ዶር ብርሃኑ ነጋ የኢዜማ መሪ፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ

Birhanu“ያለፈው ሥርዓት)ሕወሃት) መጥፎ ስለነበር ማህበረሰቡን ወደ ቀውስ ከቶታል፤ ከዛ ወጥቶ ወደ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መኬድ አለበት የሚል ግፊት በመፍጠሩ ለውጡ መጥቷል። ነገር ግን ለውጡ የመጣው አብዮታዊ በሆነ መንገድ የነበረውን ሥርዓት ጥሎ አይደለም። አብዮት ሳይሆን ለውጥ (ሪፎርም) ነው። ራሱ ገዢው ፓርቲ ውስጥ ክፍፍል ተፈጥሮ፤ ‹‹እንደፓርቲ ከአሁን በኋላ መሄድ አንችልም፤ በአዲስ መልክ መሄድ አለብን›› የሚሉት አካላት አሸንፈው፤ በዚህ ሁለት ዓመት ሁኔታውን አመቻችተን ወደ ምርጫ እንሄዳለን ብለው ቀጥለዋል። ስለዚህ አብዮት ቀርቶ ለውጥ (ሪፎርም) መጥቷል። ይህ ሲባል ከሞላ ጎደል መስማማት ተፈጥሯል። መስማማቱ ያለው መንግሥት ይቀጥል የሚል ነበር። ያለው መንግሥት ይቀጥል ሲባል ባለው ሕገ መንግሥት እና ሕግ እንቀጥላለን ማለት ነው” ሲል ለውጥ እንደመጣ ይናገራል፡፡

እርግጥ ነው “ለውጥ” መጥቷል፤ ግን የመጣው ለውጥ ውጫዊ ለውጥ ነው፡፡ ወደ ውስጥ ፣ ወደ መዋቅሮችና ወደ ተቋማት ስንሄድ እንደውም በአንዳንድ ክልሎች በሕወሃት ጊዜ ከነበረው የባሰ ሁኔታ ነው ያለው፡፡

የኛ ዘር አይደላችሁም ተብለው ከየቦታው በተለይም ከኦሮሞ ክልል ለተፈናቀሉት ለውጥ አልመጣም፡፡ 40፡40፡20 በሚል(40 ለኦሮሞ፣ 40 ለሶማሌ፣ 20 ለተቀረው ማህበረሰብ) በድሬዳዋ በተዘረጋው አፓርታይዳዊ አሰራር ኦሮሞና ሶማሌ ላልሆኑ የድሬዳዋ ከተማ ነዋሪዎች ለውጥ አልመጣም፡፡ 50፡50 በሚል አሰራር (50% ለሃረሬ፣ 50% ለኦሮሞ) ሃረሬና ኦሮሞ ላልሆኑ፣ ዜሮ መብት ለሌላቸው የሃረር ነዋሪዎች ለውጥ አለመጣላቸውም፡፡ በቡራዩ፣ በሰበታ፣ በባሌ ፣ በአርሲና በመሳሰሉ ቦታዎች በግፍና በጭካኔ ለታረዱ ወገኖችና ለቤተሰቦቻቸው ለውጥ አልመጣም፡፡ በለገጣፎ፣ በአዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ አሁንም በግፍና በጭካኔ የ”ለውጥ ኃይል” በሚባሉት ቤቶቻቸው ለፈረሰባቸው፣ በየሜዳው ላይ ለተጣሉ ለነርሱ ለውጥ አልመጣላቸውም፡፡

ምን አልባት ዶር ብርሃኑ ነጋ፣ የዶር አብይ መስተዳደር በመጣ የመጀመሪዎቹ 3 ወራት የነበረው ሁኔታ፣ አሁን ከልቡ ስላልጠፋ ይሆናል ለውጥ አለ የሚለው፡፡ እኛም ያኔ የነ ዶር አብይ ንግግሮች ሰምተን ፣ እንደ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳና ዶር ዳንኤል በቀለ መሾማቸውን አይተን ለውጥ የመጣ መስሎን ነበር፡፡

ግን ለውጡ ገፍቶ ስላልሄደ፣ እንደው በተወሰነ መልኩ ስለተቀለበሰ፣ ለውጥ ያልነው በርግጥ ለውጥ አለመሆኑን ከተረዳን አመት አልፎናል፡፡ ህዝብ በነቃበትና እውነተኛ ለውጥ እየጠየቀ ባለበት ወቅት ግን ፣ ዶር ብርሃኑ ከአንድ አመት ተኩል በፊት ብዙዎች የነበራቸውን አመለካከት አሁንም እያራመደ ያለ፣ በብልጽግና ፓርቲ ሃላፊዎች እየተፈጸሙ ያሉትን ሙስናዎች፣ የሰብአዊ መብት ረገጣዎችና በዘረኛ የተረኝነት መንፈስ የሞሉ አሰራሮች ላለማየት አይኑን የሸፈነ ነው የሚመስለው፡፡

ከዚህ ጋር በተገናኘ አንድ የሚያሳዝነው ነገር ቢኖር ፣ ብዙዎች ትልቅ ተስፋ ያደረጉበት ኢዜማ በዶር ብርሃኑ አስተሳሰብ ቅኝት መቀኝቱ ነው፡፡ ኢዜማ ገዢውን ፓርቲ ቻሌንጅ የማድረግ ድፍረት ያነሳው መሆኑን ብዙዎች ይናገራሉ፡፡

