የትግራይ ክልል ምርጫ፤ ስለ ዴሞክራሲ ወይስ አልሞት ባይ ተጋዳይነት? – በፍቃዱ ኃይሉ

በፍቃዱ ኃይሉ

103953728 3438895959476809 4487208472393352782 nየትግራይ ክልል ብሔራዊ ምክር ቤት ምርጫውን ከጳጉሜ በፊት ለማካሔድ ዛሬ ሰኔ 5፣ 2012 ወሰነ። የዚህ ውሳኔ አዝማሚያ ወዴት ነው?

ሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ከብልፅግና ጋር ያለው ፀብ የትግራይ ክልል ከኢትዮጵያ ጋር ያለው ፀብ ተደርጎ መቆጠር ከተጀመረ ውሎ አድሯል። በሕወሓት ደጋፊነታቸው የሚታወቁ አክቲቪስቶች ኢትዮጵያን “ጎረቤት አገር” እያሉ የሚጠሩበት ጊዜ አለ። ሕወሓትም ክልሉን እንደ ነጻ አገር በመቁጠር የሚያደርጋቸው ብዙ ነገሮች አሉ። በክልሉ መንግሥት እና በፌዴራሉ መንግሥት መካከል የነበረው ኩርፊያ ወደለየለት ፀብ የተሸጋገረው ብልፅግና ከተመሠረተ በኋላ ቢሆንም ቅሉ፥ ፀቡ እየተባባሰ መታየት የጀመረው ደግሞ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳው ከተሰረዘ በኋላ ነው። ሕወሓት በክልሌ ምርጫ በጊዜው አካሔዳለሁ ማለቱ ውዝግቡን እስካሁን ያልደረሰበት ቁንጮ ላይ ያደርሰዋል። በተለይም ደግሞ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ሁሉንም ክልሎች የሚመለከት ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ ይህ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ውሳኔ መምጣቱ፣ ጉዳዩን ከድጡ ወደ ማጡ ይሰደዋል። ትግራይ በሌላ አነጋገር ራሷን እንደ ሉዓላዊ አገር እየተመለከት ያስመስላታል።

ሕወሓት፤ የገዛ ‘ትሩፋቱ’ ሰለባ

ሕወሓት በአሁኒቷ ኢትዮጵያ ፖለቲካዊ መዋቅር ዝርጋታ ላይ ዐቢይ ተዋናይ ነው። ሕገ መንግሥቱ፣ የፌዴሬሽኑ አወቃቀር፣ የምክር ቤቶቹ አደረጃጀት እና ሥልጣን በዋነኝነት የተወጠኑት በሕወሓት ነው። ሕወሓትም እንከን አልባ መንግሥታዊ መዋቅር እንደሆነ ይናገር ነበር፤ ነገር ግን ድንገት ከፌዴራሉ መንግሥት ገዢ ፓርቲነት ተገልሎ የክልል ገዢ መንግሥት እና የፌዴራሉ መንግሥት ተቃዋሚ ሲሆን፥ በፊት እንከን አልባ መስለው ይታዩት የነበሩት ስርዓቶች እና አሠራሮች በሙሉ ተቃዋሚ ሆኗል። ይህ ነው ሕወሓትን የገዛ ትሩፋቱ (ሌጋሲው) ሰለባ የሚያሰኘው።

የመጀመሪያው ሰለባነቱ ከመሐል አገርነት ወደ ዳር አገርነት መገፋቱ ነው። የፌዴራል አወቃቀሩ በሕዝብ ብዛት ሦስት ትልልቅ ክልሎችን (ኦሮሚያ፣ አማራ እና ደቡብ) በመፍጠሩ ምክንያት ሌሎቹ ክልሎች በሙሉ ከአጋርነት በስተቀር ዋጋ የሌላቸው አድርጓቸዋል። በክልሎች መሐል ያለው የሥልጣን ልዩነት (በሕዝብ ተወካዮች እና ፌዴሬሽን ምክር ቤት ባላቸው መቀመጫ መሠረት) እጅግ የተበላለጠ ሆኗል። ሕወሓት የፌዴራል ገዢ ፓርቲነት ሥልጣኑን ካጣ በኋላ፥ ኢሕአዴግ ውስጥ ሆኖ አጋር ፓርቲ ይላቸው የነበሩ “ትራፊ ይጣልላቸው” የነበሩ ክልላዊ መንግሥታት ዕጣ ደርሶታል።

