አብን የሕወሓት የምርጫ እንቅስቃሴ በህግ እንዲታገድ ሊጠይቅ ነው

454በቀደመው ሕወሓት መራሹ የኢህአዲግ አመራር “በኃይልና ያለ ሕዝብ ፍላጎት ወደ ትግራይ ተካለዋል” ባላቸው የአማራ ግዛቶች ሕወሓት አካሂዳለሁ ያለው ምርጫ በህግ እንዲታገድ እንቅስቃሴ መጀመሩን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ አስታወቀ።

የአማራ ህዝብ ግዛቶች በሕወሓት በጫናና በማን አለብኝነት የተካለሉ ናቸዉ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽ/ቤት የትግራይ ክልል ም/ቤት ምርጫን እንዲያስፈፅምለት ያቀረበለትን ጥያቄ ምንም እንኳ ባይቀበለውም አሁንም የክልሉ ምክር ቤት የተናጥል ምርጫ አካሂዳለው በሚለው አቋሙ የሚገፋበት ከሆነ በተለይም አወዛጋቢ በሆኑትና በሀገራዊው ምርጫ ተሳትፎ ልናደርግባቸው በወሰንባቸው ሕወሓት በኃይል ወደ ትግራይ ባካለላቸው ቀደምት የአማራ ግዛቶች የሚካሄደው ምርጫ እንዲታገድና የሀገራዊ ምርጫው ሂደት መራዘምን አስመልክቶ የፌዴሬሽን ምክርቤት ያሳለፈው ውሳኔ እንዲከበር አቤቱታችንን ለሕገመንግስት አጣሪ ጉባኤ ለማቅረብ ዝግጅታችንን አጠናቀናል ሲሉ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ /አብን/ አመራር በተለይ ለዶይቼ ቨለ “DW” ገልፀዋል። የጉባኤውን የህግ ትርጌሜና ውሳኔ ካወቅን በኋላም በፌዴሬሽን ምክርቤትና በፍርድ ቤት የህግ ጥሰቱ በአፋጣኝ እርምት እንዲያገኝ ለመንቀሳቀስ ወስነናል ሲሉም ነው የአብን ምክትል ሊቀመንበር አቶ የሱፍ ኢብራሒም የንቅናቄውን አቋም ይፋ ያደረጉት።

ሃላፊው እንዳሉት “የአማራ ህዝብ ቀደምት ግዛቶች በነበሩትና የሕወሓት የስልጣን የበላይ በነበረበት ዘመን ወደ ትግራይ ክልል አስተዳደር ያለ ሕዝብ ፍላጎት በጫናና በማን አለብኝነት ያለአገባብ በተካለሉት አካባቢዎች ማለትም በወልቃይት፣ በሁመራ፣ በራያ፣ በጠገዴ፣ በጠለምት እና በሌሎችም አካባቢዎች በአገራዊው ምርጫ ለመወዳደር በማኒፌስቷችንና በምርጫ መርሃግብራችን በዕቅድ አስቀምጠን ከፍተኛ ዝግጅት ስናደርግ ቆይተናል”። ይሁንና በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልል ምርጫ በተናጥል እንደሚያደርግ ማስታወቁን ተከትሎ በነዚህ ግዛቶች ሊደረግ የታቀደው ኢ-ሕገመንግስታዊ የምርጫ ሂደት እንዲታገድልን ነው ህጋዊ ጥያቄ ለማቅረብ የተገደድነው ሲሉ ተናግረዋል። በመሰረቱ የትግራይ ክልል የፌዴሬሽን ምክርቤት በኮረና ወረርሽኝ አስገዳጅ ምክንያት አገራዊ ምርጫው እንዲራዘም ካሳለፈው ውሳኔ በተቃራኒው በፖለቲካ ሹክቻ ምክንያት የጀመረው የተናጥል የምርጫ እንቅስቃሴ ፈፅሞ ተቀባይነት የለውም ብሎታል አብን::መንግስትም “ሕግና ሥርዓትን ለማስከበር ዳተኛና ቸልተኛ ሆኗል” ሲሉ ተችተዋል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሙስሊሙ መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት የፍርድ ቤት ቀጠሮ ለፊታችን ሰኞ መዘዋወሩን ለጠበቆቻቸው በስልክ ተነገራቸው

