/

የልውጥ ሕያዋንን (GMO) ነገር በኢትዮጵያ ለምን ድብቅ ማረግ ተፈለገ – ሰርፀ ደስታ

GMOሰሞኑን የልውጥ ዝርያን ወሬ አስመልክቶ መነሻው ምን እንደሆነ ለእኔ ግልጽ  አልነበረም፡፡ ብዙዎች ትክክለኛው መረጃ ኖሯቸው ሳይሆን ከወሬ ወሬ የሰሙትን ነበርና የሚያደርሱን፡፡ ጉዳዩን ከየት እንደጀመረ ለማወቅ አስቤ ስፈልግ አገኘሁት፡፡ ብዙዎች ለመንግስት ቀረብ ያለ ግለሰቦች ምንም የተፈጠረ አዲስ ነገር የለም በሚል ይሞግታሉ፡፡ ችግሩ ግን በእርግጥም እነሱ እንደሚሉት ነገሩ አዲስ ሳይሆን በድብቅ ተይዞ ከዓመትና ሁለት ዓመት በኋላ በስማ በለው መነገሩ ላይ ነው፡፡ ጥሩ የሆነ አካሄድ እንዳልሆነ ግን ቢታሰብበት መልካም ነው፡፡ እንግዲህ በአገሪቱ የሚሰሩ ተመራማሪዎች ሳይቀር ምን እየሆነ እንደሆነ አያውቁም፡፡ ባለፈው ዶ/ር ተወልደ ገብረእግዚአብሔር አሁን እየሆነ ያለውን ነገር ምንም እንደማያውቁ አስረድተው ስጋታቸውን ጽፈው ነበር፡፡ ሌሎች የዶ/ር ተወልደን ስጋት ሳይንሳዊ ያልሆነ ሲሉ ሲተቹም ሰምቻለሁ፡፡ እኔም የዶ/ር ተወልደን አስተያየት አንብቤዋለሁ፡፡ ዶ/ር ተወልደ ያነሷቸው ጉዳዮች በእርግጥም እንደ አገር ሁላችንም ልናስብበት የሚገባ እንጂ ሳይንሳዊ ያልሆነ አደለም፡፡ ዶ/ር ተወልደን ለመተቸት ሳይንሳዊ ያልሆነ ሲል የተቸውንም ጽሁፍ አይቻለሁ፡፡ ምን አልባት ጸሐፊው ዶ/ር ተወልደ ያነሱትን ጭብጥ በትክክል አልተረዳው ይሆናል ወይም ከእነ ጭርሱ አላነበበውም ይሆናል፡፡ የሆነ ሆኖ ጸሀፊው ዶ/ር ተወልደ ላይ ከማነጣጠር ጽሁፉን እንደ ራሱ ሀሳብ ቢያቀርበው ጥሩ ነበር፡፡ ዶ/ሩን ለመተቸት ከመሞከሩ በቀር ቀሪው ሀሳቡ ትክክል ነው፡፡ እንግዲህ ብዙዎች ምን እየሆነ እንደሆነ እየተረዱ አደለም፡፡ የደንና አካባቢ ጥበቃ ኮሚሽን ውስጥ የሚሰሩ ባለሙያዎችንም ለማናገር ሞክሬ ነበር፡፡ ከእነጭርሱ ጉዳዩ ከእነሱ ጋር ለመገናኘቱ ራሱ የሚረዱት አይመስልም፡፡ ሆኖም ፍቃድ ሰጭው የእነሱ ኮሚሽን ነው፡፡ ቢያንስ በምርምርምሩ ላይ ያለው ማህበረሰብ እየሆነ ስላለው ነገር ማወቅ  ይገባው ነበር፡፡ የመገናኛ ብዙሀንም ዜናው ሊኖራቸው ይገባ ነበር፡፡ ችግሩ ከሀ እስከ ፐ ሁሉም ፖለቲካ ላይ ተጥዶ እንዲህ ያሉ ወሳኝ ጉዳዮችን ማን ያስታውስ? በዚህ አጋጣሚ በተመሳሳይ ስለ አባይ ማወቅ የሚገባንን ያህል ያወቅን አይመስለኝምና ሁሉም ቢያስብበት እላለሁ፡፡ ከኢትዮጵያ በኩል እየተሰራ ካለው ይልቅ ከግብጽ በኩል ያለውን አካሄድ ብዙዎቻችን ለመረዳት ችለናል፡፡ ግድቡ እንግዲህ በዚህ ክረምት እንደሚሞላ ቀጠሮ ተይዟል፡፡ እስከዚያች ቀን ድረስ ይሞላል ከማለት በቀር ምን ዝግጅት እንዳለ አላውቅም፡፡ ሆኖም ቀኑ ሲደርስ ምክነያት ፈጥሮ ማስተጓጎልም ሊኖር እንደሚችል ይሰማኛል፡፡ከዛ አንድ ሰሞን ነው ይረሳል፡፡  አሁንማ ሕዝብ የበሽታ አደጋ ተጋርጦበታል፡፡ ማዘናጋት የተለመደው አካሄድ ነውና የግድቡ ጉዳይ አልተመቸኝም፡፡ አካሄዱም ጥሩ አይመስለኝም፡፡ ብዙ ነገሮች በእንዲህ አይነት እየሆኑ ነውና፡፡ ሌላ ቀርቶ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ታፍነው የት እንደደረሱ እስካሁንም ግልጽ የሆነ ነገር የለምና፡፡ ችግር ነው፡፡

