መለስና ሶስቱ ጄኔራሎች በ1993ቱ ዓመተ ምህረት የህወሃት ክፍፍል ወቅት – ክብሮም ሙሉጌታ

ጦርነት ኪሳራ እንጂ ትርፍ የለውም። የ1990 ዓመተ ምህረቱ የኢትዮ- ኤርትራ ጦርነት በሁለቱም ሀገሮች ከፍተኛ የሆነ ሰብዓዊና ኢኮኖሚያዊ ኪሳራ አድርሷል። ጦርነቱ በኢትዮጵያ በኩል ሁለት ወሳኝ ነገሮችን አስከትሏል። ህወሃት ለሁለት በመከፈሉ በእነ ስዬ አብርሃና ተወልደ ወልደ ማሪያም ይመራ የነበረው አክራሪው የህወሃት ክንፍ ከኢትዮጵያ ህዝብ ጫንቃ እንዲራገፍ አድርጓል። ክፍፍሉ የህወሃት የውድቀት ቁልቁለት መጀመሩን አብሳሪ ነበር። ይህ አክራሪ ክንፍ በኢህአዴግ የነበረውን የህወሃት የበላይነት ያቀነቅን የነበረ ብቻ ሳይሆን የበላይነቱ እንዲቀጥልም ተግቶ የሚሰራ ሃይል ነበር። የአክራሪው ሃይል የነበሩ አንዳንድ አባላት አሁን ደርሰው ለኢትዮጵያ ህዝብ ጥቅም ይሰሩ እንደነበር ለማሳየት ሲዋትቱ ማየት ያስገርማል። እውነታው ግን ያ አልነበረም። አንዳንዶቹም የቀድሞ በሽታቸው አገርሽቶባቸው የኢትዮጵያን ህዝብ ለማስፈራራት እየሞከሩ ነው።

መለስ ዜናዊ ከክፍፍሉ በኋላ ስልጣኑን ለማደላደል ሲል ከሌሎች የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች አመራር ጋር ተቀራርቦ መስራትና ሃሳባቸውንም መስማት ግድ ሆኖበት ነበር። በክፍፍሉ የመጀመሪያ ሁለት ዓመታት መለስ በትግራይ የነበረው ተቀባይነት ቀንሶ ነበር። በተለይም አዲሱ ለገሠና በረከት ስምዖን አንጃውን አስመልክተው ይሰጧቸው የነበሩ መግለጫዎች የአንጃውን ደጋፊዎች ልብ አድምተዋል። ሌላው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ያመጣው ለውጥ በህወሃትና በሻዕቢያ መካከል የነበረው የረጅም ጊዜ ወዳጅነት ላይመለስ እስከነአካቴው ማክተሙ ነው። በጦርነቱ ማግስት የኤርትራ መንግሥት ህወሃትን ለሚቃወሙ ድርጅቶችና ግለሰቦች መጠጊያና ከለላ መስጠቱ ለህወሃት አገዛዝ መገርሰስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርጓል። የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ስለህወሃት ክፍፍል ትንተና ለመስጠት ሳይሆን ክፍፍሉን ተከትሎ በሶስት ጄኔራሎችና በመለስ መካከል ተከስቶ ስለነበረው ፍጥጫ አንዳንድ ነጥቦችን ለማንሳት ነው። በዚህ ፍጥጫ አንዱ ጄኔራል ይዞት በነበረው አቋም በመጽናት የመለስ የበቀል ገፈት ቀማሽ ሲሆን ሁለቱ ጄኔራሎች ግን ጓደኛቸውን በመክዳት ለመለስ በመንበርከክ ጥቅማቸውና ጡረታቸው ተከብሮላቸው እስከ መለስ ሞት ድረስ ድምጻቸው ሳይሰማ ቆይቶ አሁን የመጣውን ለውጥ ለመቀልበስ ወዲያ ወዲህ እያሉ መሆኑን የኢትዮጵያ ህዝብ አሳምሮ የሚያውቀው ጉዳይ ቢሆንም እኔም የራሴን ምልከታ ለማቅረብ ነው።

