አዎ እርግጥነ ነው ጣና ታሟል ፡፡ ልንታደገው ይገባል፡፡ – ፋሲል ተዘራ ከአዲስ አበባ

Tana 1

አዎ እርግጥ ነው ጣና ታሟል ፡፡ ልንታደገው ይገባል፡፡ ነገር ግን የጣና በለስ የሀይል ማመንጫ ፕሮጄክት ለእንቦጭ አረም መስፋፋት ዋነኛ መንስኤ ነው በሚል እየቀረበ ያለው አመክንዮ ትክክል አይመስለኝም፡፡ የጫራጫራ ግድብ መሰራትም እንዲሁ፡፡

የዚህ ፅሑፍ መነሻ ወንድምስሻ የተባሉ ፀሀፊ  በፌስ ቡክ ገፃቻው ላይ የፃፉትን ፅሁፍ በዘ- ሀበሻ ድረገፅ ላይ  ተለጥፎ ስላየሁ ነው (https://zehabesha.info/archives/105790) ፡፡ ይህንን ፅህፉ የቅርብ ወዳጆቼን ጨምሮ በርካታ ሰዎች በፌስቡክ ላይ ሲቀባበሉት ተመልክቻለሁ፡፡

ወንድምስሻ የተባሉት ፀሐፊ በዘ-ሀበሻ ላይ እንዳስነበቡን ለጣና ሀይቅ ወቅታዊ ችግር ዋነኛው መንስኤ እንቦጭ ሳይሆን የጣና በለስ የሃይል ማመንጫ ፕሮጄክት ፣ የጫራጫራ ክትር (ግድብ) እና ደለል ናቸው ይላሉ፡፡ ከዚህም አልፎ ፕሮጄክቱን  “’አጥፍቶ ጠፊው አሸባሪው ጣና በለስ”  ይሉታል፡፡ እኔ ደግሞ እነዚህ ምክንያቶች ትክክለኛና በሳይንሳዊ መንገድ ያልተረጋገጡ ምክንያቶች ናቸው ባይ ነኝ፡፡

የጣና በለስ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ውሃ የሚያገኘው ከጣና ሀይቅ ነው፡፡ ውሃው በቦይ (ዋሻ) ከሀይቁ ተጠልፎ ሃይል እንዲያመነጭ ከተደረገ በኋላ  በሌላ አቅጣጫ ተመልሶ ወደ ሐይቁ እንዲፈስ ስለተደረገ በዚህ ሂደት የሚጨምርም ሆነ የሚቀንስ የውሃ መጠን የለም፡፡

ደለልን በተመለከተ የጫራጫራ ክትር (ግድብ) በመገንባቱ ምክንያት  ወደ አባይ ወንዝ መግባት  የሚገባው ደለል  ጣና ሀይቅ ላይ እንዲከማች አድርጓል የሚለውም ሃሳብም ከመላ ምትነት የዘለለ አይደለም፡፡ ምክንያቱም ወደ ሃይቁ ደለል በብዛት የሚገባው በክረምት ወራት ነው፡፡ በዚህ ወቅት ደግሞ የጫራጫራ ግድብ በስፋት ተከፍቶ ወደ አባይ የሚፈሰው የውሃ መጠን ሲጨምር እያየን ነው፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ባህርዳር ድልድዩ ላይ ወይም ጢስ አባይ ፏፏቴ ላይ በክረምት እና በበጋ ወራት ያለውን የውሃ እና የደለል መጠን ልዩነት መመልከት ይቻላል ፡፡

ግድቡ እና ደለሉ ለእንቦጭ መስፋፋት ዋነኛ ምክንያት ናቸው ከተባለ ከዚህ ግድብ በፊት የተገነቡ ሌሎች የሃገራችን  ፕሮጄክቶች ለምን ቀድመው በእንቦጭ አልተወረሩም? ለምሳሌ የቆቃን ግድብ መመለከት ይቻላል፡፡ ቆቃ ለሃይል ማመንጫ አገልግሎት የተገደበው ከጣናው የጫራጫራ ግድብ በርካታ ዓመታት በፊት ነው፡፡ ቆቃ ዛሬ ላይ በከፍተኛ ደረጃ በደለል እየተሞላ ነው፡፡ ነገር ግን የእንቦጭ መጠኑ በጣም ዝቅተኛ ነው፡፡ የጊቤ ቁ.1 የሃይል ማመንጫ ግድብ የተገነባው ከጣና በለስ በፊት ነው፡፡ ወደ ግድቡ ቀስ በቀስ ደለል እየገባ ነው፡፡ ይህም ተፈጥሯዊ ግዴታ ነው፡፡ የእንቦጭ ችግር ግን የለበትም ማለት ይቻላል፡፡ ወይም ዝቅተኛ ነው ፡፡ የተከዜ ግድብም የተጠናቀቀው ከጣና በለስ ፕሮጄክት በፊት ነው፡፡ እንዲያውም በገፀምድር አቀማመጥ ካየነው በከፍተኛ ደረጃ በደለል ሊጠቃ የሚችለው የተከዜ ግድብ ነው፡፡ ምክንያቱም የተፋሰሱ የላይኛው የውሃው መነሻ አካባቢዎች እጅግ ተዳፋታማና በከፍተኛ ደረጃ የእፅዋት መመናመን ችግር የሚስተዋልበት አካባቢ በመሆኑ በከፍተኛ ደረጃ ለደለል ስጋት ተጋለጭ ግድብ ነው፡፡ ነገር ግን እሰካሁን ምንም አይነት የእንቦጭ ችግር አልሰማንም፡፡ ሌላው ቢቀር  የአባይ ወንዝ ውሃችንን እና ለም አፈራችንን ተሸክሞ ድንበር ተሻግሮ በደለል መልክ እየተጠራቀመበት ባለው የግብጹ አስዋን ግድብስ ለምን ይህንን ችግር አናይም ነበር?

