ግብጽን ያመነና ጉም የዘገነ አንድ ነው – ከመርሐጽድቅ መኮንን አባይነህ

Merhaኢትዮጵያና ግብጽ በመልክአ-ምድራዊ አቀማመጣቸው ሲታዩ ድንበር ተዋሳኝ አገሮች አይደሉም፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱም የሚገኙት በናይል ተፋሰስ እቅፍ ውስጥ እንደሆነ ይታወቃል፡፡

‘የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ማማ’ በመባል የምትታወቀው ሀገራችን ኢትዮጵያ ብቻዋን በጥቁር አባይና በበርካታ ገባሮቹ አማካኝነት ለናይል ወንዝ እስከ86 በመቶ የሚሆነውን የውሃ ሀብት ስታመነጭ ቀሪውንና እስከ14 በመቶ የሚሆነውን ደግሞ በላይኛው የተፋሰሱ ክፍል የሚገኙ ሌሎች አገሮች ከቪክቶርያ ሀይቅና እርሱን ተንተርሰው እየተቀባበሉና አንዳንዴም በየመንገዱ እያንቀላፉ በነጭ አባይ ስያሜ በሚፈሱት ትናንሽና ትላልቅ ወንዞችና ረግራጋማ ስፍራዎች አማካኝነት ያበረክታሉ፡፡

ግብጽን የወሰድን እንደሆነ ግን አያሌ አገሮችን ለሚያካልለው ለዚህ ተፈጥሯዊ የውሃ ፍሰት አንዳች አስተዋጽኦ እንዳይኖራት ተደርጋ ነው በደረቁ የተሰራችው፡፡ እንግዲህ በመሬት ላይ ያለው እውነታ ይህ ሆኖ ሳለ ይሉኝታቢሷ ፈርኦናዊት ምድር እንደአንድ ክፍለ-ሀገር ከምትመለከታት ከሱዳን ጋር በተናጠል የውል ስምምነት ተጋርቸዋለሁ ከምትለው አነስተኛ ድርሻ በስተቀር መላውን የወንዙን የውሃ ፍሰት በብቸኝነትና በማናለብኝነት ተቆጣጥራ መበዝበዝ ከጀመረች ድፍን ክፍለ-ዘመን አለፋት፡፡

በተፋሰሱ የመጨረሻ ግርጌ የምትገኘው ግብጽ ቀድሞ ነገር ተፈጥሯዊ አቀማመጧ የድንበር ተሻጋሪው ወንዝ የውሃ ፍሰት ተቀባይ እንጂ አመንጪ ሊያደርጋት እንደማይችል እሙን ነው፡፡ ሆኖም በየጊዜው ስልጣን ላይ የሚወጡት መሪዎቿ ለተራው የግብጽ ህዝብ በሚዲያዎቻቸው አማካኝነት አበክረው የሚነግሩት ይህንን ሀቅ አይደለም፡፡ በረዥሙ ተጉዞ ከነግንሳንግሱ በምድረ-ግብጽ በረሃ ላይ እንደደረሰ እረፍት የሚያደርገው የናይል ወንዝ መነሻው ከርሱ እንደሆነና ሀብትነቱም የርሱ ብቻ እንደሆነ ጭምር ሀሰተኛ መረጃዎችን ደጋግመው ሲረጩበት አንዳች ሀፍረት አይሰማቸውም፡፡

አነታራኪዎቹ የቅኝ አገዛዝ ውሎች

በአመት ውስጥ ይህ ነው የሚባል የረባ የዝናብ ጠብታ የማይጎበኛት ግብጽ የናይልን የውሃ ፍሰት በብቸኝነት የመጠቀም ታሪካዊ መብት እንዳላት አጥብቃ ስትወተውት መስማቱ የተለመደ ፈሊጥ ሆኗል፡፡ ነገር ግን አለም-አቀፉ ሕብረተ-ሰብ በሀሰት እንዲያዝንላትና ከጎኗ እንዲቆም  አብዝታ የምትጣራው ይህችው ሞገደኛ አገር በቂና ለተራዘመ ጊዜ ጥቅም ላይ ሊውል የሚችል እምቅ የከርሰ-ምድር ውሃ እንዳላት በሚገባ ከተረጋገጠ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ አሸዋማነት በተጠናወተው ማህጸኗ ውስጥ ተቀብሮ የሚኖረውንና ቢያንስ ከአምስት መቶ ዓመታት ለሚበልጥ ጊዜ ሊያገለግል እንደሚችል የሚገመተውን ይህንኑ የከርሰ-ምድር ውሃ፣ (aquifer ይሉታል የመስኩ ሙያተኞች)፣ አውጥቶና በቴክኖሎጂ አበልጽጎ ከመጠቀም ይልቅ ድንበር ተሻጋሪውና ሁሉም የተፋሰሱ አገሮች አስቀድሞ በሚደረግ የትብብር ስምምነት እንደየፍላጎታቸው ሊጋሩት የሚገባው የናይል ወንዝ “በኔ በኩል የልማት ብቻ ሳይሆን የደህንነቴም ዋስትና ነው” ስትል ከመቃዠት አልፋ “በቀደምት ተባራሪ ውሎች ተጠብቆልኛል የምትለውን ታሪካዊ የውሃ ድርሻ የሚነካ ሀይል ቢኖር ወዮለት” በማለት ድምጿን ከፍ አድርጋ የላይኛውን የተፋሰሱን አገሮች ስታስጠነቅቅ ኖራለች፡:፡

