እንደ እየሩስአሌም እንደ አክሱም ጽዮን… – አስቻለው ከበደ አበበ

የሰው ልጅ እጥቁሩ የሰማይ ሰሌዳ ላይ የተለያየ ቅርጽ ሰርተው የተደረደሩትን ክዋክብት በመመልከት ዘመኑን ሲዋጅና እጣፋንታውን ለመተንበይ ሲሞክር ዘመናት አልፈዋል፡፡ ከአውደ ነገስቱ፤ፉካሬ ክዋክብት እስከ ስነፈለክ ጥናት ያሉ ሁሉ የሰው ልጅ እራሱን ለማኖርና ህልውናውን ለማረጋገጥ የፈጠራቸው የባህል ዘርፎች ናቸው፡፡

crኮኮብ ቆጣሪዎች(Astrologers) የሰው ልጅ እጣ ፋንታ ሁሉ በከዋክብት እንቅሰቃሴ ይወሰናል ብለው ያምናሉ፡፡ ጥንታዊው ፍልስፍና በላይ በሰማይ የሚሆነው ሁሉ በምድርም ህልው ይሆናል (As above, so below) እንደሚለው ሁሉ፣ ዕጣ ፋንታችን-እድል ተርታችንን የክዋክብቱን አቀማመጥ ተመልክተን ማወቅ እንችላለን የሚሉ ጥቂት አይደሉም፡፡

ለእንደዚህ ላለው አስተሳሰብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃም የሚያቀርቡ ፀሐፊዎች ብዙ ናቸው፡፡ ክርስቶስ ሲወለድ ስበአ ሰገል(The three magi) በኮኮብ መመራትን ምሳሌ አድረገው ይጠቅሳሉ፡፡ ምን ይሄ ብቻ፣ ከመጽሐፈ መሳፍንት፤ የነብይት ዲቦራ ምስጋና፤

ክዋክብት ከሰማይ ተዋጉ

በአካሄዳቸውም ከሲሦራ ጋር ተዋጉ፡፡

የሚለውን ጠቅሰው፣ ለጦርነት ለመውጣት ፉካሬ ክዋክብቱን ማንበብ ግድ ይለናል ይላሉ፡፡ ከሐይማኖቱ ጎራ የሆኑት ሌሎቹ ደግሞ፣ እንዲህ አይደለም፣ ለትልልቅ ኩነቶች ክዋክብቱ ምልክት ይሰጣሉ፣ ነገር ግን አውደ ነገስቱ የሰው ፍልስፍና እንጂ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር አብሮ አይሄድም ይሉናል፡፡ ክርሰቶስ የፀሐዮች ፀሐይ በመሆኑ ሰማይና ምድሩ ሁሉ ለእሱ የተገዛ ነውና ከእሱ በቀር ምንም አያሻንም የሚለው ክፍልም ብዙ ነው፡፡ በአብርሐምውያን እምነቶች ማለትም፣ አይሁድ፣ ክርስትናና እስልምና ሐይማኖቶች ውስጥ እንደየእምነታቸው ኮኮብ ቆጠራን የሚያወግዙ አሉ፡፡ ተሞልሏዊ( Mystic) የሆኑ ግን ሰማያዊ ምልክቶችን አጽንኦት ሰጥተው የሚከታተሉ ናቸው፡፡

ከመካከለኛው ዘመን በኋላ ካባላውና አልኬሚው ውስጥ የነበረው ክዋክብትን ማንበብ ወደ ጂኦደሲ- ስነፈለክ(Geodetic Astronomi) ጥናት ሲቀየር፣ ኮኮብ ቆጠራን እንደ አጉል እምነት የሚቆጥሩ በምክንያተዊነትና በተጠየቅ የሚያምኑ ሰዎች እየተበራከቱ መጥተዋል፡፡ በነገራችን ላይ ካባላ የህብሪው ቃል ሲሆን ትረጓሜው ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ የተቀበልነው ማለት ነው፡፡ ልክ እንደ አማርኛው መቀበል ማለት ነው፡፡ ካባለው የሚከተለውና ነገሮችን የሚያመሰጥርበት የህይወት ዛፍ ምስል( Sefirot) አለው፡፡

