ አዙሪት መውጣት ካለበት የእራሱን አስከፊ  የእንቆቅልሽ  አዙሪት በሌላ ዳኝነት ፊት ሳይሆን በእራሱ የህሊና ዳኝነት ፊት ቆሞ ‘እውነትም እኔ/እኛ…’  በማለት የእራሱን አስከፊ ውድቀት መጋፈጥ ግድ ይለዋል “ ነው የሚለን

አዎ! የጥላቻ፣ የጎሰኝነት፣የጎጠኝነት ፣የሸፍጠኝነት ፣የሴራኛነት ፣ የአድርባይነት ፣የፖለቲካ አመንዝራነት ፣  የወስላታነት  ፣የብልግና ፣ የሞራለ ቢስነት  ፣ከልክ ያለፈ ስግብግብነት (እራስ ወዳድነት) ፣  ወዘተ ካባን በማውለቅ የነፃነትና የፍትህ አርበኝነት ወኔን ሲላበስ  ብቻ ነው ይህ ትውልድ  እራሱን ብቻ ሳይሆን መጭውን (ተከታዩን) ትውልድ  ለመታደግ ያለመቻል  የሞራልና የፖለቲካ ቀውስ  ውስጥ  መሆኑን  ከምር  አምኖ በመቀበል የሚበጀውን ሁሉ ነገ ሳይሆን ዛሬ እውን ማድረግ የሚችለው የሚል  ነው የዚህ ግጥም  ጥልቅና መሪር መልእክት ።

መከረኛውን የአገሬ  ህዝብ እየተፈራረቁ ለዘመናት አደንቁረው የመከራና የውርደት ቀንበር ሲያሸክሙት በኖሩት እኩያን ገዥ ቡድኖችና ፖለቲከኞች ምክንያት የፖለቲካ ባህላችን በሸፍጥ፣ በርካሽ የግል ዝና ስካር እና ጠልፎ በመጣል ወይም ተጠላልፎ በመውደቅ እኩይ ባህሪያት የተበከለ ነው።

ይህ ጎጅ የፖለቲካ ባህል ለሩብ ምእተ ዓመት ተንሰራፍቶ ከቆየው የኢህአዴግ (የአሁኑ ብልፅግና) የግፍ አገዛዝ ሥርዓት ማስፈፀሚያ ሥልቶች ጋር እንዲቀናጅ  ሲደረግ ደግሞ የሚያስከትለውን አስከፊ ውጤት ያየነውና የሰማነው ብቻ ሳይሆን የኖርንበትና አሁንም የቀጠልንበት  መሪር እውነት  ስለሆነ ማስረጃ ጥቀስ የሚል ውዝግብ ውስጥ አያስገባንም።

የአገራቸው ጉዳይ ከሚያሳስባቸው ወገኖች የሚሰነዘሩ  ሂሳዊ መልእክቶችን በምክንያታዊነት መሞገት ሳይሆን መልእክተኞችን በማጥላላት እና ሲያስፈልግም አሳዶ  በመበቀል  ክፉ ልማድ የተበከለው የፖለቲካ ባህል  የእያንዳንዱን ነፃነትና ፍትህ ፈላጊ ዜጋ የእለት ከእለት ህይወት ሲያመሰቃቅል የኖረና እያመሰቃቀለ የቀጠለ መሪር እውነት ነው።  ግፈኛና ሸፍጠኛ ገዥ ቡድኖችና ፖለቲከኞች አደንቁረው ሲገዙት የኖሩትን መከረኛ የአገሬ ህዝብ አሁንም ከባድ ዋጋ የከፈለበትን የለውጥ እንቅስቃሴውን እና የነፃነትና የፍትህ ጩኸቱን በተሃድሶ ስም ቀምተው ወደ ነበረበት (ምናልባትም ወደ ባሰ) አዙሪት እየገፉት መሆኑን  በግልፅና በቀጥታ መነጋገር ከአዙሪቱ ለመውጣት የግድ ከሚሉ ሁኔታዎች አንዱ ነው ።

የበርካታ  ቅን ዜጎች አእምሮ አምጦ የወለዳቸው እና የመሪሩ እውነት ነፀብራቅ የሆኑ መልእክቶችንና ጩኸቶችን ለሁልጊዜው አፍኖ ማስቀረት ባይቻልም  ለብዙ ዓመታት በማፈን የግፍና የመከራ አገዛዝን ማራዘም  እንደሚቻል ከእኛው ከእራሳችን የተሻለ ማስረጃ ከቶ የለም። ለዚህ ነው ግዙፍና መሪር መስዋእትነት ከተከፈለበት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ አቅጣጫና ሃዲድ  እየተንሸራተትን ወደ መጣንበት የአያሌ ዓመታት አዙሪት በከፍተኛ ፍጥነት  በመውረድ ላይ መገኘታችንን  ከምር ተረድተን ሳይመሽ የሚበጀንን ማድረግ አለብን ማለት ትክክል የሚሆነው ።

አዎ! በገሃዱ ዓለማችን የሚገኘውን መሪር እውነት በገሃዱ ዓለም ከማይገኘው ህልማችን በቅጡ በመለየት ሊጨበጥ የሚችለውንና የሚበጀውን ለማድረግ ያለመቻል ወይም ያለመፈለግ ቸግር (insanity/stupidity) የሽፍጠኛና ሴረኛ የኢህአዴግ/የብልፅግና ፖለቲከኞች ሰለባ አድርጎን ቀጥሏል ።