ሁለተኛው ሰለባነቱ ሰሞኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ተርጓሚ ሆኖ በሕገ መንግሥት ከመሰየሙ የሚነጭ ነው። እንደሚታወቀው የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ መዋቅር አብላጫ መቀመጫ በገዢው ፓርቲ ይወሰዳል፤ እነዚህም ቁጥራቸው የሚወሰነው በብሔሩ ሕዝብ ቁጥር ነው። ይህም ሁለት ችግሮች ይፈጥራል። ብዙ ተወካዮች የሚኖረው/ራቸው ብሔር/ሮች ውሳኔ ሁሉም ላይ እንዲጫን ያደርገዋል። በሌላ አነጋገር እንደ ትግራይ አናሳ ቁጥር ያላቸውን ብሔሮች አናሳ ዕድል ይሰጣቸዋል። ሁለተኛቸው ችግር የምክር ቤቱ አባላት የፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች እንደመሆናቸው፥ የሚወስኑት ውሳኔ በምንም መልኩ የፓርቲያቸውን ጥቅም የሚነካ ይሆናል ተብሎ አይጠበቅም። ስለዚህ ብዙኀን ተወካዮች ያሉት ብልፅግና የሚፈልገው ውሳኔ ሲወሰንለት፣ ሕወሓት ግን “የበይ ተመልካች” ብቻ ሆኗል። ለዚህም ነው አፈ ጉባዔዋ በፓርቲያቸው ግፊት ከኃላፊነታቸው “በገዛ ፈቃዳቸው” እንዲነሱ የተደረጉት።
ሕወሓት መልሶ ራሱን ጠልፎ የሚጥል፣ የክልሉንም ተጠቃሚነት የሚጎዳ ውሳኔዎችን በኀይለኝነት እና አፍላ ዘመኑ ለምን አደረገ ለሚለው ትክክለኛ ምላሽ ማግኘት ይከብዳል። ምናልባት በየዋሕነት፣ ምናልባት ትክክለኛው መፍትሔ ይህ ነው በሚል ቅንነት፣ አልያም ደግሞ ሥልጣን አላጣም ወይም ከሥልጣን አልወርድም በፈለግኩት መንገድ ሕጉን አስፈፅማለሁ በሚል ከንቱ ምኞት ሊሆን ይችላል።

ምርጫ ማሰናዳት

ሕወሓት በክልሌ ምርጫ አካሒዳለሁ በማለት ተደጋጋሚ መግለጫ ያውጣ እንጂ በሕግ አግባብ በሦስት ወር ዕድሜ ብቻ ለቀረው የምርጫ ጊዜ መርሐ ግብር አላወጣም። የምርጫ ዝግጅት ገለልተኛ ተቋም የሚፈልግ ሲሆን፣ አሁን ያለው ተቋም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ብቻ ነው። ሕወሓት በመግለጫው እንዳመላከተው ምርጫ ቦርድ ምርጫ ያዘጋጅልኝ ብሎ ጥያቄ ቢያቀርብ እንኳን፣ ቢያንስ የስድስት ወር ጊዜ እና በግምት ከመቶ ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ያስፈልገዋል። ይህ እንግዲህ በኮቪድ ምክንያት የሚስፈልገው ተጨማሪ ወጪ ከግምት ውስጥ ሳይገባ ነው። ይህ በአንድ በኩል አፈፃፀሙ ከሚፈልገው ግዜ አንፃር ምርጫው ወቅቱ ካለፈ በኋላ እንዲካሔድ የሚያስገድደው ስለሆነ የተነሳውን የጊዜ ጥያቄ መልስ እንዳያገኝ ያደርገዋል። በሌላ በኩል ይህንን የሚያክል በጀት ክልሉ ለምርጫ ማውጣት ይችላል ተብሎ አይታሰብም። የፌዴራሉ መንግሥት ደግሞ ይህንን ለመስጠት ፈቃደኛ ይሆናል ብሎ ማሰብ የዋሕነት ነው፤ ምክንያቱም የፌዴራሉ መንግሥት ምርጫ የሚካሔድበትን ጊዜ በፌዴሬሽን ምክር ቤቱ እንዲራዘም አስወስኗል። ያንንም ለሁሉም ክልሎች ተፈፃሚ እንዲሆን ነው የሚፈልገው። ይሄም ሁሉ ደግሞ የትግራይ ክልል ምርጫ ይዘጋጅልኝ ብሎ ቦርዱን የሚጠይቅበት የሕግ አግባብ ካገኘ ነው። ስለዚህ የምርጫ መሰናዶው ጉዳይ በትግራይ ክልል ብቻ ይሳካል ብሎ ማሰብ፣ ‘ላም አለኝ በሰማይ፣ ወተቷንም አላይ’ በሚል ያስተርታል። ይልቁንም መፍራት ሌላ ሌላውን ነው።

