“መንግስት ለመገልበጥ እንደበፊቱ ጋራና ሸንተረር መሄድ አይጠበቅብንም” ንጋቱ ተፈሪ

የወያኔዉ ጌታቸዉ ረዳ (ጌታቸዉ ምላሱ)

woyane “መንግስት ለመገልበጥ እንደበፊቱ ጋራና ሸንተረር መሄድ አይጠበቅብንም”  ንጋቱ ተፈሪ
ከሁለት ዓመታት በፊት መወደቂያቸዉ አስራ አንደኛዉ ሰዓት ላይ  የወያኔን በስብሰናል  ሸተናል በድለናል  የሚል  የማስመሰል ኑዛዜ ሰምተን ነበረ፡፡  በመላዉ ሀገሪቱ  ሰላማዊ ተቃዉሞ በተቀጣጠለበት ወቅት የወያኔ መሪዎች  አባይ ጸሃዬ ስዩም መስፍን  ጌታቸዉ ረዳ ይመጥነናል በሚሉት ቋንቋ ማስፈራሪያ  ተናገሩ፡፡ጭድና እሳት  ተጣመሩ ፤ ልክ እናስገባቸዋለን ፤የያዛቸዉ ሰይጣን እስኪለቃቸዉ ድረስ  እናሳያቸዋለን ወዘተ የሚሉ፡፡ አቅማቸዉ ማንሱን  ትንፋሻቸዉ ማጠሩን ጉልበታቸዉ መድከሙን  ተስፋቸዉ መመንመኑን   የገለጹበት ቋንቋ ነበረ፡፡
ዛሬም   ክሁለት ዓመታት በኃላ ተመሳሳይ  ንግግሮች እያሰሙ ነዉ፡፡ የስዩም መስፍንን  ንግግር የሰማ  በቁጭት ስሜት የእጆቹን መወራጨወት ያየ ፤ የጌታቸዉ ምላሱን  የጦርነት ፉከራና  ፊቱ ላይ የሚታየዉን ተስፋ መቁረጥና ገጽታ መጨማመድ  የተመለከተ ብዙ ትንብት እንዲነገረዉ አይጠብቅም፡፡  ወያኔ ከመሸገበት መቀሌ  ወደመቀበሪያዉ እያዘገመ  የመጨረሻ ኑዛዜ እያሰማ ነዉና፡፡
እጅግ የሚገርመኝና በእድሜም በትምህርትም በማየትም በመስማትም  የወያኔ መሪዎች ያልተማሩት  ነገር ነዉ ፡፡
ወያኔ ከተመሰረተ እነሆ 45 ዓመታት  ተቆጠረ፡፡ ከአርባአምስት ዓመታት  በፊት የነበሩ ወጣቶች የዛሬ አዛዉንቶች ሆነዋል፡፡ከአርባአምስት ዓመታት በፊት የነበረዉን እሳቤ ርዮት ዓለምና ፕሮግራም  የጻፉ ድርጅቱንም የመሰረቱናን የመሩ አሁንም እዛዉ ናቸዉ  ዘመን ሲለዋወጠ እድገት ሲመዘገብ ስዎች ሲወለዱና አርጅተዉ ሲመቱ  ቲክኖሎጅ ሲዳብርና ሃሳብ ሲለዋጥ ወያኔና የወያኔ መሪዎች እሳቤአቸዉና ርዮተዓለም እዛዉ ነዉ፡፡፡
    በ moderate politician ወይም ጥግ ባልያዘ ዘመናዊ ፖሎቲከኝነት የሚታወቁት ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና  የዛሬን አያድርገዉና  ከዘመኑ ጋር  የሚሄደዉን መልካም ሀሳባቸዉን አሸንቀንጥረዉ  በመጣል ኃላቀርና መርዛም  በሆነዉ የጃዋርና በቀለ ገርባ ጎሰኝነት ተጠምቀው በአዲስ ስብእና ብቅ ከማለታቸዉ በፊት  የሚደነቅላቸዉ አባባል