ዶር ብርሃኑ ነጋና ድርጅታቸው ኢዜማ፣ የዶር አብይ መንግስት ይቀጥል ሲሉ፣ ቅድመ ሁኔታዎችን እንኳን ማስቀመጥ አልቻሉም፡፡ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አሁን ያለው መንግስት ይቀጥል ማለት ትልቅ ስህተት ነው፡፡

እርግጥ ነው አሁን ባለው ሁኔታ ብዙ ድርጅቶችን አሰባስቦ የሽግግር መንግስት መመስረት ተግባራዊ ሊሆን የማይችል ነው፡፡ ይሄ የኢዜማ ብቻ ሳይሆን የአብን፣ የኦነግ፣ የኢሶዴፓ የመሳሰሉ ድርጅቶችም አቋም ነው፡፡ እነ ኢዴፓ ያሉበት አብሮነቶችም የሽግግር መንግስት ሲሉ፣ የሽግግር መንግስት በነ ዶር አብይ መመራት እንዳለበት ያስቀመጡ በመሆኑ፣ በተዘዋዋሪ መንገድ እነ ዶር አብይ በተወሰነ መልኩ መቀጠላቸውን ነው የገለጹት፡፡

ግን እነዚህ ድርጅቶች በአንድ መልኩ ይሁን በሌላ መልኩ የዶር አብይ መስተዳደር ይቀጥል ሲሉ፣ የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን በማስቀመጥ ነው፡፡ ለምሳሌ አብን የሕገ መንግስት ማሻሻያ ሂደት እንዲጀመር ጠይቋል፡፡ ኦነግ መጪው ምርጫ ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚረዱ ኮሚሽኖች እንዲቋቋሙ ሐሳብ አቅርቧል፡፡ የዶር አብይ መስተዳደር መቀጠሉ ላይ ስምምነት ቢደረሰም፣ እንዴት ይቀጥል በሚለው ላይ ውይይቶች መደረግ እንዳለባቸው ብዙዎች ይስማማሉ፡፡

በኔ እይታ አሁን ያለው መስተዳደር ጥሩ ነው፣ ያሻግረናል፣ ባለው ይቀጥል ብሎ በነጠላው መከራከር ከአንድ ተቃዋሚ ድርጅት የሚጠበቅ አይደለም፡፡ እንዲህ አይነት ድርጅቶች ፣ ራሳቸውን አፍርሰው የብልጽግና ፓርቲ በይፋ ቢቀላቀሉ ነው የሚሻላቸው፡፡

አሁንም በዚህ አጋጣሚ ለኢዜማዎች የምመክረው ከዶር ብርሃኑ ነጋ የፖለቲካ አመለካከት ቅኝት እንዲወጡ ነው፡፡ ብዙዎች የኢዜማ አባላት ለፍትህ፣ ለእኩልነት፣ ለዲሞክራሲ ትልቅ ዋጋ የከፈሉ ናቸው፡፡ እነርሱን የቀድሞ ኢሕአዴግ አሁን ብልጽግና ፓርቲ ተለጣፊና ተደማሪ ተደርገው ሲታዩ ማየት፣ እንደኔ ላሉ እነርሱን ለሚያውቁ ሰዎች ያማል፡፡ ያንን ማስተካከል የሚችሉት ደግሞ እነርሱ ራሳቸው ናቸው፡፡ ለምን “ተደማሪና ተለጣፊ” ተደርገን ታየን ብሎ መናደድና ማኩረፍ ሳይሆን፣ ይሄን አመለካከት ለመቀየር መስራት ነው የሚሻለቸው፡፡ አንዳንድ አመራሮች ደስተኛ ላይሆኑ ቢችሉም፣ ኢዜማ መሰረታዊ የአካሄድ ለውጥ እንዲያደርግ፣ እውነተኛ፣ ለሕዝብ ጥቅም የቆመ፣ የዜጎች ሕመም የሚያመው ፣ የፖለቲካ አደርባይነትን የማያስተናገድ ድርጅት ሆኖ እንዲወጣ በአባላቱ ከታች ወደ ላይ ትልቅ ግፊት መደረግ አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡በርግጥም እንደሚባለው ኢዜማ ዴሞክራሲያዊ አሰራር ካለው፣ ኢዜማ በራሱ በድርጅቱ መድረክ፣ በአባላት ግፊት ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብለን ልንጠብቅ እንችላለን፡፡ ግን ድርጅቱ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ፣ በስውርና ሲስተማሪክ አሰራር፣ ከአንድ ግለሰብ ፍላጎትና ፍቃድ ውጭ ውሳኔዎችን የመወሰን አቅም ድርጃታዊ አሰራር ከሌለው ግን አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ ሁሉንም ነገር በሂደት የምናየው ይሆናል፡፡

(በነገራችን ላይ ይህ ጽሁፍ በዶር ብርሃኑ ግለሰባዊ ማንነት ላይ ያነጣጠረ አይደለም፡፡ በአዲስ ዘመን ላይ በተናገረው የፖለቲካ አመለካከት ላይ እንጂ፡፡ ስለዚህ በዚህ የቀረበውን ሐሳብን በነጻነት በመተቸትና መሞገት ይችላል፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ለምን ዶር ብርሃኑ ተቸህ ብሎ የሚሳደቡ ካድሬዎች ካሉ ግ ን በስድባቸው እነርስ ያነሱ መሆናቸውን እንደሚያመለከቱ ከወዲሁ ልነግራቸው እወዳለሁ)

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.