የለውጥ አራማጅ እያልን ያሞካሸነው የኢህአዴግ/ የብልፅግና መሪና ጠቅላይ ሚኒስትር የትየለሌ መስዋእትነት የተከፈለበትን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እውን ከማድረግ አንፃር ምን አሰበ ? ምን አቀደ? ከነማን ጋር መከረ ? ምን አደረገ (ሠራ)?  ለነገስ (ለመጭው ትውልድ) ምን ሰንቋል?  ከሰነቀስ ከነማን ጋርና እንዴት? ፣ ወዘተ ሳይሆን በሰላ አንደበቱ ምን አይነት ድንቅ ዲስኩር ደሰኮረ? ስንት ሰው አስጨበጨበ? ስንቱ ዘፋኝ “አብይ”  የሚለውን ስም ቅኔያዊ ትርጉም በመስጠት አንጎራጎረው ? ስንቱን ዘፋኝ ደምሳሳና ግልብ የሆነውን የመደመር ፖለቲካ ድርሰት “ተደመር” በሚል በስሜት ዳንኪራ አስደነከረው? ስንቱን ሰው ከንፈር አስመጠጠው? ከቴሊቪዥን መስኮት ሲጠፋ ስንት ሰው ጨነቀው? ስንቱን አክቪስት ነኝ ባይ ጉድ አደረገው? ስንቱን ልሂቅ ነኝ ባይ ጉድ ሠራው? ስንት ጊዜ መጽሐፍ ቅዱስንና ቁሩንን ጠቀሰና አጣቀሰ? ስንት ጊዜ እግዚአብሔር አገራችን ይባርክ አለ ? ወዘተ በሚል   እጅግ የኮሰመነ/እንጭጭ (infantile and clumsy) የፖለቲካ አስተሳሰብ መጠመዳችን ይኸውና ከባድ ዋጋ እያስከፈለን ቀጥለናል ።

ለዚህ ነው  ወደ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ የሚወስድ ትርጉም ያለው የለውጥ መንገድ ይቅርና ግልፅና የሚጨበጥ የፖለቲካ ምህንድስና በሌለበት “ስለ ዴሞክራሲያዊ አሻጋሪነታችን ሃሳብ አይግባችሁ” ማለት ከውሸትም አልፎ  በመከረኛው  ህዝብ ላይ መሳለቅ የሚሆነው።

ለነገሩ በመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ ለዘመናት ከኖረበት የመከራና የውርደት ቀንበር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መላቀቅ ተስኖት የከፈለውን የትየለሌ መስዋእትነት ለእነርሱ እያስረከበ ወደ ነበረበት (ወደ አዘጋጁለት) ክፉ አዙሪት በመመለስ አስቀያሚ ክፉ ልማድ የተለከፈ ትውልድ ሲያገኙ እነርሱ ምን ያድርጉ?

ይህ አይነቱ ማቆሚያ ያጣ አስቀያሚ የፖለቲካ ጨዋታ ሲካሄድ የቆየውና አሁንም የቀጠለው በዓለማዊው ወይም በሃይማኖታው እምነት ልሂቃን ነን በሚሉ ወገኖች ተባባሪነት  የመሆኑ መሪር እውነት ደግሞ  ህሊናን በእጅጉ ያቆስላል። እነዚህ ወገኖች በለውጥ ስም መንበረ ሥልጣን ላይ ከወጣውና ከሚወጣው  ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኛ ጋር የፖለቲካ አመንዝራ እየፈፀሙ ለመኖር ፈቃደኞች ሲሆኑ  ልጆቻቸውን ጨምሮ ለዚህ ወጣት ትውልድ ምን እያስተማሩት (እየነገሩት) እንደሆነ ለአንድ አፍታ እንኳ ቆም ብለው ህሊናቸውን ለማዳመጥ አልተቻላቸውም።ታዲያ ይህ አይነት አስተሳሰብና አካሄድ ትውልድን ወደ መግደል የፖለቲካ አዙሪት ተመልሶ መዘፈቅን ካልሆነ ሌላ ምን  ሊያሳየን ይችላል? 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚያስበውንና የሚያውቀውን በእራሱ የብቃት/የችሎታ መጠን በመፅሃፍ መልክ አስጠርዞ ለንባብ ማብቃቱን በደምሳሳው (ከምክንያታዊነት ውጭ) ማጣጣል ከሃሳብ ልዩነት ሳይሆን ከግለሰባዊ  ጥላቻ ወይም ኩርፊያ የሚመነጭ ነው የሚሆነው  ። ትእግሥትና  ሂሳዊ ሚዛናዊነት ያለው ሰው “መደመር” የሚለውን የፖለቲካ  ድርሰት አንብቦ ሲጨርስ አወንታዊ  ሃሳቦች ጨርሶ የሉትም ብሎ እንደማይደመድም እገምታለሁ ። በመቶዎች በሚቆጠሩ ገፆች ምንም አይነት ይሁን የሚያሰኝ ሃሳብ የለም ማለት ጨርሶ ትክክለኛ ምልከታ ሊሆን አይችልምና።

በሌላ በኩል ግን ልክ  ለሌው የፖለቲካ ዝና ገፅታ ግንባታ (narcissit political image building)  ሲባል  በምክንያታዊነትና በሂሳዊ ሚዛናዊነት ሳይሆን ልክ በሌለው የስሜታዊነት ፈረስ እየጋለበ ጠቃሚውን ከጎጅው፣ ዘላቂውን ከጊዜያዊው፣ ሸፍጥን ከቅንነትና ግልፅነት፣ መሠረታዊውን ከጥገናዊው፣ የምር ፖለቲካ ጨዋታን ከተራ ፕሮፓጋንዳ ፣ ባዶ ዲስኩርን (ስብከትን) ከድርጊት፣ ወዘተ ለመለየት እየተሳነው የተቸገረውን ትውልድ  “መደመር” በሚል ግልብና የተውገረገረ ( clumsy and disorganized) የፕሮፓጋንዳ ድርሰት እንዲቀበል መጠየቅ የማታለል አቀራረብ ስልትን ከመቀየር ያለፈ ብዙም ፋይዳ የለውም።  የመነሻውን ፣የመንደርደሪያውን ፣ የይዘቱን (የፍሬ ነገሩን) እና  በአንባቢያን አእምሮ ውስጥ  የሚፈጥራቸውን ንጥረ ሃሳቦች ለማያያዝና ትርጉም በሚሰጥ ሁኔታ ለመረዳት በሚያስቸግር  የፖለቲካ ድርሰት ትውልድን ግራ ማጋባት ከሞራልም ሆነ እውን እንዲሆን እንፈልጋለን ከምንለው ሥርዓት አንፃር ጨርሶ አሜን (ይሁን) ተብሎ ሊታለፍ የሚገባው  አይደለም ። አካፋን አካፋ ብሎ ለመጥራት ወኔው እየከዳን ወይም በፖለቲካ አመንዝራነት እየተሽኮረመምን ስለ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ ማውራት (መስበክ) ጨርሶ ስሜት የሚሰጥ ነገር አይደለም። የመደመር ፖለቲካ ድርሰትን አንብቦ ለመጨረስ የሚጠይቀውን ትእግሥት የማጣት ስሜት እንደምንም ተቋቁሞ የሚጨርስ አንባቢ ከሚታዘባቸው ትዝብቶች አንዱ የተፃፈው ከልክ ባለፈ እራስን የማስተዋወቅ ስሜታዊ  ግፊትና ልክ የሌለው ዝናን አጥብቆ በመፈለግ የፖለቲካ ትኩሳት ውስጥ መሆኑን ነው።  ለዚህ ነው አንብበው ሲጨርሱ ከርዕሰ ጉዳዩ አንፃር በአእምሮ ውስጥ የሚያስቀመጡት (የሚያስቀሩት) በቅጡ የተያያዘና የተደራጀ ንጥረ ሃሳብ ማግኘት አስቸጋሪ የሚሆነው።

