የሪፍት ቫሊ “ዩኒቨርስቲ” ባለቤት አቶ ድንቁ ደያስ ኢትዮጵያን በስንት ሠይፍ ነው እየቀላት ያለው? – ነፃነት ዘለቀ        

ስለርዕሴ መንዘላዘል ከፍተኛ ይቅርታ እጠይቃለሁ፡፡ ርዕስ እንዲህ ረዝሞብኝ የሚያውቅ አይመስለኝም፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደእንጉዳይ ከፈሉ የግል ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መካከል አንዱ ሪፍት ቫሊ “ዩኒቨርስቲ” የሚባለው ነው፡፡ ይህ ተቋም በትምህርት ጥራቱ እጅግ የሚወቀስና ተመራቂዎቹ ራሳቸው ሳይቀሩ ከምርቃታቸው በኋላ  ለወረቀት እንጂ ለዕውቀት እንዳልታደሉ በቁጭት የሚመሰክሩት  ፀሐይ የሞቀው እውነት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሀገራችን አለመታደል ፈርጀ ብዙ እንደመሆኑ ይህ ተቋም በአሉታዊ ጎኑ ሀገራችንን እንጦርጦስ እያወረዱ ከሚገኙ ተቋማት አንዱ እንዲሆን ታሪክ ጨካኝ ፍርዱን አሸክሞናል፡፡ ከዕውቀት ወረቀትን ማስቀደም ብዙ ጣጣ አለው፡፡

Dinku e1592310369307

በስማ በለው ባገኘሁት መረጃ ላይ ተመሥርቼ አይደለም ይህን ማስታወሻ የምጽፈው፤ እንደዚያ ባደርግ ወንጀልም ኩነኔም ነው፡፡ ምራቅ የዋጥኩ ዜጋ እንደመሆኔ ስም በማጥፋት የምጠቀመው ነገር እንደሌለ እረዳለሁ፡፡ በመንግሥትም ሆነ በግል ከፍተኛም ይሁን ዝቅተኛ የትምህርት ተቋማት ዘንድ የጥራት ችግር፣ የአስተዳደር በደልና አጠቃላይ የአሠራር እንከን ሊጠፋ ባይችልም ይህ ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርስቲ ተብዬ ግን እውነተኛ መንግሥት ቢኖረን ኖሮ አንድ ቀንም ማደር ሳይኖርበት በደቂቃዎች ውስጥ ሊዘጋ በተገባው ነበር፡፡ ይሁንና ገንዘብና ዘረኝነት እየተፈራረቁ በሚሰጡት ያልተገባ አገልግሎት ሳቢያ ይሄውና ትውልድ እየተበላሸ፣ የትምህርት ጥራትም ድራሹ እየጠፋ “ዩኒቨርስቲ”ው የወረቀት ፋብሪካ ሆኖ ቀረ፡፡ ገንዘብ ትከፍላለህ፤ ትመዘገባለህ፤ ሲበዛ A+  –  ሲያንስ B+ በየኮርሱ  እያስመዘገብክ – እንዳየሩ ጠባይ ክፍል ገብቶ መማርም ሳያስፈልግህ – ኮርተህ ተንቀባርረህ – “ከፍዬ እኮ ነው – በነፃ መሰለህ?!” እያልክ ዲኑን ከፕሬዝደንት – ዘበኛውን ከጽዳት እያሽቆጠቆጥክ – ምናልባትም የጊዜ ዑደትን መጠበቅም ሳይኖርብህ … በ flying colors መመረቅ ነው፡፡ ለትምህርት ጥራት ክትትል የተቋቋመው ሄርቃ (HERQA) የሚሉት የመንግሥት መሥሪያ ቤት የጥራት ቁጥጥር አባላትም ከእላቢ ወተቱ የድርሻቸውን ካገኙ ደንታ የላቸውም፡፡ ሆዳቸው ከሞላ ሀገር አበጠች ፈረጠች እነሱን ምን ገዷቸው!

