‹‹የተጠየቅነው የሕግ ጉዳይ በመሆኑ ሒደቱ ሕግን ብቻ የተከተለ እንዲሆን አድርገናል›› ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊ

Meaza

የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በአብዛኛው የሚታወቀው የግለሰቦች፣ የቡድኖች ወይም የክልሎች አለመግባባቶች ሲፈጠሩና ክርክር ተደርጎባቸው ውሳኔ ያረፈባቸው ወይም በክርክር ሒደት ላይ እያሉ፣ ሕገ መንግሥታዊ ተቃርኖ ያላቸውን ሕጎችና ሐሳቦች በፍርድ ቤት ወይም በግለሰቦች ሲቀርቡለት፣ ጉዳዩን መርምሮ ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል ወይም አያስፈልጋቸውም›› የሚል ውሳኔ ሲሰጥ ነው፡፡ በዚህ ዓመት መገባደጃ ላይ የገጠመው ጉዳይና ራሱም የወሰደው ያልተለመደ ዕርምጃ ግን፣ ‹‹እንዲህም ይቻላል እንዴ?’›› ከማስባልም ባለፈ የአብዛኛውን ሕዝብ ትኩረት ያገኘ ሲሆን፣ ትችትና ተቃውሞም ቀርቦበታል፡፡ ጉባዔው ከሕግ አውጪው ምክር ቤት የቀረበለትን ጥያቄ ባልተለመደ ሁኔታ ግልጽ በሆነ መድረክ ለሕዝብ ይፋ በማድረግ፣ ‹‹ጉዳዩ የግለሰብ፣ የቡድን ወይም የተቋማት ብቻ ሳይሆን የሁሉም ሕዝብ ነው›› በማለት የተመረጡ የዘርፉ ባለሙያዎችንና ኤክስፐርቶች ሐሳባቸውን እንዲሰጡበት አድርጎ ውሳኔውን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ሰሞኑን ልኳል፡፡ ጉባዔው ያደረጋቸውን አጠቃላይ ሒደቶችና ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከት፣ የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት ወ/ሮ መዓዛ አሸናፊን ታምሩ ጽጌ አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡– በኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመታወጁና አገራዊ ምርጫ ማካሄድ ስላልተቻለ የፓርላማውና የሥራ አስፈጻሚው ቀጣይ ዕጣ ፈንታን ለማወቅ፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱን መተርጎም ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም?›› የሚለውን ጥያቄ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ መርምሮና አጣርቶ የውሳኔ ሐሳቡን ለፌደሬሽን ምክር ቤት እንዲያቀርብ የላከለትን ጥያቄ በአጭር ቀናት ውስጥ መርምሮና አጣርቶ ባለፈው ሳምንት የውሳኔ ሐሳቡን ለምክር ቤቱ ልኳል፡፡ ጉባዔው እንደተለመደው የቀረበለትን ጥያቄ ቢሮው ውስጥ ጨርሶ የውሳኔ ሐሳቡን ከመላክ ይልቅ ጥያቄውን በግልጽ መድረክ ላይ በማቅረብ የባለሙያዎችንና ኤክስፐርቶችን አስተያየትና ሐሳብ አዳምጧል፡፡ በአገሪቱ ያልተለመደና አዲስ ጅምር መሆኑን የሚበረታታ እንደሆነ የሚገልጹ ቢኖሩም፣ ሒደቱ ያልተሟላና አድሏዊነት ያለበት ነው የሚሉም አሉ፡፡ ስለአጠቃላይ ሒደቱ እርስዎ የሚሰጡት አስተያየት ምንድነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- አመሰግናለሁ፡፡ መጀመርያ አንድ ነገር ገልጬ ለማለፍ እፈልጋለሁ፡፡  እኔና አንተ የምናደርገው ውይይት፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ከሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የተላኩለትን የውሳኔ ሐሳብ ዓይቶ አንድ ውሳኔ ከደረሰ በኋላ ቢሆን ኖሮ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ምክንያቱም ዝርዝር ጉዳዮችን አንስተን መነጋጋር እንችል ነበር፡፡  በሌላ በኩል ግን ይህንን ቃለ መጠይቅ ለማድረግ ፈቃደኛ የሆንኩበት ሌላ ምክንያት ስላለኝ ነው፡፡ ያም ምንድነው? ይህ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ብዙ ሐሳቦች እንዲነሱ አድርጓል፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ያልተመለሱ ጥያቄዎች ካሉ መቆየት ስለሌለባቸው ሕዝቡ ምላሽ ማግኘት አለበት የሚል እምነት ስላለኝ ነው፡፡ ዝርዝር ጉዳይ ውስጥ አልገባም፡፡ ላይ ላዩንና አንዳንድ ጉዳዮች ላይ ብንወያይ ደስ ይለኛል፡፡  በተደረገው ውይይት ከተጠበቀው በላይ አስተያየቶች ተንሸራሽረዋል፡፡ ይህ ጥሩ ነገር ነው፡፡ ጉዳዩ ግዙፍ ከመሆኑ አንፃር ግን ብዙም የሚገርም አይደለም፡፡ ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ብዙ ጉዳዮች ይመጡለታል፡፡ በፍርድ ቤት ክርክር እርካታ ያልተገኘባቸው ጉዳዮች፣ ‹‹የሕገ መንግሥት ትርጉም ያስፈልጋቸዋል›› እየተባሉ ይመጣሉ፡፡ ይህ ግን ‹‹የአንድ አገር ሕግ አውጭና የሕግ አስፈጻሚ አካል የሥራ ዘመን ምን ይሁን?›› የሚል፣ ሁሉንም ኢትዮጵያዊ የሚመለከት ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ጉዳዩ በሰፊው መነሳቱ የሚገርም አይደለም፡፡ የሕግ ባለሙያዎች ያንሸራሸሩት ሐሳብ፣ ያሳዩት ፍላጎትና በጽሑፍ ጭምር ያደረጉት አስተዋጽኦ እንድኮራ አድርጎኛል፡፡ ለጉባዔውም ቢሆን ትልቅ ዕድልና በር የከፈተ ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ጉባዔው በአንድ በኩል የሚሠራው ቴክኒካዊ ሥራ ነው፡፡ ስለዚህ እስካሁን ስለሚሠራው ሥራ ብዙም የሚታወቅበት ሁኔታ አልነበረም፡፡ አንዳንድ ሰዎች ሲናገሩ፣ ‹‹የጉባዔው ጽሕፈት ቤት እንኳን የት እንዳለ አናውቅም ነበር›› ይላሉ፡፡ ትክክል ናቸው፡፡

