/

ሲያልቅ አያምር! የአምባገነኖችና የጎሰኞች እጣ ፈንታ – አገሬ አዲስ

ግንቦት 29 ቀን 2012 ዓም(06-06-2020)

67ማንኛውም በተፈጥሮ ሂደት የሚያልፍ አካል መጀመሪያና መጨረሻ አለው።ከመኖር ወደ አለመኖር ይሻገራል።ይወለዳል ፣ያድጋል፣አርጅቶም ይሞታል።ከቶም ቢሆን እንደነበረ አይቆይም።በጊዜ ብዛት በመልክ፣በጸባይ፣በቁመና ይለዋወጣል።ከላይ የምናዬውም የአበባ ምስል ይህንኑ የተፈጥሮ ሕግ ተከትሎ ማለፍ የሚገባውን ደ,ረጃ አልፎ መጨረሻው ላይ ጠውልጎ የመክሰሙን  ሂደት የሚያሳይ ነው። ይህ የለውጥ ሂደት  ህያው በሆኑ አካላት ብቻ የሚከሰት ሳይሆን በሌላም  ቁሳዊ ባልሆኑት ለምሳሌም ባስተሳሰብና አመለካከት ላይም ይንጸባረቃል።እንደዚህ የአበባ ተክልም  የሰው ልጅ ወይም የሱ ጥርቅም የሆነው  ህብረተሰብም  ብዙ ውጣ ውረዶችን፣ ለውጦችን  የሚያስተናግድ ህያው አካል ነው። በዚህ የግለሰቦች ትልቅ ክምችት በሆነው ህብረተሰብ በሚባለው  ውስጥ  ተወልደው ፣አድገውና አርጅተው የሚያልፉ ትውልዶች እንዳሉ ሁሉ ትውልዱ የሚያስተናግዳቸው ተወልደው፣አድገው ፣አርጅተው የሚያልፉ ባህል፣ልማዶችና አስተሳሰቦችም ይኖራሉ።ከትውልድ እድገትና  ለውጥ ጋር የሚያያዙ በመሆናቸው እንደትውልዱ ተቀያያሪነት አላቸው። ምንም እንኳን ለውጥ ይኖራል ቢባልም መልካምና ጠቃሚ የሆኑትን እሴቶች በመጠበቅና በማዳበር ለተተኪው ትውልድ የማስረከብ ግዴታና ሃላፊነት እንዳለ  መዘንጋት አይኖርብንም።ለአዲስ መጡ መሰረት የሚሆነውም ተጠብቆ የኖረው በጎ   ወግና ልማድ ነው።

የዓለም ሕዝብ በተለያዩ የስርዓት ጎዳናዎችና የእድገት ደረጃዎች አልፏል።የዓለም አካል የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብም እንዲሁ የተለያዩ ስርዓቶችን፣መሪዎችን፣ባህል፣ ልማዶችንና አስተሳሰቦችን ሲያስተናግድ ኖሯል።አሁን ያለበት ደረጃም የዚያ ሂደት ውጤት ነው።ይህ ሂደት ይቀጥላል።ህብረተሰብ ወይም የሰው ልጅ እስካለ ድረስ አይቆምም።የማይጥመውን እያሶገደ፣አሮጌውን እየነቀለ አዲሱን እዬተከለ ከትውልድ ትውልድ ይሸጋገራል።