በመሰረቱ ግብጽ በተናጠል ከሱዳን ጋር እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር November 8 ቀን 1959 ዓ.ም ከተፈራረመችው የሁለትዮሽ ውል በስተቀር የናይልን ውሃ አጠቃቀም በሚመለከት ከየትኞቹም የተፋሰሱ ራስጌ አገሮች ጋር ያደረገችው ስምምነት የለም፡፡ በርግጥ ከጉዳዩ ጋር በተገናኘ ደጋግማ የምትጠቅሳቸው ሁለት ሌሎች የቆዩ ስምምነቶች አሉ፡፡

ከነዚህ ውሎች አንደኛውና የመጀመሪያው ዳግማዊ አጼ ምኒልክ ከያኔው የታላቋ ብሪታንያ ንጉሠ-ነገሥት እንደራሴ ጋር አዲስ አበባ ላይ በ1902 ዓ.ም ተፈራርመዉታል እየተባለ የሚነገርለትና በዋነኝነት ሀገራችን በእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ስር ተጠርንፈው ይተዳደሩ ከነበሩት የጥምረተ-ግብጽ ወሱዳን ግዛቶች ጋር የምትዋሰንባቸውን ስፍራዎች ለማመላከት የተደረገው ውል ነው፡፡ በወቅቱ ስልጣን ላለው አካል ቀርቦ ያልጸደቀው ይህ የቅኝ አገዛዝ ውል በአንቀጽ 3 ላይ የኢትዮጵያ ንጉሠ-ነገሥት “በጥቁር አባይ ወንዝና የዚሁ ወንዝ መነሻ በሆነው የጣና ሀይቅ ዳርቻዎች ላይ የውሃውን ተፈጥሯዊ ፍሰት የማገድ ወይም አስሮ የመያዝ ውጤት ያለውን ማናቸውንም አይነት ግንባታ አላከናውንም ወይም በሌሎች እንዲከናወን አላደርግም” ሲሉ ለብሪታንያው አቻቸው ግዴታ እንደገቡላቸው ያጠይቃል፡፡

ለነገሩ እኮ በዚያ ነባር የስምምነት ሰነድ፣ (ለያውም ውል ከተባለ ነው)፣ የዛሬዋ ግብጽ ራሷ በቅኝ አገዛዝ ቀንበር ወድቃ ስትማቅቅ የነበረች አገር በመሆኗ የውሉ ተካፋይ ሆና በስም እንዳልተጠቀሰች ልቦናዋ ጠንቅቆ ያውቀዋል፡፡ ለማናቸውም እንደውጫሌ ውል ሁሉ በአማርኛና በእንግሊዘኛ ቅጅዎቹ ሳይቀር እኩል የማይናበበው ይህ የሻገተ ውል ቅኝ ተገዥነቷን በቅርስነት ለማስታወስ ይጠቅማት ካልሆነ በስተቀር እነሆ ከ120 ዓመታት በኋላ በሕግ ፊት እንደሚጸና ውል ተቆጥሮ ግብጽን ሊያገለግላት አይችልም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  የሰላማዊ ትግል እድገታችን - ግርማ ሞገስ