የምርጫው ጉዳይ እውን የማይሆነው በአፈፃፀም የጊዜ ፍላጎት፣ በጀት እጥረት እንዲሁም የሕግ አግባብ ጉዳይ ብቻ አይደለም። ሕወሓት ራሱ ሌሎች ክልሎች ውስጥ ምርጫ በማይካሔድበት ጊዜ በክልሉ ለብቻው ምርጫ ማካሔድ አይፈልግም። ምክንያቱም ምርጫው ሕወሓት የማይፈልገውን ዓይነት ትኩረት ይስብበታል። በዚያ ላይ የክልሉ ተቃዋሚ ፓርቲዎች እና አገር ዐቀፍ ተብለው የተመሠረቱት ፓርቲዎች፣ ብልፅግና፣ ኢዜማ፣ ኦነግና አብንን ጨምሮ ተወዳዳሪ ማቅረብ የሚችሉት በሙሉ ተሳትፎ ያደርጋሉ። ወልቃይትና ራያ እንዲሁም ተቃውሞ እየተነሳባቸው ያሉ የትግራይ አካባቢዎች በሙሉ የጦፈ ክርክር እና ፉክክር ሊታይባቸው ይችላል። ሕወሓት የመሐል አገርን በጠላትነት በመፈረጅ የፈጠረውን ጊዜያዊ የተጋሩዎች አንድነት የሚሸረሽር እና ትግሉን ውስጣዊ ገጽታ የሚያሰጠውን ፉክክር ለማስተናገድ ዝግጁነት የለውም። ስለዚህ በትግራይ ክልል ውስጥ ከፌዴራል መንግሥቱ ምርጫ በተለየ የጊዜ ሰሌዳ የሚካሔድ ምርጫ አለ ብሎ መጠበቅ የዋህነት ነው።

የዘፈኑ ዳርዳርታ

ሕወሓቶች ምርጫውን በጊዜው ለማካሔድ የፈለጉት ለሕዝብ ድምፅ ዋጋ የሚሰጡ ሆነው እንዳልሆነ ለማወቅ መመራመር አያስፈልግም። ጉዳዩ በአንድ በኩል የውስጥ የቤት ሥራቸውን ለማዳፈኛ የውጭ ጠላት መፈለጊያ ሲሆን፣ በሌላ በኩል የፉክክር ነው። የሕወሓት አመራሮች በፊት ይንቋቸው በነበሩ የኢሕአዴግ አባላት በካልቾ ተመትተው ወደ ዳር መገፋታቸውን አምነው መቀበል አልፈለጉም ወይም አልቻሉም። ለዚህም የማዕከላዊ መንግሥቱን የሚቃረን ነገር በሙሉ ያደርጋሉ። በዚህ መንገድ ውጥረት ውስጥ የሚገባውን ማዕከላዊ መንግሥት ማሳጣት ወይም ማሸነፍ ይፈልጋሉ። ይህ ካልሆነላቸው ግን ተያይዞ መጥፋትም ቢሆን ይሞክራሉ። ትግራይን እንገነጥላለን የሚለው ጥያቄ የትግራይን ሕዝብ መደራደሪያ በማድረግ እንደሚመጣ መጠበቂያው ጊዜ አሁን ነው። በርግጥም ሕወሓቶች አሁን የፖለቲካ ካርዶቻቸውን በሙሉ ጨርሰዋል፤ አንቀፅ 39 የመጨረሻዋ ካርድ ልትሆን ትችላለች። በሕወሓቶች የኩራት፣ እንዲሁም የአልሞት ባይ ተጋዳይነት ፖለቲካ ምክንያት የአገር እና ሕዝቦች ደኅንነት አደጋ ጫፍ ላይ ቆሟል። የሕወሓት የአጥፍቶ መጥፋት የመጨረሻው መጀመሪያ እነሆ የዚህ የምርጫ እናካሔዳለን መፈክር ነው። ምርጫ ማካሔድም ይሁን እንገንጠል ማለት ሕገ መንግሥታዊ መብቶች ናቸው። የሕወሓት እርምጃ ግን ከሥልጣን እና ጥቅማጥቅም ጋር አብረው የቆረቡ ባለሥልጣኖች የትግራይን ሕዝብ ለመስዋዕትነት የሚዳርግ እርምጃ እንጂ የዴሞክራሲ ዒላማ የለውም።