አሁን ግን አዲስ ዕርምጃ ወስደናል፡፡ አዲሱ ዕርምጃ፣ ለጉባዔው የቀረበለት አገራዊ ጉዳይ ግዙፍ መሆኑን ተረድተን፣ ውይይቱ በግልጽ መካሄድ እንዳለበት ተስማማን፡፡ ‹‹ሕገ መንግሥቱ ይተርጎም ወይም ትርጓሜ አያስፈልገውም›› ከተባለ በተለመደው አካሄድ እንሄዳለን የሚለውን የቀድሞ አሠራርን ትተን፣ በግልጽ መድረክ ውይይት ለማድረግ ሁላችንም ተስማማን፡፡ እንደዚያ በማድረጋችን ለእኛም ሆነ ለሕዝቡ ትልቅ ጥቅም አስገኝቷል ብዬ አምናለሁ፡፡ በሌላ በኩል ስለሕገ መንግሥት ትርጉም በአገር ደረጃ እንዲህ ያለ ውይይት ተደርጎ ስለማያውቅ ከዚያም አንፃር ጥሩ ጥቅም ሰጥቷል፡፡ ተማሪዎችን ለጥናት ያነሳሳል፡፡  ሕገ መንግሥት መኖሩ ብቻ ሳይሆን የሕገ መንግሥት ሥርዓት ግንባታ ላይ ያለውን ጠቀሜታ ግንዛቤ እንድንወስድ አድርጓል፡፡ ሒደቱም የጉባዔው ተጠያቂነትን ያሳየም ይመስለኛል፡፡  ምክንያቱም ‹‹የተነሱት ጉዳዮች ምንድን ናቸው? ባለሙያዎች ምን ብለዋል? ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆኑ የመንግሥት ተቋማት ማለትም የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድና የጤና ሚኒስቴር አስተያየት ምንድነው?›› የሚለው ስለተገለጸ፣ በጉባዔው ውሳኔ ውስጥ ካልተካተቱ እኛም በሕዝቡ ተጠያቂ እንደምንሆን ራሳችንን አቅርበናል፡፡ ከዚህ አንፃር ሒደቱ ጥሩ ጅምር ነው የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡– የጉባዔው ሥራ ከፍርድ ቤት አሠራር የተለየ ባለመሆኑና ብቃት ያላቸው የሕግ ባለሙያዎችንና ከፍተኛ የፖለቲካ ተሳትፎ ያላቸው አባላት የያዘ በመሆኑ በራሱ ምርመራ አድርጎ ውጤቱን ማሳወቅ ሲገባው፣ ለሕዝብ ይፋ ተደርጎ ሐሳቦችን ማድመጥ አልነበረበትም የሚሉ አሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

ወ/ት መዓዛ፡-  ጉባዔው በትክክል ፍርድ ቤትን ተክቶ ይሠራል የሚለው ትንሽ አስቸጋሪ ነው፡፡  ነገር ግን የፍርድ ቤት ዓይነት (Quasi-Judicial) ቢባል የሚቀርብ ይመስለኛል፡፡  ምክንያቱም የሕግ ባለሙያዎቹ የጉባዔው አባል የሆኑት በሹመት ቢሆንም፣ የፍርድ ቤት ዳኞች በሚሾሙበት ሒደት ስላልተሾሙና ሁሉም አባላት የሕግ ባለሙያዎች ባለመሆናቸው፣ አሠራራቸውም ከፍርድ ቤት ዳኝነት ትንሽ የተለየ ነው፡፡ ነገር ግን ሌሎች መደበኛ ፍርድ ቤቶችም በአሁኑ ጊዜ አሠራራቸው ግልጽ ሆኗል፡፡ በቴክኖሎጂ የዳበሩ አገሮች እንኳን ትልልቅ ጉዳዮችን ትንንሽ ጉዳዮችንም በቀጥታ እያስተላለፉ ነው፡፡ ማንም ፍላጎት ያለው ቀርቦ ሊከታተል ይችላል፡፡ በተለይ በቀላሉ ስሜት የሚነኩ ትልልቅና አከራካሪ የምርጫ ጉዳዮችም በግልጽ ችሎት ይካሄዳሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል በጎረቤት አገር ኬንያ ባለፈው ያካሄዱትን የምርጫ ክርክር ፍርድ ቤቱ በግልጽ ችሎት ዓይቷል፡፡ ይህ የሚደረገው ግልጽነትን ለማምጣት ነው፡፡ ኢትዮጵያም ውስጥ ከዚህ በኋላ በተለይ የሕዝብ ፍላጎት ያለበት ጉዳይ በፍርድ ቤትም ቢሆን በግልጽ በመገናኛ ብዙኃን መተላለፍ አለበት፡፡ ይህ ደግሞ የሕዝብን ተሳትፎ ያዳብራል የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡- የሕገ መንግሥት ትርጉም ለመስጠት ተከራካሪ ወገኖች መኖር አለባቸው፡፡ ይህ ደግሞ የተነሱት ክርክሮች የሕገ መንግሥቱን ድንጋጌ በሚቃረን ሁኔታ በተሰጡ ውሳኔዎች ላይ እንጂ፣ በራሱ በሕገ መንግሥቱ ድንጋጌዎች ላይ የማሻሻያ እንጂ የትርጉም ጥያቄ ሊቀርብ እንደማይችል ለሚከራከሩ ወገኖች የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡ እንግዲህ ከመግቢያችን እንደነገርኩህ የምናገረው ጥንቃቄ እያደረግኩ ነው፡፡ ምክንያቱም ጉባዔው ያነሳቸውን ጭብጦች፣ ያደረጋቸውን ክርክሮችና የደረሰባቸውን ውሳኔዎች መግለጽ አልችልም፡፡ ነገር ግን በዚህ ጥያቄ ላይ ጉባዔው ብይን ሰጥቶበት ስላለፈ የተወሰነ ነገር ማለት እችላለሁ፡፡ እንደተባለው የተለያዩ ሐሳቦች ቀርበዋል፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካቀረባቸው ጥያቄዎች አንዱ ጥያቄ ‹‹ጉባዔው ሥልጣን የለውም›› የሚል ነው፡፡ ነገር ግን ጉባዔው ሥልጣኑ ሰፋ ያለና ከሕገ መንግሥቱ የመነጨ መሆኑን በማስረዳት ነው ወደ ሥራ የገባው፡፡ የፍርድ ቤቶችንና ሕገ መንግሥቱን በሚቃረን መንገድ ውሳኔ ያገኙ ጉዳዮች ሲመጡለት ብቻ ሳይሆን፣ ከዚያም ሰፋ ያሉ ጉዳዮች ሊመለከት ይችላል፡፡ የሕገ መንግሥት ክርክር ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹የሕገ መንግሥት ጉዳዮችንም ይመለከታል›› የሚል ሥልጣንም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 84 ተሰጥቶታል፡፡  በዚህ ላይ ብይን ሰጥቶ ነው ወደ ሥራ የገባው፡፡ ዝርዝሩ ጉባዔው የሰጠው ውሳኔ ለሕዝብ ይፋ ሲደረግ የሚታይ ይሆናል፡፡