እርግጥ ነው  ከጣና ሃይቅ እና ዙሪያው ውጪ የጫራጫራ ግድብን አልፈን በአባይ ወንዝ ጭምር የእንቦጭ ችግርን እያስተዋል ነው፡፡ እዚህ ቦታ ላይ እየተፈጠረ ላለው እንቦጭ ከጣና ወደ አባይ የሚፈሰው የውሃ መጠን ግፊት በመቀነሱ ምክንያት ደለል ስለሚተኛበት እና የወንዙን ዳር ዳር ገበሬው ስለሚያርሰው ነው በሚል የቀረበው አመክንዮ ውሃ አያነሳም – ምን አልባት ግድብ በመሰራቱ የውሃ መጠናችን ሊቀንስብን ነው ብለው ከወዲሁ ለሚሰጉት ለነ ግብፅ ጥሩ ድጋፍ ይሆን ካልሆነ በስተቀር፡፡  ከላይ እንደተጠቀሰው የደለል መጠናኑ ከጣና ሐይቅ በብዙ በሚበልጠው የአስዋን ሐይቅና ከዚያ በታች እስከ ሜዴትራኒያን ባህር ዳርቻ ድረስ የእንቦጭ መጠኑ ያን ያህል አስቸጋሪ ሆኗል ሲባል አልሰማንም፡፡ ስለሆነም የጣና በለስ እና የጢስ አባይ ቁ.1 እ ቁ. 2 የውሃ ሀይል ማመንጫ ፕሮጀክቶች ለእንቦጭ አረም መስፋፋት መንስኤ ናቸው የሚለው አስተሳሰብ በበቂ ጥናት የተደገፈ አይደለም፡፡

በሌላ በኩል ወደ ጣና ሐይቅ በሚፈሱ ወንዞች ላይ የተጀመሩ የመስኖ ግድቦችን መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ምንም እንኳ በተፈለገው ፍጥነት እና መጠን ባይሰሩም አሁን የተጀመሩ ግድቦች ወደ ሃይቁ የሚገባውን የደለል መጠን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋፅኦ እያበረከቱ ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ለምሳሌ የቆጋን ግድብ እና የመስኖ ፕሮጄክትን መመልከት ይቻላል፡፡ የርብ፣ ጉማራ እና መገጭ ፕሮጅክቶችም ቢዘገዩም እንኳ ወደፊት ደለልን ለመከላከል ከፍተኛ አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ ይልቅ ጥያቄው መሆን ያለበት ወደ ሀይቁ ከሚፈሱ በርካታ ወንዞች አንፃር እየተሰሩ ያሉ ግድቦች ጥቂት ብቻ ለምን ሆኑ?  ነው መሆን የነበረበት፡፡ በበርካታ ወንዞች ላይ ግድብ ቢሰራ ወደ ሐይቁ የሚገባው የደለል መጠን ይቀንሳል፡፡ እንደተባለው ደለል ለእነቦጭ መስፋፋት መንስኤ ከሆነም ችግሩን ይቀንሳል፡፡ በተጨማሪም ሰፋፊ የመስኖ ስራዎችን በማካሄድ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ፣ የስራ እድል በመፍጠር እንዲሁም የገበሬውን እና ከተማውን የገቢ ምንጭ ለማሳደግድ ይጠቅማል፡፡ በሌላ በኩል በአካባቢ ጥበቃ ዙሪያ ትኩረት ሊሰጥ ይገባል፡፡ የደኖች መመናመን እና የአርሶ አሰደሩ የአስተራረስ ዘይቤ ለሀይቁ የደለል ስጋት ዋንኛ መንስኤዎች ናቸው፡፡

