/

ለፍትህ ዛሬውኑ እንቁም – ትህዳ ኃሣኤ ዘ ናዝሬት

101003522 1654352514716090 8022579711529975808 nግፍ በአገር እንዳይናኝ፣ኩበት ጠልቆ ዲንጋይ እንዳይዋኝ፣ከፈለግን ፣ “የሰብዓዊ መብት ረገጣ ዛሬውኑ ይቁም!!
” በማለት ለፍትህ ዛሬውኑ እንቁም ።

ትህዳ ኃሣኤ ዘ ናዝሬት

“The 46-year-old man  George Floyd died Monday night(may 25/2020) after an officer held him pinned to the ground with a knee on his neck.”  A video posted on social media of the incident allegedly showed white police officer Derek Chauvin pushing down on Mr Floyd’s neck with his knee as he yelled, “I can’t breathe.” Mr Chauvin and his three colleagues present at the death were fired and an FBI investigation began .

የ46 ዓመቱ፣ጥቁር አሜሪካዊው ጆርጅ ፍሎይድ ፣ለዘጠኝ ደቂቃ ያህል ፣አንድ አሜሪካዊ ፓሊሥ፣ አንገቱን በጉልበቱ ረግጦ ፣ አየር በማሳጣት እጅግ ነውረኛ በሆነ ግፍ እና በነውረኛ ጨካኝ ተግባር ፣”እረ መተፈሥ አቃተኝ፣አየር አጣሁ፣..በማለት እየተማፀነው ፣የእብድ ተግባሩን ድብቁ ካሜራ እየሳየን  ህይወቱን ቀምቶታል።

በዚህ ነውረኛ የእብድ ነጭ ፖሊሥ ተግባርም የተቆጡ አሜሪካዊያን ፣ነጮችን ጨምሮ፣ ጥቂት በመይባሉ የአሜሪካ ግዛቶች በ23 ግዛቶችና 40 ከተሞች (At least 40 cities in 23 states)  ህዝባዊ ቁጣ ተቀስቅሶ ፣በሚሊዮን ዶላር የሚቆጠር ንብረት መውደሙን  ፣ለተቃውሞ ሰልፍ ከወጡትም መካከል አምሥት ሰዎች መሞታቸውን ከመገናኛ ብዙሃን ከመሥማታችንም በላይ፣በአሜሪካ በፕሬሥ ታሪክ የሲኤን ኤን  ጋዜጠኛ የተቃውሞ እንቅሥቃሴውን ከሚዘግብበት ሥፍራ እጁን በካቴና ተጠፍሮ ወደ አካባቢው ፖሊሥ ጣቢያ ሲወሥዱት በሲኤን ኤን ቀጥታ ሥርጭት  ተመልክተናል።  (አጋጣሚ ይህም ጋዜጠኛ ጥቁር ነበር።)

ጋዜጠኛው ከሰዓታት በኋላ ቢፈታም ይኽ በነፃው ፕሬሥ  ላይ የተፈፀመ ህገወጥ ተግባር  እና  በጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ፣በነጭ ፓሊሥ የተፈፀመው አሥደንጋጭ እና አሥፈሪ ድርጊት የሚያሣብቀው፣በአሜሪካ ውሥጥ ፣ሥልጣን እንጂ ጭንቅላት የሌላቸው ነጮች ዛሬም ያሻቸውን እኩይ ድርጊት  ለመፈፀም የሚያሥችል ከህግ በላይ የሆነ አቅም እንዳላቸው ነው።