ሳይንስ ሰማያዊ አካላት(Celestial bodies) በሰው ልጅ ፊሶሎጂ የውስጥ አካል አሰራር ላይ በአካሄዳቸው ለውጥ ሊያሰከትሉ እንደሚችሉ ያምናል፡፡ የሰው ልጅ ትክክለኛ ተክለ ሰውነት እንዲኖረው ከፀሐይ የሚያገኘው ቫይታሚን ዲ ያሰፈልገዋል፡፡ ከፀሐይ የሚመጡ የጨረር አይነቶችም በሰው አካል ላይ ሊያደርሱ የሚችሉት ጉዳት አለ፡፡ ይህንን የሳይንስ ቀዳዳ ተጠቅመው የባህር መዕበል የሚነሳው በጨረቃ ስበት ምክነያት ስለሆነ የሰው ልጅ በአማካኝ ሰልሳ በመቶ አካሉ ውሃ በመሆኑ፣ በተለይም የውስጥ ብልቶቻችን ማለትም ልብ፣ሳንባ፣ኩላሊት፣አዕምሯችን… ከ70- 85 % ውሃ በመሆናቸው ፣ የክዋክብት አካሄድና አቀማመጥ ባህሪያችንና ዕጣ ፋንታችን ላይ ተጽእኖ ያደርጋል ሲሉ የሚሞግቱ አሉ፡፡

 

ወደ ዋናው ነገሬ ስመለስ ይህን ያክል የተንደረድረኩት ሰኔ 14፣2012 ዓ.ም. ሰለሚከሰተው የፀሐይ ግርዶሽ ጥቂት ለማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ነገስታቱና ካህናቱ በዘመናቸው በሰማይ ላይ ይከሰቱ የነበሩ ምልክቶችን ሁሉ ዘግበው አስቀምጠዋል፡፡ ራቅ ያለውን ትቼ በሪቻርድ ፓንክረስት ተሰብስቦ በኢትጵዮጵያ ጥናት ኢንስቲቱዩት ከቀረበ ጽሑፍ ያገኘሁትን ላካፍላችሁ፡፡

ከ መቶ ሀምሳ አመት በፊት ኢትዮጵያን ለማዘመን የቻሉትን ያህል የሞከሩት አፄ ቴውድሮስ ነበሩ፡፡ በግዜያቸው አሰገድደው መድፍ ለማስራት ካሰሯቸው ፈረንጆች ማስታውሻ የምናነበው አፄው ስለ ሰነፈለካት ለማውቅ ከፍተኛ ጉጉት እንደ ነበራቸውና አዘውትረው ፈረንጆቹን ይጠይቁ እንደነበር ነው፡፡በእሳቸው ዘመን አውሮፓውያን የደረሱበት የስነፈለክ ጥናትን(Astronomy)  የማወቅ ጉጉት ነበራቸው፡፡

በሸዋው ንጉስ ሣህለስላሴ ዘመን 1834ዓ.ም. ከጥምቀት በዓል በኋላ ኢትዬጵያ ውጥ የጨረቃ ግርዶሽ ተከስቶ ነበር፡፡ በወቅቱ አንኮበር ከተማ ላይ የነበረውን ስሜት ካፒቴን ሃሪስ የተባለ እንግሊዛዊ በጥሩ ሁኔታ ዘግቦታል፡፡ ህዝቡ፤ ወንዱ፣ ሴቱና ቀሳውስቱ በየጎዳናውና ቤተክርሰቲያኑ ተሰብስቦ ይህንን ምልክት ተከትሎ ከሚመጣው በሽታ፣ርሃብና ጦርነት ፈጣሪያቸው እንዲጠብቃቸው በአማርኛና ኦሮሚኛ በከፍተኛ ጩኸት ፀሎት አድርገዋል፡፡

ንጉሱ ግርዶሹን እንደ መጥፎ ምልክት ነበር የተመለከቱት፡፡ ለመኳንቶቻቸውም የትግሬው ስባጋድስ የተገደሉትና የ ወሎው ራስ አሊ የተሸነፉት እንዲህ አይነት ምልክት በሰማይ ከታየ በኋላ መሆኑን ገልጸው፣ የቤተመንግሰታቸውን የአንጥረኞች አለቃ እራሱን ለሎጋሊዚም ሰንጠረዥና ሰማያትን መንበብ ሚያስችለው እውቀት ለማወቅ እንንዲተጋ ትእዛዝ ሰጡት፡፡ በግዜው ንጉሱ በህክምና ላይ የደርጉ የነበረውን ጥናት ወደ ስነፈለክ አዙረውት ነበር፡፡