ሁለተኛው ደግሞ አሁንም ታላቋ ብሪታንያ በቀድሞው አቋማቸው የግል ቅኝ ግዛቶቿ በነበሩት በላይኛው የተፋሰሱ አገሮች ጫማ ውስጥ ሆና ማንም ሳይወክላት ከግብጽ ጋር እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር በMay 7 ቀን 1929 ኣ.ም ያደረገችው ውል ነው፡፡ ግብጻውያን በተደጋጋሚ የሚዘምሩለት ይህ የቅኝ አገዛዝ ውል ቅኝ ገዥ የነበረችው አገር ቅኝ ግዛቶቿ የነበሩትን የምስራቅ አፍሪካ አገሮች የቅድሚያ ፈቃድ ሳትጠይቅ በራሷ ጊዜ ከግብጽ ጋር ያደረገችው በመሆኑ ድህረ-ስምምነት ከአስከፊው የቅኝ አገዛዝ ቀንበር ነጻ የወጡት አዳዲሶቹ መንግሥታት ያልተቀበሉትና ከናካቴው ያወገዙት መሆኑ እዚህ ላይ ሊታወስ ይገባል፡፡

ይልቁንም እንዲህ ያለው ያረጀና ጉዳዩ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ወገኖች ፈቃድ ውጭ የተደረገ የቅኝ አገዛዝ ውል ተተኪዎቹ መንግሥታት ነጻ ከወጡ በኋላ ካላጸደቁት በስተቀር በአለም-አቀፍ ሕግ ፊት ተፈጻሚነት እንደማይኖረው በግልጽ ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡

በMay 7 ቀን 1929 ዓ.ም የተደረገው ይህኛው ውል የግብጽን የውሃ ድርሻ እስከ48 ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ያደረሰው ሲሆን፡፡ ገና ነጻ ባልወጣችው ሱዳን ውስጥ ለሚከናወኑ የመስኖ እርሻዎች ልማት ደግሞ እስከአራት ቢሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ ተመድቦላቸው ነበር፡፡:

ይህም አነሳትና ግብጽ ሆየ ከእንግሊዝ ቅኝ አገዛዝ ዘግየት ብላ ነጻ ከወጣችው ሀገረ-ሱዳን ጋር በቀድሞ ቅኝ ገዢዎቿ ሙሉ ድጋፍ ተደራድራ አዲስና የተሻሻለ የውሃ ክፍፍል ስርአት እንዲዘረጋ ማድረግ በመቻሏ የ1959ኙ ስምምነት ተፈረመ፡፡ ይህ የተናጠል ስምምነት ታዲያ ለናይል ወንዝ የአንበሳውን ድርሻ የምታበረክተውን እናት ኢትዮጵያን ሳይቀር ያገለለ ሆኖ መላውን የናይል ወንዝ ውሃ ኢ-ፍትሃዊ በሆነ መንገድ ለግብጽና ለሱዳን ብቻ የሚያከፋፍል ነው።

መደበኛው የውሃ ድልድል ተከናውኖ ከበረሃው ትነት የሚተርፍ ፍሰት ቢኖር እንኳ ማንም ድርሽ ሳይልባቸው ሁለቱ አገሮች ብቻ በተጨማሪነት እንዲከፋፈሉት ያለአንዳች ይሉኝታ ስምምነቱ ይደነግጋል፡፡ በዚህም መሰረት በታላቁ የአስዋን ግድብ ላይ ሲለካ እስከ84 ቢሊዮን ይደርሳል ከሚባለው ጠቅላላ የናይል ውሃ ውስጥ 55.5 ኪዩብ ሜትር የሚሆነው ለግብጽ ሲመደብ 18.5 ኪዩብ ሜትር በሚሆነው ደግሞ ሱዳን እንድትጠቀምበት ተወስኗል፡፡

በላይኛው የተፋሰሱ ክፍል የታቀፉት አገሮች በቂ ዝናብ ስለሚያገኙ የናይል ውሃ ፍሰት ተጋሪዎች አይደሉም ተብሎ የተደመደመ ይመስላል፡፡ ይልቁንም እነዚህ አገሮች ወደሱዳንና ግብጽ በሚፈሰው አቢይ ወንዝም ሆነ እርሱን በሚመግቡት ሀይቆችና ሌሎች የውሃ አካላት ላይ አንዳች ግንባታ ከማከናወናቸው በፊት የእመቤቲቱን የግብጽን ፈቃድ እንዲጠይቁ አሳሪ ማእቀብ ተጥሎባቸዋል፡፡

በዚህ ጸሀፊ አስተያየት በዘመናዊው የአለም-አቀፍ ሕግ ስርአት ውስጥ እንዲህ ያለው ፍርደ-ገምድል ስምምነት ሲፈረም መታየቱ ብቻ ሳይሆን ዛሬም በዋቢነት ሲጠቀስ መሰማቱ በጅጉ ይዘገንናል፡፡ ዘመነኞቹን የዚያች አገር የሕግና የፖለቲካ ጠበብትንም በአደባባይ ክፉኛ ያሳጣል፡፡

