/

ውድ እናት አገራችን ከገጠማት ዘርፈ ብዙ ፈተና ለማሻገርና ሕልውናዋንም ለማስጠበቅ በልዩነት ሳይሆን በአንድነት በመቆም – አበባየሁ አሉላ

ዛሬን በድል መሻገር ለነገም ዲሞክራሲያዊ  መሠረቱን ማመቻቸት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ድርብ ግዴታችን ሊሆን ይገባል!

አበባየሁ አሉላ
ዋሽንግተን ዲሲ

ethiopiaመግቢያ

እናት አገራችን ከፊት ለፊቷ አስከፊና አሳሳቢ አደጋዎች ተጋርጠውባታል! መላውን ዓለማችንን ያናጋው ሃብትና ስልጣኔ ረድፍ ላይ ያሉ አገራትን እየተፈታተነ ያለው የኮሮና ወረርሽኝ አደጋና በወገኖቻችን ሕይወት ላይ የደቀነው ስጋት እጅግ ከፍተኛ መሆኑ እውን ነው፤ ይህንን ተከትሎ የሚያስከትለው ማህበራዊ ቀውስና የምጣኔ ሀብት ውድመት ለደኃይቷ አገራችን እጅግ ከባድ ነው ፣ በተመሳሳይምን  ወኃችንን ለመጠቀም ባለመው የሕዳሴው ግድብ ግንባታ ሳቢያ በሉዓላዊነታችን ላይ ያጠላው የግብፅ ምኞት ፤  ጎሬቤት ሱዳንንም በመደለል ፣ አረብ ሊግንና አባል አገራትን በማስተባበር ፣ ወሮታ ፍለጋ አሜሪካንን ጨምሮ በአንድ ግንባር ማስተባበር መሞከርዋና በውጭ ግንኙነት ዘርፍ ያለ ዕረፍት በሃሰት ፕሮፓጋንዳ ኢትዬጵያ ላይ እየዘመቱ ነው! አልፈውም የመንግሥታቱ  ፀጥታውን ምክር ቤት ግንባታውን እንዲያስቆም መንቀሳቀሳቸው ምንስ ያክል ለጉዳዩ ትኩረት ስጥተው መስራታቸው ከፊት ለፊታችን የአጠላብን አደጋ ከባድ መሆኑን ጠቋሚ ነው ፣

እንደዚሁም የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ  ሕገመንግሥቱና  ሕገመንግሥታዊ ቀውሱ ከአስከተለው መንገጫገጭ ጋር አገራችንን ለማሻገር ከምን ጊዜውም በላይ ሕዝባችን ፣ መንግሥት ፣ የፓለቲካ ድርጅቶችና በተለይም አንድነት ኃይሎች ፣ ሲብክ ማህበራትና ምሁራን ልዩነትን በማስወገድ በጋራ መቆም ታሪካዊ ግዴታችን ሊሆን ይገባል ፤

በዚህ ፁሑፌ እንዲሁ ሁኔታዎችን መተንተን ሳይሆን አገራችንና ሕዝባችን ትላንት ያለፈበትን ውጣ ውረድና የከፈለው መስዋዕትነት ያስገኘውን ውጤትና ያጣውን ማሳየት፣ ዛሬ የምንገኝበትን ነባራዊ ሁኔታውን የሚገመግም ፤ አፍጠው የሚጠብቁንን ችግሮች የሚዳስስና የመፍትሔ አማራጮችን በሚገባ ያስቀመጠ ይህንን ለመተግበር ኃላፊነት ያለባቸውንም አካላት ለይቶ ያስቀመጠ ፤ በአፈፃፀሙና አተገባበሩ ላይ መወሰድ ያለባቸውን ጥንቃቄዎች ለይቶ ያስቀመጠ  መጠነ ሰፊ ጉዳዬችን ያካተተ ስለሆነ በግርድፍ ሳይሆን ሙሉውን ተያያዥ ግንዛቤ እንድትወስድ በቅድሚያ አሳስባለሁ።

ውድ ኢትዬጵያዊያን!! ዛሬ የገጠመን ቀውስ በወገንተኝነትን ፣ በፓለቲካና የስልጣን ጥያቄ የሚፈታ ሳይሆን በጋራ ውይይትና መደማመጥ  አገራችን ለገጠማት ችግር እውነተኛ ፈውስ ሊሰጥ የሚችል ዘላቂ መፍትሔን መሻት የግድ ይሆናል ፤ ይህም እውን እንዲሆን በዳተኝነት የሚመስለንን በመወራወር  ሳይሆን እንደ አንድ የአገሩ ጉዳይ እንደሚያሳስበው ሁነኛ ዜጋ በጥሞና ተደማምጠን ያለወገንተኝነት በክብ ጠረጴዛ ዙርያ ሰብሰብ ብለን ነባራዊ ሁኔታውን ባገናዘበና መጪውንም ጊዜ ታሳቢ በአደረገ ጥናት ገምግመን ፣ በመረጃና ምክንያት ሃሳብ አዋጥተን የተሻለውንና ብዝኃኑ ላመነበት እራሳችንን አስገዝተን ለተግባራዊነቱ በእኩል መረባረብና መንቀሳቀስ ግድ ይሆናል! ይህም ሲባል እንዲሁ አንድን ወገን የማሞገስ ወይም የማጣጣል ጉዳይ  አይደለም ክርክሩ! መልካም ጅማሮዎች ተሳክተው በሕዝበኝነት እንዲቀጥሉም እንሻለን፣ ዛሬ እመሬት ላይ ከምናየው ነባራዊ ዕውነታ ተነሥተን መፍትሔ ፈልገንና ችግሩንም ፈትተን እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገራችን እውን እንዲሆን እንዳለፉት ዘመናት መጪው ጊዜም አሁንም እንዳይቀድመንና ብሎም እንዳይደበዝዝብ ከወዲሁ አሻግረን በማየት የኢትዬጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚሉ ወገኖች ሁሉ ድምፅ ይስማ ዘንድ ኢትዬጵያን የሚለው ኃይል ግዜ ሳይወስድ መላም መጠበቂያም ከወዲሁ  ሊያበጅለት ግድ ይላል።

የሕወኃት/ኢህአደግ አገዛዙ ሃያ ሰባት ዓመት ሕዝብን ቁም ስቅል ሲያሳይ እልፍ አዕላፍ ወገኖችን በበርካታ ማሰቃያ እስር ቤት ለዘመናት አጉሮ ግፍ ፈፅሟል! ሺዎች በዘረኝነት አለንጋ አገራቸውን ጥለው እንዲሰደድ አድርገዋል፣ብዙዎች ወዳቀድበት ሳይደርሱ የበረሃ አሸዋና ባሕር በልቶአቸዋል፣ ሌሎችም የሽብርተኞች ሲሳይ ሲሆኑ በሰናይ በረሃ ታግተው መሻገሪያ ገንዘብ የሌላቸው በቁማቸው የውስጥ አካላቸው ተሸንሽኖ ለሃብታሞች ሕይወት መቀጠል ሲሳይ መሆናቸውን በጀርመን ድምፅ ከስፍራው ላይ እማኝ አድርገው አሰምተውናል ።

እናት አገራችንን በጎጥ ከፍለው ዛሬ እንደ አሸን በፈላው የማንነት ጥያቄ ሳቢያ ወገን በእርስ በርስ ጥላቻ በተረጨው መርዝ እልፍ ዓዕላፍ ንፁኃን ዜጎች ሕይወት በከንቱ ጠፍቷል ፣ የንፁኃን ደም እንደጅረት ፈስዋል፣ በገጀራ የንፁኃን አንገት ተቀልቷል፣ እልፎች በድንጋይ ተወገረዋል ፣ ክቡር የሰው ልጅም ተዘቅዝቆ በራስ ወገን ሲሰቀል ለታሪክ አየን ፣ እናት በጠራራ ፀሐይ ልጅዋን የምታጠባበት ጡትዋ ተቆርጦም ሰማን ፣ የእናንት ቀዬ አይደለም ተብሎ ወላይታው አዋሳ በቁሙ በእሳት እንዲጋይ መደረጉንም በእማኝ ሰማን ፤ ከቤት ንብረታቸው ከቀያቸው ሚሊዬኖች አማራ ናቸሁ ወዘተ በሚል ተሰደድ፣ ዩኒበርሲቲዎች የዘር መጨፋጨፊያ ሆኑ ኳስ ሜዳዎችም በተመሳሳይ ፣ በጠራራ ፀሐይ መንግሥት አለ በሚባል አገር በቅርቡ ሴት ልጃገረድ ወጣቶች ታፍነው ተወሰድ ሰሚ አጥተው ተረሱ፣ የሕዝብ ሀብት በእሳት ጋየ ተዘረፈም ፣ ወንጀለኞች ተመሳጥረው በአንድ ጀምበር 17 ያክል ባንኮች በጠራራ ፀሐይ ዘረፉ ፤ ዛሬም ቢሆን በኦሮሚያ ክልል ቄሮ ባለንብረቶችን ይህንን ያክል ሺህ ብር ለነገ አዘጋጅ ብሎ ያዛልም ይነጥቃልም!!

ወገን! ይህ ሁሉ ሲሆን በርግጥ መንግሥት ሁሉም ሥፍራ አለን? የሚያስብል እንቆቅልሽ ነው ! ይህ ዛሬ በየቦታው የምናየው ዘር ተኮር ጥላቻ ፣ ግጭትና ቀውስ መድኃኒት ካልተገኘለት ቀጣይና የዚህ የሃያ ሰባቱ ዓመት ፅልመት ሥርዓት መሠረቱ አልተናደምና  እትዩጵያንና ኢትዬጵያዊነትን እንዳደበዘዘ ይቀጥላል።

በእዚህ ዓመታትን በወሰደውና ሺዎች ዋጋ በከፈሉት ሕዝባዊ እምቢተኝነት ሕዝብን የበላይ ሊያደርጉ የሚችሉ ብዙ መልካም አጋጣሚዎች አልፈውናል! ለምን? ህዝባዊ ቅንጅት፣ መርሕና መሪ ባለመኖሩ ይህ አስከፊ የሕወኃት/ኢህአደግ አገዛዝ አገርን ማስተዳደር ተስኖት እልፎች መስዋዕት ሆነው ከስረ መሠረቱ እስከነ ግሳንግሱ ሳይገርሰስ ቀጠለ።

በመሆኑም በግለሰቦች ሽግሽግ ሥርዓቱ ነፍስ ዘርቶ ቀጠለ! ከአብራኩ የወጡት ” የለውጥ ሃይል” በመባል ከነባራዊ የመንግሥታዊ ለውጥ ዕውነታው ውጭ ”  ጥገናዊ  ሂደቱን ” መሩት ሕዝባችን መስማት ይመኝ የነበረውን ቃል (ፈልቅቀው) አበሰሩለት ከጋመው የሕዝባዊ እምቢተኝነት የመተንፈስና የመረጋጋት ዕድልም ሰጡት!

” ኢትዬጵያዊነት ሱስ ነው” ብለው ተስፋን አሰንቀው ጮቤ አስረገጡን! ትንሽም ሳይቆዬ ወደ መንደራቸው ስንሸራተቱም ሰማን! እንደ ጎምም ድምፃቸው ለዘበ! ክህደት ወይንስ ማንነት? ለዚህም መፍትሔው ምንስ ይመጣ ይሆን ብሎ ነገን አሻግሮ ማየት ጎበዝ ግድ ይለናል ፤ የቀሩትም በዚህ ኢትዬጵያ በሚሏት አገር

” ስንኖር ኢትዬጵያዊ ስንሞት ኢትዬጵያ” ብለውን ስንትስ ዓመት የተጠማነውን ኢትዬጵያን ከፍ የሚደርግ ቃል ለሃያ ሰባት ዓመታት የተጠማንበት ቃል  አሰምተውን ልባችንን አሸፈቱት!! ባሉን ነገርም አብረውን ይዘልቃሉ አልን! ተከትለን ነጎድንም! ጎምቱ የተባሉ ሊሂቃንና ፓለቲከኞችም እዘለን! አሻግረንም አሉ! እሰዬው ስንል በበነጋታው አንዳንድ ፅንፈኞች ብዙ የተነገረላቸው አደባባይ ወጥተው …..

” ነፍጠኛውን እግር እግሩን ሰብረን ” ሲሉን ፣ በእውቁ ዩኒቨርሲቲ አዲሱን ትውልድ ይገራሉ የተባሉ ምሁራን መንደራቸው ወርደው ” ኦሮምኛ ካልተናገሩ አትሽጡም አትግዙም ” ብለው የዋሁን ሕዝብ ሲመርዙም ሰማን፣ ኢትዬጵያዊነትን ሲፀየፉ የነበሩ ባንዲራዋና ክብሯ በዓለም አደባባይ እንዳይሰማ የጣሩ በውጭው ዓለም ወሽመጣችንን የቆረጡትም እድሉን አግኝተው ለዓላማቸው መሳካት የኦሮሞን ወጣት ጓዳው ገብተው በግላጭ አገኙት በማንነት አሰከሩት!! አዲስ አበባም የእኛ ነው አሉን! አስደነገጡንም!