ሃሳባችንን ሰብሰብ አድርገን ወደ ህብረተሰብና የስርዓት ለውጦች ብናተኩር በአገራችን ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም አገሮች የተከሰቱትን ተመሳሳይ ሁኔታዎች በማውሳት ለውጥ አይቀሬ መሆኑን እንገነዘባለን።ታዲያ ለውጥን ለማቆም ከሚደረገው አጉል ሙከራ ይልቅ ለለውጥ ዝግጁ ሆኖ መገኘት የሚሻል ይሆናል።ከወደቁ ወዲያ መፈራገጥ ለመላላጥ የሚሉትን ለመቀበል ካልሆነ በስተቀር ፋይዳ የለውም።በለውጡ የሚጠቀሙና የሚጎዱ መኖራቸው አይካድም።የሚጠቀሙት ለውጥ ፈላጊዎቹ ሲሆኑ የሚጎዱት ደግሞ መለወጥ ያለበትን ስርዓት ለማቆዬት ሙጭጭ ብለው የሚቀሩት ናቸው።ይዋል ይደር እንጂ ለውጥ አይቀርም።ስለሆነም በለውጡ ግፊት ወይም ማዕበል ከሚመጣው ክፉኛ አወዳደቅ ለመዳን የሚያርፉበትን ቦታ ማመቻቸቱ ብልህነት ነው።ለውጥ ፈላጊዎቹም ማሰብ የሚኖርባቸው ለውጡም ወዳላስፈላጊ አቅጣጫ እንዳያመራ ወይም በጠላፊዎች እንዳይጠለፍ  መጠንቀቅ ተገቢ መሆኑን  ነው። በመጠለፍ መክነው የቀሩ ብዙ የለውጥ ሂደቶች ባገራችንም በተደጋጋሚ ተከስተዋል።የሩቁን ትተን የቅርቡን ማለትም የ1997ቱን የምርጫ ሂደትና ያንን ተከትሎ ከደረሰው ትምህርት መቅሰም ይቻላል።

በአፍሪካም ሆነ በሌሎቹ አገሮች የተደረጉት የሕዝብ አመጾችና በነበሩት መሪዎችና ሥርዓቶች ላይ የደረሰው አስከፊ እጣፈንታ ለሌሎቹ ማለትም ህሊና ላላቸው ትልቅ ተመክሮ የሚሰጥ ነው።አንዳንዶቹ ተመክሮውን አይተው ሲጠቀሙበት፣ብዙዎቹ በግትርነት አጥፍተው ለመጥፋት ሲባዝኑ ይታያሉ፤ግን መጨረሻቸው ያው የሚፈሩት የለውጥ እራት መሆን ነው።ነደደችን ያዬ በሳት አይቀልድም እንዲሉ ሊያቆሙ የማይችሉትን የለውጥ ጉዞ ለማቆም ከመከጀል ይልቅ የሌሎቹን  አምባገነኖች የመጨረሻ ፌርማታ ማሰቡ በተገባ ነበር።ከዘጠኝ ዓመት በፊት በቱኒዚያ ሕዝብ ሲብላላ የኖረው የለውጥ ፍላጎት  በአንድ ግለሰብ የተቃውሞ እርምጃ በተቀጣጠለው የለውጥ ሰደድ እንደቋያ እሳት ከባቢውን ሁሉ ለማዳረስ ችሉዋል።የቱኒዚያውን መሪ የቤን አሊን መንግሥት ከሥልጣን አሶግዶ እንዲሰደድ አድርጎታል።የሊቢያው  መሪ  ጋዳፊ ከሁኔታው መማር አቅቶት ግትርነቱ ለከፋ ስቃይና ውርደት ዳርጎታል።የነዚህን ውድቀት እያዬ ያልተማረው የግብጹ ኡስኒ ሙባረክም በሃይል በሥልጣኑ ላይ ለመቆዬት ያደረገው ሙከራ ሳይሳካለት፣የፈለገውን ሲያስፈርድበት በኖረው ፍርድ ቤት ችሎት ፊት እሱም በተራው ቀርቦ ከሕግ በታች መሆኑን አይቶበታል።ከሱ ና ከሌሎቹም ያልተማረው የሱዳኑ መሪ የነበረው ጄነራል አልባሽርም እንዲሁ በሕዝቡ ተቃውሞና ትግል የወንጀሉ ተባባሪ በሆነው የወታደር ቡድን ተገፍቶ ከሥልጣን ከወረደ በዃላ በእስርቤት ፍርዱን በመጠባበቅ ላይ ይገኛል።