እንኳን በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብ  ሊያፈላስፍ የተነሳበትን ርዕሰ ጉዳይ ምንነት ፣ ለምንነት፣ እንዴትነትና ወዴትነት በቅጡ ሳይነግረን ድንብርብራችን እንዳወጣን “ተፈፀመ” የሚለንን የፖለቲካ ድርሰት (መደመርን ) የማድነቂያ ቋንቋ (ቃላት) ፍለጋና መረጣ ብዙ የተጨነቁና የሚጨነቁ “ልሂቃንን” መታዘብ ባይገርምም ምነው እውነተኛ ትርጉም ላለው ልሂቅነት የሚገደው ወገን የት ገባ?ያሰኛል ።

ታዲያ በዚህ አኳኋናችን ሸፍጠኛና ሴረኛ የኢህአዴግ ተሃድሶ (የብልፅግና) ፖለቲከኞች የትየለሌ መስዋእትነት ከተከፈለበት የሥርዓት ለውጥ እንቅስቃሴ አቅጣጫና ሃዲድ አንሸራተው ወደ ተለመደው የፖለቲካ አዙሪታቸው ቢያወርዱን ለምን ይገርመናል? የደራሲና ጋዜጠኛና   አበራ ለማ  “እውነትም እኛ…” የሚነግረን መሪር እውነትም ይኸው ነው።

መንበረ ሥልጣን በሚያስገኘው ጥቅም ህሊናቸው የታወረና ሥልጣን በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ቢተካ ሊያጋጥማቸው የሚችለው የተጠያቂነት ፈተና የሚያቃዣቸው  የኢህአዴግ/የብልፅግና  የበላይ ፖለቲከኞች እና ኢህአዴግ ብልፅግና  የሚል የማጭበርበሪያ ስያሜ  ተለጥፎለት በገዥነት እንዲቀጥል ከማድረግ የተሻለ የሥራ (የኑሮ) ዋስትና  ጨርሶ እንደሌለው  አሳምሮ የሚያውቀው በሚሊዮኖች የሚቆጠር የካድሬ ሠራዊት በወንጀል ከበሰበሰውና ከከረፋው ሥርዓታቸው ጋር በቀጠሉበት መሪር እውነታ ውስጥ መሠረታዊ የሥርዓት ለውጥን መጠበቅ ወይ የፖለቲካ ቂልነት ነው ወይም የለየለት የትግል ውድቀት ነው ወይም ደግሞ የለየለት አድርባይነት /የፖለቲካ አመንዝራነት  ነው።

እናም ለዚህ ነው ከዓመታት በፊት ያነበብነውና ያዳመጥነው  “እውነትም እኛ…”  ዛሬም ለዘመናት ከነበርንበት  እጅግ አስቀያሚ የፖለቲካ እንቆቅልሽ የሚገላግለንን  የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ  ለሸፍጠኛና ሴረኛ የኢህአዴግ (የብልፅግና) ፖለቲከኞች አሳልፎ በመስጠት ክፉ አዙሪት ውስጥ የመውደቃችን መሪር እውነት መልሶ የሚነግረን።

ደራሲው የግጥሙን መልእክት “ከለውጡ” በኋላ እንዴት እንደሚተረጉመው (እንደሚያየው) አላወቅሁም ። “ለውጡ” ለግጥሙ መሪርና ጥልቅ ጩኸት (መልእክት) መልስ ሰጥቷል ብሎ የሚከራከር ካለ ግን በመሬት ላይ ያለውን መሪር ሃቅ በራሱ የቅዠት ዓለም  (dellusional belief ) እየተረጎመ  እራሱን የሚደልል (የሚያታልል) መሆን አለበት ባይ ነኝ።

ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ ለዚህ ግጥሙ መነሻ የሆነው ምክንያት የአገራችን ፖለቲከኞች ላለመስማማት መስማማት   (agree to disagree) የሚሉት “የፌዝ አነጋገር አንድነትን ሳይሆን ልዩነትን የሚያጎላ እና በአገራችን እንዲመጣ የምንመኘውን የፍትህና ርትዕ ሥርዓት የሚያዘገይ” ሆኖ ስለተሰማው እንደሆነ ይገልፃል። መሪር እውነትን የሚገልፅ አገላለፅ ነው።