ወደ ተነሳሁበት የለውጥ ሕያዋን ነገር ልመልሳችሁ፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው በ2018 በፈረንጆች የደንና አካባቢ ኮሚሽን የልውጥ ጥጥና በቆሎ እንዲገቡ ይፈቅዳል፡፡ ይሄን ተከትሎ የጥጥ ልውጥ ዘሩም የበቆሎውም እንዲሁ ሙከራ ተጀምሮ ከዓመት በላይ ሆኖታል፡፡ የአንድ ዓመት ሙከራ አልቆ ሁለተኛው ዓመት ተጀምሯል፡፡ የልውጥ ዘሩ ሙከራ የተባለው በዚህ በ2019 በ130 ሄክታር መሬተ ላይ ነው የተተከለው፡፡ 130ሄክታረ መሬት ሙከራ ሊሆን አይችልም፡፡ ምን ዓልባት ሙከራው ቀደም ብሎ ተጀምሮ አሁን ወደ ምርት ተገብቶ ካልሆነ፡፡ ሙከራው የሚሰራው በወረር ምርምር ማዕከል ነው ተብሏል፡፡የወረር ምርምር ማዕከሉ ራሱ 130 ሄክታር መሬት እንዳለው እጠራጠራለሁ፡፡ የሆነ ሆኖ አሁን የተባለው ይሄ ነው፡፡ በእርግጥ ነው የጥጥ ልውጥ ዘር ቀደም ብሎም ተሞክሯል የሚል መረጃ ነበረኝ፡፡ ሙከራውን ስላላየሁ በእርግጠኝነት መናገር ባልችልም ከአስር ዓመት በላይ ይሆነዋል ወሬው ከተወራ፡፡

ሌላው ገብቶ በመሞከር ላይ ያለው ልውጥ ዘር የበቆሎ ነው፡፡ የበቆሎው ልውጥ ዘር ተባይንና ድርቅን መቋቋም በሚችልበት ሁኔታ እንደተቀየረ ነው የተነገረለት፡፡ ድርቅን ለመቋቋም የተለወጠ ዝርያ ለመኖር እርግጠኛ አደለሁም፡፡ እንደሚገባኝ ድርቅን ለመቋቋም በዘረመል ምህንድስና ዝርያ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ድርቅ መቋቋም ባህሪ በብዙ ወሳኝ ዘረመሎች (ጂኖች) ስለሚወሰን፡፡ ተባይና በሽታ በአብዛኛው እንደዛ አደለም፡፡ የበቆሎው ልውጥ ዘር የተባለው ግን ለድርቅና ለተውሳክ ነው፡፡ የሆነ ተባይን የሚቋቋም ልውጥ ሕያው ከጸረ-ዓረም (ጅምላ ጨራሽ) ከሚቋቋመው አንጻር ለጤና ጠንቅ ሊሆን ስለሚችል ከፍተኛ ጥንቃቄ ያስፈልገዋል፡፡ ምክነያቱም ተባዮችና ሰዎች ሁለቱም ከእንስሳ ስለሚመደቡ ተባዮችን የሚገድል ከሆነ ለሰውም አደጋ ሊሆን ስለሚችል ነው፡፡ ይሄ ግን ሁሌ አደለም በብዙ የሰውነት ክፍል ስለምንለያይ፡፡ ሆኖም ተባይ ገዳይ የሆነን ነገር የሚያመነጭ ወሳኝ ዘረመል (ጅን) ለሰውም መርዛማ ሊሆን ይችላል፡፡

