በለቡ ሊዝ መንደር በተለምዶ ዶርዜ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እየተካሄደ ስላለው ሕገ ወጥ ግንባታ እና የመሬት ወረራ

ግንቦት 25/2012 ዓ/ም

ለወረዳ 2 አሰተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ
ለንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣
ለን/ስ/ላፍቶ ክ/ከተማ የመሬት ይዞታ አስተዳደር ሃላፊ

አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡ በለቡ ሊዝ መንደር በተለምዶ ዶርዜ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ እየተካሄደ ስላለው ሕገ ወጥ ግንባታ እና የመሬት ወረራን ይመለከታል

ባለፈው አንድ ወር በተለይም ባለፉት ሁለት ሣምንታት በአካባቢያችን በተለያዩ ቦታዎች የሚገኙ ለህብረተሰቡ የጋራ መጠቀሚያነት (green area) የተተው ህብረተሰቡም ዛፎችን ተከሎባቸው በእንክብካቤ የያዛቸውን ቦታዎች ጥቂት የተደራጁ ግለሰቦች ዛፎችን በመመንጠር በስፋት እያጠሩ እና ግንባታም ጭምር እያካሄዱባቸው ይገኛሉ፡፡ እስካሁን ድረስ ከታች በጉግል ካርታ ላይ እንደተመለከተው እነዚያን አራት ቦታዎችን ወርረው ይዘዋል፡፡

ለወረራ ሲመጡ ሕጋዊ ነን በማለት የሚያሣዩን ካርታ እንዲሁም አካሄድ ተመሣሣይ በመሆኑ የአንዱን ቦታ ካርታ፤ ተጨባጭ ሁኔታና አካሄድ ለናሙናነት ከዚህ በታች እናቀርባለን፡፡

  1. ግንቦት21/2012 ዓ/ም ከሃያ እስከ ሰላሳ ብዛት ያላቸው ቡድኖች መጥተው ለአካባቢ ነዋሪዎች የተያዘ ቦታ በወረራ አጥረውታል (በጉግል ካርታ ላይ green area 2 የተባለውን ቦታ ነው)
  2. በቦታው ተገኝተን ስለሕጋዊነታቸው ጠይቀን

ሀ)  ያሣዩን መረጃ በአቶ ሃሰን ሙሰማ አብዶ ስም የተዘጋጀ ካርታ ነው፡፡

ለ)   በካርታው ላይ ያለውን ሀሳባዊ ቁጥር (xy coordinate) ከጂፒኤስ ጋር ስናስተያየው አይገጥምም

ሐ)   በዕለቱ የተደራጁት አካላት ራሳቸው መጥተው ችካሉን ቸከሉ እንጂ ከመሬት አስተዳደር የተገኘ ባለሥልጣን አልነበረም፡፡ በቦታዉ ተገኝተን ስንጠይቃቸው ሃላፊነት የወሰደ ግለሰብም ሆነ በአግባቡ ሊያስረዳን የሚችል ባለሙያ አልነበረም፡፡

መ)   እነዚህ የተደራጁ አካላት የያዙት መረጃ በአብዛኛው ሕጋዊ ማህተም የሌለው ከመሆኑ ባሻገር እርስ በርሱ ያልተናበበ ሐሰት የበዛበት መረጃ ነው ::

ተጨማሪ ያንብቡ:  እጅግ አሳዛኝ ዜና ---የኢፌዴሪ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ

ለምሳሌ :- የግንባታ ፈቃድ ሰርተፍኬት ላይ ያለው የቦታው ንድፍ እና የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ላይ ያለው የተለያዩ ናቸው ፡፡ (ከደብዳቤ ጋር ተያይዟል)