Tsadikanብርጋዴር ጄኔራል ታደሠ በርሀ / ጋውና/፣ ሌትናል ጄኔራል ጻድቃን ገብረ ትንሳኤና ሜጄር ጄኔራል አበበ ተክለ ሃይማኖት ህወሃትን የተቀላቀሉበት ወቅት ተቀራራቢ ነው። ታደሠ የአድዋ አካባቢ ተወላጅ ነው። ጻድቃን ዛላምበሳ አካባቢ ልዩ ስሙ ምኹያብ በተባለ አካባቢ ቢወለደም ወላጆቹ የተሻለ ኑሮ ፍለጋ ወደ ራያ ተሰደው ሲመጡ ጻድቃንን አባቱ በጫንቃቸው ተሸክመውት እንደመጡ እስካሁን ድረስ የራያ ጨርጨር አዛውንቶች ያስታውሳሉ። አበበ የመቀሌ ልጅ ሲሆን ከጻድቃን ጋር የተዋወቁት ሁለቱም መቀሌ በሚገኘው አጼ ዮሃንስ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የአንድ ክፍል ተማሪዎች በነበሩበት ወቅት ነው። ይሄው ቅርርብ በትጥቅ ትግሉም ቀጥሎ የጠበቀ ጓደኝነት ሊፈጥሩ ችለዋል። አበበ የአየር ኃይል አዛዥ በነበረበት ወቅት ከጻድቃን ጋር የነበረውን ቅርርብ ተገን በማድረግ በአንዳንድ የአየር ኃይል ከፍተኛ መኮንኖችና ፓይለቶች ላይ ጫናና በደል ይፈጽም እንደነበር በወቅቱ የአየር ኃይል አባላት የነበሩ ሰዎች ይገልጻሉ።

የህወሃት ክፍፍል በተቀሰቀሰበት ጊዜ መለስ ለኤታማዦር ሹሙ ጄኔራል ጻድቃን ገብረ ትንሳኤና ለመከላከያ ትምህርትና አስተዳደር ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ታደሠ በርሀ ለሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች በወቅታዊ ሁኔታ ላይ መግለጫ መስጠት ስለሚፈልግ የስብሰባ ጥሪ እንዲደረግ ትዕዛዝ ይሰጣቸዋል። የአየር ኃይሉ ጄኔራል አበበ ጉዳዩ በቀጥታ ባይመለከተውም ከጻድቃን ጋር በነበረው ግላዊ ቅርርብ የመለስ የስብሳባ ይጠራልኝ ትዕዛዝ ይሰማል። ጄኔራል ታደሠ ለሁለቱ ጄኔራሎች መለስ የሚጠራው ስብሰባ የእነ ተወልደን ቡድንን ለመምታት ያለመ በመሆኑ ሠራዊቱ ተጠሪነቱ ለህገ መንግሥቱ እንጂ ለፓርቲው ስላልሆነ መለስ የህወሃትን ክፍፍል በተመለከተ ለሠራዊቱ ገለጻ ቢሰጥ ህገ መንግሥቱ ይጣሳል። ሠራዊቱ ስለ ፓርቲው ክፍፍል ማወቅ አለበት ከተባለም ዕድሉ ለአንጃውም ሊመቻችለት ይገባል። ይህንን ሃሳብ ለመለስ መግለጽ አለብን። መለስ ሁለቱን ሃሳቦች የማይቀበል ከሆነ ግን አካሄዱን መቃወም አለብን፣ ስብሰባውንም መጥራት የለብንም የሚል ጠንከር ያለ አቋሙን ይገልጽላቸዋል። ጻድቃንና አበበም ታደሠ ያነሳው ሃሳብ ትክክል ቢሆንም ለአንጃውም ዕድል ይሰጠው የሚለው ሃሳብ መለስ እንደማይቀበለውና ባይሆን በስብሰባው ተሳትፈው ፓርቲው በሠራዊቱ ላይ ጣልቃ እየገባ ስለሆነ መቀጠል እንደማይፈልጉ በመግለጽ መሰናበት ይሻላል የሚል ሃሳብ ያቀርባሉ። ታደሠም አቋማቸውን እንደሚያከብር ነገር ግን በስብሰባውም ሆነ ጥሪ በማስተላለፉ እንደማይሳተፍ በመግለጽ ከእነሱ ይለያል።