የናይል ተፋሰስ ጅማሮና የኢንቴቤው ስምምነት

የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችና ሌሎች የውሃ አካላት አጠቃቀምና ጥበቃ ውጤታማ የሚሆነው በተፋሰሱ ውስጥ በታቀፉትና ሀብቱን በሚጋሩት አገሮች መካከል አመርቂና አሳታፊ ድርድር ተካሂዶ ፍትሃዊ ክፍፍሉን በተመለከተ ሁሉንም ተዋሳኝ አገሮች ከመላ ጎደል የሚያግባባ የትብብር ስምምነት ላይ ሲደረስ ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ አፍሪካ ውስጥ ናሚብያና የደቡብ አፍሪካ ሪፓብሊክ፣ በእስያ ህንድና ፓኪስታን እንዲሁም በሰሜን አሜሪካ ዩናይትድ ስቴትስና ሜክሲኮ ያደረጉት ይህንኑ ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በናይል ተፋሰስ ቀጠና ለረዥም ጊዜ የተጠቀሰው አይነት ስምምነት አልነበረም፡፡ ጥረቱ ራሱ የተጀመረው እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር በ1999 ዓ.ም ነበር፡፡ ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ

ያን ጊዜ በላይኛው የተፋሰሱ ክፍል የሚገኙት አገሮች እንቢተኞቹን ግብጽና ሱዳንን ሳይቀር በመጋበዝ ለአስር ዓመታት ያህል በንቃት ያካሄዱት እልህ አስጨራሽ ድርድር የመጨረሻ መቋጫው እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር በ2010 ዓ.ም ኢንቴቤ ዩጋንዳ ላይ የተፈረመው የናይል የትብብር ማእቀፍ ስምምነት ይሰኛል፡፡ ሆኖም በእንግሊዘኛ ቋንቋው አህጽሮት C.F.Aእየተባለ የሚጠራውና በቅኝ አገዛዝ ውሎች ሳቢያ አለቅጥ ተዛብቶ የኖረውን የውሃ ድልድል ስርአት ያርማል ተብሎ ብርቱ ተስፋ የተጣለበት ይህ ተፋሰስ አቀፍ የትብብር ማእቀፍ ውል ብዙዎች በደስታ ቢቀበሉትም ግብጽና ሱዳን እንደልማዳቸው በተቃውሞው እንደገፉበት ታዝበናል፡፡ በሌላ አነጋገር ያዲያቆነ ሰይጣን ሳያቀስስ አይለቅም እንዲሉ ሁለቱ ሞገደኛ አገሮች በነባር የቅኝ አገዛዝ ውሎች አግኝተነዋል የሚሉትን ታሪካዊ የውሃ ድርሻ ጠብቆ የሚያቆይ ሀረግ ካልተካተተበት በስተቀር አዲሱን የትብብር ማእቀፍ ስምምነት ለመፈረም ፈቃደኞች እንዳልሆኑ በግብር አሳይተዉናል፡፡ ከዚህ የተነሳ ብዙ የተለፋበት የኢንቴቤ ውል እስከዛሬ ድረስ በየተፋሰስ አባል አገሩ ሕግ አውጪ ፓርላማ በኩል ጸድቆ በስራ ላይ እንዳይውል እንቅፋት ሆነዋል ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡

ተጨማሪ ያንብቡ:  በኢትዮጵያዊያ የመሳፍንት ዘመን አጭር ታሪክ

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታና እንድምታዎቹ

እንግዲህ ግብጽና ሱዳን ከፍ ብሎ የተጠቀሰውን የትብብር ማእቀፍ ስምምነት ፈጥነው ከመፈረም ተቆጥበው እግራቸውን ሲጎትቱ በአንክሮ እየተመለከተች ከበቂ ጊዜ በላይ የታገሰችው ሀገራችን ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን በመጠቀም ዜጎቿን ከአስከፊ ድህነት ለማላቀቅ ይቻላት ዘንድ የራሷን እርምጃ ከመውሰድ የተሻለ ሌላ አማራጭ አልነበራትም፡፡ ለዚህ ነበር የአለም-አቀፉን ሕብረተ-ሰብ ትኩረት የሳበውንና የባለብዙ ቢሊዮን ዶላር ፕሮጀክት የሆነውን ታላቁን የህዳሴ ግድብ ግንባታ በራሷ ወጪ ለመጀመር ቁርጠኝነት በማሳየት እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር በApril ወር መባቻ በ2011 ዓ.ም የመሰረት ድንጋይ ያስቀመጠችው፡፡