ደረጃው ይለያይ እንጂ በህክምናውም ሆነ በሌላው ዘርፎች ሪፍት ቫሊን መሰል ሌሎች ተቋማትም እንዳሉ ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ (አንዳንድ ቦታዎች ስትሄድ የተንጋደደና እንዳይወድቅ በአጣና ውሻል ተደግፎ እንደሰካራም የሚንገዳገድ ፎቅ ብታይ፣ በእግሩ ወይ በመኪናው ራሱ ሀኪም ቤት  እየሮጠ ገብቶ በህክምና ስህተት ይሞትና ማለትም ይገደልና ለዘመድ አዝማድ ተደውሎ ሬሣውን ሲወስዱ ብታይ፣ በችሎት የተሰየመ ዳኛ በሙስና ወይም በችሎታ ማነስ ወይም በሁለቱም ምክንያት ፍርድን ሲያጣምም ብታይ፣ ሲያስተምር “is”ን ከ“was” መለየት አቅቶት እንግሊዝኛን ባማርኛ ሲያስተምር ብታይ፣ በጎሣው ምክንያት ያለአንዳች ውድድር ከበላይ በመጣ ቀጭን የሥልክ ትዕዛዝ ብቻ ወረዳና ክፍለ ከተማ ተሰግስጎና ኃላፊነት ላይ ተመድቦ አንድ ተራ ደብዳቤ ለመጻፍ ሲቸገር ብትታዘብ … የነሪፍት ቫሊ ውጤት መሆኑን አደራህን እንዳትረሣ!)፡፡ አንዳንዶቹ ልካቸውን አውቀው ወይም ለበላይ አካል በየዙሩና ከዙሩም ውጪ ለአንዳንድ አስቤዛ የሚከፍሉት ጉቦ አንገሽግሾኣቸው ወይም በራሳቸው የሆነ ምክንያት የተነሣ ዘግተው ተገላግለዋል፡፡ ስለዚህ ተቋም ሁኔታ ግን በዚያ የሚመረቁ ሳይቀሩ ለወረቀት ብለው እንጂ ለዕውቀት ብለው እንዳልሆነ በግልጽ ይናገራሉ፡፡ ዛሬ ዛሬ የሚፈለገው ደግሞ ዕውቀት ሳይሆን ወረቀት ሆኗል፡፡ (ይህች መስከረም ለቺሣ የተባለች ዶክተር ግን እንዴት ያለችዋ እሳት ናት በል? አሁን በዩቲዩብ እየሰማናት … እንዲህ ነው እንጂ መማር! የበረሃ ላይ ምንጭ፤ በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ የሚታይ  ተስፋ ሰጪ የብርሃን መቅረዝ…. እነኚህን መሰሎች ያብዛልን፡፡)

ተጨማሪ ያንብቡ:  በዛሬው የተቃውሞ ሰልፍ የኢቲቪ የሀሰት ዘገባ ሲጋለጥ

አንድ ወቅት በምሠራበት አንድ የመንግሥት ከፍተኛ የትምህርት ተቋም የቅበላ ኮሚቴ አባል ነበርኩ፡፡ በዚያ ተቋም  ዕጩዎች ለሁለተኛ ዲግሪያቸው ይመዘገቡና የመግቢያ ፈተና ይወስዳሉ፡፡ ፈተናው በየትምህርት ዓይነቱ ይሰበሰብና ለአራሚዎች ይሰጣል፡፡ የቋንቋውን ክፍል የወሰደው መምህር በማግሥቱ አንድ ነገር ሊያሳየኝ እንደሚፈልግ ገልጾ ላግኝህ ይለኛል፡፡ እንገናኝ ባለኝ ሰዓት ተገናኘን፡፡ አንድ የመግቢያ ፈተና ወረቀት አሳየኝ፡፡ የሚገርም ወረቀት ነው፡፡ ቅጂው አሁንም እኔም ዘንድ አለ፡፡ የደርግ መንግሥት የሁለተኛ ክፍል ተማሪ በዚያ ወረቀት ላይ ከፈሰሰው ዕውቀት የበለጠ ዕውቀት አለው፡፡ ከሰሞነኛ የዚሁ ዩኒቨርስቲ የበር ላይ ማስታወቂዎች ደግሞ ከፌስ ቡክ ያገኘሁትን ቀጥዬ አስቀምጣለሁ፡፡ ይህ እንግዲህ ትውልድን ከሚያ(ስ)በቃ ተቋም ቢሮ ተጽፎ የወጣና ለሕዝብ በአደባባይ የተለጠፈ ነው፡፡ በቅርብ ቋንቋ በአንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም እንዲህ ከተጻፈ በሩቁ ቋንቋ በእንግሊዝኛ ቢሆን ኖሮ እንዴት እግር አውጥቶ ይሽቀነጠር እንደነበር አስቡት፡፡

 