የሰውን ሰው መሆን የማይቀበሉ በቆዳ ቀለም ሰውን የሚያበላልጡ  ጭንቅላተ ቢሥ ቆዳ አምላኪ በዘረኝነት ያበዱ ነጮች ጥቂት ቢሆኑም፣ በአሜሪካ ውሥጥ እሥከ ከፍተኛው የሥልጣን አካል ድረሥ የሉም ብለን ምሥክርነት መሥጠት አንችልም።እነዚህ እብዶችን ከአሜሪካ መንግሥት የመንግሥት ተቋማት (ፖሊሥ፣ፍርድ ቤት ፣እሥርቤቶች እና ሌሎች የፀጥታ መዋቅሮች ውሥጥ) መኖራቸውን የሚያመላክቱ በጥቁሮች ላይ የሚፈፀሙ ኢ ሰባዊ ተግባራት ያመላክታሉና የአሜሪካ ምክር ቤት ጉዳዩን በጥልቀት እንደሚገመግመው እና ዘላቂ መፍትሄ እንደሚሻለትም እንጠብቃለን።

ዛሬም በጥቁሮች ላይ የሚፈፀመው ግፍ እንዳላባራ  በማሥተዋል፣በጥቁሮች ላይ እያየለ የመጣው የዘረኛ ነጭ ፓሊሶች ግፍ እና ማንኛውም የሰብዓዊ መብትጥሰት እንዲቆም የሚያሥችል ተጨማሪ ህግና መመሪያም እንደሚያወጡ አሥባለሁ ። ይህ ዘግናኝ እና የመላ ዓለም እናቶችን ልብ ያሳዘነ  ግፍ ለተቀረው ዓለም የሰጠው ግልፅ መልዕክት በአሜሪካ ህግ የተገላቢጦሽ መሆኑን እና ኩበት ጠልቆ ዲንጋይ እንደሚዋኝ ያሣይ ነውና ፣ከ200 ዓመት በላይ የአሜሪካ ህዝብ የገነባውን  ዴሞክራሲ በነቀዞች ውሥጥ፣ውሥጡን ተበልቶ ፀረ-ዴሞክራሲነት እያበበ ሲመጣ ቁጭ ብለው እንደማያዩት አምናለሁ።…

ጥቂት ነቀዝ ዘረኛ ነጮች፣በዙሃኑ ድብልቅ ዘር ያላቸው አሜሪካዊያን፣ ለዘመናት ታግለው፣በታላቅ መሥዋትነት የተጎናፀፉትን ነፃነት ና ዴሞክራሲ ፤ የተቀዳጁትን ፍትህን ለመላው አሜሪካዊ በእኩልነት  የሚያሰፍን ሥርዓት ለመቀልበሥ እና የጥቂት ዘረኞች ጥቅም ና ፍላጎት ፈፃሚ መንግሥት በአሜሪካ እንዲኖር እየጣሩ መሆኑን ከድርጊታቸው ማንም መገንዘብ ይችላል ። ይህ ሃሳባቸው ግን ከምኞት የዘለለ እንደማይሆን የአንድ ጥቁር ህይወት ያለፍትህ፣ያውም በነጭ ዘረኛ ፖሊሥ መሞት የአሜሪካ መንግሥትን  የሚያሥከፍለውን ዋጋ ተመልክተናል።ነገም ያላቸውን ኃይል ከማሳየት ወደኋላ እንደማይሉም መገንዘብ መልካም ነው።