ነበረ፡፡ “ወያኔዎች  ከጫካ ዉስጥ ወጡ እንጂ ጫካዉ ከእነርሱ አልወጣም” የሚል ነበረ፡፡  እንዴት ሰዉ መቃብር  እስከሚገባ  እኔ  ብቻ ነኝ የማዉቅላችሁ  እያለ በእርጅና  አይኑን እየሞጨሞጨዉ ከንፈሩ እያንቀጠቀጠዉ  ስልጠኑን ለአዲሱ ትዉልድ ማስርከብ ያቅተዋል፡፡ ዛሬም  የሚያስቡትም የሚናገሩትም የሚፎክሩትም ከአርባአምስት ዓመታት በፊት እዛዉ ጫካ ዉስጥ እያሉ የሚሉትንና የሚያልሙትን ነዉ፡፡ ቢያንስ ከቁምጣና ከሸበጥ ወጥተዉ ባለ ቪላና ቪ8 መኪና ባለቤት እንዲሁም ኢንቭስትርና ሚሊየነር  ሆነዉ በቃን ማለት አለማቻላቸዉ ይገርመኛል፡፡
የጎሰኝነት ፖሎቲካ   መስራች ስብሃት ነጋ ዛሬም ነብይም ጠንቋይም  አዋቂም መስራችም ፈጣሪም  ቀባሪም እኔ ነኝ  ብለዋል፡፡ ካልሰማችሁኝ ህገር ይፈርሳል ምድር ይረክሳል እቶን ይነዳል ይሉናል፡፡ አባይ ጸሃዬ ስዩም መስፍንና   የዘረኝነት በሸታ ያልተላቀቀዉና ከእስሩና ከዉድቀቱ ያልተማረዉ  ስዬ አብርሃ ጨምሮ ዛሬም ወያኔን መንካት የትግራይ ህዝብን መድፈር ነዉ ይሉናል፡፡ አንዳንዴ  ክልሉን የሚመራዉ ማን እንደሆነም ለማወቅ ግራ ያጋባል፡፡የክልሉ መንግስት ሃላፊዎች ቋንቋና  ከበስተኃላ  እየመሩ መሆናቸዉን እየነገሩን ያሉ አዛዉንቶች ንግግር ለየቅል ነዉ፡፡ፍከራ  ቀረሮቶ፤ ማስፈራሪያ ፤ እንጠፋለን፤ ትጠፋላችሁ ትንቢትና ክፉ ምኞት ከእነርሱ አንደበት አይለይም፡፡ኮሚንስቶች ስለሆነ  ሽምግልናና ጸሎት አያዉቁም፡፡ በክፋት የጀመሩትን ትግል  በክፉ መንፈስ ይዝዉ ወደምቃብር ይወርዳሉ፡፡የሚጠብቃቸዉን ስለሚያዉቁ  ጸሎት  ምን አደክመን ባዮች ናቸዉ፡፡
አዲሱን ትዉልድ የምጠይቀዉ ጥያቄ አለ፡፡ ለመሆኑ  ትግራይ ዉስጥ ከእነርሱ ዉጭ አዲሱ ትዉልድ የሃሳብ መካን ነዉ ?  መመራት እንጂ መምራት አይችልም? የህዝብ አመኔታ ማግኘት ተሳናዉ? ወይስ አዛዉንቶቹ ለትግራይ ህዝብ ከሰማየ ሰማያት የወረዱ መለኮታዊ ሥልጥን የተሰጣቸዉ ናቸዉ?   የትግራይ  ወጣት ሃይል  ዘመኑ የእነርሱ መሆኑንና  የ21ኛዉ ክፍለዘመን አስተሳሰብ ከሸማግሌዎቹ የነተበ አዕምሮ ሊፈልቅ እንደማይችል ሊነግራቸዉ አልደፈረም ?  አዛዉንቶቹ  ያደጉበትን የሴራ ፖሎቲካ  እየዘሩ መርዛም  ቅርሻታችዉን እየተፉ እስከለተ ሞታቸዉ ይዝናኑ ብሎ ፈቅድዶላቸዋል? በምንስ ሞራል ነዉ አርባ አምስት ዓመታት በሙሉ ስለአልኖሩበት ዲሞክራሲና ነጻነት እያወሩ  ወደመቃብራቸዉ የሚጓዙት?