ሪፖርተር፡– ምርጫና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ቢገጣጠሙ ፓርላማውና አስፈጻሚው ምን እንደሚሆኑ ድንጋጌ ማስቀመጥ ያልተቻለው ባለማስተዋል ሳይሆን፣ ሆን ተብሎ መሆኑን ጉባዔው የጋበዛቸውና ሕገ መንግሥቱ ሲረቀቅ የተሳተፉ ሰዎች ምስክርነት ሰጥተዋል፡፡ የተተወውም ድንጋጌውን ምክንያት በማድረግ የሕግ ጥሰት እንዳይፈጸምና ሲደርስ ይታያል በሚል መሆኑን ስለገለጹ፣ አሁን የተፈጠረውን ችግር ትርጉም በመስጠት ሳይሆን፣ ሁለቱም ምክር ቤቶች ተወያይተው በሁለት ሦስተኛ ድምፅ ማሻሻል ይችላሉ የሚሉ በርክተዋል፡፡ ጉባዔው በዚህ ላይ ምን ይላል?

ወ/ሮ መዓዛ፡– አሁንም ይህንን ጥያቄ ዝርዝር አድርጌ ብመልስ ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ይህ ያነሳኸው ጥያቄ የጉዳዩ ዋና ‹‹ጭብጥ›› ነው፡፡ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ልንወያይበት እንችላለን፡፡ አሁን ግን ሐሳቤን ባልገልጽ ደስ ይለኛል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ በጽሑፍና በአካል ብዙ አስተያየቶች ለጉባዔው ቀርበዋል፡፡ ምክንያታቸው የተለያየ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱን ለመተርጎም የሚከለክል ነገር የለም የሚል ሐሳብ ቀርቧል፡፡ አንዳንድ አስተያየቶች ደግሞ ‹‹ትርጓሜ አያስፈልገውም››፣ ምክንያቱም በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 ድንጋጌ መሠረት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ ስለተፈቀደና መንግሥት ደግሞ በዚያ አዋጅ ብዙ መብቶችን መገደብ ስለሚችል፣ ያንን አንቀጽ መጠቀም ይችላል የሚል አስተያየት አለ፡፡ ከዚያ ባለፈ ደግሞ የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች ግልጽ ናቸው፡፡ ምንም ይሁን ምንም ‹‹ምርጫ በየአምስት ዓመቱ መካሄድ አለበት›› ይላል የሚሉ አሉ፡፡ አገላብጠን ብናያቸው ያው ናቸው
ሌላ ሐሳብ የለም፡፡ እነዚህን ሐሳቦች ጉባዔው ‹‹በጭብጥነት›› ይዞና በደንብ ተወያይቶ ውሳኔ ሰጥቶባቸዋል፡፡  ፌዴሬሽኑ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት ብዙ መወያየት ስለማንችል ነው እንጂ በዝርዝር መነጋገር እንችል ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- ጉባዔው አስተያየት የሚያቀርቡ (Amicus Curiae Brief) በተለይ የሕገ መንግሥት ምሁራንን የሚመርጥበትን መሥፈርት አውጥቶ መርጦ የተመረጡትም ያቀረቡት የትንተና መንገድ የተለየ ቢሆንም፣ የሁሉም መደምደሚያ ግን ‹‹ትርጉም ያስፈልገዋል›› የሚል ስለሆነ በደንብ ታስቦበት የተመረጡ ናቸው የሚሉ አሉ፡፡ የእርስዎ ምላሽ ምንድነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ይህ ጥያቄ ሒደቱን ለማስረዳት ስለሚጠቅመኝ ማንሳትህ ጥሩ ነው፡፡ ይኼንን ሒደት ያጠናቀቅነው በሃያ ቀናት ነው፡፡ በእነዚህ ቀናት ቢሆን ሌላ ሥራ አቁመን ይህንን ብቻ ነው የሠራነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይኼንን ጉዳይ ሲመራልን የድርጊት መርሐ ግብር (Action Plan) አወጣን፡፡ ምን ምን መሠራት እንዳለበት ዕቅድ አወጣን፡፡ ግልጽ የሆነ መረጃ የመሰብሰብ ሒደት ለማካሄድ ሁለት መንገዶች ነው የመረጥነው፡፡  አንዱ በቀጥታ ባለሙያዎችን መስማት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የባለሙያዎችን አስተያየት በጽሑፍ እንዲቀርብ ማድረግ ነው፡፡ ለሁለቱም ዕቅድ ስናወጣ የምንሰማቸውን ሰዎች በየትኛው ጉዳይ ላይ እንስማቸው በሚለው ላይ ብዙ ተወያይተን ነው ያሳለፍናቸው፡፡ በግምት ያደረግነው ነገር አይደለም፡፡ ያ ማለት ግን በመሀል አለመግባባት አይፈጠርም ወይም ክፍተት አይኖርም ማለት አይደለም፡፡ የመጀመርያ ሒደትም በመሆኑ ሊኖር ይችላል፡፡  ነገር ግን በደንብ እያሰብንበት ነበር የሄድነው፡፡ አራት መሥፈርቶችን አወጣን፡፡ የመጀመርያው ከሕግ ጋር ግንኙነት ያላቸው ተቋማት ማለትም የሕግ ትምህርት ቤቶች፣ የጠበቆች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበርና የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያ ሴቶች ማኅበር ናቸው፡፡ ሁለተኛው ሕገ መንግሥት የሚያስተምሩና ብዙ መጻሕፍት የጻፉ ናቸው፡፡ ሦስተኛ ጠቅላላ የሕግ ባለሙያዎች ሆነው በሕገ መንግሥት ጉዳይ ላይ አስተያየት መስጠት የሚችሉ ሲሆኑ፣ አራተኛ ሕገ መንግሥቱ ሲቀረፅና ሲፀድቅ ተሳትፎ የነበራቸው ናቸው፡፡ እከሌ ዘመዴ ስለሆነ፣ ጓደኛዬ ስለሆነና ስለማውቀው በሚል ሳይሆን በተቀመጡት መሥፈርቶች መሠረት የሚመጥነውን መርጠን አሳልፈናል፡፡ ሰዎቹ ከመመረጣቸው ባለፈ ሐሳባቸውን ሲያቀርቡ በቀጥታ በቴሌቪዥን እንደሚተላለፍ ከማወቅ ውጪ፣ ማን ምን  እንደሚያቀርብ ከሕዝቡ ጋር እኩል ከማወቅ ባለፈ የተለየ የምናውቀው ነገር አልነበረም፡፡

