/

እውን አሜሪካ እዚህ የሚያዳርስ ዘረኝነት አለ? – ከናፍቆት ገላው

racism in America e1593108671811የሚሞሪያል ደይ ምሽት፤ በሜኖሶታ ግዛት፤ ለሲጋራ ግዥ የተከፈለን 20 ዶላር የተጭበረበረ ነው ያሉ የስቶር ጠባቂዎች፤ ለፖሊስ ባደረጉት ጥሪ ተይዞ፤ በፖሊስ እጅ ህይወቱ በጠፋው ጥቁር አሜሪካዊ፤ ጆርጅ ፍሎይድ ጉዳይ የተቀሰቀሰው ቁጣ፤ እስካሁን በአንድም በሌላም መልኩ እንደቀጠለ ነው። የድርጊቱ ኢሰባዓዊት ሁሉንም ወገን ያግባባ ነው። እንደዚህ አይነቱን ክስተት ለመከላከል፤ የሆነ ለውጥ ማስፈለጉ ላይም ስምምነት ያለ ይመስላል። በመንስኤው እና መፍትሄው ላይ ያለው የእይታ ልዮነት ግን፤ ከቀን ቀን እየከረረ ሀገራዊ ቀውስ ወደመሆን አድጓል።

ሁኔታው በእኛ፤ በሀበሻ ኮሚውኒቲ ውስጥም ሀዘን የፈጠረ ነው። ብዙዎች ቁጭታቸውን እና ወገንተኝነታቸውን በተለያየ መልኩ ሲገልጹ ነው የሰነበቱት። እንደ አሜሪካ ነዋሪነታችን፤ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ፤ እየሆነ ያለው ነገር ይመለከተናል። ሆኖም፤ ነገሩ ብዙ አጀንዳ እና መሳሳብ የበዛበት እንደመሆኑ፤ አካሄዳችን ግራ ቀኙን የመረመረ መሆን እንዳለበት ይሰማኛል።

የጆርጅ ፍሎይድን ግድያ ተከትሎ፤ አወዛጋቢ እየሆነ የመጣው አብይ ጉዳይ፤ መሰረታዊ መንስኤውን በተመለከተ ያለው የተራራቀ እይታ ነው። በአንድ በኩል፤ በጥቁር አሜሪካውያን ላይ በተደጋጋሚ በፖሊስ የሚደርሰው የሞት አደጋ፤ ምንጩ ስር የሰደደ የነጭ ዘረኝነት ነው የሚል አቋም፤ በተለይ አላማቸውን የነጭ ዘረኝነትን በመታገል ላይ አድርገው በተመሰረቱ፤ ብላክ ላይቨስ ማተርን መሰል እንቅስቃሴዎች ውስጥ በስፋት ይስተጋባል። በሌላ በኩል፤ ክስተቱ፤ ከዘረኝነት ይልቅ፤ በአንዳንድ የፖሊስ አባላት፤ ኃይል ያለአግባብ የመጠቀም ዝንባሌ ምክንያት የሚደርስ ጥፋት እንደሆነ የሚያምኑ ወገኖች አሉ።

አሜሪካ አስከፊ የጥቁር ባርነት ታሪክ ያስተናገደች ሀገር ናት። ምንም እንኳን፤ የሃምሳ እና ስልሳዎቹ የመብት ትግል፤ በጥቁር አሜሪካዊያን ላይ ተጥሎ የቆየውን ህጋዊ አድሎ አስቀርቶ፤ ሙሉ የዜግነት መብት ከማስከበር አንጻር፤ ትልቅ ድል ቢያስገኝም፤ ሰርጾ የቆየ የዘረኝነት አመለካከት እንዲሁ በኖ የሚጠፋ ነገር አይሆንም። ግዜ ይፈልጋል። አሁን ላይ፤ አሜሪካ እንደ ሀገር፤ ለጥቁር የነበረውን አሉታዊ አመለካከት ከመቅረፍ አንጻር ብዙ እርቀት እንደተጓዘች አጠያያቂ አይመስለኝም። ሁኔታዎች በብዙ መልኩ ተቀያይረዋል። ያም ሆኖ፤ ዘረኝነት ከነ አካቲው ከስሟል ብሎ ማሰብ አይቻልም። ቅሪቱ አይጠፋም። ጥያቄው የመጠን ጉዳይ ነው። አሜሪካ ውስጥ፤ በዚህ ዘመን፤ ጥቁሮች ላይ ለሚደርስ ማንኛውም ጥቃት ሆነ፤ የኑሮ ተግዳሮት፤ ዘረኝነት የሚጫወተው ሚና ምን ያህል ነው?

ነገሩን ሰሞንኛ ርዕስ ወደሆነው፤ በፖሊስ እጅ ጥቁሮች ላይ የሚፈጸም ግድያ አጥብበን ብንመለከት፤ ያሉት መረጃዎች፤ እንደዚህ አይነቱ ክስተት፤ ሁሌም ምንጩ ዘረኝነት ነው ብሎ ለመደምደም የሚያስደፍሩ አይደሉም። በዋሽንግተን ፖስት፤ በፖሊስ ተኩስ የሚደርስ የሞት አደጋ የመረጃ ክምችት (The Washington Post police shooting database) መሰረት፤ ከ2014 እስከ 2019፤ በአምስት አመት ውስጥ፤ በፖሊስ ተኩስ ህወታቸው ያለፈ ዜጎች ቁጥር፤ በዘር ስብጥር ሲቀመጥ፤ 2,469 ነጭ፤ 1,293 ጥቁር፤ 900 ስፓኒሽ እና 219 ሌሎች ሲሆን፤ ይህው ቁጥር ከእያንዳንዱ ዘር የህዝብ ብዛት አንጻር ሲሰላ ውጤቱ፤ 13% ነጭ፤ 31% ጥቁር፤ 23% ስፓኒሽ እና 4% ሌሎች ይሆናል1

first graph

መረጃው እንደሚያሳየው፤ ምንም እንኳን በጥሬ ቁጥር ደረጃ፤ የነጭ አሜሪካዊያን ተጎጅዎች ቁጥር ከጥቁሮቹ ቢበልጥም፤ ከህዝብ ብዛት አንጻር ሲሰላ፤ የጥቁር አሜሪካዊያን በፖሊስ እጅ የመሞት ተጋላጭነት፤ ከነጮቹ ከሁለት እጅ በላይ የከፋ ሆኖ ይገኛል። በአንድ መልኩ፤ ይህ ቁጥር፤ በጥቁር ላይ ያነጣጠረ ጥቃት እንዳለ አመላካች ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። በሌላ በኩል ግን፤ ከሃምሳ ፐርሰት በላይ የሚሆነው ወንጀል፤  ከአጠቃላዩ የአሜሪካ ህዝብ ከአስራ አምስት ፐርሰት በታች በሚወክሉት፤ ጥቁር አሜሪካዊያን የሚፈጸም መሆኑ ከግምት ውስጥ ሲገባ፤ ልዮነቱ ብዙም የተጋነነ አይሆንም። ለምሳሌ፤ በፍትህ ቢሮ ስታትስቲክስ (Bureau of Justice statistics)፤ ከ1980 እስከ 2008 በተሰበሰበ መረጃ፤ ከአጠቃላዩ የወንጀል ተግባር 45.3% የሚሆነው በነጭ አሜሪካዊያን የተፈጸመ ሲሆን፤ 52.5% የሚሆነው በጥቁር አሜሪካዊያን የተፈጸመ ነው2። ጥቁር አሜሪካዊያን፤ በወንጀል ተግባር ላይ ያላቸው፤ ከብዛታቸው ጋር ያልተመጣጠነ ውክልና፤ ቢያንስ በተወሰከነ ደረጃ፤ በፖሊስ እጅ የመሞት ተጋላጭነታቸው ከፍተኛ ለመሆኑ አስተዋጾ ይኖረዋል።