በአፄ ዮሃንስ 4ኛው ዘመነ መንግስት 1874 ዓ.ም. የሚያበራ ኮኮብ(ኮሜት) በመታየቱ ደስ ብሎአቸው ስለነበር የወሎን ክፍለሀገር ዋና ከተማ ደሴ ብለው ጠሩት፡፡ በዚያን ግዜ የእሳቸው ልጅ አራያ ስላሴ ከነጉስ ምንሊክ ልጅ ዘውዲቱ ጋር ተጋብቶ ስለ ነበር እንደ ጥሩ ምልክት ነበር የተወሰደው፡፡በትግራይ የሚነገር አንድ ታሪክ አለ፡፡ በእሳቸው ዘመን የጨረቃ ግርዶሸ ተከስቶ ጨረቃ ደም መሰለች፡፡ ይኼኔ ነጉሱ ተረበብሸው ሕዝቡ ሁሉ እንዲጸልይ ለአጋፋሪ ኪዳኑ መልእክት እንዲያስተላልፍ ይነግሩታል፡፡ አጋፋሪ ኪዳኑም መልእክቱን ሳያስተላለፉ ይቀራሉ፡፡በኋላ አፄ ዮሃንስ ተቆጥተው ወደ አጋፋሪው ቢሄዱ፤ የእኔ ፀሐይ ንጉስ ዮሃንስ ደህና ከሆኑ ስለ ታመመች ጨረቃ ምን አገባኝ ብለው አሳቋቸው ይባላል፡፡

አፄ ምንሊክ የአያታቸውንና የአፄ ቴውድሮስ 2ኛን  ፈለግ በመከተል እሳቸውን ያገለግል ከነበረውን ከአርመናዊው የሳይንስ ሊቅ ከሪኮር ሆውያን ጋር በመሆን በ108 ሚሊሜትር ባርዶ ቴሌስኮፕ በ1900 ዓ.ም.  ህዳር ወር መጀመሪ ላይ ፕላኔት ሜርኩሪን ማየት ችለው ነበር፡፡ በወቅቱ የፈረንሳይ የስነፈለክ ፕሬዚዳንት የነበረው ቻሚሌ ፍላማሪዎን መሐበሩ በረጅም ግዜ የሚከሰተውን የዚህን ክስተት ዘገባ ለሳይንስና ሥነጥበብ ፍላጎት ከነበራቸው ንጉስ በማገኘቱ ንጉሱን በማድነቅ በአለም ላይ ክስተቱን ያዩ ብቸኛው ንጉስ በማለት አድንቆ ንግግር አድርጓል፡፡

ከስድስት ወራት በኋላ አፄ ምኒልክ ለፈረንሳይ ስነፈለክ ምርምር ማህበር ባቀረቡት ማመልከቻ መሰረት 4730ኛ አባል ሆነዋል፡፡ ለመሐበሩም የአንድ ሺህ ፍራንክ ስጦታ አበርክተዋል፡፡

ሰኔ 14፣ 2012ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሰማይ ላይ የሚሆነው አኑላር የፀሐይ ግርዶሽ  ተከትሎ የሚመጣ ነገር ስለሚኖር ግዜያችንን ልንዋጅበት ይገባል? ለኢትዮጵያውያንስ ትርጉሙ ምን ሊሆን ይችላል? እንዲህ ያሉ ጥያቄዎችን ስናነሳ የታሪክ መዛግብትን ማገላበጥ የግድ የሚል ነው፡፡