እንደተባለውም ለሠራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች የስብሰባ ጥሪ በጠቅላይ ኤታማዦሩ ጄኔራል ጻድቃን ይተላለፋል። በመሰረቱ ይህ ዓይነቱ ስብሰባ የሚጠራው በሠራዊቱ ትምህርትና አስተዳደር ዋና መምሪያ ኃላፊ ነበር።በቦታው የነበረ የሰራዊት አባል እንደገለጸለኝ ስብስባው ከመካሄዱ ሁለትና ሶስት ቀናት በፊት መሿለኪያ አራተኛ ክፍለ ጦር ይገኝ የነበረው የጄኔራል ታደሠ ቢሮ ለዚሁ ስብሰባ ከየጦር ግንባሩ በመጡ ጄኔራሎች ተጨናንቆ ነበር። ጄኔራሎቹ ታደሠ ሃሳቡን እንዲቀይር በማግባባት መለስ በቀጣይ በጓዳቸው ላይ ከሚያደርስበት በቀል ለመታደግ ነበር። ታደሠም ጓደኞቹን ስላሰቡለት በማመስገን እሱ ግን ሃሳቡን እንድማይቀይር ገልጾ አሰናብቷቸዋል።ታደሠ ከጻድቃንና አበበ በሃሳብ ከተለየ በኋላ አራተኛ ከፍለ ጦር በሚገኘው ቢሮው ውስጥ መደበኛ ስራውን ይሰራ ነበር። የሠራዊቱ ስብሳባ የተካሄደው በጦር ኃይሎች ጠቅላይ መመሪያ ግቢ በሚገኘው የመኮንኖች ክበብ ነበር። በተደረገው ጥሪ ስብሰባው በመለስ እንደሚመራ ቢገለጽም ባልታወቀ ምክንያት የደህነነቱ መስሪያ ቤቱ ዋና ሃላፊ ክንፈ ገብረ መድህን ስብሰባውን መምራት ይጀምራል። ስብሳባው የተወሰኑ ቀናት ከተካሄደ በኋላ ክንፈ በስብሰባው ቦታ በሻለቃ ጸሃየ ተገደለ። በስብሰባው ጻድቃንና አበበ በተሰብሳቢዎቹ ከፍተኛ ውርጅብኝና ዘለፋ ደርሶባቸዋል። ጻድቃንና አበበ ፈለጉም አልፈለጉም ከመከላከያ ጋር ሊቀጥሉ እንደማይችሉ ከስብሰባው መንፈስ ተረድተውታል። የቀረ ነገር ቢኖር የመለስን ውሳኔ መጠበቅ ብቻ ነበር። በሌላ በኩል የ1993ቱ ዓመተ ምህረት የተሃድሶ ስብሰባ በሰራዊቱ ከፍተኛ አመራሮች መካከል አለመተማመንንና መቃቃርን ፈጥሮ አልፏል። ለነገሩ ጄኔራል ጻድቃንና ጄኔራል ሳሞራ በባላንጣነት መተያየት የጀመሩት ከተሃድሶው በፊት ነበር። ሳሞራ ምድቡ ግምባር አካባቢ የነበረ ቢሆንም አዲስ አበባ መከላከያ ዋናው መስሪያ ቤት ሲመጣ አንድም ቀን ተሳስቶ ጻድቃን ቢሮ ጎራ ብሎ አያውቅም። በዘመቻና በመረጃ ዋና መምሪያዎች የሚገኙ ጄኔራሎችን መጎብኘት ያዘወትር ነበር። ሳሞራ ኤታማዦርነቱን ሲቆጣጠር ቀዳሚ ያደረገው ነገር የጻድቃንን ስታፍ ከመከላከያ ሚኒስቴር ዋና መስሪያ ቤት ልዩ ልዩ መምሪያዎች ጠራርጎ ማስወጣት ነበር።

