/

የሰሚ ያለህ! እንደ አሜሪካው ጆርጅ ነፍስ ሁሉ የኢትዮጵያውያን ሰማእታት ነፍስም ፍትህን እየጮኸ ነው!

ከበላይነህ አባተ ([email protected])

bubu bar

ባለፈው ሳምንት አሜሪካ አንድ ነጪ ፖሊስ የጥቁሩን ጆርጆ ፍሎይድን የአየር ቧንቧ ተመሬት አጣብቆ መግደሉ ዓለምን አነጋግሯል፡፡ በኢትዮጵያ ግን መርጠው ባልተፈጠሩበት ዘራቸው ምክንያት ተነነፍሳቸው እንደ ድንጋይ ገደል የተወረወሩት፣ በቆንጨራ የተቀሉት፣ በስናፐር የረገፉት፣ በቁማቸው ዓይናቸውን የተመንቀሉት፤ ብልታቸውን የተቆረጡት፤ እንደ ውቃቤ በግ ተዘቅዝቀው የተሰውት፣ ተረሽነው ልጃቸው እንዲቀመጥባቸው የተደርጉት፣ እንደ እስጢፋኖስ በድንጋይ ተወግረው የሞቱት ወዘተርፈ በጪራሮ እንደ ረገፈ ትንኝ ተረስተዋል፡፡ እንኳን ሌላው ዓለም ሊያስታውሳቸው ለእነዚህ ወገኖች ስብእና እንደሚታገሉ ሲደሰኩሩ የኖሩት አስመሳዮችና ሕዝብን ነጣ እናወጣለን እያሉ በየአዳራሹ ሲፎክሩ የነበሩት ጉደኞች ተገዳይና ታስገዳዮቻቸው ጋብቻ ፈጥመው ጫጉላ ውስጥ ሲጨጎሉና ሲሽሞነሞኑ ይታያል፡፡ ምሁራን መሳይ ደስኳሪዎችም እጃቸውን በደም የነከሩ ባንዳዎች አገር ያስከብራሉ ብለው ስለ ዓባይ አህያውን ቢፈራ ዳውላውን ዓይነት ግሳንግስ እጃቸው ወሀ እስተሚቋጥር ሲጠለስሙ ይስተዋላል፡፡

የጆርጅ ፍሎይድ ነፍስ ለፍትህ ጮኻ ለጊዜውም ቢሆን ገዳይዎቹ ለችሎት ቀርበዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንን እንደ አበደ አውሬ እየዘነቸሩ የበሉት፣ እንደ ድንች በእሳት የጠበሱት፣ በቆንጨራ አንገት የቀሉት፣ ያመከኑት፣ ዓይን ያዋጡትና ገደል የጣሉት ወንጀለኞች ግን ዛሬም በስልጣንና በሐብት አብጠው ሲንደላቀቁ ይታያል፡፡ የሰሚ ያለህ! የኢትዮጵያውያን ሰማእታት ነፍስም እንደ ጆርጅ ፍሎይድ ነፍስ “የፍትህ ያለህ!” እያለ ሲጮህ ተኢትዮጵያ ገደሎች፣ ደኖች፣ ሸለቆዎች፣ መስኮች፣ ወንዞች፣ ሐይቆች፣ ከተማዎችና መንደሮች ይሰማል፡፡

የጆርጅ ፍሎይድ አገዳደል የዘረኝነት አገደዳል መሆኑን ብዙው የዓለም ሕዝብ ተረድቷል፡፡ የዘረኝነትን  እርኩስነት በአውሮጳ ሂትለር፣ በደቡብ አፍሪካ አፓርታይድ፣ በሩዋንዳ እነ ካቡጋ፣ በኢትዮጵያም እነ ገሰ ዜናዊ፣ ሽፈራው ሽጉጡና ጃዋር መሐመድ አሳይተዋል፡፡ ዘረኝነት የራስን ወገን ተወውደድ ወይም የራስን ወገን ጥቅም ተማስጠበቅና ለራስ ወገን ጠበቃ ተመቆም እጅግ ይለያል፡፡ እንዲያውም የራስን ወገን መውደድና ለራስ ወገን ጠበቃ መቆም ሐላፊነትን በሚገባ እንደመወጣት ይቆጠራል፡፡ ዘረኝነት በዘር አሳቦ የክፋት ዓይነቶችን ሁሉ በሌላው ዘር ላይ መፈጠምን ያጠቃልላል፡፡ ዘረኝነት በራስ ወገን ሥም የሌላውን ወገን ወይም ዘር እንደ ሂትለር ማሳደድ፣ መጨርገድንና ማጥፋትን ይጨምራል፡፡ ዘረኝነት ለራስ ወገን ጥቅም ሲሉ ሌላውን የመኖር መብቱን መንፈግና ተነነፍሱ ገደል እንዲወረወር ወይም ተወግሮና አንገቱን ተቀንጥሶ እንዲሰዋ የማድረን ክፋት ይጨምራል፡፡ ዘረኝነት የራስን ወገን እንደ ችግኝ እየተከሉ ሌላውን እንደ አረም እየነቀሉ የመጣልን ክፋት ያጠቃልላል፡፡

