እባክህ ዓባይ ሆይ! – በላይነህ አባተ

Nile

እባክህ ዓባይ ሆይ መጣፉን መርምረው፣
ድሮ ወደ ካይሮ ፍሰስ የተባልከው፣
ሙሴን ተፈርኦን ለማዳን ብቻ ነው፡፡

ዛሬ እናት እያስራብክ ባድ የምትቀልበው፣
በየትኛው አምላክ ነቢይ ታዝዘህ ነው?

እባክህ ዓባይ ሆይ መንገድህን ቀይረው፣
በአንድ ጎዳና ተጓዥ ለጠላት ምቹ ነው፡፡

ሽቅብ ወደ ምስር መንጎዱን ተውና፣
ደጀንን አቋርጠህ ግባ አዲስ አበባ!

እባክህ ዓባይ ሆይ የሕዝብ ጩኸት ስማ፣
እምቦጭ ይህ አድግን ተአስዋን ጣልና፣
እምቢ አልመጣም ብለህ ዙረህ ግባ ጣና!

እባክህ ዓባይ ሆይ ራስህን ፈትሸው፣
የእናት ልብ ሩህሩህ አንጀቷ እንስፍስፍ ነው፣
ትተኻት ስትሄድ ደም እያነባች ነው፡፡

ስትጓዝ የምታድር እንደ አፍቃሪ ኮብላይ፣
ተዶሮ ወጥ ፉሉ ለአፍህ ጣፍጦህ ነወይ?

አፈር ተሸክመህ ብአዴንን መተው፣
በቁሙ የተላ ሙት በድን ሸቶህ ነው?
ወይስ የአማራ ሕዝብ ይሰቃይ ብለህ ነው?

እባክህ ዓባይ ሆይ የሕዝብን ድምጥ ስማው፣
በመሸከም ፋንታ ግንድን እንደ ድሮው፣
ብአዴንን ውጠህ ታገር ውጪ ትፋው፡፡

ቴዎድሮስ ተበላይ እንዳልበቀሉብህ፣
ምኒልክ ሚካኤል እንዳልተሻገሩህ፣
ምን ገላህ ቢቆሽሽ ምን ጊዜ ቢጥልህ፣
አረሙ ብአዴን እንደ እንቦጭ ወረረህ፡፡

እባክህ ዓባይ ሆይ እንደ ልጅ ተመከር፣
ከሀዲ ባንዳውን አስምጠህ ደለል ሥር፣
ተሚያፉጫጭ ፋኖ ስትጫወት እደር፡፡

እባክህ ዓባይ ሆይ አዝዝ አዞዎችን፣
አርበኛን አሻግረው እንዲውጡ ባንዳን፡፡

እባክህ ዓባይ ሆይ ተወጣ አደራህን፣
ለአምስት ሺ ዘመን እንዳቆላለፍከን፣
እትፍ እትፍ ብልሀ ድል ንሳ ስይጣንን፣
በአምላክ ልጅነትህ መልሰህ አንድ አርገን፡፡

ወንዞችን ኑ ብለህ ጉንጪ እንዳሳሳምከው፣
በሽሎን ተዴዴሳ እንዳገናኘኸው፣
ጀማን ተበለስ ወንዝ እንዳቀላቀልከው፣
መገጪን ተጉደር እንደ ደባለከው፣
እባክህ ዓባይ ሆይ ሕዝቡን አገናኘው፣
የሰይጣን ማደሪያን ክልልን ደርምሰው፡፡

እባክህ ዓባይ ሆይ የኦሪቱ ግዮን፣
ግርማ ሞገሳችን ደምና ነፍሳችን፣
አንት ሁለተኛ ወንዝ እባክህ ተለመን፣
ፀንተህ ኑር በአገርህ አትልቀቅ ኤደንን፣
የጀግና ተክል አብቅል ነቅለህ ብአዴንን!
ድልድይ ስሩብኝ በል ጠርገህ ይህ አድግን፣
ሕዝብህን አገናኝ ደርምሰህ ክልልን፡፡

በላይነህ አባተ ([email protected])
ሰኔ ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.