ሕዝብ አይነሳ እንጂ ከተነሳ የሚያቆመው የለም፤በአንድ ሰው ወይም በጥቂት ግለሰቦች የተነሳ እምቢባይነትና ተቃውሞ አገር አቀፍ ንቅናቄ ይሆናል።ያ ንቅናቄ ደግሞ ለውጥ የሚያመጣ አብዮት ይሆናል።ያ አብዬት በትንሽ ጅረት ላይ የዝናብ ዶፍ ሲጨመርበት ወደ ጎርፍነት የሚለወጠውን ይመስላል። በመንገዱ ላይ የቆሙውን ጸረ ለውጥ ሃይል ሁሉ ይጠራርጋል። ከአርባ አምስት ዓመት በፊትና ከሰላሳ ዓመት በፊት ብሎም በቅርቡ ከሁለት ዓመት በፊት በአገራችን የታዩት የለውጥ ሂደቶች፣ከላይ በተጠቀሱት የሰሜን አፍሪካ አረብ አገሮች ያዬነውም ይህንኑ ሃቅ የሚመሰክሩ ናቸው።  ላለፉት ሰላሳ ዓመታት ኢሕአዴግ በሚል የወል ስም የሚጠራው በኢትዮጵያ ሰፍኖ የቆዬው የጎሰኞች ስርዓት በሕዝቡ ያላሰለሰ ትግልና መስዋእትነት  ምንም እንኳን በይዘት ባይሆንም ላለፉት ሁለት ዓመታት የስምና የመሸጋሸግ ለውጥ እንዲያደርግ አስገድዶታል፤ቀድሞ የመሪነቱን ቦታ ይዘው የነበሩት ጥቂቶቹ በሕዝቡ ትግል ተገደው በተወለዱበትና ለመገንጠል ትግል በጀመሩበት ቦታ ሲመሽጉ ሌሎቹ የነሱ አጋር የነበሩት በቦታቸው ተተክተዋል።የዚህ ተረኛነት የትግል ድምር ውጤቱ ሲሰላ የአንዱ ጎሳ የበላይነት በሌላው ጎሳ የበላይነት  ተቀዬረ እንጂ መሰረታዊ ለውጥ አልመጣም። ለውጡ ከእሳት ወደ እረመጥ የሆነበት ሕዝብ ያገሩን አንድነት የሚፈታተነውን፣እርስ በርሱ የሚያጫርሰውን፣አንዱን በሌላው የሚያፈናቀለውን በተረኝነት ስሜት  የሚፈጸመውን የወንጀል ተግባር በመቃወም ባለፉት ሁለት ዓመት ተኩል ብዙ መስዋእትነት ከፍሉዋል አሁንም እዬከፈለ ነው።የዚህም ትግል ውጤት የሚታይ ይሆናል።

በሥልጣን ላይ የተቀመጠው ቡድን ሰሞኑን የዛሬ ሰላሳ ዓመት ገደማ ኢሕአዴግ በሚል ጭንብል የተገንጣዬች ሃይል ሥልጣን ላይ የወጣበትን፣ የመከራና የግፍ አስተዳደር የዘረጋበትን፣ የጸረ አንድነት ዕቅዱን በተግባር የገለጸበትን፣የማፈራረስ ዓላማውን ሃ ብሎ የጀመረበትን  የግንቦት ሃያን ዕለት  በኩራት ሲያከብርና ሲያወድስ በአንጻሩ ሕዝቡ  ለኢትዮጵያ የመከራ ዘመን የጀመረበት  እንጂ የሚዘከርለት ብሩህ ተስፋ የፈነጠቀበት እለት አይደለም ሲል ዕለቱን ይረግማል።ባለፈው ሰላሳ ዓመት እንኳንስ ለሌላው ይቅርና  ቆመንለታል የሚሉትንም  የትግራይን ሕዝብ ከድህነት አሮንቃ አላወጡትም።በመሆኑም በአሁኑ ወቅት የትግራይ ሕዝብ እንደተቀሩት ወገኖቹ አደባባይ ወጥቶ  የተቃውሞ ድምጹን በማሰማት ላይ ነው።

