ይድረስ ለብልጽግና ፓርቲ ሊቀመንበርና ለጠ /ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ (ምክክር ፓርቲ)

ከምክክር ለአንድነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ(ምክክር ፓርቲ)

mekekkerጉዳዩ፦ የሀገሪቱን ጉሮሮ ለኤርትራ አሳልፎ የሰጠው የኢሕአዴግ መንግስት ዳግም ታሪካዊ ስህተት በመስራት እኛ ኢትዮጵያውያን ውሀ እየተጠማን ለጅቡቲ ውሃ በነጻ የሰጠው የአሮጌው የኢሕአዴግ መንግስት ውሳኔ መንግስትዎ የእርምት እርምጃ እንዲወስድ ስለማሳሰብ

     ኢሕአዴግ ዛሬ ኢትዮጵያን የጅቡቲ ጥገኛ አድርጓታል በኢትዮጵያና በጅቡቲ መካከል የተፈረመው የውሀ ስምምነት በአገሮች መካከል የተመሰረተውን ግንኙነት ሚዛን ለመጠበቅ የሚረዳ ሊሆን ቢችልም፣ ከጎረቤት አገሮች ጋር ትብብር ማጠናከር አንድ ጉዳይ ሆኖ ሳለ ከፍተኛ ዋጋ ያለውን የተፈጥሮ ውሀችንን በነጻ ለ30 ዓመታት አሳልፎ መስጠት ሀገርንና ሕዝብን ከመካድ ለይተን አናየውም፡፡ ምክንያቱም የጅቡቲ መንግስትና ህዝብ በቀን 103 ሺ ኪዩቢክ ሜትር ውሀ ከሺኒሌ ዞንና ከኪሲ ሸለቆ አልምቶ ውሀ በነፃ እንዲወስድ የሚፈቅድ ረቂቅ አዋጅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 26 ቀን 2006 ዓ.ም የወሰነው ውሳኔ ሀገርንና ሕዝብን የሚጎዳ ነው ብሎ ምክክር ፓርቲ ያምናል። በመሆኑም በፓርላማ ኢትዮጵያ ለሚቀጥለው 30 ዓመታት ለጅቡቲ ውሀ በነፃ ለማቅረብ የተፈራረመችው ስምምነት የፖለቲካና፣ የኢኮኖሚ ጥቅምና ጉዳቱ እንዴት እንደተሰላ አዋጁም አይናገርም ለኢትዮጵያ ሕዝብም በወቅቱ በነበረው መንግስት ግልፅ አልተደረገም፡፡

     ስምምነቱ ከመፈረሙ አስቀድሞ በሁለቱ አገሮች እንዲሁም በአካባቢው የፖለቲካ ማዕቀፍ ውስጥ መታየትና ጥቅሙና ጉዳቱ በትክክል መመዘንና ለህዝብ መቅረብ ሲገባው መንግስት ይህንን አላደረገም፡፡ በመሆኑም ምክክር ፓርቲ አገራዊ ጥቅምን አሳልፎ የሰጠው ፓርላማ እና አሮጌው ኢህአዴግ የታሪክ ተወቃሾች ናቸው ብለን እናምናለን ።

      ይህ ታሪካዊ ስሕተትን ክብርነትዎ እንዲያርሙት የሚከተለውን እናሰምርበታለን።

  1. ኢትዮጵያን በሺኒሌ ዞን ለጅቡቲያ የንፁህ ውሀ የመስመር መዘርጊያ የሚሆን (ማሰራጫ) የሚሆን 20 ሄክታር ቦታና ለውሀው ማመንጫ ልማት የሚሆነው 4000 ሺህ ሄክታር ከልላ መስጠቷ በተለይም የውሀ አቅርቦቱ ከክፍያ ነፃ በመሆኑ አገራችን በጅቡቲ ወደብ ለመጠቀም ስትል የጅቡቲን መንግስት ለማግባባት ወይም ለመለማመጥ ያደረገችው በመሆኑ የውሀ ሀብት ከነዳጅ የማይተናነስ መሆኑ ታምኖበት አያሌ አገሮች ከዚህ ሀብት ጥቅም ለማግኘት ሲተጉ ይታያሉ፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ለጅቡቲ በስምምነቱ መሰረት መሬት በነጻ ሰጥታ ኢትዮጵያ ከ 2006/7 ዓ.ም ጀምሮ ለ30 ዓመታት ለጅቡቲ ውሀ በነፃ ለማቅረብ የተፈራረመችው ስምምነት ያሳምማል። ምክንያቱም የአካባቢው አርብቶ አደር ያለበት የመጠጥ ውሀ ችግር ይታወቃል፣እነሱን ተጠቃሚ የሚያደርግ ወይም ኢኮኖሚያዊ ፋይዳም በሕግ ማዕቀፉ ወስጥ አለመካተቱ የሀገርን መሬት ቆርሶ ከመስጠት አይተናነስም።

  2. አሮጌው የኢህአዴግ መንግስት የውሀ ሀብታችንን በነፃ መስጠቱ ግራ የሚያጋባና ከጀርባው የተደበቀ ፖለቲካ ሴራ መኖሩን ፓርቲያችን ምክክር እንዲጠራጠር አድርጎታል ፣ በመሆኑም ጉዳዩ እንዲጣራ እናሳስባለን።