አብን በትግራይ ክልልና በፌደራል መንግስቱ መካከል ያለው የፖለቲካ ውዝግብ ለመፍታት፤ በቀደመው ሕወሓት መራሹ ኢህአዴግ በማን አለብኝነት ከአማራ ቀደምት ታሪካዊ ግዛቶች በግዳጅ ተወስደው የተጠቃለሉበትን ሂደት የድርድር አካል እንዲሆን አንፈቅድም” ሲልም በአፅንዖት አሳስቧል፡፡ አካባቢዎቹን እንደ “መታያና ጉቦ፣ በሰጥቶ መቀበል ስሌት የፖለቲካ መደራደሪያ እንዲያደርጉት እንደማንፈቅድ የትግራይ ክልል አስተዳደርም ሆነ ፌደራል መንግስቱ ሁለቱም አካላት እንዲያውቁት እንፈልጋለንም ሲሉ አቶ የሱፍ ጨምረው አስረድተዋል።

“የፌደራል መንግሥትና ሕወሓት እነዚህን አወዛጋቢ ቀደምት የአማራ ርስቶች ባላቸው የፖለቲካ አሰላለፍ “በሰጥቶ መቀበል ስልት የቅራኔያቸው መፍቻ ቁልፍ ለማድረግ ፍንጮችን አስተውለናል”

“የፌደራል መንግስት የትግራይ ክልላዊ መንግስትን ህገ ወጥ እቅስቃሴ የህግ እርምት በመውሰድ እስካሁን ማስቆም ነበረበት” ያሉት ሃላፊው በክልሉ በዜጎች ላይ የሚፈፀመው የሰብዓዊ መብት ጥቃት ተባብሶ ቢቀጥልም የፌደራል መንግሥት ግን ማስቆም አልቻለም ሲሉ ወቅሰዋል። ከለውጡ በፊት ኢሕአዲግ የሕወሓትን የመብት ጥሰት፣ አፈናና ዜጎችን የማፈናቀል ወንጀል አይቶ እንዳላየ በማለፍ ሽፋን ሲሰጥ እንደቆየ ሁሉ ዛሬም በአደባባይ አፈናና የመብት ረገጣ ሲፈፀም እጁን አጣምሮ እንደታዛቢ ከተቀመጠ በወሬ ደረጃ የሚለፈፈው፣ የኢትዮጵያ ቀጣይነትና ብልፅግና በተግባር አደጋ ላይ መውደቁ አይቀርም” ሲሉም አሳስበዋል። ማቆሚያ በሌለው ሰቆቃ የዜጎች ሕይወት እየተቀጠፈና የግፍ ሰለባ እየሆኑ አይደለም ሀገረ መንግስት የሚረጋግጠው ያሉት አቶ አቶ የሱፍ ፤የፌደራል መንግሥት የዜጎቹን መብት በማስከበርም ሆነ ሀገር በማዳን ጉዳይ ለሚያደርገው እንቅስቃሴ ፤ እኛም ሆንን የትግራይ ህዝብ ከጎኑ መሆናችንን ማወቅ አለበት ብለዋል።