ከአርባ አምስት ዓመት በላይ ጥቂቶች በስሙ ሲነግዱበት የነበረው የትግራይ ሕዝብ ኑሮው ከድጡ ወደማጡ ሆነበት እንጂ ያገኘው ጥቅም የለም።ተጠቃሚ የሆኑት ስርዓቱን የሚንከባከቡት አድርባዮች፣የስርዓቱ ቁንጮ የሆኑትና ቤተሰቦቻቸው ናቸው።የትግራይ ወጣት እንደሌላው ክፍላተሃገር ወጣት አጋሮቹ በሥራ አጥነት፣በችግር፣ተስፋቢስነትና በስደት የሚሰቃይ ነው።የትግራይ ወጣትም ሆነ የትግራይ ብዙሃን የኢትዮጵያን አንድነት የሚሻ፣በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን፣ በኢትዮጵያ አገሩ ከዳር እስከዳር እንደልቡ ተንቀሳቅሶ ሠርቶ በሰላም ለመኖር የሚፈልግ ነው።በአንድ ጠባብ የክልል እስር ቤት ተቀፍድዶ መኖርን አይመርጥም።በጨካኞቹ የሕወሃት ክንድ በቅርበት እየታሸ ፣በፍርሃትና በጭንቀት የኖረ እንጂ ሁሉ ነገር ተሟልቶለት ከሌላው በተሻለ መልኩ የኖረ አይደለም።ለዚያም ነው በተደጋጋሚ የሚያሰማው የተቃውሞ ድምጹ አሁን ላይ ፈርጠም ወዳለ ተቃውሞ ለመሸጋገር በማኮብኮብ ላይ የሚገኘው።

የቀናት ጉዳይ ነው ፤ትግሉ የሚፈለገውን  አገራዊ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ይሆናል።የተነቃነቀ ጥርስ እንዲሉ በመውረግረግ ላይ ያለው የጎሰኞች ስርዓት ለማክተሙ  ከተተከለበት ቦታ ጀምሮ እስከተስፋፋበት ሙሉ የኢትዮጵያ መሬት ትግሉ  እንደሚቀጣጠል የሌሎቹ ተመክሮ ብቻ ሳይሆን የአገራችንን ተደጋጋሚ የትግል ታሪክ ማዬቱ ይበቃል።ጠቢቡ ሰለሞን “ ለሁሉም ጊዜ አለው” እንዳለው ጊዜውን ጠብቆ የመጣው የለውጥ ንፋስ ወይም ጎርፍ  በቀላሉ የሚከስም አይሆንም። ሌላው ትግሉን በመቀላቀል የጎሳ ተኮር የጭቆና ስርዓቱን ዕድሜ ለማሳጠር መረባረብ ይኖርበታል።

