ለጣናና ለአባይ በእውቀትና በጥናት ላይ ተመስርቶ የተፃፈ ድንቅ መፍትሄ ነው

ለጣናና ለአባይ በእውቀትና በጥናት ላይ ተመስርቶ የተፃፈ ድንቅ መፍትሄ ነው፡፡ ሰሞኑን የሚካሄደው የሶሻል ሚዲያ ዘመቻ የጣና ችግር እንቦጭ እንጅ ጣና በለስ፣ ደለልና ጨረጨራ ግድብ ናቸው ብሎ የሚያስብ ሰው ባለማየቴ ነው ጓደኛየ ወንድምስሻ በፌስቡክ ገፁ የፖሰተውን ፁሑፍ ያጋራዋችሁ፡፡
Wendemsesha A. Angelo
June 22, 2019Tana
እምቦጭ ይለምልም!
ጣና ሐይቅ ይውደም!

(በጣና ሀይቅ ጉዳይ ዝርዝር መረጃና ሂስ)

በ1811 ዓ.ም. የተወለደው የራስ ኃይሉ ልጅ  ካሳ ቴዎድሮስ ገና በ19 ዓመቱ የገነነበትን ጦርነት ያደረገውና በድል ያሸበረቀው ዓባይን መቆጣጠር የሞትና ሽረት ጉዳይ ከሆነባት ከግብጽ ጋር ተዋግቶ ነው፡፡ #ግብጾች ደግሞ ራስ ምታታቸው ምግባቸው የሆነው የአባይ ወንዝ ምንም ችግር እንዳያጋጥመው ለማድረግ ከራሳቸው በቀር ማንንም ላለማመን የሚደረግ የአካባቢ የበላይነት ጉዳይ ነው፡፡ እንኳን አሁን በቀድሞ ነገሥታት ዘንድ ሳይቀር አባይን ገድባ በፍጹም የበላይነት መደራደር እንደምትችል የኢትዮጵያን አቅም ዐይተው አንዴ ደንግጠዋልና በአባይ ላይ ቀልድ አያውቁም፤ ስለዚህም የአባይን ወንዝ እስከምንጩ ድረስ ለመቆጣጠር በቀጥታም በተዘዋዋሪም ይመላለሳሉ፡፡ የጉ-ራና ጉ-ንደት ጦርነት ባይሳኩም ኢትዮጵያ ላይ ጥቃት አድርሶ ሊያዳክማት የሚችልን ማንኛውንም አጋጣሚ ትጠቀማለች፤ ታግዛለች፡፡ ኢትዮጵያን ከዚህ መዳከም የሚታደጋት አንድነትና ሥልጣኔ መሆኑን በተግባር የሰበከው አጼ ቴዎድሮስ ተተኪ ልጅ ያጣ ይመስል ዛሬ ላይ አባይና ጣናን ለስጋት የዳረጉትን ችግሮች በንስር ዐይን ለይቶ መፍትሔ የሚሰጥ አካል የታጣው ንጉሦቻችን ግብጻውያን ሆነው ይሆን ያሰኛል! 3ኛው ስጋቷ ጉ-ባ ላይ ያላት ዕቅድ ምን እንደሆነ ግልጽ ባይሆንም ከጥቂት ክርክር በቀር ብዙም አላስቸገረችም፡፡ ‹‹ጉ›› የተባለች ፊደል ገዴ አይደለም ብላ ተስፋ ቆርጣ ግን አይመስለኝም፡፡

የጉዳዩን አሳሳቢነት ለመረዳት ያህል ከቅርቦቹ አጋጣሚዎች ብጠቅስ የደርግ መንግሥት አመራሮች/ባለሙያዎች በጣና ሐይቅ ላይ በአባይ ወንዝ መውጫ የሚሠራውን የጫራጫራ ግድብ በ30 ሚሊየን ብር ሊሠራ ጨረታውን አሸንፎ የነበረውን የግብጽ ተቋራጭ በፖለቲካዊ ውሳኔ ትተው ለኛው ልጅ በርታ ኮንስትራክሽን መስጠታቸው ግብጾችን ከአባይ የማራቅ የጥንቃቄው አካል ነው፡፡ ይህን የፈጸመው ያው አንዱ የመብራት ኃይል ተቋም ግን መንግሥት ሲቀየር #የህዳሴ_ግድቡ ውሀ የሚተኛበት ቦታ ላይ የወርቅ ማዕድን እንዲያወጣ ለግብጻዊው የማዕድን አምራች ፈቅዶለታል፡፡ የወርቅ ማዕድኑ ስንት ሜትር ድረስ ቢያወጣው እንደሚበቃው ፈጣሪ ይወቅ እንጂ የቦታውን የውሀ ማቆር/አለማስረግ ችሎታ ሊፈታተነው እንደሚችል መገመት ከባድ አይደለም፡፡ የዚህም ግድብ ተስፋ ግን የዓባይ ወንዝና ገባሮቹ በመሆናቸው መጀመሪያ ምንጩን እንርዳው እስኪ፤ ጣናን፡፡