second graph

በርግጥ፤ አብዛኛው በፖሊስ ተኩስ የሚደርስ የሞት አደጋ፤ ተጠርጣሪን በቁጥጥር ስር በማዋል ሂደት ላይ፤ በአስገዳጅ ሁኔታ የሚፈጸም እንደመሆኑ፤ የጆርጅ ፍሎይድን አሟሟት በዚህ ስታትስቲክስ መነጽር ማየት ይከብዳል። እጁን ታስሮ መሬት ላይ የተኛ ሰው አንገት ላይ፤ ያን ያህል ሰአት ጉልበት ማሳረፍ፤ ከፖሊስ ሥራ አንጻር ትርጉም የሚስጥ አይደለም። ፖሊሱ ያደረገውን እንዲያደርግ የገፈው፤ እብሪትም ሊሆን ይችላል፤ ንቀትም ሊሆን ይችላል፤ ዘረኝነትም ሊሆን ይችላል፤ ድርጊቱ ኢሰባዓዊ ከመሆኑ በስተቀር ስለ ምክንያቱ እርግጠኛ መሆን የሚቻል አይመስለኝም። ሟቹ ጥቁር፤ ገዳዮ ነጭ እንደመሆኑ፤ ነገሩ ከዘረኝነት ጋር ለመያያዝ የተመቸ ነው። ነገር ግን፤ እንደዚህ አይነቱ ክስተትም ቢሆን በጥቁርዎች ላይ ብቻ የታጠረ አይደለም። በ2016፤ በተመሳሳይ ሆኔታ፤ በፖሊስ በደረሰበት አላስፈላጊ እንግልት፤ ቶኒ ቲምፓ የተባለ ነጭ አሜሪካዊ ህይወቱ ሲያልፍ የሚያሳይ ቪዲዮ፤ ዮቱብ ላይ Tony Timpa ብሎ ሰርች በማድረግ ማግኛት ይቻላል3

በዚህም አለ በዛ፤ የፖሊስ አሰራር ላይ ለውጥ ማስፈለጉ የሚያከራክር ነገር አይደለም። በጆርጅ ፍሎይድ ላይ አደጋውን ያደረሰው ፖሊስ፤ ከዚህ ቀደም አላስፈላጊ ኃይል ከመጠቀም ጋር በተያያዘ፤ አስራ ስምንት ያህል አቤቱታ ቀርቦበት፤ በሁለቱ ብቻ በዲሲፕሊን ሲቀጣ፤ በተቀረው እንዲሁ የታለፈ ሰው መሆኑ በራሱ፤ የፖሊስ ተጠያቂነት ላይ ያለውን ክፍተት ያሳያል። የጆርጅ ፍሎይድ ሞት የቀሰቀሰው ቁጣ፤ የፖሊስ አሰራር ላይ የሚታዩ ግድፈቶች፤ ትኩረት አግኝተው እንዲታረሙ ያግዝ ይሆናል። ከዚያ ባለፈ ግን፤ የፖሊስ በጀት ይቀነስ ከሚለው ጀምሮ፤ ተቋሙ ጭራሹኑ ይፍረስ እስከሚለው ጥግ የተለጠጠው ፖሊስ ጠል ቅስቀሳ፤ ሌላ መዘዝ አለው።

የፖሊስ ቁጥጥር ሲላላ፤ የወንጀል ተግባር በዛው ልክ ይጨምራል። በ2014፤ በፈርጉሰን ሚዞሪ፤ ማይክል ብራውን የተባለ ጥቁር አሜሪካዊ፤ በፖሊስ ተኩስ መሞትን ተከትሎ፤ ፖሊስ ላይ የተከፈተው ተቃውሞ፤ በተለይ ጥቁሮች በብዛት በሚኖሩበት አካባቢ፤ ለፖሊስ አባላት፤  እንደልብ ተዘዋውሮ ቁጥጥር ለማድረግ አዳጋች ሁኔታ በመፍጠሩ ምክንያት፤ የተከሰተው የወንጀል መጨመር፤ ይህን እውነት በተግባር ያሳየ ነው4። አሁንም፤ የተጀመረው፤ ፖሊስን በጅምላ የማሸማቀቅ ዘመቻ፤ ፈር መልቀቁን ከቀጠለ፤ ፖሊስ ጫናውን ፍራቻ ማፈግፈግ መጀመሩ አይቀሬ ነው። በዚህ መኃል፤ የሚፈጠረው ስርአት አልበኝነት፤ ጦሱ የሚተርፈው፤ ህግ አክብሮ ሰርቶ ለማደር ለሚተጋው ዜጋ ነው።

ማንኛውም ሙያ ሆነ ተቋም፤ ሙሉ በሙሉ ከስህተት የጸዳ ሊሆን አይችልም። ለምሳሌ፤ በአመት ውስጥ በህክምና ባለሞያዎች እንዝህላልነት፤ ቁጥሩ ቀላል ያልሆነ የሰው ህይወት ያልፋል። ነገር ግን፤ ማንም ጤነኛ አይምሮ ያለው ሰው፤ የተወሰኑ ሐኪሞች ስላጠፉ፤ የሐኪም ቤት በጀት ይቀነስ ወይም ሐኪም ቤት ይዘጋ አይልም። ችግሩ የጥራት ነው። በጀት መቀነስ ሆነ፤ ተቋም ማፍረስ፤ ጥራትን ከማሻሻል ጋር ግኑኝነት የላቸውም። እውነት ለመናገር፤ በቀን ውስጥ፤ ለህግ ማስከበር ስራ ከሚሰማራው ቁጥሩ እጅግ ብዙ የሆነ የፖሊሰ ኃይል እና ከሚሰጠው አገልግሎት ብዛት አንጻር ሲመዘን፤ የጥፋቱ መጠን በምንም መልኩ እዚህ የሚያዳርስ አይደለም።

የፖሊስ አሰራር ላይ የሚደረግ ማሻሻያ፤ ያለአግባብ የሚጠፋ የሰው ህይወትን፤ በተቻለ መጠን ለመቀነስ ይረዳል። ኃይል መጠቀምን ከፖሊስ ስራ ጨርሶ ማስቀረት ግን አይቻልም። የፖሊስ ውሎ ከወንጀለኛ ጋር ነው። አደጋ የሚያደርሰው፤ ፖሊስ በተጠርጣሪ ላይ ብቻ ሳይሆን፤ ተጠርጣሪ በፖሊስ ላይም ነው። በ2019 ብቻ 48 የፖሊስ አባላት፤ ከተጠርጣሪ በተሰነዘረ ጥቃት ህይወታቸውን አጥተዋል5። ህግ በማስከበር ሂደት ላይ፤ ለህይወት የሚያሰጋ ሁኔታ ከተፈጠረ፤ ፖሊስ፤ ቀድሞ እራስን የመከላከል እርምጃ ለመውሰድ፤ የህግ ከለላ አለው። ይህ መብት ባልተከበረበት፤ ማንም ፖሊስ ከወንጀለኛ ጋር ተጋፍጦ ህግ እንዲያስከብር መጠበቅ አይቻልም።

መዘንጋት የሌለበት ነገር፤ ፖሊስ እንዲሁ ደርሶ ማንም ላይ አይተኩስም። ዞሮ ዞሮ አላማው፤ የጥቁር አሜሪካዊያንን ህይወት መታደግ ከሆነ፤ ፖሊስን ከማረም በተጎዳኝ፤ ግለሰቦችን፤ በፖሊስ እጅ ለሚደርስ አደጋ ተጋላጭ የሚያደርጉ ሶሾኢኮኖሚያዊ ሁነቶች ላይ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል። ባለፉት ሀምሳ እና ስልሳ አመታት፤ ጥቁር አሜሪካዊያን፤ በብዙ ዘርፍ ከፍተኛ እድገት ያሳዩ ቢሆንም፤ አሁንም ቁጥሩ ቀላል የማይባል ጥቁር አሜሪካዊ፤ በድህነት እና ለኑሮ ባልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ ይገኛል። በአንድ ወገን፤ ከባርነቱ ዘመን ሲንከባለል የመጣ ጫና፤ በሌላ ወገን፤ እራስን ከማስቻል ይልቅ፤ የጠባቂነት ስሜትን ሚያበረታቱ የመንግስት የእርዳታ ፕሮግራሞች፤ ለችግሩ መፈጠር በምክንያትነት ይቀርባሉ። ያም ሆነ ይህ፤ ችግሩ አለ።