በጥንት ግዜ ቻይና ሀገር ውስጥ ቀን ሆኖ ሳለ ፀሐይ ትጨልማለች፡፡ በሁኔታው የተደናገጠው ንጉሰ ፀሐይን ድራጎን የተባለ አውሬ እየዋጣት ስለሆነ ህዝቡ የሚነኮሻኮሽ ነገር ሁሉ ይዞ ወጥቶ ድራጎኑን እንዲዋጋ አዋጅ ያስነግራል፡፡ ከዚያም ፀሐይ ወደ መንበሯ ተመለሰች፡፡ ንጉሱ የቤተ መንግሰቱ ኮኮብ ቆጣሪዎች የነበሩትን ሆ እና ሂስን ጠርቶ ይህ ነገር እንደሚከሰት አስቀድመው ባለማስጠንቀቃቸው አንገታቸውን ተቀልቶ እንዲሞቱ አደረጋቸው፡፡

ከመካከለኛው አፍሪካ ከኮነጎ ተነስቶ እስከ ቻይና ድረሰ ሄዶ ሰላማዊ ውቅያኖስ ውስጥ የሚያበቃው የፀሐይ ግረዶሹ አካሄዱ ከምዕራብ ወደ ምስራቅ ወደ ላይ ከርቭ ሰርቶ ነው፡፡ ኢትዮጵያንም በሚያቋርጥበት ግዜ ጉዞው ከደቡብ -ምዕራብ ተነሰቶ ወደ ሰሜን-ምስራቅ በመጓዝ ነው፡፡

በዚህ ጉዞ ላይ የፀሐይ ግርዶሹ እሳታማ ቀለበት ሰርቶ ከሚታይባቸው ጥቂት የኢትዮጵያ ቦታዎች አንዱ ላሊበላ ነው፡፡ ይህን ክስተት ከኮረና በሽታ ጋር አያይዘው የሚተርኩ የውጭና የሃገራችን ተመራማሪዎች አሉ፡፡ አኔ ደግሞ ሃሳቤን ለማካፈል ከውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ አሰራረ ጀምሬ መመርመርን አሻሁ፡፡

ስለ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት አሰራርና የተሰሩበት ዘመን የተለያየ አመለካከት አለ፡፡ ውቅር አብያተ ክርሰቲያናቱ ከክርስቶስ ልደት በፊት በሚያስደንቁ የሰማይ ኃያላት የተሰሩ ናቸው፡፡በኋላ ላሊበላ በዘመኑ የለበሱትን አፈር አራግፎ ቁጥቋጦውን መንጥሮ ገለጣቸው ብለው የጻፉ አሉ፡፡ ኢምጋርድ ቢድር ላሊበላ በሚለው መጽሐፏ ከቄሶቹ ሰማሁት የለቸውን መረጃ ይዛ ተመሳሳይ አመለካከት አንፀባርቃለች፡፡

ሌላው የውጭ ጸሐፊ ፐሮፌሰር ዴቪድ ፊሊፐሰን ሲሆን፣ የውቅሮቹን ሰተራከቸር ምህንድስና ተከትሎ ከ7ኛው ክ/ዘመን ጀምሮ እስከ 13ኛው ክ/ዘመን ድረስ የተሰሩ ናቸው የሚል ጥናት አቅረቧል፡፡ ሌለኞቹ ወገኖች ደግሞ፣ በላሊበላ ዘመን ኢትዮጵያውያን ወደ ርስት ምድራቸው እየሩሳሌም( ዴርሱልጣን) የደርጉ የነበሩት ሐይማኖታዊ ጉዞ በመስቀል ጦርነት(Crusade) ምክንያት ተስተጓጉሎ ስለነበር፤ ንጉስ ላሊበላ ዳግማዊት እየሩሳሌምን ለመፍጠር አብያተ ክርሰቲያናቱን  ላሊበላ ላይ እዚሁ ኢትዮጵያ ውስጥ አነጻቸው የሚሉ ናቸው፡፡

በውቅር አብያተ ክርሰቲያናቱ ላይ ያሉ ክርስቲያናዊ ምልክቶችን ዋቢ በማድረግ፣ አብያተ ክርስቲያናቱን አቋርጦ የሚሄደውን የዮርዳኖስ ወንዝ ጨምሮ፣በተጨማሪም ድርሳናቱንና ገድላቱን በማጣቀስ ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ ከላሊበላ ዘመን በኋላ የተወቀሩ ናቸው የሚለው ሃሳብ ሚዛን ደፍቶ ገዢ ሆኗል ይተረካል፡፡