ይኼንን ኃላፊነት (Risk) ወስደን ነው ያቀረብናቸው፡፡ አሳማኝ፣ ምክንያታዊ፣ መሠረታዊና በቂ አስተሳሰብ ያለውን ለመቀበል ጉባዔው ይገደዳል፡፡ ያ የሚያሳየው አስቀድመን ያሰብንበት ነገር አለመኖሩን ነው፡፡ ግልጽነት የሚባለውም ይኸው ነው፡፡ በሌላ በኩል ሙያዊ አስተያየት በሦስት ሺሕ ቃላት የተገደበና በተወሰነለት ጊዜ እንዲቀርብ አስታውቀን ነበር፡፡ በአካል ቀርበው አስተያየታቸውን የሰጡ ባለሙያዎች በጽሑፍም ማብራሪያ አቅርበው ሊሆን ይችላል፡፡ እውነት ለመናገር በወቅቱ የእነሱን የጽሑፍ ማብራሪያ አላየነውም፡፡ የጽሑፍ ማብራሪያ የመጨረሻ ማስገቢያ ቀን ግንቦት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ነበር፡፡ በቀጥታ ቴሌቪዥን አስተያየታቸውንና ሐሳባቸውን የሚያቀርቡት ባለሙያዎች የተቀጠሩት ግንቦት 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ነው፡፡ ጊዜ ስላልነበረን የጽሑፍ ማብራሪያውን ልናየው አልቻልንም፡፡ ምን እንደ ጻፉም ያወቅነው ነገር አልነበረም፡፡ አንድ ቀን አርፈን ደግሞ ግንቦት 10 ቀን 2012 ዓ.ም. ሌሎች የተመረጡ የሕገ መንግሥት አርቃቂዎችና አፅዳቂዎችን ሰማን፡፡ ጊዜ ስላላገኘንና የጽሑፍ ማብራሪያቸውን ለማየት ሌላ ጊዜ ስለያዝንለት በዚያን ወቅት አላየነውም፡፡ የሆነው ይኸው ነው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን “ሆን ብለው አስቀድመው መርጠው፣ እያወቁ፣ ወዘተ” የሚሉ አስተያየቶችን ሰምቻለሁ፡፡ የመንግሥት ተቋምና ኃላፊዎች ሊተቹ ይችላሉ፡፡ ለትችትም ዝግጁ መሆን አለብን፡፡  የተባለው ግን በፍፁም ከእውነት የራቀ ነው፡፡ ምንም እንኳን አንዳንድ ጊዜ ችግር ቢኖርብንም፣ አዳዲስና ያልተለመዱ ዕርምጃዎችን ስንወስድ ልንበረታታ ይገባል፡፡ ተቋማትን ስንገነባ ማበረታታት ያስፈልጋል፡፡ ዕድል ሊሰጠን ሲገባ አንዳንድ አስተያየቶች ግን ተገቢ ናቸው ብዬ አላስብም፡፡