ማንን ከማንስ እንለይ መዘወሪያው በእነዚሁ እጅ ሆኖ ፈርጥመው ሕግን አስታከው አገሬን ብለው በዜዴ ሕልማቸውን ዕውን ያደርጉ ይሆን ብለን ኢትዬጵያን የምንል ኢትዬጵያ ትቀጥል ይሆን ብለን እንደትላንትም ተስፋም ስጋትንም ቢወራረስብን ትዝብትም ሊሆንብን ከቶውንም አይገባም ።

በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይና አመራራቸው ብዙ እጅግ አበራታችና ተስፋ ሰጪ በርካታ እርምጃዎች በመውሰዳቸው ኢትዬጵያዊያን ድጋፋችንን ሰጥተናል።

በውጭው ዓለም በስደት በኖርንበት ወቅት ኢትዬጵያውያን በአገራቸውና በወገናቸው ላይ ይደርስ በነበረው መራር የሰብአዊ መብት እረገጣ የአገሩን አገዛዝ በዓለም አደባባይ ወጥቶ በመቃወም ከአፍሪካ ግንባር ቀደሙን ሥፍራ ይይዛል ምናልባትምትም በዓለም አቀፍ ደረጃም ከቻይና በመለጠቅ ሁለተኛ እንሆናለን የሚል ግምት አለኝ!

ፕሬዝደንት ኦባማ የአፍሪካ መሪዎችን ጉባኤ በአውጳሮውያን አቆጣጠር August 2014 ዋሽንግተን በአደረጉበት ወቅት የ50 አገራት መሪዎች ዋሽንግተንን አጣበዋት ነበር! ቀደም ባሉ እረጅም ዓመታት የሕወኃቱ መሪ የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ስልጣን ላይ በቆዩባቸው ዘመናት ሁሉ ኢትዬጵያዊያን ያለፋታ ወጥተው በየአደባባዩ እንደተቃወሙ ሁሉ በዚህ የአፍሪካ ጉባኤም ኢትዬጵያን ወክለው የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም የመጡ ጊዜ ኢትዬጵያዊያን ከአጎራባች ግዛቶች ጭምር በመምጣት ተቋውሟቸውን አሰምተዋል!

በዚያን ወቅት በአፍሪቃ ቀዳሚዋ ዲሞክራሲያዊ አፍርካ አገር የሆነችው የዲሞክራቲክ ጋና ፕሬዝደንት የነበሩት ፕሬዝደንት ጆንያ ማሃማ በአንድ የዋሽንግተን ሆቴል አርፈው የጋና ባንዲራ እየተውለበለበ የጋና ነዋሪዎች ከሌሎችም ግዛቶች በመቶዎች ሰልፍ ገብተው መሪያቸውን እጅ ለመንሳት መታደማቸውን ከሆቴሉ ሰራተኛ በመረዳቴ በአግራሞት እየተመለከትኩ በአይነሂሊናዬ ከቶዋንም ቅኝ ያልተገዛችዋን ነገር ግን የዜጎች እስር ቤት የሆነችውን እናት አገሬን ኢትዬጵያን አስብኩ በዚህም አገራችን እንዲህ ዲሞክራሲያዊ አገር ሆና የመሪያችንን ቃል ለመስማት የምንጋፋበት ጊዜ ይመጣ ይሁን በሚል በአይነሂሊና አወረድኩ አወጣሁም ! በዚህን ወቅት የኢትዬጵያ ባንዲራ ሆቴል ላይ መሰቀል ቀርቶ በሺዎች የሚገመተውን ተቃውሞ ላለመስማት በተሽከርካሪዎች ላይ የአገርን ባንዲራ ማውለብለብ ባለመቻላቸው ስንደናበር ሳንገጣጠም የአፍሪካው ጉባኤው ተጠናቀቀ!!

ብዙም ሳንቆይ ከጥቂት አመታት በኃላ ሕዝባዊ እምቢተነቱ ፋታ አሳጥቶ የኢሕወኃት/ኢህአደግ አገዛዝ ሊገረሰስ ደርሶ በግለሰቦች ሽግሽግ አገገመና ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ በጥገናዊ ለውጡ በሕወኃት/ኢሕአደግ ይሁንታ ተመርጠው ወደስልጣን በመምጣታቸው የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትርና የድርጅቱም ሊቀመንበር በመሆን በባዕለስመታቸው ወቅት ያደረጉት ኢትዬጵያን ከፍ ያደረገው ንግግርና የገቡት ቃል ይህንንም ተከትሎ የወሰዷቸው እርምጃዎች ተስፋን አሰነቀን!

ይህም በመሆኑ እንደ ጋናና አንዳንድ ጥቂት የአፍሪቃ አገሮች ሥርዓታዊ ለውጥ መጥቶ በፈቃዳችን መሪ ለመምረጥ ባንታደልም ኢትዬጵያዊያን ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ይህንን መንገድ በቅንነት ይከፍቱልን ይሁን በሚል ድጋፋቸውን በየተገኙበት በነቂስ ወጥተው ሰጥተዋል! ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አሜሪካን አገር መጥተው በተለያዩ ግዛቶች በተዘዋወሩበት ወቅት ኢትዬጵያዊያን በሌሊት ወጥተው ተሰልፈው አዳራሽ የመግባት ዕድል ያገኙትት በሕዝብ የተመረጡ ያክል ድጋፋቸውን በተመሳሳይ ሰጥተዋል! ተስፋቸውንም ገልፀዋል! ይህ አንድ በጎና ቅን ሃሳብ ይዞ ለተነሳ መሪ ከድርጅት ወገንተኝነት ወጥተው አገርን ወደ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ ሥርዓተማህበር  ለማሻገር እጅግ ከፍተኛ አቅምና ግዙፍ ስንቅ ነው።

ከዚህ የሕዝብ ድጋፍ ምላሽ ከወሰድዋቸው እርምጃዎች ተጠቃሽም ከሚሆኑት ቀንደኛ ተዋናዩን ሕወኃት አቅም ማሳጣታቸው ፣ ራዕይው መሪያችን የሚለው አሰልቺ ትርክት ከአየር መውረድ ፣ አገራችንን በዘር ያቧደናት ፅልመተ ቀን የሆነው ግንቦት ሃያ ዕለት አከባበር ከኢትዬጵያችን በለሆሳሱም መታቀቡና መቀሌ መግባቱ ፣ በፍትህ ዕጦት የተሰደድት ወገኖች ትግሉንም በውጪ ያደረጉት በሰላም አገራቸው እንዲገቡ መደረጋቸውቸው ይህንንም ተከትሎ በሕወኃት በሽብርተኝነት የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ፍርድ እንዲነሳ መደረጉ  ፣ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም አመራርና ውሳኔ ተጀምረው የነበሩት እስረኞችን የመልቀቅ ውሳኔ በይበልጥ አድማሱን በማስፋት አምባገነንትን በምሬት የታገሉ ለፍትህ የቆሙት ከማሰቃያ እስር ቤቶች መለቀቃቸው ፣  የቀደሙ ነገሥታትንና መሪዎች ሥራና ታሪክ እንደ አንድ የአገር ታሪክና ትውፊት ተወስደው ጎልተው ለሕዝባችንም ለዓለማችንም በይፋ ቅርስ መሆናቸው ወዘተ..  ብዙዎቻችንን አርክተዋል ተስፋም አሰንቀውናል ።

በዚህ ሁሉ ጭላንጭል ውስጥ አገራችንን ሰንጎ የያዘው አለመረጋጋትና የማንነትና ክልል እንሁን  ጥያቄዎች መጦዝ  ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ አገር ውስጥ የገቡ ታጣቂዎች የራስ ገዝ ስፍራዎችን ይዘው የአገርን ሰላም ፀጥታ መንሳታቸው ፣ ክልል መንግሥታት ከፌዴራሉ አቅም ባላነሰ ( ገደብ ሳይኖር ) ጦር መታጠቃቸውና በሺዎች ልዩ ኃይል ማሰልጠንና መፈርጠም፣ የአንድ አገረ መንግሥት ተቀዳሚ ተግባር የሆነውን የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ለማስጠበቅ መንግሥት ደካማና ዳተኛ መሆን፣ የማዕከላዊው መንግሥትና የዋና ከተማችን አዲስ አበባ ጨምሮ አንዳንድ ከፍተኛ ወታደራዊ ፣ የደህንነት ተቋማት የፍትህና መንግሥታዊ ቁልፍ ኃላፊነቶች ፣የዲፕሎማትክ ኃላፊነቶች ጉልቻ ቢቀየር ዓይነት ትላንት በተለያዩ ቦታዎች በአገዛዙ ውስጥ ቁልፍ ሚና የነበራቸው ዕውቀትንና ብቃትንም ባላሟሉ በአካባቢ ወይም በድርጅት ማንነት መመመዘኛ ብቻ  ወዘተ ..ኃላፊነት እንዲይዙ መደረጋቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው።

ይህ ሁሉ ሆኖ አገራችንን ዛሬ ላይ ሆነን ስናይ የተጀመሩት መልካም አገራዊ ውጥኖች ይሳኩ ዘንድ ምኞታችን ሆነው ከፊታችን የተደቀኑብንም ችግሮች ብዙ ናቸው! በገጠመን የወረርሽኝ አደጋ ስጋትና በአገራችን አንዳንድ አካባቢዎች አለመረጋጋት አኳያ የሚታዩት አገራዊ ቅራኔዎች ጡዘት ሳቢያ ስጋትን ያንዣበበው አገር አቀፍ ምርጫ በዕንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዳይሆን መተላለፉም ለአገራችንና ለሕዝባችን ሰላም ትልቅ አጋጣሚ ነው።

በሁኔታው አስገዳጅነት ምርጫው በመተላለፉ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መንግሥታዊ የአገዛዝ ዘመን በአስገዳጅ ሁኔታ እንዳይገፋ እነርሱ የፃፉት ሕገ መንግሥት በጦርነትም ይሁን በወረርሽኝ የገዥውን መንግሥት ዕድሜን ስለማራዘም የተደነገገ ምንም አንቀፅ የለም! በሕገመንግሥቱ መግቢያ “አንቀጽ 9” መንግሥት ሥልጣን

የሚይዘው በሕዝብ ምርጫና በዚሁ ሕግ ብቻ ነው የሚተካው ይላል።

ይህ በርግጥም አጋጣሚው በፈጠረው ክስተት ያለምንም ማጋነን ሕገመንግሥታዊ ቀውስ ማስከተሉ ” Constitutional cries ” ማሆኑ እሙን ነው።

በሕወኃት/ኢህአደግ ያለምንም የሕዝብ ይሁንታ የተረቀቀው ሕገ መንግሥት 27 ዓመት በአገር ላይ ቀውስ ማስከተሉ በርግጥ እውን ሆኖ ዛሬ ደግሞ ይኽው ሕገመንግሥት ከአምስት ዓመት በዘለለ የአገዛዙን ዘመን ስለመጨመር የጠቀሰ ግልፅ ድንጋጌ አለመኖር ” ለሕገመንግሥታዊ ቀውስ ” ውስጥ እንደዳረገን ለመረዳት የሕግ ሰው መሆንን ከቶውንም አይጠይቅም ፤ ይህንንም ተከትሎ ሁሉም የራሱን መፍትሔ ቢሻም ቃሉ በሕገመንግሥቱ ከቶውን ባልሰፈረበትና ባላወዛገበበት ሕገመንግሥት ትርጓሜ ፍለጋ ተብሎ ወደ ፌዴሬሽንና ምክር ቤት በጠቅላይ ሚኒስትሩና በአገዛዛቸው መላኩም አጠያያቂ ሂደትም ነው!

ውድ ኢትዬጵያዊያን!  ይህንን የተመለከተው የተወካዬች ምክር ቤት የራሱን ጉዳይ እራሱ ለመመልከት ከ 547 መቀመጫ ውስጥ ብቸኛው ገዢው ኢሕአደግ (ብልፅግና)  512 ወንበር ሲይዝ እራሱን የነጠለው ሕወኃት 35 ወንበሮች የያዘ በመሆኑ ብልፅግና ራሱ የሌሎችን ባለድርሻ አካላት አማራጭ ለመስማት ገለልተኛም አለመሆኑን ልብ ልንል ግድ ይላል! ይህንኑ ፈለግ ተከትሎ በመፍትሔነት ሕገመንግሥታዊ ትርጉም ፍለጋ የተላከለትም የፌዴሬሽን ም/ቤት እነ አስቴር መቆ፣ ካሳ ተክለብርሃን ፍርደ ገምድል የነበሩበትና ሳሬም ተረኛዋ ኬሪያ ኢብረሂም የሕግም መደበኛ እውቀት የሌላቸው የፓለቲካ ተሿሚ ሲሆኑ ሰብሳቢዋ የሕወኃት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ሲሆኑ በሕወኃት ድርጅት ውክልና እዚህ ስፍራ በመሆናቸው የድርጅታቸውን ፈለግ ተከትለው የጠቅላይ ምንስትር አቢይን አገዛዝ አምባገነን ስለሆነ እንደዚሁም በሕገ መንግሥቱ የሥልጣን ዘመኑ አልቆ ሕገመንግሥቱን በመተላለፍ በስልጣን ላይ አገዛዙ ለመቆየት የሚሄድበት መንገድ ልክ አይደለም በሚል ሰበብነት ከፌዴሬሽኑ ውሳኔ በመቅደም መቀሌ እንደገቡ ስልጣን መልቀቃቸው መግለጫ መስጠታቸውን በብዙኃን መገናኛ ተከታትለናል!! ይህ የግል ውሳኔ በንፁህ ሂሊናና የህግ ሚዛን አለመሆኑን ልብ ልንል ይገባል! ከልብ ለፃፉት ሕገመንግሥት መቆም መስዕዋዕት የሚያስከፍል ችግር ከፊታቸው ቢደቀን እንኳን ለዕውነት እራሳቸውን አሳልፈውም ቢሆን ፌዴሬሽን ምክር ቤቱን ቀሪ አመራር አባልትን በማሳመን ውሳኔውን ማስወሰን አልያም ድምፃቸውን በልዩነት በማስመዝገብ በግል እይታቸው በዚህ አስከፊ አገሪቱ በምትገኝበት ችግር መንግሥታዊ ክፍተት እንዳይኖርና ሥርዓተ ዓልበኝነት እንዳይነግሥ አማራጭ የሚሉትን አገርንና ሕዝብን ታሳቢ በማድረግ ኃላፊነት የሚሰማው ዜጋዊ ውሳኔ ባስቀመጡ ነበር ።

