በደቡባዊ አፍሪቃ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ በተደረገዉ ዉይይት ያስተላለፉት የአቋም መግለጫ

ሰኔ 20 ቀን 2012 ዓ.ም.

ፕሪቶሪያ ፣ደቡብ አፍሪቃ

113112896 5af62ee6 a632 47ad bbf0 3f0051356236እኛ በደቡብ አፍሪካ፣ በሞዛምቢክ፣ በናምቢያ፣ በቦትስዋና ፣በሌሴቶ፣ በኢስዋቲኒ እንዲሁም በማዳጋስካር የምንኖር ኢትዮጵያዉያንና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን በፕሪቶሪያ የኢፌዴሪ ኤምባሲ እና በደቡባዊ አፍሪካ የኢትዮጵያ ምሁራን ማህበር ትብብር አዘጋጅነት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከቱ ጉዳዮች፣ የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ለአገራችንና ለቀጠናው ሃገራት የሚኖረው ፋይዳ ፣ የናይል ወንዝ ለዘላቂ ትብብር፣ ለአህጉራዊና አለማቀፍ ግንኙነት ፣እንዲሁም የኢትዮጵያ የውሃ ኃብትና አለማቀፍ ግንኙነት ላይ ትኩረት በማድረግ ሰኔ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. በዌቢናር ዙም ቴክኖሎጂ በመታገዝ ያካሄድነውን ውይይት መሰረት በማድረግ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡

ሀ) የናይል ወንዝ የኢትዮጰያን 70 በመቶ የሚሆነዉን ዓመታዊ የገጸ ምድር ዉሃ መጠን ይሸፍናል፡፡30 በመቶ የሚሆነዉን የሀገሪቱን የቆዳ ስፋት አካሎ ይፈሳል፡፡40 በመቶ የሚሆነዉ ህዝቦቿ ህይወት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በዚህ ወንዝ ላይ የተመሰረተ ነዉ፡

  • ከ110 ሚልዮን ህዝቦቿ ዉስጥ 60 በመቶ የሚሆነዉ ህዝብ መሰረታዊ የኤሌክትሪክ አገልግሎት የማያገኝ ፣ ዓመታዊ የኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ፍላጎት በየዓመቱ በ19 በመቶ እየደገ ይገኛል፡፡ ፡ 86 በመቶ የሚሆነዉ የናይል ዉሃ ከኢትዮጵያ ይመነጫል፡፡ኢትየጵያ ዉሃዉን በመጠቀም የህዝቦቿን የልማት ፍላጎት ለማሟላት ሉአላዊ ተፈጥሮአዊ እንዲሁም ህጋዊ መብት ያላት እንደሆነ በጥብቅ እናምናለን ፡፡

ለ) ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡን መገንባት የፈለገችበት ምክንያት የቅንጦትና የተጨማሪ አማራጭ ፍለጋ ጉዳይ ሳይሆን ከድህነት ወለል በታች የሚኖረዉን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝቧን ከድህነት የማዉጣት ፣ እያደገ የመጣዉን የኤሌክትሪክ ሃይል ፍላጎት የማሳካት ፣ የመጠጥ ዉሃ አቅርቦትን የማሟላትና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚደረግ ጥረት አካል ነዉ፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የናይል ዉሃ መፍሰስን ሳያቆም ኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጭ ግድብ እንደሆነ ተረድተናል ፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሚኒስትሮች ም/ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 77ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል

ሐ) ኢትዮጵያ በግድቡ ዙሪያ በተፋሰስ ሀገራት ትብብር እንዲጠናክርና መተማመን እንዲፈጠር ያደረገችዉ የግልጽነትና አሳታፊነት ያልተቆጠበ ጥረት፣ ግድቡ የትብብር እንጅ የግጭት ምንጭ እንዳልሆነ በአጠቃላይ ቀጠናዊ ኢኮኖሚያዊ ዉህደትን እዉን ለማድረግና ለታችኞች ተፋሰስ ሀገራት በርካታ የልማት ትሩፋቶች ያሉት ፕሮጀክት እንደሆነ ተገንዝበናል፡፡ የተፋሰሱ ሃገራት ለዘላቂ ትብብርና ተጠቃሚነት ባያዘጋጁትን የናይል ቤዚን ኢኒሼቲቭ ማእቀፍ ሃገራት በሙሉ ተቀብለው በማጽደቅ ተግባራዊ ማድረግ ያለውን ፋይዳ ተረድተናል፡፡