የዘር ፖሎቲካዉ ሲገርመን  በትግራይ ክልል  ስልጣኑን በጋብቻና አምቻ ጨምድደዉ መያዛቸዉ የሚያሳይ ዝርዝር ይፋ ሲወጣ  የትግራይ ህዝብ ምን ይላቸዉ ይሆን? ለእነርሱና ለቤተሰቦቻቸዉ የተንደላቀቀ ህይወት መቀጠል ስንት ጊዜ ነዉ የትግራይ ወጣት መሞት አለበት ?
ደግነቱ በወሬ ሳይሆን መረጃና ማስረጃ ይዞ እያጋለጠ ያለዉ “ፈንቅል” የተባለዉ ንቅናቄ ካሁን ወድያ ብዙ እድሜ እንደማይሰጣቸዉ ይታወቃል፡፡ የሚያወጣዉ ምስጥር ሽማግሌዎቹን በድንጋጤ ብቻ እንዲበቃላቸዉ የሚያደርግ ነዉ፡፡
በቃላት  ተድበስብሰዉ  ሊታለፉ በሚመክሩ አስተያቶችን  መልዕክት  በሰዉነት እንቅስቃሴ (body language) ማወቅ ይቻላል፡፡  በስሞኑ  የወያኔ ኑዛዜ ገላጮች የሆኑት ስዩም መስፍንና ጌታቸዉ ረዳ ያሳዩት ይኸንኑ ነዉ፡፡ ስዩም መስፍን  ከተስፋ መቁረጥና  ከንዴት  የተነሳ ሃሳቡን መግለጽ አቅቶት ስሩ ተገታትሮ  ተጠፍሮ እንደታሰረ ፍየል  እጆቹን ወደላይና ወደታች ሲያወራጭ ይታያል፡፡ጊታቸዉ ረዳ (ምላሱ) ፊቱ ላይ የሚታየዉ የተስፋ መቁረጥና ጥላቻ ገጽታዉን ጭራቅ አስመስሎታል፡፡ያለምንም ጥርጥር አለን  የሚሉትን የመጨረሻዉን  ጥይት ተኩሰዋል፡፡
                          ፡
ሱይም መስፍን  የእኔና  የዶ/ር አብይ ባንክ አካዉንት ይመርመር ብሎ እንደህጻን ልጅ ሲናገር ምን ዓይነት የሞራል ዉድቀት  ላይ እንደደረሰ ማሳያ ነዉ፡፡  አዲስ አበባ  በራሱና በሚስቱ ስም ያሉትን ህንጻዎች  ቪላ ቤቶችና የንግድ ተቋማት ማስረከቡንና  ባዶ መቅረቱን  እያለቀሰ መንገሩ ይሆን  ብዬ ተጠራጠርኩ ፡፡ ” በኢትዮ ኤርትራ ድንበር ዉዝግብ በዓለም ኣቀፍ  ፍርድ ቤት ኢትዮጵያ   የተሸነፈችበትን ጉዳይ አሸንፈናል ብሎ  ህዝቡን እንዳስጨፈረዉ ሁሉ  ድሃ ነኝ ምንም የለኝም ብሎ  የኢትዮጲያን ህዝብ ከንፈር ለማስመጠጥ  ያደረገዉ ሙከራ የመርሳት በሸታ እንደያዘዉ ማረጋገጫ ነዉ፡፡ አለበለዚያ ጤነኛ ሰዉ በህዝብ ፈት ዳግም ሊዋረድ  አፉን ባልከፈተ ነበረ፡፡
የወያኔ  የመጨረሻ ምሽግ ማብቂያ ምልክቶቹ መሆኑ ሌላዉ ማረጋገጭ  የጌታቸዉ  ምላሱ ቃለ ምልልስና እራሱንና ብጤዎቹን “አይዟችሁ” ለማለት  የጣረበት  ንግግሩ ነዉ፡፡ ፊቱን አጨማዶና በተስፋ መቁረጥ  ተዉጦ ”የፌድራል መንግስት  ትግራይን የማንንበርከክ ፍላጎት አለዉ ፡፡ ፍላጎት አቅም ይጠይቃል፡፡  ሊመጡብኝ ነዉ   በሚል ድንጋጤ የሚፈጽመዉ ነዉ ፡፡እኛ  በአፍሪካ ስመ ጥሩ የነበረና ትልቅ ሰራዊትና መንግስት በማስወገድ የአንበሳዉ ድርሻ ያለንና ልምድ ያካበትን ነን፡፡ አሁን  ያለዉን መንግስት ለማስወገድ ግን ዳግም ጋራና ሸንተረር መሄድ አይጠበቅብንም “” ነበረ ያለዉ፡፡
