ለጣና መፍትሄ ቢኖረንም ከማን ጋር ልንሰራ እንችላለን? ጥሪ! – ሰርፀ ደስታ

Tana 1

ታላቁ ሳይንቲስት አይንሽታይን (አንስታይን) ችግሩ በተፈጠረበት መንገድ ችግሩን መፍታት አይቻልም ያለው በአገራችን ብዙ ችግሮች መፍትሄ ማጣትን በደንብ ይገልጸዋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ለዘመናት ችግሩን የፈጠሩ አሰራሮች፣ አስተሳሰቦችና ሰዎች በችግር ፈችነት ግንባር ቀደም ሆነው ስለተሰለፉ የዘመናት ችግሮቻችን እየባሱ እንጂ እየተወገዱ መሄድ አልቻሉም፡፡ ከዘማናት ጀምሮ በረሀብ በዓለም የተመዘገበችባቸው ክስተቶችን በቁጭትና በእልህ መፍታት አቅቶን ድሮ በስንት አመት አንዴ የሚመጣው ረሀብ ዛሬ በየዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠር ሕዝብ ረሀብተኛ የሚሆንባታ ቋሚ የረሀብ መዝገበቃላት ትርጉም ማሳያ ሆና እናገኛታለን፡፡  ከብዙ የምድራችን አገራት በላይ የምግብ እህል ለማምረት ትልቅ አቅም እያላት ነው፡፡

ሰሞኑን የጣና ጉዳይ ዜናዎቹንና ማህበራዊ መገናኛዎችን አጥለቅልቆት እናያለን፡፡ ሁሉም ስለችግሩ ምሁር ሲሆንበት ታዝበናል፡፡ አንድም ቦታ ግን መፍትሄ የሚለውን በግልጽ ሊነግረን የሞከረ የለም፡፡ እኔ ችግርን በመተንተን ምሁር መሆን አልፈልግም፡፡ ይልቁንም መፍትሄ ሊሆን የሚችል አንድ ነገር ማበርከት እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህ የመንግስትን ቁርጠኝነት እፈልጋለሁ፡፡ ይሄ ቃል ተራ የፌስ ቡክ ቃል አደለም፡፡  ጣና ብቻም ሳይሆን ሌሎች ውሀዎቻችንን ሁሉ ማዳን ይቻላል፡፡ ጣናን ከማዳንም በላይ ልዩ የእድገት ማዕከል ማድረግ ይቻላል፡፡ የዚህን ንድፈ ሀሳብ ያጋራኋቸው ሰዎች አሉ፡፡ የተወሰኑት በምን ያህል ደረጃ እንደተረዱት ባላውቅም ግን ሀሳቡን በማድነቅ የመለሱልኝ አሉ፡፡ ለመደነቅ ግን አደለም፡፡ መፍትሄ ለመስጠት እንጂ፡፡ የኢትዮጵያ ጉዳይ እጅግ አድካሚ ነው፡፡ በተለይ ለይት ያለ ሀሳብ ከሆነ የመንግስት የሚባለው አካል የተንሸዋረረ ትርጉም ከመስጠት ጀምሮ ምሁርና አዋቂ ነን የሚሉትን የትላልቅ ሀሳቦችን የመበረዝ ልምድ እጅግ አደካሚ ብቻም ሳይሆን ተስፋ አስቆራጭ ነው፡፡