በመሠረቱ ላለመስማማት መስማማት (agreeing to disagree) የሚለውን አነጋገር አውቀን ወይም ሳናውቅ በተሳሳተ መንገድ እየተረጎምነውና ለተሳሳተ ዓላማ እያዋልነው ነው የተቸገርን እንጅ በትክክል ብንረዳው፣ ብንተረጉመውና ሥራ ላይ ብናውለው ኖሮ ደራሲው ከምር  እንደሚነግረን  ዞረን ዞረን ከነበርንበት አዙሪት ባልተዘፈቅን ነበር።  እናም የአገራችን  አስከፊ  የፖለቲካ ማንነት ውድቀት የሚመነጨው ከዚሁ  ማቆሚያ ካጣው ሁሉንም ነገር እኩይ የግል ወይም የቡድን ፍላጎትንና ጥቅምን ከማስገኘትና ከማስጠበቅ አንፃር የመተርጎምና የማስኬድ  የሞራልና የፖለቲካ ክፉ አባዜ  እንጅ አነጋገሩ (ላለመስማማት መስማማት) በእራሱ ችግር ፈጣሪ ሆኖ አይደለም። ደራሲውም  አነጋገሩን “የፌዝ አነጋገር” በሚል የገለፀው ከዚሁ  እይታ አንፃር  እንጅ አባባሉ በደምሳሳው (በእራሱ)  ፌዝ ነው ለማለት እንዳልሆነ  እገምታለሁ።

በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ሊኖሩ የሚችሉ የተለያዩ የሃሳብና የአቋም ልዩነቶችና ግጭቶች (differences and conflicts of ideas and positions) በሰው ልጅ መስተጋብራዊ ግንኙነት አካልነታቸው የነበሩ፣ያሉና ወደ ፊትም የሚኖሩ የገሃዱ ዓለም እውነታዎች ናቸው። በሁሉም አይነት የሃሳብና የአቋም ልዩነቶችና ግጭቶች ላይ መስማማት የማይታሰብ የገሃዱ ዓለም እውነታ በመሆኑ ጥቃቅን፣ መለስተኛ እና ጊዜና ሁኔታ ሊፈታቸው የሚችላቸውን ጉዳዮች የግድ ካልተስማማን ሳንል (ባለመስማማት እየተስማማን) ወደ ፊት መራመድ ትክክል ነው።

በሌላ በኩል ግን መሠረታዊ (ወሳኝ) በሆኑና እንደ የአንድ አገር ህዝብና  እንደ መልካም ዜጋ ተከብሮ ፣ተከባብሮ እና በጋራ በልፅጎ ለመኖር በሚያስችሉን ጉዳዮች ላይ “ላለመስማማት መስማማት” የሚለውን እንደ መከራከሪያ (compromising argument) ማቅረብ ተያይዞ የመጥፋትን (mutual suicideን) መጋበዝ   ነው የሚሆነው። በአሳዛኝ መልኩ  በጎሳ/በመንደር/በቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካ ልክፍተኛ ገዥ ቡድኖችና ግብረ በላዎቻቸው ለሩብ ምዕተ ዓመት በሰፊው ተዘርግቶ ሲሰራበት የኖረውና አሁንም እንኳን የፈውስ መፍትሄ ትርጉም ያለው  የማስታገሻ መፍትሄም ሳይገኝለት የቀጠለው አደገኛ የፖለቲካ ቫይረስ ይኸው ነው። “ከጎሳዬ/ከመንደሬ በላይ ልዑላዊ የሆነ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት አላውቅም። አለ ካላችሁኝም አፈራርሼው የጎሳየን/የመንደሬን ልዑላዊነት አረጋግጣለሁ”  የሚል ተያይዞ የመጠፋፋት ክፉ ቫይረስን ተሸካሚ ከመሆን የከፋ ውድቀት የለም። የሥርዓት ለውጥ ሳይሆን በተሃድሶ ስም የበሰበሰውን ሥርዓት በተረኛ ጉልቾች የበላይነት የመተካት የፖለቲካ ጨዋታ እያስከተለ ያለው  አስከፊ ውጤት ይኸው ነው።

ይህ ትውልድ የየራሳቸው መንደር ንጉሦች ወይም ንግሥቶች በመሆን ነፃ አወጣንህ ብለው የሚመፃደቁበትን መከረኛ ህዝብ ደም እየመጠጡ (እየዘረፉ/እየበዘበዙ) ለመኖር የሚቋምጡትን ህሊና ቢስ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ቫይረስ ከማስወገድና ለእራሱ የሚበጀውን ሥርዓት በአብሮነት እውን አድርጎ በጋራ በልፅጎ ለመኖር ስለተሳነው የቫይረሱ ተጠቂ ከመሆን ለማምለጥ አልተሳካለትም።

የኢህአዴግ/የብልፅግና ሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች ዴሞክራሲያዊ አሻጋሪዎች በሚል ሌት ተቀን በሚሰብኩበት በዚህ ወቅት ሥልጣን ያስገኝልናል በሚሉት ጥቅም የሰከሩ የደቡብ ኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ   ፖለቲከኞች  በኦዴፓ/ኦነግና/ኦፌኮ እገዛ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ተልእኮ አስፈፃሚ አድርጎ በመደበው  በአባዱላ ገመዳ ተልኮ አስፈፃሚነት  የጎሳ/የመንደር መንግሥታትን መሥርተው ከዘመነ መሳፍንት በከፋ ሁኔታ ሌላውን ኢትዮጵያዊ ብትፈልግ/ጊ ተገዥነትክን/ሽን ተቀብለህ/ሽ ኑር/ሪ ፤ ካልሆነ ግን መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ/ሽ ለማለት የሚያስችላቸውን  ሁኔታ በከፍተኛ ፍጥነት በማጣደፍ ላይ ይገኛሉ። ይህንን  ከዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ጋር ጨርሶ አብሮ የማሄደውን እና መሠረታዊ የዜግነትንና የሰብአዊ መብትን በአፍ ጢሙ የሚደፋው የፖለቲካ ጨዋታ የሚመነጨው እኩያን ፖለቲከኞች ለእኩይ ዓላማቸው ከተጠቀሙበትና እየተጠቀሙበት ካለው ህገ መንግሥት ተብየ ነው። ዛሬ በአንድ በኩል በብልፅግና ተብየውና መሰሎቹ ፣በሌላ በኩል ደግሞ  እና በህወሃትና መሰሎቹ መካከል የምንታዘበው እሰጥ አገባ ይህኑ የእኩይ ዓላማ ማስፈፀሚያ ሰነድ ማን አከበረውና ማን ሸራረፈው የሚል እንጅ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን እውንና ዘላቂ ለማድረግ የሚያስችል ህገ መንግሥት በአገራዊ መክክርና በህዝብ ተሳትፎ እናዘጋጅ የሚል አይደለም። ለዚህ ነው ከአንድ አስቀያሚ ሥርዓት የሚወለዱት የሁለቱም ወገኖች ያዙንና ልቀቁን ባይነት “አህያ ቢራገጥ ጥርስ አይሳበርም” አይነት ነው ማለት ትክክል የሚሆነው። እንዴት ? የሚለውን በሌላ አስተያየት ማየቱ የሚሻል ስለመሰለኝ ለአሁኑ በዚሁ ልለፈው።