  • የካርታ ንድፉ ላይ በሁለት ጎን እንጂ በቀረው መንገድ እንደሌለው ነው የሚያሳየው፤ ሆኖም በመሬት ላይ ባለው እና በአካባቢው ንድፍ (site plan) ላይ በሁሉም አቅጣጫ መንገድ እንዳለው ያሳያል፡፡
  • እነዚህ የተደራጁት አካላት በያዙትና በዚህ ዓመት በ12/7/12 ቀን በተሰጣቸው ካርታ ላይ በመሬቱ ላይ የነበረ ቤት እንዳለ ለመመልከት ችለናል ሆኖም በየትኛውም ዓመት በአዲስ አበባ መስተዳደር በተመዘገቡ የGIS ካርታዎችም ሆነ በአካል ምንም አይነት የተሰራ ግንባታ አያሳይም፤ አልነበረምም፤ አሁን ግን እንደነበረ ለማስመሰል ምንም አይነት መሰረት (foundation) የሌለው የቆርቆሮ ቤት አስቀምጠዋል፡፡
  • ለዕቃ ማስቀመጫ/store ግንባታ ፈቃድ ተሰጠን ያሉት በመሬቱ ሰሜን ምእራብ ማዕዘን በኩል ቢሆንም የሰሩት ግን ቀደም ሲል የጠቀስነውን ቤት በማስመሰል በመሬቱ ደቡብ በኩል ባለው አጥር መሃል ላይ ነው፡፡
  • ቦታው የሚፈልገውን የወለል ቦታ ምጣኔ/FAR ያላማከለ ሥራ መሆኑ ሕጋዊ መሰረት እንደሌለው ሌላ ማሳያ ነው፡፡
  • ካርታውን የሠጠው አካል በካርታው ላይ ስለይዞታ ሲገልጽ ‹‹ነባር ይዞታ›› በማለት ይገልጸዋል፡፡ ሆኖም ከ97 ዓ/ም በፊት በአካባቢ መሬቱን ይጠቀሙ ለነበሩ ባለቤቶች ካሣ ተከፍሎ አካባቢው ወደ ሊዝ መሬት መቀየሩን በወቅቱ ቦታው ሲሸነሸን የነበሩ ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም ከ97 ዓ/ም በኋላ ነባር ቦታ ብሎ በአካባቢ የለም፡፡
  • ብዙ የሰው ኃይል ይዞ መጥቶ መሬቱን ማጠርና ቆርቆሮ ቤቱን መስራት ሲጀምሩ በጊዜው ሆነ ከዚያ በኋላ ምንም አይነት ከሚመለከተው ቢሮ የተወከለ የምህንድስና ባለሙያ አልነበረም ስለሆነም የመንገድ ስፋትም ይሁን የነበረ መንገድን ሳያገናዝቡ እንዳሰኛቸው አካለዋል፡፡ ከዚህም የተነሣ አሁን በመሠራት ላይ የነበረው ኮብል ስቶን ሥራ ተስተጓጓሏል፡፡
  1. እቦታው ላይ ተገኝተን ይህን ከተገነዘብን በኋላ ለወረዳ 2 ለሚመለከተው አካል ሁሉንም አስረድተን ይህንን ሕገወጥ ወረራ እንዲያስቆሙ ስናመለክት ከላይ የተገለጸውን ያፈጠጠ እውነት እያዩ ሕጋዊ ናቸው በማለት አጥሩን ማጠር እንዲቀጥሉ በመፍቀድ፤ እናንተ ከፈለጋችሁ ካርታ የሠጠውን አካል መክሰስ ትችላላችሁ በማለት ሕገወጥ ወረራ እንዲቀጥሉ ፈቅደው ሄደዋል፡፡ በዚህ ሁኔታ በአካባቢው ነዋሪዎች የጋራ አገልግሎት እንዲሆን ተይዞ የነበረ ከላይ እንደገለጽነው አራት ቦታ በወረራ መልክ ታጥሮ ቀለል ያለ ግንባታ እየተካሄደበት ለሽያጭ ቀርቧል፡፡
ተጨማሪ ያንብቡ:  ፕሮፌሰር አየለ በክሪ፤ ስለንግሥተ ሳባ አፈ ታሪኮችና ታሪክ ይናገራሉ - Audio

 

  1. ይህ ከላይ የተገለጸው ቦታ እንደታጠረ በማግሥቱ በ22000000 (ሃያ ሁለት ሚሊዮን ብር) እንዲሸጥ ደላሎች ቦታውን እያሣዩ ይገኛሉ፡፡

ይህ በመሆኑ፤ እስካሁን ድረስ በአካባቢው አራት ቦታ ላይ ተመሣሣይ ካርታ ተሠርቶ የታጠረና ግንባታ እየተካሄድበት ለሽያጭ የቀረበ በመሆኑ ቦታዎችን የሚመለከተው አካል ከዚህ በታች ለናሙና ያቀረብነውን የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ ተመልክቶ እና ቀደም ብሎ የነበረውን መንገድ መሃል ገብተው ማጠራቸውን አይቶ፤

ሀ) ቤት በሌለበት ቦታ ላይ ቤት እንዳለ አድርጎ ካርታ አዘጋጅቶ የሰጣቸውን፤ የሊዝ መሬትን ወደ ‹‹ነባር ይዞታ›› የቀየረውን እንዲሁም የጂፒኤስ ኮኦርዲኔት የማያመለክተውን ቦታ እንዲያጥሩት በተጨማርም መንገድ እንዲያጥሩ የፈቀደ የመንግሥት ቢሮ የቱ እንደሆነ በማጣራት ተገቢ እርምጃ እንዲወስድ

ለ) የተሠሩ አጥሮችና የተጀመሩ ግንባታዎች ፈርሰው ቦታው ቀደሞ ለታቀደለት ሥራ እንዲውል፤ የተስተጓጎለው የኮብል ሰቶን ሥራ እንዲቀጥል እንዲደረግና ለአካባቢው ህጋዊ ማህበራት እና ነዋሪዎች እንዲመለስልን በአክብሮት እናመለክታለን

አሁን ባለው ገበያ እነዚህ ቦታዎች ከሃምሳ እሰከ መቶ ሚሊዮን ብር በላይ ሊያወጡ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ የመንግስት እና የህዝብ ሃብት አልባሌ በሆነ መንገድ ሲወረር ተገቢና ህጋዊ እርምጃ አለመውሰድ የሞራልም የህሊናም ተጠያቂነት እንዳለው በማመን ይህን አቤቱታ አቅርበናል፡፡ አፈጣኝ እርምጃ እንደሚወሰድ ተስፋ እናደርጋለን፡፡

እንደ አስፈላጊነቱና በምንጠየቀው መሠረት የምናቀርባቸው የምስል የተንቀሳቃሽ ምስልና የዓይን እማኝ ምስክሮች መኖራቸውን ለመግለጽ እንወዳለን፡፡

የጀሞ ሊዝ መንደር ነዋሪዎች፡ የአባላት ፊርማ አባሪ ሆኖ ከደብዳቤዉ ጋር ተያይዟል፡፡

ከሰላምታ ጋር

 

ግልባጭ

ለአዲሰ አበባ ከተማ ከንቲባ ጽ/ቤት፤
ለጠቅላይ ሚ/ር ጽ/ቤት፤
ለጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር፤
ለብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሃላፊ
ለብዙሃን መገናኛ ድርጅት

ተጨማሪ ያንብቡ:  እስራኤል ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ 60ሺህ አፍሪካውያንን ከሃገሬ አስወጣለሁ አለች

61 62 63 64 65 66

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.