ከላይ የተጠቀሰው የጥጥ ለውጥ ዘርም ተባይን ለመቋቋም ነው፡፡ እሳቤው ጥጥ ለምግብነት አይውልም ነው፡፡ ሆኖም ይሄ እኔ በማውቀው የኢትዮጵያ ሁኔታ ትክክል አደለም፡፡ የጥጥ ፍሬ ለምግብ ዘይት ለማምረት ይውላልና፡፡ አሁን ትተውት ከሆነ አላውቅም፡፡ ግን ቢያንስ እኔ እንማውቀው የአዲስ ሞጆ የዘይት ፋብሪካ ከዋነኛ ግብዓቱ አንዱ ጥጥ እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ይሄም ከወዲሁ ሳይታሰብ ከሆነ ችግር እንዳሆን፡፡ ሌላው ጸረ-ተባይ ልውጥ ዘር ለጠቃሚ ነብሳት ማለትም እንደንብ ላሉ ነብሳት አደጋ ሊሆን እንደሚችል ታስቦበት እንደሆነ አላውቅም፡፡ የጥጥ አበባ በንቦች ምን ያህል እንደሚጎበኝ አላውቅም፡፡ ሆኖም በንቦች የሚጎበኝ ከሆነ ሌላ ችግር እንደሆነ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ ንብ ብቻም ሳይሆን ሌሎች ብዙ ዓይነት ነብሳት አሉ የበርሀ ትንኞች የመሳሰሉት፡፡

እኔ የልውጥ ዝርያዎች መጥቀምና አለመጠቀም ላይ ትልቅ ችግር ብዬ የማስበው ስለ ልውጥ ዘረመሉ በቂ እውቀትና ዝግጅት ሳይኖር የሚደረገው አካሄድ ነው፡፡ ልውጥ ዝርያዎች ከውጭ አምጥቶ ማላመድ የሚባለው ነገር ከምንም በላይ ለእኔ አሳሳቢ ነው፡፡ ለውጥ ዝርያዎችን መጠቀም ከአስፈለገ በራሳችን የተዘጋጁ መሆን አለባቸው የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ ይሄ አሰራር ስለ ልውጥ ሕያዋን በቂ እውቀትና ክህሎት እንዲኖረን ከማድረጉም በላይ የራሳችንን የዘረመል ሀብት ወደፊት ለዓለም ገበያ ለማቅረብም እድል ይኖረዋል፡፡ የልውጥ ሕያዋንን አደጋዎችንም በቀላሉ ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡ ከምንም በላይ ከጥበቡ ጋር መተዋወቅ ወሳኝ ነው፡፡ አሁን እንደማየው የለውጥ ጥጡ ከውጭ ገብቶ እየተሞከረ ያለው በወረር ምርምር ማዕከል ነው፡፡  ማዕከል ልውጥ ዝርያው ለመሆኑ እንኳን ማረጋገጫ ያለው አይመስለኝም፡፡ በመስክ በሚያየው በተባይ ያለመጠቃት ባሕሪ ካለው ከማየት በቀር፡፡  በአገራችን የእንሰትን አጠውልቅ ለመከላከል ሙከራ እየተደረገ እንደሆነ ሰምቻለሁ፡፡ይሄን ከሚበረታቱ አካሄዶች አንዱ ነው፡፡ በራሳችን መሆን አለበትና፡፡ ሆኖም ብዙዎች እንሰት አገር በቀል ስለሆነ መነካት የለበትም ይላሉ፡፡ እርግጥ ነው የሚቻል ከሆነ አንሰትን በተፈጥሮ ባለው ባሕሪው አጠውልግን የሚቋቋም ዝርያ ማውጣት ከምንም በላይ ቅድሚያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ሆኖም የራስን ለውጥ ዝርያ ለመስራት ከመሞከር አንጻር ልውጥ ዝርያ መጠቀም ከአለብን ቢያንስ በአብዛኛው በራሳችን የሚሰራ መሆን አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡ ከሌሎች ማምጣት ቢያስፈልግን እንኳን እውቀቱና ክህሎቱን በደንብ ካዳበርን ከውጭ የገባን ለውጥ ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ለመቆጣጠር፣ የበለጠ ለመጠቀም ያስችላልና ነው፡፡