ከዚህ በፊት በግሌ የጤፍ ፓተንት ተጠየቀ ተብሎ ብዙ ወሬ በሚወራበት ወቅት ከወሬ ይልቅ የተጠየቀው ነገር እውን አዲስ ግኝት ነው ወይስ የጤፍ ተፈጥሮአዊ ባሕሪ የሚለውን ለመመለስና ለሕግ ሂደትም አስተማማኝ መረጃ ለማዘጋጀት የጤፍ ፓተንት የተጠየቀበትን ጉዳይ በላቦራቶሪ በመስራት ወሳኝ መረጃ በማግኘት ለሚመለከታቸው ሁሉ ሰጥቼ ነበር፡፡ ሆኖም በወቅቱ ለተፈጠረው ነገር ደንታ የሌላቸው ባለስልጣናት (የፖለቲካ ሳይሆን የሙያ) መረጃውን ተጠቅመው የአገርን ነብረት ከማስጠበቅ ይልቅ አንዳንዶች እንደውም በበጎ እኔን እስከ አለማየት ደርሰው ነበር፡፡ በዚህ ሂደት ነበር ፓተንቱ ጸድቆ ይሄው ዛሬ ፓተንቱ መጀመሪያ በተመዘገበበት በኒዘርላንድ ከ10 ዓመት በኋላ የተሻረው፡፡ ፓተንቱ ከጸደቀ በኋላ በሕግ እንጠይቃለን በሚል ብዙ ዘመቻ ሲደረግም ነበር፡፡ ከፍተኛ ወጪ ወጥቶም የሕግ ሰዎች አውሮፓ ድረስ ሲመላለሱ ነበር፡፡ አስቂኙ ነገር የፓተንት ጉዳይ በመረጃ እንጂ በዘመቻ  የሚሻር አልነበረም፡፡ መረጃው ደግሞ እኔ ጋር ነበር፡፡ ማንም ሰው አልጠየቀኝም፡፡ እርግጥ ነው እንደገና በመስራት መረጃውን ማዘጋጀትም ይቻል ነበር፡፡ ሆኖም ሂደቱ እንደዛ አልነበረም፡፡ ይልቁንም ትልቅ ዘመቻና የወረ ገበያ ሆኖ ነበር፡፡ በመጨረሻም በ2018 የሄጉ ፍርድ ቤት ሲሽረው ኢትዮጵያ አሸነፈች በሚል ትልቅ ችፈራ ሲደረግ ነበር፡፡ የሆነው ግን የፓተንቱ መሻር ምክነያት ከኢትዮጵያ ጋር ምንም ግንኙነት የሌለውና ይልቁንም ሌላ ጤፍ መጠቀም የጀመረ ድርጅት ጤፈ በመጠቀሙ ስለተከሰሰ ይሄው ተከሳሽ የፓተንቱ ባለቤት አዲስ ፈጠራ ሳይሆን ጤፍ ያለውን የተፈጥሮ ባሕሪ ነው ፓተንት ያደረገው በሚል በእኔና በሌሎች ሪፖረት የተደረግን መረጃ ይዞ ነበር የተከራከረና ያሸነፈው፡፡ በተመሳሳይ የጣፍ ፓተንት በጀርመን እንዲሁ እንዲሻር  የህግ ሰዎች ለፍርድ ቤት አቅርበው የፓትንቱ ባለቤት መከራክር ያልቻለና አሁን ይሄንኑ ለመመዝገብና ፓትንቱን ሙሉ ለሙሉ ከጀርመን ለማንሳት በመጠባበቅ ላይ ሲሆን የጀርመኑ የሕግ ባለሙያ ከተጠቀመባቸው ሰነዶች አንዱ በእኔ ሪፖረት የተደረገው መረጃ ነው፡፡ ከሕግ ባለሙያው ጋር በግል የኢሜይል ልውውጥ ያደረግን ሲሆን ይሄው የሕግ ሰው ቀጥሎ በአውሮፓ በሙሉ ፓተንቱን ለማሰረዝ እየሰራ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ፓንቱ በአውሮፓ ፓተንት ኦፊስ የተመዘገበ ስለሆነ እያንዳነዱ የፓትን ቢሮው አባል አገራት በተናጥል መሰረዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ እስካሁን ከኒዘርላንድ ብቻ ነው ፓተንቱ ሙሉ በሙሉ የተሰረዘው፡፡

ከላይ ያለውን ጉዳይ ያነሳሁት ምን ያሕል የአስተሳሰብ ችግር እንዳለብን ለማሳየት የራሴንው ተሞክሮ ለማቅረብ ነው፡፡ ሌላ ባቀርብ ልሳሳት እችል ይሆናል፡፡ ይሄ የሆነው ግን እኔው እራሴ በተሳተፍኩበት ሂደት ነው፡፡ አሁንም የጣናን ጉዳይ ሀሳብ አለኝ መንግስትም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው ሁሉ ሀሳቤን መስማት ቢችሉ ጣናን ዛሬ ያለበትን ችግር ማስወገድ ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት እስካሁን ከሚሰጠው ጥቅም በላይ በልዩ ሁኔታ በማስዋብ ጣናን የእድግት ማዕከልና ለሌሎች ቦታዎችም ሆን ሌሎች መፍትሄ ያጣንባቸው ጉዳዮች ልዩ ምሳሌ ለማድረግ ነው፡፡ አሁን በየማህበራዊ ሚዲያውና ዜና ማሰራጫው ስለጣና የሚወራው ጉዳዩን አሰልች ከማድረግና ለወደፊቱም መፍትሄ እንዳይኖር ቀድሞ የወሬ ገበያ ከመሆን ያለፈ ፋይዳ እንደሌለው አስባለሁ፡፡ ጣናም ሆነ ሌሎች ችግሮቻችን የሚፈልጉት በተግባር የሚቀለፁ መፍትሄዎች እንጂ  ወሬና ዘመቻ አይደለም፡፡ አሁንም አላለሁ መንግስትም ሆነ ሌሎች የሚመለከታቸው ለመፍትሄ ሀሳቦች እድል ይስጡ፡፡ መንግስት የሚባለው አካል ሁሉን ነገር ከፖለቲካ ትርፍና ኪሳራ ጋር በማያያዝ መፍትሄ የሚሆኑ ሀሳቦችን ከማክሰም ይልቅ ጥልቅ ሥራ በመሥራት ጥሩ መሆንን ማሳየት እንደእርግማን ሆኖ አይታየውም፡፡ አዝናለሁ፡፡ በዚህ ጉዳይ ሊያናግረኝ የሚፈልግ [email protected] ሊጽፍልኝ ይችላል፡፡  ጥርዬ ለሁሉም አገር ወዳድ ዜጋ ነው፡፡

አመሰግናለሁ

ቅዱስ እግዚአብሔር ማስተዋልና ጥበቡን ይስጠን! አገራችንን ከክፉ የጠብቅልን አሜን!

 

1 Comment

  1. Most of the political science scholars of Ethiopia had not even governed a woerda in their lifetimes . It is waste of time to include them in these talks.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.