ሪፖርተር፡- ‹‹ሕገ መንግሥቱ መሻሻል እንጂ ሊተረጐም አይገባም” የሚል አቋም ያላቸው፣ ለምሳሌ ዓለም አቀፍ የኦሮሞ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር በአካልም ሆነ በጽሑፍ ለመሳተፍ ያቀረበውን ጥያቄ ጉባዔው እንዳልተቀበለው አስታውቋል፡፡ ሌሎችም በተመሳሳይ ሁኔታ ወቀሳ ሲያቀርቡ ነበርና ስለዚህ ጉዳይ ቢያብራሩልን?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ጉባዔው ባቀረበው መሥፈርት መሠረት የቀረቡና ያቀረቡ ሰዎች ተመርጠዋል፡፡  በጽሑፍ አስተያየት የሰጡ ቡድኖችና ግለሰቦችም አሉ፡፡ በቁጥር  የፈረሙ 34 ሰዎች ሲሆኑ፣ አስተያየቶች ግን እንደ አስተያየት ሲቆጠሩ 22 ናቸው፡፡  የጠቀስከው ዓለም አቀፍ የኦሮሞ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበርም አንዱ ነው፡፡ የጻፈውን አስተያየት በደንብ አንብበነዋል፡፡ ‹‹አስተያየታችን ከግምት ውስጥ አልገባም፣ አልተቀበሉንም›› የሚለው ወቀሳ መምጣት ያለበት፣ ወይም ‹‹ያነሳነው ሐሳብ ከግምት ውስጥ ገብቷል ወይስ አልገባም›› የሚለውን ለመናገር፣ ጉባዔው የሰጠውን ውሳኔ ዝርዝር ማየት ያስፈልጋል፡፡ ‹‹እከሌ እንደዚህ አቅርቧል፣ እከሌ እንደዚህ አላቀረበም›› ማለት ባልችልም፡፡ ትንታኔ ሲሰጥ ግን፣ ‹‹ሕገ መንግሥቱ ሊተረጎም ይገባዋል›› የሚለው ሰፊ ክፍል ሲሆን፣ “በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 ድንጋጌ መሠረት መንግሥት ሥልጣኑን ማራዘም ይችላል፣ በመሆኑም ትርጉም አያስፈልገውም” እና ‹‹ሕገ መንግሥቱ ግልጽ ስለሆነ ምንም ዓይነት ትርጉም አያስፈልገውም›› የሚል ነው የቀረበው የጽሑፍ ማብራሪያ፡፡ አንዳንዱ የፖለቲካ ስሜት ያለው አለ፡፡ ጉባዔው በያዘው ጭብጥ ውስጥ ከሆነ ታሳቢ ተደርጎ ሊሆን ይችላል፡፡ ከጭብጥ ውጪ ከሆነ ለማስተናገድ ሁኔታው አይፈቅድም፡፡ በሌላ በኩል ይህ የሕግ ሒደት ነው፡፡ የፖለቲካ ውይይት፣ ንግግርና ስምምነት ያስፈልጋል፡፡ ይህ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን ሁሉም እንዳገባቡ (context) መሆን አለበት፡፡ የተጠየቅነው የሕግ ጉዳይ በመሆኑ ሒደቱም ሕግን ብቻ የተከተለ እንዲሆን አድርገናል፡፡ በዚህም ግቡን መቷል ብዬ አስባለሁ፡፡ በእንደዚህ ያለ ሰፊ ጉዳይ ደግሞ ቅሬታዎች መነሳት የለባቸውም አይባልም፡፡ መነሳቱ ክፋት የለውም፡፡ የመንግሥት ኃላፊ ስትሆን ከሥራው ጋር ተያይዞ ለትችት ትዳረጋለህ፡፡ ይህ ደግሞ የሚያስከፋ አይደለም፡፡  ሕዝቡ ጥሩ መረጃ እንዲያገኝ ትችቱም ሆነ አስተያየቱ እውነት ላይ የተመሠረተ ቢሆን ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- ጉባዔው የሕግ ባለሙያዎችን መስማት እንደሚችል በአዋጅ የተደገፈ ሥልጣን ከመስጠት ባለፈ፣ የሰማውን አስተያየት በውሳኔው ውስጥ እንዲያካተት የሚያስገድደው ነገር የለም፡፡ አቅራቢውም ‹‹ለምን አስተያየቶቼ አልተካተቱም›› ብሎም የመጠየቅ መብት የለውም፡፡ ሐሳብ እንዳላቸው የሚገልጹትን ሁሉ ቢያዳምጥ ከሚጠቅመው ባለፈ የሚጐዳው ነገር አለ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ትክክል ነው፡፡ ጉባዔውን ለማቋቋም በወጣው አዋጅ ቁጥር 798(9) ድንጋጌ፣ ጉባዔው የሰውም ይሁን የሰነድ ማስረጃ አስቀርቦ መመልከት እንደሚችል ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡ እስካሁን ብዙ አልተጠቀምንበትም፡፡ አልፎ አልፎ ኤክስፐርቶችን አስጠርተን እንሰማ ነበር፡፡ ይህ የጉባዔው ግዴታ ሳይሆን መብት ነው፡፡ ጉባዔው ያስፈልገኛል ያለውን ብቻ መውሰድ ይችላል፡፡ ሰፋ ያለውን መርሆ ስናይ ደግሞ በሕገ መንግሥቱ ተደንግጎ እንደሚገኘው፣ የመንግሥት አካላት አሠራራቸው ለሕዝብ ክፍት መሆን አለበት፡፡ ግልጽነት ሊኖር ይገባል፡፡ በዚህ በኩል ስናየው ለሕዝብ ግልጽ አድርገን መሥራታችን ተገቢ ነው፡፡ ከዚያ በላይ ቀን ወስደን ለመስማት ግን ቀድመን ያቀድነው ሦስት ቀናት ብቻ ሲሆን፣ ይህም የባለሙያዎችን አስተያየት ለመስማት ነበር፡፡ ያንን አድርገናል፡፡ ሐሳባቸውን መግለጽ የሚፈልጉ በግል የጻፉልን ነበሩ፡፡ ሁሉንም ማስተናገድ ቢቻል ጥሩ ነበር፡፡ ነገር ግን አንዳንድ ጉዳይ በጊዜ ገደብ መከናወን አለበት፡፡ ለዚህ ግዙፍ ሐሳብ ደግሞ እኛ ያደረግነው ውይይት ብቻ በቂ አይደለም፡፡ ገና ብዙ ብዙ የውይይት መድረኮች ይኖሩታል፡፡ ሳይካተት የቀረና ጉባዔው ያልያዘው ጭብጥ ካለ የጉባዔው ውሳኔ ሲታይ ለመተቸት ዝግጁ ነን፡፡

ሪፖርተር፡- ጉባዔው በግልጽ መደረክ ያደረገው ውይይት ፈር ቀዳጅና ወደፊትም በሌሎችም ተቋማትም ልምድ ሆኖ እንዲቀጥል ብዙዎች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ነገር ግን ጉባዔው ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች አመራሮችን ዕድል ሰጥቶ ቢሆን ኖሮ፣ ጅምሩን ሙሉ ያደርገው ነበር የሚሉ አሉ፡፡ ይህ ባለመደረጉ ቅሬታቸውን የገለጹ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህንን ለማድግ ሐሳብ አልነበራችሁም?