አሁንም ይህ ሲመሩት የነበሩት የፌዴሬሽን  ምክር ቤት ገለልተኛ የሆነ  አካልም ከቶውን ሳይሆን! እንደ ተወካዬች ምክር ቤቱ የአገዛዙ የኢህአደግ መንግሥት ( የብልፅግና ፓርቲው ) ቅጣይ በመሆኑ ውጤቱም ብሔራዊ መግባባትን ባገለለ አገዛዙ ራሱን በራሱ ማስቀጠሉ አይቀሬ ነው።

ይህ በቀደሙት ሳምንታት ጀርመን ድምፅ ራዲዬ በርካታ የሕግ ምሁራን ሕገ መንግሥታዊ ቀውስ መከሰቱን አስምረው በውይይቱ ፌዴሬሽን ምክር ቤትና ሌሎችም ገለልተኛ አለመሆናቸውን በስጋት አስቀምጠዋል !  ይህ አገሪቱን በወደፊት በማያባራ የሕገ አልባነት መንግሥታዊ ቀውስ ውስጥ እንዳይከት ስጋታቸውን ምሁራኑ ገልፀዋል ፤ ሌሎችም የሕግ ምሁራን የስርዓቱ አምላኪዎች በባትሪ ተፈልገው በጠቅላይ አቃቢዋ ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ሰብሳቢነት ሕገ መንግሥቱ ውስጥ እንዲሁ ምንም በሌለ አንቀፅ በባትሪ ፍለጋ ገብተው ይህ አንቀፅ እንዲህ ማለት ፈልጎ በሚል የደበዘዘ የሕግ ጥምዘዛ ትርጉም ገብተው ሕግ ለማውጣት ምንም ውኃ በማይቋጥር ሲፈላሰፉም በጥሞና ተከታትለናል።

አንዳንድ የሕግ ሰዎች ደግሞ በሕግ ትርጉም ሕገመንግሥቱ እንዲሁ ከአምስት ዓመትን ገድቦ ለመንግሥት የሰጠ ቢሆንም ምርጫን የማያስደርግ አስገዳጅ ሁኔታ ቢፈጠርም ይህንን አስመልክቶ ምንም በአንቀፆቹ የተደነገገ  ነገር ባይኖርም ቅሉ መንግሥት አልባ አገር ተፈጥሮ ሕገመንግሥቱ “የራሱን ህልውና ለማጥፋት ” አይወስንም ስለሆነም ይልቁንም እራሱን ለማዳን ሲል ምንም መንግሥታዊ ክፍተትና ቀውስ እውን እንዳይሆን መንግሥት ቀጥሎ ሕገመንግሥቱ እራሱ እንዳይወድም ምርጫ እስከሚደረግ ክፍተት እንዳይኖር ( በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ) ጊዜ ለመንግሥት ለመስጠት ይገደዳል ብለዋል።

ሌሎች ገለልተኛ የሕግ ምሁራን ደግሞ አገዛዙ በዶ/ር አቢይ አመራር ምክንያት የቅቡልነት ጭላንጭል የነበረው ቢሆንም ይህ በራሱ መዘውር እራሱን ያለ በቂ የሕግና ገለልተኛ ባልሆኑ አካላት ድምዳሜና ሌሎችን ከቶውን በአገለለ ስልጣኑን ቢያራዝም ቢያንስ የሁሉም ባለድርሻ አካሎች ይሁኝታ አለመኖርና በዚህም ” ብሔራዊ መግባባት አለመኖር” የአገዛዙን ቅቡልነቱን አደጋ ውስጥ እንዳይጥል ልንሰጋም ይገባል ብለዋል ምሁራኑ።

አገሪቱ ዛሬ በገጠማት ብሔራዊ ችግር በተለይም የዓለምን አኗኗር የለወጠው የኮሮና ወረርሽኝ በሕዝብ ሕይወትና ደህንነት እንደዚሁም ይህንን ተከትሎ በማህበራዊና አገራዊ ኤኮኖሚ ዙሪያ ሊከሰት የምችለው ቀውስ እጅግ የከፋ ነው ፤ በሕዳሴው ግድብ ግንባታ ሳቢያ ያጠላው የግብፅ ጣልቃ ገብነትና ምኞት ወዘተ እንደዚሁ በአገራዊ ደሕነታችን ያንሻበቡ ስጋቶች ውስጥ ይህንን የሚመክት ጠንካራ ሙሉ የሕዝብ ቅቡልነት ያለው መንግሥት እንዲኖረን መመኘት ብቻ ሳይሆን የባላንጣችንንም ሞራል ለማሳነስም አንድነታችንን ከምን ጊዜውም በላይ ማጠንከር የግድ ይላል።

እንኳንስ አሁን በምንገኝበት ሁኔታ ቀርቶ ምን ጊዜም ቢሆን መንግሥት ለደቂቃዎችም መቀጠል የለበትም ብሎ ሙግት ውስጥ የሚገባ ማንም ዜጋ አይኖርም!

ይሁንና ይህች አገር የጋራችንም ስለሆነች አገዛዙ እራሱ ቀድሞውኑ ሕጋዊ መሠረት ሳይኖረው እራሱን በራሱ ከመሾም ታቅቦ ሁሉም ” ባሉድርሻ አካላት ” ( Stakeholders ) የጋራ መድረክ አመቻችቶ ያለውን ነባራዊ ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ  በብሔራዊ መግባባት የአገዛዙን ዕድሜ መጨመር ለሥርዓተመንግሥቱ ሙሉ ተቀባይነት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ሁላችንም ግድ ሊለንም ይገባል ፤

 

በመሆኑም በቅሬታ ያልተወጠረ መንግሥት ከምን ጊዜውም በላይ እንሻለን! ከአንድ ወገን ብቻ የምንጠብቀው ሳይሆን በቅንነት፣ ሁሉም ወገን አገርንና ሕዝብን በማስቀደም ከምንግዜውም በተሻለ ጠንካራ ሕብረት ያጠሉቡንን አደጋዎች በብቃት ለመመከትም በድልም ለመሻገር የግድ የተናበበ አንድነት እጅግ አስፈላጊ ነው!!  ለአገር ጠቃሚ ይሆናሉ ተብለው የታመኑ የማናቸውም አማራጭ ሃሳቦች ለሕዝብም ይሁን ለመንግሥት ይፋ መደረጋቸው እንደ ስጋት ሊታዩ አይገባቸውም ይልቅ ሃሳቡን መሞገት ሲገባን ጦር የተሰበቀ ያክል የግለሰቦችን ስዕብና መንካትና አልፎም ማስፈራራት ትዝብት ከመሆኑም በሌላው ጉራ በሰላማዊ ዜጎች ምትክ የሌለው ዕልፍ ሕይወት ሳይጠየቅ ዛሬም እንደፈለገ የሚሆንን፣ ሌሎችም በአደባባይ ጥላቻን በህዝብ መኃል ሲነዙ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ሆነና ሰላማዊና ገንቢ አማራጭ ( ሃሳብን) እንደ ጦር መፍራት ቃልን ማጠፍና ስልጣን ወደፊትም የህዝብ የመሆንን ተስፋ የሚያደበዝዝ ክስተት ስለሆነ ኢትዬጵያዊያን በተለይ የአንድነት ኃይሉ የምር ልብ ብሎት ሊገደውም ይገባል።

ይልቁንም ቀድሞውንም ሥልጣንን በሕዝብ እውነተኛ ድምፅ ያልጨበጠው መንግሥት ብሔራዊ መግባባትን መድረክ አመቻችቶ የገጠሙንን ችግሮች በፓለቲካዊ ውሳኔ እንዲፈቱ መድረክ ማመቻቸት ፣ ብልህነት የተሞላው  አገራዊ እርምጃ ሊሆን ሲገባው ይህንን አማራጭ መንንድ አሁንም ቆም ብሎ ለማየት የዘገየ አይሆንም፤

የሚመቻቸው ብሔራዊ መግባባትን መሠረት ያደረገ መድረክም አገራችን የገጠማትን ችግር ለመፍታት በጥሞና የምንመክርበት ከፊታችን የተጋረጡብንን ችግሮች ለማለፍ አሁን ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት የሁሉንም ይሁንታ አንኝቶ አቅምና ብርታት ኖሮት እንዲቀጥልና አገር እንዲመራ በባለሙያተኞች የተገመተ የአገዛዝ ዕድሜ መስጠትና በጋራም ለስኬቱ መረባረብ ግድ ይለናል ።

ይህም ሲሆን ጠንካራ ጎኖች በበይበልጥ እንዲጎለብቱ መሰናክል ሆነው መንግሥታዊ ቁመናን ያሳጡትን ድክመቶች በጋራ መለየትና ከፊታችን የተደቀኑብንን ችግሮቻችን ለመወጣት የሚመጥኑ የጋራ መፍትሔዎች በማስቀመጥ  ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እስካሁን በሰጡት ብልህ አመራርና በኖቨል የሰላም ሽልማት የአገኙት ሞገስ ለአገራችንም ሞገስ በመሆኑ በጠቅላይ ሚኒስትርነት አገራችንን በጀመሩት መንፈስ እንዲመሩት የሚያምኑባቸውን ካቢኒያቸውን እንደያዙ ሌሎች ጢቂትም ቢሆኑ በፓለቲካ ተሞክሯቸው ፣ በልምድና በዕውቀት የበለፀጉትን ማካተት፣ በውጭ አገራት ካሉት አዋቂና አገር ወዳድ ምሁራን በሙያ ዘርፋቸው በምጣኔ ሀብት፣ በሕዝብ አስተዳደር ፣ በምህንድስና ወዘተ..ባዕድ አገራትን እያገለገሉ  ያሉትን ምሁራን ማካተትና በሙያቸውም በተለያዩ ዘርፎች የዶ/ር አብይን መንግሥት በአቅም መደገፍ በይበልጥ ጉልበት በመጨመር አገዛዙ የሚታይበትን ጉድለት መሙላትና ለእውነተኛ ሽግግርም ጥሪጊያ መንገድን ማመቻቸት የግድ ይላል ።

ይህ እርምጃ በዋነኝነት ግቡ የስልጣን መጋራት ጉዳይ ሳይሆን አቅምን የመደገፍና (ለቀጣዩ ምርጫ ምህዳሩን ለማስፋትና) በተለይም ነገን ብሩህና ግልፅ ለማድረን በገቢር ነፃ የዲሞክራሲ ተቋማትን ለማዋቀር አንበሳውን ድርሻ አንደኛው ባልተቆጣጠረበት በየደረጃው በፍፁም ገለልተኝነት ማደራጀትን ግብ የአደረገ ነው!