ጥቁር አሜሪካዊያን ላይ፤ በዋናነት የተጋረጠው ማህበራዊ ቀውስ፤ የተረጋጋ የቤተሰብ መዋቅር መመንመን ነው። በ2015 ስታስቲከስ መሰረት፤ ሰባ ፐርሰንት ያህል ጥቁር አሜሪካዊያን፤ ከትዳር ውጭ ይወለዳሉ። ከዚህ ውስጥ፤ አብዛኛዎቹ፤ አባቶቻቸውን በቅርብ የማያገኙ ወይም ጭራሹኑ የማያውቁ ናቸው።  በተለይ፤ ጥቁሮች በብዛት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች፤ ችግሩ አጠቃላይ የኮሚውኒቲው ሁነት ስለሚሆን፤ ታዳጊ ወጣቶች፤ የኑሮ ክህሎት የሚቀስሙበት ሰው በቤታቸው ብቻ ሳይሆን በአካባቢያቸውም ያጣሉ። ከዚህ የተነሳ፤ አብዛኛዎቹ ሐይስኩል ሳይጨርሱ ትምህርት ያቋርጣሉ፤ ለሱስ ተጠቃሚነት ይጋለጣሉ፤ ያለ እድሜያቸው እና ከትዳር ውጪ ይወልዳሉ። ከዚህ ሲከፋም፤ ቤታቸው ያጡትን ከለላ እና ድጋፍ ፍለጋ፤ የተደራጀ የወንጀል ቡድኖችን ይቀላቀላሉ።

ባለፉት አመታት፤ በአሳማኝም ሆነ፤ አሳማኝ ባልሆነ ምክንያት ይባል፤ በፖሊስ እጅ ሞተው፤ ሀገር ያነጋገሩ ጥቁር አሜሪካዊያን የኑሮ መዝገብ ሲፈተሽ፤ ሁሉም ላይ ማለት ይቻላል፤ የተከማቸ የወንጀል ሪከርድ ይገኛል። ሌሎቹን ትተን፤ የቅርቡን፤ የጆርጅ ፍሎይድን ብናይ፤ ከ1997 እስከ 2005፤ ለስምንት ያህል ግዜ፤ ከአደንዛዥ እጽ ጋር በተያያዘ ተፈርዶበት፤ በተለያየ ወቅት እስር ቤት አሳልፎል። በ2007፤ ከሌሎች ጎደኞቹ ጋር በመሆን በፈጸመው በመሳርያ የታገዘ ዝርፊያ ምክንያት ተፈርዶበት፤ 2009 እስከ 2013 ለአምስት አመት ታስሮ ወጥቶል። በርግጥ ከ2013 ወደዚህ ያለው ሪከርድ ንጽህ ቢሆንም፤ አደጋው በደረሰበት እለት፤ በሁለት አነቃቂ መድሐኒቶች ተመርዞ እንደነበር፤ የአስከሬን ምርምራው ውጤት ያሳያል። ይህን የምለው፤ ማናቸውንም ለመውቀስ አይደለም። ነገር ግን፤ ፖሊስ በሚያደርሰው አደጋ እና በተጠቂዎቹ ባህርይ መኃከል ያለው ዝምድና፤ ከቆዳ ቀለም ይልቅ፤ ህግ የመተላለፍ ዝንባሌ፤ ለአደጋው ይበልጥ እንደሚያጋልጥ አመላካች ነው።

እድሜአቸው ከአርባ አራት አመት በታች ለሆነ ጥቁር አሜሪካዊያን፤ ቁጥር አንድ የሞት መንስኬ ግድያ ነው6። የአንድም ሰው ህይወት ግድ ሊሰጥ ይገባል። ይህ እንዳለ ሆኖ፤ ለዚህ አሃዝ፤ በፖሊስ እጅ የሚደርስ አደጋ የሚያደርገው አስተዋጾ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም። የጥቁር ወጣት አሜሪካዊያንን ህይወት፤ በአሳሳቢ ሆኔታ እየቀጠፈ ያለው፤ በሌላ ጥቁር አሜሪካዊ የእድሜ አቻዎቻቸው የሚሰነዘር ጥቃት ነው7። አስቀድሜ እንዳልኩት፤ የአንድም ሰው ህይወት ዋጋ አለው። ነገር ግን፤ ብላክ ላይቨስ ማተርን መሰል፤ የጥቁር መብት ተሟጋቾች፤ ጥቁር በፖሊስ እጅ ሲሞት፤ ሀገር የሚነቀንቁትን ያህል፤ በእርስ በእርስ ግጭት፤ በየቀኑ፤ ስለሚጠፋው የጥቁር ወጣት ህይወት፤ ጀሮ ዳባ ልበስ ማለት መምረጣቸው፤ አላማቸው ላይ ጥያቄ የሚያስነሳ ነው።

በአልተመቻቸ ሁኔታ ውስጥ የሚኖሩ ጥቁር አሜሪካዊያንን፤ ስነልቦናዊ፣ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ህይወት ለማሽሻል የሚያግዙ ሁኔታዎችን ማመቻቸት፤ ከመንግስትም ሆነ ከሌሎች አካላት ይጠበቃል። ሁኔታውን ለመቀየር፤ ወሳኝ ድርሻ የሚኖረው ግን፤ ጥቁር አሜሪካዊያን እራሳቸው፤ ለሁኔታው ኃላፊነት ወስደው የሚፈጥሩት ውስጣዊ ለውጥ ነው። አሁን ላይ፤ በጥቁሮች መብት ዙርያ የሚደረገው ትግል መሰራታዊ ህጸጽ፤ አይን ያፈጠጡ ማህበረሰባዊ ቀውሶችን እያድበሰበሱ፤ ውጫዊ ተግዳሮቶችን የማግዘፍ ባህሪ ያለው መሆኑ ነው።

የዘር አድሎ፤ ለጥቁር አሜሪካዊያን የህይውት እንቅፋት ስለመሆኑ የሚያሳይ የጎላ ምልክት በሌለበት ሁኔታ፤ የነጭ ዘረኝነት ላይ ዘመቻ መክፈት፤ ምናባዊ ጠላት ማሳደድ ነው የሚሆነው። እውነተኛውን ችግር በመጋረድ፤ መፍትሄ የሚገኝበትን ግዜ ከማራቅ በቀር፤ ከዚህ ለድሃው ጥቁር የሚተርፍ ነገር አይኖርም። ይልቁንስ፤ በነጭ እና ጥቁር መካከል የሚኖረውን ግንኝነት አላግባብ በማሻከር፤ ሁኔታውን ይበልጥ የማወሳሰብ አደጋ ይጋርጣል። እንቅስቃሴውን፤ ከውስጥ የሚገፉትም ሆነ፤ ከውጭ እየተቀበሉ የሚያራግቡት፤ ግራ ዘመም ፖለቲከኞች ይህ ጠፍቷቸው አይደለም። ድጋፋቸው ጥቅማቸውን ያሰላ ነው። ለአሜሪካ ዲሞክራቶች፤ የጥቁር አሜሪካዊያንን ብሶት እየቆሰቆሱ፤ የምርጫ ድምጽቸውን መቆጣጠር፤ አዲስ ዘይቤ አይደለም። ሁሉም ማለት ይቻላል፤ ድህነት እና ወንጀል የሚበረክትባቸው ከተሞች፤ በዲሞክራት ነው የሚተዳደሩት። ፍላጎቱ ቢኖር፤ እስከዛሬ ሁኔታውን ለመቀየር ብዙ ነገር ማድረግ ይችሉ ነበር።

 

የሰው ልጅ፤ በአፍጢሙ ተደፍቶ፤ ጉልበት አንገቱ ላይ ተተክሎበት፤ ትንፋሽ እየለመነ፤ ነፍሱ ቀስ በቀስ ስታመልጠው ባይን ማየት፤ ከአይምሮ በቀላሉ የሚፋቅ ነገር አይደለም። በዚህ ላይ፤ ጥቁሮች በነጮች ባርነት ያሳለፉት አስከፊ ዘመን ሲታሰብ፤ ሁኔታው የበለጠ ቁጭት እና ሀዘን ይቀሰቅሳል። እንደ ሰውነታችን፤ እንደ ጥቁርነታችን እና እንደ አሜሪካ ነዋሪነታችን፤ በሆነው ነገር፤ እኛም ጋር፤ ቁጣ እና ስጋት መፈጠሩ የሚጠበቅ ነው። ነገር ግን፤ ይህን አሳዛኝ አጋጣሚ በመቃዎም ስም፤ ፖሊስ ላይ፤ አልፎም የአሜሪካ የስልጣኔ መሰረቶች ላይ፤ በየአቅጣጫው የተከፈተውን የአመጽ ዘመቻ ከመቀላቀላችን በፊት፤ የሚባለው ነገር፤ ከነባራዊ ሁኔታው ጋር፤ ምን ያህል የተገናዘበ መሆኑን መመርመር ይኖርብናል። አነሰም በዛ፤ ሁላችንም የአሜሪካን ኑሮ ኑረን እናውቀዋለን። ሌላው ቢቀር፤ ሁኔታውን ከእራሳችን እና በዙርያችን ባሉ ሰዎች ተሞክሮ ጋር ማመሳከር እንችላለን። ህግ አክብረን፤ ስርአት ጠብቀን፤ ኑሮን ለማሸነፍ እስከተጋን ድረስ፤ እውን በአሜሪካ፤ በቆዳ ቀለማችን ምክንያት፤ የሚደርስብን አድሎ፤ የሚዘጋብን በር አለ? መልሱን ለአንባቢ እተዋለሁ።