ታዲያ ይህን እጅግ አስቀያሚ ብቻ ሳይሆን አደገኛ የፖለቲካ ጨዋታ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የዴሞክራሲያዊ ሽግግሩ መገለጫ እንደሆነ ሊሰብከን ሲሞክር ከመስማት የባሰ ወደ ክፉ አዙሪት የመከርቸም አደጋ የለም።

የዚህ አስከፊና መሪር እውነት ተዋናይ  የሆኑ ገዥ ቡድኖች በሚኖራቸው የማጭበርበር ችሎታና  የሃይል ሚዛን ክብደት  ምክንያት ተጨማሪ ጊዜና አጋጣሚ ባገኙ ቁጥር ህዝብ ለዘመናት የኖረበትን አስከፊ አዙሪት የማራዘም አቅማቸው በእጅጉ ሰፊ ነው ። በዚህ አስከፊ የአዙሪት አደጋ ውስጥ መሆናችንን ተረድተንና ተቀብለን ነገ ሳይሆን ዛሬውኑ በትክክለኛው የለውጥ አቅጣጫና ግብ (የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ሽግግርና ምሥረታ) ላይ እንረባረብ ብለው የሚጮሁትን ዜጎች “በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድና በለውጥ ጓዶቹ ላይ ጥላቻ መንዛት  ወይም ጨለምተኝነት ነው” የሚልና በእጅጉ የሰለቸ የደናቁርት ውንጀላ ወደ ነበርንበት አዙሪት እየተመለስን የመዘፈቃችንን ክፉ አባዜ ነው የሚነግረን ። ምክያቱም የምንነጋገረውና መነጋገርም ያለብን ስለ  የሥርዓት ለውጥ እንጅ ስለ ባለሥልጣናትና ስለ ፖለቲከኞች  የግል ጉዳይ ወይም ህይወት ወይም ባህሪ አይደለምና ።

የኢህአዴግ/የብልፅግና /የአብይ/የለማ/የገዱ/የደመቀና መሰሎቻቸው “የተሃድሶ ለውጥ” ለደራሲና ጋዜጠኛ አበራ ለማ እና ተመሳሳይ መሪር ጩኸት ለጮሁ (ለሚጮሁ) ወገኖች ምላሽ የሰጠ ስለመሆኑ ወይም ስላለመሆኑ ለማወቅ የተለየ እውቀትና ምርምር ጨርሶ አይጠይቅም። በሁለት ቫይረሶች (ኮቪድ-19 እና የገነገነ የፖለቲካ ቫይረስ) መካከል የሚገኘው  የመከረኛው ህዝብ የእለት ተእለት ህይወት በራሱ ከበቂ በላይ ምሥክር (ማስረጃ) ነውና ።

ጥያቄው ከሁለቱ ቫይረሶች የትኛው የሁሉንም ዜጋ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትና እርብርብ ይጠይቃል? ነው እንጅ ለዘመናት ተንሰራፍቶ የዜጎችን ህይወት ምስቅልቅሉን ሲያወጣ የኖረው ወንጀለኛ ሥርዓት ተወግዶ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እውን ይሆን ዘንድ የሚደረገው ትግል በኮቪድ-19 ምክንያት ለሸፍጥ ተሃድሶ ፖለቲከኞች (ኢህአዴጋዊያን/ብልፅግናዊያን) መስዋእትነት ይቅረብ ማለትእንዳልሆነ ግልፅ መሆን አለበት ።

በአሁኑ  ወቅት እያነጋገረንና እያሳሰበን ያለው የአባይ ወንዝ አጠቃቀምና የግብፅ ለከት የሌለው አቋምና አካሄድም መስተናገድ ያለበት   ከዚሁ የቅድሚያ ቅድሚያ ትኩረትን አውቆ ከመዘጋጀትና ከመንቀሳቀስ አንፃር እንጅ የአገር ውስጥ የህዝብ ልዑላዊነትን ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ እየደፈጠጡ ልክ የሌለው የብልግና እና የሸፍጥ የሥልጣን ዘመናቸውን ለማራዘም ለሚሞክሩ የኢህአዴግ/የብልፅግና ፖለቲከኞች ሰፊ እድል ለመፍጠር ጨርሶ መሆን የለበትም።

እንደ ኮቪድ-19 እና ሌሎች  በተፈጥሮም ይሁን በሰው ስህተት ሊከሰቱ የሚችሉ ወረርሽኞች በተከሰቱና እና እንደ ግብፅ አይነት ልዑላዊነትን የሚዳፈሩ ሃይሎች ያዙንና ልቀቁን ባሉ ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ሥጋት ውስጥ የምንገባውና ስጋት በገባ ቁጥር ደግሞ ማድረግ ያለብን ነገር ሁሉ ድብልቅልቁ እየወጣብን የተቸገርነውና እየተቸገርን ያለነው የውስጥ የቤት ሥራዎቻችን የመገንባት ሳይሆኑ የማፈራረስ በመሆናቸው ነው ። ለዚህ አይነት አስከፊ የፖለቲካ አዙሪት  እንደ አሸን እየፈሉ አንዳችም ትርጉም ያለው ፋይዳ ያልነበራቸውና አሁንም የሌላቸው ተቀዋሚ የፖለቲካ ድርቶች ተብየዎች ተጠያቂነት እንደተጠበቀ መሆኑ ሳይዘነጋ  ከምንምና ከማንም በላይ ግን  ተጠያቂዎች በፈጣሪያቸው፣ ባሰልጣኛቸውና በቀጣሪያቸው (በአሠሪያቸው) ህወሃት መሪነት ለሩብ ምዕተ ዓመት የህዝብን ልዑላዊ መብት ደፍጠጠው የአገርን አጡራ ሃብት እየዘረፉ የኖሩት ኢህአዴጋዊያን (የአሁኖቹ ብልፅግናዊያን) ናቸው ።