2 Comments

  1. የትግራይ ክልል ምርጫ? ምርጫ የሚለው ቃል ያለቦታው ነው የገባው። በትግራይ እውነተኛ ምርጫ ኑሮ አያውቅም ሊኖርም አይችልም ወያኔ በስልጣን ላይ እስካለ ድረስ። በሰው ህይወት መቀለድ ነው። ምርጫ እኮ ድምጽ መስጠት ብቻ አይደለም። በምርጫው ቀንም እቤት መዋልም ምርጫ ነው። ያን ማድረግ ግን የትግራይ ህዝብ አይፈቀድለትም። እያደረ ሲሄድ እኔ ወያኔዎች ጭራሽ ጨርቃቸውን ጥለው አብደዋል ያሰኛል። ትሩፋቱ ምንድን ነው በዚህ አስከፊ ጊዜ ስመ መርጫ ማድረግ? የትግራይ ህዝብ እንደሆነ ለይቶ ካወቃቸው ቆየ። ያው በእልፍ ካድሬዎቻቸውና የደህንነት አውታራቸው አፍነው በመያዝ ወያኔና የትግራይ ህዝብ አንድ ነው ይሉናል። ሞኛችሁን አሞኙ። እንኳን አሁን በበረሃ እያላቹሁም እናንተን ለመምሰል የትግራይ ህዝብ ፍላጎት የለውም። አሁን ተከበናል፤ አማራ መጣባችሁ፤ የብልጽግና ፓርቲ የትግራይን መብት ሊቀማ ነው፤ ኤርትራ ልትወረን ነው ወዘተ በማለት የሚዘላብደው ወያኔ ልብና ዓለማዊ አቀፍ እይታ ቢኖረውማ ዙሪያውን አይቶ ህዝባችን ባነቃ ነበር። የቱርኩ Erdogan በአፍሪቃ ቀንድ ላይ እያመቻቸ ያለው የጦር ሃይል በአሰብ ወደብ የዓረብ መንጋ መንጋጋትና ሌሎችም የጥቁር ህዝቦች መብት ሊያሳስባቸው ይገባ ነበር። ግን ወያኔ እይታው አለም አቀፋዊ ሳይሆን የመንደር ነው። የድሮውን ኦቶማን ግዛት እመልሳለሁ ሱዳን ውስጥ የምትገኘውን የድሮ የኦቶማን ወደብ Suakin አድሳለሁ በማለት ቱርክ ለራሷ ወታደራዊ ጠቀሜታ በማመቻቸት ላይ እንዳለች ግልጽ ነው። በሱማሊያ ትልቁን ኤምባሲና የወታደር ማሰልጠኛ መክፈቷ ስንዴ ለማብቀል አይደለም። እስልምናን ለማስፋፋት እንጂ! ታዲያ ወስላታው ወያኔ ሁልጊዜ ክላሽን እና ሌላም ነገር አስታጥቆ የፈረደባቸውን ሁሉ በየአመቱ በጸሃይ እያስመታ ሲፎከር ለተሰላፊዎቹ ወታደሮችም ሆነ ለበአሉ ታዳሚዎች ልቤ ያዝናል። ያረጀ ያፈጀ የግርግር ጉራ በመሆኑ። እነርሱ ለዝርፊያ ሲፋተጉ አለሙ ትቷቸው ሄዷል። የሚያስቡትም የሚኖሩትም ልክ ጫካ እንደነበሩት ነው።
    ወያኔ ዲሞክራሲን አያውቃትም። በበረሃ እያለ እንኳን የዲሞክራሲ ተምሳለው አልባኒያ ነበረች። ወያኔ መግደል፤ ማሰር፤ መዝረፍ፤ ዘርፎ ማዘረፍ፤ ሃገር መቁረስና ማስቆረስ፤ ለትግራይ ህዝብ ቆሜአለሁ ብሎ ምንም ሳያረግ አፍኖ የሚገዛ የአረመኔዎች ስብስብ ነው። ይፋዊ የመንግስት ስርቆት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የተጀመረው በወያኔ ዘመን ነው። ሁሉም ገዥዎች ሰርቀዋል፡ ግን ከማህል ከተማ በብዙ መቶ ቶን ቡና ጠፋብኝ የሚል እንደ ወያኔ ያለ አይነ ደርቅ ሌባ የለም። ስለዚህ ምርጫው ከዲሞክራሲና ከትግራይ ህዝብ መብት ጋር ጭራሽ አይገናኝም። በስልጣን ለመሰንበት ከሚደረጉ አንድ ሴራ ጋር እንጂ። ወያኔ የትግራይን ህዝብ አይወክልም። የትግራይን ህዝብ ይወክላል የሚሉ ሁሉ አፋቸውን ቢዘጉ ይመረጣል። የትግራይን ህዝብ መናቅ ነው። የትግራይ ህዝብ ትግርኛ በሚናገሩ ደርጎች አፉን ተቀፍዶ የተያዘ ነጻነት የሚሻና ኢትዮጵያን የሚወድ ህዝብ ነው። በቃኝ!