ከናፍቆት ገላው

 

Link to Reference: –

 1. https://www.washingtonpost.com/graphics/investigations/police-shootings-database/
 2. https://www.bjs.gov/content/pub/pdf/htus8008.pdf
 3. https://www.youtube.com/watch?v=_c-E_i8Q5G0
 4. https://www.washingtonpost.com/news/volokh-conspiracy/wp/2016/07/20/the-ferguson-effect/
 5. https://www.fbi.gov/news/pressrel/press-releases/fbi-releases-2019-statistics-on-law-enforcement-officers-killed-in-the-line-of-duty
 6. https://www.cdc.gov/healthequity/lcod/men/2017/nonhispanic-black/index.htm
 7. https://www.amjmed.com/article/S0002-9343(12)00638-9/pdf

 

 

8 Comments

 1. Of course, the race relation in the USA is much better than the oromo-ruled current Ethiopia. Look the number of White Americans who take part in the BLM movement. Was there a single oromo, politician or ordinary citizen, who denounced the killings of 86 Amharas in a very savage way? Of course, none. Is there any oromo, politician or ordinary citizen who stood with non-oromo Ethiopians living in so-called oromia when their rights to use own language, elect and be elected was denied? Is there any oromo, politician or ordinary citizen, who denounced the delivery of condominium houses in Addis on the basis being oromo? Of course none. All of the above do not happen in the USA although it is not a perfect country. All of the above happen only in Ethiopia, a country led by savage people like Takele Goma.

 2. በፓሊስ በኩል የደረሰና የሚደርስ ችግር በቆዳ ቀለም ሰበብ የለም ብሎ ማመን እባብን አቅፎ አልነደፍም እንደማለት ነው። ችግሩ ግን አሁን የምናየው ብቻ ሳይሆን የቆየና ሥር የሰደደ ችግር ነው። ለችግሩ ፓሊስን ብቻ ተጠያቂ ማድረግም እውነትነት የለውም። እንዲያውም ለጥቁር ህዝብ ቀዳሚ ጠላቱ ራሱ ነው። አሁን በፓሊስ ጫና መተንፈስ አቅቶት ህይወቱ ያለፈው ወገን በእርሱ ሞት ብቻ ይሄ ሁሉ ግርግርና ጥፋት ተፈጠረ ብሎ መቀበልም ጅልነት ነው። ሩቅ ያልሆኑ የፓሊስ ወንጀሎችን ለመረመረ መተንፈስ አቃተኝ ብሎ የሞተ ይህ ሰው ብቻ አይደለም። አሉ ብዙዎች። አንዳንዶች እስር ቤት ከገቡ በህዋላም የተገደሉ አሉ። ያው ግን በዚህም በዛም የጤና ጉድለት ስለነበረባቸው ሞቱ ተብሎ ይነገረናል፤ ተነግሮናል።
  ከላይ ጸሃፊው የለጠፈልን ስታቲክስ በነጭ ተቀምሮ የቀረበለትን ነው። ያላወቀው ነገር ግን 40% የፓሊስ ገጠመኞችና ግብግቦች ሪፓርት እንደማይደረጉ ነው። ስለዚህ የአሃዙ ቅማሬ ቀበሮን የዶሮዎችን ቤት ጠብቂልኝ ብሎ አደራ እንደመስጠት ነው። ምን አልባት የአሜሪካ የወሬ አውታሮች የሚያናፍሱትን ላዳመጠ ውሸት ከእውነት ጋር ተቀይጦ ለገቢያ እንደሚወጣ ለይቶ ማወቅ ይችላል። የጥቁር ህዝቦች መከራ አለማቀፋዊ ነው። በየትኛውም አለም በቆዳቸው ቀለም ብቻ ወደዳር ተገፍተው በፓሊስ ወከባና ግድያ የሚደርስባቸው በሁሉም የዓለም ጫፍ አሉ። ፈረንሳዪች ለራሳቸው መዝናኛ ከሶሪያ ቆርጠው ሃገር ያረጓት ሊባኖን በሃበሻ ሰራተኞች ላይ የሚያደርሱትን ግፍ መጥቀስ ይቻላል። ግን በአሜሪካ በቅርብ ጊዜ የተፈጠረውን የጥቁር ግድያ አስመልክቶ ግርግሩ የተፋፋመው በጥቁሩ ሞት ብቻ አይደለም። 40 ሚሊዪን ህዝብ ሥራ አጥ የሆነባት፤ በሲያትል በሳንፍራንሲስኮ በሌሎችም ከተሞች ጎዳና ተደዳዳሪዎች እንደ አሸን የፈሉባት ይች አሜሪካ አያሌ ውስብስብ ነገር ውስጥ ናት። ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት ነጥቦች የጥቁሩን ሞት ተገን አርጎ ሰው የታፈነውን ቆጣ ገልጦበታል እየገለጠበትም ነው።
  በቅድሚያ ችግሩ የሃገሪቱ መሪ ፕረዚዳንቱ ናቸው። በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ እንዲህ ያለ ብቀላንና እከክልኝ ልከክልህ የሚለውን የፓለቲካ ፈሊጥ ለራሱ ጥቅም ያደረገ፤ በውጭና በውስጥ ፍልሚያ እንዲፈጠር ያደረገ መሪ ኖሯት አያውቅም። በቅርቡ John Bolton The Room Where It Happened በማለት የጻፈውን መጽሃፍ ላነበበ ዋይት ሃውስ መቀለጃ መሆኑ ይረዳል። አንድ ብቻ ልጥቀስ ከመጻሃፉ ቴሌቪዚን ላይ ቀርቦ መግለጫና ማብራሪያ ከሰጠ በህዋላ ፕሬዝደንቱ ጠርቶ “You (John Bolton) have done a good job. But you forgot to praise me” በማለት ይናገረዋል። ሌላው ሁሉ በየጊዜው ታክሎበትም ሆነ እንዳለ በየሚዲያው የምናየው በመሆኑ እዚህ ላይ መጥቀስ አስፈላጊ አይደለም
  ሁለተኛው ሳይወድ በግድ በቫይረሱ ምክንያት የተቆለፈበት ሰው በግድያው ምክንያት አግኝቶ እሮሮውን ያሰማበት መንገድ ነው። ሶስተኛ የጥቁሮች በየጊዜው መገደልን በመቃወም የወጣ ግሩፕ ነው። ግን በማሃከላቸው ደግሞ ጠፋትና ዝርፊያን የሚሹ ሃይሎችም አሉበት።
  የዚህ ጽሁፍን ጸሃፊ Evicted by Matthew Desmond; Confessions of an Economic Hit Man by John Perkin ሌሎችንም መጽሃፍቶችና ተጨባጭ ሁኔታዎች አገናዝቦ የችግሩ ምንጭ ለዘመናት ወደ ጎን የተጣለ ህዝብ መከራ እንጂ የአንድ ሰው ሞት ብቻ እንዳልሆነ መረዳት ይቻላል። ለምሳሌ ከላይ ኮሜንት የጻፈውን ሰው እይታ ብቻ ማየት በቂ ነው። አሁንም የሚተነፍሰው በዘር ፓለቲካ ነው። ምንም ከተጻፈው ሃሳብ ጋር አይገናኝም። ለዚህም ነው የጥቁር ህዝብ ዋና ጠላቱ ራሱ ነው የምለው። በህብረት መቆም ቢቻል ነገሮች እንዲህ ባልሆኑም ነበር። በቃኝ!

 3. Wow Wow wow Please the Zehabesha Please remove this article from your website. Please. As an Ethiopian living in America, I am extremely disgusted let alone Black leaders. Even conservative white writers are not writing this kind of disgusting thing at this movement. Black Caucus begidebu egnan degifew eyetefalemu eyalu, tsehafew gin yewuha balbetnetachinen asalifew lemesitet lemiasgedidun nechoch activist hone. Please remove this thing immediately. Amarigna yeminager Gibitsawi wod Englizegna tergumo letkur meriwoch email liargew yichilal minchun keEthiopian Community in America bilo. It may cost us. Gibitsoch yemiyareguten Atwal. Even the writer may be an Egyptian origin. Please remove it.