ይህም አሁን ያለው አገዛዝ ከአንድ ዓመቱ ተጨማሪ የመንግሥት ዕድሜ በኃላ ለተጨማሪ አንድ ዓመት ጊዜ የሚቆይ በጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ቀጣይነትም የሚመራ ከላይ የተጠቀሱ ግቦችን የሚያሳካ

የእርቅና ብሔራዊ መግባባት ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት ” መመስረት አንድ ፍቱን አማራጭ ነው።

ይህም ማለት ከላይ እንደተጠቀሰው በባለድርሻዎች ተሳትፎ ውሳኔ አሁን ያለው መንግሥት (አንድ ሙሉ ዓመት) ዕድሜ ይሰጠውና ከገጠሙን ችግሮች በሁሉም እርብርቦሽ እንደወጣን (ከዓመት በኃላ ፤ ወይም የጤና  ሙያተኞች በወቅቱ በሚሰጡት ምክረሃሳብ ) በቀጣይ የሁሉም ወገን ቅቡልነት ያለው በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራ ጠንካራ የሆነ ጊዚያዊ የሽግግር መንግሥት በነበረበት ማስቀጠልና እውን ማድረግ የግድ ይሆናል ።

በዚህ እውነተኛ የሽግግርር ዘመን በውዝግብና እርስ በርስ ቅራኔዎች የተወጠረችውን አገር እንደ ደቡብ አፊሪካ ከዘረኝነት ሥርዓት ሲሻገሩ እንዳደረጉት

የእርቅና ሰላም አገር አቀፍ ጉባኤ ” በየደረጃውም ጭምር በማካሄድ የሚታዩ ውጥረቶችንና ልዩነቶችን በቅድሚያ ማርገብና ለአገር አንድነትና ለሕዝብ ሰላም ሲባል በጥልቀት ታድሶ ማካሄድ ግድ ይላል ፤ ለእውነተኛ ምርጫ ወሳኝ የሆኑትን የድሞክራሲ ተቋማት ሕግ ተርጓሚውን፣ ሕግ አስከባሪውን ገለልተኛ በማድረግ ፣ ምርጫ ቦርድን ከላይ እንደነበረ ይዞ እስከ ታችኛው አካል ድረስ ወዘተ ከቀድሞው ኢህአደግ ጥርነፋ ነፃና

( Transparent ) በሆነ መልኩ በአዲስ መልክ ማዋቀር ፤ ” ሕገመንግሥቱ ” ብዙ ችግሮች ቢኖሩትም ካስፈለገ ለጊዜውም ቢሆን ለሕዝብና ለአገር አንድነት መጠንከርና ለሰላም መስፈን በሚበጅ መልኩ (በሁሉም ሙሉ ውሳኔ) ትንሽ ማጥራትና የሽግግር ዘመኑ እጅግ ሰላምና የተረጋጋ  ከውዝግብ የፀዳ ይሆን ዘንድ አጨቃጫቂ ድንጋጌዎች ውስጥ ሳይገባ ለአገር አንድነትና ለሕዝብ ሰላም ባልተመቹ  ክፍሎች ላይ ማሻሻያዎች ማድረግ  ይቻላል።

አጠቃላይ ሕገመንግሥቱን ክፍሎች በሽግግሩ መንግሥት ዘመን ሙሉ ማሻሻያ ማድረግ ውዝግብ ካለው በቀጣይ በምርጫ ሂደቱ ድርጅቶች በሚያስቀምጧቸው የሕገመንግሥትና መንግሥታዊ ቅርፅ ሰነዳቸውን ለሕዝብ ይፋ አድርገውና አስረድተው በነፃ ምርጫ አሸናፊ የሆኑት በሚመሠረቱት የሕዝብ መንግሥት ተወካዬች ምክር ቤት በጥልቅ ውይይት ረቂቅ ሰነድ መነሻ በሕዝበ ውሳኔ ሙሉ ሕገመንግሥታዊ ማሻሻያ ማድረግ ይቻላል።

የሕገመንግሥት ሙሉ ማሻሻያ በሽግግር ዘመኑ ማከናወን ይገባል ብለው የምያምኑና የሚከራከሩ ይኖራሉ! በርግጥ ይህ በኢትዬጵያ አንድነት ኃይሎች በኩል ስምምነት ቢኖረውም በዜውጌዎቹ ድርጅቶች በኩል ትልቅ ተቃውሞ እንደሚገጥምና በሽግግር ዘመኑ ዋነኛ ግብ ( Ultimate Goal ) ለአገር አቀፍ ምርጫው ተቋማት ግልፅና ተጠያቂ የማድረጉን የጋራ ሂደት የሚያውክ ማናቸውም ውዝግብ ውስጥ ከሚከቱ ጉዳዬች መቆጠብና በዚህም የሽግግሩን ዘመኑን ሰላማዊ ማድረግ ፣ በዚህ ሂደት ምርጫውም በመላ አገሪቱ ክልሎችና ቀበሌዎች (ሰላማዊ) እንዲሆን ሁሉም ድርጅቶችና ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት እንዲሸከም ማድረግ ነው!

እነዚህ ቅድመ እርምጃዎች ለነፃና ፍታዊ ምርጫ ወሳኝ በመሆናቸው በሙሉ ልብ ተግባራዊ በማድረግ በአገራችንም በአፍሪካም አርዓያ ሊሆን የሚችል ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች የሚገኝበት ነፃና ሰላማዊ ምርጫ ማድረግ ይቻላል።

በዚህም ከእኛ በኃላ ከቅኝ ግዛት ነፃ የሆኑ እንደ ጋናና መሰል ጥቂት የአፍሪካ አገሮች ወደ ደረሱበት የዲሞክራሲ ምዕራፍና ላይ አገራችንን ማሻገር በሚገባ ይቻላል።

ውድ ወገኖች!! የዚህ ሁሉ ጭንቅ እንዲሁ ለኮፍ በማድረግ ዛሬ ላይ ሆነን እንደዚሁ ወደ ምርጫ በመግባት ሕዝብን ባለቤት የማያደርግ አገዛዝ ለማምጣት መጣደፍ የለብንም ይልቁንም በጥሞና ለዕውነተኛ ሽግግር የሚያደርሰንን ብሔራዊ ፍኖተካርታ ( Roadmap ) በቅድሚያ መንደፍ የግድ ነው።

ይህ በእጃችን በሌለበት እኔ አውቅልሃለሁ አሻግረሃለሁ ከሚል ግብዝ ስሜትና እምነት ወጥተን ሁሉም ምርጫውን ሰላማዊና በተለይም ታአማኒ ለማድረግ አሻራውን የሚያሳርፍበት የሽግግር ሂደት እንዲኖር በማድረግ እጅግ የተሳካ አገር ዓቀፍ ምርጫ ማድረግ ይቻላል።

በጥድፊያ ገብተን መራጮች ወከባ ደረሰባቸው ፣ ድምፅ ተሰረቀ፣ ኮሮጆ ተገለበጠ ፣ እዚህ ክልል ጨፍላቂ አንድነት ድርጅት ናችሁ በመባል መግባት ተከለከልን ወዘተ… በሚል ክስና ዕሮሮ ሳንወዛገብ አንፃራዊ ሰላምን በማረጋገጥ የተሻለ ነፃና ዲሞክራሲያዊ ምርጫ እውን ማድረግ ይቻላል።

አሁን ያለው መንግሥት ባለድርሻ አካላት ( Stakeholders ) ታክለውበት (የዕርቅና ሰላም ሽግግር መንግሥቱንም  እየመራ ዲሞክራሲያዊ ተቋማትን በየደረጃው በስኬት ለማዋቀር አስፈላጊ መሆኑ ታምኖበት በቂ ጊዜ ቢወስድ እንኳን ውጤታማ ለመሆን እስከሆነ ሊያሳስበን የሚገባ አይመስለኝም !

ምክንያቱም በአዋጅ በሚቀመጥ ድንጋጌ ሁሉም ስልጣን ለመቀራመት ያለመ ሳይሆን ይልቁንስ በዕውነተኛ ምርጫ የሕዝብ መንግሥት ዕውን ማድረግ ነው ትኩረት የሚሆነው።

እንደዚህ ዓይነት በቂ ጊዜ ማግኘች እንዲያውም አንድነት ኃይሉ ከየትንንሽ ድንኳኑ ወጥቶ በግንባር ፣ በቅንጅትና ከተቻለም (በውህደት) አንድ ወይም ሁለት ጠንካራ ዕውነተኛ ተፎካካር አገር አቀፍ የአንድነት ኃይል ለመፍጠርና የተበታተነውን ትግል ለማማከል በአቅምም ገዥውን ብልፅግናን ለማሸነፍ ብሎም ሰፊ የፓርላማ መቀመጫ ለማግኘት ሰፊ አስተማማኝ ዕድል ይሰጣል።

ጎበዝ እንዲህ ዓይነት ሰፊ ሁሉን አሳታፊ እርምጃ ብንወስድና ምሕዳሩን ማስፋት ቢቻል በብዙዎቻችን ውስጥ የገባውን ስጋት በእጅግ ይቀንሳል! የሕዝብ ድምፅም በተገቢው ይደመጣል፣ የራሱንም መሪዎች ለመምረጥ ሰፊ ዕድል ያገኛል፤

ይህ ባልሆነበት ኢህአድግ አሁን ውስጡን ሳይሆን ስሙን አስውቦ በሰየመው ( ብልፅግና ) ፓርቲ ሰንጎ በያዘው መዋቅር፣ እንደዚሁም በውል መንግሥትንና ፓርቲን መለየት በሚያዳግት ውስብስብ ቁመና ፣ የመንግሥትን ሎጅስትክስና ሃብት እንደፈለገ በያዘና ለጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ ለራሱ እንኳን በአግባቡ የማይታዘዙት በየደረጃው የሚገኙት የቀድሞው የኢህአደግ አካላት ፣ ዘርን መሰረት ያደረጉ ክልላዊ መንሥግስታዊ አገዛዝ ቁጥጥር ሥር ነፃ ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ ምርጫ ማድረግ ከቶውንም የማይታሰብ ነው።

እንዲያውም በዘውግ ፌዴራዝልምና በአንድነት ኃይሎች መንግሥታዊ የፌዴራል አወቃቀር መካከል በሚደረግ የምርጫ ቅስቀሳና የድምፅ አሰጣጥ ሂደት ደም አፋሳሽ ውዝግብ መኖሩ አይቀሬ ነው።

በዚህ ረገድ በተለይም ኢትዬጵያን የሚለው የአንድነት ኃይል ማናቸውም የግልም ይሁን የድርጅትን ሥልጣን ማለትም እራሱን እዜማ ፣ አብሮነት ፣ ባልደራስ ፣ አብን ወዘተ.. ከሚል አባዜ ወጥተን አርቀን ማሰብና ኢትዬጵያችንን ወደ እውነተኛና ፍታዊና ዲሞክራሲያዊ አገርነት ማሻገሩ ላይ ልናተኩር ይገባል እላለሁ ።

በዚህ ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እኔ አሸጋግራችኃለሁ ያሉት እምነት ልጣልበት የማይችል መሆኑን በቅን ልቦና ታሳቢ በማድረግ ከፊታችን የተጋረጡብንን አደጋዎች በአንድነት ቆመን መጋፈጥ የሚገባን በመሆኑ ቢቻል ገዥው መንግሥት ሁሉም ባለድርሻ አካላት አታስፈልጉንም ፣ አያገባችሁም ከሚልና ሌሎች አማራጭ ሃሳቦችን እንደ መንግሥታዊ ስጋት ከማየት ግብዝነት  በመቆጠብ ይህች አገር የሁሉም መሆንዋን ተገንዝበው ከላይ እንደተጠቆመው ሁሉም ባለድርሻ አካላት በአንድ ሰፊ መድረክ በጥሞና ተቀምጠው አገሪቱን አሁን ለገጠሟት ችግሮች የጋራ መፍትሔ ለመሻት የብሔራዊ መግባባት (National Dialogue ) ሊፈጥር የሚያስችል የምክክር ጉባኤ በአስቸኳይ ማዘጋጀት ይገባል! ይህንንም ጉባኤ ከሁሉም ገለልተኛ የሆኑ ክፍሎች እንዲመሩት ማድረግ ይቻላል!

የዚህ አቢይ ዓላማውም አሁን የአለው መንግሥት በሕገመንግሥቱ መግቢያ ( አንቀፅ 9 ) ድንጋጌ የተቀመጠው 5 ዓመት  የአገልግሎት ዘመን የፊታችን መስከረም የሚያበቃ ስለሆነ አገሪቱ በገጠማት የኮሮና ወረርሽኝ ሳቢያ ምርጫ ማካሄድ ባለመቻሉ የጋራ ፓለቲካዊ ውሳኔ በመስጠት አንድ ዓመት ወይም በጤና ባለሙያዎች ግምታዊ ጊዜ በመውሰድ ተጨማሪ የስራ ዘመን ማራዘምና በዚሁ የጋራ መድረክ ከሌላ ተጨማሪ (አንድዓመት) በኃላ ወደ አገር አቀፍ ምርጫ ከመካሄድ በፊት የእርቅና ሰላም የሽግግር መንግሥት እንደሚካሄድ በጋራ ስምምነቱ መነሻነት ዋስትና እንዲሰጥ በልዩ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መደንገግ ይህንኑ የብሔራዊ ዕርቅና ሰላም የሽግግር መንግሥት ጉባኤውን ከወዲሁ ኃላፊነት ወስዶ የሚያመቻች ልዩ ገለልተኛ ኮሚሽን መሰየም በተመሳሳይ በልዩ አዋጅ ማካተትና መደንገግ ይገባዋል

አንድ ዓመት ተጨማሪ የስልጣን ዘመን የተሰጠው የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አገዛዝ የጀመራቸውን ውጥኖችንና ተግዳራቶች ትኩረት ሰጥቶት እንዲረባረብ ሰፊ ዕድል ያገኛል! ይህንንም ለማሳለጥ ሁሉም አካላት መንግሥት እንደ አስፈላጊነቱ በሚያወጣው መርሃ ግብር በዘመቻ መልክ መንግሥትንና ሕዝብን ለመርዳት ርብርቦሽ ይደረጋል ፤ ከላይ እንደተጠቆመው አሁን ያለውን የዶ/ር አቢይ መንግሥት ከፊታችን የተጋረጡብንን ችግሮች ፈር ለማስያዝ ይቻል ዘንድ ሌላ ፓለቲካዊ ውዝግብ ሳይኖር በሙሉ አቅሙ ይሠራል ማለት ነው።

የብሔራዊ እርቅና ሰላም የሽግግር መንግሥት ጉባኤ ዝግጅት የተቋቋመው ገለልተኛ ኮሚሽን በጎንዬሽ ሙሉውን ዓመት እራሱን ችሎ በዝህ መጠነ ሰፊና ወሳኝ ጉዳይ ላይ በጥልቀት እየሰራ ጉባኤ በማመቻቸትና በማሳካት ሥራ ይቀጥላል።