ወ/ሮ መዓዛ፡- የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ሚናው በግልጽ ተተርጉሟል፡፡ ሚናው ሕገ መንግሥታዊ ጉዳዮችን መተርጎም ነው፡፡ ሕገ መንግሥት የሚተረጎመው በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት የሕግና የፖለቲካ ሠነድ ቢሆንም፣ ወደ ሕገ መንግሥት ትርጉም ሲገባ ደግሞ የፍርድ ቤትን አካሄድ ተከትሎ የሚከናወን ነው፡፡ እኛም ያደረግነው ያንን ነው፡፡ ዕድሉ ቢኖር ጥሩ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድና የጤና ሚኒስቴርን የሚያነሱ አሉ፡፡ እነሱ የቀረቡት የኤክስፐርት አስተያየት እንዲሰጡ ነው፡፡ ምክንያቱም ሁለተኛው ጥያቄ፣ “የኮረና ወረርሽኝ የአገር ሥጋት መሆኑ የሚያቆመው መቼ ነው? ምርጫስ የሚካሄደው ወረርሽኙ ከቆመ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ነው?” ለሚሉት ጥያቄዎች ጉባዔው በግምት መናገር ስለማይችል፣ የሁለቱንም ተቋማት ኤክስፐርቶች ጋብዞ ማብራሪያ እንዲሰጡ አድርጓል፡፡ የእነሱም አስተያየት ከፖለቲካ ፓርቲዎች አስተያየት የተለየ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱ በታወቀ በሳምንቱ ፍርድ ቤቶች በከፊል ዝግ እንዲሆኑ አድርጋችኋል፡፡ ከዚያም በኋላ በሁለት ዙር እስከ ግንቦት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ተራዝሟል፡፡ በተለይ በወንጀል ጉዳይ ተጠርጥረው የተከሰሱና የታሰሩ የመብት ጥያቄ እያነሱ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ ምን እያሰበ ነው?

ወ/ሮ መዓዛ– ኮሮና ለእኛም ሆነ ለሌላው አለም ፈታኝ የሆነ ወረርሽኝ ነው፡፡ በምንም ሁኔታ ፍርድ ቤት ሊዘጋ የማይችል ተቋም ቢሆንም በከፊል ለመዝጋት ተገደናል፡፡ ይህ ሁኔታ ግን በመላው ዓለምም የተደረገ ነው፡፡ ምንም እንኳን ፍርድ ቤቶች በከፊል ቢዘጉም፣ በየደረጃው ያሉ ፍርድ ቤቶች ዳኞች በሺዎች የሚቆጠሩ መዝገቦች ላይ ውሳኔ ሰጥተዋል፡፡ ምንም እንኳን ፍርድ ቤቶች ዝግ ቢሆኑም ወደ ፍርድ ቤት የሚያመጡ ጉዳዮች አሉ፡፡ የቤተሰብ፣ የቀለብ፣ የሁከትንና ቀላል የወንጀል ጉዳዮችን ፍርድ ቤቶች  እያዩ ነው፡፡ ቀደም ብሎ “ተረኛ ችሎት” ብለው በአንዳንድ ዳኛ ይታዩ የነበሩ ጉዳዮች በመብዛታቸው ሁለት፣ ሁለት ዳኞች እየሆኑ በቋሚነት እየሠሩ ነው፡፡  የኮረና ጉዳዮችም ተጨምረዋል፡፡ ጊዜ የማይሰጡ የፍትሕ ጉዳዮችን ማየት ግዴታችን ነው፡፡ በሌላ በኩል አሁን እያየናቸው ካሉ ጉዳዮች በተጨማሪ፣ ‹‹ምን ዓይነት ጉዳዮችን በተጨማሪ እንይ?›› በሚለው ላይ እየተወያየን ነው፡፡ በማረሚያ ቤት ላሉ ተከሳሾች በቪዲዮ ኮንፈረንስ ክርክሮችን ማድረግ ጀምረናል፡፡ አስቸኳይ የሆኑና የሰው መብት የሚነኩ ጉዳዮችን በሚመለከትም እየተነጋገርን ነው፡፡   

ሪፖርተር፡– በተለይ የወንጀል ጉዳዮችን በሰፋፊ ችሎቶች ርቀትን ጠብቆ በማከራከር ፍትሕ መስጠት አይቻልም ነበር?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ትክክል ነው፡፡ ሁሉንም የወንጀል ጉዳዮች ባንልም አንዳንድ ክሶች ሊቆዩ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ቀለል ያሉ ክርክሮችን ተጠርጣሪዎቹ ብቻ ባሉበት ክርክር ለማድረግም እያሰብን ነው፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚያያቸው ጉዳዮች ከበድ ያሉ ናቸው፡፡ ከ50 እስከ 100 የሚደርሱ ሰዎች አንድ ላይ ይከሰሳሉ፡፡ እነዚህን ደግሞ በቪዲዮ ኮንፈረንስም ሆነ በችሎት ለማየት ከባድ ነው፡፡

ሪፖርተር፡– በቪዲዮ ኮንፈረንስ የሚደረጉ ክርክሮች ምን ያህል ሥነ ሥርዓታዊ ናቸው? ተገቢ የሆነ ክርክር ማድረግና ትክክለኛ ፍትሕ ለመስጠት ይቻላል?

ወ/ሮ መዓዛ፡- የሚቻለው ነገር እየተሞከረ ነው፡፡ በተወሰነ ደረጃ ክርክሮቹ በጥሩ ሁኔታ ተጀምረው የሚጠናቀቁበት ሁኔታ አለ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የመቆራረጥ ችግሮች አሉ፡፡ እየተሻሻሉ ይሄዴሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡ የግድ አቅማችንን በቴክኖሎጂ አጠናክረን መቀጠል አለብን፡፡

ሪፖርተር፡– ተከሳሾች በሌሉበት ውሳኔ እየተሰጠና ውሳኔው በፍርድ ቤት ድረ ገጾች እየተለቀቀ መሆኑ ተገልጿል፡፡ ነገር ግን ቴክኖሎጂ ሊያገኙ የማይችሉ ተከራካሪ ወገኖች የውሳኔ ግልባጭ ሊያገኙ አይችሉም፡፡ ከዚህ አንፃር ውሳኔው ቢሠራም ጊዜው ሲስተካከል ውሳኔው እንዲነገር መደረግ አለበት ለሚሉ ወገኖች ምላሽዎ ምንድነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ሦስቱም ፍርድ ቤቶች ተነጋግረው ካለው ተጨባጭ ሁኔታ አንፃር፣ ውሳኔዎችን አጠር አድርጎ በድረ ገጽ መግለጹ የተሻለ መሆኑን ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቶቹም በስምምነቱ መሠረት እየሠሩ ቢሆንም፣ አንዳንድ ዳኞች ‹‹ውሳኔ ሠርቼ ማሰማት የምፈልገው በችሎት ነው›› የሚል አስተያየት ስላቀረቡ፣ ያቀረቡት አማራጭ ተትቶላቸዋል፡፡ ይኼ ደግሞ የዳኞቹን መብት ያከበረ አካሄድ ነው፡፡ ነገር ግን ከሚቀጥለው ሳምንት ጀምሮ ውሳኔ ያገኙ መዝገቦችን ውሳኔ ግልባጭ እንዲወስዱ ይደረጋል፡፡ ምክንያቱም ተከራካሪ የውሳኔ ግልባጭ አግኝቶ የተወሰነበትን ወይም የተወሰነለትን ውሳኔ የማወቅ መብት አለው፡፡ ምንም እንኳን የተወሰነለት ማስፈጸም፣ የተወሰነበት ደግሞ ይገባኝ ለማለት ጊዜ እንዲያገኝና እንዲዘጋጅ ያደርጋል፡፡ የፍርድ ቤትን ሥራም ያቃልላል፡፡ ይኼንንም በጥንቃቄ ነው የምናደርገው፡፡ ምክንያቱም በርካታ ሰው በአንድ ጊዜ ሊመጣ ስለሚችል፣ በቅደም ተከተልና በወረፋ ግልባጫቸውን ለመስጠት እየተዘጋጀን ነው፡፡

