ዶ/ር አብይ የእርሶ ይባስ፤ የአምነስቲ መግለጫ ድርሰት ወይስ መሬት ላይ ያለ እውነታ – ያሬድ ኃይለማርያም

103933004 10222785803732728 2377869291128782005 n ዶ/ር አብይ የእርሶ ይባስ፤ የአምነስቲ መግለጫ ድርሰት ወይስ መሬት ላይ ያለ እውነታ   ያሬድ ኃይለማርያም

ትላንት በተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ላይ ተገኘትው ለምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎች ምላሽ ሲሰጡ የነበሩት ዶ/ር አብይ ለበርካታ ጥያቄዎች አግባብነት ያለው ምላሽ ቢሰጡም በሁለት ጉዳዮች ግን ሲፎርሹ ታዝቤያለሁ። አንደኛው የታፈኑትን ሴት ተማሪዎች በተመለከተ የተናገሩት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የአምነስቲ ኢንተርናሽናልን መግለጫ የገለጹበት መንገድ ነው።

የታፈኑትን ሴት ተማሪዎች በተመለከተ ከዚህ ሁሉ ወራት ቆይታ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተድፈነፈነ ምላሽ በመስጠት ነገሩን አድበስብሰው ለማለፍ የሄዱበት መንገድ ያሳዝናል። እንደ መንግስት በዚህ ጉዳይ ላይ ጥያቄና ውትወታም ሳይነሳበት በምርመራው የደረሰበትን ደረጃ በየጊዜው በዝርዝር ለቤተሰቦቻቸው እና ለሕዝብ ማሳወቅ ነበረበት። ጠቅላዩ ጭራሽ ስለ እነዚህ ልጆች መታፈን በተለያዩ መድረኮች ድምጻቸውን የሚያሰሙ ወገኖችን በንግግራቸው ወርፈው እረብ ያለው ነገር ሳይናገሩ አልፈውታል። ድርጊቱን ማንም ይፈጽመው ማንም መንግስታቸው ግን ያለበትን ኃላፊነት በአግባቡ እየተወጣ አይደለም ወይም ያከናወናቸውን ተግባራት በአግባቡ ለሕዝብ አላስረዳም።

ሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ የአምነስቲን የቅርብ ጊዜ እና አውዛጋቢ የሆነውን ዘገባ በተመለከተ የተናገሩት ጉዳይ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርቱን ለማጣጣል ሲሉ ይህን የንጹሃን ዜጎችን ግድያ፣ ሕገ ወጥ እሥራት፣ ድብደባ፣ አስገድዶ መድፈር እና ሌሎች ከፍተኛ ግምት ሊሰጣቸው የሚገቡ ጉዳዮችን የያዘ መግለጫ ድርሰት ሲሉት ተደምጠዋል። እንደማንኛውም የድርሰት ሥራ የራሱ ደራሲ አለው ብለዋል። ደራሲውም የራሱ ፍላጎቶች እና የፖለቲካ አቋም ሊኖረው ይችላል በሚል ለማጣጣል ሞክረዋል። ይህ አይነቱ አገላለጽ እጅግ አሳፋሪ እና በመግለጫ ውስጥ በደላቸው የተገለጸውን ግለሰቦች ጉዳት እንዳልተፈጠረ አድርጎ የመካድ አዝማሚያም ጭምር ነው።

የአምነስቲ ሪፖርት የሚወቀስበት እና የሚተችበት ክፍተቶች አሉት። አምነስቲ በብዙዎች ዘንድ በዚህ ሪፖርቱ የተወቀሰው በአገሪቱ ውስጥ የተፈጸሙትን ሁሉንም በደሎች አላካተተም በሚል እንጂ ባቀረበው ዝርዝር መረጃዎች ላይ ስህተት አለ በሚል አልነበረም። እኔም በተለያዩ ሚዲያዎች በመግለጫው ላይ የታዩኝን ክፍተቶች ለመጠቆም ሞክሬያለሁ። ይሁንና በውስጡ ያካተታቸውን በደሎች እና በዜጎች ላይ የደረሱት የመብት ጥሰቶች በበቂ ማስረጃዎች ላይ የተመሰረቱ እና ሊካዱ የማይችሉ ክስተቶች ናቸው። የአምነስቲን መግለጫ ተከትሎ የተፈጠረውን ግርግር በመጠቀም በዚህ መልክ ለማጣጣል መሞከር በመንግስት በኩል ስህተቶችን ለማረም ዝግጅቱም ሆነ ፍቃደኝነቱ ብዙም የሌለ መሆኑን ነው የሚያሳየው።

ከቀናት በፊት ጠቅላይ አቃቤ ሕጓ ጉዳዩን እንመረምራለን ካሉ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ድርሰት ነው ማለታቸው እርስ በርሱ የሚጣረስ ብቻ ሳይሆን በሰብአዊ መብቶች አጠባበቅ ላይ ያሉ ግድፈቶችን ለማረም በመንግስት በኩር ቁርጠኝነት የሌለ መሆኑን ያሳያል። እንዲሁም በተዋረድ ያሉ የመንግስት አካላት እንዳይታረሙ፤ ከዛም አልፎ አጥፊዎቹ እንዲበረታቱም ያደርጋል። በአምነስቲ መግለጫ ውስጥ በደላቸው በበቂ ማስረጃ የተዘረዘረው ግለሰቦች ፍትሕን እንደሚሹ መዘንጋት የለበትም። በመገልጫው ውስጥ በዝርዝር በተገለጹትም ሆነ መግለጫው ባላካተታቸው ሌሎች የመብት ጥሰቶችም ላይ አስተዳደርዎት ቀጥተኛ ተጠያቂ ነው። ጉዳዩን ድርሰት ነው ከማለት የሚታረመውን ማረም፣ አጥፊዎችን ለፍርድ ማቅረብ እና ተበዳዮችን መካስ በለውጥ ላይ ካለ መንግስት የሚጠበቅ የዲሞክራሲያዊ ባህሪ ምልክት ነው።

ያሬድ ኃይለማርያም

 

1 Comment

  1. I share your opinion. But our incidental PM Abbiy os a naive politician who aspires to become dictatorship. His response for the abdacted girl student and human right report is the manifestation of the making of one man rule or authoritarian government.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.