በመንግሥት በተወጠነው መርሃግብር መሠረት ሰፊ በሕዝባዊ ርብርቦሽ በማድረግ ኮሮና በሽታው ሊያስከትል የሚችለውን ቀውስ እጅግ ለመቀነስ መሥራትና በድል መሻገር ፣ የአገር ሉዓላዊነትንም በተመለከተ በተጠንቀቅ ሁሉም ዜጋ ዘብ እንደሚቆም ሂሊናዊ ዝግጅት ማድረግና የሕዳሴውን ግድባችንን ቢቻል ከሽግግር መንግሥት ምሥረታው በፊት እውን ማድረግ፣ በኃላም በዚህ ከባድ ችግር በኤኮኖሚያችን ላይ የደረሰውን ጉዳትና ማህበራዊ ቀውስ ለመፍታት የመልሶ ማቋቋም ዘመቻ መላውን ሕዝባችንን፣ ባለሀብቶችን፣ ዓለም አቀፍ ኃያላን መንግሥታትም በዚያን ወቅት ከራሳቸው ቀውስ ስለሚያገግሙ አንድ ወጥ የኤኮኖሚ ዕርዳታ ልገሳን የሚያስተባብር ልዑክ ማዘጋጀት፣ እንደዚሁም የሬድኤት ድርጅቶችን ሙድረስ ወዘተ.. ያሳተፈ ሁሉ አቀፍ ተሳትፎና መርሃግብር ማውጣትና ማሳካት ፤ አገር አቀፍ ምርጫውንም ለማድረግ ጭምር ከፍተኛ ገንዘብና አቅምን የሚጠይቅ ስለሆነ መልሶ ማቋቋሙ ቅድሚያም የሚሰጠው ምትክ የሌለው አንድ ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫ ይሆናል።

(ማጠቃለያ)

ከላይ በተቀመጠው ግርድፍ ፍኖተ ካርታ ለአንድ ዓመት አሁን የገጠመንን ቀውስ በመንግሥት መሪነት መወጣትና አገሪቱን ማረጋጋት ፣ ከዓመት በኃላ የእርቅና ሰላም የሽግግር መንግሥት ምሥረታ ጉባኤ ማካሄድና ፣ ለአንድ ዓመት የሚዘልቅ የሽግግር መንግሥት መመስረት፣ ሁሉንም አሳታፊ ሕወኃትንም ሊያካትት በሚያስችል መርሃግብር  አገሪቱን ለዘመናት የገጠማትን መጠነ ሰፊ ቅራኔዎች ዋነኛ የሆኑትን በመለየት የእርቅና ሰላም ውይይት በየደረጃው እስከ ክልሎች ድረስ ማካሄድ ቅራኔዎችን መፍታት  ለተረጋጋ የሽግግር ሂደትና በተለይም ለሃገር አቀፍ ምርጫው ሰላማዊ መደላድል መፍጠር ፣ ለምርጫው የሕዝብ ውክልናን ለማስላት ጎንዬሽ ( የአገር አቀፍ የሕዝብ ቆጠራ ማካሄድ ) ሥራ ይከናወናል ፣ የተመሠረተው የሽግግር መንግሥት የምርጫ ቦርድ የሚያወጣውን የአገር አቀፍ የምርጫ ጊዜ ሰሌዳና መርኃግብር በመመርመር ማፅደቅ ፣ በዚህ የሽግግር መንግሥት ዘመን ተቀዳሚው ሥራ ( መንግሥት አገር ይመራል ) በሽግግር መንግሥቱ የተካተቱትን በተመለከተ መንግሥት ይረድኛል በሚላቸው ተቋማት ሙያዊ ድጋፋቸውን መጠቀም ሲችል በአብዛኛው  የድሞክራሲ ተቋማትን  (ሕግ ተርጓሚውን አካል) ጨምሮ በገለልተኝነት ከምርጫ ቦርድና ከመንግሥት ተወካዬች ጋር በመቀናጀት በየደረጃው እስከ ክልሎችና ምርጫ ጣቢያዎች ድረስ ማደራጀትና ማዋቀር ፣ ያላዳላ ነፃ ክርክር መድረኮች እውን እንዲሆኑ የመንግሥት የሚዲያ ተቋማት በሙሉ በአንድ ነፃ ኤጄንሲ ስር ከሽግግር መንግሥቱም በገለልተኝነት በልዩ ማደራጀት ፣ መራጮች ምዝገባ ማድረግ ፣ ፓለቲካ ድርጅቶችን የክርክር መድረኮች ማዘጋጀት፣ አስፈላጊው የሽግግር መንግሥቱ የደህንነት ጥበቃ በማድረግ ፓለቲካ ድርጅቶች ሕዝብ ዘንድ ወርደው እቅዶቻቸውን መግለፅና ይፋ የቅስቀሳ ዘመቻ በፈቀድባቸው ቦታዎች ሁሉ እንዲያደርጉ በቂ ድጋፍ መስጠት፣ ገለልተኛ የምርጫ ታዛቢዎች መምረጥና መጋበዝ! በአገር ቤት ለሚገኙ ታዛቢዎች የምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ስልጠና ይሰጣል። በመጨረሻም በአገር አቀፍ ደረጃ የድምፅ አስጣጥ ሂደት ይካሄድና አሸናፊዎች ከግማሽ በላይ ያገኘ ከሌለ ከሌሎች ጋር ጥምር መንግሥት በይፋ መመሥረት ይሆናል።

ውድ ወገኖች!!

ከላይ በግርድፍ ለማሳየት እንደተሞከረው በፈርጅ ፈርጅ መርሃ ግብር በማውጣት የሽግግር መንግሥቱ ዋነኛ ግብ የሆነው ምርጫውን ታዓማኒ ማድረግ ፣ አሁን ያለው በዶ/ር አቢይ የሚመራው መንግሥት ስጋቱ በዕርሱ ሥልጣን ውስጥ ጣልጋ መግባትን እንደመሆኑ የሽግግር መንግሥቱ ያስፈለገው ለመጪው ምርጫ ምቹ ዲሞክራሲያዊና ነፃ መደላድል ማመቻቸት እስከሆነ  ምርጫውን በራሱ መዳፍ ለሌላ ፍላጎት እስካልፈለገ ድረስ የሽግግር መንግሥቱን ከቶውንም እንደ ስግጋት ሊመለከተው ይገባል ብዬ አልገምትም ።

ውድ ኢትዬጵያዊያን እንዲዚህ ያለ የአፈፃፀም ፍኖተ ካርታ ዕውን ባልሆነበትና ሥራ ላይ ባልሆነበት በመሬት ላይ ከሚታየው ነባራዊ ሁኔታ አኳያ እጅግ አስቸጋሪና ፈታኝ ነው የሚሆነው።

በአንዳንድ ክልሎች በተለይም በኦሮሚያ ክልል ከሁለትም ሶስት ጊዜ በሺዎች ልዬ ኃይል ማሰልጠንና ማስመረቅ በጦርና ትጥቅ መደለብ፣ አንዳንድ ፅንፍ የረገጡ መሪዎች ድብቅ አጀንዳና ተልዕኮ! በአገዛዙ ከፍተኛ አካላት ውስጥ ኢትዬጵያ ጠል ግለሰቦች ለምሳሌ በለንደኑ የኦሮሞ ፅንፈኞች ስብሰባ ላይ እነ ጃዋርና ፀጋዪ አራርሳ፣ ፕሮፌሰር እዚቄል ጋቢሳ በጠሩት ስብሰባ ሊበል ዋቆ ዓይነት ” ኢትዬጵያ ትበጣጠስ ከፈለገችም ትጥፋ”  ብለው ጥላቻውን ሲገልፅ አዳራሹ በሞቀ ጭብጨባ ድጋፉን የሰጡለት አይነት ግለሰቦች በመንግሥት ፕሬስ ድርጅት ውስጥ በተሰገሰጉበት፣ ልጅም በተመሳሳይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢሮ ውስጥ ቁልፍ መንግሥታዊ ቦታ በምትሰራበት ፣ እንደዚሁ በርካታዎችም ተመሳሳይ ግለሰቦች ቁልፍ ወታደራዊና ድህንነት እንደዚሁም በፍትህ አካላት መዋቅር ውስጥ መሰግሰግና በሌላ በኩል ሕወኃት ዛሬም ሰላምንና መረጋጋትን ለማናጋት ያለው ሚና ከትግራይ ሕዝብን ፍላጎትን ከመደፍጠጥ አዃያ በሰሞኑ የትግራይ ሕዝቡ በሕወኃት ላይ እያሳየ ያለው ቅሬታ በወደፊት የሚያንዧብቡ አደጋዎችና ስጋቶች ሰፊ ናቸው።

የኢትዬጵያ አንድነት ኃይሎች የተካተቱበት የሽግግር መንግሥት ዕውን መሆን ከኢትዬጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት አኳያና መጭውን ምርጫ በነዚህ ኢትዬጵያን አንድነት በማይሹ ወገኖች እንዳይጠለፍ ላለን ስጋት ይህ የሽግግር ሂደት ዋስትና የሚሰጠን እጅግ አስተማማኝ መሳሪያ ነው።

ውድ ኢትዬጵያዊያን በትልቁ እንዲሰመር የሚያስፈልገው በሽግግር መንግሥቱ ካስፈለገ ማንም ድርጅት ስልጣን አይኑረው ፤ ያለው አገዛዝም ውዝግብ በሌለበት የሽግግር መንግሥቱን ይምራው ፤ ከላይ በተደጋጋሚ ለማስመር እንደተፈለገው ባለድርሻ አካላት (Stakeholders ) በውስጡ ተካተውበት የምርጫ ተቋማትን በገለልተኝነት እስከ ገበሬ ማህበራት ድረስ ማዋቀር ዋናው ተልዕኮአቸውና ግባቸው ሊሆን ይችላል ! በዚህም አሁን በወ/ሮ ብርቱኳን ሚደቅሳ የሚመራው የምርጫ ቦርድና ገለልተኛ ሙያተኞች ታክለውበት በምርጫው ሂደት ሚና ያላቸውን ተቋሟት በማዋቀሩ ደረጃ ድርጅቶችና ሊሂቃን ቁልፍ ሚና ከብልፅግና ፓርቲ ጋር በእኩል ውክልና ማንም አንበሳዊ ድርሻ ሳይኖር በጋራ የሚያቀናጅ መሆኑ ለምርጫው ሂደት ታዓማኒ መሆን ትልቅ ዋስትና  ይሰጣል።

ይህም እውን የሚሆነው በብልፅግና ፓርቲ ይሁንታ ብቻ ሳይሆን የኢትዬጵያ ተቃዋሚ ድርጅቶች የኢትዬጵያን አንድነት ብዙም ግድ የማይሰጡት ዘውጌ ድርጅቶች የኃይል አሰላለፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ በመሆኑ ” አንድነት ኃይሎች ” በብዙ አገራዊ ፓሊሲ ተቀራራቢ ፕግሮግራም እያላቸው በጋራ መስራትና መቀናጀት አልቻሉም!!

አሁን ከትላንት ውድቀትና ጉድለት ተምረው  ከልዩነትና የበርካታ ዓመታት ቂምና የታሪክ እስረኝነት ተላቀው ወደፊት ከመሄድ ሌላ የተሻለ መፍትሔ የለንም ፤ ይህም ሲሆን ሃሳብ አዋጥተው ፣ የጋራ ራዕይ በመቅረፅ  ” አሻግራችኃለሁ ” ከሚል ጭብጥም ዋስትናም ከሌለው በብልፅግና ዲስኩር ከቶውንም መዘናጋት አይገባም!!

በመሬት ከሚታየው በሚታየው እውነታ ዛሬ የኃይል አሰላለፉ ወደ ዘውጌው ያጋደለ መሆኑ ከወዲሁ በማጤን የጋራ ሽግግር ሂደት እንዲኖር በአንድነት መቆም ፓለታቲካዊ ብልህነት ነው።

የጋራ ጥረት ተደርጎ የአገዛዙ እምቢተኝነትና ግብዝነት አሁንም ቀጥሎ ይህ የሽግግር መንግሥት እውን እንኳን ባይሆን የአንድነት ኃይሉ በቂ ጊዜ ስለሚኖረው ከወዲሁ ትኩረት ሰጥቶት አንድ አስተባባሪ አካል በመሰየም በአስቸኳይ የጋራ ግንባር ፣ ጥምረት እንዲያም ውህደት መፍጠር ላይ በማተኮር አቅምን በአንድ በማድረግ ማንኛውንም የአገዛዙን ተፅዕኖ መከላከል  ይቻላል ።

ዓላማችን ሥልጣንን ለመቀራመት ግብ ያደረገ ሳይሆን መጪው ምርጫ ከኢህአደግ ድጋሚ ጥርነፋ ወጥቶ እጅግ ገለልተኛና ሰላማዊ የሆነ ምህዳር በማመቻቸት ” ነፃ ፣ ፍታዊ ፣ ዲሞክራሲያዊና ሰላማዊ አገር አቀፍ ምርጫ ” እውን እንዲሆን ለማስቻል ነው ፣ ይህም እውን ባይሆን በህብረት ተፅዕኖውን ሰብሮ ለመውጣት ይደር ይዋል የማይባል መሳሪያ ነው።

በዚህ ረገድ በተመሳሳይ በቀደመው 27 ዓመት ሕወኃት/ኢህአደግን ለማስወገድ አቅምን በአንድ ማዕከል በማድረግ መታገል አለመቻሉ ብዙ ዋጋ ማስከፈሉና ውጤት አልባ ከሆንበት ውድቀት ልንማርም ይገባል ።

ውድ ኢትዬጵያዊያን ወገኖች !!