“በህይወት ውስጥ ትልቁ ስህተት ለሁሉም ሰው ትክክለኛ ሆኖ ለመታየት መሞከር ነው። ያለዉ አቶ ስብሃት ገብረእግዚአቤር ነበረ፡፡
አቶ ጌታቸዉ መናገርና መለፍለፍ ስለሚችል የእርሱ ቅዠት ሁሉ የሌላዉ ሰዉ ራዕይ  ሆኖ እንዲወሰሥድለት ይፈልጋል ፡፡  ምን እንድናዉቅለትና  እንድናምንለት  ነዉ የፈለገዉ? እንደ አክቲቪስቱ አሉላ ሰለሞን   “የትግራይ ህዝብ ጦርነት የባህል ጭዋታዉ ነዉ “ ያለዉን በተዘዋዋሪ እየነገረን ነዉ? ወይስ እስካሁንም አዝነን እንጂ ብንፈልግ ኖሮ የአብይን አስተዳደር   በአንድ ቀን ፉት እናረገዉ ነበረ! እያለን ነዉ?
አቶ ጌታቸዉ ኮሚንስት ቢሆንም  በልጅነቱ ክርስቲያን ስለነበረ  ከመጽሃፍ ቅዱስ  ኤርሚያስ መዕ 9፡23 እንዲያነብ ጋብዤዋለሁ፡፡(ጠቢብ በጥበቡ  ኃያልም በኃሉ……እንዳይመካና  ከተመካም እንደሚዋረድ ያስተምራል)፡፡
ሌላዉ አቶ ጌታቸዉንና ብጤዎቹን ያያዘዉ  በሽታ Narcissism ይባላል፡፡Narcissism is the pursuit of gratification from vanity or egotistic admiration of one’s idealized self-image and attributes
ይኸን በሽታ ነዉ ያልኩበት ሶስት ምክንያቶች ላቅርብ፡፡ አንደኛ እነጌታቸዉ እራሳቸዉን  የሣሉበት  ገጽታ እነርሱን አሳምሮ የሚያዉቃቸዉ ሌላዉ  የህብረተሰብ ክፍል ከሚሰጣቸዉ ግምት ተቃራኒ ነዉ፡፡ ሁለተኛዉ የአሜሪካን ሳይካትሪክ ሶሳይቲ  እንዲህ ያለዉን  ዝቅጠት  personality disorder በማለት እንደህመም ይለየዋል፡፡ ሶስተኛ  እንደ አቶ ጌታቸዉ   ያልሆኑትን ነን እያሉ በዉድቀታቸዉ ማግስት ጭምር “ዋ! ትናንት እንዲህ ነበርን እኮ አታዉቁንም እንዴ!” በማለት  ይጽናኑበታል፡፡ አልፈርድባቸዉም፡፡ እዉነቱ ግን ሌላ ነዉ፡፡