አሁን በትግራይ ተቃዋሚ  ወጣቶች  ላይ የሚፈጸመው ግፍና ጭካኔ  ህወሃት ትግራይን ከኢትዮጵያ ለመገንጠል  ትግሉን ሲጀምር በተቃወሙት የትግራይ ተወላጆች ላይ የፈጸመውን ይመስላል። እስከ አሁን ድረስም በኢትዮጵያዊነታቸው የማይደራደሩ የትግራይ ተወላጆች ላይ የሚፈጽወው ወንጀል እየበረከተ እንጂ እዬቀነሰ አልመጣም።በጣም የሚገርመው በመጀመሪያው ላይ ተመሳሳይ ግፍና በደል ሲፈጽሙ የነበሩት የህወሃት መሥራች መሪዎች አሁን ተቃዋሚና ለትግራይ ሕዝብ ብሎም ለኢትዮጵያ ሕዝብ ተቆርቋሪ መስለው፣ቆባቸውን ለውጠው መጮሃቸው ነው።አንዳንዶቹም አፍንጫን ቢመቱት ዓይን ያለቅሳል በሚል መልኩ የይናችሁ ላፈር ከተባሉት የዓላማ አጋሮቻቸው ጋር በህወሃትነታቸው መልሰው  ሲቆሙ ታይተዋል። ዓላማቸው ያጡትን የሥልጣን ቦታ በቀሪዋ ዕድሜያቸው ቢደርሰን የሚል ጉጉት አድሮባቸው እንጂ ለሕዝቡ አስበው አይደለም።የጀርባ ታሪካቸው እንደሚመሰክረው ከአርባ አምስት ዓመት በፊት  ለመገንጠል ሲነሱ የተቃወማቸውን በጉድጓድ ውስጥ ቀብረው በሳትና በጥይት እንደጨረሱት ነው።የትግራይም ሕዝብ ጠንቅቆ ያውቀዋል።ለኢትዮጵያ አንድነት ቢያስቡማ ኖሮ አሁንም ብሔር ብሔረሰብ የሚል ያረጀ ከፋፋይ ፈሊጥ ይዘው በጎሳና በከባቢ ስም ባልተደራጁ ነበር።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለአንድነቱና ለሰላሙ፣ለእኩልነቱና ለመብቱ መከበር የሚያደርገውን ትግል አጠናክሮ መቀጠል ይኖርበታል። ስም እዬለዋወጡ የሚመጡትን በጎሳ ፖለቲካ የተበከሉትን በቃችሁ ሊላቸው ይገባል። በኢሕአዴግ በረት ውስጥ የሚፈለፈል ድርጅት የኢሕአዴግነትን ባህሪ የተላበሰ እንጂ የተለዬ አይሆንም።ተግቶ ያደገበትም ያንኑ በጸረ አንድነት፣በጸረ ዴሞክራሲ፣በጸረ ኢትዮጵያ  የተሞላውን የጎሰኝነት  ጡጦ ነው።የሚመራበትም ህገመንግሥት በዚያው ቁመና የተቀረጸ፣በሕዝብ ላይ የተጫነ አስገዳጅ መመሪያ ነው።የጎሳ ፖለቲካ ለአንዴና ለዘለቄታው መወገዝና መወገድ አለበት።ጎሰኛ ጎሰኛ ነው።አንዱ ጎሰኛ ከሌላው ጎሰኛ የሚሻል አይደለም።

በአንድነት ጎራ የተሰለፉት የፖለቲካ ድርጅቶች ያገራችንን ሁኔታ ከራሳቸው የሥልጣን ፉክክር በላይ አድርገው አለማዬታቸው ሌላው ችግር ነው።እያንዳንዱ ከሌላው ጋር ተባብሮ ከመሥራት ይልቅ እራሱን ከሌለው ሃያልና የበለጠ አድርጎ በማሰብ የአብረን እንሥራን ጥሪ ሰምቶ እንዳልሰማ ይሆናል።ከእኔ በላይላሳር በሚል ትቢት ተወጥሮ ብቻውን ደፋ ቀና ሲል ይታያል።ይህ የሥልጣን አባዜ የሚያመጣው እብደት በጊዜው መታረም አለበት።ለአንድነት ቆሜያለሁ የሚል የጋራ ግንባር ለመፍጠር የሚቀርበውን ጥሪ ተቀብሎ በተግባር መግለጽ ይኖርበታል። አገር ሳይኖር ሥልጣን አይኖርም።