የሽግግር መንግሥት ወይም የጋራ መንግሥት ምርጫን አስተማማኝ ለማድረግና በአንድ ወገን የተያዘ መንግሥታዊ አገዛዝ ሚና መልካም ነገሮችን በማሳየት ስልጣንን መጠቅለልና መቀጠል ግቡ እንደሚሆን ለአፍታም ልንዘናጋ አይገባንም!!  የምርጫ ሂደቱን በቀጥታም በተዘዋዋሪ የመዘወሩን ተፅዕኖ ለመቀነስ የታለመ ሲሆን በዚህም በርካታ አገሮች ሰላማዊ ሽግግርን እውን ማድረጋቸውን ከግምት ማስገባት ይገባናል!! በአንዳንድ የዓለም አገሮች ለምሳሌ በኤዥያ ንፍቀ ክበብ የምትገኘዋ በወቅቱ በርማ የምትባል ዛሬ ( Republic Union of  Myanmar) ዓይነት አገሮች በወታደራዊው መንግሥት የሕዝብ ድምፅ በጉልበት ሲነጠቅ ተቃዋሚዎች ከአገር ተሰደው በአውሮጳና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ አሰባስበው (የስደት መንግሥት) መስርተው በኃላ በሃያላን መንግሥታት ግፊት የሽግግር መንግሥት በአገራቸው እንዲመሰረት ተፅዕኖ ፈጥረው አገራቸው በመመለስ ያለሙትን የሽግግር መንግሥት እውን አድርገዋል ፤

በጠላት አገራችን ኢትዬጵያ በተወረረች ጊዜ ቀዳማዊ ንጉሥ ኃይለስላሴ እንግሊዝ አገር ሄደው ለአምስት ዓመት በስደት በቆዩበት የእንግሊዝ መንግሥት ንጉሳዊ ክብራቸውን ጠብቆ ኢዚያው የስደት መንግሥት ( Exile government ) መስርተው የበርካታ አገራትንና የ( League of Nations)  ጭምር ዕርዳታና ዲፕሎማሲያዊ ድጋፍ አግኝተው ወራሪውን ጠላት በአርበኞቻችን መስዋዕትነት ድል አድርገው ወደ ዙፋናቸው ተመልሰዋል ።

እንደዚሁ በሕወኃትን/ኢሕአደግ አገዛዝ ቀኖናው ተሰብሮ የተገፋፉትን የኢትዬጵያ ኦርቶዶክስ ፓትያርክ በመከተል የኢትዬጵያ ስኖዶስ በውጭ አሜሪካ በስደት ተመስርቶ ( ስደተኛው ስኖዶስ ) ትግሉን በማማከል ብዙ ደማቅ ስራዎች በማከናወን በሕወኃት ዘመን እንኳን ስኖዶሱን ለመመለስ ድርድሮች መደረጋቸው የዚህ በስደት በፈጠሩት ድርጅታዊ ተፅዕኖ እንደነበር ልብ ማለት ይገባናል! ለዛሬው ድል ጭምር ደርሶ ጳጳሱ በክብር ወደመንበራቸው መመለሳቸውን የዚሁ ትግል ውጤት ነው።

የአምባገነን የሕወኃት/ኢህአደግ ዘረኛ መንግሥት ለማስወገድ በምርጫ 97 ድምፁ የተነጠቀበት የቅንጅትና ዲሞክራሲ አመራር ከጅምላ የቃሊቲ እስር ቤት እንደወጡ ውጭ አገራት ሄደው በዕርስ በርስ የስልጣን ጥም መላውን ትግል በሁለት ከፍለው አዳክመውታል!! ይልቁንስ በምርጫ 97 በሕወኃቱ ቁንጮ መለሰ ዜናዊ ትዕዛዝ በ197 ንፁሐን ወገኖች ወጣትዋን ብርቄንና ነብዩ ጨምሮ በአምባገነኑ አጋዚ አልሞ ተኳሾች ጥይት  በአንድ ጀምበር ሕይወታቸው በከንቱ ተቀጥፏል ፣ የሺዎች ደም ፈስዋል ፣ ይህ ብዙ መስዋዕትነት የተከፈለበትን ሕዝባዊ አብዬት መቀጨት እልህ ውስጥ የገባውን ሕዝብ ትግል በአንድ ማዕከል መርተውት ለድል ባበቁት ነበር ።

በመሆኑም በወቅቱ አብዛኞቹ የቅንጅት አመራሮች ከመንፈቅ የውጭ አገራት ቆይታ በየመድረኩ ሳይራኮቱ እልህ ቢገቡ ያንን መድረክ ተጠቅመው የውስጡን ትግል የሚመራና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዳፕሎማሲያዊ ሚናም የሚጫወትና ድጋፍም የሚያስተባብር በአንድ ለማድረግ ” የስደት መንግሥት”ወዘተ እንደ አማራጭ መታገያ በመመስረት ሕወኃትን በሕዝባዊ እምቢተኝነት ወደ ሁሉ አቀፍ የሽግግር መንግሥት መመስረት እንዲመለስ የተባበረ ሕዝባዊ እምቢተኝነት በውስጥም በውጪ አገራትም በማቀጣጠል ማስገደድ ይቻል ነበር ።

በወታደራዊ ትግል ሥርዓቱን እናስወግዳለን በሚል በርግጥም ብዙዎች የሞቀ የአውሮጳ ኑሮአቸውን በመተው በሻቢያ መሬት ላይ ወታደር ለማዘጋጀት በግምት በቢሊዬን የሚገመት ዶላር ውጪ ከሚገኘው ሕዝብ ተሰብስቧል! በዚህ ትግል አንድም ፋይዳ ያለው ውጤት አልተመዘገበም! ይልቅ በፕሮፓጋንዳው ኢሳት ራዲዬ የተጫወተው ሚና ካልሆነ በስተቀር ፣ ይህንን ሃብትና የሕዝብ ድጋፍ ትግሉን በማማከል በሕዝባዊ እምቢተኝነት አምባገነኑን ሥርዓት ለማስወገድ ከፅንፈኛ የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር ብቻ ያልተሳኩ ሕብረቶች በመፍጠር ጊዜና በቢሊዬኖች የሚገመት ኦዲትና ሳይኖር በባከነው ገንዘብ ጠንካራ የተባበረ ኃይል መፍጠርና የውጪውን ትግል ከውስጡ ጋር በማቀናጀት ለሦስት ተከታታይ ዓመታት የተካሄደውን ሕዝባዊ እምቢተኝነት ነውጥ አመራር በሚሰጥ የተማከለ አመራር  ዕውነተኛ ለውጥ እውን በሆነ ነበር ።

ከዚያም በፊትም ይሁን በኃላ አንድ የተባበረ ኃይል ዕውን ለማድረግ ብዙ ሙከራዎች ገንዘብና ጊዜ ባክኖ ፍሬ ሳይሰጥ በእርስ በርስ መሻኮት እርባና አጥተዋል ።

ከዚህ በተለየ መንገድ በአዳራሽ ተቀምጦ አመራር በመፍጠር ትግልን ከላይ ወደታች ከማዋቀር ኢትዬጵያ ጉዳይ ያገባናል የሚለውን ነገር ግን ድምፁን አቅቦ የተቀመጠውን ሰፊ ብዙኃን ሕዝብ ( Silent  majority ) የሆነውን ከታች በማደራጀት ወደ ላይ በማዋቀር ትግሉን የሚመራና የሚደግፍም ሰፊ ሠራዊት መፍጠር ነው በሚል ጥናታዊ መነሻነት በወቅቱ ለረጅም ጊዜ እጅግ  የተበታተነውን  ትግል ለማማከልና ለመምራት በተለይም የአገር ውስጡን ትግል በውጭ ለመደገፍ

ሁኔታዎችን ለማመቻቸት ታሳቢ በማድረግ  በአርባ የዓለም ከተሞች ኢትዬጵያዊያንን በማወያየት ጭብጡንም በማስረዳት በበርካታ ቻፕተሮች እንዲመሰረቱ ተደረጉ ! በኃላም ከእያንዳንድ ቻፕተር ሁለት ተወካዬች በአንድ መስራች ጉባኤ እንዲሳተፉ ሁኔታዎች ተተመቻቹ ፤ በመሆኑም ከእስራኤል ፣ ኢንግሊዝ ፣ ጀርመን፣ ሲዊድን ፣ ካናዳ ወዘተ አገሮችና ከአፍሪካ ናይሮቢ ፣ በኡጋንዳና እንደዚሁም ደቡብ አፍሪካ በዚሁ መልክ ከተመሠረቱ ቻፕተሮች ለሁሉም ሁኔታው እንዲመቻች ተደርጎ ቪዛ ችግር የሚገጥማቸውን ከአሜሪካ የውጭ ጉዳይና እንደዚሁ በአየአገሩ ለሚገኙ የአሜሪካ ኤምባሲዎች ደብዳቤ በመፃፍና በማመቻቸት  ጉባኤተኞች ከአሜሪካ 30 ከተሞች ጭምር ተገኝተው ነበር ፤ ከድርጅቶች ጥሪ ተደረገላቸው የሕወኃት/ኢህአደግ ጥሪ ተደርጎ ምላሽ ሳይሰጥ ሲቀር በውጭ ከሚገኙ የፓለቲካ ድርጅቶች ብዙዎች ከላይ ባስቀመጥነው ዓይነት ሳይገኙ ሲቀሩ ጥቂቶች በአሜሪካ ዳላስ ክፍለግዛት በተጠራው ጉባኤው ላይእንዲገኙ በማድረግ ሙሉውን ዝግጅት ተሳትፈዋል።

የዚህ ጉባኤ ሂደቱ በቀጥታ ስርጭት ( Live stream) ከአዳራሹ ውጪ ለሚገኘው ሕዝብ ጭምር እየተሰራጨ የስድስት ቀናት የምክክር ጉባኤ በማድረግ አንድ ስብስብ መስርቶ አመራሮች ሰይሞና የተያዘለትን በጀት በማፅደቅ ጉባኤው ተበትኗል ።

በወቅቱ በሥፍራው የተገኝው የአሜሪካ ድምፅ ራድዬ በስፋት ሂደቱን ዘግቦታል። በኢትዬጵያ ዩኒቲ ( Unity University ) ብቸኛውን የግል ዩኒቨርሲቲ ከፍተው የነበሩት በኃላም በሕወኃትና በመለስ ባለቤት አዜብ መስፍን ተፅዕኖ ከአገራቸው የተሰደድት የህክምና ባለሙያው የነበሩት ፍሰሀ እሸቱ (ዶ/ር) በዚህ በቅድመ ዝግጅቱ ዙሪያ ለኢሳትና አሜሪካ ድምፅ ወዙተ ሚዲያዎች ተከታታይ ቃለ ምልልስ ሲሰጡ የነበሩት በቀዳሚነት ለዚህ ስብስብ መመስረት ጊዜአቸውንና ገንዘባቸውን አፍስሰው በመሪነት በኃላም በስራ አስፈፃሚው አካል ሲካተቱ እንደዚሁ በለንደን ነዋሪ የነበሩት አቶ ስለሺ ጥላሁን በአፈጉባኤነት እንዲመሩት ሲደረግ እኔና ሌሎች ሰባት እንደዚሁ በሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴነት ታቅፈን ነበር ፤ በጉባኤውም ውሳኔ መሠረት የኢትዬጵያ ብሔራዊና ሽግግር ም/ቤት የተባለ

ድርጅት እውን ሆኖ ተመሠረተ።

በዚህም ይኽው ሽግግር ም/ቤቱ በዋሽንግተን ዲሲና ለንደን ዋና ቢሮዎችን አድርጎ ስራውን እንዲጀምር ሁሉም ነገር  ተወስኖና ተመቻችቶ በበርካታ አገራት የምክር ቤቱ በተመሳሳይ በየከተማው ቻፕተሮች ጉባኤ እያደረገ በዚሁ ስም እንዲዋቀር በመደረጉ

የኢትዬጵያ ብሔራዊ ሽግግር ም/ቤት” ( Ethiopian national transitional council ) የሚባል ድርጅት በበርካታ አገሮች ደረጃም  ተመሠረተ!! በነዚህ ቻፕተሮች ባሉባቸው ከተሞች ሙያ ያላቸው አንዳንድ ሰው በብቸኝነት በዲፕሎማሲው መስክ የውክልና ደብዳቤ በመያዝ መንግሥታትን በር በማንኳኳት ኢትዬጵያ የምትገኝበትን ማስረዳትና በዚሁ ደረጃ የሽግግር ምክር ቤቱን ዓላማና ግብ ማስረዳት ነበር ፤ በዚህም የሽግግር ምክር ቤቱ ዓላማ አድማሱን በማስፋት የፓለቲካ ድርጅቶችና ሲቭክ ማህበራትን በሁለት ዘርፉ የዚሁ ስብስብ ባለቤት በማድረግ ዋነኛ ተልዕኮና ግቡም በየትኛውም መንገድ አምባገነኑን ሥርዓት ለማስወገድ ከላይ እንደተጠቆመው አንደ አንድ ማዕከል ትግሉን በውጪ አገራት የሚይስተባርና የሚያቀናጅ አገር ውስጥ የሚካሄደውን ትግል የሚረዳ ኃይል አስፈላጊ መሆኑን በማመን ነበር ።