የጣና ገባሮች

ሐይቅ የሚፈጠረው ከዙሪያው የሚገብሩት ውሀዎች ሊተኙበት የሚችል ጎድጓዳ ስፍራ ሲሆንና ቦታውም ከምድሩ ተፈጥሮ አንጻር ውሀ ማቆር ሲችል፣ እንዲሁም ከሚሸኘው ውሀ ይልቅ የሚቀበለው ሲበዛለት ነው፤ አንጻራዊ የገቢ ብልጫ ማለት ነው፡፡ ጣና ሐይቅ ከጎንደርና ከጎጃም ተራሮች /አርማጭሆ፣ ጉና እና ጮቄ/ የሚነሡ ከ60 በላይ መጋቢ ወንዞች እንዳሉት ሰነዶች የሚጠቁሙ ሲሆን በዋናነት በ4 ተፋሰሶች ተከፍለው ውሀቸውን ለጣና ገቢ ያደርጋሉ፡፡ እነዚህም ግሼ አባይ ተፋሰስ 1,656 ፣ ጉመራ ተፋሰስ 1,284፣ ርብ ተፋሰስ 1,303 እና መገጭ ተፋሰስ 514 በድምሩ 4,757 ካሬ ኪሎ ሜትር ሲሆኑ ውሀቸው 3,600 ካሬ ኪሎ ሜትር ስፋት ያለው ጥንት ደምቢያ ተብሎ የሚታወቅ ቦታ ላይ ጣና ሐይቅ ተብሎ ይተኛል፡፡ በነዚህ ተፋሰሶች ላይ ያለው የገጸ ምድርና የከርሰ ምድር ውሀ እንደጊዜውና እንደአፈሩ ጠባይ የውሀው መጠን ከፍ ዝቅ እያለ ጣና ሐይቅ ውስጥ ይከትማሉ፡፡ መውጫቸው ደግሞ #አንድ_አባይ_ወንዝ_ብቻ ነው፡፡

ጎንደር ከተማን ለመጠጥ ውሀ ምንጭነት አገልግሎ የሚያልፈው አንገረብ ወንዝን ጨምሮ በአካባቢ ጥበቃ ሥራ መዳከም ምክንያት በበጋ ደርቀው የሚታዩ የጎንደር ዙሪያ ወንዞች ብዙ ናቸው፡፡ እንደውም ከከተማው 25 ኪሜ የማይርቀው መገጭ ወንዝ ላይ እየተሠራ ያለው የ10 ቢሊየን ብር ግድብ ለከተማው ዘርፈ ብዙ ጥቅም እንዲሰጥ የታሰበ ቢሆንም ከፕሮጀክቱ መጓተት በላይ አስተማማኝነቱ ጥያቄ ላይ ወድቆ አሁን የመጠጥ ውሀ መስመር የተገነባው 45 ኪሎሜትር ርቆ ከሚገኘው ጎርጎራ-ጣና ነው፡፡ ወደጣና የሚገቡት አንገረብና መገጭ ወንዞች ላይ መተማመን ያቃተው መንግሥት ከሌሎች ወንዞች የተቀበለውን የጣናን ውሀ ወደኋላ መልሰው እነ ንጉሥ ፋሲለደስ ለውሀው ብለው ለዋና ከተማነት ወደ መረጡት ጎንደር ይጭኑታል፡፡ ይህንን አማራጭ የጎንደር ሕዝብን ጥያቄ ለመመለስ ብቻ የፈለገ ለጣና ሕልውና ግን ደንታቢስ የመሆን ምልክት አድርጌ እወስደዋለሁ፡፡ /ዓለማያን ሐይቅ አድርቆ ከሐይቁ ቦታ ላይ ጥልቅ ጉድጓድ ቆፍሮ ለሐረር ውሀ የወሰዱት ሰዎች ካገኙት ልምድ ነው መሰል¡