ዛሬ ትግራይ መሬት ላይ የሚካሄደው ” የፈንቅል” ትግል አገራዊ መሠረት እንዲኖረውና ለአስተማማኝ ለውጥ እንዲበቃ ከጎሳ ሳጥን ውስጥ መውጣት አለበት።ትግራይ ሳይሆን ኢትዮጵያ  የሚለውን ሰንደቅና መርሆ መያዝና መከተል አለበት።የየካቲት 66ቱም ሕዝባዊ እንቅስቃሴደርግ በተባለ በገዳዪች ወታደራዊ ቡድን ከመጠለፉ በፊት የጀመረው በዚህ መልኩ ነበር።የአረቦች ጸደይ ሕዝባዊ አመጽም እንዲሁ ከትንሽ ወደ ትልቅ፣ከአንድ ከተማ ወደ ሌላው ከተማ የተሸጋገረና አገር አቀፍ የሆነ ነበር።ምንም እንኳን ውጤቱ ባያመረቃም፣ሌሎች አምባገነኖችን ለሥልጣን ቢያበቃም የነበሩትን አሮጌ  አምባገነኖችን አሶግዱዋል።አሁን በትግራይና በሌሎቹ ቦታዎች የተለኮሰው የለውጥ ችቦ በሁሉም የኢትዮጵያ መሬት ተስፋፍቶና በጋራ አመራር እዬተመራ  በጎሳ ከፋፍለው ሲያባሉት፣ሲያጋድሉት፣ሲያፈናቅሉት፣ሲዘርፉት በኖሩትና አሁንም የዳቦ ስም አውጥተው ባሉት ኢሕአዴጋውያንና የመንፈስ አጋሮቹ ላይ የተባበረ ክንዱን ሊያነሳባቸው ይገባል።በሚነዙት ፕሮፓጋንዳ መጭበርበር የለበትም።ከጎሰኝነት የጸዳ፣ለአገር አንድነትና ለሕዝብ ልዑላዊነት፣ለሰብአዊ መብትና ፍትህ፣ለዴሞክራሲ ስርዓት መስፈን ተባብሮ መታገል ይኖርበታል።በጥቃቅን ጥገናዊ ለውጦች መታለልና መጠለፍ ብሎም የጠላቴ ጠላት ወዳጄ ነው በማለት ለተመሳሳይ የጎሰኞች ስርዓት፣ዳግም በስሙ ለሚነግዱ በር መክፈት አይኖርበትም።

የትግራይም ሆነ የኦሮሞ፣የአማራም ሆነ የደቡብ፣የሶማሌም ሆነ የአፋር፣የጋምቤላም ሆነ የሲዳማ…ወዘተ ጎሳ ተወላጅ ሁሉ አብሮ የኖረ፣ክፉ ደጉን የተጋራ፣የተዋለደ የአንድ አገር፣የኢትዮጵያ  ሕዝብ ነው።አንዱ በሌላው ላይ ክፉ ነገር አያስብም።ሁሉንም አንድ አይነት ፍላጎት ያስተሳስራቸዋል።ያም እንደሰውና እንደዜጋ ተከብሮ የመኖር ፍላጎት ነው።ክፉ ነገር እንዲያስብና ወንጀል እንዲፈጽም የሚገፋፉትና የሚያስገድዱት በደካማ ጎኑ፣በድህነቱ እዬገቡ  በስሙ ሥልጣኑን ለመያዝ ወይም ይዘው ለመቆዬት  ወይም ኢትዮጵያን ለማፈራረስ በሚሹ የውጭ ሃይሎች የተገዙ ባንዳዎች ናቸው።

አብዛኛው የኢትዮጵያ ወጣት እንደቀረው የዓለም አቀፍ ወጣት በዘመናዊ አስተሳሰብ መመራት የሚሻ፣ዓለም አቀፋዊነት እይታ እንጂ በአስራ አምስተኛው ክፍለዘመን  በጎሳና በመንደር እይታ  የጫጨ ጭንቅላት ያለው ትውልድ  አይደለም።በትናንትናዎቹ ጎሰኞች ትርክት የሚኖር የጠባብ አይምሮ ባለቤት አይደለም።አልፎ አልፎም ከመካከሉ ያሉት ስህተት ቢፈጽሙም  የጊዜ ጉዳይ ነው ወደ ቀልባቸው ሲመለሱ ባሳሳቱዋቸው ላይ እርምጃ ከመውሰድ አይቆጠቡም።የአምባገነኖች የመጨረሻው እጣፈንታቸው የሚቋጨው ይከተለናል ብለው አሳስተው በመሩትና በተማመኑበት ተካታያቸው ውሳኔ ነው።ሞሶሎኒን ዘቅዝቆ የሰቀለው ይከተለው የነበረው የራሱ ሕዝብ ነው፤የሌሎቹም እንዲሁ።