ለህግ ተገዢ ያልሆኑ ዘረኞች ከመንግሥት መዋቅር ሁሉ ተለቅመው ፣ከሥልጣን እሥካልተገለሉ እና የጥቁር አሜሪካዊያን ነፃነት፣ እኩልነት፣ ህገመንግሥታዊ መብት እሥካልተከበረ ጊዜ ድረሥ ኃይላቸውን በሰላማዊ ትግል ማሳየታቸውን አያቆሙም።ይህንን ትግላቸውንም ሰው መሆናቸውን ከሚያምኑ፣ከብዙሃኑ ነጭ ወንድሞቻቸው እና እህቶቻቸው ጋር ሆነው እንደሚቀጥሉም እሙን ነው።…
……………………………………………………..
* ከዚህ ኢ ሰብአዊ ድርጊት እና ህዝባዊ ተቃውሞ ሀገሬ ምን ትምህርት ትወሥዳለች?
በሀገሬ በየቀኑ የሚፈፀም የሰብአዊ መብት ጥሰት መኖሩ የታወቀ ነው።ይህ የሰብአዊ መብት ጥሰትም ፈርጀ ብዙ ነው።
በኢትዮጵያም እንደአሜሪካ ሁሉ  በህግ አሥፈፃሚው የሚፈፀም የሰብአዊ መብት ጥሰት ብቻ አይደለም
ያለው።በያንዳንዱ ክልል፣ዞን፣ወረዳ እና ቀበሌ፤ በእያንዳንዱ የመንግሥት ተቋም(በሲቭል ሰርቪሱ ) የመንግሥት
የልማት ድርጅቶችን ጨምሮ ጥቃቅን እና ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰት ዛሬም እንደሚፈፀም ማንም ማሥተባበል
አይችልም።
በየክልሎች እሥከቀበሌ መዋቅር ድረሥ፣ ዜጎች በህግ የተሰጣቸውን መብት   ያለህግ ያጣሉ።ሠራተኞች
በአሠሪዎቻቸው ማን አለብኝነት ያለህግ ከሥራቸው ይታገዳሉ፣ይባረራሉ።ያለአግባብ ከአሠሪና ሠራተኛ ህግ ውጪ
፣በዘፈቀደ ይቀጣሉ ።  በልዩ፣ልዩ ሱስ የደነዘዙ እና የራሳቸውን ቤተሰብ መመራት የማይችሉ አሥተዳደሮችም በርካሽ
ሙሥና አንዱን ሠራተኛ ጎድተው ሌላውን ለመጥቀም ሲለ  በትርፍ ሰዓት ክፍያ ጭምር በግዳጅ መውጣት የሌለበትን
የ2012 ዓ/ም የአመት እረፍት ፈቃድ ኮሮናን ተገን አድርገው ያሶወጣሉ።የህክምና ባለሙያን ጭምር የግዳጅ እረፍት
በማሶጣት የመጀመሪያ ረድፍ ተዋጊውን ቤቱ እንዲከትም ያደርጋሉ።ይህ በተጨባጭ መረጃ የተረጋገጠ ነው። ” ደሞ
በሥልጣኔ ማናለኝ ከለከይ” ድርጊት ነው በአንዳንድ ፣በመንግሥት የልማት ተቋማት የሚከናወነው።
መንግሥት እነዚህን በልማት ድርጅትነት ያሉትን፣” ቀዳዳ በርሜሎች” ለግል ባለሀብት ሸጦ ለምን እንደማይገላገል
ፈፅሞ አይገባኝም።እርግጥ ለሀገር የሚጠቅሙ እንደ አየር መንገድ፣የኤሌትሪክ ኃይል ና ቴሌኮምኒኬሽን መሸጥ
እንደሌለባቸው ቢታመንም፣ ሌሎቹ የግለሰብን ኪሥ ከማደለብ ና ሀገሪቱ በእዳ ከመዝፈቅ ባሻገር ምን ጥቅም አመጡ?
አዎ የበለፀጉባቸው፣ኃብትና ንብረት ያፈሩባቸው ግለሰቦች እንዳሉ እናውቃለን።አዎ የሜቴክን እዳ የሚከፍሉ
በኬሚካል ኮርፖሬሽን ሥም እንደ አዲስ የተቋቋሙ ድርጅቶች እንዳሉና በየሦሥት ወሩ ሚሊዮኖችን ለኮርፖሬሽኑ ፈሠሥ