 4. The writer is simply apologetic to racism and whatever he says runs in the face of reality. I don’t think you understand the problem. It is not a matter of education.

 5. The writer sounds much the apologists of the carnage in Ethiopia! It is a shame to have such a view as an Ethiopian a country considered by the global race as a beacon of freedom. Alas, times has changed!!!

 6. ይህንን ጽሑፍ ሳነብ የተሰማኝን ጥልቅ ሐዘን እና የተደበላለቀ ስሜት ለመግለጽ ያቅተኛል። ቢሆንም በመጀመሪያ ጸሐፊው በዚህ ጉዳይ ላይ ጊዜያቸውን ወስደው በቁም ነገር በድምዳሜ መልክ ሳይሆን በጥያቄ መልክ ሃሳባቸውን በመግለጻቸው ሳላመሰግናቸው አላልፍም።
  በበኩሌ ጽሑፉን በመጀመሪያ ሳነበው አንድ ፈረንጅ በእንግሊዝኛ ከጻፈው የተተረጎመ ነበር የመሰለኝ። ይኸውም ጽሑፉ ከበደሉ ተቀባይ አፍሪካዊ ያለውን ርቀት በማየት ነው። በጥልቀት ሳስበው ግን ይህን ዓይነት ለበደሉ ባይተዋርነት ብቻ ሳይሆን አልፎ ተርፎም ይበላቸው የሚያሰኝ ስሜትን መፍጠር ትልቁ የዘረኝነት ጭቆና፣ በተለይ ደግሞ የአሜሪካው ሥርዓት ባሕርይ ነው። እንኳን አላፊ አግዳሚ ወይም ከጭቆናው ተጠቃሚ የሆነውን ይቅርና ከተጨቋኙ ወገንም ሳይቀር የጭቆና ዋና በትር ለሚያርፍበት ወገን ተቆርቆሪነት እንዳይሰማቸው የማድረግ ችሎታ አለው። የሥርዓቱ ባሕርይ። ይህንን እንደ ማልኮም ኤክስ ያሉ የነጻነት ታጋዮች የቤትና የውጭ ባርያ በሚል ይገልጹታል። ከማድቤት እና በእልፍኝ የሚውለው ባርያ፣ የጌቶቹን ፍርፋሪና ጭላጭ እየቀማመሰ ቀለል ባለ ሥራ ተጠምዶ የሚውል እንደመሆኑ ጌቶቹ ሲያስነጥሱ እሱን ጉንፋን የሚይዘው፣ እነሱ ሲታመሙ፣ ዛሬ አሞናል የሚል ነው ይለናል። በአንጻሩ የበደሉ ገፈት ቀማሽ የሆነው የውጭ (የእርሻ) ባርያ ግን፣ ጌቶቹ ሲያስነጥሱ ይድፋህ! ይድፋሽ! የሚል ነው። ይህ የዝንባሌ ልዩነት የሚፈጠረው በጭቆናው ምሬት ልዩነት ብቻ ሳይሆን ሥራዬ ተብሎ በሚደረግ የፕሮፓጋንዳና የስብከት ሥራም ጭምር ነው።
  ይህንን የነጭ የዘረኝነት ጭቆና ባሕርይ በሀገራችን በኢትዮጵያ ስናየው፣ ጣልያን የኤርትራን ትግሬዎች እናንተ የተሻላችሁ፣ ጨዋዎችና የሰለጠናችሁ፣ ሐቀኞች፣ ንጹሕና የተለያችሁ ናችሁ ብሎ መረብን ተሻግሮ ያሉትን ትግሬዎች ደግሞ የማይታመኑ፣ ኋላቀር፣ ቆሻሾች፣ ያልሰለጠኑ ወዘተ በሚል ስብከት የከፋፈለበት እና እስከ ዘመናችን የዘለቀ ከንቱ መናናቅን የፈጠረበትን ማየት እንችላለን። እንዲህ የተደለሉት የኤርትራ ትግሬዎች ለጣልያን በወታደርነት ተቀጥረው (300, 000 የሚሆኑ) ወንድሞቻቸውን ለመውጋት አብረውት ተሰልፈዋል። በቀደመው ዘመን። የኋለኛውም ጦስ (መልኩን ቀይሮ) ለኛም ትውልድ ተርፎናል።
  የጥቁር አሜሪካውያንን ጭቆና ለመረዳት አንድም የነሱን ኑሮ መኖር አለዚያም ጠለቅ ያለ ምርምር አድርጎ የዓለም አቀፉን የዘረኝነት ባሕርይም ተረድቶ በዚህ በአሜሪካ በምን መልኩ እየተተገበረ እንደሆነ ማስተዋልን ይጠይቃል። ካለበለዚያማ ሥርዐቱ በሚሰጠው መረጃ እና ፕሮፓጋንዳ ተመሥርቶ ቢበዛ ግልብ የሆነ ግንዛቤ ከማግኘት አልፎ የበደሉን ክፋትና ደረጃ ለማወቅ አይቻልም። እንዲያውም የሥርዓቱ አሞጋሽ ሊያደርግ ሁሉ ይችላል። ከሕወሃት ሥርዓት ፕሮፓጋንዳና መረጃ ተነስቶ ስለዲሚክራሲያዊ ምርጫዎቹና ስለኢኮኖሚው እድገት ትክክለኛ ግንዛቤ ለማግኘት እንደማይሞከረው። የሚቀርበውን መረጃ ሐስትነትና ድፍረት በሥፍራው የተገኘ ሰው ብቻ ነው በትክክል የሚረዳው። አንዳንድ ጊዜም ድፍረቱ በማናለብኝነት የሰውን ግንዛቤ ሁሉ የሚያዋርድና ፈጣጣ ይሆናል። ዓለም እየተከታተለው በነበረው ወንጀል እንኳን ፍሎይድ የሞተበትን ምክንያት ፖሊሶች የላቦራቶሪ ውጤት በልብ ድካም እንደሞተ አሳየ ማለታቸው የብልግናቸውን ጥግ፣ የድፍረታቸውንም ልክ ያሳያል።
  በአሜሪካን ሀገር ስለ ፖሊስ ግፍ ስናወራ ስለካቴናው መጥበቅና መላላት፣ መገዝገዝና መቁረጥ እንጂ ስለ ሰብዓዊ ጥላቻ የምንነጋገር ከመሰለን ነገሩ አልገባንም። ላብራራው። ፖሊስ የጭቆናው ሥርዓት መጠቀሚያ እንጂ ራሱ ጨቋኙ አይደለም። አንድ እሰረኛን የታሰረበት እግር ብረት ወይም ካቴና እየገዘገዘ ቢያደማው፣ እጅግ ጠብቆ ቢያሰቃየው ስለካቴናው ብርታትና ክፋት ስናወራ ብንውል ፋይዳ የለውም። ለውጥ ከተፈለገ ማተኮር ያለብን በእስረኛው ላይ ካቴናውን ስላጠለቀው አሳሪና ግፈኛ መሆን ይኖርበታል። ፖሊስ በታዘዘውና በተፈቀደለት ልክ የሚንቀሳቀስ የመጨቆኛ መሳሪያ ነው። አሁንም ወደ ሃገራችን ተመልሰን በምሳሌ እንይ። ሕወሃት ወደ አዲስ አበባ በምትገሰግስበት ጊዜ ከገንጣይነታቸው በመነጨ በጥላቻ በሚያይዋቸው ሰላማዊ ሰዎች ብዙ ስድብና ማንቋሸሽ የሚደርስባቸው ታጋዮቿን በሰጠቻቸው ጥብቅ ትእዛዝ ምክንያት ታጋዮቹ ክፉ አጸፋ አይመልሱም ነበር። ተሰድበው፣ ተዋርደው፣ በትሕትና ፈገግ ብለው ያሳልፉት ነበር። አዲስ አበባን ከተቆጣጠረች በኋላ በሰዓታት ጊዜ ውስጥ ይህ ባሕርይ ተለውጦ መስደብ አይደለም የገላመጣቸውን መሃል ግንባሩን በጥይት እያሉ ይደፉት እንደነበር ታይቷል። ሠራዊት በታዘዘው ልክ በተፈቀደለት ልክ የሚንቀሳቀስ የጌታው መሣርያ ነው። የአሜሪካ ፖሊሶች በወንጀላቸው የሚጠየቁ፣ የሚቀጡ፣ ከሥራ የሚባረሩ፣ የሚታሰሩ ቢሆን እንዲህ አይጨማለቁም ነበር። እንዲጨማለቁ የፈቀደላቸው ብቻ ሳይሆን ያበጃቸው ሥርዓት አለ።