በመሰረቱ የህዳሴው ግድብ ግንባታ መጀመር በይፋ የተበሰረበት መንገድ መላ ኢትዮጵያውያንን ያኮራ፣ ወዳጆቻችንን ያስደመመና ጠላቶቻችንን ያሳፈረ ነበር፡፡ በዚህ ረገድ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ዜናዊ ያሳዩት ተነሳሽነትና መደፋፈር ምስጋና ሊቸረው ይገባል፡፡

እንደትልቅ ድፍረት የተቆጠረውን ይህንን እርምጃ ተከትለው የግብጽ ሲቪልና ወታደራዊ ባለስልጣናት እንደቀደምት አባቶቻቸው ሁሉ በህቡእም ሆነ በአደባባይ ሊያስፈራሩንና ሊወርፉን መሞከራቸው አልቀረም፡፡ ይህ ግን ጉዳዩን የበለጠ ከማወሳሰብ  የዘለለ ፋይዳ አልነበረውም፡፡ ስለሆነም የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድቡን ተጨባጭ የግንባታ ጅማሮ ከርቀት አስፈራርታ ልትቀለብስም ሆነ መሬቱ ይቅለለውና የበረሃውን አንበሳ የኢንጂኒየር ስመኘው በቀለን እስከወዲያኛው ታጥቆ በጉባ ተራሮች መመላለስ ለጊዜው ልታስቆም እንደማይቻላት በውል የተረዳችው ግብጽ እስከካርቱም ድረስ ግማሽ መንገድ በመጠጋት ከሱዳንና ከኢትዮጵያ ጋር እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር March 23 ቀን 2015 ዓ.ም የመርሆች መግለጫ በመሰኘት የሚታወቀውን አሳሪ ያልሆነ የሶስትዮሽ ስምምነት ለመፈራረም ተገዳለች፡፡

ዛሬም ድረስ ቢሆን አጥብቃ ከምታመልካቸው የቅኝ አገዛዝ ውሎች ጋር ሲነጻጸር ለአለም-አቀፉ የውሃ ሕግ ቅርብ ሆኖ በሚታየው በዚህ የመግባቢያ ሰነድ አንቀጽ 5. መሰረት ደግሞ የህዳሴው ግድብ ግንባታ ሲጠናቀቅ የውሃ ሙሊቱ በሚካሄድባቸውና አለቃቀቁ የታችኞቹን የተፋሰስ አገሮች የውሃ ፍላጎት ክፉኛ ሳይጎዳ በሚፈጸምባቸው ጉዳዮች ላይ የሶስቱን አገሮች የቴክኒክና የሕግ ባለሙያዎች ያሳተፈ ድርድር በ15 ወራት ውስጥ ተካሂዶ እንዲጠናቀቅና ዝርዝር የማስፈጸሚያ ደንቦች እንዲቀረጹ ይጠይቃል፡፡ ‘እረኛ ቢቆጣ ምሳው ራቱ ይሆናል” እንዲሉ ግብጽ ራሷ ለራሷ ፍጹም ዳተኛ ባትሆን ኖሮ ይህ እምብዛም ባልከበደ ነበር፡፡

የውሃ ሙሊቱ መጀመር ግብጽን ያን ያህል የሚያስበረግጋት ለምን ይሆን?

ታላቁን የህዳሴ ግድብ በጥቁር አባይ ወንዝ ላይ የምንገነባው ከመጪው ክረምት አንስቶ በቂ ውሃ ሞልተን ለሁለንተናዊ ልማት የሚሆነን የኤሌክትሪክ ሀይል ልናመነጭበት እንደሆነ ከኛ በብዙ ቀድመው የአስዋን ከፍተኛ ግድብና የናስር ሀይቅ ባለቤቶች ለሆኑት ለጎረቤት ግብጻውያን አይጠፋቸውም፡፡ ግድቡ ያመረትነውን የእርሻ ሰብል የምናከማችበት የእህል ጎተራ አይደለም፡፡ ይህ አይቀሬ እውነታ ከሆነ ደግሞ ያች አገር ተኝታ በተነሳች ቁጥር ለምን ያን ያህል እንደሚያባንናት ፈጽሞ ግልጽ አይደለም፡፡