እንደማነኛውም አገር ታሪክ በታሪክ ሂደት የተፈፀሙ ስህተቶች እንዳሉ ሆነው እንድ አንድ ታሪካዊት አገር ህዝብ በአብሮነቱ ፀንቶ የኖረውን የኢትዮጵያ ህዝብ በጥላቻና በማፈራረስ ህገ መንግሥት እና ለዚሁ ማስፈፀሚያነት በተዋቀረ (በተደራጀ) መንግሥታዊ መዋቅር  የኢትዮጵያዊነት ስሜቱን ለከፍተኛ ፈተና የዳረጉት ኢህአዴጋዊያን የኸውና ዛሬም የፕሮፓጋንዳ ዲስኩር እያዥጎደጎዱ እና የስያሜና የአደረጃጀት  ቅርፅ እየቀያየሩ ቀጥለዋል።

ለዚህ አይነት የፖለቲካ ተውኔታቸው በመሪነት የመረጡት ፖለቲከኛ (ጠቅላይ ሚኒስትር) ደግሞ በእጅጉ የተዋጣለት መሪ ተዋናይ ነው።  እጅግ ስስ ሥነ ልቦናውን የሚያሸንፉ ቃላትን በሰላ አንደበታቸው ሲያዥጎደጉዱለት ከመከራው ብዛትና አስከፊነት የተነሳ “የምህረት ዘመን መልእክተኞች ከህአዴግ ማህፀን ተወለዱ” የሚል የዋህ የአገሬ ህዝብ  ለሸፍጠኛና ሴረኛ ፖለቲከኞች የፖለቲካ ጨዋታ የተጋለጠ መሆኑን ለማወቅ እየተጀመሩ የመከኑትን የለውጥ እንቅስቃሴዎችን በጥሞና ማስታወስ በቂ ነው። አንቅቶ እና አደራጅቶ  ከዚህ ክፉ አዙሪት ሊገላግለው የሚችል ሃይል ለማግኘት  ያልተሳካለት  የአገሬ ህዝብ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ዋና ገፀ ባህሪነት በሚተወን ተውኔተ ፖለቲካ  ቢታለል ከቶ የሚገርም አይደለም ።

ከላይ ለመግለፅ እንደሞከርኩት የቅድሚያ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ እንደ ተጠበቀ ሆኖ በሩብ ምእተ ዓመት ለመግለፅ በሚያስቸግር ፖለቲካ ወለድ ወንጀል የበከተውና የከረፋው ሥርዓተ ህወሃት/ኢህአዴግን በኦዴፓ/ብልፅግና በመተካት እና እንደ ሥርዓት እንዲቀጥል በማድረግ ዴሞክራሲን እውን ማድረግ ፈፅሞ አይቻልም።ከዚህ  የከፋም በመከረኛው ህዝብ የመሳለቅ ርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ ጨርሶ  የለም። ለዚህ ደግሞ በሁለት ዓመት ውስጥ ከሆነውና አሁንም በመሬት ላይ ካለው መሪር እውነት በላይ ማስረጃ የለም። ይህንን  አይነት ደጋግሞ የመውደቅና እራስን በሸፍጠኛና ሴረኛ ገዥ ቡድኖችና ፖለቲከኞች የመከራና የውርደት አዙሪት ውስጥ ተመልሶ የማግኘትን እጅግ አስቀያሚ እንቆቅልሽ ነበር ደራሲው ከዓመታት በፊት እንዲህ ሲል ከእራሳችን ጋር ያሟገተን፦

ላለመስማማት ተዋደን

ላለመዋደድ ተስማምተን

ላለመፋቀር ተቃቅፈን

አንድ ላለመሆን ተማምለን

አንድ እራሳችንን አሸንፈን

እኛን ታግለን የጣልን

ለአያ ጅቦ ተመቻችተን

አንድ እራሳችንን ገድለን

በአሸናፊነት እንኮራለን

እኛ ልዩ ነን እንላለን።

ይኸው ዞረን፣ዞረን፣ዞረን  እዚያው ነን

እውነትም እኛ ልዩ ነን።

 

……………………………

……………………………

……………………………

 አምና  ታች አምና ከነበርንበት

 ይኸው ዞረን ዞረን ግጥም አልንበት

ይኸውና ዞረን ዞረን  

ዛሬም እዚያው ነን

እውነትም እኛ ልዩ ነን።”

ለሩብ ምእተ ዓመት በአሽከርነት (በፍፁም ታዛዥነት) በህዝብ ላይ ሲፈፅሙት የኖሩትን እጅግ አስከፊ ፖለቲካ ወለድ ወንጀል በሸፍጥ በተለወሰ የተሃድሶ ለውጥ ስም እየተሿሿሙና እየተሸላለሙ ጌቶቻቸውን (የህወሃት ፖለቲከኞችን) ከቤተ መንግሥት ማስወግድን እንደ አልፋና ኦሜጋ ድል በመቁጠር “ብልፅግና ሆነናል” ሲሉንና ጎሮ ወሸባየ! ብለን እንቀበላቸው ዘንድ ሊያሳምኑን ሲሞክሩ “ልክ ከሌለው የብልግና ፖለቲካ ሥርዓት  ብልፅግና ፈፅሞ ሊገኝ (ሊወለድ) አይችልምና ይልቁንም ይህን ክፉ ልክፍታችሁን ትታችሁ እውነተኛ ዴሞክራሲና የጋራ ብልፅግና እውን ለማድረግ የሚያችስችለንን ሥርዓት በጋራና በእኩልነት እንፍጠር”  በሚል መርህና አቋም ላይ ፀንተን መቆም አልሆነልንም። ታዲያ በዚህ አይነት የወረደ የፖለቲካ አስተሳሰብና ቁመና ብዙ ዘመን ያስቆጠረውን የፖለቲካ አዙሪት ሰብሮ መውጣት እንዴት ይቻላል? ፈፅሞ የሚቻል አይደለም። እናም ደራሲው ከምር እንደሚያስገነዝበን  እራሳችንን በእራሳችን ከምር መሞገትና በእጅጉ ከተሳሳተው የፖለቲካ አስተሳሰብና አካሄድ ወጥተን ወደ ትክክለኛው መንገድና መዳረሻ መመለስ ይኖርብናል።