  የአሜሪካ ሕዝብ ጥቁሮች የተለዩ፣ ወንጀለኛ፣ ዘገምተኛ፣ ሥራ ጠል፣ ታሪክ የለሽ ፍጡሮች ናቸው የሚል ፕሮፓጋንዳ በጡጦ እየጠባ የሚያድግ ነው። ዜና እና ፊልሙ ይቅርና የንግድ ማስታወቂያው ሳይቀር የረቀቀ ዘረኝነትን የሚያጎላ መልእክት ይበዛበታል። በትምህርት ቤት መጻሕፍት ላይ የሚመረጡት ስእሎች ከዚህ አኳያ መርዘኝነታቸው ተጠንቶ የሚመረጡ ናቸው። የሕጻናት የካርቱን ፊልሞች በዘረኝነት መልእክት የተጥለቀለቁ ናቸው። ብዙ ፊልሞች የሚወክሉት የጥቁር ገጸ ባሕርይ ክፋት ለአንድ ጥቂር ተዋናይ እጅግ አዋራጅ ከመሆኑ የተነሳ ተውኔቱን ፈረንጆች ሬንጅ ተለቅልቀው ጥቁር መስለው የሚሰሩበት ጊዜ ነበር። እግረ መንገዱንም የሥራ እድል ለመንፈግ አገልግሏል። በፓሊስ ከሚቀጠረው ውስጥ በዚህ ፕሮፓጋንዳ ያደገ እና ልክ አገባቸዋለሁ ብሎ የሚቀጠር ጥቂት አይሆንም። ሥልጠናውም የተለየ አይሆንም። ልክ በማግባት ”ሥራው”ም (ሞትና አካል ጉዳትን ጨምሮ) እድገትና ሽልማት እንጂ ሌላ እክል አይገጥመውም።
  ዘጠና በመቶ ጥቁሮች በሚኖሩባቸው ብዙ ከተሞች ውስጥ ፖሊስ የሚመለመለው በሰላሳና አርባ ደቂቃ ርቀት ከሚኖሩ የጀርመን ወይም የአይሪሽ ዝርያ ካላቸው ነጮች ሰፈር ነው። መንግሥት ይህንን የሚያደረገው በምን ዓላማ ነው ብለን መጠየቅ ነው ያለብን። የጥቁሩ ደሃ ጨቋኝ ነጩ ደሃ ነው። ነጩ ደሃ በጥቁሩ መናጢ ደሃ ዓይን በፖሊስነት በአንጻራዊነት የተንደላቀቀ ኑሮ፣ የመንግሥት መኪና ኮምፒውተር፣ ጥሩ ደሞዝ ያገኛል። የኦህዴድ፣ የአዴፓና የሕወሃት ካድሬ በቪ8 እና በጥቅማጥቅም ተደልሎ በወገኑ ላይ እንደሚከፋው። የወያኔ ታጋይ (ደሃ የደሃ ልጅ) ተጠቅሚያለሁ በሚል በየእስርቤቱ ደሆች ወገኖቹን ቶርቸር ሲያደርግ እንደከረመው። ይህ የዘረኝነት ወይም የጎሰኝነት የጭቆና ሥርዓት መገለጫ ነው። ደሃን በደሃ ማሰር። ደሃም ለደሃ እንዳያዝን ማድረግ። ለሩቅ ተመልካች ደግሞ ደሃው በተፈጥሯዊ ባሕርዩ “አስቸጋሪ” በመሆኑ መንስኤ በደሉና ግፉ የሚዘንብበት መሆኑን አበክሮ ማስገንዘብና ገጽታ ግንባታን መሥራት።
  ይህ የሥርዓት መገለጫ ነው። በሀገራችን በእርሻ እና በእደጥበባት ሥራ የሚታወቁ፣ በታታሪነትና በጨዋነታቸው የሚደነቁ የነበሩት ቤተ እስራኤላውያን ዛሬ የእስራኤልን እስር ቤት ያጣበቡ “ወንጀለኞች” የሆኑት የዘር “አስቸጋሪነት” ስላለባቸው ነውን? ወይስ ቀይ ባሕርን ሲሻገሩ የሆነ ጋኔን ተጠናውቷቸው?
  ለማለት የፈለግኩት የዘረኝነት የጭቆና ሥርዓት ሰዎችን በዚህ መልኩ የማስተዳደር ባሕርይ ስላለው ማንም ሆነ ማን በዚህ ሥርዓት ውስጥ የተፈቀደለትን ቦታ ነው የሚይዘው የሚለውን ነው። ጸሐፊው የቤተሰብ መፍረስን ወይም አለመኖርን ጠቅሰዋል። ይህ የሥርዓቱ ዓይነተኛ ዱላ ነው። ያረፈበት ሁሉ በዚህ ዱላ ይደቅቃል። ከሱዳን ወደ አሜሪካ በመጡ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች ላይ አንድ ጥናት ተሰርቶ ነበር። ወደ መቶ ከሚጠጉ ትዳር ይዘው ከመጡ ኢትዮጵያውያን ውስጥ ከአሥር ዓመት በኋላ ስድስት ብቻ በትዳራቸው ላይ ተገኝተዋል። እነዚህ ያልተማሩና በአብዛኛው በግብርና ይተዳደሩ የነበሩ ቤተሰቦችን የተቀበላቸው በጥቁር አሜሪካውያን ላይ ሲያርፍ የነበረው ዌልፌር የተባለው ዱላ ነው። በአሥር ዓመት ትዳራቸውን አፈራርሶ ብዙዎቹን ልጆቻቸውን እስር ቤቱ ተረክቧቸዋል።
  ብዙ ሰው የማይረዳው ብዙ እስር ቤቶች የግል መሆናቸውን እና እስራትና የፍርድ ሂደት ከፍተኛ የገንዘብ እና የሥራ ቅጥር ምንጭ መሆናቸውን ነው። ኩባንያና ፋብሪካ በሉት። ስለ ጥቁር አሜሪካውያን ጭቆና ሲነሳ ብዙ ሰው ሲሶው አፍሪካዊ ወንድ እስር ቤት መሆኑን ያውቃል። ልብ የማይለው ጉዳይ ግን ከታሰራው ሳይታሰር የታሰረው፣ በእስር ቤት ቅጥር ግቢ ሳይሆን በውጪ ሆኖ በፍርድ ቤት ትእዛዝ እና በፖሊስ ክትትል ውስጥ ያለው የመብዛቱን ነገር ነው። በዚህ ምክንያት አፍሮ አሜሪካውያን ከድህነታቸው በላይ እያንዳንዱ ቤተሰብ ማለት በሚቻል ደረጃ በተለያየ የጠበቃና የፍርድ ቤት ወጪ እና እዳ ውስጥ የተዘፈቁ ናቸው። የእስር ቤት ነገር ከተነሳ እስረኞች ጠያቂ በማይፈቀድበት እና ምግብ ከውጭ በማይገባባቸው እስርቤቶች ሳይቀር ሰማንያ በመቶ ድረስ የኮሮና (ኮቪድ 10) ተጠቂ የሆኑበት ምሥጢርስ ምን ይሆን?
  ጥቁር አሜሪካውያን ትምህርት እንዲጠሉ ከመቶ ዓመት በላይ የዘለቀ የተንኮል ሥራ ተሰርቶባቸዋል። ከመሀከላቸው ተጽእኖውን አምልጠው ትምህርት የሚወዱ ቢገኙ እንኳን በደሃው ጥቁር ሰፈር ባሉት ትምህርት ቤቶች የሚሰጠው ትምህርት እጅግ የወረደ ነው። ለምሳሌ ከኢትዮጵያ ጋር ብናስተያየው በአስራ አንደኛ ክፍል የሚሰጠው የሂሳብ ትምህርት በደርግ ዘመን አምስተኛ ክፍል ከተማርነው ጋር አንድ ዓይነት ነው። Math for Urban Schools ይላል አንዱ መጽሐፍ ለምሳሌ። ይህ በጥቁሮች ሠፈር ብቻ የሚሠራበት መጽሐፍ በመጀመሪያ ርእሱን ሲያዩት የከተማ ልጆች ለገበያ እና ለንግድ ባላቸው ቅርበት እና ንቃት ደረጃው ከፍ ያለ ሂሳብ እንዲማሩ የተመቻቸላቸው ይመስላል። ውስጡን ሲገልጡት ግን ሀ + ለ = ለ + ህ የሚለውን ለ11ኛ ክፍል ተማሪ የሚያስተምር ነው። በዚህ ክፍል ደረጃ ቁጥሩ ቀላል የማይባል ነጭና እስያዊ ልጅ ፕሪ ካልኩለስ ወስዶ ለኮሌጅ በመዘጋጀት ላይ የሚገኝበት ነው። በደሆች አፍሪካውያን አሜሪካውያን ሰፈሮች የሚያድጉ ልጆች ፏ ብሎ የተከፈቱላቸው የኮሌጅና የሥራ እድል በሮች ሳይሆኑ የአደንዛዥ እጽ ዝውውር ችርቻሮ እና የእስር ቤት በሮች ናቸው። ይህንን አደንዛዥ ዕጽ የሚያመላልሱ ባለ አሥራ ስምንት ጎማ ትራኮች፣ መርከቦች፣ ባቡሮች እና አውሮፕላኖች ያሏቸው ግን ጥቁሮች አለመሆናቸውን መገንዘብ ያሻል። አፍሮ አሜሪካውያን በአብዛኛው የአሜሪካ ትላልቅ ከተሞች ውስጥ ነጮች አውድመውና አብክተው ጥለዋቸው (ባጀቱን ግን ይዘው) በሄዱት የከተማው እምብርት ውስጥ ይኖራሉ። እነዚህ ሰፈሮች ውስጥ ተወልዶ ያደገ ኢትዮጵያዊ፣ ኤርትራዊ ወይም ሶማልያዊ የአፍሪካን አሜሪካኖቹ እጣ ነው የሚጠብቀው። ሜክሲካን ወይም ጓቴማላዊም ቢሆን ያው ነው። የፖሊስ ጭካኔ ሰለባ መሆን የሥራና ትምህርት እድል አለማግኘትና በወንጀል አዙሪት መጠለፍ። ለነዚህ ልጆች ውትድርና ፖሊስነት እና ዘበኝነት እንኳን እጅግ የራቁ የሥራ መስኮች ናቸው።