ወደ ጄኔራል ታደሠ ጉዳይ ስንመለስ መለስ በታደሠ ላይ የበቀል በትሩን ማሳረፍ የጀመረው ስብሳባው ባለቀ ሁለትና ሶስት ቀናት ውስጥ ነበር። በታደሠ ቦታ ሜጄር ጄኔራል ዓለሙ አየለ /ጡንቼ/ የመከላከያ ትምህርትና አስተዳደር ዋና መምሪያ ኃላፊ ሆኖ ተመደበ። ታደሠም ያለ ጡረታና ጥቅማ ጥቅም ተሰናበተ። ጡረታውን ለማስከበርም ጡረታና ማህበራዊ ዋስትና መስሪያ ቤት ይመላለስ ነበር። በመለስ የአገዛዝ ዘመን ታደሠ ጡረታውን ስለማክበሩ እርግጠኛ አይደለሁም። በቀሉ በዚህ ብቻ የተገደበ አልነበረም። መንግሥት ለከፍተኛ መኮንኖች መኖሪያ ቤትና ሌሎች ጥቅማ ጥቅሞች እንድሚሠጥ ይታወቃል። ታደሠም መንግሥት በሰጠው ቤት ውስጥ ነበር የሚኖረው። ደህንነቶች ታደሠ ቤት ውስጥ የማይኖርበትን ሰዓት በማጥናት ዕቃውን ሜዳ ላይ አውጥተው ነበር የጣሉለት። የታደሠ ሚስት ወደ ወንድሟ በመደወል የተፈጠረውን ችግር ገልጻለት ዕቃውን አፋፍሰው ወደ ዘመድ ቤት እንዲገባ አድርገዋል። የታደሠ ሚስት ወንድምም ታደሠን ደውሎ ካገኘው በኋላ የመለስ ደህንነቶች ያደረጉቱን ገልጾለት ካረጋጋው በኋላ ታደሠ በዚህ መልኩ ወደ አዲስ ህይወት ገብቷል። ጄኔራል ታደሠ ከፍተኛ የትምህርት ፍላጎት ስለነበረው መንግሥት ለቤት መስሪያ የሰጠውን ቦታ በመሸጥ ለትምህርት ወደ እንግሊዝ ሃገር አቅንቶ ሁለተኛ ድግሪውን ሰርቷል። ወደ አዲስ አበባ ተመልሶም በአንድ ትልቅ የግል መስሪያ ቤት ተቀጥሮ ይሰራ እንደነበር አውቃለሁ።

ለመለስ የተንበረከኩት ጻድቃንና አበበ ግን ጡረታቸውና ሌላም ጥቅማ ጥቅሞች ተሟልቶላቸው ከሠራዊቱ ቢወጡም መለስ ዜናዊን በመፍራት አንዲት ቃል ሳይተነፍሱ በፍርሃት ቆፈን ውስጥ ሲኖሩ ከመለስ ሞት በኋላ ግን የኢትዮጵያ ፖለቲካ አዋቂና ተንታኝ ሆነው ብቅ ማለት ጀመሩ። መለስ የኢትዮጵያን ፖለቲካ እንደልቡ ሲዘውረው ትንፍሽ ብለው የማያውቁ ሰዎች የኢትዮጵያ ህዝብ ታግሎ ያመጣውን ለውጥ ለማደናቀፍ የህወሃት የአዲስ አበባ ክንፍ በመሆን እያሴሩ ይገኛሉ። ራሳቸውን የአሰብ ኢትዮጵያዊነት ፖለቲካ ኤክስፐርት አድርገው ያቀርባሉ። በህግ አግባብ አሰብ የኢትዮጵያ እንዲሆን የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ ይኖራል ብሎ ማሰብ ይከብዳል። ይህንን የሚቃወም ባንዳ ብቻ ነው። አሰብ ለኢትዮጵያ እንደምትገባም ጥናት ላይ ተመርኩዘው መጀመሪያ ያቀረቡት በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩትና ሁሌም ለኢትዮጵያ ጥቅም የሚታገሉት ዶክተር ያዕቆብ ኃይለ ማሪያም ናቸው። ጻድቃንና አበበ አሰብን የሚያነሱት በጠቅላይ ምንስትር ኃይለ ማሪያም ደሳለኝ ዘመን ፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂን ለማጥቃት ሲፈልጉ ነበር። ያው የህወሃት አገዛዝ ለማራዘም ከማሰብ እንጂ የኢትዮጵያን ጥቅም ከማስከበር የሚነሳ አልነበረም። በጠቅላይ ምንስትር ዓብይ አህመድ ዘመን ደግሞ በዓብይና በኢሳያስ የተመሰረተውን ግንኙነት ለማኮላሽት አሰብን እንደ ካርታ በመምዘዝ ግንኙነቱን ለማሻከር አበክረው እየሰሩ ይገኛሉ።