የተለያዩ ተመራማሪዎችን ጽሑፍ አንብቤ በሶስት መጽሓፎቼ ላይ ስለ ላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት፣ የራሴን አመለካከት ላለፉት ሃያ አንድ አመታት ለህዝብ ሳቀርብ ቆይቻለሁ፡፡ በተደጋጋሚ ላሊበላን በጎበኘሁበት ግዜ ካገኘኋቸው አባቶች ያገኘሁት መረጃም ያረጋገጠልኝም ነገር ቢኖር ያሾለቅኩበት መነጽሬ ትክክለኛነት መሬት የያዘ መሆኑን ነው፡፡

ልክ ሰኔ 14፣2012 ዓ.ም. የሚሆነው የፀሐይ ግርዶሽ መንገድ፣ ኢትዮጵያን በተመለከተ፣ በደቡብ- ምዕራብ ኢትዮጵያ ጀምሮ ሰሜን- ምስራቅ ኢትዮጵያ ላይ ያበቃል፡፡ ይህ ፍኖት ሙሉ በሙሉ አስራ አንዱን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ለሁለት ከደቡብ-ምዕራብ ወደ ሰሜን-ምስራቅ አቋርጦ የሚሄደውን ዬዮርዳኖስ ወንዝ ከሰማይ አመላክቶ በላዩ ላይ ተደርቦ የሚያልፍ ባይሆንም፣  በቤተ ግዮርጊስና ዮርዳኖስ ወንዝ መጀመሪያ አካባቢ አቋርጦት ያልፋል፡፡ ስካይ ማፑን መሬት ካለው ሁኔታ ጋር አነፃጽሮ ማየትም ግን ያስፈልጋል፡፡

በላሊበላ ጉብኝቴ ግዜ ቤተጊዮርጊስ ያገኘኋቸው ቄስ ይዘው የወጡትን ክብ መስቀል አሰታውሳለሁ፡፡ ይህ የቤተ ጊዮርጊስ ምድራዊ ፕላን( Floor plan) ነው ብለው ነግረውኛል፡፡ ቤተ ጊዮርጊስ በመስቀል ቅርጽ የተሰራና በአራቱም የመስቀል ጎን ክፍሎች ላይ ሶስተት መስኮቶች አሉት፡፡ ቄሱ አሰራሁለት ጉጥ ያለውን ክብ መስቀል የቤተ ክርስቲያኑ ወለል ፕላን ነው ሲሉ ገለጻ ሰጥተውኛል፡፡ ላሊብላ የሰራቸውን ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ዲዛይን፣ ተመርዞ ለሞት በተቃረበበት ግዜ ወደ ሰማይ ነፍሱ ተነጥቃ ስለነበር ንድፉን ከፈጣሪ ተቀብሎ መምጣቱን ገድሉ ያትታል፡፡

የአስራ ሁለት ቁጥር ጥያቄን ከእየሩሳሌም ምስጢር ጋር አገናኝቼ 1991 እና 1995 ዓ.ም. ላይ መጽሐፍት ጽፌ ስለነበር የቄሱ ገለፃ ግምቴን ያረጋገጠልኝ ነበር፡፡ ላሊበላን በተመለከተ ሁል ግዜ አዕምሮዬን ያዝ አድርጎ ጥያቄ የሚያጭርብኝ  ነገር ቢኖር አስራ ሁለት ቁጥር ነው፡፡

የዮሴፍ ህልም( ዘፍ ም.37 ቁ. 9-10፤ እራሱን ሲቀር አስራ አንድ ኮኮቦች( ወንድሞቹ)፣ ፀሐይ( አባቱ)ና ጨረቃ(እናቱ) የሰገዱለት ምስጢር፡፡ ይህም በግብጽ ስደት ግዜ የተፈፀመ ነው፡፡ እንዲሁም ሚካ. ም 4 ቁ 9-10 ታላቅ አንደምታ ያለው፤ የባቢሎንን ስደት የሚያስታውሰን ሲሆን አስራሁለት ቁጥር  በአስራሁለት ነገድ፣ በአስራሁለት ክዋክብት፤ በአስራ ሁለት ዕንቁዎች የሚመሳጠር በብሉይ ኪዳንም ሆነ በአዲስ ኪዳን ምስጢራዊና መንፈሳዊ የሆነ ቁጥር ነው፡፡