ሪፍት ቫሊ ዩኒቨርሲቲ ዱራሜ ካምፖስ

የተከበሩት ደንባኞቻቺን ኮሮና ቫይራስ ለመከላከል እጂ በመታጠብ ና ዉስጥ ያሉትን ሰራተኞች ጋራ ኒኪኪ አላመደረግ እንዲት ተባበሩን የእርሶም ሆኖም የማንም ህዮትን እንድትጠብቁ ጥር እናስተላልፋለን

በመተባበሪ ቫይራሱን እናስወግድ፡፡

ያ የመግቢያ ፈተና የተጻፈው በእንግሊዝኛ ፊደላት ሆኖ አማርኛ ነው – ለምሣሌ  Yameleketkut bakawunting  MA lememar new ዓይነት – ይህ የኔ ምሣሌ የሆሄ ችግር የለበትም – ማለቴ በትክክል ተጽፏልና ይነበባል፤ ለመረዳትም አያስቸግርም፤ ያኛው ግን ለማለት የተፈለገውን ማግኘት የሚቻለው በስንት ‹ጥናትና ምርምር› ነው፤ ሁሉም ሰው ደግሞ አያገኘውም፡፡ ፈተናው በእንግሊዝኛ አጭር ድርሰት መጻፍ ሆኖ ሣለ ወረቀቱ ላይ ያለው እጅ እግር የሌለውና አማርኛውን በላቲን ፊደል ያስቀመጠ  ኮተት  ነው፡፡ የዚያ ወረቀት ባለቤት በሐረር ይሁን በድሬዳዋ ካምፓስ ከሪፍት ቫሊ በቢኤ ዲግሪ የተመረቀ መሆኑን በዚያ ውልንግዙ በጠፋበት “ድርሰት” ላይ ጠቅሷል፡፡ ያን የመሰለ ስሙን እንኳን በአግባቡ መጻፍ ያልቻለ የቢኤ ምሩቅ በዚያ ተቋም እንዴት ሊመረቅ እንደቻለ ተገረምን፡፡ ከዚያም በከተማው ስለተቋሙ የሚወራውንና በቀጣሪዎች ዘንድ የሚሰማውን እሮሮ አሰናስለን ስናየው ሪፍት ቫሊ በርግጥም ሀገርንና ትውልድን ለመግደል ኢትዮጵያ ላይ ከዘመቱ ዘመን አመጣሽ ወረርሽኞች – እንዳሁኑ ቢሆን ኮሮናዎች ማለትም ይቻላል – አንዱ እንደሆነ ተገነዘብን፡፡ “ዐመል ያወጣል ከመሃል” እንዲሉ መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ይህን ጉድ እየተረዱ በመምጣታቸው ተጽፎ ባልተለጠፈ የውስጥ ማስታወቂያ “ከሪፍት ቫሊ በስተቀር” በሚል ቅድመ ሁኔታ የሥራ አመልካች ዕጩዎችን መቀበል እንደጀመሩም ሰማን፡፡ ጥሩ ነው፡፡ “ሥራው ያውጣው” የሚባለውም ለዚህ ነው፡፡ ድንቁ ደያስ የሚበላው “ሰው” እንጀራ እንዴትና ለምን እንዳላነቀው ግን የሚገርም ነው፡፡ የበሉበትን ወጪት መስበር ከዚህ በላይ የለም፡፡ የመርገምት እንጀራ ከመብላት ደግሞ የለዬለት የኔ ዓይነቱ ንጡህ ድህነት በስንት ጣሙ! ሁሉም ለሚያልፍ ከንቱ ዓለም በወንጀል ተዘፍቆ የገንዘብ ሀብታም መሆን ድህነት ነው – የአእምሮ ምክነት!

ተጨማሪ ያንብቡ:  ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት ሁኔታ ስልጣን በእጁ ያለው ህወሓት በፍጥነት እና በድፍረት መውሰድ ያለበት አስራ ስድስት ቁልፍ እርምጃዎች ( ጉዳያችን)