  2. የፌዴሬሽን ም/ቤት ያሳለፈውን የምርጫና የስልጣን ማራዘምን አስመልክቶ በርካታ ፓርቲዎች እየተቃወሙት ነው፡፡ ተቃውሞውም ሆነ ድጋፍ መስጠቱ መብታቸው ነው፡፡ ሁሉም ፓርቲዎች ሊባል በሚችል ደረጃ የምርጫውን መራዘም ተቀብለውታል፡፡ ችግራቸው የስልጣን ጥያቄ ብቻ ነው፡፡
    ነገር ግን በተመሳሳይ በተለይ አገራዊ ፓርቲ ነን በሁሉም የአገሪቷ ክፍል እንወዳደራለን የምትሉ ፓርቶዎች ለምሳሌም ኢዜማ፣ አብሮነት፣ አብን፣ ኦነግ፣ ኦፌኮና የመሳሰላችሁት ለምንድነው በክልሌ ምርጫ አደርጋለሁ፣ ኮረና አይገታኝም ብሎ ውሳኔ ያሳለፈውን ህወሀት ስትቃወሙ የማንሰማው፡፡ ምክንያቱም ቀድሞ ስትሉት እንደነበረው በሁሉም የአገራችን የምርጫ ክልሎች ለፌዴራልና ለክልል ም/ቤት እንደምትወዳደሩ ነው፡፡ ታዲያ የትግራይ ክልል የኢትዮጵያ አካል አይደለምን፣ ወይንስ የክልሉ ውሳኔን ተቀብላችሁ በምርጫው እጩ ልትልኩ ነው፡፡ ይመስለኛል አንዳንድ ፓርቲዎች ከህወሀት ጋር አብረው ስለሚሰሩ አቧራውን አብረው በማቦነን አንድ እጩም ቢሆን በመላክ ሶሊዳሪቲያቸውን ማሳየት እንደሚሹ መገመት እንችላለን፡፡ ከህገወጥ ጋር መተባበር ደግሞ በህግ ማስጠየቁን እንዳትረሱት፡፡
    ለማንኛውም አገራዊ የተባላችሁ ፓርቲዎች የፌዴሬሽን ም/ቤት ውሳኔ እንደተቃወማችሁት ሁሉ የትግራይ ክልል ምርጫ ከጳጉሜ ወር/2012 በፊት ምርጫ አከናውናለሁ ብሎ ያሳለፈውን ውሳኔ አስመልክቶ ያላችሁን አቋም፣ በምርጫው ላይ ስለሚኖራችሁ ተሳትፎ እንድትነግሩን እንፈልጋለን፡፡ አስከአሁን የህወሀትን የምርጫ ውሳኔ በመቃወም ሃሳቡን የገለጸው ዶ/ር አረጋዊ የሚመሩት ፓርቲ ብቻ ነው፡፡
    አገራዊ ፓርቲዎች አቋማችሁን ግለጹልን

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.