ከስምንት ዓመት በፊት ከዚያም ወዲህ በተደጋጋሚ በኢሳት ቴሌቪዥን ባስተላለፍኩት “እምቢበል” በሚለው  የግጥም መልእክት እንዲህ ብዬ ነበር

እምቢበል ሰሜን እምቢበል ትግራይ፣
ለዚህ ከፋፋይ ለዚህ አጋዳይ፣
አትሁን መሣሪያ አትሁን አገልጋይ።
የእኔ ነው ብለህ አትሁን ወላዋይ፣
ብቻህን ቀርተህ መከራ እንዳታይ፣
ለዜግነትህ ላገርህ ክብር በኢትዮጵያዊነት ታገል አንድላይ።

ከችግር ዓለም ላልወጣህበት ፣
በስም፣በትግልህ፣በልጆችህ ደም፣ጥቂት ጨካኞች ተጠቀሙበት፣
ሥልጣኑን ይዘው እዬዘረፉ በለጸጉበት፣
በውጭ አገር ባንክ አከማቹበት፣ንብረት ያዙበት
ልጆቻቸውን አስተማሩበት፣
ለመተካካት አዘጋጁበት፣
ያንተ ግን ሆኗል ኑሮህ አቀበት፣
ገቢህ ቂልቁለት፣

ልጅህ ተጋልጧል ለሥራ አጥነት፣ለሞት ለስደት
ክልል ከሚሉት የጎሳ እስርቤት፣
ለመውጣት ታገል በኢትዮጵያዊነት።

ሙሉ መልእክቱን ከዚህ በታች ባለው የዩቱብ እርዕስና መስመር ሊገኝ ይችላል።

Hager Addis EMBE BEL

https://youtu.be/7WQcSmVdTQ8 (ለመክፈት ctrl+ click)

ከሦስት ዓመት በፊትም ወያኔና ለግብረአበሮቹ ከስልሳ ሰንጋ በላይ አርዶ፤ውስኪ እዬረጨ ድል ያለ አስረሽ ምችው ድግስ በሚሊኒዬም አዳራሽ ውስጥ ሲያዘጋጅ፣ከውጭ በሕዝቡ ኑሮ ላይ የሚታዬው ቁጣና ተቃውሞ የሚያስከትለውን ውድቀት በመገመትና ድግሱ የመጨረሻ ስንብት የቁም ተስካር/ተዝካር/ የማብላት ያህል እንደሆነ በማሰብ ” የቁም ተስ(ዝ)ካር” በሚል እርዕስ ጽሑፍ አዘጋጅቼ ለንባብ አብቅቼ ነበር።የቁም ተስ(ዝ)ካር በአገራችን ባህል  አንድ ሰው ዕድሜው ገፍቶ መሞቻው መቃረቡን ሲያስብ ወዳጅ ዘመዱን ሰብስቦ የኑዛዜ ቃል የሚሰጥበትና የሚሰናበትበት በድግስና በፍትሃት አልፎ አልፎም በለቅሶ የታጀበ ክንዋኔ የሚታይበት ነው።

በሁለቱም በኩል ጥሪ ያደረኩበትና  የጠረጠርኩት ለውጥ ጊዜውን ጠብቆ  ከሞላጎደል ተከስቶ ለማዬት በቅተናል።የሚቀጥለውንም እንዲሁ ዕድሜ ከሰጠን ለማዬት እንችላለን።የዚህንም ጽሁፍ እርዕስ ሆነውንም “ሲያልቅ አያምርንም” እንዲሁ!