የድንቁ ጉድ በዚህ ብቻ ተወስኖ ቢቀር ዕዳው ገብስ በሆነ፡፡ አንዳንዶቻችን ቀደም ካለ ጊዜ ጀምሮ፣ ብዙዎች ደግሞ ከሰሞኑ የዋልታ ቲቪ አንድ ዘጋቢ ፊልም (ዶኩመንታሪ) ሥርጭት በኋላ መረዳት የቻልነው ሰውዬው ሀገርን በዘርና በቋንቋ ሸንሽነው ሠላሣ ቦታ ለመበታተን ከሚያሤሩና ሌት ተቀን ያለዕረፍት ከሚሠሩ የኢትዮጵያ አፍራሽ ኃይሎች ጋር እጅና ጓንት ሆኖ የዕብድ ገላጋይ መሆኑን ነው፡፡ አማራ ኦሮሞ፣ ትግሬ ከምባታ ሳይል ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዚያ ትውልድን ገዳይ ተቋሙ ተመዝግቦ “እየተማረ” በከፈለው ገንዘብ አዳሜ የራሱን መቃብር ሲቆፍር እንደሰነበተ ከዋልታ ዝግጅት ሊገነዘብ ችሏል፡፡ የሥራውን ይስጠው ከማለት ሌላ ምን ይባላል? በተቋሙና በተለያዩ የንግድ ዘርፎች ተሠማርቶ በገፍ ከሚዝቀው ገንዘብ ለዚያም ለዚህም የጠባብ ፖለቲካ አራማጅ ቡድን ገንዘብ እየረጨ ሀገራችን ሰላሟን እንድታጣ የሚያደርግ በሁለት ወገን የተሣለ ጎራዴ ነው – ድንቁ ደያስ፡፡ ዘር ከልጓም ሲስብ፣ ማይምነት በዕውቀት ካባ ተጀቡኖ ሀገርን ሲንድ በድንቁ ደያስ በገሃድ አየን፡፡

ለማንኛውም  እውነትና ንጋት እያደር ይጠራልና የዚህ ሰውዬ ጉዳይም እንዲህ ከያቅጣጫው ፍንትው ብሎ መታየት ከጀመረ መንግሥት ለራሱ ሲል በተጨባጭ ማስረጃ ላይ ተመሥርቶ አስፈላጊውን እርምጃ እንዲወስድና ከሰውዬው ዕኩይ ሤራና ተንኮል ትውልዱ በአፋጣኝ ይድን ዘንድ ግዴታውን እንዲወጣ  እንደ አንድ የሀገር ችግር የሚሰማው ዜጋ በግል ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ጠላት ሠርጎ የሚገባበት ቀዳዳ ብዙ እንደመሆኑ መንግሥት በመሠሪዎች የአፍ ጂዶና ጎሣዊ ቅርርብ ሳይንበረከክ አስፈላጊውን የእርምት እርምጃ ወስዶ ሰላምን ቢያስጠብቅ ጥቅሙ ለራሱም ነው፡፡ “መጽሐፍ በሽፋኑ (ማማር) አይታወቅም፡፡” በዚህ ዘመን አባትና ልጅ እየተካካደና እናትና ልጅ እየተባላ ጎሣዊና ነገዳዊ መቀራረብ ብቻውን የትም እንደማያደርስ ግልጽ ነው፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የኢትዮጵያ መንግስት የኮቪድ 19 ወረርሽኝን ለመከላከል የወጣውን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ በመጠቀም እየተወሰደ ያለውን ያልተገባ የሃይል እርምጃ ያቁም

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ከተኩላና ቀበሮዎች ይታደግልን፤ ከተደቀኑባት ኆልቁ መሣፍርት የሌላቸው ችግሮቿም ፈጥኖ ያውጣት፡፡ አሜን፡፡

2 Comments

 1. I wonder how much people like this DENKU DIABLOS criminals have ruined the brains of the youth in Ethiopia. I had spent my savings to help my fellow Ethiopians to get a better education and had built a school in Adama with fellow share holders and started Awash Elementary and secondary school in 1997. the school was admitting student and had hired retired teachers and had brought hope for the community and I had organized a fund rising to buy and collect education materials to the school from Canada. Myself and my wife visited the school in 2005 and that was the happiest time in my life when we visited the class rooms and had to respond to the questions from the future generation about life in Canada, and their ambitions and their dreams. The Director at that time Mr.Lulseged and my self were teachers at Emperor Gelawdious high school in Adama.
  When Adama was expanding the location of the school become the target of DENKU DIABLOS and ond day he brought his armed guards and owned the school and my dream and desire to help my country was badly affected, he was part and parcel with oromo wayanes there was no justice to bring him to face charges. I feel bad for those who spent their time and money and could see him face charges. No wonder I hear, see and read the standard of education is hitting the bottom in Ethiopia because evil people like Diablos and those who were trained at his” RIP off Valley colcolage” are trouble to the society.
  I heard that this criminal had made the US his shelter and sooner or later he will face justice for the dishonor and embezzlement he committed on education and the country.

  God bless and protect Ethiopia.

  Muchfun

  Canada.

 2. It is a pity tjat Ethiopia has become a country of chieftains like that of Zemene Mesafint who act as an independent state.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.