በርግጥ የግድቡ ግንባታ ተገባዶ እንደታቀደው የውሃ ሙሊቱ በሚጀመርበት ወቅት በቅኝ አገዛዝ ውሎች መሰረት እስካሁን ታገኘው የነበረው የውሃ መጠን እንደሚቀንስ ደጋግማ ስትወተውት እንሰማታለን። ይሁን እንጂ የተባለው ቅናሽ እንደሚባለው ያን ያህል የተጋነነ አይደለም። የመስኩ ሊቃውንት እንደሚነግሩን ከአስር እስከአስራሁለት በመቶ ቢሆን ነው።

የድንበር ተሻጋሪ ወንዞችን አጠቃቀም በሚወስነውና እንደፈረንጆቹ የዘመን ቀመር በ1997 ኣ.ም በተፈረመው አለም-አቀፉ የውሃ ስምምነት ኣንቀጽ 7 መሰረት ደግሞ ይህ አይነቱ የጉዳት መጠን ‘አቢይ ጉዳት’ (significant harm) ተብሎ ኢትዮጵያን በፍርድ አደባባይ ጥፋተኛ የሚያሰኝና የሚያስወቅሳት አይደለም፡፡ ግብጽም ብትሆን በህዳሴው ግድብ ምክንያት አጣዋለሁ ብላ የምትሰጋበትን ይህንኑ ጉድለት ለማካካስ የከርሰ-ምድር ውሃን አውጥቶና የሜዲተራኒያንን ጨዋማ ውሃ አጣርቶ በአማራጭነት የመጠቀም እድልና ችሎታው አላት፡፡

ከዚህ አልፋ ሀገራችንን ጨምሮ መላው የተፋሰሱ አባል አገሮች ሊጋሩትና ፍትሃዊ በሆነ አመዳደብ  ሊጠቀሙበትና ሊለሙበት የሚገባውን የናይል ውሃ በብቸኝነት እየተንበሸበሽኩበት እንደወትሮው ካልቀጠልኩ በማለት የኣዞ እንባ የምታፈስበትን የግብዝነት አድራጎት ጨርሶ ልንቀበለው አንችልም፡፡ “በድሮ በሬ ያረሰ የለምና” የዋሽንግተኑ ድርድር አልሳካ ሲላት ለተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ የከፈተችውን የክስ ዶሴ በአፋጣኝ ዘግታ ወደጠረጴዛ ውይይቱ ብትመለስ ነው ለራሷም የሚበጃት፡፡

እኛ ምን ማድረግ አለብን?                

ግንባር-ቀደሙ ኀላፊነታችን የዘመናት ቁጭት አነሳስቶን በራሳችን ወጪ የምንገነባውን ግድብ በጥፍራችን ላይ ቆመንም ቢሆን በቶሎ ማጠናቀቅና ለምርቃት ማብቃት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ብቻ ይበቃል ተብሎ አይታመንም፡፡ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ተጨማሪና ምናልባትም የላቀ የቤተት ስራ አለብን፡፡

የጥቁር አባይ ወንዝ መነሻው የጣና ሀይቅ ነው፡፡ ሀይቁ ግና በአደገኛው መጤ አረም ክፉኛ በመጠቃት ላይ በመሆኑ የድረሱልኝ ጥሪ ማሰማት ከጀመረ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ ጉዳዩ ለአንድ ሰሞን ያንቦጀቡጀንና ወዲያው እንረሳዋለን፡፡

እነሆ እንቦጭ የጣናን ሀይቅ በወረረበት ፍጥነትና ስፋት ሳይገታ መቀጠሉ እውን ሆኗል፡፡ ‘ሳይቃጠል በቅጠል’ እንዲሉ ከክልል እስከፌደራል ያለን ሀይሎች ከአካባቢው ሕብረተ-ሰብ ጋር እጅና ጓንት በመሆን ተረባርበን ካልተከላከልነው በስተቀር እስከጉባ ዘልቆ የህዳሴውን ግድብ ከማጥቃት አይመለስም፡፡ አይበለውና ከዚያ በኋላ የአባይ መፍለቂያ የሆነውና በቀላሉ እንዳይነጥፍ ሆኖ የተሰራው ብርቅዬ የጣና ሀይቅ ደርቆ የትኛውን የውሃ ፍሰት ወደግድቡ እንደምንሞላ ራሱ አንድዬ ብቻ ይሆናል የሚያውቀው፡፡ ስለዚህ በተደቀነብን አደጋ ልክ ሁላችንም መንቃት፣ መታጠቅ፣ መደራጀትና እንቦጭን መከላከል ይኖርብናል፡፡