ይህ አድግና ክልል የሚባሉ እርስኩስ መንፈሶች በኢትዮጵያ ተሰፈኑ ጀምሮ የዘረኝነት ክፋት በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩትን ጨፍጭፏል፤ ሚሊዮኖችን ተሜዳ ጥሏል፡፡ የዘረኝነት ክፋት ሚሊዮኖችን የመኖር መብት ሊነፍግ አሁንም የክፋት ደመናውን አርግዞ ይገኛል፡፡ ክፋት እንደ ሳጥናኤልና ጃዋር ሚሊዮን ተከታይዎች ሲያተርፉ ደግነት ክርስቶስ ሲሰቀል እንደታየው ሶስት ተከታይም አጥቷል፡፡ ተፈቃቅሮ፣ ተዋልዶና ተዛምዶ መኖር የሚለው የኢትዮጵያ ደግነት በይህ አድግና በወነግ ክፋት ድል ተመቶ ሕዝብ መርጦ ባልተፈጠረበት ዘሩ ምክንያት መብቱ ሲገፈፍ፣ ሲፈናቀል፣ ሲሰደድ፣ ሲራብ፣ ሲጠማ፣ ሲወገር፣ ሲታሰር፣ ሲጠለፍ፣ ሲሰደድና ሲረሸን ይውላል፡፡

ክፋት የአውሬ ሳይሆን የሰው ባህሪ ነው፡፡ ተሰው ባህሪም ዘረኝነት የክፋቶች ሁሉ ቁንጮ ነው፡፡ ዘረኝነት ሰዎችን መርጠው ባልተፈጠሩበት ዘር ምክንያት ማሳደድ ወይም ማጥፋት ነው፡፡ ክፋት በህሊና ታልተሸፈነ የነፈረቀ አንጎል እየተንደቀደቀ የሚፈስ ደም የጎረሰ መግል ነው፡፡ ክፋተኞችን ለችሎት አቅርቦ ይኸንን ደም የጎረሰ መግል በፍትህ ፎጣ ማድረቅ በምድር ሰውነትና ደግነት በሰማይ ደግሞ ብሩክነትና ጽድቅ ነው፡፡ ይህ መግል ባለመድረቁ ያለፉት ሰማእታት ተሰማይ ፍትህን እየጮሁ ዛሬ እሚሰቃይቱም ተምድር የፍትህ ያለህ እያሉ ነው፡፡ በሆዳምነትና በአስመሳይነት ክፋት ተወጥረን መግሉን በፍትህ ፋሻ ለማድረቅ ስለለገምን ዛሬም የክፋቱ የመግል ጎርፍ ብዙዎችን ሰማእታት እየጠረገ ነው፡፡  ይኸንን ልግመታችንና አድርባይንታችንን ተመልክቶ የሰማእታት ነፍስ እያዘነብንና ደም እያለቀሰብን ነው፡፡

የሰሚ ያለህ! እንደ አሜሪካው ጆርጅ ነፍስ ሁሉ የኢትዮጵያውያን ሰማእታት ነፍስም ፍትህን እየጮኸ ነው!

 

ሰኔ ሁለት ሺ አስራ ሁለት ዓ.ም.

 

2 Comments

  1. Killers kill the helpless because they know they will get away with it. If only they knew their victims could defend themselves and they would get killed instead, they wouldn’t try it. Hence the secret to survival is to get organized to defend one’s own community. If that is not possible, it is better for the targeted community to leave the area and regroup in another area with a stronger similar community.The only security is might. It doesn’t matter how righteous you are. If you do not back up your cause with force, your case is a lost cause.