ዋናው ግን በራዕየ ዮሐንስ ምዕራፍ 12 የተነገረው ነው፡፡ የአይሁድ እምነት ተከታይ የነበሩት በቁምራን ገዳም ገድመው የነበሩት እሴይዋውያንም ተመሳሳይ መገለጥ እንደነበራቸው እነሱ ጽፈውት የነበረ ጽሑፍ ነው ተብሎ ወደ እንግሊዘኛ የተተረጎመ ጽሑፍ አንብቤለሁ፡፡ ዮሃንስ ራዕይ ም. 12፤

ታላቅ ምልክት በሰማይ ታየ፡፡ ፀሐይን ተጎናጽፋ፣ ጨረቃን የተረገጠች በራሷም ላይ አስራ ሁለት ክዋክብት አክሊል የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች…

ሴቲቱ አህዛብን በብረት በትር ይገዛቸው ዘንድ ያለውን ወንድ ልጅ ወለደች፡፡ ልጁም ወደ    እግዚአብሔር ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ፡፡ ሌላም ምልክት ታላቅ ቀይ ዘንዶም የተወለደውን ልጅ ሊበላ በሴቲቱ ፊት ቆመ፡፡ እግዚአብሔርም ሺህ ሁለት መቶ ስልሳ ቀን በበርሃ እንድትቀመጥ የታላቁ የንስር ክንፍ ለሴቲቱ ሰጥቶ አበረራት፡፡ በዚያም የሚመግባት ከእግዚአብሔር ዘንድ ተዘጋጅተ ነበር፡፡…እባቡም ሴቲቱን በወንዝ እንድትወሰድ ሊያደርግ ወንዝ የሚያክልን ውኃ ከአፉ በስተ ኋለዋ አፈሰሰ፡፡ ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት፡፡ ምድሪቱም አፉዋን ከፍታ ዘንዶው ከአፉ ያፈሰሰውን ወንዝ ዋጠችው፡፡

ይህንን ጥቅስ ከላይ ከተጠቀሱት ሁለት ጥቅሶች ጋር አያይዘው የሚተረጉሙ ሊቃውንት በቀጥታ ለቅድስት ድንግል ማርያም ነው የሚመለከተው ብለው፣ ልጇን ክርስቶስን ይዛ ካደረገችው ሽሽት ጉዞ ጋር በማመሳጠር ይተረጉሙታል፡፡ የዚህ አንደምታ በመስቀሉ ዙሪያ ሁሌ የሚታወሱትን አስራ ሁለቱን ሐዋርያትንና ክርስቶስንም ያመሳጥራል ይላሉ፡፡

በላሊበላ ጎሎጎታ የሚገኘው የላሊበላ መጾር መስቀል በሁለት በተያያዙ ክበበ ፀዳል ውስጥ ሁለት መስቀሎችን ይዞ፣ ከላይ ያዘረዘሩ አስራ ሁለት ክዋክብትን በመመሰል ተቀርጾ፣ ከጎኑና ከጎኑ ሶስት-ሶስት ክንፎችን በድምሩ ስድስት ክነፎችን በመያዝ የተሰራ መስቀለወ ነው፡፡

ይህ መስቀል ዮሃንስ ራዕይ ም. 12 የተገለጠውን ሰማያዊ ትእይንት በቀጥታ ገላጭ ነው፡፡ ሁለቱ ክበበ ፀዳሎች ፀሐይና ጨረቃን ሲወክሉ፣ ያዘረዘሩት አስራሁለት ቅርንጫፎች ደግሞ አስራሁለቱ ክዋክብት ናቸው፡፡ ስድስቱ ክንፎች የታለቁ ንስር(ሱራፌል) ክንፎች ሆነው ይተረጎማሉ፡፡ በላሊበላ የሚገኙ መስቀሎች ብዙ ሚስጥራትነ በውስጣቸው የያዙ ናቸው፡፡

እኔ እራሴን እጠይቅ የነበረው፣ ላሊበላ አሰራሁለት ቁጥር በመጽሐፍ ቅዱስ ትርክት ውስጥ ታላቅ ሚና እንደሚጫወት እያወቀ ለምን በውስጥ ለውስጥ ዋሻ መንግድ የሚገናኙትን አስራ አንድ ውቅር ቤተ ክርስቲያናት ብቻ ወቀረ የሚል ነበር፡፡