ይህ ድርጅትም የትግል ዘይቤው ሁለገብ ትግል ሆኖ በዋነኝነት ” በሕዝባዊ እምቢተኝነት” በሂደት ሥርዓቱን በሕዝባዊ እሚቢተኝነት ትግል በማዳከምና በማስወገድ ” ሁሉ አቀፍ ሽግግር መንግሥት ” በኢትዬጵያ ውስጥ ለመመስረት ያለመ ነበር ። በዚህ ዙሪያ እጅግ አድካሚ በርካታ ጥረቶች ከብዙ መጥለፍና በፓልቶኮች ጭምር ዘመቻቻዎች እየተደረጉበት ጥረት አድርጓል ፤ እንደዚሁ ከወቅቱ ጋር የሚመጥን ሕገመንግሥት ረቂቅም በሁለት አማራጭ ተቀርፆ ሃሳብ እንዲታከልበት ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁራንና ወደ ስድሳ ለሚያክሉ የፓለቲካና ሲቭክ ማህበራት መላኩንም እናስታውሳለን! ይህንን አስታኮ የሕወኃቱ አንጋፋው ክንድ የነበሩት ” አቦይ ስብሃት ” በወቅቱ በአንድ ሚዲያ በውጭ አገራት እየተካሄደ ስለነበረው የሽግግር ምክር ቤቱ እቅድ ተጠይቀው አቦይ ስብሃት ሲመልሱ እጠቅሳለሁ

” ተከታትያለሁ ግን ኢትዬጵያ ውስጥ እራሳቸውን የቻሉ አራት መንግሥታት እውን አድርገናል” ስንቱንስ ያስወግዳሉ በማለት ክልል መንግሥታትን በማንሳት ማጣጣላቸውንና ኢህአደግ 1991 ሽግግር መንግሥት መስርተን ነበር በሚል በወ/ሮ ሚሚ ስብሃቱ ሚድያ ተጠይቀው ሲመልሱ ተደምጠዋል።

እንዲህ ዓይነት የተበታተለውን ትግሉ በአንድ የመምራት እቅዶች ዛሬም በአገራችን የችግራችን ሁሉ ቁልፍ እንደመሆኑ ሁሉ በዚያን ወቅትም ሁሉም የአንድነት ድርጅቶች እያንዳንዳቸው እንደዛሬው ሁሉ ዘውድ በኪሳቸው በመያዛቸው የሽግግር ምክር ቤቱን ዓላማ ለማሳካትና  እውን ማድረግ ሳይቻል ቀርቷል፤

የሽግግር ም/ቤቱ ህልውናውን ጠብቆ ቆይቶ በአሁኑ የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አገዛዝ አገር ቤት በመግባት ” ሕብር ኢትዬጵያ ድሞክራሲያዊ ድርጅት ” ከመሰረቱ ስድስት ድርጅቶች አንድ በመሆን በኃላ ” አብሮነት” ስብስብም በመፍጠር ትግሉን ቀጥሏል።

ይህ የሽግግር መንግሥት ወይም የጋራ መንግሥት ሃሳብና ውጥን ዛሬም አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ተንተርሶ  ” ኢዴፓ ” ምክር ቤት አባል ታዋቂውው ፓለቲከኛ አቶ ልደቱ አያሌው እጅግ በረቀቀ መልክ ያዘጋጀው 25 ገፅ ሰነድ ” በኢዴፓ ብሔራዊ ም/ቤት ” ፀድቆ በአድማስ ጋዜጣ ይፋ እንደሆነና አብሮነት ሦስት ድርጅቶች የሚገኙበት ስብስብ የተወሰኑ ማሻሻያዎች አድርጎ የራሱ ሰነድም አድርጎት ይህ ጥልቅ  የሽግግር መንግሥት ሰነድ የሰሞኑ መነጋገሪያ መሆኑ ይታወቃል ፣ ይህ ሰነድ አሁን አገሪቱን የሚመሩት ጠቅላይ ምንስትር የሽግግር መንግሥቱ ሰብሳቢም የሚሆኑበት እንደሆነ አስምሮበታል።

ሌሎችም ድርጅቶች በተመሳይ በምሳሌነትም በጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ የሚመራው ባልደራስ ባለአደራ መንግሥት ሲል፣ እንደዚሁ የኦሮሞ ድርጅቶች በጋራ (ኦብፓ) ኦሮሚያ ብሔራዊ ፓርቲ በቅርቡ የተመሰረተው ዶ/ር መራራ የሚገኙበት

” የምክክር መንግሥት” በሚል ይፋ አድርገዋል! በአፈፃፀሙም እነዚህ ወገኖች ስለ ( ምክክር መንግሥት ) ፅንሰሃሳብ በሰጡት መግለጫ ማንኛውም የመንግሥት ክንዋኔዎች ውሳኔ የውጭ ግንኙነት ሥራ ጭምር በዚህ አካል እየተመከረበት ነው የሚያልፈው! በእኔ ኢይታና ሌሎችም ስጋታቸውን እንዳስቀመጡት አሁን ያለውን መንግሥታዊ አገዛዝ ሥራ ቢሮክራሲያዊ የሚያደርግና አለመግባባትን ሊያስከትል እንደምችል ፣ የመንግሥችንም ቁመና የሚለውጥና በተለይም በዋነኝነት አሁን አገሪቱ ባገጠማት መጠነ ሰፊ ችግሮች ሳቢያስ ለቀልጣፋ መንግሥታዊ ውሳኔ አመቺ እንዳልሆነ በግሌ ምልከታዬን ሳስቀምጥ የዚህ ሽግግር ሂደት ዋነኛ ግቡም ነጥሮ በግልፅ ማሳየት አለመቻሉንም ለምንስ እንዳስፈለገ ማስረዳት አለመቻሉንም ከግምት በማስገባትም ነው፤ ሆኖም ሁሉም አማራጭ ሃሳቦች ለአገሪቷ ችግሮች መፍትሔ ይሰጣሉ ተብሎ ከተገመተ ሁሉንም ጠረጴዛ ላይ በማስቀመጥ በአንድ ብሔራዊ መግባባት መድረክ ለውይትይ ሊቀርቡ ይገባል ።

ውድ ኢትዬጵያዊያን በዚል ፅሑፌ ከርዕሴ የወጣሁትም የሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት የተቀነቀኑ ታሪካዊ ዳራዎች ለማሳየትና የአገራችን ጥያቄዎችም ብቸኛ አለመሆናቸውን በሌሎች አገራትም ጭምሮ የተከሰቱትን ታሪካዊ ክስተቶች ጭምር ለማመላከት ፈልጌ ነው።

ወደ ፅሑፌም ቁንፅል የሽግግር መንግሥት አስፈላጊነት ዙርያ ስመለስ ለምንስ ዛሬ አስፈለገን? እንዴትስ እውን ማድረግ ይቻላል!  አገራዊ መግባባትን ለምንስ አስፈለገን? ግቡስ ምንድነው? ወዘተ ዋነኛው ትኩረት ያደረገ ነው።

የሁሉን ባለድርሻ አካላትን ያሳተፈ በብሔራዊ መግባባትን ( National dialogue ) መሠረት በማድረግ የአገራችንን መሠረታዊ ችግርን ሊቀፍ የሚችል መፍትሔና ምላሽ የሚሰጥ የሕዝብ ቅቡልነት ያለው መንግሥት እንዲኖረን ያለመ ነው ።

አሁን በስልጣን ላይ ያለው የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አገዛዝ በብሔራዊ መግባባት የጋራ ውሳኔ አሁን አፍንጫችንን የሰነገንን ችግር ለመፍታት በቂ ግምት በመስጠት የገዥውን መንግሥት ዕድሜ ቢጨመር ለአገርም ጥቅም እንጂ ችግር ከቶውንም ጉዳት አይሆንም።

ይሉቁንም በተደጋጋሚ ከላይ እንደገለፅኩት በአገራችን ጊዜ ወስደንም ይሁን እውነተኛ የሕዝብ መንግሥት እውን የማድረግ መደላድል ለማመቻቸት ልዩ መሳሪያ የሽግግር መንግሥት መሆኑን አጥብቄ ለማስመር ነው።

የኢትዬጵያና የሕዝቧ ጉዳይ ያገባናል የምንል በተለይም የአንድነት ኃይሉ መመልከት ያለበት አፍንጫችን ሥር ያለውን ሳይሆን ነገን የሚያዩ የጋራ አማራጭ ሃሳቦችን ማበልፀግና ግንዛቤአችንን ማስፋት ስለሚገባን ነው! ይህንን መሬት ለማውረድ ዛሬም ቁልፍ ችግራችን  ትግሉን ማማከል አለመቻላችንና የኢትዬጵያዊያንን ድጋፍ በአንድ ፈርጅ በማድረግ ኢትዬጵያ በቆዳ ስፋትም ይሁን በሕዝብ ብዛት ግዙፍ በመሆንዋ በመላ አገሪቱ ከአድማስ አድማስ በመንቀሳቀስ በሁሉም የምርጫ ወረዳዎች ቤሮዎችን በመክፈት በተቀናጀ መልኩ ሕዝብን መድረስና መቀስቀስ ይቻላል በዚህም ለምርጫ አሸናፊነት የሚያበቃ ኃይል መገንባት ይቻላል።

ዶ/ር አብይን አሁን ላይ መደገፍና የተረጋጋ ምህዳር መፍጠር ችግር የለበትም !!  ኢትዬጵያን የሚለው የአንድነት ኃይል መጪውን ምርጫ ተአማኒ ለማድረግ ቢቻል ቢቻል በሽግግር መንግሥቱ ውስጥ ድርሻ ኖሮት በአገዛዙ የዕለት ዕለት መንግሥታዊ ሥራ ሳይገባ በዋነኝነት በተቋማት ግንባታ ላይ ሚና እንዲኖረው ማስቻል ነው ፤

ከላይ ተደጋግሞ እንደተገለፀው አሁን ያለው የጠቅላይ ምንስትር አቢይ አገዛዝ በሽግግር መንግሥቱ መሪ ሚና ኖሮት ኢትዬጵያን በቅንነት ማሻገር ዕውን ግቡ ከአደረገ መንግሥታዊ አቅምን ለማሳደግ ሽግግር  መንግሥቱን ከተቀላቀሉት ባለድርሻ አካላት በዕውቀትና ልምድ ያካበቱትን የመጠቀም ዕድሉን ማግኘት የሽግግር ሂደቱንም ለማቀላጠፍ አገራችንንም ለማዘመን ሰፊ ሚናና ዕድልም ይኖረዋል።

የአንድነት ኃይይቻላልሱ አሻራ አርፎበት በራሱ ተዋናይነት ጭምር በመጪው ምርጫ የምር የሕዝብ የሆነ ነፃ መንግሥትን እውን መሆኑን ማረጋገጥ ግድ ስለሚሆን ነው።

ለዚህም አንድነት ኃይሉ ይህንን የሽግግር መንግሥት በአንድነት ታግሎ እውን ለማድረግ መተማመን ይገባዋል፤ ይህንን ይሁንኝታ አግኝቶ እውን ማድረግ ቢያዳግተው በአንድነት ቆሞ ትግሉን አማክሎ ቢያንስ በወልጋዳው ምርጫ በጋራ ማኒፌስቶ መወዳደር ፣ በአንድ ምርጫ ጣቢያ ላለመፎካከር የተናበበ እቅድ ማውጣት፣ በዚህም ኢትዬጵያን ለሚያሻግርና ፍትህንና ዲሞክራሲን የምር ዕውን ለሚያደርግ ዓላማና እንደዚሁም ግብን አንድ ላይ ግሉን ማቀናጀት ለነገ የሚተው ከቶውንም አይደለም በምርጫ ማግሥት ጭምር ቢቻል ጥምር መንግስት እውን ለማድረግ የሚከለክለን ምድራዊ ኃይል አይኖርም።

በዚህም ረገድ የድርጅቶች ጥምረት የሆነው አብሮነት ፣ አብን ፣ ባልደራስ ፣ መኢአድ ፣ በፕሮፌሰር በየነ የሚመራው ማህበረ ዲሞክራሲ  ወዘተ መጪውን ዘመን የሕዝብ በማድረግ ልዩ ትኩረት ተሰጥተው የጋራ ውይይቶች ማድረግ ሰጥቶ መቀበልን መርህ በማድረግና አንድ ተፅዕኖ ፈጣሪ አገር አቀፍ ” አንድነት ድርጅት ” እውን ማድረግና በቀጣይም አድማሱን በማስፋት ኢዜማ ሌሎችንም በማካተት በዚሁ መልክ በአንድ ቆመውን ዘውጌውን አገዛዝ ለማሸነፍ በመቀናጀት መስራት ቢችሉ የኢትዬጵያን የኃይል አሰላለፍ መለወጥ ይቻላል።

የብልፅግና ድርጅት ከታች እራሱ ኢህአደግ ድርጅት እንደመሆኑ ዘውጌው ፌዴራላዊ የብሔረተኝነት መዋቅር ከላይ እንደተጠቀሰው ሃያ ሰባት ዓመት የመንግሥትን ንብረትና ሃብት ተጠቅሞ በመላ አገሪቱ እስከ ገበሬ ማህበር መዋቅር እንደ ሸረሪት ድር የተጋመደ ፅሕፈት ቤት ኖሮት በጠንካራ መሰረት የደረጀ ፓለቲካዊ ከባድ ሚዛን ተቋም መሆኑን መዘንጋት የለበትም ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የኢህአደግ የፓርቲው ሊቀመንበር ለመሆን ቃለመኃላ የፈፀሙት ኢህአደግን በኢትዬጵያ መንበር በብልፅግና ስም ለቀጣይ አምስት አመት በጎጥ ለዘመናት የተቃኙትን ስብስቦቹ ይዞ አሸናፊ ማድረግና በእነርሱ ሚዛን በደፋ የኃይል አሰላለፍ ቀጣይ የአገሪቱ ምክር ቤት ይህንኑ ብሔረተኛ ሕገመንግሥት ማስቀጠል እንደሚገደድ ልብ ልንል ይገባል።