ከምር በሆነና ተግባራዊ ውጤት ሊያስከትል በሚችል ይቅርታ ጠያቂነት (a real sense of apology) የጋራና ዘላቂ የመፍትሄ ሃሳብ ላይ የሚመክር አገራዊ (ሁሉን አቀፍ) የምክክር መድረክን በማዘጋጀት መከረኛው የአገሬ ህዝብ በጉጉት ይጠብቅው የነበረውን የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለውጥ እውን ለማድረግ ስላልተሳካልን ይኸውና ውሎ ሲያድር ወደ ነበርንበት ክፉ የፖለቲካ አዙሪት ተመልሰን በመከርቸም ላይ እንገኛለን ።

 የቀድሞው ኢህአዴግ  የአሁኑ ብልፅግና  እና በእርሱ የሚመራው መንግሥት መሪ (ጠቅላይ ሚኒስትሩ) መንበረ ሥልጣኑን ከተረከበበት ጊዜ ጀምሮ  በየአጋጣሚውና በየምክንያቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ሌላ ባለሥልጣንና ባለሙያ በአገር የጠፋ እስኪመስል ድረስ በየቲቪ መስኮቱና በየአደባባዩ የሚያደርጋቸው ዲስኩሮችንና መግለጫዎችን  መሬት ላይ እየሆነ ከነበረውና እየሆነ ካለው መሪር ሃቅ ጋር እያመሳከረ ለሚታዘብ የአገሬ ሰው እውነትም  ዞረን ፣ዞረን ፣ ዞረን በነበርንበት አዙሪት ውስጥ እየተንደፋደፍን  መሆናችንን ለመገንዘብ ብዙ ማሰብን አይጠይቀውም።

በጠቅላይ ሚኒስትሩ የፖለቲካ ሰብእና ውስጥ የሚስተዋሉ ባህሪያትን ማለትም ፦

  • ልክ የሌለው የግል ዝናን የማግኘትና የማስጠበቅ ፖለቲካ ( narcisit political personality)፣
  • የህዝብን ደካማ ጎን እየፈለጉና እያጠኑ ለርካሽ ፖለቲካ ፍጆታ ማዋል (deliberate and cheap political manipulation)፣
  • ሃላፊነትንና ተጠያቂነትን ለመሸሽ ደካማ ሰበብ ( clumsy execuse) የመደርደርና በህዝብ አእምሮ ውስጥ እንደ እውነተኛ ምክንያት እንዲሰርፅ የማድረግ የቆሸሸ የፖለቲካ ጨዋታ (uncritical  and dirty political indoctrination)፣
  • የሥልጣን መሠረቴን አጣለሁ በሚል ህገ ወጥና ወንጀለኛ ግለሰቦችንና ቡድኖችን ለህግ ተገዥ ሳያደርጉ ስለ ህግ የበላይነት  ፍትህ መስበክ/መደስኮር (hypocracy) ፣
  • የህዝብን ጆሮና ስሜት የሚገዙ ዲስኩሮችን (ንግግሮችን) በአደባባይ በሰላ አንደበት እያዥጎደጎዱ ከአደባባይ በስተጀርባ የጎሳና የቋንቋ አጥንት ቆጠራ ፖለቲካን በተረኝነት ማስቀጠል ብቻ ሳይሆን የማስፋፋትና የአገር ውስጥ የፖለቲካ ካርታን የመቀየር ቅዠት ከሚቃዡ ፖለቲከኞችና ቡድኖች ጋር መዶለት   (political conspiracy ) ፣
  • የፖለቲካ እንጭጭነት (political infantility/stupidity) ፣
  • ለእራስን ሥልጣንና ለሴራ ማራመጃ ተቋማት ምቾት የማይሰጡ መረጃዎችንና ጠንካራ ሂሶችን የመካድን (denial of facts ans evidences) እና
  • የተቃርኖ ፖለቲካ ሰብእና  (self-contradictory political personality) በግልፅ የሚታዩና  ከመሻሻል ይልቅ እየባሰባቸው በመሄድ ላይ የሚገኙ መሆኑን መካድ ወይ የሆነውንና እየሆነ ያለውን ለመረዳት ያለመቻል (ድንቁርና) ወይም ከድንቁርና በሚከፋው አድርባይነት መለከፍ ወይም ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሚመራው ፓርቲና መንግሥት ውስጥ ካሉት የኢህአዴግ/ብልፅግና ፖለቲከኞች ጨርሶ የተለየ ጻድቅ ይመስል “ብቻውን ምን ያድርግ?” የሚል እጅግ የዘቀጠ አመለካከት ወይም ደግሞ  በፖለቲካ ፕሮፓጋንዳና በመሬት ላይ ያለውን እውነታ ለይቶ ያለመረዳት ችግር (dellusional disorder) ነው የሚሆነው።

እንደ አጠቃላይ እውነት (general truth) እነዚህ አሉታዊ የፖለቲካ ሰብእና መገለጫ ባህሪያት እንኳን እንደ እኛ በሁለመናው በእጅጉ ወደ ኋላ በቀረ አገር በአንፃራዊነት በልፅጓል በሚባል ዴሞክራሲያዊ አገርም ሊያጋጥሙ የሚችሉ ናቸው ። ከሰው ልጅ ሁሉን ነገር ለግል ወይም ለቡድን ዝና እና ጥቅም ለማዋል የመፈለግ አስቸጋሪ ባህሪያት ጋር የተቆራኙ በመሆናቸው።