ይባስ ብሎም ጻድቃንና አበበ ባገኙት መገናኛ ብዙሃን ሁሉ የኢትዮጵያን ህዝብ ለማስፈራራት ይሞክራሉ። ለምሳሌ ያህል ሰሞኑን አበበ በኤል ቲቪ ቀርቦ የህወሃት ተላላኪነት ሚናውን ለመወጣት በዓብይ መንግሥት ላይ በኦሮሚያና በደቡብ ህዝቦች አመጽ እንዲነሳ እየቀሰቀሰ ይገኛል። የህወሃት ምርጫ ከልተካሄደ ሙቼ እገኛለሁ አቋም ትክክል እንደሆነና ኮሮና ምርጫው እንዳይከናወን ምክንያት እንደማይሆን እሱም እንደ ወያኔ ይሞግታል። የነጃዋር ኦፌኮና ኦነግ ብቻ በኦሮሚያ ተቀባይነት እንዳላቸው እነሱም እንደ ህወሃት ምርጫው ከመስከረም 30 በፊት ይከናወን የሚለውን የህወሃት የቀውስ መንገድ እንደሚቀላቀሉ እርግጠኛ ሆኖ ይነግረናል። ምናልባት አበበ የውስጥ አዋቂ ነውና እየነገረን ያለው ህወሃትና ጃዋር ያቀዱትን ሊሆን ይችላል።

አበበ ህዝቡ በፌዴራል ተቋማት ያለውን ተአማኒነት ለመሸርሸርም ሲጥር ይታያል። ከምርጫ ጋር በተያያዘ ወሳኝ ሚና ያላቸውን እንደ ጠቅላይ ፍርድ ቤትና ምርጫ ቦርድ የመሳሰሉትን ተቋማት የሚመሩ ሰዎች ባልተጨበጠ መረጃ ሲወነጅል ይታያል። ለምስክርነትም ጃዋርን ይጠራል። ካለፈ ስራቸው በመነሳት አሁን ሁለቱ ተቋማት የሚመሩት በጠንካራ ሰዎች መሆኑን ብዙ ሰው ያምናል። እንደ ህወሃት ዘመን እነዚህን ተቋማት በቀጭን ትዕዛዝ ይህን አድርጉ ይህን አታድርጉ ማለት አይቻልም። በተለይም የወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ ህገ መንግሥቱን ለመተርጎም በተከናወነው ውይይት ያሳዩት የመሪነት ችሎትና ብቃት ያናደደው ይመስላል። የህገ መንግሥቱ ትርጉም ውሳኔ የህወሃትን ግብዓተ መሬት ሊያፋጥን ይችላል ብሎ ስለገመተ በምርጫ ቦርድና በጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ላይ ከወዲሁ ጦርነት ከፍቶባቸዋል። መቼም አበበና መሰሎቹ ይሉኝታ የላቸውምና ከኤል ቲቪ ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ ህወሃት ላለፉት 30 ዓመታት አፍኖ የያዘውን የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ የዓብይ መንግሥት ችግር አድርጎ ለማሳየት ይኳትናል። እውነታው ግን የሲዳማ ብቻ ሳይሆን በደቡብ ክልል የክልል እንሁን ጥያቄ እየተፈታና እየተደመጠ ያለው በዓብይ ዘመን ነው። አበበ ስለብሄር መብትና መሬት ዝርፊያ ያቀረበው ሃሳብም ውሃ የሚቋጥር አይደለም።