አሰራ አንዱን ውቅር አብያተ ክርሰቲያናት ለሁለት ከፍሎ የሚያለፍ ላሊብላ የስራው የዮርዳኖሰ ወንዝ አለ፡፡ ከወንዙ ሰሜን -ምዕራብ አምስቱን ውቅሮች ስናገኝ፣ በደቡብ ምዕራብ በኩል ሌሎቹ አምስቱን እናገኛልን፡፡ ቤተጊዮርጊስ ወደ ደቡብ ፈንጠር ብሎ ነው የሚገኘው፡፡ ከቤተ ጊዮርጊስ በስተምስራቅ በዮርዳኖ ወንዝ ውስጥ አንድ ውቅር መስቀል ቆሞ ይገኛል፡፡

ክርስቶስ በተጠመቀበት  ዮርዳኖስ ወንዝ ውስጥም መስቀል አድርጎ መሳል ከበባዛነታይን ዘመን ጀምሮ የነበረ የምስራቃውያኑ መንፈሳዊ የአሳሳል ጥበብ ባህል ነበር፡፡ ከመረመርነው ግን ይህን ውቅር መስቀል አንደ አንድ ውቅር ስራ በመቁጠር አስራሁለተኛ ልናደርገው እንችላለን፡፡

ናሳ የለቀቀውን የፀሐይ ግርዶሹ ጎግል ማፕ ትክክለኛነት መቶ በመቶ እርግጠኛ እንዳለሆነ መግለጫ ቢሰጥበትም፤ እሳታማ ቀለበት የጠቆረች ጨረቃን ይዛ ሰኔ 14  የምታልፈው  በመስቀል ቅርጽ በተሰራው ቤተ ጊዮርጊስና በውቅር መስቀሉ አናት ላይ  አቋርጦ ነው፡፡ ግንቦት 28፣ 2012 ዓ.ም.  የነበረውን የጨረቃ ግርዶሽም አንርሳ፡፡ ሌላ የጨረቃ ግርዶሽ  ሰኔ 28፣ 2012 ዓ.ም. ይሆናል፡፡

በስነፈለክና ፉካሬ ክዋክብት ላይ ጥናት የሚያደርጉ ተመራማሪዎች በዮሃንስ ራዕይ ም. 12 ላይ የተገለጠው ሰማያዊ ምልክት መስከረም11፣ 2010 ተከስቷል ይላሉ፡፡ በፉካሬ ክዋክብቱ ሴቷ ቪርጎ  በእግሯ ስር ጨረቃን አናቷ ላይ ፀሐይን ይዛ አስራሁለት ክዋክብትን ከአንበሳው አውደ ነገስት በመያዝ በሰማይ ሰሌዳ ላይ ወጥታለች፡፡ ጁፒተር ሆዷ ውስጥ ቆይቶ በእግሯ ስር ሾልኮ ወጥቷል ስለዚህም የራዕዩ ገለጻ ተፈጽሟል ይላሉ፡፡

የዚህ አይነቱ የክዋክብት ድርድር በየሁለት መቶ አረባ አመት የሚከሰት ነው፡፡ የመጨረሻው ዘመን መገለጫ አድርገው የወሰዱትም ነበሩ፡፡ ነገር ግን የነበረው የክዋክብት አቀማመጥ ዮሃንስ ያየው ነው ብለን ብንወስደው እንኳን፣ስለ ዘንዶውና ወንዙ እንዲሁም የንስር ክንፎቹ ክዋክብቱ የሆነ የሚመስል ነገር ማለት አለባቸው፡፡

እሺ ነገራቸውን ከኢትዮጵያ ሰማይ አንጻር አይተን፣ እሳታማው ቀለበት እንደጥንቱ ባህል ፀሐይ በበራሪው እባብ ስትዋጥ ተከሰተ እንበል፣ወንዙስ? ወንዙንም ከኮንጎ እስከ መጨረሻው ሰላማዊ ውቂያኖስ ድረስ ያለው የግርዶሹ መሰመር ነው ብለን እንውሰድ፣ የተወለደውስ ንጉስ የት አለ?