ከላይ ለማስመር እንደተሞከረው የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አመራር አገርን ለመምራት የሚከተለው መስመር መርህ የሚጎለውና ሁሉንም የማስደሰት ተልዕኮው አገሪቱን ለማረጋጋት አንድ ችግር መሆኑ ሊሰመርበት ግድ ይላል ሰሞኑን በግንቦት 20 በዓል ዙርያም ሸርተት ብለው ሁሉንም ለማስደሰት ያንን ጨለምተኛ ቀን በቀለም ሲያጌጡም ስምተን የብዙዎቹ መነጋገሪያ መሆኑን ጎበዝ ልብ እንበል! በቀደሙት ሳምንታት በመንግሥት የአምስት ዓመት ገደብ መስከረም ወር ድረስ በተቆሩጠው ዕድሜ ሳቢያ ኃይል እልህም በታከለበት የጠቅላያችን  ንግግር ሰምተናል በዚህም

” ብልፅግና ” በቀጣዩ ምርጫ ያለምንም ጥያቄ ቀጣይ ሆኖ እንደሚኖርና መንግሥትም እንደሚሆን በገሃድ አብስረዋል ።

ስለሆነም የኢትዬጵያ አንድነት ኃይሎች በኢትዬጵያ አንድነት ላይ ባጠላው አደጋ ሁሉንም በአንድ ሊሰበስበን የሚገባ በመሆኑ ትላንትን ለታሪክ በመተው ቀጣዩን ምርጫ ፍታዊና ዲሞክራሲያዊ ለማድረግና ከዘውጌው መዳፍ ለማውጣት ሁሉን አቀፍ የሽግግር መንግሥት ታሳቢ ማድረግ ይህም ባይሳካ እንኳን ከላይ እንደጠቆምኩት በአገር አቀፍ ደረጃም ይሁን በውጭ አገራት የኢትዬጵያዊያን እምቅ ኃይልና ድጋፍ ” Resource ” በአንድ ማዕከል በማድረግ ከቅንጅትና ዲሞክራሲ የትግል ውጤትና ልምድ በመማር ገዥውን መንግሥት  በአንድ ግንባር መፋለምና መወዳደር አማራጭ የሌለው የአገር አንድነትና ሉዓላዊነት ጥሪ መሆን የግድ ነው።

ይህንንም ዕውን ለማድረግ ዛሬ የተጋረጡብንን አገራዊ ችግሮች እንደ አንድ መመከት ፣ የአንድነት ኃይሉን አንጥሮ በአንድ ማዕከል መምራት ጊዜ የማይሰጠው አስቸኳይ ታሪካዊና አደራ መሆኑን ልብ ልንል ይገባል ፤ ይህንንም ዕውን ለማድረግ አንድ የጋራ አስተባባሪ ከእያንዳንድ በመወከል ዛሬ መሬት ማውረድና መተግበር በእያንዳንዳችሁ ቅን መንፈስና ትከሻም ላይ የወደቀ ታሪካዊ አደራ ነው።

ይህንን ሳናደርግ አሁንም ከቀደመው የ 27 ዓመት ውድቀት ሳንማር ብንቀርና ዜውጌዎች ኢትዬጵያን አሁንም እንዲቆጣጠሩ ብናደርግ ታሪክና ትውልድ የማይዘነጋውና ይቅር የማይለው አገራዊ ክህደት እንደፈፀምን ያክል ልንቆጠር ይገባል እላለሁ።

አበባየሁ አሉላ

ዋሽንግተን ዲሲ

 

በሽግግር መንግሥት ዙሪያ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ በኢድፓ በኃላም በአብሮነት የወጣ አማራጭ ሰነድ! , 2012https://drive.google.com/file/d/12D0aJy1ZIzTw_JxfYdi9hubUjVQ-htCS/

3 Comments

 1. Postponing elections can be a must to fight coronavirus when a country already got a democraticaly elected government but in a country such as Ethiopia who had been under siege for close to three decades with a rebel group seizing all the powers , where currently Covid 19 is growing at a faster rate than any other country in the region, one wonders if a different government could have done a better job fighting coronavirus than the current government which is in power now .

  Clearly the current government in Ethiopia isn’t doing a good job in international relations , in security , in education (including education about Covid-19) , in upholding the law …. with no signs of improvement being visible in the horizon from the government’s part , it simply is sad to see them continue to go on for another nine months. The people’s moral is so low with suicide rates and hopelessness steadily climbing up to all-time high during the past two years.
  news-media/multimedia-reports/global-overview-covid-19-impact-elections

 2. ወንድሜ አሉላ – በረዘመው ሃሳብህ ያነሳሃቸው ሃሳቦች ሁሉ ማለፊያ ናቸው። ግን ለማይኖርበት አለም ወንድምና እህቱን ገድሎ ለሚፎክር እኩይ የሆነን ሰው ልብ እንዴት መለወጥ ይቻላል? ዛሬ በሃገራችን ከስልጣኑ ተሽንቀጥሮ መቀሌ ላይ መሽጎ የትግራይን ህዝብ ፍዳ የሚያስቆጥረው የወያኔ ትራፊዎች እናት ሃገራችን ለመሸጥና ህዝባችን እርስ በራሱ እንዲባላ ለማድረግ የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። ትላንት መለስ ሰካራም እንደ ረገጠው ጣሳ በእርግጫ ብሎ ያባረራቸው ስመ ጀኔራሎች በየሚዲያው የሚሉትን ለሰማ እነዚህ ሰዎች ሰክረው ነው ወይስ እጽ ነገር አጭሰው ነው እንዲህ የሚያወሩት ያሰብላል። ትላንት የሰዎች ቆለጥ ሲጎተት፤ በወንድ ላይ ሶዶማዊ ድርጊት ሲፈጸም፤ በእህቶቻችን እና በወንድሞቻችን ላይ ሽንት ሲሸና እና ሲጸዳዳ የነበረ የአፈና እና የግድያ ቡድን አሁን ለሃገር አንድነትና ለብሄር ብሄረሰቦች መብት ተረገጠ ብሎ ሲወራገጥ በእርግጥም ሞታቸው በደጅ እንደሆነ አብስሮ ያስረዳል። ገድለው፤ ዘርፈው፤ ሰርቀውና አሰርቀው በሰሩት ቤትና ባከማቹት ሃብት ጥላ ስር ተጠግተው ዛሬም እንደ በፊቱ በህዝባችን ላይ ሲያላግጡ ማየት ልብ ያቆስላል። በስልጣን ላይ እያሉ ለምን ለሰው ልጆች መብት አልተቆረቆሩም? ግን የፓለቲካ ወራዳነት እንዲህ ነው እያዛለ ወደ መቃብር ያወርዳል። እይታቸው ሰፈርተኝነት በመሆኑ የሚያስቡትና የሚያሸቱት ያንኑ የጠባብ ብሄርተኝነት ሽታ ብቻ ነው። ለወያኔ የአለም ጥቁር ህዝቦች ተባበሩ ቢባሉ ከአድዋ እንጀምር ነው የሚሉት። ለአድዋ ወይም በስሙ ለዘመናት ለነገድበት የትግራይ ህዝብ ግን ምንም ያደረጉለት ቅንጣት ነገር የለም።
  አሁን ያለንበት አለም ጥልፍልፉ የበዛ ነው። በአውሮጳ፤ በአሜሪካ፤ በእስያ፤ በላቲን አሜሪካ የጥቁር ህዝቦች ሃበሳ ጣራ እየደረሰ ነው። በዚህ ላይ ነዳጅ ያሰከረውን የዓለም ክፍል ሲታከልበት ጥቁር ህዝብ ያለ ልክ መጠላቱን ያመላክታል። ታዲያ በአፍሪቃ አህጉር ከካሜሩን እስከ ኢትዮጵያ በዘርና በቋንቋ ጦርነት ሰዎች ሲተላተሉ ማየት ለአህጉሩ ጠላቶች እፎይታ ነው። የጥቁር ህዝብ ደም ለነጩም ሆነ ለአረቡ ወይም ለቻይናው ደንታ አይሰጠውም። ይህን የምለው ጊዜ የፈጠረውን የፓለቲካ ትኩሳት ተከትዬ አይደለም። ገና ገና ድሮ የገባኝ ብሂል እንጂ! ታዲያ ጥቁሩ ህዝብ ነጭና ቻይናን ወይም አረብን ማምለክ ትቶ የራሱ የሆነውን አክብሮ በፍቅር መኖር እስካልቻለ ድረስ የግፈኞችን ድላ መመከት አይችልም። የሃበሻው ፓለቲካ ደግሞ እጅግ ጸያፍ ነው። አሁን በቫይረሱ ምክንያት ምርጫው ይተላለፍ ሲባል የሚነሱ ተቃውሞዎችን ስሰማ ድሮ ምርጫ ተብሎ ወያኔ 99% መረጠኝ ብሎ ተቃዋሚን በጥይት ሲያረግፍ እነዚህ የወያኔ የአሁን ቡችሎች የት ነበሩ? አብረው ሲያጨበጭቡና ሲሰርቁ አልነበረምን?
  ሃገሪቱን ሊመጣ ካለው የከበባ መከራ ማዳን የሚቻለው አንደኛ ወያኔን ጽጥ ማድረግ ሲቻል ብቻ ነው። ሁለተኛ ዛሬ በቱርክ የተከበበችው ኢትዮጵያ፤ በግብጽ ማስፈራራት ሲደርስባት፤ ወያኔ ደግሞ ምስራቅ አፍሪቃ እሳት ይነሳል እያለ ለዓለም መንግሥታ መጻፍ ጀምሯል። ለአፍሪቃ የሚበቃ ሰራዊት አለን የሚለው ይህ የማፊያ ቡድን ሰው በወታደርና በመሳሪያ ብዛት እንደማይድን ገና አልገባውም። የሚፎክረው በባዶ ሜዳ ነው። ለኢትዮጵያ ጠ/ሚ አብይ የሚያደርጋቸውና እያደረገ ያለው ነገር ሁሉ የሚያነቃቃ ነው። ስለሆነም የማይተማመን ባልንጀራ በየወንዙ ይማማላል ሆኖ እንጂ መጠየቅ ያለበት በስልጣን ላይ ያለው ሃይል እንዴት ሃገሪቱን ያስተዳድራል እንጂ ዘሩ ማን ነው ሊሆን አይገባም ነበር። ግን በዘርና በቋንቋ እንዲሁም በክልል ለተሸለተ ሃገር ግን ሁሌ ዘርን ጎሳ እንጂ ሥራው አይታይም። ለዛ ነው ሁልጊዜም ስንናኮር የምንኖረው። ሃገሪቱ እውን ሆና ሁሉ በእኩልነት እንዲኖርባት ከተፈለገ ሁሉም ሰው አሰላለፉን ማሳመር አለበት። ያለዚያ ጨለማ ጊዜው የባሰ ድቅድቅ ጨለማ ይሆናል። ውይ አንተን አስረዘምከው እያልኩ የእኔም ረዘመ። ይብቃኝ።

 3. የ አገራችንን ችግሮች ለ መፍታት ያለው ብቸኛ መፍትሔ ህግን ማስከበር ነው። መጥፎ ቢሆንም፣ ከ ምንም ስለሚሻል፣ በ አለው ህግ መገልገል ይሻላል። በ ህግ ሥር ሆኖ ህግን ማሻሻል ይቻላልና። ህግን ንዶ ህግ ለ ማውጣት መሞከር በ አለፉት ሁለት መንግሥታት ያስከተለብንን ጥፋት አይተናል። ያን መልሰን መጋፈጥ የለብንም።
  ህገ- መንግሥትን ማሻሻል ( reform ) ከ አብዮት (revolution) ይመረጣል። የማያባራ ቅራኔን፣ የ ሰዎች ህይወትን እና ንብረትን ከ ማውደም ያድናልና።
  አገራችን ከ 100 በላይ ፓርቲ ተብዬዎች ያሉባት አገር ናት። ለ እኔ ማፈሪያዎች ናቸው። የተሰባሰቡት ለ ጥቅም ፍለጋ እንጂ ለ አገር እና ህዝብ ፋይዳ ለ መሥራት አይደለም። ቢሆን ኖሮ በ ሦሥት ወይም አራት ፓርቲዎች ተሰባስበው ለ አገር ይሠሩ ነበር። አብዛኞቹ አገር ከ መሸጥም ወደ ኋላ አይሉም። እነዚህ ሁሉ ፓርቲዎች መክረው ለ አገር የሚበጅ መንግሥት ያቋቁማሉ ብዬ ለ አንድ ሰከንድ እንኳን አላምንም።
  ስለዚህ የ ሽግግር መንግሥት ፈፅሞ የማይሆን ዕቅድ ነው። የሚሻለው ያለውን መንግሥት ለ አገር ልዕልና እና ለ ዜጎች ዕኩልነት እንዲሠራ ተፅዕኖ ማድረግ እና መደገፍ ነው። ዶር አቢይ ብዙ ድክመቶች እና ወገናዊነት ቢታይበትም ከ እሱ የተሻለ ሰው የለም።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.