እነዚህ አሉታዊ ባህሪያት  ሊያደርሱት የሚችሉትን ጉዳት ቀድሞ የመከላከልና ያደረሱትን ጉዳት በጊዜና በአግባቡ  የመቆጣጠሩ  ሁኔታ  በዴሞክራሲያዊ አገር እና እንደ እኛ የህዝብ ድምፅና ልዑላዊ መብት ከላይ እስከታች በተበላሸ ሥርዓተ ፖለቲካ በሚደፈጠጥበት አገር ውስጥ በእጅጉ የተለያየ ነው።

በዴሞክራሲያዊ አገር የሚያጋጥሙ ችግሮች በአሉታዊ ባህሪያት ከሚሸነፉና ጉዳት ከሚያደርሱ ግለሰቦች እንጅ  በህግ የበላይነትና በህዝብ ዴሞክራሲያዊ መብቶች መሠረት ላይ  ከተገነባው ሥርዓት ብልሹነት  የሚመነጩ   አይደሉም።

እነዚህ አሉታዊ የፖለቲካ ሥልጣን ባህሪያት በእንደኛ አይነቱ አገር የሚመነጩትና ከቁጥጥር ውጭ የሚሆኑት ከላይ እስከታች በእጅጉ ከተበላሸ (ከሚገማ) ሥርዓተ ፖለቲካ ነው። በእንዲህ አይነት ብልሹነት ከአናቱ እስከ እስከ እገር ጥፍሩ እጅግ የገማውን (የከረፋውን) ኢህአዴጋዊ ሥርዓት ከዚያው ከእራሱ በወጡ ፖለቲከኞች በለየለት የሸፍጥ ተሃድሶ (ብልፅግና የሚል ስም በመለጠፍ) እንደ ሥርዓት ለማስቀጠል ሲሞክሩ ለምንና እንዴት ? ብሎ አለመጠየቅና አስፈላጊውን የነፃነትና የፍትህ ትግልን አለመቀጠል (አለማስቀጠል) ወደ ነበርንበት ብቻ ሳይሆን ምናልባትም የባሰ አስከፊ ወደ ሆነ አዙሪት ተመልሰን የመዝቀጣችን እጣ ፈንታ ፈቅዶ መቀበል የሚሆነው።  መፍትሄውም ይህን አይነት ሥርዓት አስወግዶ ዴሞክራሲያዊና ለህዝብ ልዑላዊ የሥልጣን ባለቤትነት ተገዥ የሆነ ሥርዓትን እውን ማድረግ ብቻ ነው።

አዎ!የለውጥ አመራር ተብየው ቡድን ኢህአዴግን ጠጋግኖ እንደ ሥርዓት ለማስቀጠል የሚያደርገውን የሸፍጥና የሴራ ፖለቲካ እንዲቀጥል መፍቀድ  “በአሮጌው አቆማዳ አዲስ ወይን” ለማስቀመጥ እንደ መሞከር ነው የሚለው አጠቃላይና አነፃፃሪ አገላለፅ ትክክል ነው። የኢህአዴግ ሥርዓት ግን ማርጀት በሚያስከትለው አሉታዊ እውነታ ብቻ የሚገለፅ አይደለም። የኢህአዴጎች ሥርዓት ከማርጀት አልፎ ለሩብ ምዕተ ዓመት ልክ በሌለውና ታጥቦ በማይለቅ መርዛማ ፖለቲካ ወለድ ግፍና የብልግና ቆሻሻ የተበከለ በመሆኑ እንዲቀጥል ከተፈቀደለት አደገኛነቱ የከፋ ነው።ለዚህ ነው ተመልሰን እየተዘፈቅን ያለንበትን አዙሪት ይበልጥ ሥር እየሰደደና እየተንሰራፋ ጨርሶ በቁጥጥሩ ሥር ሳያደርገን የሚበጀውን ሁሉ ማድረግ የሚኖርብን።

ይህን ማድረግ ቀላል ነው? አይደለም። ግን ማነው ቀላል እንዳይሆን ያደረገው ? በዋናነት የሸፍጠኛና ሴረኛ የኢህአዴግ/የብልፅግና ፖለቲከኞች ርካሽ የፖለቲካ ጨዋታ እንደ ተጠበቀ ሆኖ እንደ መልካም ግለሰብ ዜጋ፣ በፖለቲካና በተለያዩ ማህበረሰባዊ እና ሙያዊ ዘርፎች እንደ ተደራጀ አካል እና በአጠቃላይ እንደ ህዝብ ሩብ ምተ ዓመት ሙሉ በዴሞክራሲዊ አርበኝነት የተደራጀ ፣ የተዘጋጀና ፀንቶ የቆመ ሃይል (ድርጅት)  አምጦ መውለድና ተባብሮ ማጎልበት አቅቶን ምሬት በወለደው የስሜት ትኩሳት እየተሳከርን ይኸውና ዛሬም አስቀያሚውን  የውድቀት (የክሽፈት) ፖለቲካ ታሪክ የመድገም አዙሪትን ሰብሮ  ለመውጣት አለመቻላችን የሚያስከትልብን  ተጠያቂነት የዋዛ አይደለም።

እናም በእጅጉ በሚያሳዝን ተቃርኖ የተተበተበውን የፖለቲካ እኛነታችን በዴሞክራሲያዊና በአገር ወዳድነት የአርበኝነት ውሎ አስፈትተንና ፈትተን እንዲህ እያልን የምንዘምርበት ወርቃማ ጊዜ ቢያንስ ዓመታትን እንደማይወስድብን እየተመኘሁ አስተያየቴን ልቋጭ ፦

ስንቱን የለውጥ እድል አበላሽተን

ያን ሁሉ ግፍ አሳልፈን

ደጋግሞ ከመውደቅ ተምረን

የጎሳ/የመንደር ፖለቲካን ተፀይፈን

አብሮነትን በመከባበር አድምቀን

እኩልነትን በዴሞክራሲ አረጋግጠን

የግፈኞች ሥርዓትን ድል ነስተን

ይኸው ዛሬ ለዚህ በቃን

እውነትም እኛ ጀግኖች ነን

 

 

 

 

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.