የሚያደርጉ እንዳሉ አናውቃለን።ወትሮም የተቋቋሙት የተዘረፈውን ብር ” ከፋይ ለማበጀት” ነውና ምን ይደረግ።ይሁን
እንጂ ያልበላውን በመትፋት ላይ ያለው ላብ አደሩ ነው።ያውም በዝቅተኛ የወር ደሞዝ ።ለምሳሌ በኬሚካል ኮርፖሬሽን
ሥር በሚገኘው አዎሽ መልካሣ ኬሚካል ፍብሪካ የአንድ ፅዳት ሠራተኛ ደሞዝ 600(ስድስት መቶ) ብር ነው።ይህንን
ሥትሰሙ መደንገጣችሁ አይቀርም።ግን እውነት ነው።በበኩሌ ክቡር ጠ/ሚ አብይ አህመድ ሥለ ኬሚካል ኮርፖሬሽኑ በቂ
መረጃ ያላቸው አይመሥለኝም።በኃላፊነት የሾማቸውም ባለሥልጣናት “ሥለ መንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ አጠቃላይ ታሪክ
የሚገልጥ ሰነድ” ያቀረቡላቸው አይመሥለኝም።ይህ ፀሐፊ ለመጪው ትውልድ  ሥኬት እኔም የበኩሌን ገንቢ ሚና መጫወት
አለብኝ በሚል መንፈሥ ይህንን ጥቆማ በትህትና ያቀርባል።
ይህ ትንሽ ጉዳይ ፣ከትልቁ የአየር መንገድ ሠራተኞች ችግር እና ከበጣም ትልቁ የግል ባለሀብት ተቀጣሪ ላብ
አደሮች ብዝበዛ ጋር ተደምሮ ነገ ተነገ ወዲያ የላብ አደሮችን አመፅ እንደሚያሥከትል መንግሥት ዛሬ ላይ ሆኖ
መገንዘብ እና የሰብአዊ መብት ጥሰትን ማሥቆም አሐበት ።እላለሁ ።
ዛሬ ላይ፣” ደሞ በሥልጣኔ ማን አለኝ ከልካይ!” ባዮችን በመቆንጠጥ በሥልጣን እንዳይባልጉ ካላደረገ
፣ነገ ተነገወዲያ የተጠራቀመው ብሶት ገንፍሎ በሀገር ልማት ላይ ጥፋት የሚያሥከተል የላባአደር አብዮት መፍጠሩ
አይቀርም። ።
ከላብ አደሩ የሰብአዊ መበት ጥሰት እና  ብዝበዛ ባሻገር፣ በህግ አሥከባሪው እና አሥፈፃሚ አካላቱ አሠራር
ዙሪያ ያለ ከህግ በላይ መሆን ከወዲሁ ካልታረመም ሌላ ተደማሪ አብዮት ፈጣሪ ይሆናል።
እናም ህግ ከሁላችንም በላይ መሆኑ መረጋገጥ አለበት።  ለህግ ተገዢነታችንን ማሣየት  የምንችለው በህገ
መንግሥቱ ላይ የተዘረዘሩትን መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ሥናከብርና ሥናሥከብር ብቻ  ነው።
በኢትዮጵያ ህገ መንግሥት( በምእራፍ 13 ከአንቀፅ 13 እሥከ አንቀፅ  44 ተጠቅሰዋል።)
ፖሊሶቻችን እና ወታደሮቻችን ሥለነዚህ ህገመንግሥታዊ መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች  ምን ያህል ያውቃሉ ?
ብለን ብንጠይቅ ፣እንኳን እነሱ በሚኒሥተር ደረጃ  እና በተዋረድ ያሉ የመንግሥት ሥራን የሚሠሩ  እና የሚያሰሩ
፣በቅጡ ያውቋቸዋልን?? በማለት ሌላ  ገራሚ ጥያቄ ማሥከተል  እንጂ መልሥ መሥጠት አንችልም። ካወቋቸው  እኮ