ወንዞቹ ጣና ሲገቡ ውሀ ብቻ ሳይሆን ደለልም፣ ግንድና ቅጠልም ይዘው ይገባሉ፡፡ ወንዞቹ ሲፈሱ ጭቃ መስለው ሲሄዱ ስናይ ቆይተን ሐይቅ ውስጥ ሲገቡ ግን ፍጥነታቸውም ቀንሶ፣ ከሐይቁ ጥልቀት አንጻርም ዝቅ ብለው ስለሚፈሱ የጣና ሐይቅ ክረምት ከበጋ ወደ ሰማያዊ ያደላ ቀለም ይዞ ዐይንን ይማርካል፡፡ ዝዝሩን ስንመለከት ግን በጥናቶች መሠረት በየዓመቱ ከ3-4 ሚሊየን ቶን ደለል/አፈር ወደ ጣና ይገባል፡፡ ይህ መጠን በሙሉ ባይወጣና ከጣና ስፋት አንጻር ሐይቁ ውስጥ ወጥ ስርጭት አለው ብለን ብንወስድ የጣና ሐይቅ በየዓመቱ ቢያንስ 5.2ሳሜ ያህል ጥልቀቱ ይቀንሳል ማለት ነው፡፡ አብዛኛው ደለልም የሚገባው በክረምት ወራት በመሆኑ ቀጥታ በጎርፉ ግፊት ከጣና መውጣት ከቻለ ምንም አያሰጋም፡፡ እውነታው ግን በ2010 በወጣ የጥናት ሰነዶች የጣና ሐይቅ ከ1.4 ሜትር በላይ ጥልቀቱ እንደቀነሰና በደለሉ ምክንያት ለመድረቅ መጋለጡ ከፍተኛ ደረጃ መሆኑ ነው፡፡ በእርግጥ ገና በ2005ቱ የጅማ ዩኒቨርሲቲ የጥናት ጉባኤ ላይ የአዲስ አበባው ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ክንፈ የመድረቅ ምልክት እንዳሳየ አረጋግጠው ማሳሰቢያ ሲሰጡ እኔ በቦታው ነበርኩ፡፡ ይህ ሁሉ እንግዲህ ጣና ሐይቅ ላይ ግድብ ከተሠራ 15ና 20 ዓመት ላይ ማለት ነው፡፡

ጣና ላይ ግድብ!

ለሰው ልጅ ኑሮ እጅግ አስፈላጊ የሆኑ ልማቶች የመኖራቸውን ያህል ከተፈጥሮና አካባቢ ጥበቃ በላይ የሚሆን ግን ምንም ነገር አይጠቅመውም፡፡ ስለዚህም የልማት ዕቅዶችና የኢንቨስትመንት ንድፈ ሀሳቦች የአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማቸውን አብረው እንዲያቀርቡ ይገደዳሉ፡፡ በዚህ አግባብ ሊተገበር በደርግ ዘመነ መንግሥት ጫፍ ደርሶ ኢሕአዴግ የተረከበው የጢስ አባይ-II እና ጣና በለስ የተቀናጀ ፕሮጀክት ጣና ሐይቅ ላይ ጫራጫራ ግድብን ሊገነባ ዕቅድ ይዞ ቀርቧል፡፡ በዚህ መሠረትም በብዙ ዓመታት አንዴ የሚከሰተው የጣና ሐይቅ ውሀ መተኛ ቦታ መስፋት ከአካባቢ ተጽዕኖ ግምገማው ሪፖርት አንዱ በመሆኑ ይህ ተጽዕኖ በጣና ዙሪያ ባሉ ባህርዳር ከተማና የገጠር ቀበሌ ነዋሪዎች ሊያደርጉት ስለሚገባ ጥንቃቄ ምክር ተሰጥቷል፡፡ በዚህም መሠረት የጣና ዳሩ የአማራ ልማት ማኅበር ዋና መሥሪያ ቤት ሕንጻ ላይ እንደተደረገው ውሀ ሊያሰምጠው የሚችለውን ያህል ቁመት ከፍ አድርገው መገንባትና ከመንገድ የሚያገናኝ ድልድይ ሠርተዋል፡፡

የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ ሥራ በጀመረበት 1990 ዓም. እስከ ኅዳር ወር ድረስ የዘለቀ የውሀ ከፍታ መጨመር ተከስቶ ግድቡ ታሳቢ ካደረገው የባህርዳር ከተማ መንገድ በላይ መጥቶ ነበረ፡፡ በአንጻሩ ውሀው ያስነሳቸዋል ተብለው የነበሩ ገበሬዎች በወቅቱ ከ35ሚሊየን ብር በላይ ቢመደብላቸውም ዕቅዱ እንዳልተፈጸመ በፕሮጀክቱ ላይ በከፍተኛ ኃላፊነት የነበረ ወዳጄ ነግሮኛል፡፡ ከ1990ዓ.ም. በኋላ ግን የውሀው አሞላል ስጋት መሆኑ ቀርቷል፡፡ ወዳጄ እንደነገረኝ ከሆነ የገበሬዎቹ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የግድቡ ዲዛይን ላይም ከፍተኛ ለውጥ ተደርጎ የጣና በለስ ውሀ መውሰጃ ቦታም ከግድቡ አፍ ባህርዳር መሆኑ ቀርቶ ወደ ምዕራብ የሐይቁ ጥግ ተወስዷል፡፡ እንግዲህ የዲዛይኑ ለውጥ ያመጣው ተጽዕኖ ዳግም ተገምግሞ ከሆነ መንግሥት ሊያስብበት የሚገባ ጉዳይ ሆኖ ዋናው የደለሉ ክምችትና የጥልቀት መቀነስ ምክንያት ግን ይህ ግድብ መሆኑን ማስተባበል የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ቀድሞ ያልነበረ የደለል ችግር በግድቡ መገንባት ማግሥት በፍጥነት እየታየ ነውና፡

አጥፍቶ ጠፊው አሸባሪው ጣና በለስ

የሐይቁ ውሀ አንጻራዊ ሁኔታው የተረጋጋ በመሆኑ ደለሉ የፍሰቱን አቅጣጫ ተከትሎ የሚሄድና የውሀው ፍጥነት ሊበጠብጠውና ሊሸከመው /turbidity/ ከሚችለው በላይ ሲሆን ሐይቁ ውስጥ የመቅረት ዕድሉ ሰፊ ነው፡፡ ጫራጫራ ግድብ የተሠራው ደግሞ የወንዞቹ ተፈጥሯዊ የፍሰት መንገድ መጨረሻ የአባይ ወንዝ መውጫ ላይ በመሆኑ ወሀው ደለሉን ትቶ እንዳይወጣ ማድረግ የሚቻለው የውሀው በር በዚሁ ቦታ ሲሆንና የበሩ ቦታም ከሥረኛው ወለል ሳይዘጋ ክፍት ሆኖ የደለሉን ገቢ መጠን ያህል ሳይቋረጥ ከተጓጓዘ ነው፡፡ አሁን እንደምናየው ግን እንኳን ሐይቁ ወንዙ ጭምር ግፊቱ ቀንሶ ደለሉን መሸከም አቅቶት /low turbid/ ይዞት የወጣውን ደለል የባህርዳር ዙሪያ የአባይ ወንዝ ይዞታ ላይ ትቶት እየሄደ፣ የመሬት ችጋራምም ጠጋ ብሎ እያረሰው ነው፡፡ የክልሉና የከተማው ከፍተኛ አመራርም ሲወጣ ሲገባ እያየው ወንዙ በእርሻ ሲተካ ምንም አይሸነቁጠውም፡፡