የጣና ሀይቅ የሚገኘው ውቢቷን የባህርዳር ከተማን ተንተርሶ በአማራ ክልል የግዛት ወሰን ነው፡፡ ድህነት በተንሰራፋበት፣ ይኸው በፊናው ያስከተለው ማሕበራዊ ውጥረት በነገሠበትና ይልቁንም የንዋይ እጥረት ጎልቶ በሚታይበት በዚህ አካባቢ ቁልፍ ችግሮችን በውል ለይቶ ለአፈታታቸው ቅደም-ተከተል ማውጣት ምን ጊዜም ቢሆን አማራጭ የለውም፡፡ ከዚህ የተነሳ ሀይቁን ከጥፋት ለመታደግ የአማራ ክልል በግንባር-ቀደምትነት ዘብ መቆሙና የበለጠውን ተግቶ መንቀሳቀሱ የሚጠበቅ ጉዳይ ነው፡፡

ለዚሁ ታስቦ በጣና ሀይቅና ሌሎች የክልሉ የውሃ አካላት ጥበቃ፣ ልማትና እንክብካቤ ላይ አተኩረው የሚሰሩ ተቋማት ተመስርተዋል፡፡ ነገር ግን ይህ ብቻውን የመጨረሻ ግብ እንዳልሆነ ከወዲሁ መታወቅ ይኖርበታል፡፡ እንቦጭ ጥርስ አውጥቶ እንዳይስቅብን የነዚህኑ ተቋማት ሁለንተናዊ አቅም በሚገባ አጎልብተን አረሙን ለመከላከል የሚያስችላቸውን ቴክኖሎጂ አስታጥቀን በሙሉ አቅም ልናሰራቸውና ልዩ ትኩረት ሰጥተን ልንደግፋቸው ያስፈልጋል፡፡

እንዲያም ሆኖ ሀይቁ ከአገር አልፎ በአለም-አቀፍ ደረጃ ሳይቀር እውቅና ተሰጥቶት በተፈጥሮ ቅርስነት የተመዘገበ ሀብት ነውና ደህንነቱን በተመለከተ የፌደራሉ መንግሥትም ቢሆን እጁን አጣጥፎ ሊመለከተው አይገባም፡፡ ይልቁንም የተለየ ትኩረት ሰጥቶ በሀገሪቱ ተወዳዳሪ ለሌለው ለዚህ የተጎሳቆለ ሀይቅ በፍጡነ-ረድኤትነት እንዲደርስለት ያስፈልጋል፣ ይገባልም፡፡

እንግዲህ የጣና ሀይቅ ንኡስ ተፋሰስ ከተራቆተ ግብጽ በራሷ ላይ ሳይቀር እንደምታሟርተው ወደግድቡ የምንሞላውም ሆነ የምንፈልገውን ሀይል አመንጭተን ለታችኞቹ የተፋሰሱ አገሮች የምንለቀው ውሃ ሊኖረን ከቶ አይችልም፡፡ ስለዚህ በወንዙ ራስጌ ላይ የምናካሂደውን የተፈጥሮ ሀብት ልማትና እንክብካቤ ሳናጓድል በመቀጠል የህዳሴውን የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ግድብ ግንባታ በታቀደለት የጊዜ ሰሌዳ ማጠናቀቅና የውሃ ሙሊቱን በመጀመር ይህንኑ ታሪካዊ ኩነት ለወዳጆቻችን ማብሰርና ገና መሰረቱን ስንጥል በአይችሉትም ሽሙጥ የተዘባበቱብንን ወገኖች ማሳፈር አይነተኛው ተግባራችን ይሆናል፡፡

በዲፕሎማሲው ዘርፍም ቢሆን እስካሁን ድረስ የላቀው ድርሻ በግብጽ የተወሰደብን መስሎ ስለሚታይ መላ ሀይላችንን አሰባስበን በብርቱ መስራት አለብን፡፡ በዘመነችው አለማችን ብሔራዊ ጥቅሞችና ቡድናዊ ፍላጎቶች ዐለቅጥ የተወሳሰቡ ናቸው፡፡ ዲፕሎማሲም ‘ሙያ በልብ ነው’ ተብሎ ብቻ የሚታለፍ ነገር አይደለም፡፡ ከተገዳዳሪዎቻችን በኩል በተቀደደልን ቦይ ብቻ መፍሰሱ እምብዛም እንደማያዋጣን እየተረጋገጠ መጥቷል፡፡