  2. አንተ ትቀልዳለህ። በዘር የሰከረ ዓለምና በክልል ፓለቲካ ጥቢራው የዞረ ምድር ለሰው ልጆች መበደልና ነጻነት ቆሞ አያውቅም። እንዲያውም እሳት ላይ ነዳጅ እያርከፈከፉ ሌላውን አቃጠልን ሲሉ እነርሱም አብረው ይጋያሉ እንጂ! ዛሬ መቀሌ ላይ መሽጎ ህገ መንግሥት አልተከበረም፤ የብሄር ብሄሮች መብት አልተጠበቀም፤ የትግራይ ህዝብ ተከቧል የሚሉን የሌባ ክምችቶች ቆመንለታል የሚሉትን የትግራይ ህዝብ አረንቋ ውስጥ የከተቱ መሰሪዎች ናቸው። ከእልፍ በደላቸው አንድ በዓይኔ ያየሁትን ላካፍልህ። ሰዎች እጅአቸው ወደ ኋላ የፊጢኝ ታስሮ ከፊትና ከህዋላ በጠበንጃ አንጋች እየተመሩ ወደ አንድ ሥፍራ ይወሰዳሉ። የለበሱት ብጣቂ ጭርቅ አይኔ ላይ አለ። አንዳንዶች ያለቅጥ ስለተደበደቡ መቆም አቅቷቸዋል። አይናቸው የበለዘ፤ ፊታቸው በደም የጨቀየም አሉበት። ሴቶችም ከፊት አሉ። ታዲያ አንድን የመገናኛ ሬዲዪ የያዘ ወያኔ ምን አድርገው ነው ስለው ዝም በል አለኝ። ቆይቶ እነርሱ ከዓይናችን ከተሰወሩ በህዋላ ተፈርዶባቸው ሊገደሉ ነው በማለት ጉድጓድ ውስጥ አስገብተው በጥይት እሩምታ እንደጨረሷቸው አይኔ አስከሬናቸውን አይቷል። ሌላ ልጨምር ወያኔ ለም ሥፍራ አለ በማለት እልፍ የትግራይን ገበሬዎች በመምራት ወደ ሱዳን ያመጣል። በዚያም የመለመኛ ጆኒኛውን ይዞ ወያኔ ህዝቤ ተራበ፤ ደርግ አስራበብኝ በማለት ላቀረበው ጥሪ ብዙ ምላሽ አገኘ። ለእርዳታ እጃቸውን ከዘረጉት መካከል ጥሬ ገንዘብ (ዶላር) የለገሱም ነበሩ። ምግብና መጠለያ እንዲገዛበት። ያን ገንዘብ ወያኔዎቹ ተከፋፈሉት። የትግራይ ህዝብ በየቀኑ እንደ ቅጠል ይረግፍ ነበር። በዚህ መካከል አንድ አዛውንት በጠና ታመው እንዲተኙ ይደረጋሉ። በመጣደፍ እኔም ሌሎችም ሆነን እንዲተጉ አደረግንና ምርመራ ተደርጎ መድሃኒት ይታዘዝላቸዋል። ለመዳን መድሃኒቱን መውሰድ አለብዎት። መድሃኒቱ የሚዋጥም መርፌም ነው ስላቸው ትኩር ብለው አዩኝና ልጄ እኔ ከአሁን በህዋላ መኖር አልፈልግም። መድሃኒትም ምንም ነገር አትስጡኝ መሞት ነው የምፈልገው አሉ። ተደናግጠን ለምን አለን? አይ ወደ እዚህ ሲያመጡን ከሃገራችን የት ነው የምትወስዱን በማለት የጠየቁትን ሽማግሌዎችና ቀሳውስት ረሽኗቸው በማለት ያለቀሱት እንባ እና ሞታቸው ለምን ጊዜም አይረሳኝም። ይህ የፈጠራ ወሬ አይደለም። አብረውኝ የነበሩ ዛሬም በህይወት አሉና! ወያኔዎች ድርቡሾች ናቸው።