በዚህ ሂሳብ ስንሄድ የውሀው ፍሰት ተፈጥሯዊ መስመር ባልሆነ ቦታ የተጠለፈው የጣና በለስ ውሀ ንጹሑን ውሀ ብቻ እየጨለፈ እንደሚወስድ ለመረዳት ቀላል ነው፡፡ በተፈጥሮው ዑደት ምጣኔ መሠረት ከጣና የሚወጣውን ውሀ ያህል ደለሉንም የሚሸከም ውሀ ካልተገኘ ሌላ ይህን የሚሠራ ሰው ሠራሽ አሠራር መፈጠር አለበት፡፡ ይህ ደለሉን በማሽኖች ጠርጎ ማውጣትን ሊጨምር ይችላል፡፡ ለደለሉ ምንም መፍትሔ ያልሰጡ ፕሮጀክቶችን ጣና ላይ መደርደር ግን ደለሉን ለጣና ትቶለት ሲሄድ ‹‹ብትደርቅስ ምን አገባኝ!›› የሚል ጨካኝ ስግብግብነት እንደሆነ ይሰማኛል፡፡
ጣና በለስ ይህን ውሀ በቋሚነት ሲወስድ ለሁለት ዓላማ ነው፡፡ በጣም ጥቂቱን /‹10 በመቶ/ ከተገነባ ጀምሮ ለእርሻና ምርት ለማስወገድ በመቶዎች ሚሊየን ብር ለማውጣት እንጂ ጠብታ ጥቅም ላላስገኘው ለጣና በለስ ስኳር ፋብሪካ ሸንኮራ አገዳ ለማምረት ሲሆን አብዛኛው ግን 460 ሜጋ ዋት ለሚያመነጨው የጣና በለስ ኤልክትሪክ ኃይል ተርባይን መምቻ ነው፡፡ ይህን ለማድረግ 11ኪሎሜትር በመሬት ውስጥ ቁልቁል ይዞ ሲፈነጠር ከባህር ወለል በላይ ከ1800ሜትር የጣና አፍ ወርዶ በረሃው ላይ 711 ሜትር ላይ ይገለጣል፡፡ የዚህን ዋሻም ደህንነት ለማስጠበቅ ሲባል ሐይቁ ደለል አልባ መሆኑ ተገቢ ሊሆን ይችላል፡፡ ጥያቄው የዚህ ፕሮጀክት ህልውና መሠረት የሆነው የጣና ሐይቅ ዋሻው ትቶት በሚሄደው ደለል ምክንያት ህልውናው አደጋ ላይ ሲወድቅ ‹‹አጥፍቶ ጠፊ››ው ራሱ የጣና በለስ ፕሮጀክት ሊሆን ነው፡፡ በምጣኔም ካየነው ተፈጥሮ ስትልክ የነበረውን ደለልና ውሀ አመጣጥና የነበረ ሲሆን ሰው ሰራሹ ፕሮጀክት ግን የሚወጡትን ውሀ ደለሉንም ይዞ እንዲወጣ ካልተደረገ ደለሉ ሐይቁ ውስጥ መቅረቱ ግልጽና የሚጠበቅ ነው፡፡

እንግዲህ ይህ ሁሉ ተደምሮ ጣና ሐይቅ ቀጣይ ተስፋው በየዓመቱ እየሞተ 500 ሜጋዋት የማይሞላ ኃይል ያመነጫል፡፡ በግድቡ ምክንያት ጢስ አባይ ላይ ተጨማሪ ኃይል ማመንጫ ተብሎ የተለፋው 50 ሜጋ ዋት ያመነጫል ተብሎ ቢታቀድም አሁን እያመረተ ያለው 30ሜዋ ብቻ ነው፡፡ የጢስ አባይ ፏፏቴን ለመጨመር ሲባልም እሁድና በቱሪስቶች ብዛት መጠን እየታየ የውሀው ፍሰት እየተለቀቀ 21 ሜ.ዋ. ብቻ ያመነጫል፡፡ ይህ ቁጥር አጼ ሚኒሊክ ካሠሩትና 11ሜጋዋት ከሚያመነጨው የአቃቂው አባ ሳሙኤል ግድብ ትንሽ ነው የሚበልጠው፡፡ ጠቅላላ የጫራጫራ ግድብን የኃይል ምርት ብንገምት አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ካለው የውሀ ኃይል ማመንጫ ግንባታ ወጪ አንጻር ከ600 ሚሊየን ዶላር በታች ነው፡፡ /ቁጥሮችን ለማነጻጸር ያህል የህዳሴ ግድብ የጣና ሐይቅን 3 እጥፍ መጠን ያለው ሐይቅ ሲፈጥር 6,200ሜጋዋት ለማመንጨት 4.4ቢሊየን ዶላር፣ ግቤ IV- 2,200ሜ.ዋ. ለማመንጨት የሸለቆ ውስጥ ሐይቅ እየፈጠረ 2.5ቢሊየን ዶላር ወጪ ይደረግበታል፡፡/ አንድ ሐይቅ በብር ሲፈጠር፣ ሌላው በብር ይገደላል፡፡