ደርግን በመጣል የአንበሳ ድርሻ አለን ለሚለዉ መጽናኛ ቃላቸዉ፡ አጭሩ መልስ ታዲያ ምን ይጠበስ ነዉ!  ዉስጡ ሲመረመር ደግሞ  መልሱ  ዉሸት ነዉ፡፡ ሰላሳ ዓመታት በኤርትራ ሲዋጋ የኖረዉን  ጀግና የቀድሞ ሰራዊት ለሸንፈት የዳረገዉ ምክንያቶች ለመዘርዘር ይኸ መድረኩም ባይሆንም ባጭሩ   የትግል ጓደኛዉ  ጀኔራል አበበ ተክለሃይማኖት  በአንደበቱ እንደመሰከረዉ ዋናዉ ምክንያት ህዝቡ ስርዓቱን ስለጠላዉ ድጋፍ ስለከለከለ ነዉ  ፟ ሁለተኛ ስራዓቱ ላይ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ሽምቅ ዉጊያ በመነሳቱና   መንግስት ከሰሜን ጦር ግንባር   ሰራዊት ማንሳት በመጀመሩ ለኤርትራ ሸማቂዎች ምቹ ሁኔታ ፈጠረ፡፡ በመሆኑም ግንባሩ እየሳሳ ሲሄድና ሰራዊቱም መሰላቸት ሲጀምር ሻቢያ ከመከላከል ወደማጥቃት ገባ፡፡ወያኔ ካለሻቢያ ጥቃትና ግፊት አዲስ አበባ መግባት ቀርቶ ከደደቢት በርሃ ባልወጣ ነበረ፡፡የአንበሳ ድርሻዉ  ወሬ ነዉ፡፡
አሜሪካኖች  ለምን ቬትናም ላይ ተሸነፉ ተብለዉ የተጠይየቁት አሜሪካዊ ጀኔራል ማክርስቲል “”ጦርነቱን ህዝቡ ስላልደገፈዉ ነዉ” ብለዋል፡፡ በሀገራችንም  የነበረዉ ሁኔታና እዉነታ ይኸ ነዉ፡፡
”የትግራይ ሃዝብ ጦርነትን እንደባህል ጫውታዉ ነዉ የሚያየው” እስከማለት የደረሱት  ናርሲስቶች እንደሚሉት ሳይሆን   በግዛቷ ጸሀይ አትጠልቅም የተባለላት እንግሊዝ እንኳን ቅኝ ግዛት ለማስፋፋት   ከብዙ አገሮች ጋር ጦርነት አካሂዳና አሸነፋ ህዝቧን “ጦርነት ባህሉ” ነዉ አላለችም፡፡ አትልልምም፡፡ ድንቁርና ስለሆነ፡፡
አቶ ጌታቸዉና  ብጤዎቹ ሳያዉቁት ያሸነፉትን ጦርነት ምክንያት አሳምረዉ ያዉቃሉ፡፡  ስልጣን ላይ የነበሩት ደግሞ  ሳያዉቁት መሽነፋቸዉን እንኳን ማመን አይፈልጉም፡፡ደርግን ያሸነፍን ጀግኖች ነን በማለት ለሀያ ሰባት ዐመታት ጠዋትና ማታ  ያላዘኑት አንሶ ዛሬ መሪዎቹ በስልጣን ብልግናና ሌብነት ምክንያት እንድሚጠየቁ ሲያዉቁ  ጭራቸዉን ቆልፈዉ ከሸሹ በኃላ የህዝቡን ስሜት በሀሰት ፖሮፖጋንዳ በማደንዘዝ ሌላ ደም ለማስፍሰሰ እየቋመጡ  ናቸዉ፡፤  ለዚህም ነዉ ሰሞኑን በገደምዳሜ   ጦርነት እንከፍታለን  ከዚያም እንደልማዳችን ስልጥኑን በጉልበት እንነጥቃለን  ዓይነት ፉከራ የጀመሩት፡፡ አንድ ያፈጠጠ እዉነት  ግን አለ ፡፡የወያኔ መሪዎች በሰረቁት ገንዘብ  እስካሁንም ህዝቡን እርስበርስ ለማፋጀት ሞክረዋል ወደፊትም እስኪያበቃላቸዉ ድረስ ይጥራሉ፡፡ ሞራል የሌላቸዉ ፈጣጦች ስለሆኑ ወደስልጣናቸዉ  ለመመለስ ይመኛሉ፡፡ መጥፎ ዜና ልንገራቸዉ!  በምኞት  እንዳሉ ወደመቃብር ይወረዳሉ፡፡

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.