ሪፖርተር፡– የተወሰነበት ተከራካሪ በወረርሽኙ ምክንያት ይግባኝ የሚልበት ጊዜ ቢያልፍ በሥነ ሥርዓቱ መሠረት ይግባኙ ውድቅ ይደረጋል? ወይስ ፍርድ ቤቶቹ ኮሮናን ከግምት ውስጥ በማስገባት በመጡበት ጊዜ የይግባኝ አቤቱታቸውን ይቀበሏቸዋል?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ይኼንን በሚመለከት ተከራካሪዎች ሐሳብ እንዳይገባቸው ከመጀመርያው ጀምሮ አስታውቀናል፡፡ በወረርሽኙ ምክንያት ተከራካሪዎች በሥነ ሥርዓት ሕጉ ድንጋጌ መሠረት ሳይሆን፣ በልዩ ሁኔታ ማስረዳት ሳይጠበቅባቸው በዚህ ወቅት ለተሰጡ ውሳኔዎች ጊዜ አይገድባቸውም፡፡ በመጡበት ጊዜ ይገባኝ ማቅረብ ይችላሉ፡፡

ሪፖርተር፡– ፍርድ ቤቶች ኮሮናን በሚመለከት ለሠራተኞቻቸውና ወደ ፍርድ ቤቱ ለሚመጡ ዜጎች ምን እያደረጉ ነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- በፍርድ ቤቶች ኮሮና ወረርሽኝን በሚመለከት መመርያዎችን አፅድቀዋል፡፡ ግብረ ኃይልም ተቋቁሟል፡፡ የጤና መጠበቂዎችና የመከላከያዎች አቅርቦት ሳይጓደል ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚከታተልና የዕርምት ዕርምጃ የሚወስድ፣ የጤና ባሉሙያዎችን በመጋበዝ ግንዛቤ የሚያስጨብጥ፣ ሙቀት መለኪያ በፍርድ ቤቶቹ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል መመርያ አፀድቋል፡፡ ከሁሉም በላይ ግን የግል ግንዛቤና ጥንቃቄ ማድረግ ወሳኝ ነው፡፡ ምንጊዜም ለሕይወት ሚዛን ያስፈልጋል፡፡ አስቸጋሪ ጊዜ ቢሆንም ከተስማማን፣ ከተደማመጥንና የምንታዘዘውን ተግባራዊ ማድረግ ከቻልን እንወጣዋለን የሚል እምነት አለኝ፡፡

ሪፖርተር፡– የጠቅላይ ፍርድ ቤትና ሰበር ሰሚ ችሎት ዳኞች ከሌሎቹ ፍርድ ቤቶች ዳኞች በተለየ ሁኔታ በሥራ ቦታቻው ተገኝተው እንዲሠሩ ተደርገዋል፡፡ ሦስትና አምስት ዳኞች በአንድ ክፍል ውስጥ ውይይት ስለሚያደርጉ ምን የተለየ ጥንቄቄ ይደረግላቸዋል? ለምን በቤታቸው ሆነው እንዲሠሩ አልተደረገም?