  3. ውሀን የመሰለ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀም በአለም አቀፍ የንግድ ሕግና በበሳል ፖለቲካ እስካልተቃኘ ድረስ በሁለቱ አገሮች መካከል የውጥረት ብሎም የግጭት መነሻ ሊሆን ብለን እንሰጋለን። በኢትዮጵያና በጅቡቲ መካከል በተደረገው ስምምነት ለፓርላማ በቀረበበት ወቅት እንደተገለፀው መንግስት የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም ከግምት አስገብቻለሁ ቢልም ጥቅሞቹ ምን እንደሆኑ ግን ለህዝብ በሚገባ አልተገለፀም፡፡ በመሆኑም መንግስትዎ ጉዳዩን ቢፈትሸው።

  4. ኢትዮጵያና ጅቡቲ የተፈራረሙትን ስምምነት በንግድ ወይም በኢንቨስትመንት መርህ ቢታይና በዋጋ ቢተመን ኖሮ ኢትዮጵያ ለጅቡቲ ውሀ በመሸጥ ከፍተኛ ገቢ ልታገኝ ትችል ነበር ብሎ ፓርቲያችን ምክክር ያምናል። አገራችን ኢትዮጵያ የውሀ ሽያጭ ስምምነት ቢኖራት ኖሮ ለጅቡቲ ወደብ የምትከፍለው የወደብ ኪራይ ጋር የውሀ ሽያጩ ባይመጣጠንም ለደሀ ሕዝባችን ቀዳዳ መሸፈኛ ይሆነን ነበር።

      ጅቡቲ ያለባትንም የመጠጥ ውሀ እጥረት ለመቅረፍ ውሀውን በመግዛት በንግድ (በኢንቨስተመንት) ስምምነት ተጠቃሚ ትሆን ነበር፡፡ መንግስት ይህንን የመሰለ አለማቀፍ ባህሪ ያለውን ስምምነት የአለም አቀፍ ኢኮኖሚ ግንኙነት ህጎች በሚደነገግበት የንግድ አሰራር ዘይቤ መመራት ይገባው ነበር፡፡

  1. በተለይም ውሀ ከፍተኛ ዋጋ ያለው የተፈጥሮ ሀብት ሆኖ ሳለ በስምምነቱ መሰረት ጅቡቲ ከኢትዮጵያ በነጻ የምታገኘውን ውሀ ለ3ኛ ወገን አሳልፋ እንዳትሸጥ የሚከለክል የሕግ ማዕቀፍ የለውም። ምክንያቱም በዚህ ዘመን ለፖለቲካ ትርፍ ተብሎ የኢኮኖሚ ጥቅምን አሳልፎ መስጠት ከቅን ልብ የመነጨ አይደለም ብለን እናምናለን ። በመሆኑም ሊታረም ይገባል ።

  2. በአገራችን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ንፁህ ውሀ የማያገኙ መሆናቸው እየታወቀ መንግስት የመጠጥ ውሀን ለጎረቤት አገሮች በነጻ መስጠት (ማቅረብ)  የውሀ የመስመር ዝርጋታው የኦሮሚያን ክልልን አልፎ የሚሄድ በመሆኑ ዜጋ የሆነው የሀረርጌ ህዝብ በውሀ ጥማት ለከፋ የጤና የማህበራዊ ቀውስ ተጋልጧል፡፡የሐረርጌና የአጎራባች ወረዳዎች ሕዝብ አለመታሰቡ እጅግ ያሳዝናል፣ ያስቆጣል፣ በቆዳ ስፋቷ እጅግ ግማሽ የሚሆነው የሐረርና የአካባቢዋ ህዝብ በብዛቱ ከጅቡቲ ከእጥፍ በላይና ይህ ህዝብ የተዘናጋ መሆኑ ምክክር ፓርቲን ያሳስበዋል።

  3.  ሌላው አነጋጋሪና አሳዛኙ ምክንያት የኢትዮጵያ መንግስት 2006 ዓ.ም ለጅቡቲ የውሀ አቅርቦት ሲያደርግ በሁለት ሀገሮች የተፈረሙ ውሎች ገጽታቸው ምን ይመስላል? የሚለው ሊፈተሽና ስርዓቱ በሀገር ሀብት ላይ ያለው ግዴለሽነትን እንደሚከተለው እናመለከታለን፡፡

  4. የፕሮጀክቱን ስራ በኢትዮጵያ በኩል ለሚቆጣጠር አማካሪም የአገልግሎት ክፍያው የሚፈፀመው የኢትዮጵያ መንግስት መሆኑና የጅቡቲ ውሀ ማልሚያ ስፍራም መብራት፣ የስልክ መስመሮች መዘርጋት እንዳለበትና ወጪውም የኢትዮጵያ መንግስት መሆኑን፣ ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ ወደ ሀገር ውስጥ የገቡ እቃዎችና ተሽከርካሪዎች ከቀረጥ ነፃ ሆነዋል። አሮጌው ኢሕአዴግ የፈፀመው ስሕተት ያማል። በመሆኑም ክብርነትዎ ሕዝባችንን ማዕከል ያደረገ ማሻሻያ እንዲደረግበት አጥብቀን እንጠይቃለን።

                   ከምስጋና ጋር

የምክክር ፓርቲ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ

            ሰኔ 07 ቀን 2012 ዓ.ም

                  አዲስ አበባ

                    ኢትዮጵያ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.