መ) ግብጽ ለታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የሚዉል ሃብት ኢትዮጵያ ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ብድርና እርዳታ እንዳታገኝ የተሳካ ተደጋጋሚ ጥረት ከማድረግም በተጨማሪ አገሪቱ የደረሰችበትን የእድገትና የቴክኖሎጂ ደረጃ በመጠቀም ከናይል ወንዝ ውጪ በርካታ የውሃ ፖቴንሽያል እያላት ይህንን ሃብቷን ከማልማት ይልቅ ናይልን የሞት ሽረት ጉዳይ አድርጋ በተሳሳተ ትርክት ህዝቧን በማነሳሳት ቀጠናውን ወደ አለመረጋጋት ለመውሰድ የምታደርገውን ጥረት ተገቢ እንዳልሆነ ተገንዝበናል ፡፡

ሠ) የኢትዮጰያ መንግስት ሀገሪቱ ያሏትን የተፈጥሮ ሃብቶች ጥቅም ላይ ለማዋል እያደረገ ያለዉን ያላሰለሰ ጥረት እናደንቃለን፣እንደግፋለን፡፡ግድቡን በፍትሃዊነት ፣በምክንያታዊነት እንዲሁም በሌሎች ላይ ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ ዓለም ዓቀፍ መርህን በጠበቀ እንዲሁም እ.ኤ.አ. ማርች 2015 በግብጽ፣በሱዳንና በኢትዮጵያ በተፈረመዉ የመርህ ስምምነት/DOP/ መሰረት እያከናወነች በመሆኑ ግድቡ እዉን እንዲሆን ጥረቱን አጠናክሮ መቀጠል የሚኖረውን ጠቀሜታ ተረድተናል፡፡

 

በመሆኑም እኛ የኮንፈረንሱ ተሳታፊዎች የሚከተሉትን ጥሪዎች እናቀርባለን፣

  1. ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በኢትዮጵያዉያንና ትዉልደ ኢትዮጵዉያን ከፍተኛ ተሳትፎና ተነሳሽነት እንዲሁም በኢትዮጵያ መንግስት ቁርጠኝነት የራሳችን አሻራ ያረፈበት በራሳችን ሃብት ብቻ የሚገነባ የኢትዮጵያውያን አንድነት ከመቼውም ጊዜ በላይ በእጅጉ የተንጸባረቀበት የብሄራዊ ኩራታችን መገለጫ ግድባችን ነዉ። ስለሆነም ኢትዮጵያዉያንና ትውልደ ኢትዮጵያዉያን ህብረታችንና አንድነታችን በማጠናከር በጽናትና በቁርጠኝነት በመቆም ግድቡ እስኪጠናቀቅ ድረስ በገንዘባችን ፣በጉልበታችን ፣በሙያችን ፣ በጥናትና ምርምር እንዲሁም ሌሎች ዙሪያ መለስ ድጋፍ በማድረግ የአድዋን ድል በዘመናችን ለመድገም ቃል እንገባለን፡፡
ተጨማሪ ያንብቡ:  Remembering Yekatit ፩፪ – Ethiopian Martyrs’ Day – SBS Amharic

 

  1. ግብጽ የናይል ወንዝን በብቸኝነትና በበላይነት የመጠቀም፣ ፍትሃዊ ያልሆኑ፣ ለዘመኑ የማይመጥኑና ተቀባይነት የሌላቸው የቅኝ ግዛት ስምምነቶች ከማሰቀጠል በመነጨ ፍላጎት የሶስትዮሽ ዉይይት ዉጤታማ እንዳይሆን በተደጋጋሚ እያደረገች ያለዉ እንቅፋት የመፍጠር አካሄድ በእጅጉ አሳዝኖናል፡፡ ስለሆነም ግብጽ ከዚህ ተግባሯ እንድትቆጠብ በጥብቅ እያስገነዘብን የግብጽና የሱዳን ወንድምና እህት ህዝብ ድርድሩ በትብብር መንፈስ እንዲሁም ሁሉንም ህዝቦች በፍትሃዊነት ተጠቃሚ በሚያደርግ መልኩ እንዲካሄድ ድጋፍ እንዲያደርግና በራሱ መንግስታት ላይ ተገቢውን ተጽእኖ እንዲያሳርፍ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

 

  1. ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የናይል ተፋሰስ ሀገራት በትብብር መተግባር ከቻሉ በርካታ ህዝቦቻቸዉን ከድህነት ሊያወጣ የሚችል መሆኑን እናምናለን፡፡ ኢትዮጵያ በናይል ጉዳይ በጋራ ተጠቃሚነትና በትብብር መንፈስ የመልማት ፍላጎትን እያራመደች ያለዉን አቋም እንዲሁም ብሄራዊ ጥቅሟን ለማስከበር እያደረገች ያለዉን ጥረት የምንገነዘብ ሲሆን የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮግራም ሶስት ሃገራት የመርህ ስምምነት መሰረት የምታሂካደዉን የመጀመሪያ ግድቡን የመሙላት ፕሮግራም በዘንድሮ ክረምት በተያዘለት ጊዜ እዉን እንዲሆን ሙሉ በሙሉ እንደግፋለን፡፡