ባለፈው የወያኔ ስርዓት የኢትዮጵያ መሬት በሙሉ የህወሃት/ኢህአዴግ የግል ንብረት እንደነበር ይታወቃል። የጋምቤላና የአዲስ አበባ መሬት የአበበ እና መሰሎቹ የግል ንብረት ነበር። ገበሬውን መሬት አልባ ያደረጉት እነ አበበና ጻድቃን የመሳሰሉ የመሬት ከበርቴዎች ሆነው ሳለ የዓብይን መንግሥት በመሬት ጉዳይ ጄኔራሉ ይከሳል። አበበ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት እንዳለ ይገልጽና በትግራይ ክልል ስላላው ጥሰት ለመግለጽ ግን ወኔ ይከዳዋል።

በአጠቃላይ አበበና ጻድቃን ከህወሃት ጋር አብሮ ካልተሰራ ሁሌም ኢትዮጵያ እንደምትፈርስ ያሟርታሉ።የኢትዮጵያ ስም ገኖ ሲነሳ ዓይናቸው ይቀላል። ደም ግፊታቸው ይጨምራል። ለኢትዮጵያ እንደ ሃገር መቀጠል ዋስትናዋ ህወሃት መሆኑንም ይደሰኩራሉ። ኢትዮጵያ ግን ያለ ህወሃት መቀጠል እንደምትችል በዓይናችን ማየት ከጀመርን ሰነባብተናል። ስለዚህ ጻድቃንና አበበ የህወሃት የአዲስ አበባ ቅርንጫፍ በመሆን ከሌሎች ጽንፈኛ ሃይሎች ጋር በማሴር ሀገሪቱን ወደ ለየለት ቀውስ ከማስገባታቸው በፊት እንቅስቃሴቸውን በአትኩሮት መከታተሉ ተገቢ ይመስለኛል።

 

2 Comments

  1. ክብሮም መረጃዉ መልካም ነዉ እኛም ጻድቃንና አበበ ምንም እንዳልሰሩ ሁሉ እየወጡ ሲዘባነኑብን የፍርድ ያለህ ስንል ነበር። በተለይም ጻድቃን 5000 ዶላር የሚከራይ ቤት አለዉ ሲሉን ደሞዙን ብናባዛም ብንደምርም ብንቀንስም ያንን ቤት የሚያሰራ ገንዘብ ማግኘት አልቻልንም አበበም ከዚህ የማያንስ አያጣም። ሰዎቹ ጭራቆች ናቸዉ አሰብን ግን መጠየቃቸዉ ወንጀለኞች አያደርጋቸዉም ምንም እንኳን የሰጡት እነሱ ቢሆኑም። ሰዎቹ መቀሌ ትጠባቸዋለች ከአዲስ አበባ ሬሳቸዉ ነዉ የሚወጣዉ እንቅስቃሴያቸዉንም እየተከታተለን ነዉ እጃቸዉ እግረ ሙቅ እስኪገባ በስጋት ይኑሩ ብለን ነዉ። ታደሰም ድምጹን አጥፍቶ ቁጭ ብሏል ተበዳዩ ህዝብ ግን እሱ አያዉቀዉም እንጂ ባይነ ቁራኛ እየጠበቀዉ ነዉ የፍርድ ቀን ሲመጣ ….።
    ስለአንተ ምንም አልነገርከንም ከላይኛዉ ትሆን ከታችኛዉ በሁለታችሁ መሀል ልዩነት ባይኖርም።ትንሺ ፍንጭ የሰጠን አሰብ ላይ ያለህ ምልከታ ነዉ። አንተስ እንዲህ ያለ ምስጢር ይዘህ ይህን ያህል ዘመን መቆየትህ ምን የሚሉት ነዉ? አንተም እኮ የትግሬዎች መንግስት ሲወድቅ ጠብቀህ ነዉ ብዙ ከምታዉቀዉ ትንሹን የነገርከን። እስቲ ሌላም ካለህ ጀባ በለን ላንተም ይቀልሀል።

  2. አቶ ክብሮም ሙልጌታ እግዛብሄር ይሲጥህ የእነዚህ ሰዎች ጉድ በአብዛሃኛው የኢትዮጵያ ህዝብ እንዲያውቀው ማድረግህ አሁንም ትልቅ አክብሮት አለኝ:
    ቀፃይየቀሩ ጎዶች ከሌሎች የእነሱ አሽከሮች ጨምሮ ተጨማሪ መረጃ አቀርባለሁኝ::

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.