  በአንጻሩ በከተማው ዳርቻ የመካከለኛ ገቢ ዜጎች መኖሪያ በሆኑት ሠፈር የሚያድጉ እጅግም ብዙ የፖሊስ ዘረኝነት ሰለባ ሳይሆኑ አንዳንድ ጭርፍራፊ ዘረኝነት ከመምህራን እና ከክፍል ጓደኞቻቸው እየቀማመሱ በትምህርትና በሥራ ጎዳና ያለ ከባድ እክል ሊጓዙ ይችላሉ። ዘረኝነት አይደርስባቸውም ለማለት ሳይሆን ችላ ሊሉት ወይም ሸክሙን ተቀብለውት ሊጓዙ ሰፊ እድል አላቸው ለማለት ነው። በቅርቡ አንድ የትምህርት ቤቱን ምርጥ ተማሪ ዲስኩር ያቀረበ የግል ትምህርት ቤት ተማሪ ኢትዮጵያዊ ልጅ ባደረገው ንግግር እንዲህ ብሎ ወላጆቹንም ጭምር አስለቀሳቸው። “እስከ አሥረኛ ክፍል ማብቂያ ድረስ፣ በሳምንት ሁለት ቀን ብቻ ነበር የኖርኩት። ቅዳሜ እና እሁድ። ቅዳሜ ከቤተሰብና ከዘመድ ጋር ስውል፣ እሁድ ቤተክርስትያን ከምእመናን ጋር ስገናኝ። ከዚህ በስተቀረ ከሰኞ እስከ አርብ የኔን ሰውነት የተጠቀመ ማስክ ያደረገ ፍጡር በትምህርት ቤቱ ግቢ ይንቀሳቀስ ነበር።” ተማሪው ማስክ ብሎ የገለጸው በዘረኝነት የታጠበው ሕብረተሰብ ያጠለቀለትን የራሱ ያልሆነ ማንነት ነበር። ወላጆቹ ያለቀሱት በኮሌጅ ደረጃ የሚከፈል ውድ የሆነ ክፍያ እየከፈሉ ያስተማሩት ልጅ ከአሥር ዓመታት በላይ “መስሎ” እንጂ “ሆኖ” ለመኖር አለመቻሉ ነው። እነሱ ያላደጉበት ሥርዓት ስለሆነ ፈጽሞ ያልጠበቁት ቁስል ነበር። ይህ ልጅ ሲናገር አሥራ አንደኛ እና አሥራ ሁለተኛ ክፍሎችን እንደ ሰው ቀና ብሎ፣ ራሱን ሆኖ፣ ማስኩን አውልቆ ለመንቀሳቀስ ያስቻለው ክስተት እንደዚህ ነበር የተፈጠረው። አሥረኛ ክፍል ሲጨርስ ወላጆቹ ለጉብኝት ኢትዮጵያ ወሰዱት። አፍሪካውያን በሀገራቸው ምን እንደሚስሉ ለማየት እድል አገኘ። የሀገሩን ባህልና ታሪክ በጨረፍታም ቢሆን በቦታው ተገኝቶ ተመለከተ፣ ተማረ። ወላጆቹ ለቤተሰብ ጥየቃ ከመሄዳቸው በስተቀር ጉዞው በልጃቸው ሕይወት ላይ እንዲህ ያለ ታላቅና በጎ ተጽእኖ ይፈጥርበታል የሚል ሃሳብ አልነበራቸውም።