እምቦጭ የስለት ልጅ

“የጣናና ሌሎች ሐይቆች ዋና ችግር ደለል ሆኖ እያለ የመንግሥት አመራሮች ምክንያቱን እምቦጭ እንደሆነ ለምን ይነግሩናል?” ይህ ለኔ መልስ ያላገኘ ጥያቄ ነው፡፡ ደለል መሆኑን በግልጽ ቢነገር በተለይ አካበባቢ ጥበቃ ላይ ሕዝቡንም ሆነ የሚመለከታቸውን አካላት ማስተባበር ያስችላል፤ የኢንቨስትመንት ዕቅዶች አካባቢ ላይ ያላቸውን ተጽዕኖም ሁሉም በንቃት እንዲከታተልና ተሸፋፍኖ እንዳይፈቀድ ያግዛል፡፡
እምቦጭ ሥሩ ረጅም፣ ውሀ አጠቃቀሙ የስግብግብ፣ እርባታው /እጥፍ ለመሆን/ 15 ቀናት የሚበቃው፣ መፍትሔው ደግሞ ግልጽ አማራጮች ያሉት ነው፡፡ አረሙ በሌሎች ዓለማት በዝርዝር የሚታወቅ በመሆኑ በኢትዮጵያ በታወቀበት 2005 ወይም በሚቀጥለው ዓመት መወገድ ወይም ጣና ላይ በነበረበት ስፋት 5ሺህ ሄክታር መግታት ይችል ነበረ፡፡ ዛሬም ቢሆን ከ50ሺህ ሄክታር በላይ የሚሸፍነው እምቦጭ እስከቀጣይ የአበባው ወቅት ድረስ የተሟላ ዕቅድ ቢዘጋጅ ለማጥፋት ያን ያህል አያስቸግርም፡፡ አሳሳቢው ጉዳይ ኃላፊነት ወስዶ እየሠራ ያለው የክልሉ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን የሚከተለው አቅጣጫ እንደሆነ በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡

#ኢቲቪ_መድረክ የካቲት/2011 በጣና ጉዳይ ዘርዘር ያለ የአውጫጪኝ ውይይት አድርጎ ነበረ፡፡ በመድረኩም የባለሥልጣኑን ተወካይና በጉዳዩ ላይ ጥናት አድርገው መፍትሔ እንዲያቀርቡ የቴክኒክ ቡድን ሆነው እንዲሠሩ ተመድበው የነበሩ ዶክተር አያሌው ወንዴ፣ ዶክተር ማማሩ አያሌው እና ዶክተር በላቸው ጌትነትን አቅርቦ ነበረ፡፡ በ2006/7 ጥናት ተደርጎ የቀረበለትን መፍትሔ ሳይጠቀምበት እንደቀረና አሁንም 2010 ላይ የተዋቀረው ቡድን የደከመበትን የመፍትሔ ምክረሀሳብ ተመሳሳይ ብክነት ከመፍጠር በቀር ባለሥልጣን መ/ቤቱ እንዳልፈለገው ምሁራኑ በምሬት ገልጸዋል፡፡ ምሁራኑ እንዳሉት የጥናት ውጤታቸው ዋናው ችግር ደለሉ መሆኑን ዕውቅና ይሰጥና ከእምቦጩ የበለጠ ደለሉ ትኩረት ያግኝ የሚል ነው፡፡ ምሁራንን ደጋግሞ እያደከሙ ምክራቸውን ለመጠቀም አለመፈለግ በራሱ ከመንግሥት የማይጠበቅ ቸልተኝነት ነው፡፡ ያም ሆኖ ‹‹ዶሮ ብታልም ጥሬዋን›› ዓይነት ጥናቱ ‹‹ችግሩ እምቦጭ ነው›› እንዲል ፈልገው ከነበረ ምሁራኑ በግላቸው ጥርስ ውስጥ ከመግባት በቀር ለሐይቁ ያተረፉት ነገር የለም ማለት ነው፡፡ በጎን ግን በእምቦጭ ስም ሕዝብ ይቀሰቀሳል፣ እርዳታ ይሰበሰባል፣ ከመንግሥትና ከግል ተቋማት ከፍተኛ በጀት ይወጣል፣ ወዘተ፡፡ ይህን በደስታ የሚመለከተው እምቦጭም ስንቱን በጀት በልቶ በ5 ዓመት ውስጥ በ10 እጥፍ ተስፋፍቷል፡፡
የጣናን ችግር ላይ መውደቅ በደስታ የሚመለከቱ ሰዎች እምቦጭን መርጠው የሚወዱት ልጃቸው ይመስል በቁልምጫ እየጠሩት እየተረባበረቡ፣ እሱም እየፋፋ ነው፡፡ የሚቆላመጥ ልጅ ችግሩ የሱ መፋፋት ብቻ አይደለም፤ የበለጠ ትኩረት የሚፈልጉትን ሌሎች ልጆች ሁሉ ያስረሳል፡፡ የባለሥልጣኖቹ የእምቦጭ ፍቅር ደለሉንም፣ ጣናንም ከዓይናቸው አርቆት የተገኘውን በጀትና ድጋፍ ሁሉ ከእምቦጭ ጋር ያገናኙታል፡፡ እንደኔ ግን ግብጾችም ቢሆኑ ጣና ላይ ይህን የሚያደርጉ አይመስለኝም፡፡