በርግጥ የመርሆች መግለጫን ከፈረመች በኋላ እንኳ የዚያ የሶስትዮሽ ስምምነት ተካፋዮች ከሆኑት ሸሪኮቿ ጋር በቅን ልቦና ከመደራደርና በራስ አቅም አስታራቂ መፍትሄ ላይ ከመድረስ ይልቅ ሀያላን አገሮችና ተቋማት እንዲያማልዷት እዚህና እዚያ መቅበዝበዝ የሚቀናት ከዳተኛዋ ግብጽ የገባችበት አሁናዊ የፖለቲካ መቀመቅ በአግባቡና በብልህነት ከተጠቀምንበት በብልጫ የተወሰደብንን የዲፕሎማሲ የበላይነት ለማስመለስ በመጠኑም ቢሆን ሳያግዘን አይቀርም፡፡

ዐበቃሁ፡፡

 

ተጨማሪ ያንብቡ:  ወያኔ፣ ፍትህ እና እኛ - ያሬድ ኃይለማርያም

3 Comments

 1. ወንድም መርሐጽድቅ እንደምንጊዜውም ሁሉ ግሩም ትንታኔ ነው የጻፍከው። እጅህን ቁርጥማት አይንካው፤ በርታ። ብዙዎች ባንቀላፉበት አስተዛዛቢ ወቅት ስለእናት መጨነቅና አቅም የፈቀደውን ማድረግ በታሪክ ትልቅ ዋጋ አለው።

 2. መርሀ ጽድቅ እግዜር ይስጥልን በእዉቀት የታገዘ ግሩም ድርሳን ነዉ። ይህን የመሰለ ብዙ ጥረት የሚጠይቅን ጽሁፍ አንብቤ እንደ አልባሌ ነገር ለማለፍ ህሊናዬ ስለሞገተኝ ነዉ የአመሰግናለሁ መልእክት ማስተላለፍ የፈለግሁት። እንዲህ እንደእናንተ ከየቦታዉ ዘረኝነትን አልፎ ዋናዉ ነገር ላይ አተኩሮ ዘመን ተሻጋሪ የሆነ ሀሳብን ከበላይ ሁኖ ሲልክ መመልከት እንዴት ደስ ይላል።

  ሰሞኑን መራራ ጉዲናም ሰዉ ሲያደርገዉ ስላየ ሰለ አባይ ሊጽፍ ሞክሮ የተሰራበት መልሶ ወደልምዱ ጥሎት ጽሁፉም ጽሁፍ ሳይመስል ቀረ እኛም ከመግቢያዉ ተራምደን ልናየዉ አልሞከረንም።
  እንግዲህ ይበርቱ መቼም እርሶ አካባቢ እንደ ህዝቅኤል ጋቢሳ፤ጁዋር መሀመድ፤በቀለ ገርባ፤ጸጋዬ አራርሶን የመሰሉ በሀሳብ የተጎዱ ዜጎች ይኖራሉ ብዬ ስለማልገምት አካባቢዎ ያሉትን ኢትዮጵያን በዚህ ጉዳይ መክተዉ እንዲይዙ ማሳሰቢያ ስጡበት። አሁን የሚያስፈልገን እንደ አል አሩሲ አለም አቀፍ መዲና ላይ የግብጽን ርካሺ ትርክት መሳቂያ የሚያደርገልን ነዉ። ተስፋችን በዜጎች ነዉ አመራሩማ አንድ ጭልፋ አላስቀርባችሁም ብሎ ቃል ከመግባቱ ባሻገር አሁን ደግሞ ሐይለ ማርያምንም የቡድኑ አባል ሊያደርግ ሀሳብ አለዉ። ለማንኛዉም እናመስግናለን
  ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር

 3. ጥሩ አባባል ነው፡፡ ሰውን ማመን ቀብሮ ነው ብላ የለ፡፡
  ለማንኛውም በሚገባቸው ቀንቋ የሚከተለው መልዕክት ቢደርሳቸው፡፡

  Wake up Ethiopian negotiator!!! Around the clock Egypt is working or backing for its advantage only.
  Their misleading diplomatic efforts have failed and hence they have no way except discussion.
  Ethiopian side shall strengthen its diplomatic effort by propagating for fair utilization of the dam despite Egypt abused use of Nile basin for long time.

  Presently Egypt delaying tactics are behind the times and a head of time all Ethiopian people is awaken from past mistakes.

  Equity & fairness shall prevail!!!

  Long live to Ethiopia!!!

ሀሃሳብ እና አስተያትዎን ይስጡ

Your email address will not be published.