  ለማጠቃለል ከመቶ ዓመታት በተሠራ ግፍና በተዋቀረ ሥርዓት ምክንያት አንድ ንጹሕ አፍሪካን አሜሪካን ታዳጊ በብዙሃኑ አሜሪካዊ ዘንድ እንደወንጀለኛ፣ የባሕርይ ችግር እንዳለበት ተደርጎ ነው የሚታሰበው። ብዙ አሜሪካውያን አንድ ግዙፍ አፍሪካዊ ባለበት ጠባብ ክፍል ውስጥ መቀመጥ ራሱ ከፍተኛ የጭንቀት ስሜት ይፈጠርባቸዋል። እንኳን ግዙፍ አፍሪካዊ ይቅርና እኔ በራሴ ልምድ (መካከለኛ ቁመትና የቀይ ዳማ) ከሊፍት (ኤለቬተር)የሚወጣ ነጭ ሰው ጋር ድንገት ከተገጣጠምን በሰውነቱ ውስጥ ከፍተኛ ድንጋጤ ሲሰራጭ አስተውላለሁ። የሕንፃ ማእዘን ታጥፌ በድንገት ካንዱ ጋር ከተገጣጠምንም እንዲሁ።
  በአፍሪካውያን አሜሪካውያን ላይ የሚሰነዘረው የጭቆና በትር ከብዙ አቅጣጫ ከመሰንዘሩም በላይ በዘመናት ደግሞ እየረቀቀና መልኩን እየቀያየረ የመጣ ነው። ትልቁ እና ዋናው ዱላ በስነ ልቡናቸው ላይ የበታችነት ስሜትን በመፍጠር ለዘላለም ባርነት ለመዳረግ የተሰነዘረባቸው በትር ነው። ሁለተኛው ደግሞ በአፍሪካ እንደተደረገው የመከፋፈል ሴራ ነው። ነጮች ጥንት በባርነት ሲያመጡ የአፍሪካውያኑን ስብእናቸውን ለማጥፋት ቋንቋና ባህላቸውን የደመሰሱባቸው በመሆኑ በአፍሪካ እንደቀረው ሕዝብዊ በአሜሪካ ያሉትን በጎሳና በቋንቋ ለመከፋፈል አልቻሉም። ቢሆንም ግን መቶ በመቶ እስላም የሆነውን እና አንድ የሶማሌ ዝርያ ያለውን የሶማልያ ሕዝብ ከፋፍለው ለመበታተን የረቀቀ ልምዳቸውን እንደተጠቀሙት አፍሪካውያን አሜሪካውያንንም ከፋፍለውና በታትነው አቅመ ደካማ አድርገው አኑረዋቸዋል። ጭቆናውም እጅግ ብርቱ ቁጥራቸው ግን እጅግ አናሳ ከመሆኑ የተነሳ አሽቀንጥረው ሊጥሉት የሚቻላቸው አልነበረም።
  የይስሙላ ነጻነታቸውን ያገኙት ሰሜኑና ደቡቡ የአሜሪካ ክፍል በነሱ ጉልበት ለመጠቀም ባደረገው ሽሚያ በተፈጠረው ፍልሚያ ነው። ሰሜኑ የኢንዱስትሪ ቀጠና በመሆኑ ጉልበታቸውን በወዛደርነት የሚፈልገው የነበረ ሲሆን ደቡቡ የእርሻ ቀጠና የነበረና ጉልበታቸውን በባርነት የኢኮኖሚ መሠረት ያደረገ ነበር። የጦርነቱ አንኳር መንስኤ ይሄ ነው። ሌላው ፉገራ ነው። በዚያን ጊዜ አሜሪካ ከእንግሊዝ በመቆራረጧ ተጨማሪ የባርያ ጉልበት ማስመጣት አትችልም ነበር። የነበረው አማራጭ አገር ውስጥ ያለውን “የባርያ” ጉልበት መሻማት ነበር።
  በአፍሪካን አሜሪካን ላይ የተደራው የጭቆና ድርና የእስራቸው ሰንሰለት ጥልፍልፍ እጅግ የተወሳሰበ ከመሆኑ የተነሳ አንዳንዴ ፈጽሞ ተስፋ የሚያስቆርጥ ነው። በአለም ላይ ለዘመናት በደረሰባቸው ከፍተኛ በደል የይስሙላ እንኳን ካሳ ካልተሰጣቸው ግፉአን በአንደኛ ደረጃ የሚመደቡ ናቸው። ሕይወታቸው ተሻሽሏል የሚል ሰው የሚገኙበትን ከእንስሳት ያነሰ የኑሮ ደረጃ እና የሕይወት ምስቅልቅል ያላስተዋለ ነው። የዛሬዎቹ ልጆች ይቅርና አያቶቻቸው እንኳን አባት የሚለውን ቃል አያውቁትም። ከሶስት ትውልድ በላይ ያለ አባት! በአባት ያደገ ይፍረደኝ ነው የሚያሰኘው።
  የጥቁሮችን በደል ብዙዎች እንደመሰላል ለመረማመጃ ተጠቅመውት ወደ አሰቡት ማማ ወጥተዋል። ወደ ረጋጩ መደብ ተሻግረዋል።
  በሃምሳዎቹ የአሜሪካ ኮሚኒስቶች የጥቁሮችን ትግል አሜሪካን ለማጋለጫ ዓይነተኛ መሣሪያ አድርገው ተንቀሳቅሰዋል።
  በስልሳዎቹ ዘመን አይሁዳውያን እና ነጭ ሴቶች ተደራጅተው በቀላሉ ዓለምን የሚያሳምነውን የጥቁሮቹን በደልና ግፍ ከፊት በማስቀደም ከፍተኛ ትግል አቀጣጥለዋል። ይህንን በራሳቸው ለማድረግ ጥቁሮች ገንዘቡ፣ የሚድያ አቅሙም ሆነ ዓለም አቀፍ ግንኙነቱ አልነበራቸውም። ለአናሶች መብት በሚል ብዙ ሕጎችን አስቀይረው ብዙ በሮችን አስከፍተው እድላቸውን ብርሃን አድርገዋል። የተረማመዱበት መሰላል ግን ተጥሎ እዚያው መሬት ላይ እንደወደቀ ቀርቷል።
  ዛሬም ሌሎች ያንን ምቹ መሰላል ዘርግተው ወዳለሙት ማማ ለመሻገሪያ አንስተውታል። ዲሞክራቶች፣ ሶዶማውያን፣ ሌሎችም ያልታወቁ በስፋት ተቀላቅለው ይታያሉ። ረጋግጠውት ከተሻገሩ በኋላ ይጥሉታል ወይስ ይስቡታል የሚለውን አብረን “የምናይ ይሆናል”።
  በጥቁሮች ላይ የሚነዛው ሰፊ ፕሮፓጋንዳ እንኳን የዘረኝነት ጭቆናን ባሕርዮች በውል ለማያውቅ እንግዳ ይቅርና እንደ ፍልስጥኤም ከተቀጠቀጠ ሕዝብ የሚመጡትን እንኳን የሚያስት ነው። በግሌ ከእንደዚህ ዓይነት ማሕበረሰብ የወጡ የአፍሪካን አሜሪካን በደል ግን ፍጹም የማይቆጠቁጣቸው ጨርሶም የማይታያቸው ብዙዎች አጋጥመውኛል። አልፈውም በራሳቸው ላይ ያለው ጭቆናን ያልተገባ በጥቁሮች ላይ ግን የሚደረገውን ግን የተገባ እና እንዲያውም የሚያንሳቸው አድርገው የሚያዩም አሉ። እንግዲህ ከግፉም በላይ የሚያመው ዱላ ይሄኛው እንደሚሆን አያጠራጥርም።
  እስኪ ምዕራባውያን በወኪሎቻቸው ሹምባሾች በሰላሳ ዓመት ብቻ ምን ያህል ጥላቻ ባንድ የኢትዮጵያ ዘውግ ላይ ከዳር እዳር እንዳሰራጩ እናስተውልና በአራት መቶ ዓመታት ባርነት በተያዙ አፍሪካን አሜሪካን ላይ በቀጥታ በእጃቸው የሠሩትን እንገምት። ጥላቻው፣ አለማዘኑ፣ ግዴለሽነቱ፣ እንዲሁ አልመጣም። የሠሩትን በደል ለማጠፋፊያ፣ ያዋቀሩትን የግፍ ሥርዓት ለማስቀጠያ በጭቆና እና በዘረፋ ከሚገኘው የደም ገንዘብ ያለመታከት እና ያለመሰሰት ለፕሮፓጋንዳ፣ ለመሸፋፈኛ እና ለማሳመኛ በትጋት አውለውታል።

 7. በጣም አሪፍ ጽሁፍ ነው።
  አንድ የተዘነጋ ነገር ቢኖር ጥቁሮች ራሳቸውን በራሳቸው እያጠፉ፤ እየጨረሱ ነጮችን ለመወንጀል መሮጣቸው ነው። ልጅ በማስወረድ ጥቁሮች ትልቁን ድርሻ ይወስዳሉ። ባለፉት 40 ዓመታት ብቻ እስክ 20 ሚሊየን ጥቁር ነፍሶች ጠፍቷል ተብሎ ይገመታል። ለዚህም በዋናነት Planned Parenthood የሚባለው የማስወረጃ ተቋም አገልግሎቱን ጥቁሮች በሚበዙበት አካባቢ በመክፈት ትልቅ ሚና ይጫወታል። ስለ Planned Parenthood አመሰራረትና ማን እንደመሰረተው እና ዋና አላማው ምን እንደሆነ ላየና ላነበበ ስራቸውን በጣም እያሳኩ መሆኑንና የዴሞክራት ፓርቲም ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚሰጠው ይረዳል።
  ዛሬ 13% ከመሆን ከ15 እስከ 20% በሆኑ ነበር።
  ሌላውን ከመወንጀል መጀመሪያ ራስን መጠየቅ ያስፈልጋል።

  • Until Derg came to power Ethiopians went to USA only to learn in schools, after graduation they all went back to Ethiopia. After Derg came to power Ethiopians started living In USA for fear of prosecution which was the start of the Ethiopian-Americam identity.

   In USA Ethiopian Americans had been given privileges which other black people had not been getting , most Ethiopians in USA do not experience racism as other black people had been experiencing racism all their lives , most other black people had been developing skills to protect themselves from racism but Ethiopians had not been developing these skills which is highly concerning.

   In USA Ethiopians had been instrumental to defeat worldwide communism , then Ethiopians had been used to side with the international fight war against terrorism so most Ethiopians in USA did not feel the problem yet but soon they will feel it same as other blacks feel it , they might even feel it worse than the other blacks because most Ethiopian Americans got black skin not knowing that they are given especial treatment since the Ethiopian Americans were needed to side with USA to fight the interrnationsl communism and war against terror, once they got no use in these endeavors then they might suffer the rascism as other black people do, now it is evident Ethiopia itself is a breeding ground of terrorism so Ethiopians are surely loosing any especial treatment as Donald Trump proposed cutting aid .

   Plus most blacks are being released from prisons getting jobs the “foreigners” had been monopolizing

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.