ምን ይሻለናል

ምሁራኑ ስለደለሉ ይሠራ ያሉትን ምክረሀሳብ መጠቀም ዘላቂው መፍትሔ ስለሆነ እኔ የምጨምረው ነገር የለም፡፡ የኔ ትኩረት ጊዜያዊ መፍትሔው ላይ ነው፡፡ ሐይቁ በየዓመቱ በተለይ ክረምቱ ላይ የሚጨመርበት ደለል አስቸኳይ ውሳኔ ይፈልጋል፡፡ ከዚህ አንጻር በአጭር ጊዜ ቢታሰቡ የምላቸውን ተግባራት ብቻ ልጠቁም፡፡

#የመጀመሪያው ወደሐይቁ የሚገባውን ደለል ገድቦ የያዘውን ጫራጫራ ይመለከታል፡፡ ግድቡ በሩን ከሥር የሚከፍት ቢሆንም የወንዙን ስፋት የሚመጥን የበሮች ብዛት ሊሆን ስለማይችልና ውሀውም በግድቡ ምንያት ተረጋግቶ ሲመጣ በሮቹን ጭምር ለመክፈት እያስቸገረ መምጣቱ አይቀርም፡፡ ከግድቡ በታች ባሉት የአባይ ወንዝ ይዞታዎች ላይም ደለል እየተኛ መሆኑ ግድቡ ጎጂ ውጤት ለማስከተሉ ጠቋሚ ነው፡፡ በዚህና ተያያዥ ምክንያቶች መከፈት የሚችሉትን በሮች ሁሉ ለቀጣዩ ክረምቶች ያለማቋረጥ ክፍት ቢሆኑ ቢያንስ ዘላቂው መፍትሔዎች እስኪጀመሩ ሊከማች የሚችለውን ተጨማሪ ደለል ይቀንሳል፤ ይቆማል ማለት ግን አይደለም፤ እንዲቆም ግድቡን በዕቅድ ማፍረስ ድረስ ሊያስፈልግ ይችላል፡፡
#ሁለተኛውና ቁርጠኛ አመራር የሚፈልገው ጉዳይ የጣና በለስ ጉዳይ ነው፡፡ መንግሥት ከሐይቁና ከጣና በለስ ፕሮጀክት መምረጥ ያለበት ይመስለኛል፡፡ ገና ለማይጠረቃና ከዝርፊያ ላልዳነ የኢትዮጵያ የኃይል ልማት 460ሜጋዋት አገኛለሁ ብሎ ጣና ላይ የሚያመጣውን ጉዳት ላለማየት ዓይኑን መጨፈን የለበትም፡፡ ሐይቁ ምንም ጥቅም የለውም ብሎ የሚያስብ ቢሆን እንኳ ተፈጥሮን ማዛባት በራሱ መንግሥትን ተጠያቂ ያደርገዋል፡፡ ይህም ሐይቁ የጎጃምና የጎንደር ውበታቸው፣ የባህርዳር ከተማና የጣና ገዳማት ህልውናቸው፣ የገቢ ወንዞች ተስፋቸው ነው፡፡ /ከዚህ በላይ የአማራ ክልል፣ የኢትዮጵያ፣ የዓለም ሀብት መሆኑ አልጠፋኝም፤ ሁሉም እንዲሞት ስለተዉት ሊጠቀሱ ስለማይገባ ነው፡፡/ ስለዚህ ዛሬ ከተሠራው የጣና በለስ ፕሮጀክት ይበልጣል፡፡ የሚበልጠውን ሐይቁን መርጦ ጣና በለስ ላይ መጨከን ሁለቴ ማሰብ የማይፈልግ ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡

ከዘላቂዎቹ መፍትሔዎች አንዱ የሆነውና በፕሮጀክቱ ምክረሀሳብ ተካቶ የነበረው የደለል ማውጫ ማሽኖች ጉዳይ ዳግም መታየት አለበት፡፡ ማሽኖቹ ጎርጎራ መቀመጣቸው በራሱ ተገቢ መሆን አለመሆኑ ዳግም ተገምግሞ ቢያንስ ግን የሚያስፈልጋቸው የአስተዳደር ሥራ ተሟልቶ በነዚህ ማሽኖች ቢጀመር ፈጣን መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ ላለፉት 20 ዓመታት የተከማቸው ደለል ግን ጊዜያዊ መፍትሔ ይፈልጋል፡፡ ጥልቀቱ 1.4 ሜትር መቀነሱም ሌላው ከባድ የቤት ሥራ ነው፡፡ በገቢና ወጪ ወንዞች የፍሰት መስመር ተከትሎ የተኛውን ደለል ለቀጣይ ጥቂት ዓመታት በማሽን መበጥበጥ ቢቻል ውሀው ራሱ ይዞት የመሄድ ዕድል የኖረዋል፡፡ ከዚያ አልፎ አዲስ ገቢ ደለልን ከግድቡ ቀጣይ ዕቅድ ጋር ማውጣት ስለሚቻልበት መፍትሔ ማሰብ ከመንግሥት የሚጠበቅ ነው፡፡

#ለማጠቃለል ያህል ችግሩ ደለሉ መሆኑን አምኖ መቀበል የመንግሥት የመጀመሪያ ከባድ ሸክም ሲሆን ለሚመለከታቸው የፌደራልና የክልል መሥሪያ ቤቶች አመራሮች የውጪ ሽርሽርና ኪስ አደላቢ ከሆኑት ከቁልምጫ ልጆቻቸው እነ እምቦጭ ይልቅ ለተፈጥሮ ሀብት ስስ ልብ እንዲኖራቸው መምከር ጊዜ የማይሰጠው ሐቅ ነው፡፡ ከላይ የገለጽኩት አመክንዮ በሌሎች ሐይቆችም ላይ ሊታይ የሚችል ሲሆን የግድቡና ተያያዥ ፕሮጀክቶች ባይኖሩም በተለይ ዝዋይና አቢያታ ሐይቆች ቀዳሚ የደለል ተጠቂ እንደሆኑና እየደረቁ መሆኑ በዓይን የሚታይ ነው፤ መፍትሔውንም አብሮ ማየት የመንግሥት ፈንታ ነው፡፡ የለውጥ አመራር ነን ያሉትም አዲሱ የክልልና የፌደራል መነግሥት የአካባቢ ጥበቃና የኢነርጂ ሚኒስቴር ሰዎችም የምሁራኑ ድምጽ የታፈነበት ዘመን በቅቶ ይሉኝታውና ዝምታውን የሚሰብሩበት ጊዜ ቅርብ እንዲሆን እመኛለሁ፡፡

1 Comment

  1. The author of this post has deep knowledge of the problem and possible solutions. The environmental impacts of hydro-power projects are vast and Tana lake is the victim of this impact. Climate change could also be an additional cause (needs detail investigation)

    I advise the Ethiopian and the regional politicians to organize such talented people and come to a concrete solution.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.