ወ/ሮ መዓዛ፡- ቢሮ ግቡ የሚባል ግዴታ አልተጣለባቸውም፡፡ ነገር ግን ውይይቶችን የሚያደርጉት በጤረጴዛ ዙሪያ ነው፡፡ በመዝገብ ላይ ውይይት ስለሚያደርጉ  በየቤታቸው ሆነው መሥራት ስለማይችሉ ካልሆነ በስተቀር፣ በቤታቸው ሆነው እንዳይሠሩ አልተገደዱም፡፡ በፈለጉበት ሁኔታና ቦታ ሆነው መሥራት ይችላሉ፡፡ መጀመርያ ጊዜ ኮሮና እንደገባ የተስማማነው በትልቅ አዳራሽ ውስጥ ሆነውና ተራርቀው በመዝገብ ላይ ውይይት እንዲያደርጉ ነበር፡፡ በሒደት ግን በቴክኖሎጂ ተጠቅመን በስካይፒ (ሲስኮ ቴክኖሎጂ) በቢሮአቸው ውስጥ ሆነው እየሠሩ ነው፡፡ ይኼም በቂ አይደለም፡፡ ምክንያቱም በጥልቀትና ጊዜ የሚወስድ መዝገብ ስለሚያጋጥም፣ በቀላሉ በስካይፒ ተወያያቶ መጨረስ የማይቻልበት ሁኔታ ስላለ ሁሉም በኃላፊነት ስሜት ራሳቸውን እየጠበቁና እየሠሩ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡– ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ የፍትሕ ሥርዓቱ ከአስፈጻሚው ጣልቃ ገብነት የተላቀቀና የተሻለ የፍትሕ ሥርዓት እየመጣ ቢመስልም፣ አሁንም በርካታ ተግዳሮቶች እንዳሉበት እየተገለጸ ነው፡፡ ፍርድ ቤት በዋስ የለቀቀውን ተጠርጣሪ ፖሊስ አለቅም በማለት፣ ክስ ተገኝቶለት እስከሚከሰስ ድረስ የተፈቀደለትን ዋስትና ተከልክሎ እስር ሲያቆይ እየታየ ነው፡፡ ሕግን ከማስከበርና ፍትሕ እንዲሰፍን ከማድረግ አንፃር ምን እያደረጋችሁ ነው?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እዚህ አገር ሴቶችን ወደ አመራር ሰጪነት በማምጣት ትልቅ ስኬት ተገኝቷል፡፡ ነገር ግን ይኼንን አናደንቅም፡፡ ለብዙ አገሮች ምሳሌ የሚሆንን ድርጊት ዕውቅና መስጠት አለብን፡፡ ምክንያቱም ከብዙ ትግልና ጥረት በኋላ የተገኘ ድል በመሆኑ ነው፡፡ ወደ አመራርነታቸው የመጡት ሴቶችም በአግባቡና በብቃት ኃላፊነታቸውን እየተወጡ ነው፡፡ ይኼንን የሚያደንቁ ወይም ዕውቅና የሚሰጥ አካል የለም፡፡ ግን መሆን አለበት፡፡ ፍርድ ቤትን በሚመለከትም እኔ ከመምጣቴ በፊት የአስፈጻሚው ጣልቃ ገብነት እንደነበር ይነገራል፡፡ ይኼንን መሻገራችንን እንደ ቀልድ ማየት የለብንም፡፡ በአሁኑ ጊዜ የፍርድ ቤቱ ዞን ተከብሯል፡፡ ምንም ዓይነት ጣልቃ ገብነት የለም፡፡ በጀትና አንዳንድ ጉዳዮች ሲኖሩን እኛ እንፈልጋቸዋለን እንጂ እነሱ ‹‹እንደዚህ አድርጉልን›› ብለው አያውቁም፡፡ አጋጥሞኝም አያውቅም፡፡ ስለአገር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ እንነጋገራለን፣ እንወያያለን፡፡ መወያየትም አለብን፡፡ አደጋው ባንነጋገር ነበር፡፡ ይኼ ትልቅ ድል ስለሆነ መነገር አለበት፡፡ ነገር ግን ሁሉም ነገር ባህል ነው፡፡ አሁንም አልፎ አልፎ ችግሮች አሉ፡፡ ፖሊስ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ አልፈጽምም አለ የሚባለው እኔ ዘንድ  ተረጋግጦ የመጣ ነገር ባይኖርም ሊኖር ይችላል፡፡ ችግር ሲኖር ግን ፊት ለፊት መጋፈጥ አለብን፡፡ ዓብይ ኮሚቴ ስላለን ያሉትን ችግሮች መፍታት አለብን፡፡ የሽግግር ወቅት ስለሆነና አሁን ደግሞ ኮሮና በመከሰቱ ለጊዜው ቢቆምም፣ የወንጀል ፍትሕ ጉዳይን መልክ ለማስያዝ ዓብይ ኮሚቴው ከሠራ ሁሉም ነገር መልክ ይይዛል፡፡

ሪፖርተር፡– እርስዎን ጨምሮ በርካታ አመራሮች ወደ ኃላፊነት ከመጣችሁ ሁለተኛ ዓመታችሁ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ በራሳችሁ ከሰማችሁት ወይም በሌላ በኩል ካረጋገጣችሁት፣ የሕዝብን ተቀባይነትና እምነት አግኝተናል ብላችሁ ታምናላችሁ?

ወ/ሮ መዓዛ፡- እኔ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም ተቋም ብዙ ክፍሎች አሉት፡፡ አንዱ አመራር ነው፡፡ ከማገኘው ግብረ መልስ ተቀባይነት ያለኝ ይመስለኛል፡፡ እኔ በሕዝብ ሥራ ላይ የኖርኩ ነኝ፡፡ ምን ዓይነት ዋጋ እንዳለኝ፣ ምን ዓይነት አስተሳሰብ እንደማራምድ፣ ፍላጎቴ ምን ሊሆን እንደሚችል፣ ምን ዓይነት ራዕይ ሊኖረኝ እንደሚችል በብዙ መንገድ የእኔን የሥራ ታሪክ ለመከታተል የቻሉ ሰዎች የሚገነዘቡት ይመስለኛል፡፡ እምነት ከሌለ ኃላፊነቴን በአግባቡ እንድወጣ የሚያስገድድ ነው፡፡ የሚፈጥረውና የሚጠበቅ ነገር (Expectation) አለ፡፡ ተቋም መገንባት ምን እንደሚፈልግና ምን ምን መደረግ እንዳለበት የማይገነዘብ፣ ‹‹ፍርድ ቤቱ ያው ነው፣ አሁንስ ምን ተለወጠ? ምን ተሠራ?›› ሊል ይችላል፡፡ ነገር ግን መታየት ያለበት ነገር አዲስ ባህል እየመጣ፣ አዲስ መሠረት እየተጣለ መሆኑን፣ በነፃነት ማሰብና ሐሳብን በነፃነት መለወጥ ችለናል? አሠራራችን ግልጽ ነው? ዜጎች ቅሬታቸውን የሚገልጹበት አሠራር ተዘርግቷል? የሚሉትን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ሁለት ትልልቅ አዋጆችን አርቅቀን ለፓርላማው ልከናል፡፡ አዋጆቹ ቶሎ ከፀደቁ ትልቅ ሥራ እናከናውናለን ብለን እናስባለን፡፡ ለፍርድ ቤቱ ሪፎርም ሥራ አዋጆች አስፈላጊ ናቸው፡፡ በሪፎርሙ እየተሳተፉ ያሉት የሕግ ባለሙያዎችን ማሳተፍ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ባለሙያዎቹ ክፍያ ሳይጠይቁ ለአገር ብለው የሚሠሩ በመሆናቸው ሊመሠገኑ ይገባል፡፡

ሪፖርተር

1 Comment

  1. ወ/ሮ መአዛ ግን ሳይስቁ ፎቶ አይነሱም ማለት ነዉ? አንድ ሳይስቁ ፎቶ አይቻለሁ የሚለኝ ማስረጃ ይላክልኝ።ሴትዮዋ አረማመዳቸዉ (ካት ዎክ) የሚሉት አይነት ሲሆን ሰዉ ጥርስሽ ያምራል ብሎ ሳያሳስታቸዉ አልቀረም መቼም ሰዉ ሁሌ አይደላዉም አንዳንዴ እራሳቸዉን ቢሆኑ ጥሩ ነዉ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.