በውጭ አገር የምንኖረው ኢትዮጵያውያን በአገር ውስጥ ወገናችን ለፍትሕና ለአንድነት የሚያደርገውን ትግል እዬደገፍንና የምንችለውንም እያበረከትን ጎን ለጎንም የውጭ ሃያላትን በተለይም የግብጽንና  ግብረአበሮችዋን መሰሪ ሴራ ተቋቁሞ በዓባይ ግድብ ግንባታ ላይ የሚያደርገውን እርብርቦሽ ማጠናከር ይኖርብናል።ግድቡ ዘመን ተሻጋሪ የሕዝብ ንብረት እንጂ  ሥልጣን ላይ የተቀመጠ ቡድን ንብረት አይደለም።

ዓባይንና ግድቡን ዘላቂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረት ለማድረግ የተደቀኑትን ጎሳ ተኮር ችግሮችና ስጋቶች ማሶገድ የግድ ይላል። ለዚያም በዋናነት ጎሰኛ ስርዓትና ክልላዊ አወቃቀሮችን ማሶገድ ነው።በአገር ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ቅጥረኛ የሽብር ቡድኖችን ማንበርከኩም ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል።አባይን መገንባትና ሥርዓቱን መናድ፣ እነዚህን መንታ ትግሎች ማያያዝ  የሁለገብ ትግል መርሆን መከተል ማለት ነው።ያለውን  ስርዓት መቃወም ለአባይ ግድብ ግንባታ ማድረግ የሚገባንን አስተዋጽኦ  ሊያግደው አይገባም፤በአባይ ግድብ ላይ መረባረቡም  ያለውን የጎሰኞች  ስርዓት በደልና ግፍ እንደ መርሳትና  መደገፍ ተደርጎ መታዬት አይኖርበትም።

አሁን ዓለማችን   ጆርጅ ፍሎይድ የተባለ አንድ አፍሪካ-አሜሪካዊ በዘረኛ ፖሊሶች መገደሉን ተከትሎ በተቃውሞ ሰልፍ ከዳር እስከዳር ስትናጥ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ግን ለብዙ ዓመታት በጎሰኞች  የብዙ ሕዝብ ደም የፈሰሰባትን አገራችንን ለማዳን  ሌላው ቀርቶ ድምጻችንን  ለማሰማት እንኳን አለመድፈራችን አልፎ ተርፎም ለጎሰኞቹ እያጨበጨብን  ድጋፍ መስጠታችን  በታሪክ የሚያስጠይቀን ከመሆኑም በላይ ጤንነታችንን ወይም እራሳችንን እንድንጠይቀው ያስገድደናል።አገራችን በጣሊያን ፋሽስቶች ስትወረር ጥቁር አሜሪካውያን ህይወታቸውን ለመስጠት በወዶ ዘማችነት የተሰለፉባት አገር ዛሬ በገዛ ልጆቿ ተክዳ በዚህ ደረጃ ላይ ስትገኝ ህሊና ላለው የሚያሳፍር ነው።ከዚህ በታች በሚቀጥለው ገጽ  ላይ የሰፈረው ምስል ጥቁር አሜሪካኖቹ ያደረጉትን “ እኔ ልሙትላት” የምዝገባ  እሽቅድምድምን የሚያሳይ የታሪክ  ምስክር  ነው።

ያገኘሁት ከፌስቡክ ልውውጥ  ገጽ ላይ በመሆኑ የጥቂት ሰዎች ስምና ምስል አብሮት ስለሚወጣ  የሚመለከታቸውን በቅድሚያ ይቅርታ እጠይቃለሁ።የተለዋወጡት ይህንን የመሰለ ቁም ነገር አዘል መልእክት ስለሆነም ቅር እንደማይላቸው ተስፋ አለኝ።ሊኮሩም ይገባል እላለሁ።ለጽሁፌም አካል በመሆናቸው ሳላመሰግናቸው አላልፍም።

ኢትዮጵያ አገራችን በአንድነትና በነጻነት ለዘላለም ትኑር!

አገሬ አዲስ

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.