በአባይም ሆነ በጣና ላይ የተገነቡት የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ፕሮጅክቶች ለተባለው የእንቦጭ ችግር ዋነኛ መንስኤ መሆናቸው ተገቢ በሆነ ሳይነሳዊ ጥናት ከተረጋገጠ ፕሮጅክቶቹን ከማፍረስ ወይም ማስቆም ይልቅ ለሚፈጥሩት ኢኮኖሚያዊ ፣ ማህበራዊና አካባቢያዊ ተጽእኖ ማካካሻ የሚሆኑ ሌሎች ፕሮጄክቶች እንዲተገበሩ ምክረ ሐሳብ ማቅረብ ተገቢ ይሆናል፡፡ እንቦጩን የሚነቃቅሉ ማሽኖቹን ቁጥር መጨመር አንዱ ቀጥተኛ መፍትሄ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ የአካባቢውን ህብረተሰብ የኤሌክትሪክ ሃይል ተጠቃሚነት እድል ይበልጥ እንዲሰፋ ማድረግ በማካካሻነት የሚታይ መፍትሄ ሊሆን ይችላል፡፡ እንቦጭ ከፈጠረው ችግር ባልተናነሰ መልኩ በክልሉ ያለው የኤልክትሪክ ሀይል አቅርቦት ስርጭት እና አገልግሎት ዝቅተኛ መሆን አካባቢውን የበይ ተመልካች እያደረገው ይገኛል፡፡ በዚህ ምክንያት በክልሉ ባለሃበቶች ገብተው ኢንዱስተሪ እንዳያስፋፉና የስራ እድል እንዳይፈጥሩ ያደረጋቸው የእስከዛሬው አድሏዊ የኤልክትሪክ ሀይል አቅርቦት እና ስርጭት አሰራር ሊስተካከል ይገባል፡፡ በአካባቢው የሚገኙ የኤልክትሪክ ሃይል ማመንጫ ፕሮጅክቶች ለዘመናት ከፍተኛ መጠን ያለው ሃይል አመንጭተው ለሃገሪቱ ብርሃን ሲሆኑ  ሰሞኑን ደብረታቦር ከተማ ላይ የተመረቀችውን አንዲት ትንሽዬ ተንቀሳቃሽ ሰብስቴሽን ለመገንባት  እና ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ ግን ይህን ያህል ደጅ መጥናት ባልተገባ ነበር፡፡ ቡሬ ና ደብረ ማርቆስ አካባቢም እየተገነቡ ያሉ ፋብሪካዎችም  ሃይል ለማግኘት እየናፈቁ ነው፡፡ ሰሞኑን የክልሉ ልሳን የሆነው በኩር ጋዜጣ እንደዘገበው በአሁኑ ወቅት 352 ኢንዱስትሪዎች በኤሌክትሪክ ሃይል አቅርቦት ችግር ምክንያት ወደ ስራ መግባት አልቻሉም፡፡  በአባይ ኢንዱስትሪያል እና በሌሎች የግል ባለሃብቶች የተጀመሩ እና ወደፊት ለመገንባት የታሰቡ ፕሮጅክቶች ነገም እንደ ዛሬው የኤሌክተሪክ ሃይል አቅርቦት ችግር ፈተና እንዳይሆንባቸው ከወዲሁ ሊታሰበብበት ይገባል፡፡ ይህ ሲሆን ቢያንስ እንቦጭም ሆነ ሌሎች ጋሬጣወቻችን እየፈጠሩብን ያሉትን ስጋት ማጥፋት ባይቻልም እንኳ ማካካስ  ያስችለናል፡፡ የሀይል ማመንጫ ግድቦችም ሆነ ደለል ለእንቦጭ መስፋፋት ምክንያት ቢሆንም ባይሆንም እንቧጬን በባህላዊና ዘመናዊ ዘዴዎች  ለማስወገድ የበለጠ መረባረብ ያስፈልጋል። በሀይቁ እና በአባይ ወንዝም ላይ የጎላ አካባቢያዊ ተጽእኖ የማያደርሱ የልማት ስራዎች ተስፋፍተው የህብረተሰቡ ተጠቃሚነት ሊጨምር ይገባል።

https://zehabesha.info/archives/105790

 

https://zehabesha.info/archives/105827

2 Comments

  1. You are a big layer. The water used by Tana Beles Hydro Power Station is not at all feed back to Lake Tana. The water is flowing to river Beles and is used also for irrigation and sugar plantation. So stop ur misinformation. Tana Beless must be closed immediately. The stolen water fall has to be restored.

  2. The nearby construction developments had been dumping so many tons of debris into Lake Tana regularly for decades which caused this problem, the Bahir Dar city knew the illegal dumping of debris into Lake Tana but failed to stop the practice due to corruption which brought this problem we face now. Investigation should be launched about illegal dumpings that went on for decades and the responsible parties including the ADP officials who let these dumping of debris
    practices continue need to be held accountable . Soon the crucifix will get robbed due to these weed problem on Tana which will be the final nail on Orthodox Ethiopia’s coffin.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.