    አሁን እንሆ በትግራይ ጥያቄ አቀረባችሁ፤ መንገድ ዘጋችሁ ተብለው በምሽትና በቀን እየተለቀሙ የገቡበት የማይታወቁ ስንቶች ናቸው። ለህዝብ የቆመ ህዝብ ወገኑን አያሸብርም። ወያኔ ግን በሽብር ተፈጥሮ በማሸበር የኖረ ድርጅት ነው። አሁን በወለጋ ህዝባችን እንዲገዳደል የሚያደርጉት እነርሱና ለእነርሱ ያደሩ በስም የኦሮሞ ህዝብ ተቆርቋሪ ነን የሚሉ እቡዮች ናቸው። ሰው ዘቅዝቆ የሚሰቅለው፤ በቆንጨራ የሚያርደው፤ ከቀየው የሚያፈናቅለው፤ ተምሬአለሁ በማለት ከእንስሳ ሃሳብ ያልወጣው ለእኔ ብቻ የሚለው የዘር ፓለቲካ ተፈጭቶ የተጋገረው በሻቢያና በወያኔ ነው። አሁን ያው የኦሮሞ ህዝብ ነጻነት ይገደናል የሚሉትም እህትና ወንድሙን ገድሎ የሚፎክረው ከዚያው ከወያኔና ከሻቢያ ማዕድ ስለተቋደሰ ነው። ሰው በሰውነቱ በማይመዘንባት ሃገር ስለ ፍትህ መናገር አይቻልም። እንደ ደመራ ችቦ ሁላችንም ቦግ ብለን አመድ ካልሆንን በስተቀር በሃበሻው ምድር ፍትህ ይኖራል ወይም ይመጣል ብሎ መጠበቅ ጅልነት ነው። የተከመረ የሚያቃጥል፤ የተዘራ የሚነቅል፤ እህትና ወንድሙን አታሎ ለመክበር የሚሻ፤ በዘሩና በቋንቋው ዙሪያ ከበሮና ክራር እየከረከረ እኔን ብቻ እዩኝ በሚል ህብረተሰብ “የሰው ልጆች ስብዕና” ይከበራል ብሎ ማሰብ ዝናብ እንደሌለው ደመና ባዶ እጅ መቅረት ነው። አሁን ጊዚአዊ መንግሥት ይቋቋም። አብይ ይብቃው፤ አብይ ኦሮሞ አይደለም፤ አብይ አማራ አቅፎ እያደረ ኦሮሞ መሆን አይችልም የሚሉን ሁሉ የስልጣን ጥመኞችና የፓለቲካ ጭቃዎች ናቸው። ግርግር ለሌባ ይመቻል እንዲሉ ነው ነገሩ እንጂ በጊዜው ምርጫ አርጎ መገላገልን የመሰለ ነገር የለም። ግን የፓለቲካ ፓርቲ ነን የሚሉት ሁሉ በዘራቸው ከተሰለፉና ሌሎችን በክልሌ አትምጡ ካሉ ምርጫው የቱ ላይ ነው? ዲሞክራሲ መቀለጃ የሆነበት አህጉር አፍሪቃ ብቻ ነው። በራሱ ወገን ላይ ጨክኖ ነጭና አረብን አለቃዬ ሁን የሚል። መከባበር ከራስ ይጀምራል። ጥቁሩ ህዝብ ራሱን ካላከበረ ሌላው የዓለም ክፍል ሊያከብረው አይችልም። ፍትህ ለሞቱት፤ አካላቸውና አእምሮአቸው ለተጎዳ ካስፈለገ ወያኔዎች ለፍርድ መቅረብ አለባቸው። ደርግ ከገደለው ይልቅ ወያኔ የገደለው የትግራይ ሰው ይበዛል። እናስብ? በትግራይ ህዝብ ደም የተጨማለቀ እንደ ወያኔ የለም። መረጃው ብዙ ነው። የሃገር አለቆች ከሆኑ በኋላም ሆነ በፊት ያደረሱት ግፍ ቤቱ ይቁጠረው። ስንቱ ነው ራሱን ገድሎ ተገኘ ተብሎ በሟች የሥራ ሥፍራ የወያኔ ሰዎች የተተኩት። ግን ህዝባችን ደንዝዟል። ሲነቃ ለዚያውም ከነቃ የከፋና የከረፋ የፓለቲካ አሻጥር ውስጥ ራሱን ያገኘዋል። ይህ ነው የሃበሻው ፓለቲካ። አታድርስ ነው። ፍትህ ያጣ የስንቶች ደም ይጮሃል። ግን ከላይም ይሁን ከሥር የሚሰማ የለም። ይብቃኝ።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.