እኒህን ጥያቄዎች እራሴን ከጠየቅኩ በኋላ ወደ ላሊበላ ልመለስ፡፡ በላሊበላ ያለው ዬርዳኖስ ወንዝ ለኔ ሚልክ ዌይ በመባል የሚታወቀውን የሰማይ ዥረት ተምሳሌት አድርጌ ነው የማየው፡፡ ውቅር መስቀሉም የደቡቡ መሰቀል(The southern cross)  ፉካሬ ክዋክብት ነው፡፡

ከላይ የጠየቅኳቸውን ጥያቄዎች ይዤ ከላሊበላው የሰማይ ጅረት ምሳሌ ጋር ያላቻም ይሁን ባልተቀደሰ ጋብቻ ሃሳቦቹን አጋብቼ የዮሃንስ ራዕይ ም. 12 እስከ ሴቲቱ በወንዝ እንድትወሰድ ውኃ ከአፉ አፈሰሰ እስከሚለው ምልክት ድረስ ተፈጽሟል ብዬ ባምንም እንኳን የንስሩን ክንፎች ለማየት እናፍቃለሁ፡፡ ያ ከሆነ እንሆ አዲስ ዘመን ለሁላችን! ምን አልባት ከሰው ልጅ ጋር እስከ ዛሬ ድብብቆሽ የመሰለ ጨዋታ ሲጫወቱ የነበሩት የሰማይ ኀያላት በቅርቡ ይገለጹ ይሆንን?

መቼም ይህ ምልክት አምና ሰኔ14 ሆኖ ቢሆን ኖሮ ከሶስቶ ጀነራሎችና ከሶስቱ የአማራ ክልል ከፍተኘ አመራሮች ሞት ጋር ይያያዝ ነበር፡፡ መቼም ትንቢት ወደኋላ አይሄድምና፣ ሁል ግዜ ነገርን ቀድሞ ይመጣል በሚለው እሳቤ እኒህ ጉምቱ የለውጥ ተወርዋሪ ኮኮቦችን ያገደለውን ሰየጣናዊ ዐይን ረግሜ ልዘክራቸው፡፡

ነገሩን ካነሳሁት ዘንደ፣ አንድ ለመንገድ ብዬ ላብቃ፡፡ ሁለት የበቁ በፍቅር የሚኖሩ ባህታውያን ነበሩ አሉ፡፡ ታዲያ አንደኛቸው አንድ አይና ሲሆኑ ሌላኛው ደግሞ አንድ እግራቸው የተቆረጠ ነበር፡፡ ሴይጣን በፍቅራቸው ቀንቶ ሚዳቆ መሰሎ ታያቸው፡፡ የሰጣቸው እይታ ግን የተለያየ ነበር፡፡ ለአንድ አይናው እግረ ቆራጣ ፣ ለቆራጣው ደግሞ አንደ አይና ሚዳቆ ሆኖ ታያቸው፡፡

ታዲያ በለአንድ አግሩ ባህታዊ ለጓደኛቸው አየሃት ያቺን አንድ አይና ሚዳቆ ሲሉ ጠየቁ፡፡ ሌላኛውም መልሰው እግረ ቆራጣዋን ማለትህ ነው ሲሉ መለሱ፡፡ አንዲ ነች እንዲያ ነች ብለው ሲከራከሩ ወደ ጠብ አመሩና አረፉት፡፡ ባህታውያኑ ጠባቸውን መርምረው ሴጣናዊ አይታቸውን ኋላ ላይ ደረሱበት፡፡ እኛ ግን ማለቴም እትዮጵያውያን ይህን የሴይጣን መነጥር ከአይናችን ላይ አውልቀን መጣል ተሳነንሳ፡፡እኸኸ እኸኸይ…  ብቻ ዘፋኟ እንዳለችው፤

እንደ እየሩሳሌም እንደ አክሱም ጽዮን

ተሳልሜው መጣሁ አይንና ጥርሱን፡፡

አይንና ጥርሱንስ በግዜ ሸኘንው

ሽንጡ ማደሪያ አጥቶ ሲጓዝ አገኘንው፡፡

እኸኸ እኸኸይ፣ እኸኸ እኸኸይ…

 

አስቻለው ከበደ አበበ

ሜትሮ ቫንኮቨር፣ ካናዳ

 

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.