 

  1. አፍሪካውያን ወንድሞችና እህቶች ከቅኝ ግዛትና ከአፓርታይድ አገዛዝ ነጻ ለመዉጣት ባደረጉት መራራና የተራዘመ ትግል ኢትዮጵያ የማይተካና ጉልህ አወንታዊ ሚና ማበርከቷ ይታወቃል።በተመሳሳይ ሁኔታ የተፈጥሮ ሃብቷን ጥቅም ላይ ለማዋል ሉኣላዊና ተፈጥሮአዊ መብቷን ለማስከበር በምታደርገዉ ጥረት አፍሪቃውያን በሙሉ ፍትሃዊ አቋም ከያዘቸው ከኢትዮጵያ ጎን እንድትቆሙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡

 

  1. የሶስትዮሽ ድርድሩን እንዲታዘቡ የተጋበዙ ሀገራት በሙሉ ለፍትሃዊነት፣ ለእኩልነትና ምክንያታዊነት እንደሚቆሙ እንዲሁም ሉአላዊነታችን በማክበር ኢትዮጵያን ያገለለና ተቀባይነት የሌለው እስከ ዛሬም የጎላ ጉዳት ያደረሰ የቅኝ ግዛት ስምምነት መቀጠልን እንደማይፈቅዱ እምነታችን የጸና ሲሆን በዚሁ እየተመሩ እስከ መፍትሄው መዳረሻ እንዲደርሱ ጥሪያችን እናቀርባለን ፡፡
ተጨማሪ ያንብቡ:  ጄ/ል ባጫ ደበሌ በሜሪላንድ ግዛት የ350ሺህ ዶላር ቤት ገዙ

 

  1. ደቡብ አፍሪካ በግብጽ ፣ሱዳንና ኢትዮጵያ መካከል እየተካሄደ ባለዉ ድርድርና ዉይይት በታዛቢነት መሳተፏን እናደንቃለን፣ እንደግፋለንም፡፡ ደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያ በሉአላዊ ግዛቷ የሚገኘዉን የተፈጥሮ ሃብቷን የመጠቀም መብትን እንደምትገነዘብና የቅኝ ግዛት ስምምነት መቀጠል እንደማትደግፍ እምነታችን የጸና ሲሆን ችግሩን በመፍታት ሂደት ገንቢና ትክክለኛ አቋም ይዛ በአፍሪቃ ህብረት የወቅቱ ሊቀመንበርነት ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ም/ቤት ተለዋጭ አባልነቷ እንዲሁም ባላት የተጽእኖ ፈጣሪነት ደረጃዋ ጭምር የተጣለባትን ታሪካዊ ኃላፊነት እንድትወጣ ጥሪያችን እናቀርባለን::

 

  1. አለማቀፉ ማህበረሰብ ግድቡን አስመልክቶ በሶስቱ ሀገራት ሲካሄድ የቆየውና እየተካሄደ ያለውን ድርድር እንደገና በማስቀጠል መግባባት ያልተደረሰባቸዉን ጉዳዮች ሁሉንም አካል ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋገጥ መልኩ በአፍሪቃ ህብረትና ሌሎች ክልላዊ ተቋማት ድጋፍ አለመግባባቱ እንዲፈታ ተገቢውን ድጋፍ እንዲያደርግ፣ ግብጽ የአህጉራዊ ተቋማትን ፋይዳና ክብር በማሳነስ ጉዳዩን ለተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ለአረብ ሊግ እንዲቀርብ ማድረጓ ስህተት እንደሆነ ተገንዝቦ ትክክለኛ አቋም ይዞ ከጎናችን እንዲቆም ጥሪ እናቀርባለን፡፡ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ከመገንባት ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ በታችኞች ተፋሰስ ሀገራት ግልጽነትና መተማመን እንዲፈጠር ከጅምሩ እስካሁን ድረስ ያደረገችዉ የዲፕሎማቲክ ጥረት የሚደነቅ ነዉ ፡፡ ይሁን እንጅ ግብጽ በሶስቱ ሀገራት መካከል እየተካሄደ ያለዉን ገንቢና የትብብር መንፈስ ዉይይት እንዳይሳካ በማድረግ በቀጠናዉ ዉጥረት እንዲፈጠር እየደረገች ትገኛለች፡፡ ስለሆነም ከዚህ ተግባሯ እንድትታቀብ የዓለም ዓቀፍ ማህበረሰብ ግፊት እንዲያደርግ ጥሪ እናቀርባለን፡፡

 

ሰኔ 20 ቀን 2012 ዓ.ም.

ፕሪቶሪያ, ደቡብ አፍሪካ

https://www.amharic.zehabesha.com/first-pretoria-declaration-on-gerd-conference/

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.