በነገራችን ላይ የ2015 ተሻሽሎ የወጣውን አዋጅ ለማንበብ ሞክሬ ነበር፡፡ መሠረታዊ የሆነ የቋንቋ ግድፈት አይበታለሁ፡፡ እንግዲህ እኔ የሕግ ሰው አደለሁም፡፡ ሆኖም እንዲህ ያለ ግልጽ ስህተት እንኳን ሕግ ቦታ ሌላውም ቦታ አስቸጋሪ ነው፡፡ አንዳንድ ቃላቶች በአማርኛ ወካይ ቃል እያላቸው እንዳለ በኢንግሊዘኛው ተጽፈዋል፡፡ ይሄ አይነቱ ነገር በአገሪቱ የገባ ትልቅ ችግር እንደሆነ አውቃለሁ ግን አዋጅ ላይ በዚህ መልኩ ባይሆን ጥሩ ነው፡፡ አብዛኞቹ የመንግስት መስሪያቤቶች ስያሜን ላስተዋለ አስቂኝ ይሆንበታል፡፡ ሁሉ ነገሩ የኢትዮጵያን ሕዝብ ሳይሆን ተማርን የሚሉት ሰዎች ነው፡፡ እሱም ቢሆን በጥራዝ ነጠቅ እንጂ በትክክል ኢንግሊዘኛውን ቢያውቁት መልካም፡፡ የቋንቋ ጉራማይሌው እንደፈለገው ግን በግልጽ ያየሁትን አንድ የትርጉም ስህተት እዚህ ልጥቀስ በኢንግሊዘኛው traditional breeding የሚለውን ባሕላዊ ማዳቀል በሚል ተተርጉሞ አይቻለሁ፡፡ ባሕላዊ ማዳቀል የሚባል ነገር እኔ አላውቅም፡፡ መባል የነበረበት መደበኛው/የተለመደው ማዳቀል ነበር፡፡ ባህልዊ መቼም ሳይነሳዊ ሊሆን አይችልም፡፡ የተለመደው ማዳቀል ሥራ በሳይንሳዊ መልክ የሚካሄድ ነው፡፡ ቀሪውን ግድፈት አንብቡት፡፡ ቢያንስ አዋጅ ጥርት ያለ መሆን ነበረበት፡፡

 

ቅዱስ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ከክፉ ይሰውር! ለዓለሙ ሁሉ ምህረቱን ያውርድ! አሜን!

ሰርፀ ደስታ

 

2 Comments

  1. The agricultural cooperation Brazil is extending to Ethiopia is a game changer , Ethiopia can learn many essential methods from Brazil on how to become self sufficient in food. Brazil got similar temperature and even similar soil to Ethiopia making Ethiopia lucky to have the Brazilian agricultural experts extending their know how to Ethiopia’s agricultural irrigation projects which is expected to make Ethiopia a country of surplus food production same as Brazil is.

    The agricultural production in Brazil amounts to $67 billion dollars USD per year . Brazil exports more than $7 billion dollars USD worth of maize and $4.6 billion dollars USD worth of coffee per year while Ethiopia exports no maize and only exports $850 million dollars USD worth of coffee per year. With this new initiative of agricultural assistance extended from Brazil Ethiopia is expected to become as successful as Brazil is in the agricultural production sector within the next decade.

  2. The agricultural cooperation Brazil is extending to Ethiopia is a game changer , Ethiopia can learn many essential methods from Brazil on how to become self sufficient in food. Brazil got similar temperature and even similar soil to Ethiopia making Ethiopia lucky to have the Brazilian agricultural experts extending their know how to launch Ethiopia’s biggest ever agricultural irrigation projects which are expected to make Ethiopia a country of surplus food production same as Brazil is.

    The agricultural production in Brazil amounts to $67 billion dollars USD per year . Brazil exports more than $7 billion dollars USD worth of maize and $4.6 billion dollars USD worth of coffee per year while Ethiopia exports no maize and only exports $850 million dollars USD worth of coffee per year. With this new initiative of agricultural assistance extended from Brazil Ethiopia is expected to become as successful as Brazil is in the agricultural production sector within the next decade.

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.