ማክበር፣ማሥከበርና በተግባር እንድናይ ማድረግ ነበረባቸው።
ከዚህ አንፃር በፖሊሶቻችን እና በወታደሮቻችን ያልተገባ ድርጊት ግንባር ቀደም ተጠያቂዎች ያለ በቂ ህገ
መንግሥታዊ ትምህርት ወደ ህጋዊ ሥራ ያሰማሯቸው የመንግሥት ኃላፊዎች እንጂ ትእዛዝ ፈፃሚዎቹ  ተጠያቂዎች
አይሆኑም። በቅጡ ህጉን ቢማሩ እና ተጠያቂ መሆናቸውን ቢገነዘቡ ኖሮ፣ለግዳጅ ሲሰማሩ የእያንዳንዱ ዜጋ ሰብአዊ
መብት ያከብሩ እንደነበር ሥለምንገነዘብ ነው እነሱን ዋነኛ ተጠያቂ የማናደርገው።ተገቢው የህገመንግሥት ቢሠጣቸው
ኖሮ ወንጀል ቢሰራ እንኳን ፣እሥካልተተናኳላቸው ጊዜ ድረሥ ፣ ያለአንዳች ዱላ እና ሥድብ ወደ ህግ ፊት
ወንጀለኞችን ያቀርቡ ነበር።
ይህ ግን እየሆነ አይደለም።የሰብአዊ መብት ጥሰት ዛሬም አለ። “በጆርጅ ፍሎይድ የተፈፀመው በጭካኔ የተሞላ
ተግባር ነው።ግፍ ነው። ያሥቆጫል ።ያንገበግ ባል። እንዴት እንዲህ ይደረጋል?!  …”በማለት የዓለም ህዝብ
ሁሉ አዝኗል።ጥቁር ሳይባል ነጭ።ግን፣ግን፣በእኛሥ ሀገር በቆዳው ቀለም ከእኛ  ባልተለየው ፣በእኛው ወንድም
፣ካየነው የባሰ ድርጊት አልተፈፀመምን?ዛሬሥ አይፈፀምምን? በድብቅ ካሜራ ተቀርፆ በይፋ አላየነውም እንጂ
በአሜሪካዊው ጥቁር ወንድማችን ከተፈፀመው ግፍ የባሰ በእኛም ሀገር በገዛ ወንድሞቻችን አማካኝነት ይፈፀማል።እናም
ይህ ግፍ በቃ! ሊባል ይገባል።ከትግራይ ክልል ጀምሮ በሁሉም ክልሎች የሰብዓዊ  መብት ረገጣ አለ።የትግራይ ክልል
ግን የከፋ ነው።አዲሶቹ ንጉሦች የትግራይን ህዝብ በሙሉ በመሣሪያ እያሥፈራሩ ጭሰኛ አድርገውታል።በኦሮሚያ
ግልፅነት እና ተጠያቂነት ቀሥ በቀሥ እየመጣ እና ህግ የበላይ መሆኑን እያየን ነው።ጅምሩ መቀጠል አለበት።…
ተሥፋ አለኝ ፣ወደፊት  ድንቁርና፣ወይም አይምሮ ቢሥነት የወለደው ፣የእብድ ሰዎች ተግባር፣ቢያንሥ በእኛ ሀገር
እንደማይፈፀም።ተሥፋ አለኝ፣ በህገ መንግሥቱ መሠረት፣ የህግ የበላይነት እየደመቀ እንደሚመጣ።ለዚህ ተሥፋ ደግሞ
ሁላችንም መታገል ይኖርብናል።
ሰው መሆናችንን ተገንዝበን ፣ለሰው ክብር በመሥጠት ፣ደሃ እና ሀብታም ሳንል፣ዘር፣ቋንቋ እና ጎሣ ሣንለይ
፣ለሰው ፊት ሳናደላ ፣የሰውን ሁሉ መሠረታዊ መብት ማክበር እና ህገ መንግሥታችን ላይ የተቀመጠውን የግለሰቦች
መብት መሥከበር ፣ካልቻልን፣አሜሪካ ውሥጥ ከታየው ነውጥ የባሰ ፣ህዝባዊ ተቃውሞ  ፣ሀገራችንን እንደሚያጋጥመት
ከወዲሁ መገንዘብ ለእርምት ይበጀናል።

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.