ሕወሓት በኃይል በተቆጣጠራቸው የአማራው መሬቶች ላይ ባለርስቱን የአማራ ሕዝብ በማሳደድ ፣ በመግደልና የሕዝብ ስብጥርን በማዛባት /በዲሞግራፊ ለውጥ/ ከፍተኛ ወንጀልና የመብት ጥሰት አሁንም ድረስ እንደሚፈፅም ገሃድ የወጣ ሃቅ ነው በማለት ያብራሩት ኃላፊው በእነዚህ አካባቢዎች ተወዳዳሪዎቻችንን በማሰለፍ በአገራዊው ምርጫ ተሳትፎ ለማድረግ የወሰንነው ፍትሃዊ ምርጫ ይካሄዳል ከሚል ዕምነት ሳይሆን ለቆምንለት ሕዝብ ያለንን አጋርነት ለማሳየት ነው ሲሉም በቃለ መጠይቁ ወቅት ገልፀዋል። አብን ከተመሰረተበት ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ በሕወሓት መራሹ መንግሥት በኃይልና ያለ ሕዝብ ፍላጎት ከተለያየ ግዛት ወደ ትግራይ እንዲካለል የተደረገው የአማራ ሕዝብና መሬቱ እንዲመለስ ማድረግ ዋንኛ የማታገያ ስልቱ አድርጎ በማኒፌስቶው መቅረፁን ያወሱት አቶ የሱፍ ይህንኑ ዓላማውን ከግብ ለማድረስ አስፈላጊውን የህግና ሰላማዊ የትግል እንቅስቃሴ ሁሉ እንደሚያደርግም ነው ያስታወቁት። የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምርጫው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት መሆኑ ካቆመ ከዘጠኝ ወር በኋላ ይከናወናል በማለት ያሳለፈውን ውሳኔ እንደሚቀበለውና በህግ አግባብ መካሄዱንም እንደሚያምን ገልጿል።

ተጨማሪ ያንብቡ:  የአቶ ኃይለማሪያም ንግግር የስርዓቱ ኑዛዜ ወይስ ተከትሎ ለሚመጣ ፖለቲካ ሾኬ መንገድ ለመጥረግ? (ቃለ-መጠይቅ ከጋዜጠኛ አናንያ ሶሪ ጋር)

እንዳልካቸው ፈቃደ

አዜብ ታደሰ

ኂሩት መለሰ/ DW

3 Comments

  1. ህወሓት በግርግር ባካለላቸው አካባቢዎች ምርጫ ማካሄድ የለበትም፣ አይችልም። ከጅምሩ የማካለል አሳቡ ህገ ወጥ ስለሆነ። አብንን እደግፋለሁ። አሁኑኑ የሚያግድ ውሳኔ መተላለፍ አለበት፤

  2. በወያኔ አጀንዳ መሳፈር ከጀመርን መጋቢት ሁለት አመት ደፈን፡፡ አሁንም የምርጫ አጀንዳን ከለቀቀልን 15 ቀናት አልፈዋል፡፡ እኛ በእሱ ጉዳይ እንዳክራለን አጋሮቹ እነጃዋር ያራግባሉ እኛ ደግሞ ተሳፍረን መጭ ነዋ
    ጃዋር በቢሲ አምሃሪክ ላይ ክልሎች ምርጫ መቼና እንዴት መካሄድ እንዳለበት ይወስናሉ ፌዴራሉ ደግሞ ያን ያስፈጽማል፡፡ ይህ ማለት ፌዴራሉ መንግስት በክልሎች ይታዘዛል እንደማለት፡፡ ገራሚ ነው ምርጫው ባይሰረዝ ኖሮ ምርጫ ቦርድ ሲሰራቸው የነበሩት ሁሉ ልክ አልበሩም እንደማለት፡፡ ማመስ የፈለገ አካል እንዲህ እየገለባበጠ ይቆላናል፡፡ እሱ ምን አለበት
    ሌላው አስገራሚው ነገር ዛሬም በአገር አቀፍ ደረጃ እንወዳደራለን ባይ የነበሩ ፓርቲዎች በትግራይ ክልል ስለታሰበው ምርጫ ተሳትፏቸውም ሆነ ህጋዊነቱ ሲናገሩ አንሰማም፡፡ ድንቄም አገራዊ! እነሱ በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች ጋር ተነጋግረናል ይሉናል፡፡ ምን ማለት ነው፡፡ በክልሉ የሚንቀሳቀሱ ማለት በትግራይ ብሄር ስም ብቻ የተደራጁትን ለማለት ከሆ አገራዊ ፓርቲ ተብዬዎች (ኦነግ፣ አብን፣ አብሮነት፣ እና ሌሎችንም ጨምሮ) አገራችሁ የት ነው፡፡ ትግራይ አገራችን አይደለችም ካላችሁ ንገሩን እና እኛም እረድፋችንን እናስተካክል

  3. ኣብን ለኣማራው ብቻ ሳይሆን ለሀገራችን ፋና ወጊ እየሆናችሁ ነው ፣ በርቱ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.